ፈተናዎች ቢኖሩም እምነታችሁን አጥብቃችሁ ያዙ!
“ወንድሞቼ ሆይ፣ . . . ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት።”—ያዕቆብ 1:2
1. የይሖዋ ሕዝቦች በእምነትና ‘ከልብ በመነጨ ደስታ’ የሚያገለግሉት ምን እየደረሰባቸውም ጭምር ነው?
የይሖዋ ሕዝቦች ምሥክሮቹ በመሆን አምላካቸውን በእምነትና “በሐሴት” ያገለግሉታል። (ዘዳግም 28:47፤ ኢሳይያስ 43:10) በብዙ ፈተናዎች ቢታጠሩም እንኳ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። መከራ ቢደርስባቸውም በሚከተሉት ቃላት ይጽናናሉ:- “የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን [“ጽናትን፣” NW] እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት።”—ያዕቆብ 1:2, 3
2. ስለ ያዕቆብ መልእክት ጸሐፊ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
2 ይህን ሐሳብ በ62 እዘአ ገደማ በጽሑፍ ያሠፈረው የኢየሱስ ክርስቶስ ግማሽ ወንድም የነበረው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ነው። (ማርቆስ 6:3) ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ጉባኤ ሽማግሌ ነበር። እንዲያውም እርሱ፣ ኬፋ (ጴጥሮስ) እና ዮሐንስ “አዕማድ መስለው የሚታዩ” ማለትም ጠንካራ የሆኑና ጽኑ መሠረት ያላቸው የጉባኤው ምሰሶዎች ነበሩ። (ገላትያ 2:9) ግርዘትን በሚመለከት ክርክር ተነሥቶ በ49 እዘአ ገደማ ጉዳዩ ‘ለሐዋርያትና ለሽማግሌዎች’ በቀረበ ጊዜ ያዕቆብ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል ላሳለፈው ውሳኔ መሠረት የሆነውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ አቅርቧል።—ሥራ 15:6-29
3. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ከያዕቆብ መልእክት ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ያዕቆብ የሌሎች ጉዳይ የሚያሳስበው መንፈሳዊ እረኛ እንደመሆኑ መጠን ‘የመንጋውን መልክ አስተውሎ የሚያውቅ’ ሰው ነበር። (ምሳሌ 27:23) በወቅቱ ክርስቲያኖች ከባድ ፈተናዎች እየደረሱባቸው እንደነበር ተገንዝቧል። አንዳንዶቹ ለባለ ጠጎች ያዳሉ ስለነበር አስተሳሰባቸውን ማስተካከል ያስፈልጋቸው ነበር። ከመካከላቸው የብዙዎቹ አምልኮ ለይስሙላ ብቻ የሚደረግ ነገር ነበር። አንዳንዶች ባልተገራ ምላሳቸው ሌሎችን ይጎዱ ነበር። ዓለማዊ መንፈስ ጎጂ ውጤቶች አስከትሎ የነበረ ሲሆን ብዙዎቹ ትዕግሥት አልነበራቸውም እንዲሁም በጸሎት የሚተጉ አልነበሩም። እንዲያውም የተወሰኑት ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ታምመው ነበር። የያዕቆብ መልእክት ገንቢ በሆነ መንገድ ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚናገር ሲሆን ምክሩም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ጠቃሚ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው። ይህን መልእክት ለእኛ በግላችን እንደተጻፈልን አድርገን ብንመረምረው በእጅጉ እንጠቀማለን።a
ፈተናዎች ሲደርሱብን
4. ለፈተናዎች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
4 ያዕቆብ ለፈተናዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ይገልጽልናል። (ያዕቆብ 1:1-4) ከአምላክ ልጅ ጋር ስለነበረው የቤተሰብ ትስስር ምንም ሳይጠቅስ በትሕትና ራሱን “የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ” ሲል ጠርቷል። ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው “ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ [የመንፈሳዊ እስራኤላውያን] ወገኖች” ሲሆን ለመበተናቸው ዋነኛ ምክንያት የሆነው ስደት ነበር። (ሥራ 8:1፤ 11:19፤ ገላትያ 6:16፤ 1 ጴጥሮስ 1:1) እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ስደትና ‘ልዩ ልዩ ፈተና ይደርስብናል።’ ይሁን እንጂ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት እምነታችንን እንደሚያጠነክርልን ካስታወስን ፈተናዎች ሲደርሱብን ‘እንደ ሙሉ ደስታ እንቆጥራቸዋለን።’ በፈተና ወቅት ለአምላክ ያለንን የጸና አቋም መጠበቃችን ዘላቂ ደስታ ያመጣልናል።
5. የሚደርሱብን ፈተናዎች ምንን የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ? እነዚህን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ በጽናት መወጣታችን ምን ውጤት ይኖረዋል?
