እምነት ከማጣት ተጠበቁ
“ወንድሞች ሆይ፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ እንዳታፈሩ ተጠንቀቁ።”—ዕብራውያን 3:12 NW
1. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፋቸው ቃላት የትኛውን አስደንጋጭ እውነታ እንድናስብበት ያደርጉናል?
በአንድ ወቅት ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና የነበራቸው ሰዎች ‘ክፉ ልብ’ ሊያፈሩና ‘ሕያው ከሆነው አምላክ ሊርቁ’ እንደሚችሉ ማሰቡ ምንኛ የሚያስፈራ ነው! እንዴትስ ያለ ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው! እነዚህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት የተነገሩት ለማያምኑ ሰዎች ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለወሰኑ ሰዎች ነበር።
2. የትኞቹን ጥያቄዎች መመርመር አለብን?
2 ይህን በመሰለ የተባረከ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ የነበረ ሰው እንዴት “እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ” ሊያፈራ ይችላል? የአምላክን ፍቅርና ይገባኛል የማይለውን ደግነቱን የቀመሰ ሰው እንዴት ሆን ብሎ ከአምላክ ይርቃል? ይህ ሁኔታ በማንኛችንም ላይ ሊደርስ ይችል ይሆን? እነዚህ ጉዳዮች ሊጤኑ የሚገባቸው ሲሆኑ ማስጠንቀቂያው የተሰጠበትን ምክንያት መመርመራችንም በጣም አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:11
እንዲህ ያለ ጠንካራ ምክር መስጠት ለምን አስፈለገ?
3. በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ በነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ላይ ተጽእኖ ያሳደሩትን ሁኔታዎች ጥቀስ።
3 ጳውሎስ በይሁዳ ለሚገኙት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በ61 እዘአ ገደማ ሳይሆን አይቀርም። አንድ ታሪክ ጸሐፊ በዚህ ጊዜ “በኢየሩሳሌም ከተማም ሆነ በግዛቲቱ በሙሉ የነበሩ ጭምትና ሐቀኛ ሰዎች ሁሉ ሰላም ወይም ደኅንነት አልነበራቸውም” ሲሉ ተናግረዋል። ጨቋኙ የሮማ ሠራዊት በዚያ መገኘት፣ የቀናኢ አይሁዶች ፀረ ሮማዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተገን በማድረግ ሌቦች የሚፈጽሙት ወንጀል አንድ ላይ ተዳምሮ ሕገ ወጥነትና ዓመፅ እንዲስፋፋ አድርጎ ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ላለመጠላለፍ ይጥሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ከባድ ችግር ፈጥረውባቸው ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2) እንዲያውም አንዳንዶች በገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት ለኅብረተሰቡ ጠንቆች እንደሆኑና ሕዝቡን ለዓመፅ እንደሚያነሳሱ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ በደል ይፈጸምባቸው ነበር፤ እንዲሁም በንብረታቸው ላይ ጉዳት ይደርስባቸው ነበር።—ዕብራውያን 10:32-34
4. ዕብራውያን ክርስቲያኖች በምን ዓይነት ሃይማኖታዊ ተጽእኖ ሥር ይገኙ ነበር?
