ወደ አምላክ ዕረፍት ገብታችኋልን?
“ወደ ዕረፍቱ የገባ፣ . . . እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።”—ዕብራውያን 4:10
1. ዕረፍት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ዕረፍት። እንዴት ያለ ተስማሚና የሚያስደስት ቃል ነው! ሩጫና ጥድፊያ በሞላበት በዛሬው ዓለም ውስጥ ስንኖር ጥቂት ዕረፍት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሁላችንም እንስማማለን። ወጣት እንሁን ሽማግሌ፣ ያገባን እንሁን ነጠላ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሚያጋጥሙን ነገሮች ብቻ እንኳን በጣም ተወጥረን ልንደክም እንችላለን። አካላዊ ገደብ ወይም እክል ላለባቸው ደግሞ እያንዳንዱ ቀን ትግል የሚጠይቅ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚሉት “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ [ኖሯል]።” (ሮሜ 8:22) አንድ ሰው ዕረፍት ስላደረገ ብቻ ሰነፍ ነው ማለት አይቻልም። ለሰው ልጅ ሊሟሉ ከሚገባቸው አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱ ዕረፍት ነው።
2. ይሖዋ ያረፈው ከመቼ ጀምሮ ነው?
2 ይሖዋ አምላክ ራሱ በዕረፍት ላይ ይገኛል። በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።” ይሖዋ ‘ለሰባተኛው ቀን’ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፤ ምክንያቱም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ በመቀጠል “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም” ይላል።—ዘፍጥረት 2:1-3
አምላክ ከሥራው ዐረፈ
3. አምላክ ያረፈው በየትኛው ምክንያት ሊሆን አይችልም?
3 አምላክ “በሰባተኛው ቀን” ያረፈው ለምን ነበር? ስለ ደከመው እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ ‘ታላቅ ኃይል’ አለው፤ “አይደክምም፣ አይታክትም።” (ኢሳይያስ 40:26, 28) አምላክ ያረፈው ፋታ ለማግኘት ወይም ፍጥነቱን ረገብ ለማድረግ ስለፈለገ አይደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” በማለት ይነግረናል። (ዮሐንስ 5:17) በዚያም ሆነ በዚህ ‘አምላክ መንፈስ’ ስለሆነ ሥጋዊ ፍጥረታት ያላቸው ዓይነት አካላዊ ዑደት የሌለው ከመሆኑም በላይ እነርሱ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች አያስፈልጉትም።—ዮሐንስ 4:24
4. ‘ሰባተኛው ቀን’ ቀደም ሲል ከነበሩት ስድስት ‘ቀናት’ የሚለየው በምን መንገድ ነው?
4 አምላክ “በሰባተኛው ቀን” ያረፈበትን ምክንያት እንድናስተውል ምን ሊረዳን ይችላል? አምላክ ቀደም ባሉትና ረጃጅም ጊዜ በወሰዱት ስድስት የፍጥረት ‘ቀናት’ ባከናወነው ሥራ የተደሰተ ቢሆንም በተለይ ግን ሰባተኛውን ቀን ባርኮታል፤ ‘የተቀደሰ’ ብሎም ጠርቶታል። ከንሳይስ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ “የተቀደሰ” የሚለውን ቃል “(ለአንድ አምላክ ወይም ለአንድ ሃይማኖታዊ ዓላማ) ሙሉ በሙሉ የተወሰነ ወይም የተገባ” በማለት ተርጉሞታል። ስለዚህ ይሖዋ ‘ሰባተኛውን ቀን’ መባረኩና የተቀደሰ ብሎ መጥራቱ ሰባተኛው ቀንና ‘ዕረፍቱ’ እሱ ከሚያስፈልገው ነገር ጋር ሳይሆን ከቅዱስ ፈቃዱና ዓላማው ጋር ዝምድና ያላቸው መሆኑን ያመለክታል። ይህ ዝምድና ምንድን ነው?
