ወጣቶች—የማስተዋል ችሎታችሁን አዳብሩ!
“ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና [“የማስተዋል ችሎታ፣” NW] ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።”—ዕብራውያን 5:14
1, 2. (ሀ) ዛሬ እኛ ያለንበት ሁኔታ ጥንት በኤፌሶን ከነበሩት ክርስቲያኖች ሁኔታ ጋር የሚወዳደረው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹ ችሎታዎች ከአደጋ ሊጠብቋችሁ ይችላሉ? እነዚህንስ ችሎታዎች እንዴት ማዳበር ትችላላችሁ?
“እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” (ኤፌሶን 5:15, 16) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ከጻፈ ወደ ሁለት ሺህ ዓመት የሆነው ሲሆን ከዚያ ወዲህ ‘ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች በክፋታቸው እየባሱ ሄደዋል።’ ያለንበት ጊዜ ‘የሚያስጨንቅ’ ወይም አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደገለጸው ‘አደጋ የሞላበት’ ጊዜ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፣ ፊሊፕስ
2 ይሁን እንጂ ‘ብልሃትን፣ እውቀትንና የማሰብ ችሎታን’ በማዳበር በጎዳናችሁ ላይ ከሚገጥማችሁ ስውር አደጋ ልትጠበቁ ትችላላችሁ። (ምሳሌ 1:4) ምሳሌ 2:10-12 እንዲህ ይላል:- “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ [“የማሰብ ችሎታ፣” NW] ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፣ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች።” ይሁን እንጂ እነዚህን ችሎታዎች እንዴት ማዳበር ትችላላችሁ? ዕብራውያን 5:14 እንዲህ ይላል:- “ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና [“የማስተዋል ችሎታ፣” NW] ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” እንደ ማንኛውም ሙያ ሁሉ የማስተዋል ችሎታን በመጠቀም ረገድም የተዋጣልን ለመሆን ሥልጠና ማግኘት አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ ‘እንደ አንድ የጂምናስቲክ ስፖርተኛ መሠልጠን’ የሚል ነው። እንዲህ ያለውን ሥልጠና የምትጀምሩት እንዴት ነው?
የማስተዋል ችሎታችሁን ማዳበር
3. ውሳኔ እንድታደርጉ የሚጠይቅ አንድ ሁኔታ ሲገጥማችሁ የማስተዋል ችሎታችሁን መጠቀም የምትችሉት እንዴት ነው?
3 የማስተዋል ችሎታችሁ ማለትም መልካምና ክፉን የመለየት ችሎታችሁ የሚዳብረው ‘ስትጠቀሙበት’ እንደሆነ ልብ በሉ። ውሳኔ የሚጠይቅ አንድ ጉዳይ ሲገጥማችሁ እንዲሁ በግምት፣ በስሜት በመነሳሳት ወይም ብዙኃኑን በመከተል ብትወስኑ ምርጫችሁ ጥበብ ያለበት አይሆንም። ጥበብ ያለበት ውሳኔ ለማድረግ የማስተዋል ችሎታችሁን መጠቀም ይኖርባችኋል። እንዴት? ከሁሉ በፊት ሁኔታውን በጥንቃቄ በመመርመርና የነገሩን ትክክለኛ ገጽታ በመረዳት ነው። አስፈላጊ ከሆነም ጥያቄዎች ጠይቁ። ያሏችሁን አማራጮች አስቡ። ምሳሌ 13:16 “ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል” ይላል። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋት ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለመመርመር ሞክሩ። (ምሳሌ 3:5) እርግጥ ይህንን ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሊኖራችሁ ይገባል። ጳውሎስም “ጠንካራ ምግብ” መመገብን ማለትም የእውነትን ‘ስፋት፣ ከፍታና ጥልቀት’ መማርን ያበረታታው ለዚህ ነበር።—ኤፌሶን 3:18
4. ስለ አምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች እውቀት ማግኘት የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 የኃጢአት ዝንባሌ ያለን ፍጹም ያልሆንን ሰዎች በመሆናችን ይህንን ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 5:12) ኤርምያስ 17:9 እንደሚለው “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው።” በአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ካልተመራን ሥጋችን ለማግኘት ስለጓጓ ብቻ መጥፎ የሆነውን ነገር ትክክል እንደሆነ አድርገን በማሰብ ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። (ከኢሳይያስ 5:20 ጋር አወዳድር።) መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ።”—መዝሙር 119:9, 104
5. (ሀ) አንዳንድ ወጣቶች የተሳሳተ ጎዳና የሚከተሉት ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት ወጣት እውነትን የራሷ ያደረገችው እንዴት ነው?
