ምዕራፍ 7
መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫልን?
በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲሰነዘር የሚሰማው ክስ እርስ በርሱ ይጋጫል የሚል ነው። ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ያለውን ነቀፋ የሚሰነዝሩ ሰዎች እንዲሁ ከሌሎች የሰሙትን ያስተጋባሉ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው አንብበውት አያውቁም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በእርግጥም የሚጋጩ የሚመስሉ ነገሮችን በማግኘታቸው ተረብሸዋል።
1, 2. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘረው ክስ ምን የሚል ነው? (ለ) የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ስናነጻጽር ልናስታውሰው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? (ሐ) ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ተመሳሳይ ስለሆነ ታሪክ ሲገልጹ አንዳንድ ጊዜ ልዩነት እንዲታይ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ከሆነ እርስ በርሱ መስማማት እንጂ መጋጨት የለበትም። ታዲያ አንዳንዶቹ ጥቅሶች ከሌሎቹ ጋር የሚጋጩ የሚመስሉት ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ቢሆንም በብዙ መቶ ዘመናት ልዩነት በኖሩ የተለያዩ ሰዎች እንደተጻፈ መዘንጋት የለብህም። እነዚህ ጸሐፊዎች የተለያየ አስተዳደግ፣ የአጻጻፍ ስልትና ተሰጥዎ የነበራቸው ሲሆን እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች በጽሑፍ ሥራቸው ላይ ተንጸባርቀዋል።
2 ከዚህም በላይ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ጸሐፊዎች ስለ አንድ ሁኔታ ቢተርኩ አንደኛው የጨመራቸውን ዝርዝር ሁኔታዎች ሌላው ሊያስቀራቸው ይችላል። በተጨማሪም የተለያዩ ጸሐፊዎች ጉዳዩን የሚገልጹበት መንገድ ይለያያል። አንዱ የጊዜ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ሲጽፍ ሌላው ደግሞ በሌላ መንገድ ያስቀምጠው ይሆናል። በዚህ ምዕራፍ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ይጋጫሉ የሚባሉ አንዳንድ ሐሳቦች አንሥተን ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት ማስታረቅ እንደሚቻል እንመለከታለን።
የየራሳቸውን አገላለጽ የተጠቀሙ ምሥክሮች
3, 4. አገልጋዩ የታመመበትን መቶ አለቃ በሚመለከት በማቴዎስና በሉቃስ ዘገባዎች መካከል የማይጣጣም የሚመስል ምን ነገር ይታያል? እነዚህ ሁለት ዘገባዎች ሊታረቁ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
3 አንዳንድ “ግጭቶች” የሚፈጠሩት ተመሳሳይ ስለሆነ ጉዳይ የሚገልጹ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ዘገባዎች በሚኖሩበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ያህል በማቴዎስ 8:5 ላይ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ “የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ” ብላቴናውን እንዲፈውስለት እንደለመነው እናነባለን። ይሁን እንጂ በሉቃስ 7:3 ላይ ይህንኑ መቶ አለቃ በሚመለከት “ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው” የሚል ቃል ሰፍሯል። ኢየሱስን ቀርቦ ያነጋገረው መቶ አለቃው ራሱ ነው ወይስ ሽማግሌዎችን ነው የላከው?
4 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው መልሱ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ልኳል የሚል ይሆናል። ታዲያ ማቴዎስ ሰውዬው ራሱ ኢየሱስን እንደለመነው አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው? በአይሁድ ሽማግሌዎች አማካኝነት ቢሆንም ኢየሱስን የጠየቀው ሰውዬው ስለሆነ ነው። ሽማግሌዎቹ የሰውዬው ቃል አቀባይ ሆነው አገልግለዋል።
5. የቤተ መቅደሱን የግንባታ ሥራ ያከናወኑት ሌሎች ሆነው ሳለ መጽሐፍ ቅዱስ ሰሎሞን እንደሠራው አድርጎ የሚገልጸው ለምንድን ነው?
