የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ጭንቀት የእምነት ማነስን ያመለክታል?
“መጨነቅ ተገቢ አይደለም።” በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አንድ ቄስ በዚህ ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን “ከባድ ኃጢአት” እንደሆነም ተናግረዋል። በቅርቡ ደግሞ አንድ ዘጋቢ ስጋትንና ጭንቀትን ስለመቋቋም ሲጽፍ “ጭንቀት በአምላክ እንደማንታመን ያሳያል” ብሏል።
ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ጸሐፊዎች ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “አትጨነቁ” በማለት የተናገረውን ተንተርሰው ነው። (ማቴዎስ 6:25) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በጭንቀት ስለሚጠቁ አንድ ክርስቲያን በጭንቀት ከተዋጠ የጥፋተኝነት ስሜት ሊያድርበት ይገባል? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። መጨነቅ የእምነት ማነስን ያመለክታል?
አምላክ አለፍጽምናችንን ይረዳልናል
መጽሐፍ ቅዱስ የጭንቀት መንስኤ ምንጊዜም የእምነት ማነስ ነው ብሎ አያስተምርም። የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ስለሆነ ይብዛም ይነስ እንጂ ጭንቀት ማጋጠሙ አይቀርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ታማኝ ክርስቲያኖች በጤና ዕጦት፣ በእርጅና፣ በገንዘብ ችግር፣ በቤተሰብ ግጭት፣ በወንጀልና በሌሎችም ችግሮች የተነሳ በየዕለቱ የሚያጋጥሟቸውን ጭንቀቶች ተቋቁመው ለመኖር ይገደዳሉ። በጥንት ጊዜም የአምላክ አገልጋዮች ፍርሃትና ስጋት ያጋጥማቸው ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሎጥ የሚናገረውን ታሪክ ተመልከት። ሰዶምና ገሞራ ሲጠፉ ሕይወቱን እንዳያጣ ወደ ተራራ ሸሽቶ እንዲያመልጥ አምላክ አዝዞት ነበር። ይሁን እንጂ ሎጥ ከባድ ጭንቀት አደረበት። ‘[ይሖዋ NW] ሆይ፣ እባክህ እንደዚህስ አይሁን’ አለ። በመቀጠልም ፈራ ተባ እያለ “እኔ እንደሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል” አለ። ሎጥ ወደ ተራሮቹ መሸሽ የፈራው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን አይነግረንም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ብቻ ሎጥ በጣም ፈርቷል። አምላክ ምን ምላሽ ሰጠው? ሎጥ እምነት አንሶሃል ወይም በአምላክ አልታመንክም ተብሎ ተወቅሶአል? ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ ለሎጥ አሳቢነት በማሳየት በአቅራቢያው ወዳለች ከተማ ሸሽቶ እንዲያመልጥ ፈቅዶለታል።—ዘፍጥረት 19:18-22
የይሖዋ ታማኝ አምላኪዎች በጣም የተጨነቁባቸው ጊዜያት እንደነበሩ የሚያሳዩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉ። ነቢዩ ኤልያስ የግድያ ዛቻ ሲደርስበት ፈርቶ ሸሽቶአል። (1 ነገሥት 19:1-4) ሙሴ፣ ሃና፣ ዳዊት፣ ዕንባቆም፣ ጳውሎስና ሌሎች ጠንካራ እምነት የነበራቸው ወንዶችና ሴቶች የተሰማቸውን ጭንቀት ገልጸዋል። (ዘፀአት 4:10፤ 1 ሳሙኤል 1:6፤ መዝሙር 55:5፤ ዕንባቆም 1:2, 3፤ 2 ቆሮንቶስ 11:28) ሆኖም አምላክ ርኅራኄ በማሳየትና በእነሱ መጠቀሙን በመቀጠል ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ችግር የሚገባው መሆኑን አሳይቷል።
‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኀጢአት’
