“እናንተም እንዲሁ ሩጡ”
በከፍተኛ የሆታ ስሜት በተዋጡ ተመልካቾች በተሞላ የስፖርት ስታዲየም ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ስፖርተኞቹ ወደ ሜዳው በመጉረፍ ላይ ናቸው። የሚደግፏቸው አትሌቶች ብቅ ሲሉ ሕዝቡ በከፍተኛ ጩኸት ይቀበላቸዋል። ዳኞች ሕጉን ለማስከበር ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። ውድድሩ በሚካሄድበት ጊዜ የአሸናፊዎቹ ሆታና የተሸናፊዎቹ ጩኸት ድብልቅልቁ ይወጣል። ተመልካቾቹ በደማቅ ጭብጨባ ለአሸናፊዎቹ ደስታቸውን ይገልጻሉ!
የተገኘኸው በዘመናችን በሚደረግ የስፖርት ውድድር ላይ ሳይሆን ከዛሬ 2, 000 ዓመት በፊት አካባቢ በቆሮንቶስ ልሳነ ምድር ይደረግ በነበረው የስፖርት ውድድር ላይ ነው። ከስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስከ አራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ በየሁለት ዓመቱ በዚህ ቦታ ይካሄድ በነበረው የስፖርት ውድድር ላይ ኢስሚየን የሚባል የታወቀ ስፖርት ይካሄድ ነበር። ይህ ክንውን ለበርካታ ቀናት መላውን የግሪክ ነዋሪ ቀልብ የሚስብ ነበር። ውድድሩ እንዲሁ የአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ አልነበረም። አትሌቶቹ የወታደራዊ ዝግጁነት ምልክት ነበሩ። የአምልኮ ክብር የሚሰጣቸው አሸናፊዎቹ አትሌቶች ከዛፍ ቅጠል የተጎነጎኑ ዘውዶች ይጫንላቸዋል። ሽልማት ይዥጎደጎድላቸዋል እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች ለቀሪው ሕይወታቸው የሚሆናቸውን ጠቀም ያለ ገንዘብ ይሰጧቸዋል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ አቅራቢያ ይደረግ የነበረውን የኢስሚየን ውድድር ያውቅ ስለነበር አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርገውን ጉዞ ከአንድ የአትሌቲክስ ውድድር ጋር በማመሳሰል ተናግሯል። ሯጮችን፣ የነፃ ትግል ተወዳዳሪዎችንና ቦክሰኞችን በመጥቀስ ጥሩ ሥልጠና፣ ተገቢ ጥረትና ጽናት የሚያስገኙትን ወሮታ ጥሩ በሆነ መንገድ ገልጿል። እርግጥ ነው፣ ደብዳቤውን የጻፈላቸው ክርስቲያኖችም ውድድሩን በሚገባ ያውቃሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት በስታዲየሙ ውስጥ ከሚጮኸው ሕዝብ መካከል እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ጳውሎስ የተጠቀመበት ምሳሌ በቀላሉ ይገባቸው ነበር። ስለ እኛስ ምን ለማለት ይቻላል? እኛም ብንሆን ለዘላለም ሕይወት በሚደረገው ሩጫ ውስጥ ገብተናል። ጳውሎስ ስለ እነዚያ ውድድሮች ከተናገረው መግለጫ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
‘በደንቡ መሠረት መታገል’
ጥንት ይደረጉ በነበሩት ጨዋታዎች ለመሳተፍ ብቃቱ በጣም ጥብቅ ነበር። እያንዳንዱ ስፖርተኛ በተመልካቹ ፊት እንዲቆም ይደረግና እርሱን የሚመለከት ጥያቄ ይቀርብ ነበር:- ‘ከመካከላችሁ ይህ ሰው ወንጀለኛ ነው ብሎ የሚከሰው ሰው አለ? ዘራፊ ወይም ክፉ እንዲሁም በአኗኗሩና በምግባሩ ነውረኛ ነውን?’ ኤርካይኦሎጂኤ ግራይኬ በሚለው መሠረት “ወንጀለኛ እንደሆነ የሚታወቅ ወይም በዚህ መልኩ ከሚታወቅ ሰው ጋር [የቅርብ] ግንኙነት ያለው ግለሰብ በውድድሩ ተካፋይ እንዲሆን አይፈቀድለትም ነበር።” እንዲሁም የጨዋታውን ደንብ የሚጥስ ሰው ከውድድሩ እንዲባረር በማድረግ ከፍተኛ ቅጣት ይፈጸምበት ነበር።
ይህን ማወቃችን የሚከተለውን ጳውሎስ የጻፈውን ሐሳብ እንድንረዳ ያስችለናል:- “በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፣ እንደሚገባ አድርጎ [“በደንቡ መሠረት፣” የ1980 ትርጉም ] ባይታገል፣ የድሉን አክሊል አያገኝም።” (2 ጢሞቴዎስ 2:5) በተመሳሳይም ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መስፈርቶች በማክበር ይሖዋ ያወጣቸውን መስፈርት ማሟላት አለብን። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” በማለት ያስጠነቅቀናል። (ዘፍጥረት 8:21) ስለዚህ ወደ ሩጫው ከገባን በኋላም እንኳ የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን ለመቀጠልና የዘላለም ሕይወት ለመውረስ በደንቡ መሠረት ለመወዳደር ጠንቃቆች መሆን አለብን።