5 ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል 2 ዜና መዋዕል 3:1 ላይ “ሰሎሞንም . . . በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ” ይላል። ከዚያም “ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን . . . ቤት ጨረሰ” የሚል እናነባለን። (2 ዜና መዋዕል 7:11) ቤተ መቅደሱን ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የገነባው ሰሎሞን ራሱ ነው ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። የግንባታ ሥራውን በቀጥታ የሠሩት ብዙ ባለሙያዎችና የጉልበት ሠራተኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ሥራውን በኃላፊነት የሚያቀናጀው ሰሎሞን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስም ቤቱን እርሱ እንደሠራው የሚናገረው ለዚህ ነው። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ የማቴዎስም ወንጌል መቶ አለቃው ኢየሱስን ቀርቦ እንዳነጋገረው ይነግረናል። ይሁን እንጂ የመቶ አለቃው በአይሁድ ሽማግሌዎች አማካኝነት እንዳነጋገረው ሉቃስ ተጨማሪ መግለጫ ይሰጠናል።
6, 7. የዘብዴዎስ ልጆች ያቀረቡትን ጥያቄ የሚገልጹትን ሁለት የተለያዩ የወንጌል ዘገባዎች እንዴት ልናስታርቃቸው እንችላለን?
6 ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ምሳሌ እነሆ። በማቴዎስ 20:20, 21 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ [ኢየሱስ] ቀረበች።” ያቀረበችው ጥያቄ ኢየሱስ በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ ለልጆቼ የተሻለው ቦታ ይሰጥልኝ የሚል ነበር። በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ይህንኑ ታሪክ በሚመለከት እንዲህ እናነባለን:- “የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ [ኢየሱስ] ቀርበው:- መምህር ሆይ፣ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት።” (ማርቆስ 10:35-37) ለኢየሱስ ጥያቄውን ያቀረበው ማን ነበር? ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ናቸው ወይስ እናታቸው?
7 በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ጥያቄውን ያቀረቡት ማርቆስ እንዳለው ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ናቸው። ይሁን እንጂ ጥያቄው ለኢየሱስ የቀረበው በእናታቸው አማካኝነት ነበር። የልጆቿ ቃል አቀባይ ሆናለች። ሌሎቹ ሐዋርያት የዘብዴዎስ ልጆች እናት ምን እንዳደረገች በሰሙ ጊዜ በእናትየው ሳይሆን “በሁለቱ ወንድማማች” እንደተቆጡ የሚገልጸው የማቴዎስ ሪፖርት ይህን ሐሳብ የሚደግፍ ነው።—ማቴዎስ 20:24
8. ስለ አንድ ተመሳሳይ ታሪክ የሚገልጹ ሁለት ዘገባዎች አንዳቸው ከሌላው የተለዩ ቢሆኑም ሁለቱም እውነት ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?
8 ሁለት ሰዎች አንድ ላይ ስላዩት ነገር ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? እያንዳንዳቸው እነርሱን በጣም ያስገረማቸውን ጉዳይ ጎላ አድርገው እንደገለጹ አላስተዋልክም? አንዱ የጨመረውን ነገር ሌላው ትቶት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሁለቱም የሚናገሩት እውነት ነው። ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የሚዘግቡት የአራቱ ወንጌሎችም ሆነ ከአንድ በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸው የሌሎቹ ታሪካዊ ክንውኖች ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። አንዱ ዝርዝር ሁኔታውን ሲገልጽ ሌላው ባይገልጽም እያንዳንዱ ጸሐፊ ያሰፈረው መረጃ ትክክለኛ ነው። ሁሉንም ዘገባዎች በመመርመር ስለ ተፈጸመው ነገር የተሟላ ግንዛቤ ማግኘት ይቻላል። እንዲህ ያሉት ልዩነቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የየራሳቸው የአቀማመጥ ስልት እንዳላቸው ያሳያሉ። መሠረታዊ አንድነታቸው ደግሞ እውነት መሆናቸውን ያረጋግጣል።
ከዙሪያው ያለውን ሐሳብ አንብብ
9, 10.ከጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ቃየን ሚስቱን ከየት እንዳገኘ ለመገንዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?
