ምዕራፍ 31
“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል”
1-3. (ሀ) አንድ ሕፃን ወላጆቹ ለሚያሳዩት ፍቅር የሚሰጠው ምላሽ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ምን ያስተምረናል? (ለ) በተፈጥሯችን ሰዎች ፍቅር ሲያሳዩን ምን እናደርጋለን? ራሳችንን ልንጠይቀው የሚገባው በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄስ ምንድን ነው?
ወላጆች ሕፃን ልጃቸው ፈገግ ሲል ሲያዩ ደስ ይላቸዋል። ብዙውን ጊዜ ፊታቸውን ወደ ሕፃኑ አስጠግተው ፈገግ በማለትና የተለያዩ ድምፆች በማሰማት ያጫውቱታል። ከዚያም የሕፃኑን ምላሽ ለማየት ይጓጓሉ። ትንሽ ቆይቶ ሕፃኑም ፈገግ ማለት ይጀምራል፤ ፊቱ ይፈካል፣ ጉንጮቹም ስርጉድ ይላሉ። ሕፃኑ የሚያሳየው ደስ የሚል ፈገግታ ወላጆቹ ላሳዩት ፍቅር ምላሽ መሆኑ ነው።
2 የሕፃኑ ፈገግታ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ያስተምረናል። ፍቅር ሲያሳዩን መልሰን ፍቅር እናሳያለን። ይህ ተፈጥሯችን ነው። (መዝሙር 22:9) እያደግን ስንሄድ ሌሎች ለሚያሳዩን ፍቅር ምላሽ የምንሰጥበት መንገድም የዚያኑ ያህል እየጨመረና እየተሻሻለ ይሄዳል። በልጅነትህ ወላጆችህ፣ ዘመዶችህ ወይም ጓደኞችህ ፍቅራቸውን እንዴት ያሳዩህ እንደነበር አሁንም ድረስ ትዝ ይልህ ይሆናል። በልብህ ውስጥ የተተከለው ይህ ፍቅር እያደገና እያበበ ሄዶ ከጊዜ በኋላ በተግባር መገለጽ ይጀምራል። ላሳዩህ ፍቅር አንተም አጸፋውን ትመልሳለህ። ከይሖዋ አምላክ ጋር ባለህ ዝምድናስ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:19) በዚህ መጽሐፍ ሦስት ክፍሎች ላይ የተሰጠው ማብራሪያ ይሖዋ አምላክ ኃይሉን፣ ፍትሑንና ጥበቡን ለአንተ በሚበጅ ሁኔታ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደተጠቀመበት መለስ ብለህ እንድታስብ አድርጎሃል። በአራተኛው ክፍል ላይ ደግሞ ይሖዋ ለሰው ልጆች በጠቅላላም ሆነ ለአንተ በግልህ ፍቅሩን እንዴት በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደገለጸ ተመልክተሃል። አሁን አንድ ጥያቄ ይነሳል። ጥያቄው ‘ይሖዋ ላሳየኝ ፍቅር ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብኛል?’ የሚል ነው፤ ይህ ራስህን ልትጠይቀው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ጥያቄ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
4. ሰዎች ‘አምላክን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው?’ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ግራ የተጋቡት እንዴት ነው?