5. አምላክ በመጀመሪያዎቹ ስድስት የፍጥረት ‘ቀናት’ ውስጥ ምን ነገሮች ሥራቸውን እንዲጀምሩ አድርጓል?
5 አምላክ ቀደም ሲል በነበሩት ስድስት የፍጥረት ‘ቀናት’ ውስጥ ምድርና በዙሪያዋ ያሉ ነገሮች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩትን ዑደቶችና ሕጎች በማዘጋጀት ሥራቸውን እንዲጀምሩ አድርጓል። ሳይንቲስቶች እነዚህ ነገሮች በሚያስደንቅ አኳኋን የተነደፉ መሆናቸውን እየተገነዘቡ መጥተዋል። ‘በስድስተኛው ቀን’ ማብቂያ ላይ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ጥንድ በመፍጠር “በምሥራቅ በዔደን ገነት” አኖራቸው። በመጨረሻም አምላክ ለሰብዓዊው ቤተሰብና ለምድር ያለውን ዓላማ በሚከተሉት ትንቢታዊ ቃላት ተናገረ:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።”—ዘፍጥረት 1:28, 31፤ 2:8
6. (ሀ) አምላክ ‘በስድስተኛው ቀን’ ማብቂያ ላይ ስለ ፍጥረት ሥራው ምን ተሰምቶት ነበር? (ለ) ‘ሰባተኛው ቀን’ የተቀደሰ የሆነው በምን መንገድ ነው?
6 ‘ስድስተኛው የፍጥረት ቀን’ ሲያበቃ ዘገባው “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ይለናል። (ዘፍጥረት 1:31) አምላክ በሠራው ነገር ሁሉ ረክቶ ነበር። ስለዚህ በምድር ላይ ያከናውን ከነበረው የፍጥረት ሥራ አረፈ ወይም መፍጠሩን አቆመ። ገነታዊው የአትክልት ሥፍራ ፍጹምና ውብ ቢሆንም የሸፈነው ቦታ በጣም አነስተኛ ነበር። በተጨማሪም በምድር ላይ የነበሩት ሰብዓዊ ፍጡራን ሁለት ብቻ ነበሩ። ምድርም ሆነች ሰብዓዊው ቤተሰብ አምላክ ወዳለመው ደረጃ ለመድረስ ጊዜ ይወስድባቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ቀደም ሲል በነበሩት ስድስት የፍጥረት ‘ቀናት’ ውስጥ የፈጠራቸው ነገሮች ከቅዱስ ፈቃዱ ጋር ተስማምተው እንዲስፋፉ ‘ሰባተኛ ቀን’ መደበ። (ከኤፌሶን 1:11 ጋር አወዳድር።) ‘ሰባተኛው ቀን’ ሲደመደም ምድር ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ ለዘላለም የሚኖርባት ዓለም አቀፋዊ ገነት ትሆን ነበር። (ኢሳይያስ 45:18) ‘ሰባተኛው ቀን’ አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድ ተግባራዊ ለማድረግ ወይም ወደ ፍጻሜ ለማምጣት የተለየ ወይም የተወሰነ ነው። “የተቀደሰ” የሆነው በዚህ መንገድ ነው።
7. (ሀ) አምላክ “በሰባተኛው ቀን” ያረፈው በምን ረገድ ነው? (ለ) ‘ሰባተኛው ቀን’ በሚፈጸምበት ጊዜ ሁሉም ነገር ምን መልክ ይኖረዋል?
7 ስለዚህ አምላክ ከፍጥረት ሥራው “በሰባተኛው ቀን” አረፈ። አምላክ ሥራቸውን ያስጀመራቸው ነገሮች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ የተዋቸው ያህል ነበር። “በሰባተኛው ቀን” ማብቂያ ላይ ሁሉም ነገር አስቀድሞ ካወጣው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚፈጸም ሙሉ ትምክህት ነበረው። እንቅፋቶች ሊኖሩ ቢችሉም ይወገዱ ነበር። የአምላክ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እውን ሲሆን ታዛዥ የሰው ልጆች በሙሉ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ይህ እንዳይሆን ምንም የሚከለክለው ነገር አይኖርም፤ ምክንያቱም አምላክ ‘ሰባተኛውን ቀን’ ባርኮታል እንዲሁም ‘ቀድሶታል።’ ለታዛዥ የሰው ልጆች እንዴት ያለ ክብራማ ተስፋ ነው!