5 በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ አንዳንድ ወጣቶች የተሳሳተ ጎዳና የተከተሉት ለምንድን ነው? እነዚህ ወጣቶች ‘የአምላክ ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኘው ምን እንደሆነ ለራሳቸው ፈትነው አላወቁ’ ይሆን? (ሮሜ 12:2) አንዳንዶች ከወላጆቻቸው ጋር በስብሰባዎች ላይ ስለሚገኙ መሠረታዊ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አይጠፏቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለ እምነታቸው እንዲያስረዱ ወይም በአምላክ ቃል ውስጥ ስላሉት አንዳንድ ጥልቅ ነገሮች እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ያላቸው እውቀት በጣም ውስን ይሆናል። እንዲህ ያሉት ወጣቶች በቀላሉ ሊታለሉ ይችላሉ። (ኤፌሶን 4:14) የእናንተም ሁኔታ ይህን የሚመስል ከሆነ ለውጥ ለማድረግ ለምን ቁርጥ ውሳኔ አታደርጉም? አንዲት ወጣት “ምርምር አደረግሁ። ‘ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት መሆኑን እንዴት አውቃለሁ? ይሖዋ የሚባል አምላክ መኖሩን እንዴት አውቃለሁ?’ እያልኩ ራሴን ጠየቅሁ” በማለት ታስታውሳለች።a ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ መመርመሯ በእርግጥም ወላጆቿ ያስተማሯት ነገሮች እውነት መሆናቸውን እንድታምን አድርጓታል!—ከሥራ 17:11 ጋር አወዳድር።
6. ‘ለጌታ ለይሖዋ ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደሆነ መርምራችሁ’ ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
6 ስለ ይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች በምታገኙት እውቀት ከታጠቃችሁ ‘ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን ነገር መርምራችሁ’ ለማወቅ ቀላል ይሆንላችኋል። (ኤፌሶን 5:8-10) ይሁንና በአንድ ጉዳይ ረገድ ምን ብታደርጉ ጥበብ እንደሚሆን እርግጠኛ ሳትሆኑ ብትቀሩስ? መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጸልዩ። (መዝሙር 119:144) ጉዳዩን አንስታችሁ ከወላጆቻችሁ ወይም ከአንድ ከጎለመሰ ክርስቲያን ጋር ለመወያየት ሞክሩ። (ምሳሌ 15:22፤ 27:17) በመጽሐፍ ቅዱስና በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ላይ ምርምር በማድረግም ጠቃሚ መመሪያ ማግኘት ይቻላል። (ምሳሌ 2:3-5) የማስተዋል ችሎታችሁን ይበልጥ በተጠቀማችሁበት መጠን ይበልጥ ስል እየሆነ ይሄዳል።
በመዝናኛ ረገድ ማስተዋል እንዳለን ማሳየት
7, 8. (ሀ) በአንድ ግብዣ ላይ ትገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የማስተዋል ችሎታችሁን መጠቀም የምትችሉት እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መዝናኛ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
7 አሁን ደግሞ በአንዳንድ የተወሰኑ ሁኔታዎች የማስተዋል ችሎታችሁን እንዴት ልትጠቀሙ እንደምትችሉ እንመልከት። ለምሳሌ ያህል በአንድ ግብዣ ላይ እንድትገኙ ተጋብዛችኋል እንበል። ምናልባትም ግብዣውን የሚያስተዋውቅ የጥሪ ወረቀት ደርሷችሁ ይሆናል። እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወጣት ምሥክሮች በግብዣው ላይ እንደሚገኙም ተነግሮአችኋል። ይሁን እንጂ ወጪውን ለመሸፈን ሲባል የገንዘብ ክፍያም ይጠየቃል። መገኘት ይኖርባችኋል?