4 ይሖዋ የፍቅር ምንጭ ነው፤ ፍቅር፣ የሰዎችን መልካም ባሕርያት በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው አሳምሮ ያውቃል። በመሆኑም ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች በዓመፅ ድርጊታቸው ቢገፉበትም እሱ ላሳያቸው ፍቅር ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች እንደማይጠፉ ሙሉ እምነት ነበረው። ደግሞም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ምላሽ ሰጥተዋል። የሚያሳዝነው ግን በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ ያሉት ሃይማኖቶች ‘አምላክን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው?’ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ሰዎች ግራ እንዲጋቡ አድርገዋል። ብዙ ሰዎች አምላክን እንደሚወዱ ቢናገሩም ፍቅራቸውን በቃል ከመግለጽ ያለፈ ነገር እንደሚጠበቅባቸው የሚያስቡ አይመስልም። አንድ ሕፃን ወላጆቹ ላሳዩት ፍቅር የሚሰጠው የመጀመሪያ ምላሽ ፈገግታ እንደሆነ ሁሉ ለአምላክ ያለን ፍቅርም መጀመሪያ ላይ በቃል ሊገለጽ ይችላል። ፍቅራችን እያደገ ሲሄድ ግን ከቃል ባለፈም መገለጽ ይኖርበታል።
5. መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ሊያስደስተን የሚገባው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ እሱን መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገልጾልናል። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው” ይላል። ስለዚህ ለአምላክ ያለን ፍቅር በተግባር የሚገለጽ መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች መታዘዝ የሚለው ነገር አያስደስታቸውም። ይሁን እንጂ ይኸው ጥቅስ “ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም” ሲል አክሎ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:3) የይሖዋ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች እኛን የሚጠቅሙ እንጂ የሚጨቁኑ አይደሉም። (ኢሳይያስ 48:17, 18) የአምላክ ቃል ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚረዱ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚረዱን እንዴት ነው? ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር የሚረዱ ሦስት መንገዶችን እንመርምር። እነዚህ ሦስት መንገዶች ከይሖዋ ጋር መነጋገር፣ እሱን ማምለክ እና እሱን መምሰል ናቸው።
ከይሖዋ ጋር መነጋገር
6-8. (ሀ) ይሖዋን ልንሰማ የምንችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) ቅዱሳን መጻሕፍትን በምናነብበት ጊዜ ሕያው እንዲሆኑልን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
6 የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ገና ሲጀምር “ከአምላክ ጋር ስለ መነጋገር አስበህ ታውቃለህ?” የሚል ጥያቄ ያነሳል። ይህ ሊሆን የማይችል ነገር እንዳልሆነ ተመልክተናል። ሙሴ ከአምላክ ጋር እንደተነጋገረ እናስታውሳለን። እኛስ ይህን ማድረግ እንችላለን? ዛሬ ይሖዋ መላእክቱን ልኮ ከሰዎች ጋር አይነጋገርም። ከዚህ ይልቅ የሰው ልጆች ከእሱ ጋር መነጋገር የሚችሉበት ሌላ ግሩም መንገድ አለ። ታዲያ ይሖዋ ሲናገር መስማት የምንችለው እንዴት ነው?
7 “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” ስለሆኑ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ይሖዋን ማዳመጥ እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መዝሙራዊው የይሖዋ አገልጋዮች ቃሉን “በቀንና በሌሊት” እንዲያነቡ አጥብቆ የመከረው ለዚህ ነው። (መዝሙር 1:1, 2) ይህ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችን መልሶ ይክሰናል። ምዕራፍ 18 ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ከሚገኘው ውድ አባታችን እንደተላከ ደብዳቤ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አሰልቺ ሥራ ሊሆንብን አይገባም። ቅዱሳን መጻሕፍትን በምናነብበት ጊዜ ሕያው ሊሆኑልን ይገባል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
8 የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በምታነብበት ጊዜ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት በእውን እንዳሉ ሆነው ሊታዩህ ይገባል። አስተዳደጋቸውን፣ ያሳለፉትን ሕይወት፣ የነበሩበትን ሁኔታ እንዲሁም ከድርጊታቸው በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት ለመረዳት ጥረት አድርግ። ከዚያም እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ስለምታነበው ነገር በጥሞና አስብ፦ ‘ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? እዚህ ላይ ጎልቶ የተንጸባረቀው የትኛው የይሖዋ ባሕርይ ነው? ይሖዋ ከዚህ ታሪክ እንድማር የፈለገው መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ላደርገው የምችለውስ እንዴት ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብክ፣ ካሰላሰልክበትና በሥራ ላይ ለማዋል ከጣርክ ቃሉ ሕያው ይሆንልሃል።—መዝሙር 77:12፤ ያዕቆብ 1:23-25
9. “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? ይህን “ባሪያ” በጥሞና ማዳመጣችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
9 በተጨማሪም ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ያነጋግረናል። ኢየሱስ በተነበየው መሠረት በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀኖች፣ የተቀቡ ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ትንሽ ቡድን መንፈሳዊ ‘ምግብ በተገቢው ጊዜ’ እንዲያቀርብ ተሹሟል። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህ ባሪያ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እንድናገኝ በሚረዱ ጽሑፎች እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት በመንፈሳዊ ይመግበናል። ይህ ቡድን የክርስቶስ ባሪያ እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስ “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ” ሲል የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን። (ሉቃስ 8:18) ይህ ታማኝ ባሪያ ይሖዋ እኛን ለማነጋገር የሚጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነ ስለምናውቅ ባሪያው የሚሰጠንን ምክር በጥሞና እናዳምጣለን።
10-12. (ሀ) ጸሎት ከይሖዋ ያገኘነው ድንቅ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ ጸሎት ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? ጸሎታችንን ደስ እያለው እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን የምንችለውስ ለምንድን ነው?