በዚህ ረገድ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግልን ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። (ማርቆስ 12:29-31) እንዲህ ያለው ፍቅር ይሖዋን እንድናስደስትና እንደ ፈቃዱ እንድንመላለስ ፍላጎት እንዲያድርብን ይረዳናል።—1 ዮሐንስ 5:3
‘ሸክምን ሁሉ ማስወገድ’
ጥንት ይደረግ በነበረው ውድድር የሚካፈሉ ሯጮች ልብስና ቁሳቁስ አይሸከሙም ነበር። “በሩጫ ውድድር የሚካፈሉ ሯጮች የሚሮጡት ሙሉ በሙሉ እርቃናቸውን ነበር” በማለት ዘ ላይፍ ኦቭ ዘ ግሪክስ ኤንድ ሮማንስ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ሯጮቹ ልብስ አለመልበሳቸው ፍጥነት ይጨምርላቸዋል እንዲሁም ያለ ችግር እንዲንቀሳቀሱና ቀልጣፎች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። አላስፈላጊ ሸክም በማብዛት የሚያባክኑት ኃይል አልነበረም። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች “እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ . . . አስወግደን፣ . . . በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW ] እንሩጥ” በማለት የጻፈው ይህን በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት።—ዕብራውያን 12:1
ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ወደኋላ ሊጎትተን የሚችለው ሸክም ምን ዓይነት ነው? አንዱ አስፈላጊ ያልሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን የማዳበር ወይም የቅንጦት አኗኗር የመከተል ምኞት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ሃብትን እንደ ደህንነታቸው ዋስትና ወይም የደስታ ምንጭ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል። እንዲህ ያለው ትርፍ “ሸክም” ሯጩ በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ ቦታ እስኪያጣ ድረስ ወደኋላ ሊጎትተው ይችላል። (ሉቃስ 12:16-21) የዘላለም ሕይወት ሊደረስበት የማይችል የሕልም እንጀራ ሆኖ ሊታየው ይችላል። አንድ ሰው ‘አዲሱ ዓለም መምጣቱ የማይቀር ቢሆንም እስከዚያው ድረስ ግን ዓለም የሚያቀርባቸው ነገሮች ሊያመልጡን አይገባም’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19) እንዲህ ያለው ቁሳዊ አመለካከት አንድ ሰው ለሕይወት ከሚያደርገው ሩጫ በቀላሉ እንዲዘናጋ ሊያደርገው ወይም ገና ከጅምሩ በሩጫው እንዳይሰለፍ ሊያደርገው ይችላል።
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ብሏል። ከዚያም ይሖዋ ለእንስሳትና ለዕጽዋት እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸውና ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች የበለጠ ዋጋ እንዳላቸው ከተናገረ በኋላ የሚከተለውን ምክር ለገሰ:- “እንግዲህ:- ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:24-33
“በጽናት እንሩጥ”
በጥንት ጊዜ የነበሩት የሩጫ ውድድሮች የአጭር ርቀት ብቻ አልነበሩም። ዶሊሆስ የተባለው አንዱ ዓይነት የሩጫ ውድድር አራት ኪሎ ሜትር የሚያህል ርቀት መሸፈንን የሚጠይቅ ነበር። ይህ ጥንካሬንና ጽናትን የሚፈትን ውድድር ነበር። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው በ328 ከዘአበ ኤዪየስ የተባለ አንድ ስፖርተኛ በዚህ የሩጫ ውድድር ካሸነፈ በኋላ የተቀዳጀውን ድል በትውልድ ከተማው ለማብሰር ሲል እስከ አርጎስ ድረስ ሮጧል። በዚያ ቀን 110 ኪሎ ሜትር የሚያህል ርቀት ሮጧል!