9 ብዙውን ጊዜ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ከተመለከትነው የሐሳብ ግጭት መስለው የሚታዩት ነገሮች መፍትሔ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል የቃየንን ሚስት በተመለከተ ባብዛኛው የሚነሣውን ጥያቄ እንመልከት። በዘፍጥረት 4:1, 2 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “[ሔዋን] ፀነሰችም፣ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም:- ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች።” ሁላችንም እንደምናውቀው ቃየን አቤልን ገደለው። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ቃየን ሚስት እንዳገባና ልጆችን እንደወለደ እናነባለን። (ዘፍጥረት 4:17) አዳምና ሔዋን የነበሯቸው ሁለት ወንዶች ልጆች ብቻ ከሆኑ ቃየን ሚስት ከየት አገኘ?
10 መልሱ አዳምና ሔዋን ከሁለት በላይ ልጆች ነበሯቸው የሚል ነው። በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ እንደምንረዳው ትልቅ ቤተሰብ ሆነው ነበር። በዘፍጥረት 5:3 ላይ አዳም ሴት የተባለ ሌላ ወንድ ልጅ እንደወለደ ይገልጽልንና ከዚያ ቀጥሎ ያለው ቁጥር “ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ” ይላል። (ዘፍጥረት 5:4) በመሆኑም ቃየን ከእህቶቹ አንዷን ወይም ከወንድሞቹ ልጆች አንዷን አግብቶ ሊሆን ይችላል። የሰው ልጅ ከፍጽምና ብዙም ባልራቀበት በዚያ የሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ ይህ መሰሉ ጋብቻ በሚወለዱት ልጆች ላይ ዛሬ እንደሚታየው ዓይነት ችግር የሚያስከትል አልነበረም።
11. አንዳንዶች በሐዋርያው ጳውሎስና በያዕቆብ መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ይናገራሉ?
11 ከጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመርመራችን አንዳንዶች በጳውሎስና በያዕቆብ መካከል አለ የሚሉትን የሐሳብ አለመጣጣምም እንድንረዳ ያስችለናል። በኤፌሶን 2:8, 9 ላይ ጳውሎስ ክርስቲያኖች የሚድኑት በእምነት እንጂ በሥራ እንዳይደለ ተናግሯል። “በእምነት አድኖአችኋልና . . . እንጂ ከእናንተ አይደለም” ብሏል። ይሁን እንጂ ያዕቆብ የሥራን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” (ያዕቆብ 2:26) እነዚህ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች እንዴት ሊታረቁ ይችላሉ?
12, 13. ያዕቆብ የተናገራቸው ቃላት ከጳውሎስ ሐሳብ ጋር ከመቃረን ይልቅ ይበልጥ የተሟላ የሚያደርጉት እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ ከተናገራቸው ቃላት ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስንመለከት አንዱ ዓረፍተ ነገር ሌላውን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ ሆኖ እናገኘዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገር የነበረው አይሁዳውያኑ የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ ስለሚያደርጉት ጥረት ነበር። ሕጉን አንድ በአንድ መጠበቅ ከቻሉ ጻድቃን እንደሚሆኑ ያስቡ ነበር። ጳውሎስ ይህ የማይቻል ነገር መሆኑን ጠቁሟቸዋል። ኃጢአት የወረስን ሰዎች በመሆናችን በራሳችን ሥራ ጻድቅ ልንሆንና መዳን የሚገባን ሆነን ልንገኝ አንችልም። መዳን የምንችለው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት አማካኝነት ብቻ ነው።—ሮሜ 5:18
13 ይሁን እንጂ ያዕቆብ እምነት በሥራ ካልተደገፈ ብቻውን ዋጋ የለውም የሚለውን ወሳኝ ነጥብ ጨምሯል። በኢየሱስ ላይ እምነት አለኝ የሚል ሰው እምነቱን በሥራ ማረጋገጥ አለበት። በሥራ ያልተደገፈ እምነት የሞተ ስለሚሆን ለመዳን አያበቃም።
14. ሐዋርያው ጳውሎስ ሕያው የሆነ እምነት በሥራ ሊገለጽ ይገባል ከሚለው ሐሳብ ጋር እንደሚስማማ የሚያሳየው የትኛው ጥቅስ ነው?
