ሥላሴ
ፍቺ:- የሥላሴ እምነት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ዋነኛ መሠረተ ትምህርት ነው። በአትናቴዎስ ሃይማኖታዊ ድንጋጌ መሠረት ሁሉም ዘላለማዊ የሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ሁሉን ማድረግ የሚችሉ፣ አንዳቸው ከአንዳቸው የማይበላለጡ፣ ሁሉም አምላክ የሆኑ ሦስት መለኮታዊ አካላት (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) አሉ። ይሁን እንጂ ሦስቱም አንድ አምላክ ናቸው እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም። ስለዚህ ቀኖና የተሰጡ ሌሎች መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት እነዚህ ሦስት “አካላት” መለኮታዊው ሕልውና የሚገለጥባቸው ሦስት መንገዶች ናቸው እንጂ የተለያዩና ግላዊ ሕልውና ያላቸው “አካላት” አይደሉም። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የሥላሴ አማኞች ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደሆነ ወይም ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ ይሖዋ እንደሆኑ አጥብቀው ይናገራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።
የሥላሴ እምነት ምንጩ ምንድን ነው?
ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ሥላሴ የሚለው ቃልም ሆነ በግልጽ የተብራራ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። ኢየሱስም ሆነ ተከታዮቹ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፈውን:- ‘እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው’ (ዘዳ. 6:4) የሚለውን ለማስተባበል አላሰቡም።. . . የሥላሴ እምነት ቀስ በቀስ የተስፋፋው በበርካታ መቶ ዓመታት ውስጥ ከብዙ ንትርክ በኋላ ነው። . . . የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አሁን ያለውን ቅርጽ የያዘው በአራተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው።”—(1976)፣ ማክሮፔድያ፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 126
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “‘አንድ አምላክ በሦስት አካላት’ የሚለው ድንጋጌ ጠንካራ መሠረት ያገኘውና በክርስትና ሕይወትና የእምነት መግለጫ ውስጥ ሙሉ ተቀባይነት ያገኘው ከ4ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነበር። ይሁን እንጂ የሥላሴ ቀኖና የሚለው ስያሜ የተሰጠው ለዚህ ድንጋጌ ነው። ሐዋርያዊ አባቶች እንዲህ ያለ አመለካከት ወይም ከዚህ እምነት ጋር የሩቅ ዝምድና እንኳን ያለው አስተሳሰብ እንደነበራቸው የሚያመለክት አንድም ማስረጃ አናገኝም።”— (1967)፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 299
ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ክርስትና የበቀለው ከአይሁዳውያን ሃይማኖት ነው። አይሁዳውያን ደግሞ አምላክ አንድ አካል ነው ብለው የሚያምኑ ሕዝቦች ናቸው። ከኢየሩሳሌም ወደ ኒቅያ ያደረሰው መንገድ ጠመዝማዛነት የበዛበት ነበር። የአራተኛ መቶ ዘመኑ የሥላሴ እምነት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ስለአምላክ ማንነት የነበራቸውን እምነት በትክክል አያንጸባርቅም። እንዲያውም እነርሱ ከነበራቸው እምነት ፈጽሞ የራቀ ነው።”—(1956)፣ ጥራዝ 27፣ ገጽ 294 ኤል
ኑቮ ዲክሲዮኔር ኡኒቬርሴል (አዲሱ ዓለም አቀፋዊ መዝገበ ቃላት) እንደሚለው “የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተምሩት የሦስት ሃይፖስታሲስ ወይም የሦስት አካላት እምነት የተወለደው ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የተለያዩ ሕዝቦች ያምኑባቸው ከነበሩት ሥላሴዎች ከተወረሰው የፕላቶ የባሕርይ ሥላሴነት ፍልስፍና ነው። . . . ይህ ግሪካዊ ፈላስፋ [በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ፕላቶ] ስለ መለኮታዊ ሥላሴ የነበረውን ፅንሰ ሐሳብ . . . በሁሉም የጥንት [አረመኔያዊ] ሃይማኖቶች ውስጥ ማግኘት ይቻላል።”—(ፓሪስ፣ 1865–1870)፣ በኤም ላሻትር የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 1467
ጆን ኤል ማኬንዚ፣ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት) በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “በባሕርይ አንድነት ውስጥ የሚገኘው የአካል ሦስትነት የሚብራራው የግሪካውያን የፍልስፍና ቃላት በሆኑት በ‘አካል’ እና ‘ባሕርይ’ ነው። እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሥላሴን ሐሳብ ለመግለጽ አገልግለው አያውቁም። ይህ ዓይነቱ የሥላሴ ፍቺ የተገኘው አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት በስህተት እነዚህንና ‘ኤሰንስ’ እና ‘ሰብስታንስ’ የተባሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ስለ አምላክ ለመግለጽ በመጠቀማቸው ምክንያት ከተፈጠረው ውዝግብ ነው።”—(ኒው ዮርክ፣ 1965)፣ ገጽ 899
የሥላሴ አማኞች ራሳቸው እንደሚያምኑት “ሥላሴ” የሚለው ቃልም ሆነ ስለ ሥላሴ ቀኖና የተሰጠ መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ቢሆንም በዚህ ቀኖና ውስጥ የተገለጸው ፅንሰ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛልን?
“መንፈስ ቅዱስ” የተወሰነ አካል ነው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራልን?
ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩ አንዳንድ ጥቅሶች መንፈስ ቅዱስ የተወሰነ አካል እንደሆነ የሚያመለክቱ ሊመስል ይችላል። ለምሳሌ ያህል መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ (በግሪክኛ ጰራቅሊጦስ፣ “ረዳት” አዓት፣ “አጽናኝ” ኪጄ፣ “ጠበቃ” ጀባ እና ኒኢ ) ‘የሚያስተምር’፣ ‘የሚመሰክር’፣ ‘የሚናገር’ እና ‘የሚሰማ’ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። (ዮሐ. 14:16, 17, 26፤ 15:26፤ 16:13) ይሁን እንጂ ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ‘እንደተሞሉ’፣ አንዳንዶችም በመንፈስ ቅዱስ ‘እንደተጠመቁ’ ወይም ‘እንደተቀቡ’ ይናገራሉ። (ሉቃስ 1:41፤ ማቴ. 3:11፤ ሥራ 10:38) እነዚህ የኋለኞቹ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩ ጥቅሶች አንድን የተወሰነ አካል እንደማያመለክቱ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው አጠቃላይ ትምህርት ለመረዳት እነዚህን ጥቅሶች በሙሉ ማገናዘብ ያስፈልጋል። እነዚህን በማገናዘብ የምንደርስበት ምክንያታዊ ድምዳሜ ምንድን ነው? በመጀመሪያ ላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ፣ ኃጢአት፣ ሞት፣ ውኃና ደም የተወሰነ አካል እንደሆኑ ወይም ስብዕና እንዳላቸው አድርጎ እንደሚናገር ሁሉ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል የተወሰነ አካል እንደሆነ ወይም ስብዕና እንዳለው በሚያስመስል የአነጋገር ዘይቤ እንደሚጠቀም የሚያመለክቱ ናቸው። (በተጨማሪም በገጽ 378, 379 ላይ “መንፈስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)
ቅዱሳን ጽሑፎች የአብ የግል መጠሪያ ስም ይሖዋ እንደሆነ ይናገራሉ። ወልድ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ይገልጹልናል። ለመንፈስ ቅዱስ ግን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የግል መጠሪያ ስም የተሰጠበት ቦታ የለም።
ሥራ 7:55, 56 እስጢፋኖስ በራእይ “ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ” በሰማይ እንደተመለከተ ይገልጻል። መንፈስ ቅዱስን እንዳየ ግን የተናገረው ነገር የለም። (በተጨማሪ ራእይ 7:10ንና ራእይ 22:1, 3ን ተመልከት።)
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ በማለት ያምናል:- “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ጥቅሶች የአምላክን መንፈስ የሚገልጹት የተወሰነ አካል እንደሆነ ሳይሆን ረቂቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ነው። መንፈስና የአምላክ ኃይል ተመሳሳይ እንደሆኑ ተደርጎ መገለጹ ይህንን ያስረዳል።” (1967፣ ጥራዝ 13፣ ገጽ 575) በተጨማሪ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “አፖሎጂስቶች [በሁለተኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት በግሪክኛ ቋንቋ ይጽፉ የነበሩ ክርስቲያን ጸሐፊዎች] ስለ መንፈስ የተናገሩት በጣም ያዝ እያደረጋቸው፣ ወደፊት የሚሆነውን በመጠበቅ፣ የተወሰነ አካል እንደሌለው አድርገው ነው።”—ጥራዝ 14፣ ገጽ 296
መጽሐፍ ቅዱስ አብና ወልድ የማይነጣጠሉና የባሕርይ ልዩነት የሌላቸው ናቸው ብለው ከሚያስተምሩት ጋር ይስማማልን?
ማቴ. 26:39:- “[ኢየሱስ ክርስቶስ] ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ:- አባቴ፣ ቢቻልስ፣ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።” (አብና ወልድ በአካል የተለያዩ ባይሆኑ ኖሮ እንዲህ የመሰለው ጸሎት ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር። ኢየሱስ የጸለየው ለራሱ ነበር ማለት ይሆናል፤ የእርሱ ፈቃድ የግድ የአባቱም ፈቃድ ይሆን ነበር።)
ዮሐ. 8:17, 18:- “[ኢየሱስ ለአይሁድ ፈሪሣውያን እንዲህ በማለት መለሰላቸው:-] የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፣ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” (ስለዚህ ኢየሱስ ከአብ በአካል የተለየና የራሱ ሕልውና ያለው እንደሆነ ተናግሯል።)
በተጨማሪ በገጽ 198, 199 ላይ “ይሖዋ” በሚለው ሥር ተመልከት።
የሥላሴ ክፍል ናቸው የሚባሉት ሁሉ እኩል ዘላለማዊና መጀመሪያ የሌላቸው እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራልን?
