የአንባብያን ጥያቄዎች
በጥንት ዘመን የነበረው መልከ ጼዴቅ በእርግጥ ሰው የነበረ ሆኖ እያለ መጽሐፍ ቅዱስ “ የትውልድም ቁጥር የሉትም” ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው?
ይህ ቃል የሚገኘው በዕብራውያን 7:3 ላይ ነው። ጥቅሱን በዙሪያው ካሉት ሐሳቦች አንጻር ልብ ብለህ ተመልከተው:-
“የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አሥራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፣ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ቁጥር የሉትም፣ ለዘመኑም ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” — ዕብራውያን 7:1–3
ከላይ እንደተገለጸው አብርሃም በእርግጥ ሰው እንደነበረ ሁሉ ከእርሱ ጋር የተገናኘውም መልከ ጼዴቅ እንዲሁ ሰው ነበረ። (ዘፍጥረት 14:17–20፤ ዕብራውያን 7:4–10) ነገሩ እንዲህ ስለሆነ መልከ ጼዴቅ ወላጆች ማለትም አባትና እናት ያሉት እንዲሁም ልጆች ኖረውት ሊሆን የሚችል ሰው ነው። ስለዚህ እንደ አንድ ሰብአዊ ፍጡር የትውልድ ቁጥር ወይም የቤተሰብ መስመር ይኖረዋል። የኖረበት ዘመንም በሞት ያበቃበት ጊዜ ይኖራል። በሮሜ 5:12, 14 ላይ ከተገለጸው የጳውሎስ አነጋገር ጋር በመስማማት አንድ ወቅት ላይ መልከ ጼዴቅ ሞቷል። ነገር ግን መልከ ጼዴቅ መቼ እንደሞተና የክህነት አገልግሎቱ መቼ እንደተቋረጠ ስለማናውቅ በዚህ መንገድ ፍጻሜው ለማይታወቅ ጊዜ አገልግሏል።
በዕብራውያን ላይ ጳውሎስ ብልጫ ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስን የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ባብራራበት ወቅት ስለ መልከ ጼዴቅ አውስቷል። በዚህ የክህነት አገልግሎት የኢየሱስ ሚና ምን እንደሚመስል ለማስረዳት ጳውሎስ መልከ ጼዴቅን እንደ ዓይነት ወይም እንደ ምሳሌ በመጥቀስ “ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት . . . ሊቀ ካህናት ሆነ” በማለት ተናገረ። (ዕብራውያን 6:20) በምን መልክ ነው የተመሳሰሉት?
ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መልከ ጼዴቅ የቤተሰብ ሐረግ ማለትም ስለ ወላጆቹም ሆነ ሊኖሩት ስለሚችሉ ዝርያዎቹ በዝርዝር የመዘገበው ነገር እንደሌለ ተገንዝቦ መሆን ይኖርበታል። ባጭሩ ይህ ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተመዘገበም። እንግዲያው ጳውሎስም ሆነ እኛ ከምናውቀው አንጻር ሲታይ መልከ ጼዴቅ “የትውልድ ቁጥር” (የአዲሰቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም፤ አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን ) “የዝርያዎች ዝርዝር” (ደብሊው ጄ ኮኒቤር) ወይም “የቤተሰብ ሐረግ የለውም” (ጄ ፊሊፕስ) ቢባል ትክክል ነው።
ኢየሱስ ይህንን የሚመስለው በምን መንገድ ነው? የኢየሱስ አባት ይሖዋ አምላክ እንደሆነና ሰብአዊ እናቱ ደግሞ ከይሁዳ ነገድ የሆነችው ማርያም መሆኗን እናውቃለን። እንዲህም ሆኖ በኢየሱስና በመልከ ጼዴቅ መካከል ተመሰሳይነት እናገኛለን። እንዴት? ኢየሱስ በእስራኤል ውስጥ የካህናት ነገድ ከሆነው ከሌዊ ነገድ አልተወለደም። ኢየሱስ በሰብአዊ የትውልድ ሐረግ መሠረት ካህን አልሆነም። መልከ ጼዴቅም እንዲሁ “በሥጋ ትእዛዝ ሕግ” ማለትም ካህን ከሆነ ነገድ ወይም ቤተሰብ በመወለድ ካህን አልሆነም። (ዕብራውያን 7:15, 16) ራሱ ካህን ከሆነ ከአንድ ሰብአዊ አባት በመወለድ ካህን ከመሆን ይልቅ ኢየሱስ “በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ” ተጠራ። — ዕብራውያን 5:10
ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ለክህነት አገልግሎቱ ዝርያዎች ወይም ወራሾች የሉትም። በዚህም በኩል የትውልድ ቁጥር የለውም። ጥሩ እርዳታ ሰጪ አስተማሪ በመሆን የክህነት አገልግሎቱን ለዘላለም ማከናወኑን ይቀጥላል። በዚህ ዘላለማዊ አገልግሎት ላይ ሐሳብ ሲሰጥ ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሏል:-
“[ኢየሱስ] ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” — ዕብራውያን 7:24, 25
እንግዲያው ጳውሎስ በዕብራውያን 7:3 ላይ የተናገራቸውን ቃላት መመርመራችን ጠለቅ ያለ እውቀት የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ እውቀት ይሖዋ አምላክ ለዘላለም የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት የምንችልበትንና ዘላለማዊ እርዳታና መምሪያ መቀበል የምንችልበትን መንገድ ላመቻቸበት ፍቅራዊ ዝግጅቱ ያለንን አድናቆት ያጠናክርልናል።