አምላክ ለአረጋውያን ያስባል
በዛሬ ጊዜ በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው በደል እየጨመረ መምጣቱ የሚያስደንቅ አይደለም። ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ “በመጨረሻው ዘመን” የሚኖሩት “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ . . . [እንዲሁም] ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) እዚህ ላይ “ፍቅር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ተፈጥሯዊ ፍቅር ሊጨምር ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተተነበየው በዛሬው ጊዜ የዚህ ዓይነቱ ፍቅር እንደሌለ በግልጽ ማየት ይቻላል።
በአረጋውያን ላይ በደል ከሚፈጽሙት ሰዎች በተቃራኒ ይሖዋ አምላክ ለእነዚህ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ያስብላቸዋል። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዴት ተደርጎ እንደተገለጸ እስቲ እንመልከት።
‘ለባልቴቲቱ ተሟጋች’
ይሖዋ ለአረጋውያን የሚያስብ አምላክ እንደሆነ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጿል። ለምሳሌ፣ ዳዊት በመዝሙር 68:5 ላይ አምላክን “ለባልቴቲቱም [“ባሎቻቸው ለሞቱባቸውም ሴቶች፣” የ1980 ትርጉም] ተሟጋች” በማለት ጠርቶታል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሴቶች አረጋውያን ናቸው።a በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “ተሟጋች” የሚለው ቃል “ጠባቂ” እንዲሁም “ደጋፊ” ተብሎ ተተርጉሟል። በግልጽ እንደሚታየው ይሖዋ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ያስባል። ሌላው ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ሴቶች ላይ በደል ማድረስ አምላክን የሚያስቆጣ ድርጊት እንደሆነ ይናገራል። (ዘፀአት 22:22-24) መበለቶችም ሆኑ ሁሉም ታማኝ አረጋውያን በአምላክ እንዲሁም በእርሱ አገልጋዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው። ምሳሌ 16:31 ይሖዋም ሆነ ሕዝቡ ለአረጋውያን ያላቸውን አመለካከት ሲገልጽ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል።
ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥ አረጋውያንን ማክበር መሠረታዊ ነገር መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” የሚል ትእዛዝ ለእስራኤላውያን ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:32) ከዚህም የተነሳ በእስራኤላውያን ዘንድ አረጋውያንን ማክበር አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና የሚነካበት ጉዳይ ነበር። አንድ ሰው በአረጋውያን ላይ በደል እያደረሰ አምላክን እወዳለሁ ማለት አይችልም።
እርግጥ ነው ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። ይሁን እንጂ በባሕርያቸውና በዝንባሌያቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ በሚያሳድረው ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ሲሆኑ ይህ ሕግ ደግሞ ለወላጆችና ለአረጋውያን ፍቅርና አክብሮት ማሳየትን ያካትታል። (ገላትያ 6:2፤ ኤፌሶን 6:1-3፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:1-3) ክርስቲያኖች ፍቅርን ማሳየት ያለባቸው ስለታዘዙ ሳይሆን ከልባቸው ተገፋፍተው መሆን ይኖርበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስም “እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” ሲል ተናግሯል።—1 ጴጥሮስ 1:22
ሐዋርያው ያዕቆብ ደግሞ አረጋውያንን እንድንንከባከብ የሚያነሳሳን ተጨማሪ ምክንያት ይሰጠናል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኲሰት ራስን መጠበቅ ነው።” (ያዕቆብ 1:27) ያዕቆብ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ልብ የሚነኩ ናቸው። አረጋውያን ለይሖዋ ምን ያህል ውድ መሆናቸውን ከዚህ መመልከት እንችላለን።
በመሆኑም በአረጋውያን ላይ በደል ከመፈጸም መቆጠብ ብቻውን በቂ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ጠቃሚ ተግባሮችን በማከናወን አሳቢነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። (“ፍቅርን በተግባር መግለጽ” የሚለውን በገጽ 6 እና 7 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) ያዕቆብ “ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” በማለት ጽፏል።—ያዕቆብ 2:26