4 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከባድ የሆነ ሃይማኖታዊ ተጽእኖ ይደርስባቸው ነበር። የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት የነበራቸው ቅንዓትና በዚህም የተነሳ የክርስቲያን ጉባኤ ያሳየው ፈጣን እድገት የአይሁዳውያንን በተለይም ደግሞ የሃይማኖታዊ መሪዎቻቸውን ቅናትና ቁጣ አነሳስቷል። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮችን ችግር ውስጥ ለመክተትና ለማሠቃየት ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም ነበር።a (ሥራ 6:8-14፤ 21:27-30፤ 23:12, 13፤ 24:1-9) አንዳንድ ክርስቲያኖች ቀጥተኛ የሆነ ስደት ባይደርስባቸው እንኳ ያንቋሽሿቸውና ያሾፉባቸው ነበር። ክርስትና ቤተ መቅደስ የሌለው፣ የክህነት አገልግሎት የሚባል ነገር የማይታወቅበት፣ በዓላት የሌሉት፣ መደበኛ መሥዋዕቶች የማይቀርቡበትና ሌሎች ነገሮችም የሚጎድሉት በአጠቃላይ የአይሁድ እምነት ያለውን ለዛ ያጣ ዘመን አመጣሽ ሃይማኖት ተደርጎ ይታይ ነበር። ሌላው ቀርቶ መሪያቸው ኢየሱስ ወንጀለኛ ነህ ተብሎ ተገድሏል። ክርስቲያኖች አምልኳቸውን ለማከናወን እንዲችሉ እምነት፣ ድፍረትና ጽናት ሊኖራቸው ይገባ ነበር።
5. በይሁዳ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው መቀጠላቸው አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
5 ከሁሉም በላይ ደግሞ በይሁዳ የነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ይኖሩበት የነበረው ዘመን በዚህ ብሔር ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ወቅት ነበር። ጌታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ሥርዓት ፍጻሜን አስመልክቶ የተናገራቸው በርካታ ነገሮች ፍጻሜያቸውን አግኝተው ነበር። መጨረሻው ሩቅ አልነበረም። ክርስቲያኖች በሕይወት ለመትረፍ ከፈለጉ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው መቀጠልና ‘ወደ ተራራዎች ለመሸሽ’ ዝግጁ ሆነው መጠባበቅ ነበረባቸው። (ማቴዎስ 24:6, 15, 16) በኢየሱስ መመሪያ መሠረት አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስፈልጋቸው እምነትና መንፈሳዊ ብርታት ይኖራቸው ይሆን? ይህ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር።
6. በይሁዳ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአፋጣኝ የሚያስፈልጋቸው ነገር ምን ነበር?
6 የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ከመጥፋቱ በፊት በነበሩት የመጨረሻዎቹ አሥርተ ዓመታት ላይ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጉባኤው ውስጥም ሆነ ከጉባኤው ውጪ ከባድ ተጽእኖ እየደረሰባቸው እንደነበረ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ማበረታቻ ያስፈልጋቸው ነበር። በተጨማሪም የመረጡት የአኗኗር መንገድ ትክክል መሆኑንና ሥቃይና መከራ የተቀበሉት ለከንቱ ነገር አለመሆኑን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ምክርና መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ደስ የሚለው ነገር ጳውሎስ ራሱን በማቅረብ የእርዳታ እጁን ዘረጋላቸው።
7. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈው ነገር ትኩረታችንን ሊስበው የሚገባው ለምንድን ነው?
7 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈውን ነገር ትኩረት ሰጥተን ልንከታተለው ይገባል። ለምን? ምክንያቱም የምንኖረው ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው። በየቀኑ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ከሚገኘው ዓለም ተጽእኖ ይደርስብናል። (1 ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስና ሐዋርያት ስለ መጨረሻዎቹ ቀናትና ስለዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ [NW]” የተናገሯቸው ትንቢቶች በጊዜያችን በመፈጸም ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ራእይ 6:1-8) ከሁሉም በላይ ደግሞ “ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ” እንድንችል በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መቀጠል አለብን።—ሉቃስ 21:36
ከሙሴ የሚበልጥ
8. ጳውሎስ በዕብራውያን 3:1 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሲናገር መሰል ክርስቲያኖች ምን እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ነበር?
8 ጳውሎስ አንድ አስፈላጊ የሆነ ነጥብ በመጥቀስ “የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 3:1) ‘መመልከት’ (በእንግሊዝኛ ኮንሲደር) የሚለው ቃል “በግልጽ መገንዘብ . . .፣ ሙሉ በሙሉ መረዳትና በቅርብ መመልከት” የሚል ትርጉም አለው። (ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ) በመሆኑም ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹ ኢየሱስ በእምነታቸውና በመዳናቸው ረገድ ለተጫወተው ሚና እውነተኛ አድናቆት ለማሳየት ትጋት የታከለበት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል። ይህን ማድረጋቸው በእምነት ጸንተው ለመቆም ያደረጉትን ውሳኔ ያጠነክርላቸዋል። ታዲያ የኢየሱስ ሚና ምንድን ነው? እሱን ‘መመልከት’ የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?
9. ጳውሎስ ኢየሱስን “ሐዋርያ” እና “ሊቀ ካህናት” ብሎ የጠራው ለምን ነበር?
