የክርስቶስ ሕግ
‘በክርስቶስ ሕግ ሥር ነኝ።’—1 ቆሮንቶስ 9:21
1, 2. (ሀ) የሰው ልጅ የፈጸማቸውን ብዙዎቹን ስሕተቶች እንዴት ማስቀረት ይቻል ነበር? (ለ) ሕዝበ ክርስትና ከአይሁድ እምነት ታሪክ ምን ትምህርት ሳታገኝ ቀርታለች?
“ሰዎችም ሆኑ መንግሥታት ከታሪክ የተማሩበት ወይም ከታሪክ የተረዷቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች የተገበሩበት ወቅት ኖሮ አያውቅም።” ይህን የተናገረው አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ ፈላስፋ ነው። እንዲያውም የሰው ልጅ ታሪክ በጣም አሳዛኝ ስህተቶች የተፈጸሙበትና ብጥብጦች እግር በእግር የተፈራረቁበት “የቂልነት ጉዞ” እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን የሰው ልጅ ካለፉት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ቢሆን ኖሮ ከእነዚህ ስህተቶች መካከል አብዛኞቹን ማስቀረት በተቻለ ነበር።
2 ስለ መለኮታዊ ሕግ በምናደርገው በዚህ ውይይት ላይ ካለፉት ስሕተቶች ለመማር ተመሳሳይ እምቢተኝነት ስለታየበት አንድ ሁኔታ እንመለከታለን። ይሖዋ አምላክ የሙሴን ሕግ በሚሻለው የክርስቶስ ሕግ ተክቶታል። ሆኖም ይህን ሕግ እናስተምራለን እንዲሁም ለዚህ ሕግ እንገዛለን የሚሉት የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ፈሪሳውያን ከሠሩት ከባድ ስሕተት አልተማሩም። በመሆኑም የአይሁድ እምነት የሙሴን ሕግ እንዳጣመመና አለአግባብ እንደተጠቀመበት ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም በክርስቶስ ሕግ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽማለች። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ስለራሱ ስለ ክርስቶስ ሕግ ምንነት፣ እነማን እንዲተዳደሩበት እንደተሰጠና እንዴት እንደሚተዳደሩበት እንዲሁም ከሙሴ ሕግ የሚለየው እንዴት እንደሆነ እንወያያለን። ከዚያ በኋላ ሕዝበ ክርስትና አለአግባብ የተጠቀመችበት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በዚህ መንገድ ከታሪክ በመማር ጥቅም እናገኛለን!
አዲሱ ቃል ኪዳን
3. ይሖዋ አንድን አዲስ ቃል ኪዳን አስመልክቶ ምን ተስፋ ሰጥቶአል?
3 ከይሖዋ አምላክ በቀር አንድን ፍጹም ሕግ ሊያሻሽል የሚችል ማን አለ? የሙሴ ሕግ ኪዳን ፍጹም ነበር። (መዝሙር 19:7) ሆኖም ይሖዋ እንደሚከተለው ሲል ቃል ገብቷል፦ “እነሆ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ . . . ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም።” የሙሴ ሕግ እምብርት የሆኑት አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉት በድንጋይ ጽላቶች ላይ ነበር። ይሁን እንጂ አዲሱን ቃል ኪዳን በሚመለከት ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ።”—ኤርምያስ 31:31-34
4. (ሀ) በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፈው የትኛው እስራኤል ነው? (ለ) ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ሌላ በክርስቶስ ሕግ ሥር ያሉት እነማን ናቸው?