5 ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች መካከል በሰው ዘር ላይ የሚደርሱት የጋራ ችግሮች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል በጤና ችግር እንሰቃይ ይሆናል። ዛሬ አምላክ ተዓምራዊ ፈውስ ባያከናውንም በሽታችንን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬ እንዲሰጠን ለምናቀርበው ጸሎት መልስ ይሰጣል። (መዝሙር 41:1-3) ከዚህም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ስደት ስለሚደርስብን ለጽድቅ ስንል መከራ እንቀበላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:14) እንዲህ ያሉትን ፈተናዎች በጽናት ከተወጣን የእምነታችን ጥንካሬ ‘በፈተና’ የተረጋገጠ ይሆናል። የእምነታችን ድል ማድረግ ደግሞ ‘ጽናትን’ ያተርፍልናል። በፈተናዎች የጠነከረ እምነት ወደፊት የሚመጡ ፈታኝ ሁኔታዎችን በጽናት ለመቋቋም ይረዳናል።
6. ‘ጽናት ሥራውን የሚፈጽመው’ እንዴት ነው? ፈተናዎች ሲደርሱብን ምን ጠቃሚ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?
6 ያዕቆብ “ትዕግሥትም [“ጽናትም፣” NW] . . . ሥራውን ይፈጽም” ብሏል። አንድን ፈተና ቸኩለን ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ መንገድ ለማስቆም ከመሞከር ይልቅ እስከ መጨረሻው ከታገሥነው ጽናት በእምነት ረገድ ምንም የማይጎድለን ምሉዓን ክርስቲያኖች እንድንሆን በማድረግ “ሥራውን” ያከናውናል። እርግጥ ነው፣ ፈተናው አንድ ዓይነት ድክመት እንዳለብን የሚያሳይ ከሆነ ይህንን ለማሸነፍ እንድንችል የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጣጣር ይገባናል። ፈተናው የጾታ ብልግና እንድንፈጽም የሚገፋፋ ሁኔታ ቢሆንስ? ችግሩን አስመልክተን እንጸልይና ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ ነገር እናድርግ። በአምላክ ዘንድ የጸና አቋም ይዘን ለመቀጠል ስንል የሥራ ቦታችንን መለወጥ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልገን ይሆናል።—ዘፍጥረት 39:7-9፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13
ጥበብን አጥብቆ መፈለግ
7. ፈተናዎችን ለመቋቋም እርዳታ የምናገኘው እንዴት ሊሆን ይችላል?
7 ያዕቆብ አንድን ፈተና እንዴት መወጣት እንደምንችል ካላወቅን ምን ማድረግ እንደሚገባን ገልጾልናል። (ያዕቆብ 1:5-8) ይሖዋ ጥበብ ስለጎደለን ጥበብ እንዲሰጠን በእምነት ወደ እርሱ ብንጸልይ አይነቅፈንም። ለፈተና ተገቢ አመለካከት እንዲኖረንና በጽናት እንድንወጣው ይረዳናል። ከመሰል አማኞች ጋር የምናደርገው ውይይት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የቅዱሳን ጽሑፎችን ሐሳብ ሊያስታውሰን ይችላል። አምላክ ለእኛ ሲል የቀየሳቸው አንዳንድ ነገሮችም ምን ማድረግ እንደሚገባን እንድናስተውል ሊረዱን ይችላሉ። የአምላክ መንፈስም ሊመራን ይችላል። (ሉቃስ 11:13) እንዲህ ያሉትን ጥቅሞች ለማግኘት ከአምላክና ከሕዝቦቹ ጋር መጣበቅ እንዳለብን ግልጽ ነው።—ምሳሌ 18:1
8. የሚጠራጠር ሰው ከይሖዋ አንዳች የማያገኘው ለምንድን ነው?
