የራስን ጥቅም የመሠዋትን መንፈስ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
“ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ።”—ማቴ. 16:24
1. ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሲል የራሱን ፍላጎትና ምቾት መሥዋዕት ያደርግ ነበር። (ዮሐ. 5:30) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ለአምላክ ታማኝ በመሆን፣ የራሱን ጥቅም ሙሉ በሙሉ ከመሠዋት ወደኋላ እንደማይል አሳይቷል።—ፊልጵ. 2:8
2. የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?
2 እኛም የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት ይኖርብናል። የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አለው የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው? በአጭር አነጋገር፣ ሌሎችን ለመርዳት ሲል የራሱን ጥቅም ለመተው ፈቃደኛ የሆነ ሰው ነው። በሌላ አባባል ራስ ወዳድ ያልሆነ ሰው ማለት ነው። (ማቴዎስ 16:24ን አንብብ።) ራስ ወዳድ ካልሆንን፣ የራሳችንን ሳይሆን የሌሎችን ስሜትና ምርጫ እናስቀድማለን። (ፊልጵ. 2:3, 4) ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የአምልኳችን ዋነኛ መሠረት እንደሆነ አስተምሯል። ይህ የሆነው እንዴት ነው? የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዲኖረን ከሚያነሳሱን ነገሮች አንዱ ክርስቲያናዊ ፍቅር ነው፤ እንዲህ ያለው ፍቅር ደግሞ የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መለያ ነው። (ዮሐ. 13:34, 35) የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚያሳይ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አባል በመሆናችን ያገኘናቸውን በረከቶች እስቲ ለማሰብ ሞክር!
3. የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈሳችን ቀስ በቀስ እንዲዳከም የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
3 ይሁንና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈሳችን ቀስ በቀስ እንዲዳከም የሚያደርግ አንድ ጠላት አለን። ይህ ጠላት የራስ ወዳድነት ምኞት ነው። አዳምና ሔዋን ራስ ወዳድ መሆናቸው የታየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ሔዋን በራስ ወዳድነት ምኞት ተነሳስታ እንደ አምላክ ለመሆን ፈለገች። ባሏም ከይሖዋ ይልቅ እሷን ለማስደሰት በመፈለጉ ራስ ወዳድ መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍ. 3:5, 6) ዲያብሎስ፣ አዳምንና ሔዋንን ከእውነተኛው አምልኮ እንዲርቁ ካደረገ በኋላም ሰዎች የራስ ወዳድነትን ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ መገፋፋቱን ቀጥሏል። ኢየሱስን በፈተነው ጊዜ እንኳ በዚህ ዘዴ ለመጠቀም ሞክሯል። (ማቴ. 4:1-9) በዘመናችንም ሰይጣን፣ ብዙ ሰዎች የራስ ወዳድነት ዝንባሌን በተለያዩ መንገዶች እንዲያሳዩ በማነሳሳት እያሳሳታቸው ነው። በዓለም ላይ ተስፋፍቶ ያለው የራስ ወዳድነት መንፈስ ወደ እኛም ሊጋባ ስለሚችል ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው።—ኤፌ. 2:2
4. (ሀ) የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎችን በአሁኑ ጊዜ ማስወገድ እንችላለን? አብራራ። (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
4 የራስ ወዳድነትን ባሕርይ ብረትን ከሚያበላሸው ዝገት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። ብረት፣ ለእርጥበት አዘል አየር ሲጋለጥ መዛግ ይጀምራል። ዝገቱ የከፋ ጉዳት የሚያስከትለው ግን ችላ ከተባለ ነው፤ ምክንያቱም ዝገቱ እየተባባሰ ሊሄድና በዕቃው ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ አልፎ ተርፎም ዕቃውን ከጥቅም ውጭ ሊያደርገው ይችላል። በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ፍጹም መሆን የማይቻል ነገር ከመሆኑም ሌላ የራስ ወዳድነት ዝንባሌያችንን ማስወገድ አንችልም፤ ያም ቢሆን እነዚህ ነገሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ መገንዘብና የራስ ወዳድነት ዝንባሌን ለማሸነፍ መታገላችንን መቀጠል አለብን። (1 ቆሮ. 9:26, 27) ታዲያ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በውስጣችን እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስን ይበልጥ ማዳበር የምንችለውስ እንዴት ነው?
የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዳለን ለመመርመር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም
5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መስተዋት ነው የምንለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በውስጣችን መኖሩን ስንመረምር ምን እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል?
5 መልካችንን ለማየት መስተዋት እንደምንመለከት ሁሉ ውስጣዊ ማንነታችንን ለመመርመርና ጉድለቶች ካሉን ለማስተካከልም መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም እንችላለን። (ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።) ይሁን እንጂ በመስተዋት ራሳችንን ማየታችን በሰውነታችን ላይ ያሉ ነገሮችን ለማስተካከል ሊረዳን የሚችለው መስተዋቱን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መስተዋቱን በጨረፍታ ብቻ አየት አድርገን የምንሄድ ከሆነ በሰውነታችን ላይ ያለውን ትንሽ ሆኖም ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እንከን ልብ ሳንል ልንቀር እንችላለን። ወይም ደግሞ መስተዋቱን ከፊት ለፊቱ ሆነን የማናይበት ከሆነ የሚታየን የሌላ ሰው ምስል ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም እንደ ራስ ወዳድነት ያለ ድክመት ይኖርብን እንደሆነ ለማወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ራሳችንን እንመረምር ይሆናል፤ ይህን ስናደርግ ግን የአምላክን ቃል ገረፍ ገረፍ አድርገን የምናነብብ ወይም አንድ ነገር ስናነብ ከራሳችን ይልቅ በሌሎች ድክመት ላይ የምናተኩር ከሆነ ከምናነብበው ነገር ጥቅም ማግኘት አንችልም።
6. ፍጹም በሆነው ሕግ ‘መጽናት’ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ የአምላክን ቃል አዘውትረን እንዲያውም በየቀኑ እያነበብንም እንኳ በውስጣችን እያቆጠቆጠ ያለውን የራስ ወዳድነት ስሜት ማየት ሊያቅተን ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ያዕቆብ ስለ መስተዋት በተናገረው ምሳሌ ላይ ያለው ሰው ችግር፣ ራሱን በመስተዋቱ ውስጥ በደንብ አለማየቱ አይደለም። ያዕቆብ፣ ሰውየው ‘ራሱን እንዳየ’ ጽፏል። እዚህ ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል በትኩረት መመልከትን ወይም በጥንቃቄ መመርመርን የሚያመለክት ነው። ታዲያ የዚህ ሰው ችግር ምን ነበር? ያዕቆብ ቀጥሎ እንደተናገረው ሰውየው “ራሱን ካየ በኋላ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል።” ሰውየው ፊቱ ላይ የተመለከተውን ጉድለት ለማስተካከል እርምጃ ሳይወስድ መስተዋቱን ትቶ ይሄዳል። በሌላ በኩል ግን ‘ፍጹሙን ሕግ በትኩረት በመመልከት’ ብቻ ሳይወሰን ‘በዚያ የሚጸና ሰው’ ስኬታማ ይሆናል። ይህ ሰው ፍጹም የሆነውን የአምላክ ቃል ከመርሳት ይልቅ በዚያ ይጸናል ወይም ትምህርቱን ሁልጊዜ ተግባራዊ ያደርጋል። ኢየሱስ “በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብም ይህንን ነጥብ ይደግፋል።—ዮሐ. 8:31
7. የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በውስጣችን መኖሩን ለመመርመር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
7 እንግዲያው የራስ ወዳድነት ስሜትን ገና ከጅምሩ ለመዋጋት፣ መጀመሪያ የአምላክን ቃል በትኩረት ማንበብ ይኖርብሃል። ይህን ማድረግህ፣ ማስተካከያ የሚያሻቸውን ነገሮች ለማስተዋል ይረዳሃል። ይሁንና በዚህ ብቻ መወሰን የለብህም። በአምላክ ቃል ላይ ጥልቅ ምርምር አድርግ። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በደንብ ከተረዳኸው በኋላ አንተም ታሪኩ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ በማሰብ ራስህን እንዲህ እያልህ ጠይቅ፦ ‘እኔ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመኝ ምን አደርግ ነበር? ትክክለኛ የሆነውን እርምጃ እወስድ ነበር?’ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ደግሞ ባነበብከው ነገር ላይ ካሰላሰልክበት በኋላ በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት ማድረግህ ነው። (ማቴ. 7:24, 25) የንጉሥ ሳኦልንና የሐዋርያው ጴጥሮስን ታሪክ መመርመራችን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ ይዘን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ከንጉሥ ሳኦል የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት
8. ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሲቀባ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? ይህንንስ ያሳየው እንዴት ነው?
