በመከራ መጽናት ጥቅም ያስገኝልናል
‘በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ [“ደስተኞች፣” NW] አድርገን እንቈጥራቸዋለን።’—ያዕቆብ 5:11
1, 2. ይሖዋ ሰዎች መከራ እንዲደርስባቸው ዓላማው እንዳልነበረ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
ጤናማ አእምሮ ያለው ማንኛውም ሰው መከራ እንዲደርስበት አይፈልግም። ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክም የሰው ልጆች እንዲሠቃዩ አይፈልግም። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን ስንመረምርና የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረ በኋላ የተከናወነውን ነገር ስንመለከት አምላክ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዳለው መገንዘባችን አይቀርም። በመጀመሪያ አምላክ ሰውን ማለትም አዳምን ፈጠረ። “[ይሖዋ] አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7) አዳም በአካልም ሆነ በአእምሮ ፍጹም በመሆኑ ሕመምና ሞት አያሰጋውም ነበር።
2 አዳም ይኖርበት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? “እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ።” (ዘፍጥረት 2:8, 9) አዎን፣ አዳም ዕጹብ ድንቅ መኖሪያ ነበረው። በኤደን መከራና ሥቃይ አልነበረም።
3. የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን ተስፋ ተዘርግቶላቸው ነበር?
3 ዘፍጥረት 2:18 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክ፣ ‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ’ አለ።” ከዚያም ይሖዋ ለአዳም ፍጹም የሆነች ሚስት ፈጠረለት። በዚህ መንገድ ደስተኛ ቤተሰብ ለመመሥረት የሚያስችል ሁኔታ አመቻቸ። (ዘፍጥረት 2:21-23) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “እግዚአብሔርም፣ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው’ ብሎ ባረካቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መላዋ ምድር ገነት እስክትሆን ድረስ ኤደን ገነትን የማስፋፋት ውድ መብት አግኝተው ነበር። በተጨማሪም ከመከራና ሥቃይ ነፃ የሆኑ ደስተኛ ልጆችን ማፍራት ይችሉ ነበር። እንዴት ያለ ግሩም ጅምር ነበር!—ዘፍጥረት 1:31
መከራና ሥቃይ ጀመረ
4. ታሪክ የሰው ልጆች ስላሉበት ሁኔታ ምን ይናገራል?
4 ይሁንና የሰው ልጆችን ታሪክ ስንመረምር ሁኔታዎች ክፉኛ እንዲበላሹ ያደረገ አንድ ችግር መፈጠሩን እናስተውላለን። በምድር ላይ መጥፎ ነገሮች ሲከሰቱና የሰው ልጆች ለከፍተኛ ሥቃይና መከራ ሲዳረጉ ይታያል። ሁሉም የአዳምና የሔዋን ዘሮች መታመማቸው፣ ማርጀታቸውና በመጨረሻም መሞታቸው ለዘመናት የኖረ ሐቅ ነው። ምድር ደስተኛ በሆኑ ሰዎች የተሞላች ገነት አለመሆኗ ግልጽ ነው። ሮሜ 8:22 እንደሚከተለው ሲል ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ይገልጸዋል:- “እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን።”
5. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በሰው ልጅ ላይ መከራ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው?
5 ለዘመናት በሰው ልጆች ላይ ለደረሰው መከራና ሥቃይ ተወቃሹ ይሖዋ አይደለም። (2 ሳሙኤል 22:31) የሰው ልጆች በተወሰነ መጠን ተጠያቂዎች ናቸው። “ብልሹዎች ናቸው፤ ተግባራቸውም ጸያፍ ነው፤ በጎ ነገር የሚሠራ አንድም የለም።” (መዝሙር 14:1) መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን መልካም የሆነው ነገር ሁሉ ተሰጥቷቸው ነበር። ይህ መልካም ነገር እንዲቀጥል ለአምላክ እንዲታዘዙ ይጠበቅባቸው ነበር። ሆኖም የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ በራሳቸው ለመመራት መረጡ። የይሖዋን የበላይ ገዢነት ለመቀበል አሻፈረን ስላሉ ፍጹም ሆነው መኖር አልቻሉም። በመሆኑም ሞት እስኪወስዳቸው ድረስ ሁኔታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ሄደ። እኛም አለፍጽምናን ወረስን።—ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮሜ 5:12
6. ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ያደረገው እንዴት ነው?
