እስከ መጨረሻው መጽናት ትችላላችሁ
“በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ።”—ዕብራውያን 12:1
1, 2. መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች “መጽናት ያስፈልጋችኋልና” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:36) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ የዚህን ባሕርይ አስፈላጊነት ለማጉላት ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን . . . ጨምሩ” ሲል መክሯል። (2 ጴጥሮስ 1:5, 6) ሆኖም መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?
2 ከግሪክኛ ወደ እንግሊዝኛ የሚተረጉም አንድ መዝገበ ቃላት “መጽናት” የሚለውን ግሪክኛ ቃል “ከመሸሽ ይልቅ በነበሩበት መቆየት . . .፣ ከአቋም ፍንክች አለማለት፣ ችግሩን መቋቋም” በማለት ተርጉሞታል። “ጽናት” ለሚለው ቃል የገባውን የግሪክኛ ስም በተመለከተ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ቃሉ አንድን ነገር በትዕግሥት ብቻ ሳይሆን ደስ የሚያሰኝ ተስፋ ይዞ የመቻልን መንፈስ ያመለክታል። . . . አንድ ሰው ችግርን ተቋቁሞ ሳይንገዳገድ እንዲቆም የሚያስችለው ባሕርይ ነው። ከባዱን መከራ ወደ ክብር ለመለወጥ የሚችል መልካም ባሕርይ ነው፤ ምክንያቱም ከስቃዩ በስተጀርባ ያለውን ግቡን አሻግሮ ይመለከታል።” እንግዲያው ጽናት አንድ ሰው ዕንቅፋቶች ወይም ችግሮች ሲያጋጥሙት ከአቋሙ ፍንክች ሳይል እንዲቆምና ተስፋ እንዳይቆርጥ ያስችለዋል። ይህ ባሕርይ በተለይ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?
3, 4. (ሀ) መጽናት የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? (ለ) እስከ መጨረሻው መጽናት ያለብን ለምንድን ነው?
3 በምሳሌያዊ ሁኔታ ሁሉም ክርስቲያኖች ጽናት በሚጠይቅ የሩጫ ውድድር ላይ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ በ65 እዘአ ገደማ ለሥራ ባልደረባውና ለታማኝ የጉዞ ጓደኛው ለጢሞቴዎስ የሚከተሉትን አጽናኝ ቃላት ጽፎለት ነበር:- “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ።” (2 ጢሞቴዎስ 4:7) ጳውሎስ “ሩጫውን ጨርሼአለሁ” የሚለውን መግለጫ ሲጠቀም ክርስቲያናዊ ሕይወቱን ከሩጫ ውድድር ጋር ማነጻጸሩ ነበር። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሩጫውን በድል ለመፈጸም ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ሽልማቱንም እንደሚቀበል እርግጠኛ ነበር። ቀጥሎም “ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል” በማለት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 4:8) ጳውሎስ እስከ መጨረሻ በመጽናቱ ሽልማቱን እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነበር። ስለ እኛስ ምን ለማለት ይቻላል?
4 ጳውሎስ በሩጫ ላይ ያሉትን ለማበረታታት “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 12:1) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ወደዚህ ጽናት የሚጠይቅ የሩጫ ውድድር የምንገባው ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ራሳችንን ስንወስን ነው። የደቀ መዝሙርነትን ጎዳና በጥሩ ሁኔታ መጀመሩ አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ውድድሩን ማጠናቀቃችን ነው። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:13) ስኬታማ በመሆን ሩጫውን የሚያጠናቅቁ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል! ከዚህ የተነሣ እኛም ይህን ግብ አድርገን እስከ መጨረሻ መጽናት ይኖርብናል። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ሊረዳን ይችላል?
የተስተካከለ አመጋገብ የግድ አስፈላጊ ነው
5, 6. (ሀ) ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ለመጽናት ለምን ነገር ትኩረት መስጠት አለብን? (ለ) ከየትኞቹ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ተጠቃሚዎች መሆን አለብን? ለምንስ?