8 የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የሳኦል ታሪክ፣ የራስ ወዳድነት ምኞት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈሳችንን ቀስ በቀስ ሊያጠፋብን የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል። ሳኦል፣ ንጉሥ ሆኖ ሲቀባ ቦታውን የሚያውቅና ትሑት ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 9:21) ንግሥናውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት እስራኤላውያን ከአምላክ የተሰጠውን ሥልጣን ባለማክበራቸው ሊቀጡ እንደሚገባ ሊያስብ ይችል ነበር፤ እሱ ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል። (1 ሳሙ. 10:27) እስራኤላውያን ከአሞናውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት ንጉሥ ሳኦል የአምላክን መንፈስ አመራር በመቀበሉ ሕዝቡ ድል እንዲቀዳጅ አድርጓል። ከዚያም፣ ድሉ የተገኘው በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ በመግለጽ ትሑት መሆኑን አሳይቷል።—1 ሳሙ. 11:6, 11-13
9. ሳኦል የራስ ወዳድነትን አስተሳሰብ ማዳበር የጀመረው እንዴት ነው?
9 ውሎ አድሮ ግን ሳኦል፣ ብረትን እንደሚበላ ዝገት የሆነውን የራስ ወዳድነት አስተሳሰብና የኩራት ዝንባሌ ማዳበር ጀመረ። ንጉሡ፣ አማሌቃውያንን ድል ባደረገበት ወቅት ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ የራሱን ፍላጎት አስቀድሟል። ሳኦል፣ የማረከውን ነገር ልክ አምላክ እንዳዘዘው ማጥፋት ቢገባውም ምርኮው ስላሳሳው ለራሱ ወሰደው። ከዚህም በተጨማሪ በትዕቢት ተነሳስቶ ለራሱ ሐውልት አቆመ። (1 ሳሙ. 15:3, 9, 12) ነቢዩ ሳሙኤል፣ ይሖዋ እንዳዘነበት ሲነግረው ደግሞ ሳኦል የፈጸማቸውን የአምላክ ትእዛዛት በመጥቀስ ድርጊቱን ለማስተባበል የሞከረ ከመሆኑም ሌላ ጥፋቱን በሌሎች ላይ አላከከ። (1 ሳሙ. 15:16-21) ከዚህም በተጨማሪ ሳኦል ኩራተኛ መሆኑ፣ አምላክን ስለማስደሰት ሳይሆን ሰዎች ለእሱ ስላላቸው አመለካከት ይበልጥ እንዲጨነቅ አድርጎታል። (1 ሳሙ. 15:30) ታዲያ እኛስ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈሳችንን ይዘን ለመቀጠል የሳኦልን ታሪክ እንደ መስተዋት መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
10, 11. (ሀ) የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስን ይዘን በመቀጠል ረገድ ከሳኦል ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) የሳኦል ዓይነት መጥፎ አካሄድ ከመከተል መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
10 በመጀመሪያ፣ ከዚህ ቀደም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ስላሳየን ምንጊዜም ይህንን መንፈስ ማሳየታችንን እንደምንቀጥል በማሰብ መዘናጋት እንደሌለብን ከሳኦል ታሪክ እንማራለን። (1 ጢሞ. 4:10) ሳኦል መጀመሪያ ላይ ጥሩ አቋም እንደነበረውና በአምላክ ዘንድ ሞገስ አግኝቶ እንደነበር እናስታውስ፤ ሆኖም የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በውስጡ ማቆጥቆጥ ሲጀምር ይህን ለማስወገድ አልሞከረም። ሳኦል ታዛዥ ባለመሆኑ በመጨረሻ የይሖዋን ሞገስ አጥቷል።