8 የማስተዋል ችሎታችሁን ተጠቀሙ። በመጀመሪያ የጉዳዩን ትክክለኛ ገጽታ ለማወቅ ሞክሩ። በግብዣው ላይ ምን ያህል ሰዎች ይገኛሉ? እነማንስ ይገኛሉ? መቼ ይጀምራል? መቼ ያልቃል? ሊከናወኑ የታቀዱት ነገሮች ምንድን ናቸው? የዝግጅቱስ ቁጥጥር ምን ይመስላል? ከዚያ በኋላ ደግሞ በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ በመጠቀም “ግብዣዎች” [Social Gatherings] እና “መዝናኛ” [Entertainment] በሚሉት ርዕሶች ላይ አንዳንድ ምርምር አድርጉ።b የምርምራችሁ ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ለመዝናናት አንድ ላይ መሰባሰብን አያወግዝም። እንዲያውም መክብብ 8:15 ጠንክሮ ከመሥራት ጋር በማያያዝ “ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና” ይላል። ኢየሱስ ክርስቶስም ቢሆን ለየት ባሉ ግብዣዎችና ቢያንስ በአንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቶ ነበር። (ሉቃስ 5:27-29፤ ዮሐንስ 2:1-10) ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ሚዛናቸውን የጠበቁ ከሆኑ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
9, 10. (ሀ) አንዳንድ ግብዣዎች ምን አደጋ ሊኖራቸው ይችላል? (ለ) በአንድ ግብዣ ላይ ለመገኘት ወይም ላለመገኘት ከመወሰናችሁ በፊት ራሳችሁን ምን ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ?
9 የሆነ ሆኖ በሚገባ ያልተደራጀ ግብዣ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ጥበብ የጎደለው ማኅበራዊ ዝግጅት እንዴት ወደ ዝሙት እንዳመራና በዚህም መዘዝ ‘በአንድ ቀን ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ [ታማኝ ያልሆኑ እስራኤላውያን]’ በሞት እንደተቀጡ 1 ቆሮንቶስ 10:8 ላይ እናነባለን። ሌላው ልናጤነው የሚገባ ማስጠንቀቂያ ደግሞ በሮሜ 13:13 ላይ የሚገኘው ነው:- “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፣ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፣ በክርክርና በቅናት አይሁን።” (ከ1 ጴጥሮስ 4:3 ጋር አወዳድር።) በአንድ ግብዣ ላይ ምን ያህል ሰዎች መገኘት እንዳለባቸው መደንገግ እንደማይቻል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከተሞክሮ እንደታየው የተጋባዦቹ ቁጥር በጨመረ መጠን ለመቆጣጠርም የዚያኑ ያህል አስቸጋሪ ይሆናል። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገኙባቸውና ተገቢ ቁጥጥር የተደረገባቸው ግብዣዎች ግን ‘መረን የለቀቁ’ የመሆናቸው አጋጣሚ ጠባብ ነው።—ገላትያ 5:21 ባይንግተን
10 የምታደርጉት ምርምር እንደሚከተለው ያሉትን ጥያቄዎች ወደ አእምሮአችሁ እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም:- በግብዣው ላይ የጎለመሱ አዋቂ ክርስቲያኖች ይገኛሉ? ይህን ግብዣ ያዘጋጀው ማን ነው? የግብዣው ዓላማ ጤናማ የሆነ ወዳጅነትን ማስፈን ነው ወይስ ለአንድ ሰው ትርፍ ማስገኘት? ተጋባዦቹ እነማን እንደሚሆኑ ምርጫ ተደርጓል? ግብዣው የሚደረገው በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከሆነ ተጋባዦቹ በሚቀጥለው ቀን በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል ይችሉ ዘንድ ዝግጅቱ ብዙ ሳይመሽ ይጠናቀቃል? ሙዚቃና ዳንስ የሚኖር ከሆነ ከክርስቲያናዊ አቋማችን ጋር የሚስማማ ይሆናልን? (2 ቆሮንቶስ 6:3) እንዲህ ዓይነቶቹን ጥያቄዎች ማንሳት ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ምሳሌ 22:3 “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” በማለት ያስጠነቅቃል። አዎን፣ የማስተዋል ችሎታችሁን በመጠቀም ከአደገኛ ሁኔታዎች መራቅ ትችላላችሁ።