5 በጥንት ጊዜ ታዋቂ የነበረው የኢስሚየን የስፖርት ጨዋታ በግሪክ በምትገኘው የቆሮንቶስ ከተማ አቅራቢያ ይካሄድ ነበር። የቆሮንቶስ ወንድሞች በዚህ ቦታ ከሚደረጉት የአትሌቲክ ግጥሚያዎችና ሌሎች ውድድሮች ጋር በደንብ እንደሚተዋወቁ ጳውሎስ ተገንዝቦ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ጳውሎስ ከሚያውቁት ነገር በመነሳት እነሱም ተካፋይ ስለሆኑበት ለሕይወት ስለሚደረገው ሩጫ እንደሚከተለው በማለት አሳስቧቸዋል:- “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፣ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።” ጳውሎስ በሩጫው ውድድር ላይ የመቆየቱንና እስከ ፍጻሜው ድረስ የመቀጠሉን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ሆኖም እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳቸው ይችላል? “የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል” በማለት አክሎ ተናግሯል። አዎን፣ በጥንት ጊዜያት ይደረጉ በነበሩ የስፖርት ጨዋታዎች የሚካፈሉ ሰዎች ለማሸነፍ ሲሉ ከባድ ስልጠና ይወስዱ የነበረ ሲሆን ለሚበሉትና ለሚጠጡት ነገርም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉና እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ይቆጣጠሩ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 9:24, 25
6 ክርስቲያኖች የሚካፈሉበት የሩጫ ውድድርስ? በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ ሽማግሌ “ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ለመጽናት ከፈለጋችሁ ለመንፈሳዊ አመጋገባችሁ ትኩረት መስጠት አለባችሁ” ብሏል። “ጽናት የሚሰጠው አምላክ” ይሖዋ ምን መንፈሳዊ ምግቦችን እንዳዘጋጀልን ተመልከት። (ሮሜ 15:5 NW) የመንፈሳዊ ምግባችን ዋነኛው ምንጭ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ጥሩ ልማድ ማዳበር አይኖርብንምን? በተጨማሪም ይሖዋ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ወቅታዊ የሆኑትን መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አዘጋጅቶልናል። (ማቴዎስ 24:45) እነዚህን በትጋት ማጥናቱ በመንፈሳዊ ያጠነክረናል። አዎን፣ ‘ዘመኑን በመዋጀት’ የግል ጥናት የምናደርግበት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል።—ኤፌሶን 5:16
7. (ሀ) መሠረታዊ የሆኑትን የክርስትና መሠረተ ትምህርቶች በማወቃችን ብቻ መርካት የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ‘ወደ ጉልምስና ማደግ’ የምንችለው እንዴት ነው?
7 በክርስቲያን ደቀ መዝሙርነት ጎዳና መመላለሳችንን ለመቀጠል መሠረታዊ የሆኑትን ‘የመጀመሪያ ትምህርቶች’ ትተን ‘ወደ ጉልምስና ማደግ’ ያስፈልገናል። (ዕብራውያን 6:1 NW) ስለዚህ የእውነትን ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት’ ለማወቅ ያለንን ፍላጎት ማሳደግና ‘የጎለመሱ ሰዎች የሚመገቡትን ጠንካራ ምግብ’ መውሰድ አለብን። (ኤፌሶን 3:18፤ ዕብራውያን 5:12-14) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት የሚናገረውን በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ ወንጌሎች ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አስተማማኝ ታሪክ ውሰድ። እነዚህን የወንጌል ዘገባዎች በጥንቃቄ በማጥናታችን ኢየሱስ ምን እንዳከናወነና ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ድርጊቶች ለመፈጸም የተነሳሳበትን ምክንያትም ለመገንዘብ ያስችለናል። በዚህ መንገድ “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ሊኖረን ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 2:16 NW
8. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ እንድንጸና ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ መሰል አማኞችን እንዲህ በማለት አሳስቧል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዴት ያሉ የማበረታቻ ምንጮች ናቸው! እንዲሁም ከሚያስቡልንና እስከ መጨረሻው መጽናት እንድንችል ሊረዱን ከሚፈልጉ አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶች ጋር መሆን ራሱ ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! ይህን ከይሖዋ የተገኘ ፍቅራዊ ዝግጅት አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ትጋት የሞላበት የግል ጥናት በማድረግና በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘት ‘በአእምሮ የበሰልን’ እንሁን።—1 ቆሮንቶስ 14:20
ማበረታቻና ድጋፍ የሚሰጧችሁ ተመልካቾች
9, 10. (ሀ) ጽናት በሚጠይቅ ሩጫ ላይ ተመልካቾች የድጋፍ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉት በምን መንገድ ነው? (ለ) በዕብራውያን 12:1 ላይ የተጠቀሱት ‘እንደ ደመና በዙሪያችን ያሉ ምሥክሮች’ እነማን ናቸው?