ቆላ. 1:15, 16 የ1980 ትርጉም:- “ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው። . . . በሰማይና በምድር ያሉት . . . ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው።” ኢየሱስ ክርስቶስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው” የተባለው በምን መንገድ ነው? (1) የሥላሴ አማኞች “በኩር” ማለት ዋና፣ እጅግ በጣም ከፍ ያለ፣ በጣም የላቀ ማለት ነው፤ ስለዚህ ክርስቶስ የፍጥረት ክፍል ሳይሆን ከፍጡራን በጣም የላቀ ተደርጎ ይታያል ይላሉ። ይህ እንዲህ ከሆነና የሥላሴ ትምህርት እውነት ከሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ የፍጥረት በኩራት ያልተባሉት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አገላለጽ ለወልድ ብቻ ይጠቀምበታል። “በኩር” የሚለውን ቃል የተለመደ ትርጉም ከወሰድን ኢየሱስ በይሖዋ ልጆች ቤተሰብ ውስጥ አንጋፋ መሆኑን ያመለክታል። (2) “የ . . . በኩር” የሚለው አገላለጽ ከቆላስይስ 1:15 በፊት ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ከ30 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። በሁሉም ቦታዎች ላይ የተሰጠው ትርጉም እዚህ ላይ ካለው ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በኩሩ የቡድኑ አንድ አካል መሆኑን ያመለክታል። “የእስራኤል በኩር” ከእስራኤል ልጆች አንዱ ነው፤ “የፈርዖን በኩር” የፈርዖን ቤተሰብ አባል ነው። “የእንስሳት በኩር” ራሱ እንስሳ ነው። ታዲያ አንዳንዶች ለቆላስይስ 1:15 የተለየ ትርጉም እንዲሰጡት ያደረጋቸው ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ነው ወይስ ቀደም ብለው ለያዙት እምነት ማረጋገጫ ለማግኘት መፈለጋቸው? (3) ቆላስይስ 1:16, 17 (ሪስ ) “በእርሱ ሁሉም ነገሮች ተፈጠሩ . . . ሁሉም ነገሮች በእርሱና ለእርሱ ተፈጠሩ” ማለቱ ኢየሱስ ያልተፈጠረ መሆኑን ያረጋግጣልን? እዚህ ላይ “ሁሉም ነገሮች” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ፓንታ ሲሆን ፓስ ከተባለው ቃል የተገኘ ነው። ይህን ቃል በሉቃስ 13:2 (የ1980 ትርጉም ) ላይ “ከሌሎቹ . . . ሁሉ” ተብሎ ተተርጉሟል። ጀባ “ከቀሩት ሁሉ”፣ ኒኢ “ከሌላው ሁሉ” ይለዋል። (በተጨማሪ ሉቃስ 21:29 ኒኢ፣ እንዲሁም ፊልጵስዩስ 2:21 ጀባ ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎቹ ቦታዎች ላይ ስለ ወልድ ከሚናገረው ጋር በመስማማት አዓት ቆላስይስ 1:16, 17 ላይ ለሚገኘው ፓንታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም ሰጥቶታል። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይነበባል። “ሌሎቹ ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካኝነት ተፈጥረዋል። . . . ሌሎቹ ነገሮች ሁሉ በእርሱ በኩልና ለእርሱ ተፈጥረዋል።” ስለዚህ ወልድ ፍጡርና አምላክ ካስገኛቸው ፍጥረታት አንዱ መሆኑን ያመለክታል።
ራእይ 1:1፤ 3:14:- “እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው [ራእይ] . . . በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- አሜን የሆነው የታመነውና እውነተኛው ምስክር በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ [በግሪክኛ አርክሄ ] የነበረው እንዲህ ይላል።” (ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ኮክ እና አዓት እንዲሁም ሌሎች ትርጉሞች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተርጉመውታል።) ይህ አተረጓጎም ትክክል ነውን? አንዳንዶች ጥቅሱ የሚያመለክተው ወልድ ‘የአምላክ ፍጥረት ጀማሪ’ እንደሆነና ‘የመጨረሻው የፍጥረት ምንጭ’ እንደሆነ ነው የሚል አስተያየት አላቸው። ይሁን እንጂ በሊዴል እና ስኮት የተዘጋጀው ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (ግሪክኛ–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት) የአርክሄ ቀዳሚ ትርጉም “መጀመሪያ” እንደሆነ ያመለክታል። (ኦክስፎርድ፣ 1968፣ ገጽ 252) በራእይ 3:14 ላይ የተጠቀሰው አካል ፍጡር፣ የአምላክ የመጀመሪያ ፍጡር የሆነና መጀመሪያ ያለው ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ወልድ ጥበብ ተብሎ እንደተጠራ ከሚስማሙበት ከምሳሌ 8:22 ጋር አወዳድር። በሪስ፣ በኒኢ፣ በጀባ እና በ1980 ትርጉም መሠረት በዚህ ጥቅስ ላይ የሚናገረው አካል ‘የተፈጠረ’ መሆኑ ተገልጿል።
ሚክያስ 5:2 ስለ መሲሑ ትንቢት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “አወጣጡ ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ [ነው።]” ዱዌይ እንዲህ ይላል:- “አወጣጡ ከመጀመሪያ፣ ከዘላለም ቀኖች ጀምሮ ነው።” ታዲያ ይህ አባባል ከአምላክ ጋር አንድ መሆኑን ያመለክታልን? ሪስ የዕብራይስጡን ቃል “ከዘላለም ቀኖች” ከማለት ይልቅ “ከጥንት ቀኖች” ብሎ መተርጎሙን ማስተዋል ይገባል። ጀባ “ከጥንት ቀናት” አዓት “ካልተወሰኑ ዘመናት ጀምሮ” በማለት ይተረጉማሉ። ሚክያስ 5:2 ከላይ ከተብራራው ከራእይ 3:14 ጋር ሲገናዘብ ኢየሱስ መጀመሪያ የሌለው መሆኑን አያረጋግጥም።
መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴ ክፍል ናቸው የሚባሉት ሁሉ አንዳቸው ከሌላው እንደማይበልጡ ወይም እንደማያንሱ፣ ሁሉም እኩል እንደሆኑና፣ ሦስቱም ሁሉን ቻይ እንደሆኑ ያስተምራልን?
ማር. 13:32:- “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም።” (በእርግጥ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እኩልና አንድነት በሦስትነት ያላቸው አንድ አምላክ ቢሆኑ ኖሮ እንዲህ ይል ነበርን? አንዳንዶች ወልድ ለማወቅ ያልቻለው በሰብዓዊ ባሕሪው ውስንነት ምክንያት ነው ይላሉ። ታዲያ መንፈስ ቅዱስስ ያላወቀው ለምንድን ነው?)
ማቴ. 20:20–23:- “የዘብዴዎስ ልጆች እናት . . . [ኢየሱስን]:- እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው። ኢየሱስ ግን መልሶ:- . . . ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም አላቸው።” (ሰዎች እንደሚሉት ኢየሱስ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ ይህ አነጋገሩ እንዴት እንግዳ በሆነ! ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረው “ሰብዓዊ ባሕሪውን” ብቻ አስመልክቶ ነበርን? የሥላሴ አማኞች እንደሚሉት ኢየሱስ በእውነት “አምላክም ሰውም” (አምላክነትም ሰብዓዊነትም የተዋሃዱት አካል) ቢሆን ይህ ዓይነቱ መግለጫ ትክክል ይሆናልን? ማቴዎስ 20:23 ወልድ ከአብ ጋር እኩል እንዳልሆነና አብም አንዳንድ መብቶችን ለራሱ ብቻ እንደወሰነ ያመለክት የለምን?)
ማቴ. 12:31, 32:- “ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሠረይላቸዋል፣ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፣ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።” (መንፈስ ቅዱስ የተወሰነ አካል ያለው አምላክ ቢሆን ኖሮ ይህ ጥቅስ መንፈስ ቅዱስ ከወልድ እንደሚበልጥ ስለሚያመለክት ከሥላሴ እምነት ጋር ሙሉ በሙሉ ይቃረናል። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የገለጸው ‘የመንፈስ’ ባለቤት የሆነው አብ ከኢየሱስ፣ ማለትም የሰው ልጅ ከተባለው እንደሚበልጥ ነው።)
ዮሐ. 14:28:- “[ኢየሱስ እንዲህ አለ:-] የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር።”
1 ቆሮ. 11:3:- “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” (በግልጽ እንደሚታየው ክርስቶስ እግዚአብሔር አይደለም፣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ በማዕረግ በጣም ከፍ ያለ ነው። ይህ የተጻፈው ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ ከ22 ዓመት በኋላ በ55 እዘአ ገደማ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። ስለዚህ እዚህ ላይ ስለ ክርስቶስና ስለ እግዚአብሔር የተገለጸው ሐቅ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደም በኋላ አልተሻረም።)
1 ቆሮ. 15:27, 28:- “ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፣ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።”
የዕብራይስጡ ቃል ሻዳይ እና የግሪክኛው ቃል ፓንቶክራቶር ‘ሁሉን ማድረግ የሚችል’ ተብለው ተተርጉመዋል። ሁለቱም በኩረ ቃላት ይሖዋ አብን ለማመልከት በተደጋጋሚ ተሠርቶባቸዋል። (ዘጸ. 6:3፤ ራእይ 19:6) ይሁን እንጂ ከሁለቱ ቃላት አንዳቸውም ቢሆኑ ወልድን ወይም መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት አላገለገሉም።
መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴ ክፍል ናቸው የሚባሉት እያንዳንዳቸው አምላክ ናቸው ይላልን?