8 ‘በምንም ሳንጠራጠር በእምነት መለመናችንን ከቀጠልን’ ይሖዋ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ ይሰጠናል። የሚጠራጠር ሰው መሄጃው እንደማይታወቅ ‘በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕር ማዕበል’ ነው። በመንፈሳዊ እንዲህ የምንዋልል ከሆነ ‘ከይሖዋ ዘንድ አንዳች እንድናገኝ አይምሰለን።’ በጸሎታችንም ሆነ በሌሎች መንገዶች ‘ሁለት ሐሳብ ያለን’ ወይም ‘የምንወላውል’ አንሁን። ከዚህ ይልቅ የጥበብ ምንጭ በሆነው በይሖዋ ላይ እምነት ይኑረን።—ምሳሌ 3:5, 6
ባለጠጋውም ድሃውም ደስ ሊላቸው ይችላል
9. የይሖዋ አምላኪዎች እንደ መሆናችን መጠን የምንደሰትበት ምክንያት አለን የምንለው ለምንድን ነው?
9 ከሚደርሱብን ፈተናዎች አንዱ ድህነት ቢሆንም ክርስቲያኖች ባለጠጋም ሆኑ ድሆች ደስተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ እናስታውስ። (ያዕቆብ 1:9-11 የ1980 ትርጉም) አብዛኞቹ ቅቡዓን፣ የኢየሱስ ተከታዮች ከመሆናቸው በፊት ቁሳዊ ሃብት የሌላቸው በመሆናቸው ዓለም በንቀት ዓይን ይመለከታቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:26) ይሁን እንጂ የመንግሥቱ ወራሾች የመሆንን መብት በማግኘት ‘ከፍ በመደረጋቸው’ የሚደሰቱበት ምክንያት ነበራቸው። (ሮሜ 8:16, 17) በአንጻሩ ደግሞ በአንድ ወቅት የተከበሩ የነበሩ ባለጠጋ ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው ዓለም ስለሚንቃቸው ‘ዝቅ ተደርገው’ ይታያሉ። (ዮሐንስ 7:47-52፤ 12:42, 43) ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ደስ ሊለን ይችላል፤ ምክንያቱም ዓለማዊ ሃብትም ሆነ ከፍተኛ ቦታ እኛ ካገኘነው መንፈሳዊ ብልጽግና ጋር ሲወዳደር ከቁጥር የሚገባ ነገር አይደለም። በኑሮ ደረጃ መኩራራት በመካከላችን ቦታ የሌለው ነገር በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ምሳሌ 10:22፤ ሥራ 10:34, 35
10. አንድ ክርስቲያን ለቁሳዊ ብልጽግና ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል?
10 ያዕቆብ ሕይወታችን የተመካው በባለ ጠግነትና ዓለማዊ ግቦችን በማሳካት ላይ እንዳልሆነ እንድናስተውል ይረዳናል። አንድ አበባ የሚያምር መሆኑ በፀሐይ “ትኩሳት” ከመጠውለግ እንደማያድነው ሁሉ የባለጠጋም ሰው ሃብት እንዲሁ ሕይወቱን ሊያራዝምለት አይችልም። (መዝሙር 49:6-9፤ ማቴዎስ 6:27) በራሱ ‘የሕይወት መንገድ’ ምናልባትም በንግድ ሥራው ሲባክን ይሞት ይሆናል። በመሆኑም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ‘በአምላክ ዘንድ ባለጠጋ መሆንና’ የመንግሥቱን ዓላማ ለማራመድ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ነው።—ሉቃስ 12:13-21፤ ማቴዎስ 6:33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
በፈተና የሚጸኑ ደስተኞች ናቸው
11. ፈተና ቢደርስባቸውም እምነታቸውን አጥብቀው የሚይዙ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
11 ባለጠጋም ሆንን ድሃ ደስተኞች መሆን የምንችለው የሚደርሱብንን ፈተናዎች በጽናት ከተወጣን ብቻ ነው። (ያዕቆብ 1:12-15) እምነታችንን እንደጠበቅን ፈተናዎችን በጽናት ከተቋቋምን በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ደስታ ስለሚያስገኝ ደስተኞች ልንባል እንችላለን። በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች እስከ ሞት ድረስ እምነታቸውን አጥብቀው በመያዝ ‘የሕይወትን አክሊል’ ማለትም የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት ያገኛሉ። (ራእይ 2:10፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50) ምድራዊ ተስፋ ካለንና በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን ከቆየን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም እንኖራለን ብለን በጉጉት ልንጠባበቅ እንችላለን። (ሉቃስ 23:43፤ ሮሜ 6:23) ይሖዋ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ምንኛ ጥሩ ነው!