የትምህርት እቅድ ስታወጡ ማስተዋል መጠቀም
11. ወጣቶች ስለወደፊቱ ጊዜ ዕቅድ ሲያወጡ የማስተዋል ችሎታቸውን ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣት ጥበብ እንደሆነ ይገልጻል። (ምሳሌ 21:5 NW) ስለ ወደፊት ሁኔታችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር ተነጋግራችኋል? ምናልባትም አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመጀመር እቅድ ይኖራችሁ ይሆናል። ደግሞም ከዚህ የበለጠ እርካታ የሚያስገኝ ሌላ ሥራ አይኖርም። ጥሩ የጥናት ልማድ እያዳበራችሁና በአገልግሎት ችሎታችሁን እያሳደጋችሁ ከሆነ ለዚህ ድንቅ ሙያ በመዘጋጀት ላይ ናችሁ ማለት ነው። በዚህ አገልግሎት ስትሰማሩ ራሳችሁን እንዴት መደገፍ እንደምትችሉ አስባችሁበታል? ወደ ፊት ቤተሰብ ለመመሥረት ብታስቡ ይህንን ተጨማሪ ኃላፊነት መሸከም ትችላላችሁ? እነዚህን በመሳሰሉት ጉዳዮች ረገድ ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቀ ውሳኔ ማድረግ የማስተዋል ችሎታ መጠቀምን ይጠይቃል።
12. (ሀ) አንዳንድ ቤተሰቦች እየተቀያየረ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመቋቋም ሲሉ ምን ለማድረግ መርጠዋል? (ለ) ተጨማሪ ትምህርት መከታተል አቅኚ የመሆን ግብ ከመያዝ ጋር ፍጹም ተቃራኒ ነውን? አብራራ።
12 ዛሬም ቢሆን በአንዳንድ ቦታዎች በአንድ ጠቃሚ የእጅ ሙያ ወይም በሌላ መስክ የሥራ ልምድ ማግኘት ይቻላል። አንዳንድ ወጣቶች የወላጆቻቸውን ንግድ ማንቀሳቀስ ይማራሉ ወይም የንግድ ሥራ ካላቸው ትላልቅ ወዳጆቻቸው ሥልጠና ይወስዳሉ። ሌሎች ደግሞ በኋለኛው ሕይወታቸው ኑሮአቸውን ለመምራት የሚያስችላቸውን ኮርስ በትምህርት ቤት ሳሉ ይወስዳሉ። እንዲህ ያሉት አጋጣሚዎች በማይገኙበት ሁኔታ ደግሞ ወላጆች ጉዳዩን በጥንቃቄ ካመዛዘኑ በኋላ ልጆቻቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ተጨማሪ ትምህርት የሚያገኙበትን ዝግጅት ሊያደርጉላቸው ይችሉ ይሆናል። በጉልምስና እድሜ የሚመጡትን ኃላፊነቶች ለመሸከምና በተለይ ደግሞ በአቅኚነት አገልግሎት ለረጅም ጊዜ ለመካፈል ሲባል በዚህ መንገድ አስቀድሞ ግብ ማውጣት የአምላክን መንግሥት ከማስቀደም ጋር የሚቃረን ነገር አይደለም። (ማቴዎስ 6:33) ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ደግሞ አቅኚነትን የሚያስቀር ነገር አይሆንም። ለምሳሌ ያህል አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ለረጅም ጊዜ አቅኚ ሆና ማገልገል ፈልጋ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉት ወላጆችዋ ተጨማሪ ትምህርት እንድትከታተል ዝግጅት አደረጉላት። ትምህርቷን እየተከታተለችም አቅኚ ሆና ማገልገል ችላ የነበረ ሲሆን ዛሬም አቅኚ ሆና እያገለገለች ባገኘችው ሙያ ራሷን መደገፍ ችላለች።
13. ቤተሰቦች ተጨማሪ ትምህርት መከታተል የሚያስከትለውን ኪሳራ ማስላት የሚገባቸው እንዴት ነው?