9 ጳውሎስ ኢየሱስን “ሐዋርያ” እና “ሊቀ ካህናት” ብሎ ጠርቶታል። የተላከ የሚል ትርጉም ያለው “ሐዋርያ” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርግበትን መንገድ ያመለክታል። “ሊቀ ካህናት” ሰዎች ወደ አምላክ መቅረብ የሚችሉበት የመገናኛ መስመር ነው። እነዚህ ሁለት ዝግጅቶች ለእውነተኛ አምልኮ እጅግ አስፈላጊ ሲሆኑ ኢየሱስ ደግሞ ሁለቱንም በተሻለ ሁኔታ አቅፎ ይዟል። ስለ አምላክ እውነት የሆነውን ነገር ለሰው ልጆች እንዲያስተምር ከሰማይ የተላከው እሱ ነበር። (ዮሐንስ 1:18፤ 3:16፤ 14:6) በተጨማሪም ኢየሱስ በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ ኃጢአትን እንዲያስተሰርይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ነው። (ዕብራውያን 4:14, 15፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በኢየሱስ አማካኝነት የምናገኛቸውን በረከቶች ከልብ የምናደንቅ ከሆነ በእምነት ጸንቶ ለመቀጠል የሚያስፈልገው ድፍረትና ቆራጥነት ይኖረናል።
10. (ሀ) ጳውሎስ ክርስትና ከአይሁድ እምነት የላቀ መሆኑን ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲገነዘቡ የረዳቸው እንዴት ነበር? (ለ) ጳውሎስ ጉዳዩን አስረግጦ ለማስረዳት ሲል የትኛውን ማንም ሊክደው የማይችል ሐቅ ጠቅሷል?
10 ጳውሎስ ክርስቲያናዊው እምነት ያለውን ዋጋማነት ለማጉላት ሲል ኢየሱስን ከሙሴ ጋር አወዳድሮታል። አይሁዳውያን ከጥንት አባቶቻቸው መካከል ሙሴን እንደ ታላቅ ነቢይ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሙሴ የሚበልጥ መሆኑን በሚገባ ከተገነዘቡ ክርስትና ከአይሁድ እምነት የላቀ መሆኑን የሚጠራጠሩበት ምንም ምክንያት አይኖራቸውም። ሙሴ በአምላክ ‘ቤት’ ማለትም በእስራኤል ብሔር ወይም ጉባኤ ላይ ኃላፊነት የተሰጠው የታመነ ሰው ቢሆንም ታማኝ ሎሌ ወይም አገልጋይ ብቻ እንደነበረ ጳውሎስ አመልክቷል። (ዘኁልቁ 12:7) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ የአምላክ ልጅና የቤቱ ጌታ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ዕብራውያን 3:2, 3, 5) ጳውሎስ ጉዳዩን አስረግጦ ለማስረዳት ሲል የሚከተለውን ማንም ሊክደው የማይችል ሐቅ ጠቅሷል:- “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው።” (ዕብራውያን 3:4) አምላክ የሁሉ የበላይ መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም። ምክንያቱም እሱ ሁሉን የገነባና የፈጠረ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ከአምላክ ጋር አብሮ ይሠራ የነበረ በመሆኑ ሙሴን ጨምሮ የሁሉም ፍጥረታት የበላይ መሆኑ ምክንያታዊ ነው።—ምሳሌ 8:30፤ ቆላስይስ 1:15-17
11, 12. ጳውሎስ ምን ነገርን ‘እስከ መጨረሻው አጽንተው እንዲጠብቁ’ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል? እኛስ ይህን ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?