9 ይሁን እንጂ አንድ ሯጭ ምንም ያህል ዝግጅት ቢያደርግ በመንገዱ ላይ የሚያደናቅፉ ነገሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። ጳውሎስ “በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ?” ሲል ጠይቋል። (ገላትያ 5:7) አንዳንድ የገላትያ ክርስቲያኖች መጥፎ ወዳጆችን በማበጀታቸው ምክንያት ለሕይወት ከሚያደርጉት ሩጫ ተዘናግተው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የሚሰጡት ማበረታቻና ድጋፍ በሩጫው መጽናትን ቀላል ሊያደርገው ይችላል። ይህ በአንድ የስፖርት ጨዋታ ላይ የተገኙ ተመልካቾች በተካፋዮቹ ላይ ከሚያሳድሩት ተጽእኖ ጋር በጣም ይመሳሰላል። ጠንካራ ስሜት ያላቸው ተመልካቾች ተወዳዳሪዎቹ ከጅምሩ አንስቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ በጋለ ስሜት እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ ተመልካቾቹ የሚያሰሙት ሞቅ ያለ ሙዚቃና ጭብጨባ የተቀላቀለበት ሆታ ተወዳዳሪዎቹ ወደ ፍጻሜው በሚቃረቡበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ኃይል ሊሰጣቸው ይችላል። በእርግጥም በስሜት ድጋፍ የሚሰጡ ተመልካቾች በተወዳዳሪዎቹ ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
10 ክርስቲያኖች ለሕይወት በሚያደርጉት ሩጫ ተመልካቾቹ እነማን ናቸው? ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በቅድመ ክርስትና ዘመን ይኖሩ የነበሩ የታመኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ከዘረዘረ በኋላ “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ . . . በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 12:1) ጳውሎስ ደመናን ምሳሌ አድርጎ ሲጠቅስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል የተወሰነ መጠንና ቅርፅ ያለውን ደመና የሚያመለክተውን ቃል አይደለም። ከዚያ ይልቅ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ በሆኑት በደብልዩ ኢ ቫይን አባባል መሠረት “ሰማያትን የሸፈነውን ቅርጽ አልባ የደመናት ስብስብ የሚያመለክት” ቃል ተጠቅሟል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ በአእምሮው የያዘው እንደ ትልቅ የደመና ክምችት ብዙ ቁጥር ያላቸውን ምሥክሮች ነበር።
11, 12. (ሀ) በቅድመ ክርስትና ዘመን ይኖሩ የነበሩ የታመኑ ምሥክሮች በጽናት እንድንሮጥ ድጋፍ ይሰጡናል የምንለው በምን መንገድ ነው? (ለ) ‘ከታላቁ የምሥክሮች ደመና’ ሙሉ በሙሉ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
11 በቅድመ ክርስትና ዘመን ይኖሩ የነበሩ የታመኑ ምሥክሮች ቃል በቃል ዘመናዊ ተመልካቾች መሆን ይችላሉ? አይችሉም። ሁሉም በሞት አንቀላፍተው ትንሣኤያቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ በሕይወት እያሉ የተሳካላቸው ሯጮች የነበሩ ሲሆን ሕያው ምሳሌነታቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በምናጠናበት ጊዜ እነዚህ የታመኑ ሰዎች በአእምሯችን ውስጥ ሕይወት ሊዘሩና በሩጫው እስከ ፍጻሜው እንድንገፋ ሊያበረታቱን ይችላሉ ብሎ ለመናገር ይቻላል።—ሮሜ 15:4a