ይሁን እንጂ የማያቋርጥ ጭንቀት እምነታችንን ሊያዳክምና በአምላክ ላይ ያለንን ትምክህት ሊያጠፋብን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እምነት ማጣትን ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኀጢአት’ ሲል ገልጾታል። (ዕብራውያን 12:1) ጳውሎስ ራሱን ጨምሮ መናገሩ አልፎ አልፎ የእምነት መዳከም ሲያጋጥመው ‘በቀላሉ ተተብትቦ’ የመያዝ አዝማሚያ እንዳለው ማመኑ ሊሆን ይችላል።
ዘካርያስ ሚስቱ እንደምትጸንስ የነገረውን መልአክ ያላመነው ምናልባት ከዚህ የተነሳ ሊሆን ይችላል። በአንድ ወቅት የኢየሱስ ሐዋርያት ‘እምነታቸው በማነሱ’ ምክንያት ተአምራዊ ፈውስ ማድረግ አቅቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ በአምላክ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት አላጡም።—ማቴዎስ 17:18–20፤ ሉቃስ 1:18, 20, 67፤ ዮሐንስ 17:26
በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ላይ ያላቸውን ትምክህት አጥተው አስከፊ መዘዝ የደረሰባቸውን ሰዎች ምሳሌም ይዟል። ለምሳሌ ያህል ከግብፅ የወጡ ብዙ እሥራኤላውያን እምነት በማጣታቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገቡ ተከልክለዋል። በአንድ ወቅት እነዚያ ሰዎች “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ!” በማለት በአምላክ ላይ ጭምር እስከማጉረምረም ደርሰዋል። አምላክ ደስ እንዳልተሰኘባቸው ለመግለጽ መርዛማ እባቦችን በመስደድ ቀጣቸው።—ዘኍልቁ 21:5, 6
ኢየሱስ ያደገባት የናዝሬት ከተማ ነዋሪዎች እምነት ስላልነበራቸው ብዙ ተአምር የማየት መብት ተነፍጓቸዋል። ከዚህም በላይ በዚያ ዘመን የነበረው ክፉ ትውልድ እምነት በማጣቱ የተነሳ ኢየሱስ ክፉኛ ነቅፎታል። (ማቴዎስ 13:58፤ 17:17፤ ዕብራውያን 3:19) ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ” ማለቱ የተገባ ነበር።—ዕብራውያን 3:12
አዎን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች የእምነት ማጣት ከክፉ ልብ ሊመነጭ ይችላል። ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሱት ምሳሌዎች እንዳየነው በዘካርያስና በኢየሱስ ሐዋርያት ላይ የደረሰው ሁኔታ ይህ አልነበረም። የእነሱ የእምነት ማነስ መንስኤ ድንገተኛ ድካም ነበር። አኗኗራቸውን በአጠቃላይ ካየን “ልባቸው ንጹሕ” እንደሆነ እንገነዘባለን።—ማቴዎስ 5:8
አምላክ የሚያስፈልገንን ያውቃል
ቅዱሳን ጽሑፎች በዕለታዊ ሕይወታችን በሚያጋጥመን ጭንቀትና እንደ ኃጢአት በሚቆጠረው እምነት ማጣት መካከል ያለውን ልዩነት እንድናስተውል ይረዱናል። ዕለታዊ ጭንቀት ወይም በሰብአዊ ድካም የተነሳ የሚያጋጥም ድንገተኛ የእምነት ማጣት ከክፉና ደንዳና ልብ ከሚመነጨው በአምላክ ላይ ፈጽሞ እምነት ከማጣት ጋር አንድ ተደርጎ መታየት አይኖርበትም። በመሆኑም ክርስቲያኖች አልፎ አልፎ ጭንቀት ቢያጋጥማቸው በጥፋተኝነት ስሜት መዋጥ የለባቸውም።
ይሁንና ሕይወታችንን እስኪቆጣጠረው ድረስ ከልክ በላይ በጭንቀት ላለመዋጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በመሆኑም ኢየሱስ “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ” ሲል ጥበብ የተሞላበት ሐሳብ ተናግሯል። ኢየሱስ ከዚህ በማስከተል የሚከተሉትን የሚያጽናኑ ቃላት ተናግሯል:- “የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል።”—ማቴዎስ 6:25-33
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ የተጨነቀባቸው ወቅቶች ነበሩ