11 በእርግጥም ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከፍተኛ ሞገስ አግኝተው ነበር። ጳውሎስ “የሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች” መሆናቸውን እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል፤ ይህ ደግሞ የአይሁድ ሥርዓት ሊሰጣቸው ከሚችለው ነገር ሁሉ ይበልጥ ውድ የሆነ መብት ነው። (ዕብራውያን 3:1) የጳውሎስ ቃላት እነዚያ የተቀቡ ክርስቲያኖች በአይሁዳዊነታቸው ሊያገኟቸው የሚችሏቸውን ነገሮች በመተዋቸው ከማዘን ይልቅ ለአዲስ ውርሻ በመታጨት ላገኙት መብት አመስጋኞች እንዲሆኑ አድርገዋቸው መሆን አለበት። (ፊልጵስዩስ 3:8) ጳውሎስ ያገኙትን መብት አጥብቀው እንዲይዙት እንጂ አቅልለው እንዳይመለከቱት ሲያሳስባቸው እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ [በአምላክ ቤት] ላይ የታመነ ነው፤ እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።”—ዕብራውያን 3:6
12 አዎን፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በጣም እየተቃረበ የነበረውን የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ በሕይወት ለማለፍ ከፈለጉ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋ አጥብቀው በመያዝ ‘እስከ መጨረሻው መጽናት’ ነበረባቸው። እኛም ዛሬ የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ለማለፍ ከፈለግን እንዲሁ ማድረግ አለብን። (ማቴዎስ 24:13) በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ አስጨናቂ ሁኔታዎች፣ የሰዎች ግድየለሽነት ወይም የራሳችን የአለፍጽምና ዝንባሌዎች በአምላክ ተስፋዎች ላይ ያለንን እምነት እንዲያናውጡት መፍቀድ የለብንም። (ሉቃስ 21:16-19) ጳውሎስ ቀጥሎ ለተናገራቸው ቃላት ትኩረት በመስጠት ራሳችንን እንዴት ማጠንከር እንደምንችል እንመልከት።
‘ልባችሁን አታደንድኑ’
13. ጳውሎስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? መዝሙር 95ንስ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ስላገኙት ሞገስ ከገለጸ በኋላ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል:- ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፣ . . . በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፣ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ [“አታደንድኑ፣” NW]።” (ዕብራውያን 3:7, 8) ጳውሎስ እየጠቀሰ ያለው ከ95ኛው መዝሙር ስለነበር “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል” ብሎ ለመናገር ይችላል።b (መዝሙር 95:7, 8፤ ዘጸአት 17:1-7) ቅዱሳን ጽሑፎች በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
14. እስራኤላውያን ይሖዋ ላደረገላቸው ነገር ምን ምላሽ ሰጡ? ለምንስ?
14 እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ ከይሖዋ ጋር በቃል ኪዳን የታሰረ ዝምድና በመመሥረት ታላቅ ክብር አግኝተዋል። (ዘጸአት 19:4, 5፤ 24:7, 8) ይሁን እንጂ አምላክ ያደረገላቸውን ከማድነቅ ይልቅ ብዙም ሳይቆዩ ዓመፀኞች ሆኑ። (ዘኁልቁ 13:25–14:10) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ልባቸውን በማደንደናቸው ምክንያት እንደሆነ ገልጿል። የአምላክን ቃል ያስተውልና ጥሩ ምላሽ ይሰጥ የነበረ ልብ እንዴት ደንዳና ሊሆን ይችላል? ይህን ለመከላከልስ ምን ማድረግ አለብን?
15. (ሀ) ጥንትም ሆነ ዛሬ ‘የአምላክ ድምፅ’ ሲሰማ የቆየው እንዴት ነው? (ለ) ‘የአምላክን ድምፅ’ አስመልክቶ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?
15 ጳውሎስ ማስጠንቀቂያውን የጀመረው “ድምፁን ብትሰሙት” በሚል ሐረግ ነው። አምላክ በሙሴና በሌሎች ነቢያት በኩል ለሕዝቡ ይናገር ነበር። ከዚያም ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተናግሯል። (ዕብራውያን 1:1, 2) ዛሬ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ሙሉው የአምላክ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ አለን። በተጨማሪም መንፈሳዊ ‘ምግብ በተገቢው ጊዜ’ የሚያቀርብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” አለን። (ማቴዎስ 24:45-47) ስለዚህ ይሖዋ አሁንም እየተናገረ ነው። ታዲያ እየሰማነው ነው? ለምሳሌ ያህል ስለ አለባበሳችንና አጋጌጣችን ወይም ስለ መዝናኛና ሙዚቃ ምርጫችን ለተሰጠን ምክር ምላሽ እየሰጠን ያለነው እንዴት ነው? ትኩረት በመስጠትና የተነገረውን በመታዘዝ ‘እንደምንሰማ’ እናሳያለንን? ለምንሠራቸው ነገሮች ሰበብ የመፍጠር ወይም የሚሰጠንን ምክር የመቃወም ልማድ ካለን ራሳችንን ረቂቅ ለሆነ አደጋ በማጋለጥ ልባችን ደንዳና እንዲሆን መንገድ እየከፈትንለት ነው ማለት ነው።
16. ልባችን ደንዳና ሊሆን የሚችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
16 በተጨማሪም ማድረግ የምንችለውንና ማድረግ ያለብንን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የምንል ከሆነ ልባችን ደንዳና ሊሆን ይችላል። (ያዕቆብ 4:17) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ብዙ ነገር ቢያደርግላቸውም እምነት ማሳየታቸውን አቆሙ፣ በሙሴ ላይ ዓመፁ፣ ስለ ከነዓን የሰሙትን መጥፎ ዜና ለማመን መረጡ፣ እንዲሁም ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት አሻፈረን አሉ። (ዘኁልቁ 14:1-4) ስለዚህ ይሖዋ የዚያ እምነት የለሽ ትውልድ አባላት ሞተው እስኪያልቁ ድረስ 40 ዓመታት ሙሉ በምድረ በዳ እንዲቆዩ ወሰነ። አምላክ ስለጠላቸው እንዲህ ብሎ ተናገረ:- “ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ፤ እንዲሁ:- ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቊጣዬ ማልሁ።” (ዕብራውያን 3:9-11) ይህ ለእኛ ምን ትምህርት ይሰጠናል?