4 በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉት እነማን ናቸው? የዚህን ቃል ኪዳን መካከለኛ የናቀው ‘የእስራኤል ቤት’ ራሱ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። (ዕብራውያን 9:15) ይልቁንስ ይህ አዲስ “እስራኤል” “የእግዚአብሔር እስራኤል” ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ብሔር ነው። (ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 2:28, 29) ከጊዜ በኋላም ይሖዋን ለማምለክ የሚፈልጉ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከእዚህ አነስተኛ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ጋር ይቀላቀላሉ። (ራእይ 7:9, 10፤ ዘካርያስ 8:23) እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ባይታቀፉም በሕጉ ሥር ይሆናሉ። (ከዘሌዋውያን 24:22 እና ከዘኁልቁ 15:15 ጋር አወዳድር።) ሁሉም ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያሉ ‘አንድ መንጋ’ እንደመሆናቸው መጠን ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ‘በክርስቶስ ሕግ ሥር’ ይሆናሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ 1 ቆሮንቶስ 9:21) ጳውሎስ ይህን አዲስ ቃል ኪዳን ‘የሚሻል ኪዳን’ ብሎ ጠርቶታል። ለምን? አንደኛው ምክንያት ይህ ቃል ኪዳን የተመሠረተው ሊመጣ ላለው ነገር ጥላ በሆኑት ነገሮች ላይ ሳይሆን በተፈጸሙ ተስፋዎች ላይ በመሆኑ ነው።—ዕብራውያን 8:6፤ 9:11-14
5. የአዲሱ ቃል ኪዳን ዓላማ ምንድን ነው? ይህ ቃል ኪዳን ከዳር እንደሚደርስ የማያጠራጥረውስ ለምንድን ነው?
5 የዚህ ቃል ኪዳን ዓላማ ምንድን ነው? ሁሉም የሰው ልጆች የሚባረኩበት የነገሥታትና ካህናት ብሔር ማስገኘት ነው። (ዘጸአት 19:6፤ 1 ጴጥሮስ 2:9፤ ራእይ 5:10) እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ በማመፃቸውና የነበራቸውን አጋጣሚ በማበላሸታቸው የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ይህን ብሔር በተሟላ መልኩ ሳያስገኝ ቀርቷል። (ከሮሜ 11:17-21 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ አዲሱ ቃል ኪዳን በዓይነቱ ልዩ ከሆነ ሕግ ጋር የተዛመደ በመሆኑ ከዳር እንደሚደርስ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ሕግ በዓይነቱ ልዩ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
ነፃ የሚያወጣው ሕግ
6, 7. የክርስቶስ ሕግ ከሙሴ ሕግ ይበልጥ ነፃነት የሚሰጥ የሆነው ለምንድን ነው?
6 የክርስቶስ ሕግ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከነፃነት ጋር ተያይዞ ተገልጿል። (ዮሐንስ 8:31, 32) “ነፃ የሆኑ ሰዎች ሕግ” እና ‘ነፃ የሚያወጣ ፍጹም ሕግ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ያዕቆብ 1:25፤ 2:12 አዓት) እርግጥ ሰዎች ያላቸው ነፃነት ሁሉ አንፃራዊ ነው። ሆኖም ይህ ሕግ ከእሱ በፊት ከነበረው የሙሴ ሕግ የበለጠ ነፃነት ይሰጣል። ይህ የሆነው እንዴት ነው?
7 በክርስቶስ ሕግ ሥር መወለድ የሚባል ነገር የለም። እንደ ዘርና የትውልድ ቦታ ያሉት ነገሮች ከዚህ ሕግ ጋር ግንኙነት የላቸውም። እውነተኛ ክርስቲያኖች የዚህን ሕግ የታዛዥነት ቀንበር ለመሸከም ከልባቸው በነፃነት ይመርጣሉ። ይህንንም ሲያደርጉ ይህ ቀንበር ልዝብና ለመሸከምም ቀላል ሆኖ ያገኙታል። (ማቴዎስ 11:28-30) እንደምታስታውሰው የሙሴ ሕግ የተሰጠው ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነና ከዚህ ኃጢአት ነፃ የሚያወጣው ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሚያስፈልገው ለማስተማር ሲባል ነበር። (ገላትያ 3:19) በአንጻሩ ደግሞ የክርስቶስ ሕግ መሲሕ እንደመጣ፣ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንደከፈለና ኃጢአትና ሞት ከጣሉብን ከባድ የጭቆና ቀንበር ነፃ የምንወጣበትን መንገድ እንደከፈተልን ያስተምራል! (ሮሜ 5:20, 21) ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ ለመሆን በመሥዋዕቱ ላይ ‘እምነት እንዳለን ማሳየት’ ያስፈልገናል።—ዮሐንስ 3:16
8. የክርስቶስ ሕግ ምንን ይጨምራል? ሆኖም በዚህ ሕግ ሥር መኖር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጎችን በቃል ማጥናትን የማይጠይቀው ለምንድን ነው?