14 ሐዋርያው ጳውሎስም ከዚሁ አባባል ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ሲሆን ብዙውን ጊዜም ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለማሳየት ሊሳተፉባቸው የሚገቡትን ሥራዎች ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል ለሮሜ ሰዎች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም ለሕዝብ ምሥክርነት በመስጠት ይድናልና።” ለሰዎች ‘ሕዝባዊ ምሥክርነት መስጠት’ ማለትም እምነታችንን ለሌሎች ማካፈል ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነገር ነው። (ሮሜ 10:10 NW፤ በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ኤፌሶን 5:15, 21-33፤ 6:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:5፤ ዕብራውያን 10:23-25ን ተመልከት።) ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ሊያደርገው የሚችለው የትኛውም ሥራ ሆነ የሙሴን ሕግ ለመፈጸም የሚደረግ ማንኛውም ጥረት የዘላለም ሕይወትን እንደ ደመወዝ ሊያስገኝለት አይችልም። ይህ፣ እምነት የሚያሳዩ ሰዎች ‘ከአምላክ የሚያገኙት ስጦታ’ ነው።—ሮሜ 6:23፤ ዮሐንስ 3:16
የተለያዩ አመለካከቶች
15, 16. ሙሴና ኢያሱ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ቦታ አንዳቸው ‘ከዮርዳኖስ ወዲህ’ ሌላቸው ደግሞ ‘ከዮርዳኖስ ማዶ’ ቢሉትም ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?
15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንድን ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫ የጻፉባቸው ወይም ዘገባቸውን በተለያየ መንገድ ያቀረቡባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እነዚህን ልዩነቶች ግምት ውስጥ ካስገባን የሚጋጩ መስለው የሚታዩትን ተጨማሪ ነጥቦችም በቀላሉ መፍታት ይቻላል። በዘኁልቁ 35:14 (NW) ላይ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ስለሚገኘው አካባቢ ሲናገር “ከዮርዳኖስ ወዲህ” ማለቱ ለዚህ እንደ ምሳሌ ይሆነናል። ኢያሱ ግን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን አካባቢ “ከዮርዳኖስ ማዶ” ብሎታል። (ኢያሱ 22:4) ትክክል የሆነው የትኛው አባባል ነው?
16 ሁለቱም ትክክል ናቸው። እንደ ዘኁልቁ መጽሐፍ ዘገባ ከሆነ እስራኤላውያኑ ገና የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር አልገቡም ነበር። ስለዚህ ለእነርሱ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለው ቦታ “ወዲህ” ነበር። ይሁን እንጂ ኢያሱ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ነበር። አሁን እርሱ ያለው ከወንዙ በስተ ምዕራብ በከነዓን ምድር ነው። በመሆኑም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ቦታ “ማዶ” ሊለው ችሏል።
17. (ሀ) አንዳንዶች በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ምን የሐሳብ አለመጣጣም አለ ይላሉ? (ለ) የሐሳብ አለመጣጣም ለተባለው ለዚህ ነጥብ መሠረታዊው ምክንያት ምንድን ነው?