“በችግራቸው” ወቅት ማጽናኛ መስጠት
ያዕቆብ ከተናገራቸው ቃላት ሌላ ቁም ነገርም እናገኛለን። ያዕቆብ፣ ክርስቲያኖች መበለቶችን “በችግራቸው” እንዲረዷቸው አሳስቧቸዋል። “በችግራቸው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በሕይወታችን ውስጥ በሚከሰቱ አንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት የሚያጋጥመንን ሥቃይ፣ ጭንቀት ወይም መከራ ለማመልከት ይሠራበታል። በርካታ አረጋውያን እንዲህ ያለው መከራ እንደሚደርስባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዶቹ ብቸኛ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ እርጅና ባስከተለባቸው የአቅም ገደብ ምክንያት ይጨነቃሉ። ሌላው ቀርቶ በአምላክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እየተካፈሉ ያሉትም ቢሆኑ ተስፋ ይቆርጣሉ። እስቲ እንደ ምሳሌ አድርገን የወንድም ጆንንb ሁኔታ እንመልከት:- ከአራት አሥርተ ዓመታት በላይ የአምላክን መንግሥት በታማኝነት የሰበኩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የመጨረሻዎቹን ሦስት አሥርተ ዓመታት ያሳለፉት በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ነው። አሁን ዕድሜያቸው በሰማንያዎቹ ውስጥ የሚገኘው ጆን ተስፋ የቆረጡባቸው አንዳንድ ጊዜያት እንዳሉ ከማመናቸውም በተጨማሪ “አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ አሰላስላለሁ፤ የሠራኋቸውን ብዙ ስህተቶች አስታውስና እንዲህ አድርጌ ሠርቼው ቢሆን የተሻለ ነበር ብዬ አስባለሁ” በማለት ተናግረዋል።
እንደ ጆን ያሉ አረጋውያን ይሖዋ ፍጹም ቢሆንም ከሌሎች ፍጽምናን የማይጠብቅ እንደሆነ በማወቃቸው ሊጽናኑ ይችላሉ። ይሖዋ ምን ስህተት እንደሠራን ቢያውቅም መጽሐፍ ቅዱስ እርሱን በተመለከተ ሲናገር “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” ይላል። (መዝሙር 130:3) እውነት ነው፣ ይሖዋ በሠራናቸው ስህተቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ በልባችን ያለውን ይረዳል። ይህን እንዴት እናውቃለን?
አለፍጽምናም ሆነ ኃጢአት መሥራት ምን እንደሆነ በደንብ የሚያውቀው ንጉሥ ዳዊት በአምላክ መንፈስ አማካኝነት በመዝሙር 139:1-3 ላይ ያሉትን የሚከተሉትን ቃላት ጽፏል። “እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል።” “አጥርተህ ታውቃለህ” የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉም ገበሬዎች እህሉን ከግርዱ ለመለየት የሚያደርጉትን “የማበጠር” ሂደት የሚያመለክት ነው። ዳዊት በመንፈስ ተገፋፍቶ፣ ይሖዋ የእኛን መልካም ሥራዎች እንዴት አበጥሮ እንደሚለይ ብሎም እንደሚያስታውሳቸው ማረጋገጫ ሰጥቶናል።
በሰማይ የሚኖረው መሐሪ አባታችን ታማኝ ሆነን እስከተገኘን ድረስ ያደረግናቸውን መልካም ሥራዎች ከማስታወሱም በተጨማሪ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሥራችንንና ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር መርሳትን እንደ ዓመጽ እንደሚቆጥረው ይናገራል።—ዕብራውያን 6:10
“የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና”
መጽሐፍ ቅዱስ በእርጅና ዘመን የሚከሰቱት ችግሮች በሙሉ በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ውስጥ እንዳልነበሩ ይነግረናል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ማለትም አዳምና ሔዋን በፈጣሪያቸው ላይ ካመጹ በኋላ ግን እርጅና እና ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ሁሉ የሰው ልጅ ሕይወት ክፍል ሆኑ። (ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮሜ 5:12) ይህ ደግሞ ለዘላለም አይቀጥልም።
ከላይ እንደተጠቀሰው በአረጋውያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ጨምሮ ዛሬ እየደረሱብን ያሉት ብዙዎቹ ችግሮች በዚህ ሥርዓት “የመጨረሻው ዘመን” እንደምንኖር የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የአምላክ ዓላማ በእርጅና ምክንያት የሚመጡ ችግሮችንና ሞትን ጨምሮ ሁሉንም የኃጢአት ውጤቶች ማስወገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና” በማለት ይናገራል።—ራእይ 21:4