8 ‘እምነት ማሳየት’ ለክርስቶስ ሕግ መገዛትን የሚጨምር ነገር ነው። ይህም የክርስቶስን ትእዛዛት በሙሉ ማክበርን ያካትታል። ታዲያ ይህ ማለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጎችንና ደንቦችን በቃል ማጥናት ማለት ነውን? አይደለም። የአሮጌው ኪዳን መካከለኛ የነበረው ሙሴ ሕጉን በጽሑፍ ሲያሠፍር የአዲሱ ኪዳን መካከለኛ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አንዲትም ሕግ አልጻፈም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሕግ በሕይወቱ እንዲንጸባረቅ አድርጓል። ፍጹም በሆነው አኗኗሩ ሁሉም ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ ትቷል። (1 ጴጥሮስ 2:21) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አምልኮም እንደ “መንገድ” ተደርጎ የተገለጸው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 9:2፤ 19:9, 23፤ 22:4፤ 24:22) የክርስቶስ ሕግ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ሲንጸባረቅ አይተዋል። ኢየሱስን መምሰል ማለት ይህን ሕግ መታዘዝ ማለት ነበር። ለእሱ ያላቸው ልባዊ ፍቅር በትንቢት እንደተነገረው በእርግጥም ሕጉ በልባቸው ውስጥ እንደተጻፈ የሚያመለክት ነው። (ኤርምያስ 31:33፤ 1 ጴጥሮስ 4:8) ደግሞም በፍቅር ተነሣስቶ የሚታዘዝ ሰው ፈጽሞ እንደተጨቆነ ሆኖ አይሰማውም። የክርስቶስ ሕግ “ነፃ የሆኑ ሰዎች ሕግ” ተብሎ ሊጠራ የሚችልበት ሌላኛው ምክንያት ይህ ነው።
9. የክርስቶስ ሕግ ዋነኛ መሠረት ምንድን ነው? ይህስ አንድ አዲስ ትእዛዝ የሚያካትተው እንዴት ነው?
9 ፍቅር በሙሴ ሕግ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት ከነበረ ለክርስትና ሕግ ደግሞ ከዚያ የበለጠ ዋነኛው መሠረት ነው። በመሆኑም የክርስቶስ ሕግ አንድ አዲስ ሕግ ያካተተ ሲሆን ይህም ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዲያሳዩ የሚጠይቅ ነው። ፍቅር የሚያሳዩት እንደ ኢየሱስ መሆን ይኖርበታል፤ እርሱ ነፍሱን ለወዳጆቹ በፈቃደኛነት አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 15:13) ስለዚህ የክርስቶስ ሕግ ከሙሴ ሕግ ይበልጥ የላቀ የቲኦክራሲያዊ አገዛዝ መግለጫ ነው ሊባል ይችላል። ይህ መጽሔት ከአሁን ቀደም እንደገለጸው “ቲኦክራሲ የአምላክ አገዛዝ ነው፤ አምላክ ደግሞ ፍቅር ነው፤ ስለዚህ ቲኦክራሲ ፍቅራዊ አገዛዝ ነው።”
ኢየሱስና ፈሪሳውያን
10. የኢየሱስ ትምህርት ከፈሪሳውያን ትምህርት የሚለየው እንዴት ነው?