17 በተጨማሪም አንድ ትረካ የተቀመጠበት መንገድ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሐሳብ እንዳለ ሊያስመስል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1:24-26 ላይ እንስሳት ከሰዎች በፊት እንደተፈጠሩ ይጠቁመናል። ይሁን እንጂ ዘፍጥረት 2:7, 19, 20ን ስናነብ እንስሳት ከሰው በኋላ መፈጠራቸውን የሚገልጽ ይመስላል። ይህ ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? ስለ ፍጥረት የሚናገሩት ሁለቱም ዘገባዎች ጉዳዩን ያቀረቡት ከሁለት የተለያየ አቅጣጫ በመሆኑ ነው። የመጀመሪያው ዘገባ የሚገልጸው ሰማይና ምድር እንዲሁም በውስጣቸው ያለው ነገር ሁሉ ስለመፈጠሩ ነው። (ዘፍጥረት 1:1–2:4) ሁለተኛው ደግሞ የሰው ዘር በመፈጠሩና በኃጢአት በመውደቁ ላይ ያተኮረ ነው።—ዘፍጥረት 2:5–4:26
18. በመጀመሪያዎቹ የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሱት የፍጥረት ዘገባዎች መካከል አለ የሚባለውን ልዩነት ማስታረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
18 የመጀመሪያው ዘገባ በስድስት ተከታታይ ‘ቀናት’ ተከፋፍሎ በጊዜ ቅደም ተከተል የቀረበ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የተጻፈው ከርዕሰ ጉዳዩ ጠቀሜታ አንጻር ነው። ከአጭር የመንደርደሪያ ሐሳብ በኋላ በቀጥታ ስለ አዳም መፈጠር መተረክ ይጀምራል። ቀጥሎ የሚጠቀሰው ጉዳይ ዋነኛ ተዋናዮች እርሱና ቤተሰቡ ስለሆኑ ይህ ምክንያታዊ አቀራረብ ነው። (ዘፍጥረት 2:7) ከዚያ ሌሎቹ መረጃዎች እንደ አስፈላጊነቱ ቀርበዋል። አዳም ከተፈጠረ በኋላ በኤደን ገነት እንደተቀመጠ እናነባለን። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለ ኤደን ገነት መተከልም እናነባለን። (ዘፍጥረት 2:8, 9, 15) ይሖዋ ‘ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሁሉ’ ስም እንዲያወጣ ለአዳም ነገረው። ምንም እንኳን የተፈጠሩት አዳም ሕልውና ከማግኘቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም ይሖዋ አምላክ ‘እነዚህን ሁሉ ፍጥረታት ከመሬት እንደሠራቸው’ ለመጥቀስ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።—ዘፍጥረት 2:19፤ 1:20, 24, 26
ዘገባውን በጥንቃቄ አንብብ
19. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሩሳሌም ድል ስለመደረጓ በሚሰጠው ገለጻ ረገድ ምን ግራ የሚያጋባ የሚመስል ነገር አለ?
19 አንዳንድ ጊዜ የሚቃረኑ መስለው የሚታዩትን ሐሳቦች ለማስማማት የሚያስፈልገው ዘገባውን በጥንቃቄ ማንበብና የቀረበውን መረጃ ማመዛዘን ብቻ ይሆናል። እስራኤላውያን ኢየሩሳሌምን ድል አድርገው ስለመያዛቸው የሚገልጸው ታሪክ ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ኢየሩሳሌም የቢንያም ነገድ ርስት ሆና ትመዝገብ እንጂ የቢንያም ነገድ ድል አድርጎ ሊይዛት እንዳልቻለ እናነባለን። (ኢያሱ 18:28፤ መሳፍንት 1:21) በተጨማሪም የይሁዳ ርስት የሆነች ይመስል ይሁዳ ድል አድርጎ ሊይዛት እንዳልቻለ የሚገልጽ ሐሳብ እናገኛለን። በመጨረሻ ይሁዳ ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ በመያዝ በእሳት አቃጠላት። (ኢያሱ 15:63፤ መሳፍንት 1:8) ይሁን እንጂ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ እንደያዘ ተገልጿል።—2 ሳሙኤል 5:5-9
20, 21. ከጉዳዩ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ ስንመረምር ዕብራውያን የኢየሩሳሌምን ከተማ የተቆጣጠሩበትን ሁኔታ የሚገልጸው ታሪክ ምን ይመስላል?