12. መከራ ሲደርስብን ‘በአምላክ እየተፈተንኩ ነው’ ማለት የማይገባን ለምንድን ነው?
12 ይሖዋ ራሱ በክፉ ሊፈትነን ይችላልን? የለም፣ “በእግዚአብሔር እፈተናለሁ” ልንል አይገባም። ይሖዋ ኃጢአት እንድንሠራ ለማሳሳት ብሎ አይፈትነንም፤ ይልቁንም በእምነት ጸንተን ከቆምን ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት በመስጠት ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 4:13) አምላክ ቅዱስ ነው፤ በመሆኑም ኃጢአት የመቋቋም ጥንካሬያችንን በሚያዳክሙ ሁኔታዎች ውስጥ እንድንገባ አያደርግም። ራሳችንን ቅድስና በሌላቸው ሁኔታዎች በማጠላለፍ አንድ ዓይነት ኃጢአት ብንፈጽም እርሱን ልንወቅሰው አይገባም፤ ምክንያቱም እርሱ “በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” ይሖዋ የሚጠቅመንን ዲሲፕሊን እንድናገኝ ሲል ፈተናዎች እንዲደርሱብን ሊፈቅድ ቢችልም በክፋት ተነሣስቶ አይፈትነንም። (ዕብራውያን 12:7-11) ሰይጣን ስህተት እንድንሠራ ሊፈትነን ይችላል፤ ይሁን እንጂ አምላክ ከክፉው እጅ ሊያድነን ይችላል።—ማቴዎስ 6:13
13. አንድን መጥፎ ምኞት ካላስወገድነው ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?
13 አንዳንድ ሁኔታዎች ወደ ኃጢአት የሚመራ መጥፎ ምኞት ሊያሳድሩብን ስለሚችሉ በጸሎት መትጋት ይኖርብናል። ያዕቆብ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” ብሏል። ልባችን የኃጢአት ምኞት እንዲያውጠነጥን ፈቅደንለት ከነበረ ኃጢአት ብንፈጽም አምላክን ልንወቅሰው አንችልም። አንድን መጥፎ ምኞት ነቅለን ካላወጣነው ‘ይፀነስና’ በልብ ውስጥ አድጎ ‘ኃጢአትን ይወልዳል።’ ኃጢአትም ከተፈጸመ በኋላ ‘ሞትን ያስከትላል።’ ልባችንን መጠበቅና የኃጢአት ዝንባሌዎችን መዋጋት እንዳለብን ግልጽ ነው። (ምሳሌ 4:23) ቃየን ኃጢአት ሊያሸንፈው እንደሆነ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ሳይዋጋው ቀርቷል። (ዘፍጥረት 4:4-8) ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ጎዳና መከተል ጀምረን ከሆነስ? ክርስቲያን ሽማግሌዎች በአምላክ ላይ ኃጢአት እንዳንሠራ ሲሉ እኛን ለማስተካከል ለሚያደርጉት ጥረት አመስጋኞች መሆን እንደሚገባን ጥርጥር የለውም።—ገላትያ 6:1
አምላክ—የበጎ ነገሮች ምንጭ
14. የአምላክ ስጦታዎች “ፍጹም” ናቸው ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?