ኢየሱስ ሲጸልይ እንዲህ አለ:- “አባት ሆይ! . . . የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።” (ዮሐ. 17:1–3 የ1980 ትርጉም፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አብዛኞቹ ትርጉሞች ስለ አብ ሲገልጹ “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንክ” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማሉ። ኒኢ “አንተ ብቻ በእውነት አምላክ የሆንክ” በማለት ተርጉሟል። ከአብ ጋር እኩል ሥልጣን ያላቸው ሌሎች ሁለት አምላኮች ቢኖሩ “እውነተኛ አምላክ አንተ ብቻ” ሊባል ይችላልን? ሌሎቹ “አምላክ” ተብለው የሚጠሩ ሁሉ አንድም የውሸት አማልክት ናቸው አለዚያም የእውነተኛው አምላክ ነጸብራቅ ብቻ ናቸው።)
1 ቆሮ. 8:5, 6:- “መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፣ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፣ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” (ይህ ጥቅስ አብ የክርስቲያኖች “አንድ አምላክ” እንደሆነና ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ ደረጃ እንዳለው ያመለክታል።)
1 ጴጥ. 1:3:- “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” (ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ ቢሆን ቅዱሳን መጻሕፍት በተደጋጋሚ አብ የኢየሱስ ክርስቶስ “አምላክ” እንደሆነ ይናገራሉ። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በዮሐንስ 20:17 ላይ አብን “አምላኬ” ብሎ ጠርቶታል። ከብዙ ጊዜ በኋላም ቢሆን በራእይ 3:12 ላይ እንደተመዘገበው በዚሁ ቃል ተጠቅሟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብ ወልድን “አምላኬ” ያለበት፣ አብ ወይም ወልድ መንፈስ ቅዱስን “አምላኬ” ያሉበት ቦታ ግን ጨርሶ የለም።)
አንዳንዶች ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት የሚጠቀሙባቸውን ጥቅሶች በተመለከተ የተሰጡትን አስተያየቶች በገጽ 213–217 ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።
ቲኦሎጂካል ኢንቨስቲጌሽንስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ካርል ራነር እንዲህ ብለዋል:- “መንፈስ Θεο΄ς [“እግዚአብሔር” “God”] የተባለበት ጊዜ የለም።” በተጨማሪም πνεῦμα ᾶγιον [መንፈስ ቅዱስ] በአዲስ ኪዳን ውስጥ ὁ θεός [በእንግሊዝኛ the God] የተባለበት ጊዜ የለም።”—(ባልቲሞር፣ ሜሪ ላንድ፣ 1961)፣ ከጀርመንኛ የተተረጐመ፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 138, 143
የሥላሴ አማኞች እምነታቸውን ለመደገፍ የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች ለዚህ እምነት ጽኑ መሠረት የሚሆኑ ናቸውን?
ስለ አምላክ እውነቱን ለማወቅ ከልብ የሚፈልግ ሰው ቀደም ሲል ከሚያምነው ጋር የሚስማማ ሐሳብ ለማግኘት በመፈለግ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር አይኖርበትም። የአምላክ ቃል ራሱ ምን እንደሚናገር ለማወቅ መፈለግ ይኖርበታል። ከአንድ የበለጠ ትርጉም ሊሰጣቸው ይችላል ብሎ የሚያስባቸው አንዳንድ ጥቅሶች ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሶች ስለ ተመሳሳይ ጉዳይ ከሚናገሩ ሌሎች ጥቅሶች ጋር ሲገናዘቡ ትርጉማቸው ግልጽ ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ የሥላሴ “ማስረጃ” ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ጥቅሶች አብዛኞቹ የሚናገሩት ስለ ሦስት ሳይሆን ስለ ሁለት አካላት መሆኑን ማስተዋል ይገባል። ስለዚህ የሥላሴ አማኞች ስለ ጥቅሶቹ የሚሰጡት ትርጉም ትክክል ቢሆን እንኳን ይህ ብቻውን መጽሐፍ ቅዱስ ሥላሴን እንደሚያስተምር ማረጋገጫ አይሆንም። የሚከተሉትን እንመልከት።
ከሌላ ትርጉም መጠቀሳቸውን ካላመለከትን በቀር ከዚህ በታች የተጠቀሱት ጥቅሶች በሙሉ ከ1954 የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የተወሰዱ ናቸው። )
ይሖዋ በሚጠራባቸው የማዕረግ ስሞች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተጠራ የሚያመለክቱ ወይም ያመለክታሉ ተብለው የሚታመንባቸው ጥቅሶች
አልፋና ኦሜጋ:- የዚህ ማዕረግ ስም ትክክለኛ ባለቤት ማነው? (1) በራእይ 1:8 ላይ የዚህ ማዕረግ ስም ባለቤት ሁሉን የሚችለው አምላክ እንደሆነ ተገልጿል። በኪጄ በቁጥር 11 ላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚስማማ መግለጫ ለተሰጠው አካል ይህ አልፋና ኦሜጋ የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ብዙ ምሁራን በቁጥር 11 ላይ አልፋና ኦሜጋ የሚል ቃል የገባው አለአግባብ እንደሆነ ያምናሉ። በዚህም ምክንያት በ1954ም ሆነ በ1980 የአማርኛ ትርጉም፣ ሪስ፣ ኒኢ፣ ጀባ፣ ኒአባ እና ዱዌይ ውስጥ አይገኝም። (2) ወደ ዕብራይስጥ የተተረጎሙ ብዙ የራእይ መጽሐፍ ትርጉሞች ቁጥር 8 የሚናገረው ስለ ይሖዋ መሆኑን ተገንዝበዋል። በዚህም ምክንያት በዚህ ቁጥር ላይ የአምላክን የተፀውኦ ስም አስገብተዋል። ባለማጣቀሻውን የ1984 አዓት ትርጉም ተመልከት። (3) ራእይ 21:6, 7 መንፈሳዊ ድል አድራጊዎች የሆኑ ክርስቲያኖች የአልፋና ኦሜጋ ‘ልጆች’ እንደሚሆኑ ያመለክታል። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና እንደሚኖራቸው የተነገረበት ቦታ አይገኝም። ኢየሱስ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ወንድሞቹ’ እንደሆኑ ተናግሯል። (ዕብ. 2:11፤ ማቴ. 12:50፤ 25:40) ይሁን እንጂ እነዚህ የኢየሱስ ‘ወንድሞች’ “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለው ተጠርተዋል። (ገላ. 3:26፤ 4:6) (4) ቱኢቨ በራእይ 22:12 ላይ አልፋና ኦሜጋ የተባለው ኢየሱስ እንደሆነ ለማመልከት በመሞከር በቁጥር 13 ላይ ኢየሱስ የሚል ቃል ጨምሯል። ይሁን እንጂ በግሪክኛው በኩረ ጽሑፍ ውስጥ ኢየሱስ የሚል ቃል አይገኝም። ሌሎች ትርጉሞችም ኢየሱስ የሚለውን ቃል አይጨምሩም። (5) በራእይ 22:13 ላይ አልፋና ኦሜጋ የተባለው አምላክ “ፊተኛውና ኋለኛው” ተብሏል። ኢየሱስም በራእይ 1:17, 18 ላይ እንደዚያው ተብሎ ተጠርቷል። ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ከኢየሱስ ተከታዮች አንዳንዶቹ “ሐዋርያት” ተብለዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ መባላቸው ኢየሱስና ሐዋርያት የተባሉት የኢየሱስ ተከታዮች አንድ አካል እንደሆኑ ወይም እኩል ማዕረግ እንዳላቸው አያመለክትም። (ዕብ. 3:1) ስለዚህ ማስረጃው “አልፋና ኦሜጋ” የሚለው የማዕረግ ስም የሚያመለክተው ወልድን ሳይሆን ሁሉን የሚችለውን አምላክ አብን ነው።
አዳኝ:- ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አዳኝ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንዲያውም እግዚአብሔር በኢሳይያስ 43:11 ላይ “ከእኔ ሌላ አዳኝ የለም” ብሏል። ኢየሱስም አዳኝ ተብሎ ስለሚጠራ እግዚአብሔርና ኢየሱስ አንድ ናቸው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። ቲቶ 1:3, 4 (ሪስ፤ የ1980 ትርጉም ) ‘እግዚአብሔር አዳኛችን’ እንደሆነ ከተናገረ በኋላ ሁለቱንም ጠቅሶ “እግዚአብሔር አብና ክርስቶስ ኢየሱስ” ‘አዳኝ’ እንደሆኑ ይናገራል። ስለዚህ ሁለቱም አዳኞች ናቸው። ይሁዳ 25 (ሪስ ) “አምላክ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አዳኛችን ነው” በማለት በመካከላቸው ያለውን ዝምድና ያሳያል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (በተጨማሪ ሥራ 13:23ን ተመልከት።) በኢሳይያስ 43:11 ላይ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል (ሞሕሽያ “አዳኝ” ወይም “ነፃ አውጪ” ተብሎ የተተረጐመው) በመሳፍንት 3:9 (አዓት ) ላይ ለእስራኤል መስፍን ለኦትኒኤል ተሠርቶበታል። ታዲያ ኦትኒኤል ይሖዋ ነበር ማለት ነውን? ኢሳይያስ 43:1–12 በማንበብ ቁጥር 11 እስራኤልን የሚያድን ወይም ነፃ የሚያወጣት ይሖዋ ብቻ መሆኑን እንደሚያመለክት መገንዘብ ይቻላል። የአካባቢው ሕዝቦች ከሚያመልኳቸው አማልክት አንዳቸውም ቢሆኑ አላዳኗቸውም።