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
17. እስራኤላውያን የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች ቢመለከቱና ቃሉን ቢሰሙም እምነት ያጡት ለምን ነበር?
17 ከግብጽ የወጣው የእስራኤላውያን ትውልድ የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች በገዛ ዓይኑ ተመልክቷል፤ ቃሉንም በገዛ ጆሮው ሰምቷል። ያም ሆኖ እስራኤላውያን አምላክ ወደ ተስፋይቱ ምድር በደህና ሊያደርሳቸው እንደሚችል እምነት አልነበራቸውም። ለምን? ይሖዋ “መንገዴን . . . አላወቁም” ብሏል። ይሖዋ ቀደም ሲል ምን እንደተናገረና ምን እንዳደረገ ያውቃሉ፤ ይሁን እንጂ እነሱን ለመንከባከብ ባለው ችሎታ ላይ ትምክህትና እምነት መገንባት ሳይችሉ ቀሩ። የግል ፍላጎቶቻቸውንና ምኞቶቻቸውን ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት ከልክ በላይ በመጠመዳቸው ለአምላክ መንገዶችና ዓላማዎች ትኩረት ሳይሰጡ ቀሩ። አዎን፣ አምላክ በገባው ቃል ላይ እምነት አጡ።
18. በጳውሎስ አነጋገር መሠረት “እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ” የሚያስከትለው የትኛው አካሄድ ነው?
18 ለዕብራውያን የተነገሩት ቀጥሎ ያሉት ቃላት ለእኛም በእኩል ደረጃ ይሠራሉ:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ እንዳታፈሩ ተጠንቀቁ።” (ዕብራውያን 3:12 NW) ጳውሎስ ‘ሕያው ከሆነው አምላክ መራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ’ እንደሚያስከትል በመግለጽ የጉዳዩን ሥረ መሠረት አመልክቷል። ቀደም ሲል በዚህ ደብዳቤ ላይ በመዘናጋት ምክንያት ‘ስለ መወሰድ’ ተናግሮ ነበር። (ዕብራውያን 2:1) ይሁን እንጂ “መራቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ገለል ማለት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን “ክህደት” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና አለው። ቃሉ አንድን ነገር በመናቅ ሆን ብሎ መቃወምን፣ ትቶ መውጣትንና መክዳትን ያመለክታል።
19. ምክርን አለመስማት የትኞቹን ከባድ መዘዞች ያስከትላል? በምሳሌ አስረዳ።
19 ስለዚህ ይሖዋ በቃሉና በታማኙ ባሪያው ክፍል የሚሰጠንን ምክር ችላ በማለት ‘ድምፁን ያለመስማት’ ልማድ ካለን ብዙም ሳይቆይ ልባችን መጅ ያወጣል እንዲሁም ደንዳና ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ያልተጋቡ ወንድና ሴት ከልክ በላይ በመቀራረብ ማድረግ የሌለባቸውን ድርጊት ፈጽመው ይሆናል። ጉዳዩን ችላ ቢሉትስ? ቀደም ሲል ያደረጉትን ነገር ደግመው እንዳያደርጉ ሊጠብቃቸው ይችላል? ከዚህ ይልቅ ያንኑ ድርጊት ደግመው እንዲፈጽሙ በር አይከፍትላቸውምን? በተመሳሳይም የባሪያው ክፍል በሙዚቃ፣ በመዝናኛና በሌሎችም ነገሮች ረገድ መራጮች እንድንሆን ምክር ሲለግሰን በአድናቆት ተቀብለን አስፈላጊውን ማስተካከያ እናደርጋለንን? ጳውሎስ ‘መሰብሰባችንን እንዳንተው’ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ይህ ምክር ቢሰጥም አንዳንዶች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ብዙም ትኩረት አይሰጡም። ከአንዳንድ ስብሰባዎች መቅረት ወይም አንዳንዶቹን ስብሰባዎች ከናካቴው እርግፍ አድርጎ መተው ምንም ችግር እንደሌለው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል።
20. ለቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር አዎንታዊ ምላሽ መስጠታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