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በእርጅና ምክንያት መሠቃየት ጊዜ ያለፈበት ነገር ይሆናል። ይህ ደግሞ በአረጋውያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደልም ይጨምራል። (ሚክያስ 4:4) ሌላው ቀርቶ በመቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ተነስተው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይኖራቸዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) በዚያን ወቅት፣ ይሖዋ ለአረጋውያን ብቻ ሳይሆን እርሱን ለሚታዘዙት ሁሉ የሚያስብ አምላክ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እርግጥ ነው፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ሁሉ አረጋውያን ላይሆኑ ይችላሉ። ይሖዋ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ወጣት ሴቶችም የሚያስብ መሆኑን በዘሌዋውያን 22:13 ላይ ተገልጿል።
b እውነተኛ ስማቸው አይደለም።
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ፍቅርን በተግባር መግለጽ
በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ለአረጋውያን አሳቢነት በማሳየት ረገድ ቅድሚያውን ይወስዳሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ” ሲል የሰጠውን ምክር ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። (1 ጴጥሮስ 5:2) ለአረጋውያን ተግባራዊ በሆነ መንገድ አሳቢነት ማሳየት የእግዚአብሔርን መንጋ የመጠበቅ አንዱ ክፍል ነው። ታዲያ ይህ ምን ማድረግን ይጨምራል?
አረጋውያን ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ትዕግሥትና በተደጋጋሚ ጊዜያት ቤታቸው ሄዶ መጠየቅ ብሎም ወዳጃዊ ጭውውት ማድረግ ያስፈልጋል። ምናልባት ገበያ ሄዶ ዕቃ በመግዛት፣ በጽዳት፣ ወደ ስብሰባዎች ለማድረስና ለመመለስ ማጓጓዣ በማዘጋጀት፣ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማንበብ እንዲሁም በሌሎች ነገሮች ረገድ እርዳታ ይሹ ይሆናል። በተቻለ መጠን ተግባራዊና አስተማማኝ የሆነ ፕሮግራም አውጥቶ በሥራ ላይ ማዋል ይገባል።c
ይሁን እንጂ በጉባኤያችሁ ውስጥ ያሉ አንድ አረጋዊ ወንድም ወይም እህት አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልገው ከባድ ችግር ምናልባትም የገንዘብ ድጋፍ ቢያስፈልጋቸውስ? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሊረዷቸው የሚችሉ ልጆች ወይም ሌላ ሥጋዊ ዘመድ እንዳላቸው ማጣራት ተገቢ ነው። ይህም በ1 ጢሞቴዎስ 5:4 ላይ ከተጠቀሰው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “አንዲት መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና።”
ምናልባትም ድጋፍ የሚፈልጉ አረጋውያንን ለመርዳት መንግሥት ያደረገው ዝግጅት ካለና እርዳታ የሚያሻቸው ወንድም ወይም እህት ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ ለመሆን ይበቁ እንደሆነ በማጣራት ረገድ እገዛ ማድረግ ይቻላል። ይህንን በማፈላለጉ ረገድ በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ሊረዳቸው ይችላል። ነገር ግን እንደነዚህ ያሉት እርዳታዎች ከሌሉ ሽማግሌዎች በዕድሜ የገፉት ግለሰብ ከጉባኤ እርዳታ ለማግኘት ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ሊወስኑ ይችላሉ። በአንደኛው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም በአንዳንድ ሁኔታዎች እንዲህ ማድረግ አስፈልጎ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ አብሮት ለሚሠራው ለጢሞቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፎለታል:- “ዕድሜዋ ከሥልሳ ዓመት ያነሰ መበለት በመዝገብ ላይ አትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤ ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለበጎ ምግባር ሁሉ ራሷን በመስጠት በመልካም ሥራም የተመሰከረላት መሆን አለባት።”—1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10
[የግርጌ ማስታወሻ]
c ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ለአረጋውያን ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት” የሚል ርዕስ ያለውን የነሐሴ 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ እንዲሁም “ሚቲንግ ዘ ኒድስ ኦቭ አወር ኦልደር ዋንስ–ኤ ክርስቺያን ቻሌንጅ” የሚል ርዕስ ያለውን የሐምሌ 15, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዶርቃ ለችግረኛ መበለቶች ታስብ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 9:36-39