6 ከዚህ በተጨማሪ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራው መንፈሳዊ ፍጡር በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቶታል። ይሁንና ለመመለክ ካለው ፍላጎት የተነሳ ይህን ነፃነቱን አላግባብ ተጠቀመበት። ሆኖም አምልኮ ሊሰጥ የሚገባው ለይሖዋ እንጂ ለፍጥረታቱ አይደለም። አዳምና ሔዋን ‘እንደ አምላክ መልካምንና ክፉን ማወቅ’ የሚችሉ ይመስል ይሖዋን ለመታዘዝ አሻፈረን በማለት በራሳቸው ለመመራት እንዲመርጡ ያሳታቸው ሰይጣን ነው።—ዘፍጥረት 3:5
የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው
7. በይሖዋ ላይ የተነሳው ዓመጽ ያስከተለው ውጤት ምን ያሳያል?
7 ዓመጽ ያስከተለው መጥፎ ውጤት፣ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን የመግዛት መብት ያለውና የጽድቅ አገዛዝ ማስፈን የሚችለው እሱ ብቻ መሆኑን አሳይቷል። ያለፉት በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናት፣ ‘የዚህ ዓለም ገዥ’ የሆነው ሰይጣን ያቋቋመው ብቃት የጎደለው አገዛዝ፣ ክፉ ብሎም በዓመጽና በጭካኔ የተሞላ መሆኑን አሳይተዋል። (ዮሐንስ 12:31) በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውና ለዘመናት የዘለቀው በሰቆቃ የተሞላ ሰብዓዊ አገዛዝም ሰዎች በጽድቅ የመግዛት ችሎታ እንደሌላቸው አስመሥክሯል። (ኤርምያስ 10:23) በመሆኑም ከይሖዋ አገዛዝ ውጪ የሆነ ማንኛውም ዓይነት የሰዎች መስተዳድር ውድቀት ማስከተሉ አይቀርም። ታሪክ ይህ እውነት መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል።
8. ሁሉንም ሰብዓዊ አገዛዝ በተመለከተ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው? ይህን ዓላማውን ከግብ የሚያደርሰውስ እንዴት ነው?
8 ይሖዋ የሰው ልጆች ከእሱ ተለይተው የራሳቸውን አገዛዝ እንዲሞክሩ ከፈቀደ በርካታ ሺህ ዓመታት አልፈዋል። በመሆኑም በቅርቡ ሁሉንም ዓይነት አገዛዝ ከምድር ላይ አስወግዶ በምትኩ የራሱን መንግሥት የሚያቋቁምበት አጥጋቢ ምክንያት አለው። አንድ ትንቢት ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በነዚያ ነገሥታት [ሰብዓዊ አገዛዝ] ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት [በክርስቶስ የሚመራ ሰማያዊ መስተዳድር] ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) አጋንንታዊና ሰብዓዊ አገዛዝ የሚያከትም ሲሆን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ብቻውን ምድርን ያስተዳድራል። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ክርስቶስ ሲሆን ከምድር የተወሰዱ 144,000 ታማኝ ሰዎች አብረውት ይገዛሉ።—ራእይ 14:1
በመከራ ማለፍ የሚያስገኘው ጥቅም
9, 10. ኢየሱስ ከደረሰበት መከራ ምን ጥቅም አግኝቷል?