10 እንግዲያውስ ኢየሱስ በዘመኑ ከነበሩት የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ጋር መቃረኑ ምንም አያስደንቅም። ጻፎችና ፈሪሳውያን ‘ነፃ ስለሚያወጣው ፍጹም ሕግ’ ጨርሶ አስበው አያውቁም። ሰው ሠራሽ ደንቦችን በማውጣት ሕዝቡን ለመቆጣጠር ሞክረዋል። ትምህርታቸው ሌሎችን የሚጨቁን፣ የሚኮንንና አፍራሽ አስተሳሰብ የሚያስተላልፍ ነበር። ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ የኢየሱስ ትምህርት የሚያንጽና አዎንታዊ ነገሮች የሞላበት ነበር! ኢየሱስ ተግባራዊ ሐሳቦችን የሚያፈልቅና የሕዝቡን የልብ ትርታ የሚያዳምጥ ሰው ነበር። በዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያጋጥሙ ምሳሌዎችን በመጠቀምና የአምላክን ቃል እንደ ባለ ሥልጣን በመጥቀስ ቀላል በሆነ መንገድ ከልቡ ያስተምር ነበር። በዚህ ምክንያት “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ።” (ማቴዎስ 7:28) አዎን፣ የኢየሱስ ትምህርት ልባቸውን ነክቶታል!
11. ኢየሱስ የሙሴ ሕግ በምክንያታዊነትና በምሕረት ሊሠራበት ይገባ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ላይ ተጨማሪ ደንቦችን ከማከል ይልቅ አይሁዳውያን ሕጉን በምክንያታዊነትና በምሕረት እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባ እንደነበር አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ደም እየፈሰሳት ትሠቃይ የነበረች ሴት ወደ እሱ የቀረበችበትን አጋጣሚ አስታውስ። በሙሴ ሕግ መሠረት እሷ የነካችው ሰው ሁሉ ርኩስ ይሆን ስለነበር ከብዙ ሰዎች መሐል መቀላቀል እንዳልነበረባት ምንም አያጠራጥርም! (ዘሌዋውያን 15:25-27) ይሁን እንጂ ለመፈወስ ከነበራት ከፍተኛ ጉጉት የተነሣ በሕዝቡ መካከል አልፋ ገብታ የኢየሱስን ልብስ ነካች። ደሙ ወዲያውኑ አቆመ። ሕጉን በመጣሷ ምክንያት ነቀፋትን? አልነቀፋትም፤ ከዚህ ይልቅ የነበረችበትን አሳዛኝ ሁኔታ በመረዳት የሕጉ ዋነኛ መሠረት የሆነውን ፍቅርን አሳይቷል። በርኅራኄ ስሜት “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ” አላት።—ማርቆስ 5:25-34
የክርስቶስ ሕግ ልል ነውን?
12. (ሀ) የክርስቶስ ሕግ ልል ነው ብለን ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ብዙ ሕጎችን ማውጣት ብዙ ማምለጫ ቀዳዳዎችን ወደ መፈላለግ እንደሚመራ የሚያሳየው ምንድን ነው?
12 የክርስቶስ ሕግ ‘ነፃ የሚያወጣ’ በመሆኑ ልል ነው፣ የፈሪሳውያን ወጎች ግን ቢያንስ ለሕዝቡ አኗኗር ጥብቅ ድንበር አበጅተውለት ነበር ወደሚል መደምደሚያ ልንደርስ ይገባልን? በፍጹም አይገባም። ዛሬ ካሉት የሕግ አወቃቀሮች ለመረዳት እንደሚቻለው ብዙውን ጊዜ ሕግ ሲበዛ ሰዎችም ያንኑ ያክል ማምለጫ ቀዳዳዎችን ይፈልጋሉ።a በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የፈሪሳውያን ደንቦች ሕዝቡ ማምለጫ መንገዶችን እንዲፈልግ፣ ከፍቅር ያልመነጩ የለበጣ ሥራዎችን እንዲሠራ እንዲሁም ውስጣዊ ድክመቱን ለመሸፈን ራስን የማመፃደቅ ጭንብል እንዲያጠልቅ ገፋፍተውታል።—ማቴዎስ 23:23, 24
13. የክርስቶስ ሕግ ከማናቸውም ሌላ ሕግ ይበልጥ ከፍ ያለ የአቋም ደረጃ ያለው አኗኗር እንዲኖረን የሚያደርገው ለምንድን ነው?