11 ሁለተኛ፣ እያደረግን ባለነው መልካም ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር፣ ማሻሻል የሚገባንን ነገሮች ችላ እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል። አለዚያ መስተዋት ስናይ ፊታችን ላይ ያለውን ቆሻሻ ልብ ሳንል በለበስነው አዲስ ልብስ ላይ ብቻ እንደ ማተኮር ይሆንብናል። እርግጥ ነው፣ እንደ ሳኦል ባከናወንናቸው ነገሮች ከልክ በላይ አንኩራራ ይሆናል፤ ያም ቢሆን እንዲህ ያለውን መጥፎ ጎዳና ወደ መከተል የሚመራንን ማንኛውንም ዝንባሌ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ምክር ሲሰጠን ሰበብ የመደርደር፣ ጥፋታችንን ቀላል የማስመሰል ወይም በሌሎች ላይ የማላከክ ዝንባሌ እንዳይኖረን እንጠንቀቅ። እንግዲያው ከሳኦል በተቃራኒ ምክር ሲሰጠን በደስታ መቀበላችን ምንኛ የተሻለ ነው።—መዝሙር 141:5ን አንብብ።
12. የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ያለን መሆኑ ከባድ ኃጢአት ብንሠራ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
12 ይሁንና ከባድ ኃጢአት ብንሠራ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሳኦል ይበልጥ ያሳሰበው በሌሎች ዘንድ ያለው ስም ነበር፤ ይህም መንፈሳዊ አቋሙን ለማስተካከል ጥረት እንዳያደርግ እንቅፋት ሆኖበታል። ከዚህ በተቃራኒ ግን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ካለን፣ ስህተታችንን መናገር ሊያሳፍረን ቢችልም እንኳ ይህ ሳያግደን አስፈላጊውን እርዳታ እንጠይቃለን። (ምሳሌ 28:13፤ ያዕ. 5:14-16) ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ወንድምን ሁኔታ እንመልከት፤ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ማየት የጀመረው በ12 ዓመቱ ሲሆን ከአሥር ዓመት በላይ በድብቅ ይህን ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ዓይነት ልማድ እንዳለኝ ለባለቤቴና ለሽማግሌዎች መናገር በጣም ከብዶኝ ነበር። ከነገርኳቸው በኋላ ግን ከላዬ ላይ ትልቅ ሸክም የወረደልኝ ያህል ቀለለኝ። የጉባኤ አገልጋይነት መብቴን ሳጣ አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳሳፈርኳቸው ስለተሰማቸው አዝነውብኝ ነበር። ይሁንና የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን እመለከት ከነበረበት ወቅት ይልቅ አሁን በማቀርበው አገልግሎት ይሖዋ ይበልጥ እንደሚደሰት አውቃለሁ፤ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ደግሞ ይህ ነው።”
ጴጥሮስ የራስ ወዳድነት ስሜትን አሸንፏል
13, 14. ጴጥሮስ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዳለው የታየው እንዴት ነው?