20 በቅዱሳን ጽሑፎችና መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረጉ ሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት በግልጽ ለሚሰማው የይሖዋ “ድምፅ” አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጠን ብዙም ሳንቆይ ‘ሕያው ከሆነው አምላክ እንርቃለን።’ ምክርን እንዲያው ችላ ማለት በቀላሉ ወደ ማቃለል፣ መንቀፍና መቃወም ሊያመራ ይችላል። ይህ ሁኔታ ካልታረመ “እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ” እንድናፈራ ያደርገናል፤ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ከእንዲህ ዓይነቱ አካሄድ መመለሱ በጣም አስቸጋሪ ነው። (ከኤፌሶን 4:19 ጋር አወዳድር።) ኤርምያስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” በማለት በትክክል ጽፏል። (ኤርምያስ 17:9) በዚህ ምክንያት ጳውሎስ መሰል ዕብራውያን አማኞችን “ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ [“ደንዳና፣” NW] እንዳይሆን፣ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፣ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ” ሲል አሳስቧቸዋል።—ዕብራውያን 3:13
21. ሁላችንም ምን እንድናደርግ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል? የትኞቹስ ተስፋዎች አሉን?
21 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ለእኛም እየተናገረ በመሆኑ እጅግ ደስተኞች ነን! “ታማኝና ልባም ባሪያ” ‘የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን እንድንጠብቅ’ እኛን መርዳቱን በመቀጠሉ አመስጋኞች ነን። (ዕብራውያን 3:14) ለአምላክ ፍቅርና አመራር ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው። ይህን ስናደርግ ይሖዋ ቃል ከገባቸው አስደናቂ ነገሮች ውስጥ አንዱ ወደሆነው ወደ ዕረፍቱ ‘ለመግባት’ እንችላለን። (ዕብራውያን 4:3, 10) ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ቀጥሎ የገለጸው ስለዚህ ጉዳይ ሲሆን እኛም በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምረዋለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጆሴፈስ ዘገባ መሠረት ፌስተስ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሰዱቃውያን ወገን የሆነው አናነስ (ሐናንያ) ሊቀ ካህናት ሆነ። የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነውን ያዕቆብንና ሌሎች ደቀ መዛሙርትን በሳንሄድሪን ፊት አቅርቦ ሞት እንዲፈረድባቸውና በድንጋይ ተወግረው እንዲሞቱ አድርጓል።
b ጳውሎስ “መሪባህ” እና “ማሳህ” የሚሉትን የዕብራይስጥ ቃላት “መጣላት” እና “መፈታተን” ብሎ ከሚተረጉመው ከግሪኩ የሴፕቱጀንት ትርጉም ጠቅሶ መጻፉን ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 350ና 379 ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ጠንካራ ምክር የጻፈው ለምን ነበር?
◻ ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በአይሁድ እምነት ሥር ከነበራቸው ሕይወት የተሻለ ነገር እንዳገኙ እንዲገነዘቡ የረዳቸው እንዴት ነበር?
◻ የአንድ ሰው ልብ ደንዳና የሚሆነው እንዴት ነው?
◻ “እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ” እንዳናፈራ ለመከላከል ምን ማድረግ አለብን?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በታላቁ ሙሴ በኢየሱስ እንደምታምን ታሳያለህን?