13 ተጨማሪ ትምህርት መከታተልን በሚመለከት ውሳኔ የማድረጉ መብትና ኃላፊነት ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የተተወ ነው። ጥሩ ምርጫ ከተደረገ እንዲህ ያለው ትምህርት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ወጥመድም ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ትምህርት ለመማር እያሰባችሁ ከሆነ ዓላማችሁ ምንድን ነው? በጉልምስና ዕድሜያችሁ የምትሸከሟቸውን ኃላፊነቶች በሚገባ ለመወጣት ትችሉ ዘንድ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ነው? ወይስ ‘ለራሳችሁ ታላቅ ነገርን ለማከማቸት?’ (ኤርምያስ 45:5፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 6:9) ከቤት ርቆ ምናልባትም አዳሪ ተማሪ በመሆን ተጨማሪ ትምህርት ስለመከታተልስ ምን ለማለት ይቻላል? “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ከሚለው የጳውሎስ ማስጠንቀቂያ አንጻር እንደዚያ ማድረጉ ጥበብ ይሆናል? (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22) ከዚህም ሌላ ‘የቀረው ዘመን አጭር መሆኑን’ አትዘንጉ። (1 ቆሮንቶስ 7:29) እንዲህ ላለው ትምህርት የምታውሉት ጊዜ ምን ያህል ይሆናል? አብዛኛውን የወጣትነት ጉልበታችሁን የሚያሟጥጥ ነውን? እንደዚያ ከሆነ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማበረታቻ እንዴት በሥራ ላይ ልታውሉ ትችላላችሁ? (መክብብ 12:1) በተጨማሪም እነዚህን ኮርሶች ስትወስዱ እንደ ስብሰባ፣ የመስክ አገልግሎትና የግል ጥናት ላሉት በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ጊዜ ታገኛላችሁ? (ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25) የማስተዋል ችሎታችሁ ስል ከሆነ ከወላጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ ስለወደፊቱ ጊዜ እቅድ ስታወጡ መንፈሳዊውን ግብ አትዘነጉም።
በመጠናናት የምታሳልፉት ጊዜ ንጹሕ ይሁን
14. (ሀ) በመጠናናት ላይ ያሉ ተቃራኒ ጾታዎች አንዳቸው ለሌላው በሚያሳዩት የፍቅር መግለጫ ረገድ ሊመሩባቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) አንዳንድ ተቃራኒ ጾታዎች በዚህ ረገድ ጤናማ ውሳኔ ሳያደርጉ የቀሩት እንዴት ነው?
14 የማስተዋል ችሎታን መጠቀምን የሚጠይቅባችሁ ሌላው መስክ ደግሞ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መጠናናት ነው። ለምትወዱት ሰው የፍቅር መግለጫ ለማሳየት መፈለግ ያለ ነገር ነው። በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ላይ የተጠቀሱት ንጽሕናቸውን የጠበቁ ወንድና ሴት ከመጋባታቸው በፊት አንዳንድ የፍቅር መግለጫዎችን ተለዋውጠዋል። (መኃልየ መኃልይ 1:2፤ 2:6፤ 8:5) ዛሬም በመጠናናት ላይ ያሉ አንዳንድ ተቃራኒ ጾታዎች በተለይ ጋብቻቸው ሲቃረብ እጅ ለእጅ መያያዝ፣ መሳሳምና መተቃቀፍ የሚቻል ነገር እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ” እንደሆነ አስታውሱ። (ምሳሌ 28:26) የሚያሳዝነው በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ተቃራኒ ጾታዎች ራሳቸውን አጠያያቂ ሁኔታዎች ውስጥ በማስገባት ጤናማ ውሳኔ ሳያደርጉ ቀርተዋል። የፍቅር መግለጫዎች ገደብ ሳይበጅላቸው ቀርቶ ከልክ በማለፋቸው እርኩሰት አልፎ ተርፎም የጾታ ብልግና እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል።
15, 16. የሚጠናኑ ተቃራኒ ጾታዎች በመጠናናት የሚያሳልፉት ጊዜ ንጹሕ እንዲሆን ምን ምክንያታዊ ጥንቃቄዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ?
15 ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ የምትጫወቱ ከሆነ ከወደፊቷ/ቱ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር በአንዳንድ አጉል ሁኔታዎች ውስጥ ብቻችሁን ከመሆን መራቃችሁ ጥበብ ነው። በመሆኑም ከሌሎች ጋር በቡድን ሆናችሁ ወይም ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ሆናችሁ መጫወቱ የተሻለ ይሆናል። አንዳንድ ተቃራኒ ጾታዎች ሌላ ታዛቢ አብሯቸው እንዲኖር ያደርጋሉ። በተጨማሪም “ወይንና ጣፋጭ ወይን ቀናውን ዝንባሌ ያዛባሉ” የሚሉትን የሆሴዕ 4:11 [NW] ቃላት አስታውሱ። አልኮል አስተሳሰባቸውን በማዛባት ከጊዜ በኋላ የሚቆጩበትን ድርጊት ወደ መፈጸም ሊመራቸው ይችላል።
16 ምሳሌ 13:10 [NW] እንዲህ ይላል:- “ትዕቢት ትርፉ ችግር ነው፤ እርስ በርስ በሚመካከሩ ዘንድ ግን ጥበብ አለ።” አዎን፣ ‘እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ’ ማለትም ምን ዓይነት ጠባይ ማሳየት እንደሚኖርባችሁ ወስኑ። አንዳችሁ ለሌላው ስሜትና ሕሊና በመጠንቀቅ በፍቅር መግለጫዎች ላይ ገደብ አብጁ። (1 ቆሮንቶስ 13:5፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-7፤ 1 ጴጥሮስ 3:16) መጀመሪያ ላይ ይህን ጉዳይ አንስቶ መወያየቱ የሚያሳፍር ሊሆን ቢችልም የኋላ ኋላ ከባድ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሊጠብቃችሁ ይችላል።
‘ከታናሽነታችሁ ጀምሮ’ መማር
17. ዳዊት ‘ከታናሽነቱ ጀምሮ ይሖዋን መታመኛው’ ያደረገው እንዴት ነው? ይህስ ዛሬ ላሉት ወጣቶች ምን ትምህርት ይዟል?