14 ይሖዋ የበጎ ነገሮች እንጂ የፈተናዎች ምንጭ እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባናል። (ያዕቆብ 1:16-18) ያዕቆብ የእምነት አጋሮቹን “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ” በማለት ከጠራቸው በኋላ አምላክ ‘የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ሁሉ’ ምንጭ መሆኑን ገልጿል። የይሖዋ መንፈሳዊና ቁሳዊ ስጦታዎች “ፍጹም” ማለትም ምንም የማይጎድላቸው ምሉዓን ናቸው። እነዚህ ስጦታዎች የሚመጡት “ከላይ” ይኸውም የአምላክ ማደሪያ ከሆኑት ሰማያት ነው። (1 ነገሥት 8:39) ይሖዋ እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ያሉት ‘የሰማይ ብርሃናት’ “አባት” ነው። መንፈሳዊ ብርሃንና እውነትም ይሰጠናል። (መዝሙር 43:3፤ ኤርምያስ 31:35፤ 2 ቆሮንቶስ 4:6) በእንቅስቃሴዋ ወቅት ምድር ላይ የሚታየው ጥላ እንዲቀያየር ከምታደርገውና በቀትር ላይ ብቻ ከፍተኛውን ኃይሏን ከምትሰጠው ፀሐይ በተለየ መልኩ አምላክ መልካም ከማድረግ ወደኋላ የሚልበት ጊዜ የለም። በቃሉና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በሚያቀርብልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ የምንጠቀም ከሆነ ፈተናዎችን ለመቋቋም የታጠቅን እንድንሆን እንደሚያደርገን ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴዎስ 24:45
15. ከይሖዋ መልካም ስጦታዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው?
15 ከአምላክ ግሩም ስጦታዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው? ከምሥራቹ ወይም ‘ከእውነት ቃል’ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚሠሩት መንፈሳዊ ልጆች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲወለዱ ማድረጉ ነው። በመንፈሳዊ ሁኔታ የተወለዱት ሰዎች በሰማይ “መንግሥትና ካህናት” ለመሆን ከሰው ዘር የተመረጡ “የበኩራት ዓይነት” ናቸው። (ራእይ 5:10፤ ኤፌሶን 1:13, 14) ያዕቆብ በአእምሮው ይዞት የነበረው ኢየሱስ ትንሣኤ ባገኘበት ዕለት ማለትም ኒሳን 16 ቀን የቀረበውን የገብስ በኩራት እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰበት የጰንጠቆስጤ ዕለት የቀረበውን ሁለት የስንዴ እንጀራ ሊሆን ይችላል። (ዘሌዋውያን 23:4-11, 15-17) ከዚህ አንጻር ሲታይ በኩራቱ ኢየሱስ ሆኖ ተባባሪ ወራሾቹ ደግሞ “የበኩራት ዓይነት” ይሆናሉ ማለት ነው። ተስፋችን ምድራዊ ከሆነስ? ተስፋችን ምድራዊም ቢሆን ይህንኑ ተስፋችንን ማስታወስ በመንግሥቱ ግዛት ሥር የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን በር በከፈተልን ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ’ ምንጭ በሆነው አምላክ ላይ ያለንን እምነት አጥብቀን እንድንይዝ ይረዳናል።
‘ቃሉን አድራጊዎች’ ሁኑ
16. ‘ለመስማት የፈጠንን፣ ለመናገርና ለቁጣ ግን የዘገየን’ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
16 በአሁኑ ጊዜ በእምነታችን ላይ ፈተና እየደረሰብን ሆነም አልሆነ ‘የቃሉ አድራጊዎች’ መሆን ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:19-25) በታዛዥነት ቃሉን የምናደርግ ሰዎች ሆነን በመገኘት የአምላክን ቃል ‘ለመስማት የፈጠንን’ መሆን አለብን። (ዮሐንስ 8:47) በሌላ በኩል ደግሞ ስለምንናገራቸው ቃላት በጥንቃቄ በማሰብ ‘ለመናገር የዘገየን’ እንሁን። (ምሳሌ 15:28፤ 16:23) ያዕቆብ፣ ፈተና የደረሰብን ከአምላክ ነው ብለን በችኮላ እንዳንደመድም ማሳሰቡ ሊሆን ይችላል። “ሰው ሁሉ . . . ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና” የሚል ምክርም ተሰጥቶናል። አንድ ሰው በተናገረው ነገር ከተበሳጨን እልኽ የተሞላበት መልስ ልንሰጥ ስለምንችል ይህ እንዳይሆን ምላሽ ለመስጠት ‘አንቸኩል።’ (ኤፌሶን 4:26, 27) በራሳችን ላይ ችግር ሊያስከትል የሚችልና ለሌሎችም ፈተና የሚሆን የቁጡነት መንፈስ በጻድቁ አምላካችን ላይ እምነት ካለው ሰው የሚጠበቁትን ባሕርያት ለማፍራት አያስችለንም። ከዚህም ሌላ “ብዙ ማስተዋል” ካለን ‘ለቁጣ የዘገየን’ ስለምንሆን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ይቀርቡናል።—ምሳሌ 14:29
17. ክፋትን ከልባችንና ከአእምሮአችን ማውጣት ለምን ነገር ይረዳል?