እስራኤላውያን ወደ አምላክ ዕረፍት አልገቡም
8. እስራኤላውያን ሰንበትን ማክበር የጀመሩት መቼና እንዴት ነበር?
8 የእስራኤል ብሔር ይሖዋ ለሥራና ለዕረፍት ካወጣው ዝግጅት ተጠቅሟል። አምላክ ለእስራኤላውያን በሲና ተራራ ላይ ሕጉን ከመስጠቱ በፊት እንኳን ሳይቀር በሙሴ በኩል እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፣ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ።” ስለዚህ “[ሕዝቡ] በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።”—ዘጸአት 16:22-30
9. የሰንበት ሕግ ለእስራኤላውያን ያለ ጥርጥር አስደሳች ለውጥ የነበረው ለምንድን ነው?
9 ይህ ዝግጅት ከጥቂት ጊዜ በፊት ከግብጽ ባርነት ነፃ ለወጡት እስራኤላውያን አዲስ ነበር። ግብጻውያንም ሆኑ ሌሎች ብሔራት ዘመናትን የሚያሰሉት ከአምስት እስከ አሥር የሚያክሉ ቀናትን በአንድ ላይ በመቁጠር ቢሆንም በባርነት ሥር ይገኙ የነበሩት እስራኤላውያን የዕረፍት ቀን ያገኙ ነበር ለማለት አዳጋች ነው። (ከዘጸአት 5:1-9 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ይህንን ለውጥ በደስታ ተቀብሎታል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። የሰንበትን ሕግ እንደ ሸክም ወይም ገደብ ከመቁጠር ይልቅ ሕጉን በመጠበቅ መደሰት ነበረባቸው። እንዲያውም አምላክ ከጊዜ በኋላ እንደነገራቸው ከሆነ ሰንበትን የሰጣቸው በግብጽ በባርነት ያሳለፉትን ጊዜ እንዲያስቡና ከዚያ እንዴት እንዳወጣቸው እንዲያስታውሱ ነበር።—ዘዳግም 5:15
10, 11. (ሀ) እስራኤላውያን ታዛዦች ቢሆኑ ኖሮ ምን ለማግኘት ሊጠባበቁ ይችሉ ነበር? (ለ) እስራኤላውያን ወደ አምላክ ዕረፍት ያልገቡት ለምን ነበር?
10 ከሙሴ ጋር ከግብጽ የወጡት እስራኤላውያን ታዛዦች ቢሆኑ ኖሮ “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር” ማለትም ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብት ይኖራቸው ነበር። (ዘጸአት 3:8) በዚያም ሆነው በሰንበት ቀን ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ እውነተኛ ዕረፍት ሊያገኙ ይችሉ ነበር። (ዘዳግም 12:9, 10) ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ አልሆነም። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እነሱ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብፅ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ ዓመትም የተቈጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፣ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።”—ዕብራውያን 3:16-19
11 ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ትልቅ ትምህርት ነው! ያ ትውልድ በይሖዋ ላይ የነበረውን እምነት በማጣቱ ቃል የተገባለትን ዕረፍት ሳያገኝ ቀረ። ከዚያ ይልቅ በምድረ በዳ አለቀ። የአብርሃም ዘሮች እንደመሆናቸው መጠን ለምድር አሕዛብ ሁሉ በረከት በማምጣት ረገድ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የተሳሰረ ሚና እንደነበራቸው መገንዘብ ተሳናቸው። (ዘፍጥረት 17:7, 8፤ 22:18) ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር ተስማምተው ከመሥራት ይልቅ በዓለማዊና በራስ ወዳድ ምኞቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ተዋጡ። እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ ፈጽሞ መከተል የለብንም።—1 ቆሮንቶስ 10:6, 10
ገና የቀረ ዕረፍት አለ
12. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ምን ተስፋ ቀርቶላቸው ነበር? እንዴትስ ሊያገኙት ይችሉ ነበር?