አምላክ:- ይሖዋ በኢሳይያስ 43:10 ላይ “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም” ብሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ በኢሳይያስ 9:6 ላይ በትንቢት “ኃያል አምላክ” ስለተባለ ከይሖዋ ጋር አንድ መሆን አለበት ማለት ነውን? እዚህም ላይ ቢሆን ከጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ አይደለም ይላል! ጣዖት አምላኪ ከነበሩት የአሕዛብ መንግሥታት መካከል አንዳቸውም ከይሖዋ በፊት ስላልነበሩ ከይሖዋ የቀደመ አምላክ ሊያስገኙ አልቻሉም። ወደፊትም ቢሆን ትንቢት ሊናገር የሚችል ሕያው አምላክ ሊኖራቸው አይችልም። (ኢሳ. 46:9, 10) ይሁን እንጂ ይህ ማለት ይሖዋ በትክክለኛ መንገድ አምላክ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ፍጡር አልፈጠረም ማለት አይደለም። (መዝ. 82:1, 6፤ ዮሐ. 1:1 አዓት ) ኢየሱስ በኢሳይያስ 9:6 ላይ “ኃያል አምላክ” ተብሎ እንደተጠራ ሁሉ ይሖዋም በኢሳይያስ 10:21 ላይ “ኃያል አምላክ” ተብሏል። ሆኖም ከይሖዋ በስተቀር “ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ” ተብሎ የተጠራ ማንም የለም።— ዘፍ. 17:1 አዓት
አንድ የማዕረግ ስም ወይም ገላጭ ሐረግ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከአንድ በበለጡ ቦታዎች በሚገኝበት ጊዜ ይህ ቃል ወይም ሐረግ ያንኑ አካል ብቻ ማመልከት ይኖርበታል ብሎ በችኮላ መደምደም ተገቢ አይደለም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ናቡከደናፆር ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳል፤ ምክንያቱም ሁለቱም “የነገሥታት ንጉሥ” ተብለው ተጠርተዋል። (ዳን. 2:37፤ ራእይ 17:14) በተጨማሪም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ኢየሱስ ክርስቶስም “የዓለም ብርሃን” ስለተባሉ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ አንድ አካል ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ያመራል። (ማቴ. 5:14፤ ዮሐ. 8:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ዓይነት ሐረግ ወይም ቃል በሁለት የተለያዩ ቦታዎች በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ የቃሉን ወይም የሐረጉን አገባብ መመልከት ይገባል።
በመንፈስ ቅዱስ ተነሣስተው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የጻፉ ሰዎች ስለ ይሖዋ የሚናገሩ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ጥቅሶችን በቀጥታ ጠቅሰው ለኢየሱስ ክርስቶስ መጠቀማቸው
ኢሳይያስ 40:3 የሚናገረው ለይሖዋ መንገድ ስለመጥረግ እንደሆነ ግልጽ ሆኖ ሳለ ዮሐንስ 1:23 ኢሳይያስ 40:3ን ጠቅሶ አጥማቂው ዮሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ስለመጥረጉ የተናገረው ለምንድን ነው? ኢየሱስ አባቱን ስለወከለ ነው። የመጣው በአባቱ ስም ነው። የአባቱን ፈቃድ ስለሚያደርግም ሁልጊዜ አባቱ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ተረጋግጦለታል።—ዮሐ. 5:43፤ 8:29
መዝሙር 102 የተነገረው ለእግዚአብሔር እንደሆነ መዝሙሩ ራሱ ሲያመለክት ዕብራውያን 1:10–12 መዝሙር 102:25–27ን ጠቅሶ ስለወልድ የተናገረው ለምንድን ነው? አምላክ መዝሙራዊው የገለጻቸውን የፍጥረት ሥራዎች ያከናወነው በወልድ በኩል ስለሆነ ነው። (ቆላስይስ 1:15, 16ንና ምሳሌ 8:22, 27–30ን ተመልከት።) ከ2 ሳሙኤል 7:14 ተወስዶ ለአምላክ ልጅ የተጠቀሰ ጥቅስ በዕብራውያን 1:5 ላይ ይገኛል። ጥቅሱ በመጀመሪያ የተነገረው ለሰሎሞን ቢሆንም በኋላ ላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ መዋሉ ሰሎሞንና ኢየሱስ አንድ መሆናቸውን አያመለክትም። ኢየሱስ ‘ከሰሎሞን ይበልጣል’፤ በተጨማሪም ሰሎሞን ጥላ የሆነለትን ሥራ አከናውኗል።—ሉቃስ 11:31
አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ የተጠሩባቸው ጥቅሶች
ማቴዎስ 28:19 እና 2 ቆሮንቶስ 13:14 ለዚህ ምሳሌ ይሆናሉ። ከእነዚህ ጥቅሶች አንዳቸውም ቢሆኑ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እኩል ሥልጣን አላቸው ወይም እኩል ዘላለማዊ ናቸው ወይም ሁሉም እግዚአብሔር ናቸው አይሉም። ቀደም ሲል በገጽ 407–411 ላይ የቀረቡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ለጥቅሶቹ እንዲህ ያለ ትርጉም እንዳንሰጥ ያግዱናል።
የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒድያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክሌስያስቲካል ሊትረቸር የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ቢደግፍም ማቴዎስ 28:18–20ን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ እንዲሁ እንዳለ ሲወሰድ የተጠቀሱትን የሦስቱን አካሎች ባሕርይም ሆነ እኩልነታቸውን ወይም መለኮታዊነታቸውን አያረጋግጥም።” (በ1981 እንደገና የታተመ፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 552) ይኸው ሳይክሎፔድያ ሦስቱን አንድ ላይ የሚጠሩ ሌሎች ጥቅሶች ብቻቸውን ሲወሰዱ ሥላሴን ለማረጋገጥ “የማይበቁ” መሆናቸውን ያምናል። (አምላክ፣ ክርስቶስና መላእክት አንድ ላይ ከተጠቀሱበት ከ1 ጢሞቴዎስ 5:21 ጋር አወዳድር።)
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አምላክ የብዙ ቁጥር ባላቸው ስሞች የተጠራባቸው ጥቅሶች
በዘፍጥረት 1:1 ላይ “አምላክ” የሚለው የማዕረግ ስም ኤሎሂም ከሚለው የዕብራይስጥ የብዙ ቁጥር ስም የተተረጐመ ነው። የሥላሴ አማኞች ይህ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ያመለክታል ይላሉ። በተጨማሪም ዘዳግም 6:4 “አምላካችን እግዚአብሔር [ኤሎሂም ] አንድ እግዚአብሔር ነው” ማለቱ ሦስቱ የሥላሴ ክፍሎች አንድ መሆናቸውን ያሳያል ይላሉ።
እዚህ ላይ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ስም በብዙ ቁጥር መነገሩ ከበሬታን ወይም ባለ ታላቅ ግርማ መሆንን ያመለክታል። (ኒአባ፣ የቅዱስ ጆሴፍ እትም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 330፣ እንዲሁም ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1967፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 287ን ተመልከት።) ጥቅሱ በአንድ አምላክ ሦስት አካላት መኖራቸውን አያመለክትም። በተመሳሳይ ሁኔታ መሳፍንት 16:23 የሐሰት አምላክ ስለሆነው ስለ ዳጎን በሚናገርበት ጊዜ ኤሎሂም በሚለው ስም ተጠቅሟል። የዐረፍተ ነገሩ ግሥ ግን ነጠላ ቁጥር ነው። ይህም የተነገረው ስለ አንድ አምላክ ብቻ መሆኑን ያመለክታል። በዘፍጥረት 42:30 ላይ ዮሴፍ የግብጽ “ጌታ” (አድሆኔህ፣ ከበሬታን የሚያሳይ የብዙ ቁጥር) ተብሎ ተጠርቷል።
የግሪክኛ ቋንቋ ‘ባለ ታላቅ ግርማ መሆንን ወይም ከበሬታን’ ለማሳየት የብዙ ቁጥር ባላቸው ስሞች አይጠቀምም። በዚህም ምክንያት የሰባ ሊቃናት ተርጓሚዎች በዘፍጥረት 1:1 ላይ የሚገኘውን ኤሎሂም የተባለ ቃል ሆ ቴኦስ (አምላክ፣ በነጠላ ቁጥር) ብለው ተርጉመውታል። ኢየሱስ ከዘዳግም 6:4 ላይ ጠቅሶ የሰጠው መልስ በተመዘገበበት በማርቆስ 12:29 ላይም የሚገኘው ሆ ቴኦስ ነጠላ ቁጥር ነው።
በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ በዘዳግም 6:4 ላይ ቴትራግራማተን (የአምላክን ስም የሚወክሉት አራቱ ፊደላት) ሁለት ጊዜ ተጠቅሰዋል። ስለሆነም “ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው” ተብሎ መተርጎም ነበረበት። (አዓት ) ይህ ቃል የተነገረው የእስራኤል ሕዝብ በሥላሴ አያምንም ነበር። የሥላሴነት ባሕርይ ያላቸውን አማልክት ያመልኩ የነበሩት ባቢሎናውያንና ግብጻውያን ነበሩ። ይሖዋ ግን ከእነዚህ አማልክት የተለየ መሆኑ ለእስራኤላውያን ተነግሯቸዋል።
በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ከአንድ የበለጠ ትርጉም ሊሰጣቸው የሚችሉ ጥቅሶች
አንድ ጥቅስ ከአንድ በበለጠ ሰዋስዋዊ አገባብ ሊተረጎም ከቻለ ትክክለኛው ትርጉም የቱ ነው? ከሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር የሚስማማው አተረጓጎም ነው። አንድ ሰው ሌሎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ችላ ብሎ እሱ በሚመርጠው አተረጓጎም ላይ ብቻ እምነቱን ቢመሠርት እምነቱ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ሳይሆን የራሱን አስተሳሰብ ወይም ፍጹም ያልሆነን ሌላ ሰው አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” (ሪስ፣ ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ጀባ፣ ኒአባ እንዲሁም የ1980 ትርጉም ከዚህ ጋር በሚመሳሰሉ ቃላት ተርጉመውታል።) ይሁን እንጂ አዓት እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፣ ቃልም አምላክ [a god] ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ።”
ከጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር የሚስማማው የትኛው የዮሐንስ 1:1, 2 አተረጓጎም ነው? ዮሐንስ 1:18 “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም” ይላል። ቁጥር 14 (አዓት ) “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ . . . በመካከላችን ኖረ፤ . . . እኛም የእርሱን ክብር አየን” በማለት በግልጽ ይናገራል። እንዲሁም ቁጥር 1, 2 እርሱ በመጀመሪያ “ከእግዚአብሔር ጋር ” ነበረ ይላል። ከሌላ ሰው ጋር የሆነ ሰው እርሱ ራሱ ያንኑ ሰው መሆን ይችላልን? በዮሐንስ 17:3 ላይ (የ1980 ትርጉም ) ኢየሱስ አብን “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንህ” ብሎታል። ስለዚህ ኢየሱስ “አምላክ” (“a god”) እንደመሆኑ የአባቱን መለኮታዊ ባሕርያት ያንጸባርቃል።—ዕብ. 1:3
“አምላክ” (“a god”) የሚለው አተረጓጎም ከግሪክኛ የሰዋስው ሕግ ጋር ይስማማልን? አንዳንድ የማመሳከሪያ መጻሕፍት የግሪክኛው ዐረፍተ ነገር “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” ተብሎ መተርጐም አለበት በማለት አጥብቀው ይከራከራሉ። ሆኖም ግን በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ ብዙ ምሁራን አሉ። ፊልፕ ቢ ሐርነር “ኩዋሊቴቲቭ አናርትረስ ፕሪዲኬት ናውን፣ ማርክ 15:39 ኤንድ ጆን 1:1” በተባለው ጽሑፋቸው ላይ በዮሐንስ 1:1 ላይ እንደሚገኘው ሐረግ “ከግሥ በፊት ኢርቱዕ ተሳቢ ከገባ ተሳቢ ሆኖ የገባው ስም ባሕርይን የሚያመለክት ትርጉም ይኖረዋል። ሎጎስ የቴኦስ ባሕርይ እንዳለው ያመለክታል” ብለዋል። “ይህ ሐረግ ምናልባት ‘ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ተመሳሳይ ባሕርይ ነበረው’ ተብሎ ሊተረጎም ይችል ይሆናል” የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል። (ጆርናል ኦቭ ቢብሊካል ሊትረቸር፣ 1973፣ ገጽ 85, 87) ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሁለተኛ ቴኦስ አመልካች ቃል (ሆ ) ያልታከለበትና ከግሥ በፊት የገባ መሆኑ በግሪክኛ ሰዋስው ትልቅ የትርጉም ለውጥ ያመጣል። ዮሐንስ 1:1 “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ተብሎ መተርጎም ይኖርበታል በማለት አጥብቀው የሚከራከሩ ተርጓሚዎች በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ነጠላ ቁጥር ያለው ስም ኢርቱዕ ተሳቢ ሆኖ ከግሥ በፊት በሚገባበት ጊዜ (በእንግሊዝኛ a ወይም an የተባለውን) ማንነትን ወይም ምንነትን ለይቶ የማያመለክት ቃል እያስገቡ መተርጎማቸው ያስገርማል። ጀባ እና ኪጄ በዮሐንስ 6:70 ላይ የአስቆሮቱ ይሁዳ ዲያብሎስ መሆኑንና በዮሐንስ 9:17 ላይ ደግሞ ኢየሱስ “ነቢይ” መሆኑን ሲገልጹ “a devil”፣ “a prophet” ብለዋል።
ጆን ኤል ማኬንዚ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት) በተባለው መጽሐፋቸው:- “ዮሐ. 1:1 ‘ቃል ከእግዚአብሔር [=ከአብ] ጋር ነበር፣ ቃልም መለኮታዊ አካል ነበር’ ተብሎ መተርጎም ይኖርበታል” ብለዋል።—(ቅንፎቹ የሳቸው ናቸው። በፈቃድ ታትሞ የወጣ) (ኒው ዮርክ፣ 1965)፣ ገጽ 317
አት ከላይኛው ሐሳብ ጋር በመስማማት እንዲህ ይላል:- “ቃል መለኮት ነበረ።” ሞፋት “ሎጐስ መለኮት ነበር”፤ ኒቴኢ “ቃል አምላክ መሳይ ነበር” ይላል። ሉድቪግ ቲመ በጀርመንኛ ትርጉማቸው ላይ “ቃል አምላክ መሳይ ነበር” ብለዋል። ቃልን (ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን) “አምላክ” ማለት ይህ ቃል በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከተሰጠው ትርጉም ጋር ይስማማል። ለምሳሌ በመዝሙር 82:1–6 ላይ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የነበሩ ሰብዓዊ ዳኞች የይሖዋ ወኪሎችና ሕጉን የሚናገሩ ስለነበሩ “አማልክት” (በዕብራይስጥ ኤሎሂም፤ በዮሐንስ 10:34 ላይ በግሪክኛ ቴኦይ ) ተብለው ተገልጸዋል።
በተጨማሪ የአዓት የ1984 ባለ ማጣቀሻ እትም ተጨማሪ ክፍል (አፔንዲክስ) ገጽ 1579 ተመልከት።
ሪስ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ሳይኖር እኔ ነኝ። [ግሪክኛ ኢጎ ኤይሚ ]’” (ኒኢ፣ ኪጄ፣ ቱኢቨ፣ ጀባ እና ኒአባ ሁሉም “እኔ ነኝ” እያሉ ተርጉመዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ቃል የማዕረግ ስም እንደሆነ ለማመልከት በእንግሊዝኛ በካፒታል ሌተርስ ጽፈውታል። በዚህ መንገድ ይህንን ጥቅስ በእነርሱ አተረጓጎም መሠረት አምላክ ራሱን “እኔ ነኝ” ብሎ ከጠራበት ከዘጸአት 3:14 ጋር ለማዛመድ ሞክረዋል።) ይሁን እንጂ አዓት የዮሐንስ 8:58ን የመጨረሻ ክፍል “አብርሃም ከመኖሩ በፊት እኔ ነበርኩ” ሲል ተርጉሞአል። (አት፣ ሞፋት፣ ቻብዊ፣ ሲኢ፣ የ1954 ትርጉም እና የ1980 ትርጉም ተመሳሳይ ሐሳብ ያስተላልፋሉ።)
በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር የሚስማማው የትኛው አተረጓጎም ነው? ኢየሱስ መልስ የሰጠበት የአይሁዳውያን ጥያቄ (ቁጥር 57) ዕድሜን እንጂ ማንነትን የሚመለከት አልነበረም። ኢየሱስ የሚሰጠው መልስ ስለማንነቱ ሳይሆን ስለዕድሜው የሚገልጽ መሆን ይኖርበታል። ያም ሆኖ መንፈስ ቅዱስን ኤጎ ኤይሚ በሚል የማዕረግ ስም ለመጥራት የተደረገ ሙከራ አለመኖሩን ማስተዋል ይገባል።
በኤ ቲ ሮበርትሰን የተዘጋጀው ኤ ግራመር ኦቭ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት ኢን ዘ ላይት ኦቭ ሂስቶሪካል ሪሰርች (የግሪክኛ አዲስ ኪዳን ሰዋስው በታሪካዊ ምርምር ብርሃን) እንዲህ ይላል:- “ግሡ [ኤይሚ ] . . . እንደማንኛውም ግሥ ተሳቢ ሆኖ በመግባት መኖርን የሚያመለክትበት ጊዜ አለ። ይህንንም [ከኤጎ ኤይሚ ] መረዳት ይቻላል። (ዮሐ. 8:58)”—ናሽቪል፣ ቴነሲ፤ 1934፣ ገጽ 394
በተጨማሪ የአዓት የ1984 ባለማጣቀሻ እትም ተጨማሪ ክፍል፣ ገጽ 1582, 1583 ተመልከት።
ሥራ 20:28:-
እንዲህ ይላል:- “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ኒአባ፣ ጀባ በተመሳሳይ ቃላት ይጠቀማሉ።) በእንግሊዝኛው አዓት ግን የቁጥሩ የመጨረሻ ክፍል “በገዛ [ልጁ] ደም” ይላል። (ቱኢቨ በተመሳሳይ መንገድ ተርጉሞታል። ሪስ የ1953 እትም “በገዛ ደሙ” ቢልም የ1971 እትም “በገዛ ልጁ ደም” ይላል። ሮዘ እና ዴር “በራሱ ደም” ይላሉ። የ1980 ትርጉም “ጌታ በገዛ ደሙ የዋጃትን” ይላል።)
“የልጁ [የአምላክ ልጅ] የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” ከሚለው ከ1 ዮሐንስ 1:7 ቃል ጋር የሚስማማው የትኛው አተረጓጎም ነው? (በተጨማሪ ራእይ 1:4–6ን ተመልከት።) በዮሐንስ 3:16 ላይ እንደተገለጸው አምላክ ሕይወት እንድናገኝ ራሱ ሰው ሆኖ መጣ ወይስ አንድያ ልጁን ላከ?