10 እኛስ ይሖዋን ማነጋገር እንችላለን? ይህን ማሰቡ በራሱ ሊያስፈራ ይችላል። የአገርህን መሪ ስለ ግል ጉዳይህ ለማነጋገር ብትፈልግ ከዚህ ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተህ ለመነጋገር የሚፈቀድልህ ይመስልሃል? እንዲያውም መሪውን አግኝተህ ለማነጋገር መሞከርህ በራሱ ሕይወትህን ለአደጋ ሊያጋልጠው ይችላል! አስቴርና መርዶክዮስ ይኖሩ በነበረበት ዘመን አንድ ሰው ሳይጠራ የፋርስን ንጉሠ ነገሥት ለማነጋገር ቢሞክር ሕይወቱን ሊያጣ ይችል ነበር። (አስቴር 4:10, 11) የጽንፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ ለማነጋገር መሞከር ደግሞ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል አስበው! በጣም ኃያላን የሚባሉት መሪዎችም እንኳ በእሱ ፊት “እንደ ፌንጣ ናቸው።” (ኢሳይያስ 40:22) ታዲያ ይህ እንድንሸማቀቅና ወደ እሱ ከመቅረብ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ይገባል? በፍጹም!
11 ይሖዋ ከእሱ ጋር በቀላሉ መገናኘት የምንችልበት አንድ መንገድ አዘጋጅቷል፤ ይህም ጸሎት ነው። አንድ ትንሽ ልጅ እንኳ በኢየሱስ ስም በእምነት ወደ ይሖዋ መጸለይ ይችላል። (ዮሐንስ 14:6፤ ዕብራውያን 11:6) ጸሎት ሚስጥር አድርገን በውስጣችን የያዝነውን ብሎም በቃላት ለማስረዳት የሚቸግረንን ሐሳብና ስሜት ሳይቀር ለመግለጽ ያስችለናል። (ሮም 8:26) በምንጸልይበት ጊዜ ይሖዋን ለማስደመም የተራቀቁና የተዋቡ ቃላት መጠቀም ወይም ረጅምና የተንዛዛ ጸሎት ማቅረብ አያስፈልገንም። (ማቴዎስ 6:7, 8) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ የጸሎታችን ርዝማኔ ምን ያህል መሆን እንዳለበትም ይሁን ምን ያህል ጊዜ ወደ እሱ መጸለይ እንደምንችል የሚገልጽ ገደብ አላስቀመጠም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ዘወትር ጸልዩ” በማለት ያበረታታናል።—1 ተሰሎንቄ 5:17
12 “ጸሎት ሰሚ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ ብቻ መሆኑን አስታውስ፤ ጸሎታችንን የሚሰማው ደግሞ ከልብ በመነጨ ርኅራኄ ነው። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በሚያቀርቡት ጸሎት ይሰላች ይሆን? በፍጹም፤ እንዲያውም አገልጋዮቹ የሚያቀርቡት ጸሎት በጣም ያስደስተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ጸሎት ጥሩ መዓዛ ካለውና ወደ ላይ ከሚወጣ የዕጣን ጭስ ጋር ያመሳስለዋል። (መዝሙር 141:2፤ ራእይ 5:8፤ 8:4) ከልብ በመነጨ ስሜት የምናቀርባቸው ጸሎቶችም ወደ ላይ በመውጣት ሉዓላዊውን ጌታ ደስ እንደሚያሰኙ ማወቅ የሚያጽናና አይደለም? እንግዲያው ወደ ይሖዋ መቅረብ የምትፈልግ ከሆነ በትሕትና መንፈስ በየዕለቱ ደጋግመህ ጸልይ። በልብህ ውስጥ ያለውን ሁሉ ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። (መዝሙር 62:8) ያሳሰበህንም ሆነ ያስደሰተህን ነገር አካፍለው፤ በተጨማሪም ሰማያዊ አባትህን በጸሎት አመስግነው እንዲሁም አወድሰው። እንዲህ ካደረግህ በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት በጣም እየጠነከረ ይሄዳል።