12 ጳውሎስ እስራኤላውያን በእምነት ማጣት ምክንያት ወደ አምላክ ዕረፍት እንዳልገቡ ከተናገረ በኋላ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ እምነት አጋሮቹ አዙሯል። በዕብራውያን 4:1-5 ላይ በተገለጸው መሠረት ጳውሎስ “ወደ ዕረፍቱ [ወደ አምላክ ዕረፍት] ለመግባት ተስፋ ገና [ቀርቶልናል]” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ‘በምስራቹ’ እንዲያምኑ አሳስቧቸዋል፤ ምክንያቱም “እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን።” በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ሕጉ የተወገደ በመሆኑ ጳውሎስ እዚህ ላይ እየገለጸ ያለው በሰንበት ቀን ስለሚኖረው አካላዊ ዕረፍት አልነበረም። (ቆላስይስ 2:13, 14) ጳውሎስ ዘፍጥረት 2:2ንና መዝሙር 95:11ን በመጥቀስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ አምላክ ዕረፍት እንዲገቡ ማሳሰቡ ነበር።
13. ጳውሎስ መዝሙር 95ን በመጥቀስ “ዛሬ” በሚለው ቃል ላይ ትኩረት ያደረገው ለምን ነበር?
13 የጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰንበት ዕረፍት “የምስራች” ሆኖላቸው እንደነበር ሁሉ ዕብራውያን ክርስቲያኖችም ወደ አምላክ ዕረፍት ለመግባት እንደሚቻል ማወቃቸው “የምስራች” ሆኖላቸው እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። በመሆኑም ጳውሎስ እስራኤላውያን በምድረ በዳ የሠሩትን ዓይነት ስህተት እነሱም እንዳይሠሩ የእምነት አጋሮቹን አሳስቧቸዋል። አምላክ ከፍጥረት ሥራው ያረፈው ከብዙ ጊዜ በፊት ቢሆንም ጳውሎስ መዝሙር 95:7, 8ን በመጥቀስ “ዛሬ” በሚለው ቃል ላይ ትኩረት አድርጓል። (ዕብራውያን 4:6, 7) ጳውሎስ ለማጉላት የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም የለየው ‘ሰባተኛ ቀን’ ገና አላበቃም። ስለዚህ ክርስቲያን መሰሎቹ የስስት ጥቅሞችን ከማሳደድ ይልቅ ከዚያ ዓላማ ጋር ተስማምተው መሥራታቸው አጣዳፊ ነበር። ጳውሎስ በድጋሚ “ልባችሁን እልከኛ [“ደንዳና፣” NW] አታድርጉ” ሲል አስጠንቅቋቸዋል።
14. ጳውሎስ ገና የቀረ የአምላክ “ዕረፍት” እንዳለ ያሳየው እንዴት ነበር?
14 በተጨማሪም ጳውሎስ ቃል የተገባው “ዕረፍት” በኢያሱ መሪነት በተስፋይቱ ምድር ላይ መስፈር ማለት ብቻ አለመሆኑን ገልጿል። (ኢያሱ 21:44) ጳውሎስ “ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፣ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር” የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርቧል። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ጳውሎስ “የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል” ሲል አክሎ ተናግሯል። (ዕብራውያን 4:8, 9) ይህ “የሰንበት ዕረፍት” ምንድን ነው?
ወደ አምላክ ዕረፍት ግቡ
15, 16. (ሀ) “የሰንበት ዕረፍት” የሚለው ሐረግ ምን ትርጉም ያዘለ ነው? (ለ) ‘ከራስ ሥራ ማረፍ’ ማለት ምን ማለት ነው?
