የአምላክ ድርጅት ክፍል በመሆን ጥበቃ ማግኘት
“የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል [“ጥበቃ ያገኛል፣” NW]።”—ምሳሌ 18:10
1. በኢየሱስ ጸሎት መሠረት ክርስቲያኖች በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?
ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተከታዮቹን አስመልክቶ ወደ ሰማያዊ አባቱ ጸልዮ ነበር። ከፍቅር በመነጨ የአሳቢነት ስሜት እንዲህ አለ:- “እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም።” (ዮሐንስ 17:14, 15) ዓለም ለክርስቲያኖች አደገኛ ቦታ እንደሚሆን ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ስለ እነርሱ ውሸት በመናገርና እነርሱን በማሳደድ ለእነርሱ ያለውን ጥላቻ ያሳያል። (ማቴዎስ 5:11, 12፤ 10:16, 17) በተጨማሪም የምግባረ ብልሹነት መፍለቂያ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 4:10፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16
2. ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ጥበቃ ሊያገኙ የሚችሉት የት ነው?
2 ክርስቲያኖችን የሚጠላው ዓለም ከአምላክ የራቁትንና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉትን ሰዎች ያቀፈ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ዓለም ከክርስቲያን ጉባኤ ይበልጥ እጅግ ስፋት ያለው ሲሆን ሰይጣን ደግሞ ከማንኛውም ሰው የሚበልጥ ኃይል አለው። ስለዚህ ከዓለም የሚሰነዘረው ጥላቻ በእርግጥም አደገኛ ነው። የኢየሱስ ተከታዮች መንፈሳዊ ጥበቃ ሊያገኙ የሚችሉት የት ነው? በታኅሣሥ 1, 1922 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣ አንድ ሐሳብ መልሱን ይሰጣል:- “የምንኖረው በክፉው ዘመን ውስጥ ነው። በሰይጣን ድርጅትና በአምላክ ድርጅት መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው። ይህ ውጊያ የሞት ሽረት ውጊያ ነው።” በዚህ ግጭት ውስጥ የአምላክ ድርጅት መንፈሳዊ ጥበቃ የሚገኝበት ቦታ ነው። “ድርጅት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፤ እንዲሁም “የአምላክ ድርጅት” የሚለው ሐረግ በ1920ዎቹ አዲስ መግለጫ ነበር። ታዲያ ይህ ድርጅት ምንድን ነው? ከእሱስ ጥበቃ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
የይሖዋ ድርጅት
3, 4. (ሀ) አንድ መዝገበ ቃላትና አንድ የመጠበቂያ ግንብ እትም በሰጡት ማብራሪያ መሠረት ድርጅት ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት ድርጅት ተብሎ ሊጠራ የሚችለው በምን መልኩ ነው?
3 ከንሳይስ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ በሚሰጠው ፍቺ መሠረት አንድ ድርጅት “አንድ የተደራጀ አካል” ነው። ይህን በአእምሯችን ይዘን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ የአስተዳደር አካል የበላይ ተቆጣጣሪነት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን በየአካባቢያቸው በሚገኙ ጉባኤዎች አደራጅተዋቸው ስለነበር ይህን ‘የወንድማማች ማኅበር’ ድርጅት ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:17) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ የሆነ ድርጅታዊ መዋቅር አላቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አካል አንድነት እንደ “እረኞችና አስተማሪዎች” በመሳሰሉ ‘የሰዎች ስጦታዎች’ ተጠናክሮ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከጉባኤ ወደ ጉባኤ ይጓዙ የነበረ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ነበሩ። (ኤፌሶን 4:8, 11, 12፤ ሥራ 20:28) በዛሬውም ጊዜ እንደነዚህ ያሉ ተመሳሳይ ‘ስጦታዎች’ የይሖዋ ምሥክሮችን አንድነት ያጠነክራሉ።
4 የኅዳር 1, 1922 የመጠበቂያ ግንብ እትም “ድርጅት” ስለሚለው ቃል እንዲህ ብሎ ነበር:- “አንድ ድርጅት አንድን ውጥን ከግብ የማድረስ ዓላማ ይዞ የሚነሳ የሰዎች ማኅበር ነው።” ይህ መጠበቂያ ግንብ በመቀጠል የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ተብለው መጠራታቸው “ቃሉ ከሚያስተላልፈው ሐሳብ አንፃር ኑፋቄ አያሰኛቸውም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች [የይሖዋ ምሥክሮች] የአምላክን ዓላማዎች ለመፈጸምና ጌታ እንደሚያደርገው ሁሉንም ነገር በሥርዓት ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 14:33) ሐዋርያው ጳውሎስ በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሥርዓት ባለው መንገድ መመላለሳቸውን ገልጿል። የተቀቡ ክርስቲያኖች ያላቸውን ኅብረት ብዙ ክፍሎች ካሉት ሰብዓዊ ሰውነት ጋር አነጻጽሮታል፤ ሰውነት በደንብ መሥራት እንዲችል እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል የተመደበለትን የሥራ ድርሻ ያሟላል። (1 ቆሮንቶስ 12:12–26) ይህ አንድን ድርጅት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌ ነው! ክርስቲያኖች የተደራጁት ለምንድን ነው? “የአምላክን ዓላማዎች” ለማስፈጸምና የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ነው።
5. የሚታየው የአምላክ ድርጅት ምንድን ነው?
