ዓለምን በእርግጥ መለወጥ የሚችል ይኖር ይሆን?
“ድሆች ከምንም ነገር በላይ ሰላምና ደኅንነት፣ ከዚያ ደግሞ ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሏቸው አጋጣሚዎች ማግኘት እንደሚፈልጉ ይነግሩናል። የበለጸጉ አገሮችና የሀብታም ኩባንያዎች ተጽዕኖ ልፋታቸውን መና እንዳያስቀረው ፍትሕ የሚንጸባረቅበት ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ይፈልጋሉ።”
አንዲት የዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት ዳይሬክተር በድህነት ተቆራምደው የሚኖሩ ሰዎችን ተስፋና ምኞት የገለጹት በዚህ መንገድ ነው። እንዲያውም እርሳቸው የተናገሯቸው ቃላት በዓለማችን ላይ የሚደርሱ አሳዛኝ ክስተቶችና ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ሰለባ የሚሆኑ ሰዎችን ስሜት በደንብ አድርገው የሚገልጹ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሙሉ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት የሰፈነበትን ዓለም ይናፍቃሉ። እንዲህ ያለው ዓለም እውን የሚሆንበት ጊዜ ይኖር ይሆን? ፍትሕ የተዛባበትን ዓለም ለመለወጥ በእርግጥ ኃይልና ችሎታ ያለው አካል ይኖር ይሆን?
ለውጥ ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶች
ብዙ ሰዎች ለውጥ ለማምጣት ጥረዋል። ለምሳሌ በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረች ፍሎረንስ ናይቲንጌል የምትባል አንዲት እንግሊዛዊት ሕመምተኞች ንጽሕናው የተጠበቀና ርኅራኄ የታከለበት እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ መላ ሕይወቷን ሰጥታለች። የጀርም መግደያ መድኃኒቶችና አንቲባዮቲኮች ባልተፈለሰፉበት በዚያ ዘመን በሆስፒታል ለሕመምተኞች የሚሰጠው እንክብካቤ እንደዛሬው ጥራቱን የጠበቀ አልነበረም። አንድ መጽሐፍ “ነርሶች ያልተማሩ፣ ንጽሕና የጎደላቸው እንዲሁም በስካርና በሥነ ምግባር ብልግና የታወቁ” እንደነበሩ ተናግሯል። ፍሎረንስ ናይቲንጌል የነርስነትን ሙያ ለመለወጥ ያደረገችው ጥረት ተሳክቶላት ይሆን? አዎን ተሳክቶላታል። በተመሳሳይም ራስ ወዳድነት የሌለባቸውና አሳቢ የሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በተለያዩ መስኮች ለምሳሌ ያህል መሃይምነትን በማጥፋት፣ ትምህርትንና ሕክምናን ለብዙዎች በማዳረስ፣ የመኖሪያ ቤት ችግሮችን በማቃለል እንዲሁም በምግብ አቅርቦት ረገድ ስኬታማ ተግባር አከናውነዋል። ከዚህም የተነሳ በችግር ተቆራምደው ይኖሩ የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኑሯቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊሻሻል ችሏል።
ይሁንና ይህንን እውነታ መዘንጋት አንችልም:- ዛሬም ቢሆን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች በጦርነት፣ በወንጀል፣ በበሽታ፣ በድርቅና በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ እየተሠቃዩ ይኖራሉ። አንድ አየርላንዳዊ የእርዳታ ድርጅት ወኪል “ድህነት በየቀኑ 30,000 ሰዎችን በሞት ይቀጥፋል” ብለዋል። ሌላው ቀርቶ ባለፉት ዘመናት በርካታ የለውጥ አራማጆች ለማጥፋት የታገሉት የባሪያ ንግድ እንኳ በዛሬውም ጊዜ ይገኛል። ዲስፖዘብል ፒፕል—ኒው ስሌቨሪ ኢን ዘ ግሎባል ኢኮኖሚ “በዛሬው ጊዜ ያለው የባሪያዎች ቁጥር በባሪያ ንግድ ዘመን ከአፍሪካ በድብቅ ተወስደው ከአትላንቲክ ባሻገር ከተሸጡት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል” ብሏል።
ሰዎች ፍጹምና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያጨናግፍባቸው ምንድን ነው? ሀብታሞችና ኃያላን የሚያሳድሩት ከፍተኛ ተጽዕኖ ብቻ ነው? ወይስ ከዚህም የበለጠ ነገር ይኖራል?
ለለውጥ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች
የአምላክ ቃል እውነተኛ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት በዋነኝነት የሚያደናቅፈው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደሆነ’ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 5:19) እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ሰይጣን ‘ዓለምን ሁሉ እያሳተ’ ነው። (ራእይ 12:9) የሰይጣን ክፉ ተጽዕኖ እስኪወገድ ድረስ በክፋትና በፍትሕ መዛባት የሚጠቁ ሰዎች ይኖራሉ። ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ያስከተለው ነገር ምንድን ነው?