15 “የሰንበት ዕረፍት” የሚለው ሐረግ “ማሰንበት” (በእንግሊዝኛ ሳበዚንግ) የሚል ትርጉም ካለው ግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) ፕሮፌሰር ዊልያም ሌን እንዲህ ብለዋል:- “ቃሉ አሁን ያለውን ትንሽ ለየት ያለ ትርጉም ያገኘው ዕረፍትና ውዳሴ ተዛማጅ መሆናቸው ጎላ ተደርጎ የተገለጸበትን ዘጸአት 20:8-10ን መሠረት በማድረግ በአይሁድ እምነት ውስጥ ከዳበረው የሰንበት መመሪያ ነው። . . . አምላክ የሚመለክበትንና የሚወደስበትን የበዓልና የደስታ ጊዜ ልዩ ገጽታ ጎላ አድርጎ ያሳያል።” ስለዚህ ተስፋ የተሰጠበት ዕረፍት እንዲያው ከሥራ ነፃ መሆንን ብቻ አያመለክትም። አድካሚና ትርጉም የለሽ የሆነን ሥራ ትቶ አምላክን የሚያስከብር አስደሳች አገልግሎት ማከናወን ማለት ነው።
16 የሚቀጥሉት የጳውሎስ ቃላት ይህን ሐሳብ ይደግፋሉ:- “ወደ ዕረፍቱ የገባ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።” (ዕብራውያን 4:10) አምላክ በሰባተኛው የፍጥረት ቀን ያረፈው ስለደከመው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ምድራዊ የፍጥረት ሥራውን ያቆመው የእጁ ሥራዎች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱና ወደ ሙሉ ክብር እንዲመጡ ሲል ነው። ይህ ደግሞ ለእሱ ውዳሴና ክብር ያመጣለታል። የአምላክ ፍጥረታት እንደመሆናችን መጠን እኛም ከዚህ ዝግጅት ጋር መስማማት አለብን። ‘ከሥራችን ማረፍ’ ማለትም መዳን ለማግኘት ስንል በአምላክ ፊት ጻድቅ መስለን ለመታየት የምናደርገውን ጥረት ማቆም አለብን። ከዚህ ይልቅ መዳናችን የተመካው ሁሉም ነገሮች እንደገና ከአምላክ ዓላማ ጋር እንዲስማሙ በሚያደርገው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ መሆኑን ልናምን ይገባል።—ኤፌሶን 1:8-14፤ ቆላስይስ 1:19, 20
የአምላክ ቃል ኃይል አለው
17. ሥጋዊ እስራኤላውያን ከተከተሉት ከየትኛው አካሄድ መራቅ አለብን?
17 እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸውና እምነት በማጣታቸው ምክንያት ወደ አምላክ ዕረፍት አልገቡም። በመሆኑም ጳውሎስ “እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ” በማለት ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ዕብራውያን 4:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ አይሁዶች በኢየሱስ አያምኑም ነበር። በዚህም ምክንያት የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት በ70 እዘአ ሲያበቃ ብዙዎቹ ከባድ መከራ ደርሶባቸዋል። እኛም ዛሬ አምላክ በሰጠው የተስፋ ቃል ማመናችን እጅግ ወሳኝ ነው!
18. (ሀ) ጳውሎስ በአምላክ ቃል እንድናምን የሚያደርጉንን የትኞቹን ምክንያቶች ጠቅሷል? (ለ) የአምላክ ቃል “ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ” የሆነው እንዴት ነው?
18 በይሖዋ ቃል የምናምንበት ጠንካራ ምክንያት አለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) አዎን፣ የአምላክ ቃል ወይም መልእክት “ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው።” ዕብራውያን ክርስቲያኖች የጥንት አባቶቻቸው ምን እንደደረሰባቸው ማስታወስ ያስፈልጋቸው ነበር። ይሖዋ በምድረ በዳ እንዲያልቁ የበየነባቸውን ፍርድ ችላ በማለት ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሞክረው ነበር። ሆኖም ሙሴ “አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ” ሲል አስጠነቀቃቸው። እስራኤላውያን በእምቢተኝነት ወደ ፊት በገፉ ጊዜ ግን “በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፣ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።” (ዘኁልቁ 14:39-45) የይሖዋ ቃል ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ በመሆኑ ሆን ብሎ ችላ የሚለው ሰው ሁሉ መጥፎ ውጤት እንደሚያጭድ የተረጋገጠ ነው።—ገላትያ 6:7-9
19. የአምላክ ቃል ዘልቆ የመግባት ኃይሉ ምን ያህል ነው? በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆናችንንስ አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?