17 ‘ከርኩሰት ሁሉ’ ማለትም አምላክ ከሚጸየፋቸውና ቁጣን ከሚያነሳሱ ነገሮች ሁሉ መራቅ እንዳለብን ግልጽ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ‘ትርፍ የሆነውን ነገር ክፋትን ማስወገድ’ ይኖርብናል። ሁላችንም ሕይወታችን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክሱ ነገሮች ሁሉ የጸዳ እንዲሆን ማድረግ ይገባናል። (2 ቆሮንቶስ 7:1፤ 1 ጴጥሮስ 1:14-16፤ 1 ዮሐንስ 1:9) ክፋትን ከልባችንና ከአእምሮአችን ማስወገዳችን ‘የእውነት ቃል በውስጣችን እንዲተከል በየዋህነት’ ፈቃደኞች ሆነን እንድንገኝ ረድቶናል። (ሥራ 17:11, 12) በክርስትና ውስጥ የቱንም ያህል ረጅም ጊዜ ብንቆይ ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች በውስጣችን መተከላቸውን እንዲቀጥሉ መፍቀድ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ይህ በውስጣችን የተተከለው እውነት ለመዳን የሚያበቃንን “አዲሱን ሰው” ያፈራልናል።—ኤፌሶን 4:20-24
18. ቃሉን ሰሚ ብቻ የሆነ ሰው ቃሉን ሰምቶ ከሚያደርግ ሰው የሚለየው እንዴት ነው?
18 ቃሉ መመሪያችን እንደሆነ የምናሳየው እንዴት ነው? ‘ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን’ ታዛዥ ‘የቃሉ አድራጊዎች’ በመሆን ነው። (ሉቃስ 11:28) ‘ቃሉን የሚያደርጉ ሰዎች’ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በቅንዓት እንዲሠሩ እንዲሁም የአምላክ ሕዝቦች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ዘወትር እንዲሳተፉ የሚያንቀሳቅስ እምነት አላቸው። (ሮሜ 10:14, 15፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ሰሚ ብቻ የሆነ ሰው “የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል።” ራሱን አይቶ ከሄደ በኋላ ፊቱ ላይ የተመለከተውን መስተካከል የሚያስፈልገውን ነገር ይረሳዋል። ‘ቃሉን የምናደርግ’ እንደመሆናችን መጠን አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አካትቶ የያዘውን የእርሱን ‘ፍጹም ሕግ’ በጥንቃቄ እናጠናለን እንዲሁም እንታዘዛለን። በዚህ መንገድ የምናገኘው ነፃነት ወደ ሕይወት የሚመራ በመሆኑ ለኃጢአትና ለሞት ባርያ ከመሆን ፍጹም ተቃራኒ ነው። እንግዲያውስ ዘወትር በጥንቃቄ በመመርመርና በመታዘዝ ‘በፍጹሙ ሕግ እንጽና።’ ደግሞም እስቲ አስቡት! ‘ሰምተን የምንረሳ ሳይሆን ሥራውን የምንፈጽም ሰዎች በመሆናችን’ የአምላክን ሞገስ በማግኘት እንደሰታለን።—መዝሙር 19:7-11
አምልኳችን ለደንቡ ያህል ብቻ የሚደረግ መሆን የለበትም
19, 20. (ሀ) በያዕቆብ 1:26, 27 መሠረት ንጹሕ አምልኮ ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል? (ለ) ያልተበከለ አምልኮ ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳዩት አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