13 በተቃራኒው ግን የክርስቶስ ሕግ እንደዚህ ላሉት አስተሳሰቦች ቦታ የለውም። እንዲያውም አንድን በይሖዋ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ሕግ መታዘዝና ክርስቶስ ለሌሎች ያሳየውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር በመኮረጅ ይህን ታዛዥነት ማሳየት ማንኛውንም ሌላ ሕግ በመታዘዝ ከምናገኘው በጣም የላቀ የአቋም ደረጃ እንዲኖረን ያደርጋል። ፍቅር ማምለጫ ቀዳዳ አይፈልግም፤ የተከለከሉ ናቸው ተብለው በግልጽ በሕግ ያልተቀመጡትን ጎጂ ነገሮች እንኳ ከማድረግ ይጠብቀናል። (ማቴዎስ 5:27, 28ን ተመልከት።) በዚህ መንገድ የክርስቶስ ሕግ ማንኛውም ሌላ ሕግ የማያደርገውን እንደ ልግስና፣ እንግዳ ተቀባይነትና ፍቅር ያሉትን ባሕርያት ለሌሎች እንድናሳይ ይገፋፋናል።—ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7፤ ዕብራውያን 13:16
14. በክርስቶስ ሕግ ሥር መኖር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል?
14 የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ አባላቱ ከክርስቶስ ሕግ ጋር ተስማምተው በተመላለሱ መጠን በዘመኑ ምኩራቦች ውስጥ ሰፍኖ ከነበረው ግትር፣ ነቀፋ የሞላበትና የግብዝነት አመለካከት ጋር ሲነጻጸር ሞቅ ያለና ፍቅር የሰፈነበት ሁኔታ ነበረው። የእነዚህ አዳዲስ ጉባኤዎች አባላት ‘ነፃ በሆኑ ሰዎች ሕግ’ እየኖሩ እንዳለ ከልባቸው ተገንዝበው መሆን ይኖርበታል!
15. ሰይጣን የክርስቲያን ጉባኤን ለመበከል ገና ከጅምሩ ያደረጋቸው አንዳንድ ጥረቶች ምንድን ናቸው?
15 ይሁንና ሰይጣን የእስራኤልን ብሔር እንደበከለ ሁሉ የክርስቲያን ጉባኤንም ከውስጥ ለመበከል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ተኩላ ያሉ “ጠማማ ነገርን የሚናገሩ” ሰዎች እንደሚነሡና የአምላክን መንጋ እንደሚጨቁኑ አስጠንቅቆ ነበር። (ሥራ 20:29, 30) ጳውሎስ የክርስቶስ ሕግ ያስገኘውን አንፃራዊ ነፃነት ክርስቶስ በፈጸመው የሙሴ ሕግ ሥር ባለው ባርነት ለመለወጥ ይፈልጉ ከነበሩት የአይሁድን እምነት የሚያስፋፉ ሰዎች ጋር መጋፈጥ አስፈልጎት ነበር። (ማቴዎስ 5:17፤ ሥራ 15:1፤ ሮሜ 10:4) የመጨረሻው ሐዋርያ ከሞተ በኋላ እንዲህ ዓይነቱን ክህደት የሚያግድ ጠፋ። በዚህ ምክንያት ብክለቱ በእጅጉ ተስፋፍቷል።—2 ተሰሎንቄ 2:6, 7
ሕዝበ ክርስትና የክርስቶስን ሕግ በክላለች
16, 17. (ሀ) በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተፈጸመው ብክለት ምን ዓይነት መልክ አለው? (ለ) የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችው ሕግ ስለ ጾታ የተዛባ አመለካከት ያስፋፋው እንዴት ነው?