5 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች አንድነት እንደሚኖራቸው፣ እንደ አንድ “ብሔር” ሆነው ወደ አንድ “ምድር” እንዲሰበሰቡ እንደሚደረግና “በዓለም እንደ ብርሃን” እንደሚያበሩ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 66:8 NW፤ ፊልጵስዩስ 2:15) በአሁኑ ጊዜ ይህ የተደራጀ “ብሔር” ከአምስት ሚልዮን ተኩል በላይ ሆኗል። (ኢሳይያስ 60:8–10, 22) ይሁን እንጂ የአምላክ ድርጅት የሚያጠቃልለው እነዚህን ብቻ አይደለም። መላእክትም ይገኙበታል።
6. ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የአምላክ ድርጅት የእነማን ስብስብ ነው?
6 መላእክት ከአምላክ ሰብዓዊ አገልጋዮች ጋር አንድ ላይ የሠሩባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። (ዘፍጥረት 28:12፤ ዳንኤል 10:12–14፤ 12:1፤ ዕብራውያን 1:13, 14፤ ራእይ 14:14–16) በመሆኑም ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ የግንቦት 15, 1925 መጠበቂያ ግንብ እትም “ሁሉም ቅዱሳን መላእክት የአምላክ ድርጅት ክፍል ናቸው” ብሎ ነበር። አክሎም “ሁሉንም ኃይልና ሥልጣን በመጨበጥ በአምላክ ድርጅት የበላይነቱን ቦታ የያዘው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ [ነው]” ብሏል። (ማቴዎስ 28:18) ስለዚህ ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የአምላክ ድርጅት የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በአንድነት የሚሠሩትን በሰማይና በምድር ያሉትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። (ሣጥኑን ተመልከት።) የዚህ ድርጅት ክፍል መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በሰማይና በምድር የሚገኙ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ይሖዋ አምላክን በአንድነት ለማወደስ የሚደራጁበትን ጊዜ በተስፋ መጠባበቁ ምንኛ ያስደስታል! (ራእይ 5:13, 14) ሆኖም የአምላክ ድርጅት በዛሬው ጊዜ የሚያስገኘው ጥበቃ ምንድን ነው?
በአምላክ ድርጅት ውስጥ ተጠብቆ መኖር—እንዴት?
7. የአምላክ ድርጅት የሚጠብቀን በምን መንገድ ነው?
7 የአምላክ ድርጅት ከሰይጣንና ከማታለያዎቹ እንድንጠበቅ ሊረዳን ይችላል። (ኤፌሶን 6:11) ሰይጣን የይሖዋን አምላኪዎች የሚያሳድደው፣ የሚፈትነውና ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው በአእምሮው አንድ ግብ ይዞ ነው፤ ይኸውም ‘ሊሄዱበት ከሚገባቸው መንገድ’ እንዲወጡ ማድረግ ነው። (ኢሳይያስ 48:17፤ ከማቴዎስ 4:1–11 ጋር አወዳድር።) በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ እነዚህን ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ ልናስቀራቸው አንችልም። ይሁን እንጂ ከአምላክና ከድርጅቱ ጋር ያለን ቅርብ ዝምድና ሊያጠነክረንና ሊጠብቀን እንዲሁም በዚህ “መንገድ” ላይ እንድንቆይ ሊረዳን ይችላል። በውጤቱም የተሰጠንን ተስፋ እናገኛለን።
8. የማይታየው የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ አገልጋዮቹን የሚደግፈው እንዴት ነው?