9 በሰማያዊው መንግሥት የሚገዙት ነገሥታት ያላቸውን ብቃት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ለመሾም ብቃት እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ሲኖር “ዋና ባለሙያ [“ሠራተኛ፣” የ1954 ትርጉም]” በመሆን የአባቱን ፈቃድ ይፈጽም ነበር። (ምሳሌ 8:22-31) በኋላም ይሖዋ ወደ ምድር እንዲመጣ ሲልከው በፈቃደኝነት ታዟል። በምድር ሳለም ዋና ትኩረቱ ያረፈው ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነትና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች በመናገር ላይ ነበር። ኢየሱስ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ በመገዛት ረገድ ለሁላችንም የሚሆን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—ማቴዎስ 4:17፤ 6:9
10 ኢየሱስ ስደት የደረሰበት ሲሆን በመጨረሻም ተገድሏል። አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመገንዘብ ችሏል። ኢየሱስ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ መመልከቱም ሆነ መከራን መቅመሱ ያስገኘለት ጥቅም አለ? አዎን አለ። ዕብራውያን 5:8 “[የአምላክ] ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ” ይላል። ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት የሰው ልጆችን ስሜት ይበልጥ እንዲረዳና ርኅሩኅ እንዲሆን አስችሎታል። በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ በእሱም ላይ ደርሷል። ይህ ደግሞ በመከራ ውስጥ ላሉት አዘኔታ እንዲያሳይና እነሱን ለማዳን የሚጫወተው ሚና ያለውን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ረድቶታል። በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለሕዝቡ የኀጢአትን ስርየት ለማስገኘት ነው። እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።” “በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”—ዕብራውያን 2:17, 18፤ 4:14-16፤ ማቴዎስ 9:36፤ 11:28-30
11. ነገሥታትና ካህናት ለመሆን የተመረጡት ሰዎች በምድር ሳሉ ያካበቱት ተሞክሮ በሰማይ ሆነው በሚገዙበት ጊዜ የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
11 በሰማያዊው መንግሥት ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ለመግዛት ከምድር ‘የተዋጁት’ 144,000 ሰዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። (ራእይ 14:4) ሰው ሆነው ሥቃይና መከራ በሞላበት ምድር ላይ የኖሩ ሲሆን እነሱ ራሳቸውም መከራ ደርሶባቸዋል። ብዙዎቹ ስደት ደርሶባቸዋል፤ አንዳንዶቹም ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ጠብቀው በመኖራቸውና ኢየሱስን ለመከተል በመፈለጋቸው ተገድለዋል። ሆኖም ‘ስለ ጌታቸው ለመመስከርና ስለ ወንጌል መከራን ለመቀበል አላፈሩም።’ (2 ጢሞቴዎስ 1:8) በተለይ በምድር ላይ ያሳለፉት ሕይወት በሰማይ ሆነው በሰው ልጆች ላይ ለመፍረድ ብቁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አዛኝና ደግ እንዲሁም ሰዎችን ለመርዳት ይበልጥ ጉጉት ያላቸው መሆንን ተምረዋል።—ራእይ 5:10፤14:2-5፤ 20:6
በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች የሚያገኙት ደስታ
12, 13. በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች በመከራ ማለፋቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
12 ከበሽታ፣ ከሐዘንና ከሞት ነፃ በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎችስ ከሚደርስባቸው መከራ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ? በመከራ ማለፍ የሚያስከትለው ሐዘንና ሥቃይ እንዲደርስበት የሚፈልግ ሰው የለም። ይሁንና በመከራ ስንጸና ግሩም የሆኑ ባሕርያትን የምናዳብር ከመሆኑም በላይ ደስታ እናገኛለን።
13 በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ይህን በተመለከተ ምን እንደሚል ተመልከት:- “ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናችሁ።” “ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ . . . ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናችሁ።” (1 ጴጥሮስ 3:14፤ 4:14) “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ።” (ማቴዎስ 5:11, 12) “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም . . . የሕይወትን አክሊል ያገኛል።”—ያዕቆብ 1:12
14. መከራ ለይሖዋ አምላኪዎች ደስታ የሚያመጣላቸው ከምን አንጻር ነው?