12 ለምሳሌ ያህል በዓለም ያሉ ነገሮች በሚያጓጉን ጊዜ ሙሴ የግብጽን ክብር ስለ መተዉ የሚናገረውን ታሪክ መመርመራችን በሩጫው እንድንቀጥል አይገፋፋንምን? በጣም ከባድ መከራ የደረሰብን ሲመስለን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ በተጠየቀ ጊዜ ያጋጠመውን ከባድ ፈተና ማስታወሳችን ለእምነት በምናደርገው ትግል እጃችንን እንዳንሰጥ እንደሚያበረታን የተረጋገጠ ነው። የእነዚህ ምሥክሮች ‘ታላቅ ደመና’ በዚህ መንገድ የሚሰጠን ማበረታቻና ድጋፍ የተመካው በማስተዋል ዓይናችን እነሱን በግልጽ በመመልከታችን ላይ ነው።
13. ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ በጊዜያችን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ማነቃቂያና ድጋፍ የሚሆኑን በምን መንገድ ነው?
13 በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ብዙ ቁጥር ባላቸው የይሖዋ ምሥክሮች መካከል እንገኛለን። ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” ክፍል አባላት የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ግሩም የእምነት ምሳሌዎችን ትተው አልፈዋል! (ራእይ 7:9) በዚህ መጽሔትና በሌሎች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ በየጊዜው የሚወጣውን የሕይወት ታሪካቸውን ማንበብ እንችላለን።b በእምነታቸው ላይ ስናሰላስል እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያስችል ማበረታቻ እናገኛለን። እንዲሁም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ካሉ የቅርብ ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን የምናገኘው ድጋፍ እንዴት አስደናቂ ነው! አዎን፣ ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ማበረታቻና ድጋፍ የሚሰጡን ብዙ ናቸው።
ፍጥነትህን በጥበብ መጥን
14, 15. (ሀ) ፍጥነታችንን በጥበብ መመጠን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ግብ ስናወጣ ምክንያታዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
14 እንደ ማራቶን ባለው የረዥም ርቀት ሩጫ ላይ አንድ ሯጭ ፍጥነቱን በጥበብ መመጠን አለበት። ኒው ዮርክ ራነር የተባለው መጽሔት “ከመነሻው ጀምሮ በከፍተኛ ፍጥነት መሮጥ ጥረትህን መና ሊያስቀረው ይችላል” ብሏል። “በመጨረሻዎቹ ርቀቶች ላይ ከፍተኛ ትግል ለማድረግ አሊያም አቋርጦ ለመውጣት ትገደድ ይሆናል።” አንድ የማራቶን ሯጭ የሚከተለውን ያስታውሳል:- “ለውድድሩ በምንዘጋጅበት ወቅት ትምህርት ይሰጡን ከነበሩት መካከል አንደኛው እንዲህ ሲል በግልጽ አስጠነቀቀን:- ‘ፈጣን ሯጮችን አትከተሉ። የራሳችሁን ፍጥነት ጠብቃችሁ ሩጡ። ካለበለዚያ ትዝሉና አቋርጣችሁ ለመውጣት ትገደዱ ይሆናል።’ ይህን ምክር መከተሌ ሩጫውን ለመጨረስ ረድቶኛል።”
15 ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ የአምላክ አገልጋዮች ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው። (ሉቃስ 13:24) ይሁን እንጂ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ላይኛይቱ ጥበብ . . . ምክንያታዊ . . . ናት” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 3:17NW) የሌሎች መልካም ምሳሌነት የበለጠ እንድናደርግ ሊያበረታታን ቢችልም ምክንያታዊነት ከችሎታችንና ከሁኔታችን ጋር የሚጣጣሙ ተጨባጭ ግቦችን ለማውጣት ሊረዳን ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚከተለው በማለት ያሳስቡናል:- “ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።”—ገላትያ 6:4, 5
16. ቦታን መጠበቅ ፍጥነታችንን ለመመጠን የሚረዳን እንዴት ነው?