19 መለኮታዊውን ሞገስ እንድናገኝ ከተፈለገ እውነተኛው አምልኮ ለደንቡ ያህል ብቻ የሚደረግ ነገር አለመሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:26, 27) ‘ለደንቡ ያህል ብቻ አምልኮ ስላቀረብን’ [NW] ይሖዋ ይቀበለናል ብለን እናስብ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ዋናው ነገር እርሱ ለእያንዳንዳችን ያለው ግምት ነው። (1 ቆሮንቶስ 4:4) አንዱ ትልቁ ችግር ‘አንደበታችንን ለመግታት’ አለመቻል ነው። የሌሎችን ስም እያጠፋን፣ እየዋሸን ወይም ምላሳችንን በሌላ መንገድ አላግባብ እየተጠቀምን አምላክ በምናቀርበው አምልኮ ይደሰታል ብለን ብናስብ ራሳችንን ማታለል ይሆንብናል። (ዘሌዋውያን 19:16፤ ኤፌሶን 4:25) በምንም ምክንያት ቢሆን ‘አምልኮአችን’ ‘ከንቱና’ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው እንዲሆን እንደማንፈልግ ግልጽ ነው።
20 ያዕቆብ እያንዳንዱን የንጹሕ አምልኮ ዘርፍ ባይዘረዝርም ‘ወላጆች የሌሏቸውን ልጆችና ባልቴቶችን በመከራቸው መጠየቅን’ እንደሚጨምር ተናግሯል። (ገላትያ 2:10፤ 6:10፤ 1 ዮሐንስ 3:18) የክርስቲያን ጉባኤ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መበለቶችን ይንከባከባል። (ሥራ 6:1-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8-10) አምላክ የመበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን እነርሱን በመንፈሳዊና በቁሳዊ ነገሮች ለመርዳት አቅማችን የሚፈቅድልንን በማድረግ ከእርሱ ጋር እንተባበር። (ዘዳግም 10:17, 18) ከዚህም በተጨማሪ ንጹሕ አምልኮ “በዓለም” ማለትም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ኃጢአተኛ የሰው ዘር ኅብረተሰብ ውስጥ ከሚገኘው ‘እድፍ ሰውነትን መጠበቅ’ ማለት ነው። (ዮሐንስ 17:16፤ 1 ዮሐንስ 5:19) እንግዲያውስ ይሖዋን ለማስከበር እንድንችልና በአገልግሎቱም እንዲጠቀምብን ከዓለም አምላክ የለሽ አኗኗር እንራቅ።—2 ጢሞቴዎስ 2:20-22
21. ከያዕቆብ መልእክት ጋር በተያያዘ ልናስብባቸው የሚገቡ ተጨማሪ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
21 እስካሁን ድረስ የተወያየንበት የያዕቆብ ምክር ፈተናዎችን በጽናት እንድንቋቋምና እምነታችንን አጥብቀን እንድንይዝ ሊረዳን ይገባል። ለአፍቃሪው የመልካም ስጦታዎች ምንጭ ያለንን አድናቆትም ሊያሳድግልን ይገባል። እንዲሁም ያዕቆብ የተናገራቸው ቃላት ንጹሑን አምልኮ እንድንከተል ይረዱናል። ያዕቆብ ሌላስ ምን የሚለን ነገር ይኖራል? በይሖዋ ላይ እውነተኛ እምነት እንዳለን ለማሳየት ምን ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህንንም ሆነ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ሁለት ርዕሶች በግል ወይም በቤተሰብ መልክ ስታጠኑ እምነት ከሚያጠነክረው የያዕቆብ መልእክት የተጠቀሰውን እያንዳንዱን ክፍል እያወጣችሁ ማንበባችሁ ይበልጥ ይጠቅማችኋል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በፈተናዎች ለመጽናት የሚረዳን ምንድን ነው?
◻ ክርስቲያኖች ፈተናዎች ቢደርሱባቸውም ደስ ሊላቸው የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ የቃሉ አድራጊዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ንጹህ አምልኮ ምን ነገር ይጨምራል?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈተናዎች ሲደርሱብህ ይሖዋ ለጸሎት መልስ ለመስጠት ባለው ችሎታ ላይ እምነት እንዳለህ አሳይ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
‘ቃሉን የሚያደርጉ’ ሰዎች በዓለም ዙሪያ የአምላክን መንግሥት በማወጅ ላይ ናቸው