ይሖዋን ማምለክ
13, 14. ይሖዋን ማምለክ ሲባል ምን ማለት ነው? እሱን ማምለካችን ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ አምላክን እናነጋግረዋለን ሲባል ከአንድ ወዳጃችን ወይም ዘመዳችን ጋር እንደምንጨዋወተው እንዲሁ ሐሳባችንን እንገልጽለታለን እንዲሁም እናዳምጠዋለን ማለት ብቻ አይደለም። ከእሱ ጋር የምናደርገው የሐሳብ ልውውጥ አምልኮም ነው፤ የሚገባውን አክብሮትና ፍርሃት የምናሳይበት መንገድ ነው። እውነተኛው አምልኮ መላ ሕይወታችንን የሚነካ ነው። ለይሖዋ ያለንን ከልብ የመነጨ ፍቅር የምንገልጽበትና ሙሉ በሙሉ ለእሱ ያደርን መሆናችንን የምናሳይበት መንገድ ነው። ይህ አምልኮ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ታማኝ የይሖዋ ፍጥረታት በሙሉ ያስተሳስራል። ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ መልአክ “ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን አምልኩ” ብሎ ሲያውጅ በራእይ ተመልክቷል።—ራእይ 14:7
14 ይሖዋን ማምለክ ያለብን ለምንድን ነው? በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተመለከትናቸውን እንደ ቅድስና፣ ኃይል፣ ራስን መግዛት፣ ፍትሕ፣ ድፍረት፣ ምሕረት፣ ጥበብ፣ ትሕትና፣ ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ ታማኝነትና ጥሩነት ያሉትን ባሕርያት መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። የትኛውንም መልካም ባሕርይ ከሁሉ በላቀ መንገድ የሚያንጸባርቀው ይሖዋ እንደሆነ ተመልክተናል። ባሕርያቱን አጠቃልለን ለመመልከት ስንሞክር ይሖዋን ለማድነቅ የምንገፋፋ ከመሆኑም በላይ ይህ ነው የማይባል ክብር የተጎናጸፈና ከእኛ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር የማይችል ታላቅ አምላክ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ኢሳይያስ 55:9) ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢያችን የመሆን መብት እንዳለው ምንም አያጠያይቅም። በእርግጥም ልናመልከው የሚገባ አምላክ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋን ልናመልከው የሚገባን እንዴት ነው?
15. ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችስ ምን አጋጣሚ ይሰጡናል?