16 እንደ አይሁድ እምነት ሁሉ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተፈጸመውም ብክለት ዓይነቱ ብዙ ነው። እሷም በሐሰት መሠረተ ትምህርቶችና ልቅ በሆነ ሥነ ምግባር ወጥመድ ወድቃለች። ባብዛኛው ከውጭ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ያደረገቻቸው ጥረቶች ሁሉ ከንጹሕ አምልኮ የቀራትን ፍርፋሪ እንኳ ጠራርገው የሚያጠፉ ሆነዋል። ድርቅ ያሉና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሕጎች እንደ አሸን ፈልተውባታል።
17 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብዛት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያን ሕጎች በማውጣት በኩል ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች። እነዚህ ሕጎች በተለይ ወሲብን በሚመለከት የተዛባ አስተሳሰብ የሚያስተላልፉ ናቸው። ሴክሹዋሊቲ ኤንድ ካቶሊሲዝም የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁሉንም ዓይነት ደስታ በጥርጣሬ ዓይን የሚያየውን የግሪካውያንን የኢስጦኢክ ፍልስፍና ተቀብላለች። ቤተ ክርስቲያኗ በትዳር ውስጥ የሚገኘውን ጨምሮ ከጾታ ግንኙነት የሚገኝ ማንኛውም ደስታ ኃጢአት ነው ብላ ታስተምራለች። (ከምሳሌ 5:18, 19 ጋር አነጻጽር።) የጾታ ግንኙነት ለመራባት ካልሆነ በቀር ሌላ ዓላማ የለውም ባይ ናቸው። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ማንኛውም ዓይነት የእርግዝና መከላከያ ከባድ ኃጢአት ነው በማለት ያወግዛል፤ አንዳንድ ጊዜም የብዙ ዓመታት ንስሐ ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ ቀሳውስት እንዳያገቡ የሚከለክለው ድንጋጌ ሕፃናትን በጾታ ማስነወርን ጨምሮ ልቅ የሆኑ የጾታ ድርጊቶች እንዲስፋፉ በር ከፍቷል።—1 ጢሞቴዎስ 4:1-3
18. የቤተ ክርስቲያን ሕግጋት መበራከታቸው ምን ውጤት አስከትሏል?
18 የቤተ ክርስቲያን ሕጎች እየተበራከቱ ሲሄዱ በመጻሕፍት መልክ ተዘጋጅተው ወጡ። እነዚህም መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ገነው መታየት ጀመሩ። (ከማቴዎስ 15:3, 9 ጋር አወዳድር።) ካቶሊኮች እንደ አይሁድ እምነት ሁሉ ዓለማዊ ጽሑፎችን ይጠራጠሩና አብዛኛዎቹንም አስጊ እንደሆኑ አድርገው ያዩአቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ይህ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ከሚሰጠው ጥበብ ያለበት ማስጠንቀቂያ ራቀ። (መክብብ 12:12፤ ቆላስይስ 2:8) በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ የነበረው ዤሮም “አቤቱ ጌታ ሆይ፣ ከአሁን ወዲህ ዓለማዊ መጻሕፍት በእጄ ቢገቡ ወይም ባነባቸው አንተን እንደካድኩ ይቆጠር” ሲል ተናግሮ ነበር። ከጊዜ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለማዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የያዙ መጻሕፍትን ሳይቀር መጽሐፍ የተባለውን ሁሉ ሳንሱር ማድረግ ጀመረች። በዚህም ምክንያት የ17ኛው መቶ ዘመን የጠፈር ተመራማሪ የነበረው ጋሊሊዮ ምድር በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች በማለቱ ተወግዟል። ቤተ ክርስቲያን ለማንኛውም ጥያቄ ሌላው ቀርቶ ስለ ጠፈር ጥናትም እንኳ ሳይቀር መልስ መስጠት ያለብኝ እኔ ነኝ የሚለው ድርቅ ያለ አቋሟ ውሎ አድሮ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት አዳክሟል።
19. ገዳማት የፈላጭ ቆራጭነትን አመራር ያራመዱት እንዴት ነው?