13 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ያሠለጥነው በነበረበት ወቅት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 5:3-11) ያም ቢሆን የራስ ወዳድነት ዝንባሌን ለማስወገድ ትግል ማድረግ ነበረበት። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ያዕቆብና ዮሐንስ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከኢየሱስ ጎን በመቀመጥ ትልቅ ቦታ ለማግኘት በጠየቁበት ወቅት ጴጥሮስ በጣም ተቆጥቶ ነበር። ጴጥሮስ ልዩ ሚና እንደሚኖረው ኢየሱስ ስለተናገረ ከክርስቶስ አጠገብ የመቀመጡ መብት ለእሱ ሊሰጥ እንደሚገባ አስቦ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 16:18, 19) ኢየሱስ ግን ያዕቆብንና ዮሐንስንም ሆነ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስተው በወንድሞቻቸው ላይ ‘ሥልጣናቸውን የማሳየት’ ዝንባሌ እንዳይኖራቸው አስጠንቅቋቸዋል።—ማር. 10:35-45
14 ጴጥሮስ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ኢየሱስ ምክር ከሰጠው በኋላም እንኳ ስለ ራሱ ያለውን አመለካከት ለማስተካከል ጥረት ማድረግ አስፈልጎታል። ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ ለጊዜውም ቢሆን ጥለውት እንደሚሸሹ በተናገረ ጊዜ ጴጥሮስ ሌሎቹ ሁሉ ቢተዉት እንኳ እሱ ብቻ በታማኝነት ከጎኑ እንደሚቆም በመናገር ራሱን ከሌሎቹ ከፍ አድርጓል። (ማቴ. 26:31-33) ይሁንና እንዲህ ያለ ከልክ በላይ በራስ የመተማመን መንፈስ ማሳየቱ ተገቢ አልነበረም፤ ምክንያቱም በዚያው ምሽት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት ሳይችል ቀርቷል። ጴጥሮስ፣ ራሱን ለማዳን ሲል ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ክዶታል።—ማቴ. 26:69-75
15. ጴጥሮስ ድክመቶች ቢኖሩበትም በጥቅሉ ሲታይ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል የምንለው ለምንድን ነው?
15 ጴጥሮስ ከራሱ ጋር ትግል ማድረግ የነበረበት ሲሆን በራስ ወዳድነት ስሜት የተሸነፈበት ወቅትም ነበረ፤ ያም ቢሆን ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ጴጥሮስ በግሉ ጥረት በማድረጉና የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ በማግኘቱ የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎቹን ማሸነፍ ችሏል፤ እንዲሁም ከጊዜ በኋላ ራስን የመግዛት ባሕርይና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ የሚያስችል ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ገላ. 5:22, 23) ቀደም ሲል ከተሰናከለበት ፈተና ይበልጥ ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት ችሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰዎች ፊት በገሠጸው ወቅት ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ ትሑት እንደነበረ ያሳያል። (ገላ. 2:11-14) ይህ ከሆነ በኋላም ቢሆንም፣ ጳውሎስ የሰጠው እርማት ሌሎች ለእሱ ያላቸውን አመለካከት እንዳበላሸበት በማሰብ ቂም አልያዘም። ጴጥሮስ፣ ጳውሎስን እንደሚወድደው ተናግሯል። (2 ጴጥ. 3:15) የጴጥሮስ ምሳሌ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስን እንድናዳብር ይረዳናል።
16. አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
16 አንተም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ምን ምላሽ እንደምትሰጥ ቆም ብለህ አስብ። ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በስብከቱ ሥራቸው የተነሳ በታሰሩበትና በተገረፉበት ወቅት “ስለ [ኢየሱስ ስም] ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ተደስተዋል። (ሥራ 5:41) አንተም ስደት ሲደርስብህ፣ ጴጥሮስን ለመምሰልና የራስን ጥቅም የመሠዋትን መንፈስ በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ፈለግ ለመከተል አጋጣሚ እንዳገኘህ አድርገህ ልታስብ ትችላለህ። (1 ጴጥሮስ 2:20, 21ን አንብብ።) እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበርህ ሽማግሌዎች አስፈላጊውን ተግሣጽ በሚሰጡህ ጊዜም ሊረዳህ ይችላል። ምክር ሲሰጥህ ቅር ከመሰኘት ይልቅ የጴጥሮስን ምሳሌ ተከተል።—መክ. 7:9
17, 18. (ሀ) ከመንፈሳዊ ግቦች ጋር በተያያዘ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን? (ለ) በልባችን ውስጥ የራስ ወዳድነት ስሜት እንዳለ ከተገነዘብን ምን ማድረግ እንችላለን?
