መስተዋቱ ምን ያሳያል?
በመስተዋት ውስጥ ተመልከት። ምን ይታይሃል? አንዳንድ ጊዜ ለቅጽበት ያህል መስተዋት መልከት ስታደርግ በመልክህ ላይ ያለ አንድ አሳፋሪ ነገር ስለሚያሳይህ ሌሎች ሳያዩህ ለማስተካከል በመቻልህ በጣም ትደሰታለህ።
መጽሐፍ ቅዱስ ከመስተዋት ጋር በጣም ይመሳሰላል። በአምላክ ፊት ስላለን ዋጋ ከተገቢው በላይ ከፍ አድርገን ወይም በጣም ዝቅ አድርገን እንዳናስብ ስለሚጠብቀን ስለ ራሳችን ሐቀኛ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል። (ማቴዎስ 10:29–31፤ ሮሜ 12:3) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልናስተካክላቸው የሚገቡንን በንግግራችን፣ በድርጊታችን ወይም በዝንባሌአችን ያሉብንን ጉድለቶች ቁልጭ አድርጎ ሊያሳየን ይችላል። በዚህ ጊዜ መስተዋቱ የሚያሳየውን ጉድለት ችላ ብለህ ታልፈዋለህን?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፣ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል” በማለት ጽፏል።—ያዕቆብ 1:23, 24
በተቃራኒው ግን “ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት” በማለት ያዕቆብ ስለ ሌላ ዓይነት ሰው ይናገራል። (ያዕቆብ 1:25) “ተመልክቶ” የሚለው የግሪክኛው ቃል ለመመልከት ከፊት ለፊት መቆም ወይም ወደፊት መጎንበስ ማለት ነው። “በቅጽበት ዓየት ከማድረግ የበለጠ ነገር ማድረግን የሚጠቁም ነው” በማለት ቲኦሎጂካል ዲክሺነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይናገራል። ቃሉ አንድን የተደበቀ ዕቃ ለማግኘት የሚደረግ ጥንቃቄ የተሞላበት ፍለጋ ያመለክታል። “ምንም እንኳ ለማየት ወይም ትርጉሙን ወዲያው ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆንበትም ተመልካቹ ሊያየው የሚፈልገው አንድ አስፈላጊ ነገር አለ” በማለት አር ቪ ጂ ታስከር የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ጽፈዋል።
ታዲያ ራስህን በአምላክ ቃል መስተዋት በጥንቃቄ መርምረህ ከሚጠይቅብህ ነገር ጋር ተስማምተህ ትኖራለህን? ያዕቆብ በመቀጠል “ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ ይሆናል” በማለት ጽፏል።—ያዕቆብ 1:25