8 የአምላክ ድርጅት ይህን ጥበቃ የሚሰጠው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የይሖዋ መንፈሳዊ አገልጋዮች የማይነጥፍ ድጋፍ አለን። ኢየሱስ በከፍተኛ ጫና ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድ መልአክ አገልግሎታል። (ሉቃስ 22:43) ጴጥሮስ በሞት አደጋ ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድ መልአክ በተአምራዊ ሁኔታ አድኖታል። (ሥራ 12:6–11) በዛሬው ጊዜ እነዚህን የመሳሰሉ ተአምራት ባይኖሩም የይሖዋ ሕዝቦች በስብከት እንቅስቃሴያቸው የመላእክት ድጋፍ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል። (ራእይ 14:6, 7) አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሲጋፈጡ አብዛኛውን ጊዜ ከወትሮው የበለጠ ኃይል ያገኛሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:7 NW) ከዚህም በላይ ‘የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ እንደሚሰፍርና እንደሚያድናቸውም’ ያውቃሉ።—መዝሙር 34:7
9, 10. “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለጠቅላላው የአምላክ ድርጅት የሚሠራውስ እንዴት ነው?
9 የሚታየው የይሖዋ ድርጅትም ጥበቃ ያስገኛል። እንዴት? በምሳሌ 18:10 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል [“ጥበቃ ያገኛል፣” NW]።” ይህ ማለት ግን እንዲያው የአምላክን ስም ደጋግሞ መጥራቱ ብቻ ጥበቃ ያስገኛል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ስም መሸሸጊያ ማድረጋችን በራሱ በይሖዋ መታመን እንዳለብን ያመለክታል። (መዝሙር 20:1፤ 122:4) ሉዓላዊነቱን መደገፍ፣ ሕጎቹንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ማክበርና በተስፋዎቹ ላይ እምነት ማሳደር ማለት ነው። (መዝሙር 8:1–9፤ ኢሳይያስ 50:10፤ ዕብራውያን 11:6) ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ መስጠትን ያካትታል። ይሖዋን በዚህ መንገድ የሚያመልኩት ብቻ ናቸው ከመዝሙራዊው ጋር እንደሚከተለው ለማለት የሚችሉት:- “ልባችን በእርሱ [በይሖዋ] ደስ ይለዋልና፣ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና።”—መዝሙር 33:21፤ 124:8
10 በአሁኑ ጊዜ በሚታየው የአምላክ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ልክ እንደ ሚክያስ “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፣ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን” ይላሉ። (ሚክያስ 4:5) ዘመናዊው ድርጅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ለስሙ የሚሆን ሕዝብ’ ተብሎ በተጠራው ‘በአምላክ እስራኤል’ ዙሪያ የተሰባሰበ ነው። (ገላትያ 6:16፤ ሥራ 15:14፤ ኢሳይያስ 43:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 2:17) ስለዚህ የአምላክ ድርጅት ክፍል መሆን ማለት በአምላክ ስም ጥበቃ ለማግኘት ከሚፈልጉና ጥበቃም ከሚያገኙ ሰዎች መካከል መሆን ማለት ነው።
11. የይሖዋ ድርጅት የእሱ ክፍል ለሆኑት ጥበቃ የሚሰጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
11 ከዚህም በተጨማሪ የሚታየው የአምላክ ድርጅት አንዱ ሌላውን የሚገነባበትና የሚያበረታታበት የመሰል አማኞች ኅብረት ማለትም አንድ የእምነት ማኅበረሰብ ነው። (ምሳሌ 13:20፤ ሮሜ 1:12) ክርስቲያን እረኞች ለበጎች እንክብካቤ የሚያደርጉበት፣ የታመሙትንና የተጨነቁትን የሚያበረታቱበት እንዲሁም የተሰናከሉትን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉበት ቦታ ነው። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 5:2–4) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ‘ምግብ በጊዜው’ የሚያቀርበው በዚህ ድርጅት አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 24:45) ይህ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች የተውጣጣ “ባሪያ” ምርጥ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ትክክለኛና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እውቀት ያቀርባል። (ዮሐንስ 17:3) ይህ “ባሪያ” ለሚሰጠው መመሪያ ምስጋና ይግባውና ክርስቲያኖች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን እንዲጠብቁና በዙሪያቸው በሚገኘው አደገኛ አካባቢ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” እንዲሆኑ እርዳታ በማግኘት ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 10:16) እንዲሁም ሁልጊዜ ‘የጌታ ሥራ የበዛላቸው’ እንዲሆኑ እገዛ እየተደረገላቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ራሱን የቻለ ጥሩ ጥበቃ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:58
የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆኑት እነማን ናቸው?
12. የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ክፍል የሆኑት እነማን ናቸው?
12 ይህን ጥበቃ የሚያገኙት የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆኑት ብቻ ስለሆኑ እነዚህ እነማንን ይጨምራሉ? ሰማያዊውን ድርጅት በተመለከተ የዚህ ጥያቄ መልስ ምንም አያጠራጥርም። ሰይጣንና መላእክቱ በሰማይ መኖራቸው አብቅቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ታማኞቹ መላእክት አሁንም በሰማይ ‘ተሰብስበው’ ይገኛሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ‘በጉ፣’ ኪሩቤሎቹ (‘አራቱ እንስሶች’) እና ‘ብዙ መላእክት’ በአምላክ ዙፋን አቅራቢያ ሆነው ተመልክቷል። ከእነሱ ጋር አብረው በክብራማ ሰማያዊ ውርሻቸው ላይ የሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የሚያመለክቱ 24 ሽማግሌዎች ነበሩ። (ዕብራውያን 12:22, 23፤ ራእይ 5:6, 11፤ 12:7-12) ሁሉም የአምላክ ድርጅት ክፍል መሆናቸውን በግልጽ ለማየት ይቻላል። ይሁንና ሰዎችን በተመለከተ ሁኔታው እንደዚህ ቁልጭ ብሎ የሚታይ አይደለም።
13. ኢየሱስ የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆኑትንና ያልሆኑትን ለይቶ የገለጸው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ተከታዮቹ ነን ስለሚሉ አንዳንድ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በዚያ ቀን ብዙዎች:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” (ማቴዎስ 7:22, 23) አንድ ሰው ዓመፅ የሚሠራ ከሆነ የፈለገውን ይበል እንዲሁም የትም ሄዶ ያምልክ የአምላክ ድርጅት ክፍል እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆነን ሰው እንዴት መለየት እንደሚቻል ገልጿል። “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ብሏል።—ማቴዎስ 7:21
14. የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆኑት ሊፈጽሟቸው የሚገቡ የአምላክ ፈቃድ ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?
14 ስለዚህ አንድ ሰው “መንግሥተ ሰማያት” ማዕከል የሆነለት የአምላክ ድርጅት ክፍል ለመሆን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አለበት። ፈቃዱ ምንድን ነው? ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ አንደኛውን አስፈላጊ ገጽታ ገልጿል:- “[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና ትክክለኛውን የእውነት እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 2:4 NW) አንድ ሰው ትክክለኛውን እውቀት ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመቅሰም፣ በሕይወቱ ተግባራዊ ለማድረግና ‘ለሁሉም ዓይነት ሰዎች’ ለማዳረስ የሚጥር ከሆነ የአምላክን ፈቃድ እያደረገ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሮሜ 10:13–15) የይሖዋ በጎች እንዲመገቡና እንክብካቤ እንዲያገኙ የአምላክ ፈቃድ ነው። (ዮሐንስ 21:15–17) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። አንድ ሰው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ላለመገኘት ምንም የሚያግደው ነገር ሳይኖር እነዚህን ስብሰባዎች ሆነ ብሎ ችላ የሚል ከሆነ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ላለው ቦታ አድናቆት የለውም።—ዕብራውያን 10:23–25
የዓለም ወዳጅ መሆን
15. ያዕቆብ በጊዜው ለነበሩ ጉባኤዎች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
15 ኢየሱስ ከሞተ ወደ 30 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ግማሽ ወንድሙ ያዕቆብ አንድ ሰው በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያለውን ቦታ አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ጠቁሟል። “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 4:4) የአምላክ ጠላት የሆነ ሰው የድርጅቱ ክፍል እንደማይሆን የተረጋገጠ ነው። ታዲያ የዓለም ወዳጅ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? የተለያየ መልክ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን መጥፎ ጓደኞች ማበጀትን የመሳሰሉ ነገሮች እንደሚጨምር ተብራርቷል። ከዚህም በተጨማሪ ያዕቆብ በአንድ ልዩ ጉዳይ ይኸውም ተገቢ ወዳልሆነ ድርጊት በሚመራ የተሳሳተ አመለካከት ላይ ትኩረት አድርጓል።
16. ያዕቆብ የዓለም ወዳጅ መሆን የአምላክ ጠላት መሆን ነው ሲል በሰጠው ማስጠንቀቂያ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምንድን ነው?