19 የቤተ ክርስቲያን ሕግ የማውጣት ልማድ መነኮሳት ከዚህ ዓለም ተገልለውና ራሳቸውን ክደው በሚኖሩባቸው ገዳማት ውስጥም ተስፋፍቶ ይገኛል። አብዛኞቹ የካቶሊክ ገዳማት ‘የቅዱስ ቤንዴክትን ደንብ’ በጥብቅ ይከተላሉ። አባዎች (“አባት” የሚል ትርጉም ካለው የአረማይክ ቃል የመጣ ነው) ፍጹም ሥልጣን አላቸው። (ከማቴዎስ 23:9 ጋር አወዳድር።) አንድ መነኩሴ ከወላጆቹ ስጦታ ቢመጣለት ስጦታውን መውሰድ ያለበት እርሱ ይሁን ወይም ሌሎች መነኮሳት የሚወስኑት አባው ናቸው። ያወጡት ደንብ የብልግና ንግግሮችን የሚያወግዝ ብቻ ሳይሆን “ማንኛውም ደቀ መዝሙር እንዲህ ያሉትን ነገሮች ሊናገር አይገባም” በማለት ተራ ወሬና ቀልድን ሁሉ የሚከለክል ነበር።
20. የፕሮቴስታንት እምነትም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ ፈላጭ ቆራጭ አመራር እንደተካነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
20 የካቶሊክ እምነት በጨመራቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሐሳቦች ላይ ተሐድሶ ለማካሄድ የተነሣው የፕሮቴስታንት እምነትም ከክርስቶስ ሕግ ማስረጃ የማይገኝላቸውን ፈላጭ ቆራጭ ደንቦች በማውጣት ተክኗል። ለምሳሌ ያህል ዋነኛ የተሐድሶ አራማጅ የነበረው ጆን ካልቪን “የታደሰችው ቤተ ክርስቲያን ሕግ አውጪ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። ካልቪን ብዙ ጥብቅ ደንቦችን በማውጣት “የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት በበላይነት የመቆጣጠር” “ሥልጣን” አላቸው ባላቸው “ሽማግሌዎች” አስፈጻሚነት በጄኔቫ የሚገኘውን ቤተ ክርስቲያን አስተዳድሯል። (ከ2 ቆሮንቶስ 1:24 ጋር አነጻጽር።) ቤተ ክርስቲያን ትናንሽ ሆቴሎችን በመቆጣጠር ምን ዓይነት የመወያያ ርዕሶች እንደሚፈቀዱ ደንግጋ ነበር። ቅጥ ያጣ ዘፈን መዝፈን ወይም መደነስ የመሰሉትን ኃጢአቶች የሚፈጽሙ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸው ነበር።b
ከሕዝበ ክርስትና ስሕተቶች መማር
21. ሕዝበ ክርስትና ያሳየችው ‘ከተጻፈው የማለፍ’ አዝማምያ በጥቅሉ ሲታይ ምን ውጤቶችን አስከትሏል?