16 በሚክያስ 6:8 ላይ የሚከተለውን በጥልቀት እንድናስብ የሚያደርግ ጥያቄ ተጠይቀናል:- “እግዚአብሔርም ከአንተ የሚሻው ምንድር ነው? . . . ከአምላክህም ጋር በትሕትና [“ቦታህን ጠብቀህ፣” NW] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ቦታን መጠበቅ ያለብንን የአቅም ገደብ መገንዘብን ይጨምራል። የጤና መታወክ ወይም የእድሜ መግፋት ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በተወሰነ ደረጃ ገድበውት ይሆን? ተስፋ አንቁረጥ። ይሖዋ ‘በሌለን መጠን ሳይሆን ባለን መጠን’ የምናደርገውን ጥረትና የምናቀርበውን መሥዋዕት ይቀበላል።—2 ቆሮንቶስ 8:12፤ ከሉቃስ 21:1-4 ጋር አወዳድር።
ዓይንህን በሽልማቱ ላይ አድርግ
17, 18. ኢየሱስ የመከራውን እንጨት በጽናት ለመቋቋም የረዳው ምንን አሻግሮ መመልከቱ ነበር?
17 ጳውሎስ ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ የመጽናትን አስፈላጊነት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲገልጽ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ሌላ የኢስሚየን የስፖርት ጨዋታ ገጽታ ጠቅሷል። በእነዚህ ጨዋታዎች የሚወዳደሩትን አስመልክቶ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ [ይሮጣሉ]፣ እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፣ ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም።” (1 ቆሮንቶስ 9:25, 26) በእነዚህ ጥንታዊ የስፖርት ጨዋታዎች የአሸናፊው ሽልማት አክሊል ወይም ከጥድ ወይም ከሌሎች ተክሎችና ከደረቅ የሾርባ ቅጠል ሳይቀር የተሠራ የአበባ ጉንጉን ስለነበር በእርግጥም “የሚጠፋ አክሊል” ነበር። ይሁንና እስከ መጨረሻው የሚጸኑ ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸው ነገር ምንድን ነው?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመጥቀስ “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 12:2) ኢየሱስ ከመከራው እንጨት አሻግሮ ሽልማቱን በመመልከቱ እስከ ሰብዓዊ ሕይወቱ ማብቂያ ሊጸና ችሏል። ሽልማቱ ደግሞ የይሖዋ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ ማድረጉ፣ ሰብዓዊውን ቤተሰብ ከሞት መቤዠቱና ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኖ በመግዛት ታዛዥ የሰው ልጆችን ገነት በሆነች ምድር ላይ ማብቂያ የሌለው ሕይወት እንዲያገኙ ማድረጉ የሚሰጠው ደስታ ይገኝበታል።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ 20:28፤ ዕብራውያን 7:23-26
19. በክርስቲያን ደቀ መዝሙርነት ጎዳና መመላለሳችንን ስንቀጥል ትኩረታችን በምን ላይ ሊያርፍ ይገባል?