የክርስቲያኖች ሩጫም ጽናታችንን የሚፈታተን የረዥም ርቀት ውድድር ነው። የይሖዋን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት በዚህ የሩጫ ውድድር እስከ መጨረሻው በጽናት መሮጥ ያስፈልጋል። ጳውሎስ በዚህ መንገድ እስከ መጨረሻው ሮጧል። በሕይወቱ ፍጻሜ አካባቢ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” ብሎ ለመናገር ችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) ልክ እንደ ጳውሎስ እኛም ‘እስከ መጨረሻው’ መሮጥ አለብን። ሩጫው መጀመሪያ ላይ አስበነው ከነበረው የራቀ መስሎን ጽናታችንን ካላላን ሽልማታችንን ሳናገኝ ልንቀር እንችላለን። (ዕብራውያን 11:6) የመጨረሻውን መስመር በቅርብ እያየነው ወደኋላ ብንል ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል!
ሽልማቱ
በጥንቱ የግሪክ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ድል ለተቀዳጁ ሰዎች በአበባ ያጌጠ ከዛፍ ቅጠል የተሠራ የአበባ ጉንጉን ሽልማት ይሰጣቸው ነበር። በፓይቲያን ውድድር አሸናፊዎች የሚሆኑት ላውረል ከሚባል ዛፍ ቅጠል የተሠራ አክሊል ራሳቸው ላይ ይደፋላቸው ነበር። በኦሊምፒያ ጨዋታዎች ከወይራ ቅጠል የተሠራ አክሊል ሲሰጣቸው በኢስሚየን ጨዋታዎች ደግሞ ከጥድ የተሠራ አክሊል ይሸለሙ ነበር። “የተወዳዳሪዎቹን የጋለ ስሜት ይበልጥ ለማቀጣጠል” ይላሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት ለድል አድራጊው የሚሸለመው ዘውድ እና የዘምባባ ቅርንጫፎች በስታዲየሙ ውስጥ ተወዳዳሪዎቹ ሊያዩት በሚችሉት ቦታ በበርጩማ ወይም በጠረጴዛ ላይ ይቀመጡ ነበር።” አሸናፊው አክሊሉን መጫኑ የታላቅ ክብር መግለጫ ነበር። ወደ ቤቱ በሚመለስበት ጊዜ በድል አድራጊነት ስሜት ሰረገላ ላይ ተቀምጦ ወደ ከተማ ይገባል።
ጳውሎስ ይህን በአእምሮው በመያዝ ለቆሮንቶስ አንባቢዎቹ የሚከተለውን ጥያቄ አቅርቦላቸዋል:- “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፣ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ [“እናንተም እንዲሁ፣” NW ] ሩጡ። . . . እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፣ እኛ ግን የማይጠፋውን።” (1 ቆሮንቶስ 9:24, 25፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4) እንዴት ያለ ግሩም ንጽጽር ነው! ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ እስከ መጨረሻዋ መስመር ድረስ የሚሮጡ ሁሉ የሚሰጣቸው ሽልማት በጥንቶቹ ጨዋታዎች ለአሸናፊዎቹ ይሰጥ እንደነበረው ዓይነት አክሊል የሚጠፋ አይደለም።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን የተሻለ አክሊል በማስመልከት “የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:4) ይህ ዓለም ሊያቀርብ የሚችለው የትኛውም ዓይነት ሽልማት ካለመሞት ባሕርይ ማለትም የማይበሰብስ ሕይወት አግኝቶ በሰማያዊ ክብር ከክርስቶስ ጋር ከመኖር ጋር ሊወዳደር ይችላልን?
በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ የክርስትና ሯጮች መንፈሳዊ ልጆቹ እንዲሆኑ በአምላክ የተቀቡና ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው አይደሉም። በመሆኑም የሚሮጡት ያለመሞትን ባሕርይ ለመውረስ አይደለም። ይሁን እንጂ አምላክ ለእነርሱም ቢሆን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሽልማት ከፊታቸው አስቀምጦላቸዋል። ይህም በሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምትተዳደረው ገነት የሆነች ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት ነው። አንድ ክርስቲያን ዓይኑ ያረፈው በየትኛውም ሽልማት ላይ ቢሆን በአትሌቲክስ ውድድር ከሚካፈል ከማንኛውም ሯጭ በበለጠ ቆራጥነትና ወኔ መሮጥ ይኖርበታል። ለምን? ምክንያቱም ሽልማቱ ፈጽሞ የሚጠፋ አይደለም። “እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።”—1 ዮሐንስ 2:25
እንዲህ ያለ ወደር የለሽ ሽልማት ከፊቱ የተቀመጠለት አንድ ክርስቲያን ይህ ዓለም ለሚያቀርባቸው ማባበያዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል? እንደሚከተለው ብሎ የተናገረውን የጳውሎስ ዓይነት አመለካከት ሊሆን ይገባል:- “በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጒዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፣ . . . በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቆጥራለሁ።” ከዚህ ጋር በመስማማት ጳውሎስ በብርቱ ሮጧል! “ወንድሞች ሆይ፣ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፣ . . . ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ [“ሽልማቴንም ለመግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፣” የ1980 ትርጉም ]።” (ፊልጵስዩስ 3:8, 13, 14) ጳውሎስ ዓይኑን በሽልማቱ ላይ ተክሎ ሮጧል። እኛም እንደዚያ ማድረግ አለብን።
ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን
በጥንቱ ጨዋታ ለአሸናፊዎች ከፍተኛ አድናቆት ይሰጥ ነበር። ግጥም ይጻፍላቸዋል፣ ቅርጽ አውጪዎች ሐውልት ይሠሩላቸዋል። ታሪክ ጸሐፊው ቪዬራ ኦሊቮቬ “ታላቅ ክብር ይላበሱና በጣም ሰፊ የሆነ እውቅና ያገኙ ነበር” ብሏል። እንዲሁም የአዲሱ ትውልድ ተፋላሚዎች ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ።
ለክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ የተወላቸው “ድል አድራጊ” ማን ነው? ጳውሎስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብራውያን 12:1, 2) አዎን፣ ለዘላለም ሕይወት በምናደርገው ሩጫ ድል ማድረግ የምንፈልግ ከሆነ ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አትኩረን መመልከት ይኖርብናል። የወንጌል ዘገባዎችን ዘወትር በማንበብና እርሱን ልንመስል በምንችልበት አቅጣጫ ላይ በማሰላሰል ይህንን ማድረግ እንችላለን። በዚህ መንገድ የምናደርገው ጥናት ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ታዛዥ እንደነበረና በመጽናት ጠንካራ እምነት እንዳለው እንዳስመሰከረ ያሳየናል። ያሳየው ጽናት በርካታ ግሩም መብቶችን ጨምሮ የይሖዋ አምላክን ሞገስ አስገኝቶለታል።—ፊልጵስዩስ 2:9-11
እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ከነበሩት ድንቅ ባሕርያት መካከል የመጀመሪያው ፍቅሩ ነው። “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15:13) ጠላቶቻችንን እንኳ ሳይቀር እንድንወድ በመናገር “ፍቅር” የሚለው ቃል ትልቅ ትርጉም እንዲኖረው አድርጓል። (ማቴዎስ 5:43-48) ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን ይወድ ስለነበር የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ደስታ አግኝቷል። (መዝሙር 40:9, 10፤ ምሳሌ 27:11) ኢየሱስን እንደ ምሳሌያችንና አድካሚ ለሆነው የሕይወት ሩጫ ዱካውን እንደተወልን አድርገን መመልከታችን እኛም አምላክንና ጎረቤቶቻችንን እንድንወድድ እንዲሁም በምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ማቴዎስ 22:37-39፤ ዮሐንስ 13:34፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ የማይቻል ነገር እንድናደርግ እንዳልጠየቀ አስታውስ። “እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ማቴዎስ 11:28-30
ኢየሱስ እንዳደረገው እኛም ዓይናችንን እስከ መጨረሻው ለጸኑ ሁሉ በተጠበቀላቸው ሽልማት ላይ መትከል ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:13) በደንቡ መሠረት የምንታገል፣ ሸክምን ሁሉ የምናስወግድና በጽናት የምንሮጥ ከሆነ ድል እንደምናደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ከፊታችን ያስቀመጥነው ግብ ወደፊት እንድንገሰግስ ግፊት ይጨምርልናል! በውስጣችን ደስታን ስለሚያቀጣጥልልን ጉልበታችንን ያድስልናል። ይህም ደስታ ከፊታችን ያለውን የምንጓዝበትን መንገድ ቀላል ያደርግልናል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቲያኖች ሩጫ የረዥም ርቀት ሩጫ በመሆኑ ጽናት ይጠይቃል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች አትሌቶቹ ከሚያገኙት አክሊል በተለየ መልኩ የማይጠፋ ሽልማት ለማግኘት ይጠባበቃሉ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽልማቱ እስከ መጨረሻው ለሚጸኑ ሁሉ ነው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Copyright British Museum