16 በያዕቆብ 4:1–3 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፣ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፣ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።” ያዕቆብ የዓለም ወዳጅ ከመሆን ስለ መራቅ ያስጠነቀቀው እነዚህን ቃላት ከጻፈ በኋላ ነበር።
17. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ “ጦርነቶችና” “ውጊያዎች” የነበሩት በምን መንገድ ነበር?
17 ያዕቆብ ከሞተ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ጦር ተማዝዘው ቃል በቃል እርስ በርስ ተገዳድለዋል። ይሁን እንጂ ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው በሰማይ ‘ካህናትና ነገሥታት’ የመሆን ተስፋ ለነበራቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ነበር። (ራእይ 20:6) ቃል በቃል ጦርነት በማካሄድ አንዳቸው ሌላውን አልገደሉም። ታዲያ ያዕቆብ በክርስቲያኖች መካከል እንዲህ ያሉ ነገሮች መኖራቸውን የተናገረው ለምን ነበር? ሐዋርያው ዮሐንስ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው ብሏል። እንዲሁም ጳውሎስ በጉባኤዎች ውስጥ የሚነሡ የባሕርይ ግጭቶችንና ንትርኮችን ‘ውጊያዎችና’ ‘ጠቦች’ ብሏቸዋል። (ቲቶ 3:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:14፤ 1 ዮሐንስ 3:15–17) ከዚህ ጋር በተያያዘ መንገድ ያዕቆብ ለመሰል ክርስቲያኖች ፍቅር ጎድሏቸው እንደነበረ ለመናገር የፈለገ ይመስላል። ክርስቲያኖች በመካከላቸው የነበረው ሁኔታ የዓለም ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ከሚያሳዩት ባሕርይ የተለየ አልነበረም።
18. በክርስቲያኖች መካከል ፍቅር የጎደለው ድርጊትና ስሜት እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
18 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንዲህ የመሳሰሉ ነገሮች የተከሰቱት ለምን ነበር? ለምኞትና ‘ለሥጋዊ ምቾት መሯሯጥን’ የመሳሰሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ነበሯቸው። በተጨማሪም ኩራት፣ ቅንዓትና ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት በጉባኤ ውስጥ ያለውን ክርስቲያናዊ የወንድማማችነት ፍቅር ሊጎዳ ይችላል። (ያዕቆብ 3:6, 14) እንዲህ ያሉ አመለካከቶች አንድን ሰው የዓለም ወዳጅ ስለሚያደርጉት የአምላክ ጠላት ይሆናል። እነዚህን የመሳሰሉ አመለካከቶች ያሉት ማንኛውም ሰው የአምላክ ድርጅት ክፍል ሆኖ ሊቀጥል አይችልም።
19. (ሀ) አንድ ክርስቲያን በልቡ ውስጥ የተሳሳተ አስተሳሰብ ሥር እየሰደደ መሆኑን ከተገነዘበ በዋነኛነት ተወቃሽ የሚሆነው ማን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን የተሳሳተ አስተሳሰብን እንዴት ሊያሸንፍ ይችላል?