21 እነዚህ ሁሉ ደንቦችና ሕጎች ሕዝበ ክርስትናን ከብክለት አድነዋታልን? በፍጹም! ሕዝበ ክርስትና በዛሬው ጊዜ ከመጠን በላይ ጥብቅ ከሆኑት አንስቶ እጅግ ልቅ እስከሆኑት ድረስ በብዙ መቶዎች በሚቆጠሩ ኑፋቄዎች ተከፋፍላለች። ሁሉም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሰብዓዊ አስተሳሰብ መንጋውን እንዲገዛውና በመለኮታዊው ሕግ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ በመፍቀዳቸው ‘ከተጻፈው አልፈዋል።’—1 ቆሮንቶስ 4:6
22. ሕዝበ ክርስትና የፈጸመችው ድርጊት የክርስቶስ ሕግ ደብዛው እንዲጠፋ አላደረገም የምንለው ለምንድን ነው?
22 ይሁን እንጂ ሕዝበ ክርስትና የፈጸመችው ድርጊት የክርስቶስ ሕግ ደብዛው እንዲጠፋ አድርጓል ማለት አይደለም። ይሖዋ እንዲያው እዚህ ግባ የማይባሉ ሰብዓዊ ፍጥረታት መለኮታዊውን ሕግ እንዲያጠፉ ፈጽሞ አይፈቅድላቸውም። ዛሬ የክርስቶስ ሕግ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል በሥራ እየተተረጎመ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ሕግ የመመራት ትልቅ መብት አግኝተዋል። ይሁንና የአይሁድ እምነትና ሕዝበ ክርስትና በመለኮታዊው ሕግ ላይ ስለፈጸሙት ነገር ከመረመርን በኋላ እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ተገቢ ይሆናል፦ ‘የመለኮታዊውን ሕግ መንፈስ በሚያፍን ሰብዓዊ አስተሳሰብና ደንብ የአምላክን ቃል ላለመበረዝ እየተጠነቀቅን በክርስቶስ ሕግ መሠረት መኖር የምንችለው እንዴት ነው?’ በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ ሕግ በውስጣችን ሊያሳድር የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዛሬ ያለው የአይሁድ እምነት ይህን የመሰለ መልክ እንዲኖረው ፈሪሳውያን ያሳደሩት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት ባለመሆኑ ዛሬም ብዙ ገደቦች ከተጨማመሩበት የሰንበት ሕግ ማምለጫ ቀዳዳ መፈላለጋቸው አያስገርምም። ለምሳሌ ያህል በሰንበት ቀን የአክራሪ አይሁዳውያንን ሆስፒታል የሚጎበኝ አንድ ሰው ተጠቃሚዎች የአሳንሱሩን ቁልፍ በመጫን እንደ ኃጢአት የሚቆጠር “ሥራ” እንዳይሠሩ ሲባል አሳንሱሩ ራሱ በየፎቁ እንደሚቆም ይገነዘባል። አንዳንድ አክራሪ የአይሁድ እምነት ተከታይ የሆኑ ዶክተሮች የመድኃኒት ትእዛዞችን የሚጽፉት ቀለሙ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚለቅ ብዕር ነው። ለምን? ሚሽና መጻፍን ከ“ሥራ” የሚመድበው ቢሆንም “መጻፍ” ማለት ዘላቂ ምልክት መተው ማለት ነው ብሎ ስለሚያብራራ ነው።
b የካልቪንን አንዳንድ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች የተቃወመው ሰርቬተስ መናፍቅ ተብሎ በእንጨት ላይ በእሳት ተቃጥሏል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የክርስቶስ ሕግ ዋነኛ መሠረት ምንድን ነው?
◻ የኢየሱስ የማስተማር ዘዴ ከፈሪሳውያን የሚለየው እንዴት ነው?
◻ ሰይጣን ግትርነትንና ጥብቅ ደንብ የማውጣትን መንፈስ ሕዝበ ክርስትናን ለመበከል የተጠቀመበት እንዴት ነው?
◻ ለክርስቶስ ሕግ መገዛት የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጠቃሚ ውጤቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የሙሴን ሕግ ምክንያታዊ በሆነና ምሕረት በተሞላበት መንገድ በሥራ ላይ አውሏል