15 ኢየሱስ “አምላክ መንፈስ ነው፤ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:24) አምላክን “በመንፈስ” ለማምለክ የእሱን መንፈስ ማግኘት እንዲሁም በመንፈሱ መመራት ያስፈልገናል። በተጨማሪም አምልኳችን ከእውነት ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር የምናደርገው ስብሰባ ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) የንጹሕ አምልኮ ክፍል በሆኑት ስብሰባዎች ላይ ተገኝተን ይሖዋን በመዝሙር በማወደስ፣ በአንድነት በመጸለይ እንዲሁም ቃሉን በመስማትና ሐሳብ በመስጠት ለእሱ ያለንን ፍቅር እንገልጻለን።
ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይሖዋን ለማምለክ የሚያስችሉ አስደሳች ዝግጅቶች ናቸው
16. ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ከተሰጡት ታላላቅ ትእዛዛት አንዱ ምንድን ነው? ይህን ተልእኮ ለመወጣት የሚያነሳሳንስ ምንድን ነው?
16 ስለ አምላክ ሌሎችን በማስተማር ለይሖዋ የምናቀርበው ውዳሴም የአምልኳችን ክፍል ነው። (ዕብራውያን 13:15) እንዲያውም ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች መስበክ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ከተሰጡት ታላላቅ ትእዛዛት አንዱ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይሖዋን ስለምንወደው በደስታ እንታዘዘዋለን። “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በይሖዋ ላይ የሐሰት ወሬ በመንዛት “የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ [እንዳሳወረ]” ስንመለከት ምሥክሮቹ ሆነን ስለ አምላካችን ጥብቅና ለመቆምና እንዲህ ያለውን ውሸት ለማጋለጥ አንገፋፋም? (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኢሳይያስ 43:10-12) በተጨማሪም በይሖዋ ድንቅ ባሕርያት ላይ ስናሰላስል ስለ እሱ ለሌሎች ለመንገር የሚገፋፋ ውስጣዊ ስሜት አያድርብንም? በእርግጥም ሰዎች ሰማያዊ አባታችንን እንዲያውቁትና እንዲወዱት ከመርዳት የላቀ መብት ሊኖር አይችልም።
17. ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ምን ነገሮችን ይጨምራል? በሙሉ ልባችን ልናመልከው የሚገባንስ ለምንድን ነው?
17 ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ሌሎች ነገሮችንም ይጨምራል። እያንዳንዱን የሕይወታችንን ዘርፍ የሚነካ ጉዳይ ነው። (ቆላስይስ 3:23) ይሖዋን ሉዓላዊ ጌታችን አድርገን የምንመለከተው ከሆነ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ማለትም በቤተሰብ ሕይወታችን፣ በሰብዓዊ ሥራችን፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነትም ሆነ ብቻችንን በምናሳልፈው ጊዜ ፈቃዱን ለማድረግ እንጥራለን። ይሖዋን “በሙሉ ልብ” ለማገልገል የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። (1 ዜና መዋዕል 28:9) የተከፋፈለ ልብ ይዘን ወይም ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራን ማለትም በድብቅ ኃጢአት እየሠራን ይሖዋን ለማገልገል ብንሞክር አምልኳችን ተቀባይነት የለውም። ይሖዋን በሙሉ ልብ የምናገለግል ከሆነ ፈጽሞ እንዲህ አናደርግም፤ ፍቅር ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ ጨርሶ እንኳ እንዳናስበው ያደርገናል። ይሖዋን የምንፈራ መሆናችንም ከእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ይጠብቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እንዲህ ያለ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸው ብቻ እንደሆኑ ይናገራል።—መዝሙር 25:14
ይሖዋን መምሰል