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ለመላው የሰው ልጅ ቤተሰብ መኖሪያ የሚሆን እንከን የማይወጣለት ገነት ማለትም “እጅግ መልካም” የሆነ ዓለም ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) ታዲያ ሁኔታው እንዲቀየር ያደረገው ምንድን ነው? ሰይጣን ነው። የሰው ልጆች ሊመሩበት የሚገባውን ሕግ በማውጣት ረገድ አምላክ ያለውን መብት ሰይጣን ተገዳድሯል። ሰይጣን የአምላክ አገዛዝ ፍትሕ ይጎድለዋል ባይ ነው። አዳምና ሔዋን ምን ነገር መልካም፣ ምን ነገር ደግሞ ክፉ እንደሆነ ራሳቸው ለመወሰን የሚያስችላቸውን የነጻነት ጎዳና እንዲከተሉ አግባባቸው። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይህ ደግሞ ሰዎች ፍትሕ የሞላበት ዓለም ለማምጣት ለሚያደርጉት ጥረት ሁለተኛ እንቅፋት የሆነውን ኃጢአትና አለፍጽምናን አስከትሏል።—ሮሜ 5:12
አምላክ ይህን የፈቀደው ለምንድን ነው?
አንዳንዶች ‘አምላክ ኃጢአትና አለፍጽምና እንዲኖር ለምን ፈቀደ? ዓመጸኞቹን አስወግዶ ሁሉን ነገር እንደ አዲስ ለመጀመር ገደብ የለሽ ኃይሉን ያልተጠቀመው ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቁ ይሆናል። እንደዚያ ማድረጉ በቀላሉ መፍትሄ የሚያስገኝ ይመስላል። ይሁን እንጂ የኃይል አጠቃቀም ከባድ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል። በዓለም ላይ ያሉ የተጨቆኑና በድህነት የሚማቅቁ ሰዎችን ቅር የሚያሰኛቸው አንዱና ዋነኛው ነገር ኃይልን ያላግባብ መጠቀም አይደለም? አንድ አምባገነን መሪ እርሱ ያወጣቸውን ደንቦች የማይታዘዝን ማንኛውንም ሰው ለማጥፋት ኃይል ሲጠቀም ቅን ልብ ባላቸው አእምሮ ውስጥ ጥያቄ አይፈጠርም?
አምላክ ኃይሉን ያላግባብ የሚጠቀም አምባገነን ገዥ አለመሆኑን ቅን ልቦና ላላቸው ፍጡሮቹ ለማሳየት ሲል ሰይጣንና ዓመጸኞቹ ሰዎች ከመለኮታዊ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ውጪ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። ጊዜ መፈቀዱ ትክክለኛው መንገድ የአምላክ አገዛዝ ብቻ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። እንዲሁም አምላክ ማንኛውንም ገደብ የሚጥልብን ለራሳችን ጥቅም መሆኑ እንዲታይ ያደርጋል። እንዲያውም ሰዎች በአምላክ ትእዛዝ ላይ ማመጻቸው ያስከተለው አሳዛኝ ውጤት የዚህን እውነታ አረጋግጧል። እነዚህ አሳዛኝ ውጤቶች አምላክ ክፉዎችን ለማጥፋት በሚፈልግበት ጊዜ ታላቅ ኃይሉን ለመጠቀም በቂ ምክንያት እንዳለው ያረጋግጣሉ። ይህም የሚሆንበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው።—ዘፍጥረት 18:23-32፤ ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 37:9, 10, 38
አምላክ እርምጃ የሚወስድበት ይህ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ፍትሕ በተዛባበት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ‘በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ መቃተታችን’ የግድ ነው። (ሮሜ 8:22) አንዳንድ ነገሮችን ለመለወጥ ምንም ያህል ብንጥር ሰይጣንን ማጥፋትም ሆነ ለዓለም ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የሆነውን አለፍጽምናን ማስወገድ አንችልም። በቀላል አነጋገር ከአዳም የወረስናቸውን የኃጢአት ውጤቶች ማስተካከል ከአቅማችን በላይ ነው።—መዝሙር 49:7-9
ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላቂ ለውጥ ያመጣል
ይህ ሲባል ታዲያ ሁኔታው ፈጽሞ ተስፋ ቢስ ነው ማለት ነው? በፍጹም አይደለም። ሟች ከሆነው የሰው ልጅ እጅግ የሚልቅ ኃይል ያለው አንድ አካል ዘላቂ ለውጥ የማምጣት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ይህ አካል ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳንን የሚያስገኝ ራስ ተደርጎ በአምላክ መሾሙን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 5:31
በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ እርምጃ ለመውሰድ አምላክ የቀጠረውን “ዘመን” እየተጠባበቀ ይገኛል። (ራእይ 11:18) በእርግጥ ኢየሱስ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? ‘እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደተናገረው ሁሉ ነገር የሚታደስበትን’ ዘመን ያመጣል። (የሐዋርያት ሥራ 3:21) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። . . . ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል።” (መዝሙር 72:12-16) አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ‘ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር እንደሚያስወግድ’ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 46:9) በተጨማሪም በጸዳችው ምድር ተቀምጦ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል” እንደማይኖር ተስፋ ሰጥቷል። ማየት ወይም መስማት የተሳናቸው እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች በሌላ አነጋገር በሕመምና በበሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ ፍጹም ጤንነት ያገኛሉ። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6፤ ራእይ 21:3, 4) ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የሞቱ ሰዎች እንኳ ተጠቃሚ ናቸው። ኢየሱስ የፍትሕ መዛባትም ሆነ የጭቆና ሰለባ የነበሩ ሰዎችን እንደገና ሕያው እንደሚያደርጋቸው ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያመጣው ለውጥ ያልተሟላና ጊዜያዊ አይደለም። ፍትሕ የሞላበት እውነተኛ ዓለም እንዳይኖር የሚያደርጉ እንቅፋቶችን በሙሉ ያስወግዳል። ኃጢአትንና አለፍጽምናን የሚያስወግድ ከመሆኑም በላይ ሰይጣን ዲያብሎስንም ሆነ የእርሱን የዓመጽ አካሄድ የሚከተሉትን በሙሉ ይደመስሳል። (ራእይ 19:19, 20፤ 20:1-3, 10) አምላክ ለጊዜው እንዲኖር የፈቀደው ጭንቀትና መከራም “ዳግመኛ አይነሣም።” (ናሆም 1:9) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት “ትምጣ” እንዲሁም ፈቃዱ “በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ ሲያስተምረን በናሆም መጽሐፍ ላይ ያለውን ሐሳብ በአእምሮው ሳይዝ አልቀረም።—ማቴዎስ 6:10
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ ‘ድሆች ምንጊዜም ከእኛ ጋር እንደሚሆኑ’ ተናግሮ የለም? እንዲህ ማለቱ መድልዎና ድህነት ሁልጊዜ እንደሚኖሩ አያሳይም? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። (ማቴዎስ 26:11) አዎን፣ ኢየሱስ ድሆች ምንጊዜም እንደሚኖሩ ተናግሮ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት መንፈስ የአምላክ ቃል ከሰጣቸው ተስፋዎች ጋር ስናወዳድረው ይህ ሥርዓት እስካለ ድረስ ድሆች ሁልጊዜ ይኖራሉ ማለቱ እንደነበረ እንረዳለን። ኢየሱስ በዓለም ላይ ያለውን ድህነትና መድልዎ ማስወገድ የሚችል ማንም ሰው እንደማይኖር ያውቃል። በተጨማሪም እርሱ ይህን ሁሉ መለወጥ እንደሚችል ያውቃል። በቅርቡ ሕመም፣ በሽታ፣ ድህነትና ሞት ፈጽሞ የማይኖሩበትን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ማለትም ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ሥርዓት ያመጣል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1
‘መልካም ማድረግን አትርሱ’
እንደዚህ ሲባል ሰዎችን ለመርዳት የቻልነውን ያህል መጣራችን ምንም ዋጋ አይኖረውም ማለት ነው? በፍጹም አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ችግርና አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው እንድንረዳቸው ያበረታታናል። በድሮ ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰሎሞን “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 3:27) ሐዋርያው ጳውሎስም “መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ” በማለት መክሮናል።—ዕብራውያን 13:16
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሌሎችን ለመርዳት የቻልነውን ያህል እንድናደርግ አበረታቶናል። ኢየሱስ ስለ አንድ ሳምራዊ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ይህ ሳምራዊ በመንገድ ላይ ሲያልፍ፣ ተደብድቦ የተዘረፈ አንድ ሰው አጋጠመው። ኢየሱስ እንደተናገረው ሳምራዊው ለተደበደበው ሰው ‘ከማዘኑ’ የተነሳ በራሱ ወጪ የሰውየውን ቁስል በማሰርና ከደረሰበትም ጉዳት የሚያገግምበትን ዝግጅት በማድረግ ረድቶታል። (ሉቃስ 10:29-37) ይህ ርኅሩኅ ሳምራዊ ዓለምን አልለወጠም፤ ይሁን እንጂ የአንድን ሰው ሕይወት በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።
ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ግለሰቦችን ከመርዳት ያለፈ ነገር ያደርጋል። በእርግጥም ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችል ሲሆን በቅርቡም ይህን ይፈጽማል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በጊዜያችን ባሉት ኢፍትሐዊ ሁኔታዎች የተጨቆኑ ሰዎች ሕይወታቸው የሚሻሻል ከመሆኑም በላይ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ያገኛሉ።—መዝሙር 4:8፤ 37:10, 11
ይህ የሚሆንበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ፍትሕ በተዛባበት በዚህ ዓለም ውስጥ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ‘በጎ ነገር በማድረግ’ በመንፈሳዊም ሆነ በቁሳዊ እነርሱን ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አንበል።—ገላትያ 6:10
[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል5]
ፍሎረንስ ናይቲንጌል በነርስነት ሙያ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥታለች
[ምንጭ]
Courtesy National Library of Medicine
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቶስ ተከታዮች ለሌሎች መልካም ያደርጋሉ
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
The Star, Johannesburg, S.A.