17 ከሰይጣን ወጥመዶች ለመሸሽ በበኩላችን የማያቋርጥ ትጋት አንዳንድ ጊዜም ትልቅ ድፍረት ማሳየት ይፈለግብናል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከእኩዮቻችሁ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም ጋር እንዳልተጣጣማችሁ ሆኖ ይሰማችሁ ይሆናል። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አቤቱ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና። አምላኬ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ።” (መዝሙር 71:5, 17)c ዳዊት በድፍረቱ የሚታወቅ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ድፍረት ያዳበረው መቼ ነው? ገና ወጣት ሳለ ነበር! ዳዊት በሰፊው የሚታወቀውን ጎልያድን በመጋፈጥ ከፈጸመው ገድል በፊትም እንኳ የአባቱን መንጋ ይጠብቅ በነበረበት ጊዜ አንበሳና ድብ በመግደል የሚያስገርም ድፍረት አሳይቷል። (1 ሳሙኤል 17:34-37) ይሁን እንጂ ዳዊት “ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህ” በማለት ላሳየው ጀግንነት ሁሉ ያመሰገነው ይሖዋን ነበር። ዳዊት በይሖዋ ላይ መደገፍ መቻሉ የገጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ በብቃት ለመቋቋም አስችሎታል። እናንተም በይሖዋ ላይ ከተደገፋችሁ እርሱ ‘ዓለምን ለማሸነፍ’ የሚያስችል ድፍረትና ጥንካሬ ይሰጣችኋል።—1 ዮሐንስ 5:4
18. ዛሬ ላሉት አምላካዊ ወጣቶች ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቷል?
18 እንደ እናንተ ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች የድፍረት እርምጃ በመውሰድ የተጠመቁ የምሥራቹ አስፋፊዎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። እናንተ ወጣቶች ለምታሳዩት እምነትና ድፍረት አምላክን እናመሰግናለን! ከዚህ ብልሹ ዓለም እንዳመለጣችሁ በዚያው አቋማችሁ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። (2 ጴጥሮስ 1:4) በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ የማስተዋል ችሎታችሁን መጠቀማችሁን ቀጥሉ። እንደዚያ ማድረጋችሁ አሁን ከመከራ የሚጠብቃችሁ ሲሆን ወደፊት ደግሞ መዳናችሁን የተረጋገጠ ያደርግላችኋል። በእርግጥም የመጨረሻው ርዕሳችን እንደሚያሳየው ሕይወታችሁን የተሳካ ማድረግ ትችላላችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በታኅሣሥ 1998 ንቁ! መጽሔት ላይ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . እውነትን የራሴ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b “ማኅበራዊ መዝናኛ—ጥቅሞቹን አግኙ፤ ወጥመዶቹን ግን ሽሹ” የሚለው የነሐሴ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ርዕስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እጅግ ጠቃሚ ሐሳብ ይዞ ወጥቷል።
ለክለሳ የቀረቡ ጥያቄዎች
◻ አንድ ወጣት የማስተዋል ችሎታውን ማሰልጠን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ አንድ ወጣት ክርስቲያኖች ባዘጋጁት ግብዣ ላይ መገኘትን በሚመለከት የማስተዋል ችሎታውን ሊጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ለትምህርት እቅድ ስናወጣ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል?
◻ በመጠናናት ላይ ያሉ ተቃራኒ ጾታዎች የጾታ ብልግናን ወጥመድ መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምርምር ማድረግን መማር የማስተዋል ችሎታችሁን ለማሰልጠን ይረዳችኋል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተጋባዦች ቁጥር ማነስ ለቁጥጥር ያመቻል፤ ቅጥ ወዳጣ ፈንጠዝያ እንዳያመራ ያደርጋል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች የትምህርት ዕቅድ በማውጣት በኩል ልጆቻቸውን ሊረዷቸው ይገባል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቡድን ሆኖ አብሮ መጫወቱ ጥበቃ ነው