በተጨማሪ የአዓት የ1984 ባለማጣቀሻ እትም ተጨማሪ ክፍል ገጽ 1580 ተመልከት።
ሮሜ 9:5:-
“አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።” (ጀባ፣ ኪጄ፣ ዱዌይ እንዲሁም የ1980 ትርጉም በተመሳሳይ ተርጉመውታል።) ይሁን እንጂ በአዓት የጥቅሱ የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ይነበባል:- “ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ:- ከሁሉ በላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም የተባረከ ይሁን፤ አሜን” (ሪስ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ኒአባ፣ ሞፋት ከአዓት ጋር በሚመሳሰል አነጋገር ይጠቀማሉ።)
ይህ ጥቅስ ክርስቶስ “ከሁሉ በላይ” እንደሆነና በዚህም ምክንያት እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ይገልጻል ወይስ እግዚአብሔርና ክርስቶስ የተለያዩ እንደሆኑና እግዚአብሔር “ከሁሉ በላይ” እንደሆነ ይናገራል? እግዚአብሔር ከክርስቶስ ኢየሱስ የተለየ መሆኑን ከገለጸ በኋላ አንባቢው “እግዚአብሔርን እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” እንዲያከብር ከሚያሳስበው ከሮሜ 15:5, 6 ጋር የሚስማማው የትኛው የሮሜ 9:5 አተረጓጎም ነው? (በተጨማሪም 2 ቆሮንቶስ 1:3 እና ኤፌሶን 1:3ን ተመልከት።) በተቀረው የሮሜ ምዕራፍ 9 ክፍል የተጻፈውን ተመልከት። ቁጥር 6–13 የአምላክ ዓላማ መፈጸም የተመካው በዘር ውርሻ ላይ ሳይሆን በአምላክ ፈቃድ ላይ እንደሆነ ይገልጻል። ቁጥር 14–18 አምላክ ከሁሉ በላይ መሆኑን ለማጉላት በዘጸአት 9:16 ላይ የተመዘገበውንና ለፈርዖን የተሰጠውን የአምላክ መልእክት ይገልጻል። በቁጥር 19–24 የአምላክ የበላይነት አንድ ሸክላ ሠሪ ከሚሠራቸው የሸክላ ዕቃዎች ላይ ባለው ሥልጣን ተመስሏል። ስለዚህ በቁጥር 5 ላይ “ከሁሉ በላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም የተባረከ ይሁን፤ አሜን” የሚለው አገላለጽ ምንኛ ተገቢ ነው!—አዓት
ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ሮሜ 9:5 አከራካሪ ነው። . . . አገላለጹ የሚያመለክተው ለክርስቶስ ነው ማለቱ ቀላልና ከቋንቋም ሥርዓት አኳያ ፍጹም የሚቻል ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ጥቅሱ ‘የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ፣ ክርስቶስ ለዘላለም የተባረከ ይሁን፣ አሜን’ ማለት ይኖርበታል። ይህም ቢሆን ክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርይ ያለው መሆኑን ያመለክታል እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንደሆነ አያመለክትም። ምክንያቱም ከቴኦስ በፊት ማንነትን የሚያመለክት ቃል አልገባም። . . . ከዚህ ይበልጥ ምክንያታዊ የሚሆነው መግለጫው ለእግዚአብሔር የተነገረ የውዳሴ ቃል ነው የሚለው ነው።”—(ግራንድ ራፒድስ፣ ሚችጋን፣ 1976)፣ ከጀርመንኛ የተተረጐመ፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 80
በተጨማሪ የአዓት የ1984 ባለማጣቀሻ እትም ተጨማሪ ክፍል ገጽ 1580, 1581 ተመልከት።
ኪጄ እንዲህ ይላል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆንን እንደ ቅሚያ አልቆጠረውም።” (ዱዌይ በተመሳሳይ ቃላት ተርጉሞታል። ጀባ ደግሞ “ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን እኩልነት የሙጥኝ አላለም” ይላል። የ1954 ትርጉም “ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም” ይላል።) ይሁን እንጂ በአዓት ላይ የዚህ ጥቅስ የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ይላል:- “እርሱ በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆንን ለመቀማት [በግሪክኛ ሐርፓግሞን ] አላሰበም።” (ሪስ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ኒአባ ከዚህ ጋር የሚመሳሳል ሐሳብ ያስተላልፋሉ።)
ከጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር የሚስማማው የትኛው አተረጓጎም ነው? ቁጥር 5 ክርስቲያኖች እዚህ ላይ በተገለጸው ጉዳይ ረገድ ክርስቶስን እንዲመስሉ ይመክራቸዋል። “ከአምላክ ጋር እኩል መሆንን” “እንደ ቅሚያ” ሳይሆን እንደ መብታቸው አድርገው እንዲመለከቱ ይመክራልን? በፍጹም አይመክርም። ከዚህ ይልቅ ‘ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆንን ለመቀማት ያላሰበውን’ ክርስቶስን መምሰል ይችላሉ። (አዓት ) (ከዘፍጥረት 3:5 ጋር አወዳድር።) እንዲህ የመሰለው አተረጓጎም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ሲል ከተናገረው ጋር ይስማማል።—ዮሐንስ 14:28
ዘ ኤክስፖዚተርስ ግሪክ ቴስታመንት እንዲህ ይላል:- “[ሐርፖዞ ] ወይም ከዚህ ቃል በእርባታ የተገኙ ሌሎች ቃሎች [ሐርፖግሞንን ጨምሮ] ‘ንብረት አድርጎ መያዝን፣’ ‘ባለቤት መሆንን’ ያመለከተበት አንድም ቦታ አናገኝም። በሁሉም ቦታዎች ‘መውሰድ፣ ’ ‘በጉልበት መንጠቅ’ የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ ‘መውሰድ’ ከሚለው ትርጉም ተንሸራትቶ ‘ይዞ መኖር’ የሚል የተለየ ትርጉም መስጠት አይቻልም።”—(ግራንድ ራፒድስ፣ ሚችጋን፤ 1967)፣ በደብልዩ ሮበርትሰን ኒኮል የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 436, 437
ኪጄ እንዲህ ይላል:- “የአምላክ [በግሪክኛ ቴኦቴቶስ ] ሙላት በእርሱ [በክርስቶስ] በአካል ተገልጦ ይኖራል።” (ኒኢ፣ ሪስ፣ ጀባ፣ ኒአባ፣ ዱዌይ ተመሳሳይ ሐሳብ ያስተላልፋሉ።) ይሁን እንጂ አዓት እንዲህ ይላል:- “የመለኮታዊው ባሕርይ ሙላት በአካል የሚኖረው በእርሱ ነው።” (አት፣ ዌይ፣ ቻኬዊ “አምላክ” ከማለት ይልቅ “የአምላክ ባሕርይ” ይላሉ። የ1954 እና የ1980 ትርጉሞች “መለኮት” ይላሉ። ከ2 ጴጥሮስ 1:14 ጋር አወዳድር።)
በእርግጥ ሁሉም ሰዎች በቆላስይስ 2:9 ላይ ለሚገኘው ሐሳብ አንድ ዓይነት ትርጉም አይሰጡም። ሆኖም በመንፈስ አነሣሽነት ከተጻፈው ከቆላስይስ ደብዳቤ ቀሪ ክፍል ጋር የሚስማማው የትኛው አተረጓጎም ነው? ክርስቶስ መለኮትነት የኖረው በራሱ ወይም የሥላሴ አንድ ክፍል በመሆኑ ነው ወይስ በእርሱ የሚኖረውን “ሙላት” ያገኘው ከሌላ ወገን ስለተሰጠው? ቆላስይስ 1:19 በክርስቶስ ሙላት የኖረው ‘አብ ስለፈቀደ’ እንደሆነ ይገልጻል። (ኪጄ፣ ዱዌይ ) ኒኢ ደግሞ ‘በአምላክ ምርጫ’ እንደሆነ ይገልጻል።
በዚያው በቆላስይስ 2:9 ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንመልከት። በቁጥር 8 ላይ አንባቢዎቹ ፍልስፍናንና የሰዎችን ወጐች በሚደግፉ ሰዎች እንዳይሳሳቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ” በክርስቶስ ውስጥ “እንዳለ” ተነግሯቸው እነርሱም ‘በእርሱ ውስጥ እንዲኖሩ’ እና ‘ሥር እንዲሰዱ፣ እንዲገነቡና በእምነት እንዲጸኑ’ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ቁጥር 3, 6, 7) ውድ የሆነው “ሙላት” የሚገኘው ሰብዓዊ ፍልስፍና ከሚያመነጩ ሰዎች ወይም ከአስተማሪዎች ዘንድ ሳይሆን በክርስቶስ ውስጥ ነው። እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ውስጥ የነበረው “ሙላት” ክርስቶስን እግዚአብሔር አድርጎታል ማለቱ ነበርን? በቆላስይስ 3:1 ላይ ክርስቶስ “በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” ስለሚል እንዲህ ማለቱ አልነበረም።—ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ቱኢቨ፣ ኒአባ ተመልከት።
በሊዴል እና ስኮት የተዘጋጀው ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (ግሪክኛ–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት) በሚለው መሠረት ቴኦቴስ (ቴኦቴቶስ የተባለው ቃል የተገኘበት ቴኦቶስ ባለቤት ሆኖ ሲገባ) “መለኮት” ወይም “መለኮታዊ ባሕርይ” የሚል ትርጉም አለው። (ኦክስፎርድ፣ 1968፣ ገጽ 792) የሰው ልጆች በሙሉ “ሰብዓዊነትን” ወይም “ሰብዓዊ ባሕርይ” የሚካፈሉ መሆናቸው ሁሉም እኩል ዕድሜ ወይም እኩልነት እንዲኖራቸው እንደማያደርግ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስም “መለኮት” መሆኑ ወይም “መለኮታዊ ባሕርይ” ያለው መሆኑ ከአባቱ ጋር እኩል አያደርገውም፤ እንዲሁም እንደአባቱ ዘላለማዊ መሆኑን አያመለክትም።
ቲቶ 2:13:-
“የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን አምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን።” (ተመሳሳይ የቃላት አገባብ በሪስ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ጀባ ትርጉሞች እንዲሁም በ1980 ትርጉም ላይ ይገኛል።) አዓት ግን “የተባረከውን ተስፋችንን፣ የታላቁን አምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብራማ መገለጥ ስንጠብቅ” በማለት ይተረጉማል። (ኒአባ ተመሳሳይ አተረጓጎም አለው።)