19 የአምላክ ቃል ‘ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለይ ድረስ የሚወጋ’ እንዴት ያለ ከፍተኛ ኃይል አለው! የግለሰቦችን አስተሳሰብና ውስጣዊ ፍላጎት ዘልቆ ሊገባ ይችላል። በምሳሌያዊ ሁኔታ አጥንትን ሰንጥቆ እስከ ቅልጥም ድረስ ዘልቆ ይገባል! ከግብጽ ባርነት ነፃ የወጡት እስራኤላውያን ሕጉን ለመጠበቅ ቢስማሙም ይሖዋ ለዝግጅቶቹና ለመሥፈርቶቹ ልባዊ አድናቆት እንዳልነበራቸው ያውቅ ነበር። (መዝሙር 95:7-11) ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር የእሱን ፈቃድ መፈጸም ሳይሆን ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸውን ማርካት ነበር። ከዚህ የተነሣ ወደ አምላክ ዕረፍት ከመግባት ይልቅ በምድረ በዳ አለቁ። ይህን ትምህርት ልብ ልንለው ይገባል፤ ምክንያቱም “እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ [በአምላክ ዓይኖች] ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” (ዕብራውያን 4:13) ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነውን ቃል የምናሟላ እንጂ ‘ወደ ጥፋት የምናፈገፍግ’ አንሁን።—ዕብራውያን 10:39
20. ወደፊት ምን ነገር ይፈጸማል? እኛስ ወደ አምላክ ዕረፍት ለመግባት አሁን ምን ማድረግ አለብን?
20 ‘ሰባተኛው ቀን’ ማለትም የአምላክ የዕረፍት ቀን እስከ አሁን ይቀጥል እንጂ አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ መፈጸሙን በንቃት መከታተሉን አላቆመም። መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን ዲያብሎስን ጨምሮ የአምላክ ፈቃድ ተቃዋሚዎችን በሙሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ኢየሱስና 144,000 ተባባሪ ገዥዎቹ ምድርንና የሰው ልጆችን አምላክ መጀመሪያ ካወጣው ዓላማ ጋር ወደሚስማማ ሁኔታ ያደርሷቸዋል። (ራእይ 14:1፤ 20:1-6) ሕይወታችን በይሖዋ አምላክ ፈቃድ ላይ ያተኮረ መሆኑን የምናሳይበት ጊዜ አሁን ነው። በአምላክ ፊት ጻድቅ መስለን ለመታየትና የግል ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት ከመጣር ይልቅ ‘ከሥራችን የምናርፍበትና’ የመንግሥቱን ጉዳዮች በሙሉ ልባችን የምናከናውንበት ጊዜ አሁን ነው። እንዲህ ካደረግንና ለሰማዩ አባታችን ለይሖዋ ታማኝ ከሆንን አሁንም ሆነ ለዘላለም ከአምላክ ዕረፍት ተጠቃሚዎች የመሆን መብት ይኖረናል።
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ አምላክ “በሰባተኛው ቀን” ያረፈው ለምን ዓላማ ነው?
◻ እስራኤላውያን ወደ የትኛው ዕረፍት ለመግባት ይችሉ ነበር? ሆኖም ሊገቡ ያልቻሉት ለምንድን ነው?
◻ ወደ አምላክ ዕረፍት ለመግባት ምን ማድረግ አለብን?
◻ የአምላክ ቃል ሕያው፣ ኃይለኛና ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ የሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን ሰንበትን ቢጠብቁም ወደ አምላክ ዕረፍት አልገቡም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?