20 እንዲሁ ከላይ ሲታይ ግራ የሚያጋባ ይመስል ይሆናል። ነገር ግን ምንም የሚጋጭ ነገር የለም። የቢንያምና የይሁዳ ርስት መለያ የሄኖም ሸለቆ ሲሆን ይህም የጥንቷን ኢየሩሳሌምን አቋርጦ የሚያልፍ ነበር። ከጊዜ በኋላ የዳዊት ከተማ እየተባለች ትጠራ የነበረችው ከተማ የምትገኘው ኢያሱ 18:28 እንደሚለው በቢንያም ክልል ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ የኢያቡሳውያኑ የኢየሩሳሌም ከተማ የሄኖምን ሸለቆ ተሻግሮ በተወሰነ መጠን ወደ ይሁዳ ክልል ይገባ ስለነበር ይሁዳም ጭምር ከከነዓናውያን ነዋሪዎች ጋር ውጊያ መግጠም አስፈልጎታል።
21 ቢንያም ከተማዋን ድል አድርጎ መያዝ አልቻለም ነበር። በአንድ ወቅት ይሁዳ ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ በእሳት አቃጥሏት ነበር። (መሳፍንት 1:8, 9) ይሁን እንጂ ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የይሁዳ ኃይሎች አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው ከቀድሞዎቹ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ከተማዋን መልሰው ተቆጣጠሯት። ከጊዜ በኋላ ትንሽ ኃይላቸውን አሰባስበው ስለነበር የይሁዳም ሆነ የቢንያም ነገድ ድል ሊያደርጋቸው አልቻለም። በዚህ መንገድ ዳዊት ከመቶ ዓመታት በኋላ ከተማዋን ድል እስኪያደርግ ድረስ ኢያቡሳውያን በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል።
22, 23. ኢየሱስ ወደሚገደልበት ቦታ ሲሄድ የመከራውን እንጨት የተሸከመለት ማን ነበር?
22 በወንጌሎች ውስጥም ሁለተኛ ምሳሌ እናገኛለን። ኢየሱስ ለመገደል ሲወሰድ የነበረውን ሁኔታ በሚመለከት የዮሐንስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- “መስቀሉንም ተሸክሞ . . . ወጣ።” (ዮሐንስ 19:17) ይሁን እንጂ ሉቃስ እንዲህ ይላል:- “በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት።” (ሉቃስ 23:26) የሚሰቀልበትን እንጨት የተሸከመው ኢየሱስ ራሱ ነው ወይስ ስምዖን?
23 በመጀመሪያ ዮሐንስ እንደገለጸው የመከራውን እንጨት የተሸከመው ኢየሱስ ራሱ ነበር። ይሁን እንጂ በኋላ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ እንደገለጹት እስከሚሰቀልበት ቦታ ድረስ ያለውን ርቀት የቀሬናው ስምዖን እንዲሸከምለት ተደርጓል።
የየራሳቸውን አገላለጽ እንደተጠቀሙ የሚያሳይ ማስረጃ
24. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙ የሚመስሉ ሐሳቦች በማግኘታችን የማንገረመው ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ከዚህ ተነስተን ምን ብለን መደምደም አይገባም?
24 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስታረቅ አስቸጋሪ የሆኑ ልዩነት ያላቸው አንዳንድ ነገሮች መኖራቸው አይካድም። ሆኖም እነዚህ ነገሮች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ነገሮች ናቸው ብለን ልናስብ አይገባም። ብዙውን ጊዜ ዝርዝር መረጃ ባለመቅረቡ ብቻ የሚፈጠሩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት የሚያስችል በቂ እውቀት ይሰጠናል። ይሁን እንጂ ሁሉንም ታሪክ አንድ በአንድ ይዘርዝር ቢባል ኖሮ ዛሬ እንዳለው ለመያዝ አመቺ የሆነ ቅልብጭ ያለ መጽሐፍ መሆኑ ይቅርና ግዙፍና ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የማይመች የመጻሕፍት ክምችት ይሆን ነበር።
25. ኢየሱስ ያከናወነውን አገልግሎት በመዝገብ ማስፈርን አስመልክቶ ዮሐንስ ምን ብሏል? ይህስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እያንዳንዱ ታሪክ ሁሉንም ዝርዝር ጉዳይ የማያሰፍርበትን ምክንያት ለመገንዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?
25 ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ሲናገር “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ እያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ሲል ጉዳዩን ትንሽ በተጋነነ መልክ አቅርቦታል። (ዮሐንስ 21:25) ከእምነት አባቶች ዘመን አንስቶ እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ድረስ ያለውን የአምላክ ሕዝቦች ረጅም ታሪክ አንድ በአንድ ዘርዝሮ መጻፍ ደግሞ ከዚያ ይበልጥ የማይታሰብ ነገር ይሆናል!
26. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ የትኛው የግድ አስፈላጊ የሆነ እውነታ እርግጠኛ መሆን የሚያስችል በቂ መረጃ ይሰጠናል?
26 መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ሐሳቦችን በሚያስገርም መንገድ ጭምቅ አድርጎ የያዘ መጽሐፍ ነው። ተራ የሰው ሥራ አለመሆኑን እንድንገነዘብ የሚያስችሉንን በቂ መረጃዎች አካትቶ ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተንጸባረቁት ልዩነቶች ጸሐፊዎቹ የየራሳቸውን አገላለጽ እንደተጠቀሙ ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተንጸባርቆ የሚገኘው አስገራሚ የሆነ ስምምነት ያለ ምንም ጥርጥር መለኮታዊ ምንጭ ያለው መጽሐፍ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ከሚቀጥሉት ምዕራፎች በአንዱ ውስጥ በሰፊው እንወያያለን። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንጂ የሰው ቃል አይደለም።
[በገጽ 89 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚታዩት የማይጣጣሙ የሚመስሉ ሐሳቦች ጸሐፊዎቹ የየራሳቸውን አገላለጽ እንደተጠቀሙ ያሳያሉ
[በገጽ 91 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ብዙውን ጊዜ ከጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመርመር እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ ለሚባሉት ሐሳቦች መልስ ለማግኘት ይረዳል
[በገጽ 93 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ልዩነቶች” አሉ ማለት የግድ እርስ በርስ ይቃረናሉ ማለት አይደለም
የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ኬኔዝ ኤስ ካንዘር በአንድ ወቅት ስለ አንድ ዓይነት ክንውን የሚገልጹ ሁለት ሪፖርቶች እውነት ሆነው ሳለ እንዴት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሊመስሉ እንደሚችሉ በምሳሌ አስረድተዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር:- “ከጥቂት ጊዜ በፊት የአንድ የቅርብ ወዳጃችን እናት ይሞታሉ። መጀመሪያ መሞታቸውን የሰማነው የጋራ ወዳጃችን ከሆነ ከምናምነው ሰው ሲሆን የወዳጃችን እናት በአንድ የመንገድ ማዕዘን ላይ ቆመው አውቶብስ ሲጠብቁ ሌላ የሚያልፍ አውቶብስ እንደገጫቸውና ለሞት የሚያበቃ ጉዳት ደርሶባቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንዳረፉ ነገረን።”
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፍጹም የተለየ ታሪክ ሰሙ። ይህንን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “ከሟቿ የልጅ ልጅ ደግሞ የነበሩበት መኪና ተጋጭቶ ተወርውረው እንደወደቁና ወዲያው እንደሞቱ ሰማን። ልጁ ትክክለኛው ነገር ይህ ስለመሆኑ ፍጹም እርግጠኛ ነበር።
“ከጊዜ በኋላ . . . ትክክለኛውን ታሪክ ለማወቅ ማጠያየቅ ጀመርን። አያትየው አውቶብስ ሲጠብቁ ሌላ የሚያልፍ አውቶብስ ይገጫቸውና ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። አንድ የሚያልፍ መኪና አንስቷቸው ወደ ሆስፒታል እየበረረ ሲሄድ ከሌላ መኪና ጋር ይላተማል። ይኼን ጊዜ ከመኪናው ተወርውረው ይወድቁና ወዲያው ሕይወታቸው ያልፋል።”
አዎን ስለ ተመሳሳይ ታሪክ የተሰጡ ሁለት ዘገባዎች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ይምሰሉ እንጂ ሁለቱም እውነት ሊሆኑ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም አንዳንድ ጊዜ የሚታየው ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። የየራሳቸውን አገላለጽ የተጠቀሙ ምሥክሮች ስለ አንድ ዓይነት ሁኔታ የተለያዩ ዝርዝሮችን ያስቀምጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚጠቅሷቸው ነገሮች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሳይሆኑ አንዱ ሌላውን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ናቸው። ሁሉንም ዘገባዎች ግምት ውስጥ አስገብተን ከተመለከትናቸው ደግሞ ስለተፈጸመው ነገር የተሻለ ግንዛቤ እናገኛለን።