17 መንፈሳዊ ግቦች ከማውጣት ጋር በተያያዘም ጴጥሮስ ከተወው ምሳሌ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ የምታደርገው ጥረት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዳለህ የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። እንዲህ ያሉ ግቦች ላይ ለመድረስ የምትጣጣረው ከሌሎች ልቀህ ለመታየት በማሰብ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልግሃል። ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎት ለማሻሻል ወይም ለማስፋት የምፈልገው እንደ ያዕቆብና ዮሐንስ ክብር የማግኘት ወይም ከሌሎች ልቆ የመታየት ምኞት ስላለኝ ይሆን?’
18 በልብህ ውስጥ የራስ ወዳድነት ስሜት እንዳለ ከተገነዘብህ ይሖዋ አስተሳሰብህንም ሆነ ስሜትህን ለማስተካከል እንዲረዳህ ጠይቀው፤ ከዚያም ለራስህ ሳይሆን ለእሱ ክብር ለማምጣት ይበልጥ ጠንክረህ ሥራ። (መዝ. 86:11) ከዚህም ሌላ የሌሎችን ትኩረት ወደ አንተ የማይስቡ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣር ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል ከባድ የሆኑብህን ባሕርያት ይበልጥ ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረግ ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የተሰጡህን ክፍሎች በትጋት የምትዘጋጅ ቢሆንም የመንግሥት አዳራሽ በማጽዳቱ ሥራ መካፈል የማያስደስትህ ከሆነ በሮም 12:16 ላይ የሰፈረውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ግብ ልታወጣ ትችላለህ።—ጥቅሱን አንብብ።
19. የአምላክን ቃል እንደ መስተዋት ተጠቅመን ራሳችንን ስንመረምር በምናያቸው ነገሮች ተስፋ እንዳንቆርጥ ምን ማድረግ እንችላለን?
19 የአምላክን ቃል እንደ መስተዋት ተጠቅመን ራሳችንን በጥንቃቄ ስንመረምር አንዳንድ እንከኖች እንዳሉብን ሌላው ቀርቶ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዳለን እናስተውል ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ስሜት ካለህ፣ ያዕቆብ በምሳሌው ላይ የጠቀሰውን ስኬታማ ሰው አስታውስ። ያዕቆብ፣ ሰውየው በራሱ ላይ የተመለከተውን እንከን በምን ያህል ፍጥነት እንዳስተካከለው ወይም ያለበትን ችግር ሁሉ ማስወገድ ችሎ እንደሆነ አልተናገረም፤ ከዚህ ይልቅ ሰውየው ‘ፍጹም በሆነው ሕግ እንደጸና’ ተናግሯል። (ያዕ. 1:25) ሰውየው በመስተዋት የተመለከተውን እንከን በማስታወስ ያንን ለማሻሻል ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። አንተም ስለ ራስህ አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር እንዲሁም ያሉብህን ጉድለቶች በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብሃል። (መክብብ 7:20ን አንብብ።) ፍጹም የሆነውን ሕግ በትኩረት መመልከትህን እንዲሁም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማዳበርህን ቀጥል። ይሖዋ፣ እንደ አንተው ፍጹም ያልሆኑ በርካታ ወንድሞችህን እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ለመርዳት ፈቃደኛ ነው፤ አንተም እንደ እነሱ የአምላክን ሞገስና በረከት ማግኘት ትችላለህ።