19 የተሳሳተ አስተሳሰብ በልባችን ውስጥ ሥር እየሰደደ ከሆነ ተወቃሽ የምናደርገው ማንን ነው? ሰይጣንን? እስከ ተወሰነ ደረጃ፣ አዎን። ሰይጣን እነዚህን የመሳሰሉ አመለካከቶች ተስፋፍተው በሚገኙበት በዚህ ዓለም ‘አየር ላይ ሥልጣን ያለው አለቃ’ ነው። (ኤፌሶን 2:1, 2፤ ቲቶ 2:12) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ አስተሳሰብ ሥሮች የሚያቆጠቁጡት ፍጽምና ከጎደለው ከራሳችን ሥጋ ነው። ያዕቆብ የዓለም ወዳጅ መሆንን በመቃወም ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ “መጽሐፍ:- በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን?” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 4:5) ሁላችንም አብሮን የሚወለድ መጥፎ ነገር የማድረግ ዝንባሌ አለን። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 7:18–20) ሆኖም ድክመታችንን አምነን ከተቀበልን በይሖዋ እርዳታ ልንወጣው እንደምንችል ከታመንን ይህን ዝንባሌ ልንዋጋው እንችላለን። “[አምላክ] ጸጋን [“ይገባናል የማንለውን ደግነት፣” NW] [አብሮን ከሚወለደው የቅናት ዝንባሌ] አብልጦ ይሰጣል” በማለት ያዕቆብ ተናግሯል። (ያዕቆብ 4:6) በአምላክ ቅዱስ መንፈስና በታማኝ ክርስቲያን ወንድሞች እርዳታ እንዲሁም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ አማካኝነት ታማኝ ክርስቲያኖች የሥጋቸውን ድክመቶች ይቋቋማሉ። (ሮሜ 7:24, 25) የዓለም ሳይሆን የአምላክ ወዳጆች በመሆን በአምላክ ድርጅት ውስጥ ተጠብቀው ይኖራሉ።
20. የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆኑት የሚያገኟቸው የተትረፈረፉ በረከቶች ምንድን ናቸው?
20 መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (መዝሙር 29:11) የይሖዋ ዘመናዊ “ብሔር” ማለትም የሚታየው ድርጅቱ ክፍል ከሆንን እኛም እሱ የሚሰጠውን ጥንካሬና ሕዝቡን የሚባርክበትን ሰላም ልናገኝ እንችላለን። እርግጥ ነው የሰይጣን ዓለም ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ይበልጥ ትልቅ ነው፤ እንዲሁም ሰይጣን ከእኛ ይበልጥ ኃይለኛ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁሉን ቻይ ነው። አንቀሳቃሽ ኃይሉ የማይበገር ነው። ኃያል መላእክቱም ከእኛ ጋር አንድ ላይ በመሆን አምላክን ያገለግላሉ። ስለዚህ ጥላቻ ቢገጥመንም እንኳ ጸንተን ልንቆም እንችላለን። ልክ እንደ ኢየሱስ ዓለምን ልናሸንፍ እንችላለን።—ዮሐንስ 16:33፤ 1 ዮሐንስ 4:4
[ልታብራራ ትችላለህ?]
◻ የሚታየው የአምላክ ድርጅት ምንድን ነው?
◻ የአምላክ ድርጅት ጥበቃ የሚሰጠው በምን መንገዶች ነው?
◻ የአምላክ ድርጅት ክፍል የሆኑት እነማን ናቸው?
◻ የዓለም ወዳጅ ከመሆን መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክ ድርጅት ምንድን ነው?
በይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ውስጥ “የአምላክ ድርጅት” የሚለው ሐረግ በሦስት መንገዶች ይሠራበታል።
1 በታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት የተዋቀረው የማይታየው የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ተብሎ ተጠርቷል።—ገላትያ 4:26
2 የሚታየው የይሖዋ ሰብዓዊ ድርጅት። ዛሬ ይህ ድርጅት ቅቡዓን ቀሪዎችንና ተባባሪዎቻቸው የሆኑትን እጅግ ብዙ ሰዎች ያቀፈ ነው።
3 የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት። ዛሬ ይህ ድርጅት የይሖዋን ሰማያዊ ድርጅት እንዲሁም መንፈሳዊ ተስፋ ያላቸውን ማለትም በምድር ላይ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸውን ቅቡዓን ያቀፈ ነው። ወደፊት በምድር ላይ የሚኖሩትን ፍጹም ሰዎችንም ይጨምራል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ድርጅት ከሁሉ የተሻለውን መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ላይ ነው