19 በክርስቲያን የደቀ መዝሙርነት ጎዳና መመላለሳችንን በመቀጠል ወደፊት ስለሚጠብቀን ደስታ አስብ። ይሖዋ የአምላክ መንግሥት ምሥራች መስበክንና ሕይወት አድን የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለሌሎች ማካፈልን የመሰለ ጥልቅ እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ስለ እውነተኛው አምላክ የማወቅ ፍላጎት ያለው ሰው ማግኘትና ይህ ሰው ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ውስጥ እንዲገባ መርዳት እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው! እንዲሁም የምንሰብክላቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ምላሽ ቢሰጡ ከይሖዋ ስም መቀደስ ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ መሥራቱ ራሱ መብት ነው። በምንመሠክርበት ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ግዴለሾች ወይም ተቃዋሚዎች ቢሆኑም በአገልግሎታችን ከጸናን የይሖዋን ልብ በማስደሰታችን እርካታ እናገኛለን። (ምሳሌ 27:11) እንዲሁም የዘላለም ሕይወትን የመሰለ ታላቅ ሽልማት እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! እነዚህን በረከቶች አሻግረን በመመልከት በሩጫው መቀጠል ያስፈልገናል።
መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ
20. ለሕይወት የሚደረገው ሩጫ ወደ መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆነው እንዴት ሊሆን ይችላል?
20 ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ከቀንደኛው ጠላታችን ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር መታገል አለብን። ወደ መጨረሻው እየተቃረብን ስንመጣ ከሩጫው ተደናቅፈን እንድንወጣ ወይም ፍጥነታችንን እንድንቀንስ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። (ራእይ 12:12, 17) ጦርነት፣ ረሃብ፣ ወረርሽኝና ይህን ‘የፍጻሜ ዘመን’ ለይተው የሚያሳውቁ ሌሎች ችግሮች እያሉ ራስን የወሰኑ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆኖ በታማኝነት መቀጠል ቀላል አይደለም። (ዳንኤል 12:4፤ ማቴዎስ 24:3-14፤ ሉቃስ 21:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ከዚህም በላይ ሩጫውን የጀመርነው ከአሥርተ ዓመታት በፊት ከሆነ አንዳንድ ጊዜ መጨረሻው እኛ ከምናስበው ይበልጥ የራቀ ሊመስለን ይችላል። ይሁንና መጨረሻው እንደሚመጣ የአምላክ ቃል ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ ቀኑ አይዘገይም ብሏል። መጨረሻው እጅግ ቀርቧል።—ዕንባቆም 2:3፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 10
21. (ሀ) ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ለመቀጠል ምን ሊያጠነክረን ይችላል? (ለ) መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ማድረግ መሆን አለበት?
21 እንግዲያው ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ስኬታማ እንድንሆን ከፈለግን ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ነገሮች ለመመገብ ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት በመጠቀም ጥንካሬ ለማግኘት መጣር አለብን። በተጨማሪም በዚህ ሩጫ ተካፋዮች ከሆኑት የእምነት አጋሮቻችን ጋር አዘውትረን ከመሰብሰብ የምናገኘው ማበረታቻም በእጅጉ ያስፈልገናል። በመንገዳችን ላይ የሚገጥሙን ከባድ መከራዎችና ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች ሩጫችንን ይበልጥ አስቸጋሪ ቢያደርጉብን እንኳ ይሖዋ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ስለሚሰጠን እስከ ፍጻሜው ልንጸና እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 4:7 NW) ይሖዋ ሩጫችንን በአሸናፊነት እንድንደመድም የሚፈልግ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ‘ባንዝል በጊዜው እንደምናጭድ’ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ‘በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት ለመሮጥ’ ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።—ዕብራውያን 12:1፤ ገላትያ 6:9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስለ ዕብራውያን 11:1-12:3 ማብራሪያ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 2-108 ከገጽ 1-8ን ተመልከት።
b እነዚህን የመሰሉ አበረታች ተሞክሮዎች ከሚገኙባቸው በቅርብ ጊዜ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:- ሰኔ 1, 1998 ገጽ 28-31፤ መስከረም 1, 1998 ገጽ 24-8፤ የካቲት 1, 1999 ገጽ 25-9
ታስታውሳለህ?
◻ እስከ መጨረሻው መጽናት ያለብን ለምንድን ነው?
◻ የትኞቹን የይሖዋ ዝግጅቶች ችላ ማለት አይገባንም?
◻ ፍጥነታችንን በጥበብ መመጠን ያለብን ለምንድን ነው?
◻ በሩጫው ከገፋን ወደፊት ምን ደስታ ይጠብቀናል?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ማበረታቻ አግኝ