‘እግዚአብሔር አብና መድኃኒታችንም ክርስቶስ ኢየሱስ’ ከሚለው የቲቶ 1:4 አገላለጽ ጋር የሚስማማው የትኛው አተረጓጎም ነው? ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክን አዳኝ ወይም መድኃኒት ብለው ቢጠሩም ይህ ጥቅስ ግን አምላክ የመድኃኒት ምክንያት ባደረግልን በክርስቶስ ኢየሱስና በራሱ መካከል ልዩነት መኖሩን ያመለክታል።
አንዳንዶች ቲቶ 2:13 ክርስቶስ እግዚአብሔርም አዳኝም እንደሆነ ያመለክታል ብለው ይከራከራሉ። ሪስ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ጀባ ቲቶ 2:13ን ክርስቶስ እግዚአብሔርና አዳኝ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ይተረጉሙታል። 2 ተሰሎንቄ 1:12ን በሚተረጉሙበት ጊዜ ግን ይህንን አተረጓጎም አይከተሉም። ሔንሪ አልፎርድ ዘ ግሪክ ቴስታመንት በተባለው መጽሐፍ:- “[በእግዚአብሔርና በክርስቶስ መካከል ልዩነት እንዳለ የሚያሳይ የቲቶ 2:13 አተረጓጎም] ዓረፍተ ነገሩ የሚጠይቀውን የሰዋስው ሕግጋት በሙሉ እንደሚያሟላ እቀበላለሁ። ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ከሐዋርያው የአጻጻፍ ስልት ጋር በቅርጹም ሆነ በቃሎቹ አገባብ ይስማማል” ብለዋል።—(ቦስተን፣ 1877)፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 421
በተጨማሪ የአዓት የ1984 ባለማጣቀሻ እትም ተጨማሪ ክፍል ገጽ 1581, 1582 ተመልከት።
“ስለ ልጁ . . . :- አምላክ ሆይ፣ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል . . . ይላል።” (ኪጄ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ዱዌይ፣ ጀባ፣ ኒአባ፣ ሪስ እንዲሁም የ1980 ትርጉም ተመሳሳይ አተረጓጎም አላቸው።) አዓት ግን እንዲህ ይላል:- “ስለ ወልድ ግን ‘እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ዙፋንህ ነው’ ይላል።” (አት፣ ሞፋት፣ ትሴ፣ ባይ ይህንን የመሰለ ሐሳብ ያስተላልፋሉ።)
በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር የሚስማማው የትኛው አተረጓጎም ነው? ከዚህ ጥቅስ ቀደም ሲል ያሉት ቁጥሮች እግዚአብሔር ራሱ እንደሚናገር እንጂ ለእግዚአብሔር እንደተነገረ አያመለክቱም። ከቁጥር 8 ቀጥሎ ያለው ቁጥር ደግሞ “እግዚአብሔር አምላክህ” ይላል። ይህም ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ልዑል አምላክ ሳይሆን ይህን ልዑል አምላክ ስለሚያመልክ አንድ አካል እንደሆነ ያመለክታል። ዕብራውያን 1:8 የተጠቀሰው ከመዝሙር 45:6 ነው። ይህ ጥቅስ በመጀመሪያ የተነገረው የእስራኤል ሰብዓዊ ንጉሥ ለነበረ ሰው ነው። የዚህ መዝሙር ጸሐፊ ይህ ሰብዓዊ ንጉሥ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ነው ብሎ እንዳላሰበ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ መዝሙር 45:6 ሪስ “መለኮታዊ ዙፋንህ” ይላል። (ኒኢ “ዙፋንህ እንደ እግዚአብሔር ዙፋን ነው” ይላል። ጁፓ “ከእግዚአብሔር የተሰጠህ ዙፋን” ይላል።) መዝሙር 45 በመጀመሪያ ደረጃ የተነገረለት ንጉሥ ነው ተብሎ የሚታሰበው ሰሎሞን “በይሖዋ ዙፋን ላይ” እንደተቀመጠ ተገልጿል። (1 ዜና 29:23 አዓት ) ዳንኤል 7:13, 14 እና ሉቃስ 1:32 የክርስቶስ “ዙፋን” ወይም የክርስቶስ ንግሥና ምንጩና መሠረቱ እግዚአብሔር ከመሆኑ ጋር በመስማማት እግዚአብሔር ይህን የንግሥና ሥልጣን እንደሰጠው ያመለክታሉ።
ከመዝሙር 45:6, 7 ስለተጠቀሰው ዕብራውያን 1:8, 9 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ቢ ኤፍ ዌስትኮት እንዲህ በማለት ይገልጻሉ:- “የሰባ ሊቃናት ትርጉም ሁለት ዓይነት አተረጓጎሞችን ይቀበላል። [ሆ ቴኦስ ] በሁለቱም ቦታዎች እንደ መጠሪያ ቃል ተደርጎ ሲወሰድ (ዙፋንህ፣ አምላክ ሆይ፣ . . . ስለዚህ አምላክ ሆይ፣ አምላክህ . . . ) ወይም እንደ ዐረፍተ ነገሩ ባለቤት (ወይም እንደ ተሳቢ) ተወስዶ በመጀመሪያው ቦታ ላይ (እግዚአብሔር ዙፋንህ ነው፣ ወይም ዙፋንህ እግዚአብሔር ነው . . . ) በሁለተኛው ቦታ ላይ የተጠቀሰው [ሆ ቴኦሱ ] ደግሞ (ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ . . . ) ሊባል ይችላል። . . . በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ንጉሡ [ኤሎሂም ] ተብሎ ሊጠራ አይችልም። ስለዚህ በሰባ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ የተጠቀሰው [ሆ ቴኦስ ] በመጠሪያ ቃልነት አገልግሏል ብሎ ማሰብ አይቻልም። በዚህ ምክንያት በአጠቃላይ በመጀመሪያው ሐረግ ላይ እግዚአብሔር ዙፋንህ ነው (ወይም ዙፋንህ እግዚአብሔር ነው ) ብሎ መተርጎም የተገባ ይሆናል። ይህም ማለት ‘መንግሥትህ የማይናወጥ ዓለት በሆነው እግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ነው’ ማለት ይሆናል።”—ዘ ኤፒስትል ቱ ዘ ሂብሩስ (ለንደን፣ 1889)፣ ገጽ 25, 26
የ1879 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲህ ይላል:- “በሰማይ የሚመሰክሩ ሶስት ናቸውና እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስም። እሌህ ሶስትም አንድ ናቸው። በምድርም የሚመሰክሩ ሶስት ናቸው እርሳቸውም መንፈስ ውኃም ደምም። ሶስቱም ባንድ ይገድማሉ።” (ይህ ሥላሴን የሚደግፍ አተረጓጎም በዱዌይ እና በኪጄ ውስጥ ይገኛል።) ይሁን እንጂ አዓት “በሰማይ አብ ቃልና መንፈስ ቅዱስ፣ እነዚህ ሶስቱ አንድ ናቸው። በምድርም የሚመሰክሩ ሶስት ናቸው” የሚለውን አይጨምርም። (ሪስ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ጀባ፣ ኒአባ እንዲሁም የ1954 እና የ1980 የአማርኛ ትርጉሞች ይህን ሥላሴን የሚደግፍ ጥቅስ አስወጥተዋል።)
ይህን ስለ ሥላሴ የሚናገረውን ምንባብ በተመለከተ የአተረጓጎም ገምጋሚ የሆኑት ኤፍ ኤች ኤ ስክራይቭነር እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “አከራካሪ የሆኑት ቃላት በቅዱስ ዮሐንስ ያልተጻፉ መሆናቸውን ከመናገር ማመንታት የለብንም። እነዚህ ቃላት በመጀመሪያ በቁጥር 8 ላይ እንደ ሃይማኖታዊ ማስጌጫ ሆነው ከሰፈሩበት የኅዳግ ማስታወሻ ወጥተው የተጨመሩት በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ነው። ከላቲን ደግሞ ዘግየት ብለው ወደተጻፉ አንድ ወይም ሁለት የግሪክኛ የብራና መጻሕፍት ተዛወሩ። ከዚያ በኋላ አለቦታቸው በታተሙ የግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ ሰርገው ገቡ።”—ኤ ፕሌይን ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ክርቲስዝም ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (ካምብሪጅ፣ 1883፣ ሦስተኛ እትም)፣ ገጽ 654
በተጨማሪ ጀባ በእነዚህ ቁጥሮች የግርጌ ማስታወሻ ላይ ያሰፈረውንና የአዓት የ1984 ባለማጣቀሻ እትም ተጨማሪ ክፍል ገጽ 1580 ተመ ልከት።
የሥላሴ አማኞች ትምህርታችንን ይደግፋሉ የሚሏቸው ሌሎች ጥቅሶች
ከእነዚህ ጥቅሶች የመጀመሪያው የሚናገረው ስለ ወልድ ብቻ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለ አብና ወልድ ብቻ ነው። አንዳቸውም ቢሆኑ አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን አንድ ላይ ጠቅሰው ሦስቱም አንድ አምላክ መሆናቸውን እንደማይገልጹ ልብ በል።
እዚህ ላይ ኢየሱስ ራሱን ከሞት እንደሚያስነሣ መናገሩ ነበርን? እንዲህ ማለቱስ ሥራ 2:32 “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው” ስለሚል ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። እንዲህ ያለው አመለካከት ኢየሱስን ያስነሳው አብ እንደሆነ እንጂ ወልድ ራሱን እንዳላስነሣ ከሚገልጸው ከገላትያ 1:1 ጋር አይስማማም። ኢየሱስ በሉቃስ 8:48 ላይ ይህን የመሰለ አነጋገር በመጠቀም ሴትዬዋን “እምነትሽ አዳነሽ” ብሏታል። ሴትዬዋ ራስዋን ፈወሰች ማለት ነውን? እምነት በማሳየትዋ ምክንያት የፈወሳት በክርስቶስ በኩል የተገኘው የአምላክ ኃይል ነው። (ሉቃስ 8:46፤ ሥራ 10:38) ኢየሱስም በተመሳሳይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ በመታዘዙ አባቱ እርሱን ከሙታን በማስነሣት የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ምክንያት አግኝቷል። ኢየሱስ በታማኝነት መንገድ ስለተመላለሰ ለራሱ ትንሣኤ ምክንያት ሆኖአል ለማለት ይቻላል።
ኤ ቲ ሮበርትሰን፣ ወርድ ፒክቸርስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል:- “ኢየሱስ ‘በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ’ ያለበትን [ዮሐንስ] 2:19ን እናስታውስ። የአባቱ ኃይል ሳያስፈልገው ራሱን ከሙታን ለማስነሣት እንደሚችል መናገሩ አልነበረም። (ሮሜ 8:11)”—(ኒው ዮርክ፣ 1932)፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 183
ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” ሲል ሁለቱም እኩል መሆናቸውን መናገሩ ነበርን? አንዳንድ የሥላሴ አማኞች እንደዚህ ማለቱ ነው ይላሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በዮሐንስ 17:21, 22 ላይ ስለተከታዮቹ ሲጸልይ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ”፣ “እኛ አንድ እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” ብሏል። በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ ላይ “አንድ” የሚለውን ለመግለጽ የተጠቀመው በዚያው የግሪክኛ ቃል (ሄን ) ነው። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሙሉ የሥላሴ ክፍል አልሆኑም። ነገር ግን አምላክንና ክርስቶስን አንድ በሚያደርጋቸው የዓላማ አንድነት ተካፍለዋል።
የሥላሴን እምነት የሙጥኝ ብለው የሚይዙ ሰዎች እንዴት ባለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
የሥላሴ እምነት አማኞች የሚገኙበት ሁኔታ በጣም አደገኛ ነው። የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ስለመሆኑና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ፈጽሞ የማይስማማ ስለመሆኑ የማያከራክር ማስረጃ አለ። (የቀደሙትን ገጾች ተመልከት።) ይህ ትምህርት የአምላክን ማንነት በተዛባ ሁኔታ ይገልጻል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ብሏል። (ዮሐ. 4:23, 24) ስለዚህ ኢየሱስ አምላክን ‘በእውነት’ ወይም በአምላክ ቃል ከተገለጸው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ የማያመልኩ ሁሉ ‘እውነተኛ አምላኪዎች’ እንዳልሆኑ በግልጽ አመልክቷል። ኢየሱስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ብሏል:- “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።” (ማቴ. 15:6–9) ይህ ቃል ግልጽ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይልቅ የሰዎችን ወግ ለሚደግፉ የሕዝበ ክርስትና አባላት ተመሳሳይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።
የአትናቴዎስ ቀኖና (የእንግሊዝኛው ትርጉም) የሥላሴ ትምህርት “ለመረዳት የሚያዳግት” እንደሆነ ይገልጻል። የዚህ መሠረተ ትምህርት አስተማሪዎች የሥላሴ ትምህርት “ምሥጢር” እንደሆነ ይናገራሉ። ኢየሱስ “የምናውቀውን እናመልካለን” ያለለት አምላክ ከዚህ የተለየ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ዮሐ. 4:22 አዓት ) አንተስ የምታመልከውን አምላክ በትክክል ታውቀዋለህን?
እያንዳንዳችን አሳሳቢ የሆኑ ጥያቄዎች ተደቅነውብናል። እውነትን ከልባችን እንወዳለንን? በእርግጥ ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና ለመመሥረት እንፈልጋለንን? ሁሉም ሰዎች እውነትን ከልብ አይወዱም። ብዙዎቹ ሰዎች ለእውነትና ለአምላክ ካላቸው ፍቅር የዘመዶቻቸውንና የጓደኞቻቸውን ፍቅር አስበልጠዋል። (2 ተሰ. 2:9–12፤ ዮሐ. 5:39–44) ነገር ግን ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ባቀረበው ልባዊ ጸሎት ላይ እንደገለጸው:- “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” ብሏል። (ዮሐ. 17:3 የ1980 ትርጉም ) መዝሙር 144:15 ደግሞ በአዓት “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” ይላል።
አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-
‘በሥላሴ ታምናላችሁ?’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህ እምነት በጊዜአችን በጣም ተስፋፍቶአል። ይሁን እንጂ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ይህን አምነት እንዳላስተማሩ ያውቁ ነበር? ስለዚህ እኛ የምናመልከው ኢየሱስ አምልኩት ያለውን አምላክ ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ኢየሱስ ያስተምር በነበረበት ጊዜ ከሁሉ ይበልጣል ያለው ትእዛዝ ይህ ነው። . . . (ማር. 12:28–30)’ (2) ‘ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነኝ ብሎ አያውቅም። እንዲህ ብሎአል . . . (ዮሐ. 14:28)’ (3) ‘ታዲያ የሥላሴ እምነት ከየት መጣ? እውቅ የሆኑ ኢንሳይክሎፔድያዎች ስለ ሥላሴ አመጣጥ ምን እንደሚሉ ልብ ይበሉ። (ገጽ 404, 405ን ተመልከት።)’
ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘የለም አናምንም። ከእዚህ እምነት ጋር ፈጽሞ ላስማማ የማልችላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ከእነዚህ ጥቅሶች መካከል አንዱ ይህ ነው:- . . . (ማቴ. 24:36) ምናልባት እርስዎ ሊያብራሩልኝ ይችሉ ይሆናል።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ወልድ ከአብ ጋር እኩል ከሆነ ወልድ የማያውቃቸውን ነገሮች እንዴት አብ ሊያውቅ ቻለ?’ ይህ የሚናገረው ወልድ ስለነበረው ሰብዓዊ ባሕርይ ነው ብለው ከመለሱ እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- (2) ‘ታዲያ መንፈስ ቅዱስስ ለምን ሳያውቅ ቀረ?’ (ሰውዬው ስለ እውነት ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት ካለው ቅዱሳን ጽሑፎች ስለአምላክ የሚናገሩትን አሳየው።) (መዝ. 83:18፣ ዮሐ. 4:23, 24)
ሌላ አማራጭ:- ‘በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። በሥላሴ ግን አናምንም። ለምን ቢባል ምክንያቱም የእኛ እምነት ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ከነበረው እምነት ጋር አንድ ነው። እስቲ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን ልብ ይበሉ . . . (ማቴ. 16:15–17)’
ተጨማሪ ሐሳብ:- ‘ሰዎች ለሥላሴ የሚሰጡት ትርጉም ይለያያል። ሥላሴ ሲሉ ምን ማለትዎ እንደሆነ ቢያብራሩልኝ ለጥያቄዎ የተሻለ መልስ ለመስጠት እችል ይሆናል።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ። ሆኖም እኔ የማምነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ብቻ ነው። “ሥላሴ” የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይተው ያውቃሉ? . . . (የእንግሊዝኛ አዓት ይዘህ ከሆነ ኮንኮርዳንሱን አሳየው።) ክርስቶስስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል? . . . አዎ፣ እኛም በክርስቶስ እናምናለን። በኮንኮርዳንሱ ላይ “ክርስቶስ” በሚለው ሥር ከተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ አንዱ ማቴዎስ 16:16 ነው። (አንብበው) እኔም የማምነው ይህን ነው።’
ወይም እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ (ሰውዬው ዮሐንስ 1:1ን ከጠቀሱ):- ‘ይህን ጥቅስ አውቀዋለሁ። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ኢየሱስ “እግዚአብሔር” ነው ይላል፤ ሌሎች ትርጉሞች ደግሞ “አምላክ” ወይም በእንግሊዝኛ “a god” ነው ይላሉ። እንዲህ የሚሉት ለምንድን ነው?’ (1) ‘የሚቀጥለው ቁጥር “ከእግዚአብሔር ጋር ” ነበር ስለሚል ይሆን?’ (2) ‘እዚያው ዮሐንስ 1:18 ላይ በሚገኘው ሐሳብ ምክንያት ሊሆን ይችላል?’ (3) ‘ኢየሱስ ራሱ የሚያመልከው አምላክ ይኖር ይሆን ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? (ዮሐ. 20:17)’
‘በክርስቶስ መለኮትነት ታምናለህ?’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘አዎ፣ በእርግጥ አምናለሁ፤ ነገር ግን ስለ “ክርስቶስ መለኮትነት” ሲናገሩ እርስዎ በአእምሮዎ የያዙትን የመሰለ እምነት ላይኖረኝ ይችላል።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘እንደዚህ የምልበት ምክንያት ምንድን ነው? በኢሳይያስ 9:6 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ “ኃያል አምላክ” ተብሏል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ’ የተባለው አብ ብቻ ነው።’ (2) ‘በተጨማሪም ኢየሱስ በዮሐንስ 17:3 ላይ ስለ አባቱ ሲናገር ‘ብቻህን እውነተኛ አምላክ’ የሆንህ ብሏል። ስለዚህ ኢየሱስ የእውነተኛው አምላክ ነፀብራቅ ከመሆን ሊያልፍ አይችልም።’ (3) ‘አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ምን ነገር ይፈለግብናል? (ዮሐ. 4:23, 24)’