የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ዕብራውያን 11:1—“እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት” ነው
“እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው፤ በተጨማሪም የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።”—ዕብራውያን 11:1 አዲስ ዓለም ትርጉም
“እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው።”—ዕብራውያን 11:1 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የዕብራውያን 11:1 ትርጉም
ይህ ጥቅስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለእምነት እጥር ምጥን ያለ ፍቺ የተሰጠበት ቦታ ነው፤ እንዲሁም ጥቅሱ እንደሚያሳየው፣ እምነት አንድን ነገር አምኖ ከመቀበል የበለጠ ነገርን ያመለክታል።
“እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ፣ ዕብራውያን 11:1 ላይ “እምነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል መተማመንን ወይም እርግጠኛ መሆንን ያመለክታል። እንዲህ ያለው እምነት፣ እንዲሁ አንድ ነገር ቢሆን ብሎ ከመመኘት ያለፈ ነገር ነው፤ ከዚህ ይልቅ ‘በእርግጠኝነት እንደሚፈጸም መጠበቅን’ ያመለክታል። “በእርግጠኝነት መጠበቅ”a ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ አገላለጽ “የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል፤ ይህ ማረጋገጫ ያለው ሰው፣ ንብረቱ እጁ ባይገባም እንኳ የንብረቱ ባለቤት እንደሆነ ዋስትና አለው።
“እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” እምነት በአሳማኝ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው። እንዲህ ያለው ማስረጃ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ግለሰቡ የሚያምንበትን ነገር ባያየውም እንኳ በእውን እንዳለ ይተማመናል።
የዕብራውያን 11:1 አውድ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዕብራውያን መጽሐፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈው ደብዳቤ ነው፤ ደብዳቤውን የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ለነበሩ ክርስቲያኖች ነው። ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ላይ የእምነትን አስፈላጊነት አብራርቷል። ለምሳሌ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና።” (ዕብራውያን 11:6) ጳውሎስ በዕብራውያን 11:1 ላይ የእምነትን ፍቺ ከገለጸ በኋላ የእምነት ሰዎች የሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ወንዶችና ሴቶችን ዘርዝሯል። እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነገር በማድረግ እምነታቸውን ያስመሠከሩት እንዴት እንደሆነ ጽፏል።—ዕብራውያን 11:4-38
a “በእርግጠኝነት መጠበቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሃይፖስታሲስ ነው፤ የዚህ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “አንድ ነገር የሚቆምበት ወይም መሠረት” የሚል ነው።