14 ደስታ የሚሰጠን በመከራ ማለፋችን የሚያስከትልብን ሥቃይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ደስታ ወይም እርካታ የምናገኘው መከራ የደረሰብን የይሖዋን ፈቃድ በማድረጋችንና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተላችን መሆኑን ስለምናውቅ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስበካቸው ምክንያት ታስረው ብሎም በአይሁድ የፍርድ ሸንጎ ተወግዘው ነበር። እነዚህ ሐዋርያት ከተገረፉ በኋላ ተለቀቁ። ታዲያ ምን ተሰማቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ “ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው” እንደሄዱ ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 5:17-41) ሐዋርያት የተደሰቱት ስለተገረፉና አካላዊ ሥቃይ ስለደረሰባቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰባቸው ለይሖዋ ታማኝ በመሆናቸውና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተላቸው እንደሆነ ስለተገነዘቡ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 16:25፤ 2 ቆሮንቶስ 12:10፤ 1 ጴጥሮስ 4:13
15. በአሁኑ ጊዜ በመከራ መጽናታችን ለወደፊቱ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
15 ተገቢ አመለካከት በመያዝ የሚደርስብንን ተቃውሞና ስደት በትዕግሥት ካሳለፍን የጽናት ባሕርይ እናዳብራለን። ይህ ደግሞ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።” (ያዕቆብ 1:2, 3) በተመሳሳይም ሮሜ 5:3-5 እንደሚከተለው ይላል:- “በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም።” በአሁኑ ወቅት በክርስቲያናዊ አኗኗራችን ምክንያት የሚደርሱብንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ስንኖር ወደፊት የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖረናል።
ይሖዋ ወሮታ ይከፍላል
16. ይሖዋ ወደፊት ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት ሰዎች ለደረሰባቸው መከራ ወሮታውን የሚከፍላቸው እንዴት ነው?
16 የክርስትናን ጎዳና በመከተላችን ምክንያት ተቃውሞ አሊያም ስደት ሊደርስብንና ቁሳዊ ንብረታችንን ልናጣ እንችላለን። ያም ሆኖ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደሚክሰን በማሰብ ደስታችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሰማይ የመኖር ተስፋ ላላቸው ሰዎች ሲጽፍ “እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት [በአምላክ መንግሥት የመግዛት መብት] ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ . . . ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ” ብሏል። (ዕብራውያን 10:34) እውነት ነው፣ እነዚህ ሰዎች በይሖዋና በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለምድር ነዋሪዎች አስደናቂ በረከቶችን በማፍሰስ ሲካፈሉ የሚያገኙት ደስታ እጅግ ከፍተኛ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለታማኝ ክርስቲያኖች “የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ” ሲል የተናገረው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው!—ሮሜ 8:18
17. ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ በታማኝነት ለሚያገለግሉት በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች ምን ያደርግላቸዋል?
17 በተመሳሳይም በምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች፣ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማምለካቸው ምክንያት ምንም ነገር ቢያጡ ወይም በፈቃደኝነት መሥዋዕት ቢያደርጉ አምላክ ወደፊት አትረፍርፎ ይክሳቸዋል። ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹምና ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል። በአዲሱ ዓለም ይሖዋ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! በዚህ ሥርዓት ፈቅደንም ይሁን ሳንፈቅድ ለይሖዋ ስንል መሥዋዕት የምናደርገው ማንኛውም ነገር፣ አምላክ መከራን በጽናት ለተወጡ ታማኝ አገልጋዮቹ ከሚሰጣቸው አስደናቂ ሕይወት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
18. ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ምን የሚያጽናና ተስፋ ሰጥቶናል?
18 በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን ማንኛውም መከራ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ስንኖር የምናገኘውን ደስታ አይቀንስብንም። በአዲሱ ዓለም የሚኖሩት አስደናቂ ሁኔታዎች በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብንን መከራ ሙሉ ለሙሉ ያካክሱልናል። ኢሳይያስ 65:17, 18 እንዲህ ይላል:- “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም። ነገር ግን በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።” የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ ‘በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ [“ደስተኞች፣” NW] አድርገን እንቆጥራቸዋለን’ ሲል መናገሩ ተገቢ ነው። (ያዕቆብ 5:11) አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብንን መከራ በጽናት የምንወጣ ከሆነ አሁንም ሆነ ወደፊት ጥቅም እናገኛለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በሰው ልጆች ላይ መከራና ሥቃይ የመጣው እንዴት ነው?
• የወደፊቶቹ የምድር ገዥዎችና ነዋሪዎቿ በመከራ ማለፋቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
• በአሁኑ ጊዜ መከራ የሚደርስብን ቢሆንም የምንደሰተው ለምንድን ነው?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳምና ሔዋን አስደናቂ የሆነ የወደፊት ሕይወት ተዘርግቶላቸው ነበር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የሌሎችን ሥቃይና መከራ ማየቱ ጥሩ ንጉሥና ሊቀ ካህን እንዲሆን ረድቶታል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያት በእምነታቸው ምክንያት ‘ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ተደስተዋል’