18, 19. ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ይሖዋ አምላክን መምሰል ይችላሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የእያንዳንዱ ክፍል የመጨረሻ ምዕራፍ ‘የተወደድን ልጆቹ በመሆን አምላክን መምሰል’ የምንችለው እንዴት እንደሆነ አብራርቷል። (ኤፌሶን 5:1) ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ይሖዋ ኃይሉን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን ያሳየበትን መንገድ መምሰል እንደምንችል መዘንጋት የለብንም። ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ መምሰል እንደምንችል እንዴት እናውቃለን? የስሙ ትርጉም እንደሚያመለክተው ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ መሆን የሚፈልገውን ሁሉ መሆን እንደሚችል አስታውስ። ይህ ችሎታው እጅግ ያስደንቀናል፤ ሆኖም መሆን የምንፈልገውን መሆን ለእኛ ጨርሶ የማይቻል ነገር ነው? በፍጹም።
19 የተፈጠርነው በአምላክ አምሳል ነው። (ዘፍጥረት 1:26) ይህ የሰው ልጆችን በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የተለዩ ያደርጋቸዋል። በደመ ነፍስ፣ በዘር ውርስ ወይም በአካባቢያችን ያሉት ሁኔታዎች በሚያሳድሩብን ተጽዕኖ የምንመራ አይደለንም። ይሖዋ ውድ ስጦታ ማለትም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። የአቅም ገደብና አለፍጽምና ቢኖርብንም መሆን የምንፈልገውን ለመሆን መምረጥ እንችላለን። ልንዘነጋው የማይገባ ሌላም ነገር አለ፦ የአምላክ ስም ትርጉም፣ አገልጋዮቹ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ ማድረግ የሚችል መሆኑንም ያመለክታል። ያለውን ኃይል በትክክል የሚጠቀም፣ አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ፍትሐዊ ሰው መሆን ትፈልጋለህ? በይሖዋ መንፈስ በመታገዝ እንዲህ ዓይነት ሰው መሆን ትችላለህ! እንዲህ ዓይነት ሰው መሆንህ የሚያስገኘውን መልካም ውጤት እስቲ አስበው።
20. ይሖዋን ለመምሰል የምናደርገው ጥረት ምን ውጤት ያስገኛል?
20 የሰማያዊ አባትህን ልብ ደስ ታሰኛለህ። (ምሳሌ 27:11) እንዲያውም ይሖዋ ያለብህን የአቅም ገደብ ስለሚረዳ የቻልከውን ያህል ከጣርክ “ሙሉ በሙሉ [ልታስደስተው]” ትችላለህ። (ቆላስይስ 1:9, 10) በተጨማሪም ተወዳጅ የሆነውን አባትህን በመምሰል ጥሩ ባሕርያትን ለማዳበር ስትጥር ልዩ መብትና በረከት ታገኛለህ። ከአምላክ በራቀውና በጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ብርሃን ማብራት ትችላለህ። (ማቴዎስ 5:1, 2, 14) ዕፁብ ድንቅ የሆኑትን የይሖዋ ባሕርያት በመላው ምድር ላይ በማንጸባረቅ ረገድ የበኩልህን ድርሻ ታበረክታለህ። ይህ እንዴት ያለ መብት ነው!
“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል”
21, 22. ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ ከፊታቸው ምን ይጠብቃቸዋል?
21 በያዕቆብ 4:8 ላይ የሚገኘው ምክር እያበረታታን ያለው አንድ ግብ ላይ ደርሰን እንድናቆም አይደለም። ይህ ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው። ታማኝ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ ይህ ሂደት ማብቂያ አይኖረውም። ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የምናደርገውን ጥረት መቼም ቢሆን አናቆምም። ደግሞም ስለ እሱ የምንቀስመው ትምህርት ማለቂያ የለውም። ይህ መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ልናውቀው የሚገባንን ነገር ሁሉ አሳውቆናል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ከሚያስተምረው ትምህርት ውስጥ ለመዳሰስ የሞከርነው ጥቂቱን ብቻ ነው ማለት ይቻላል! መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ስለ ይሖዋ ልንማረው የምንችለውን ነገር ሁሉ ይዟል ማለት አይደለም። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ያከናወነው ነገር ሁሉ ይጻፍ ቢባል “ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 21:25) ስለ ልጁ እንዲህ ከተባለ ስለ አባቱማ ምን ሊባል እንደሚችል ገምት!
22 ለዘላለም ስንኖርም እንኳ ስለ ይሖዋ ተምረን አንዘልቀውም። (መክብብ 3:11) እንግዲያው ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን አስብ። በመቶዎች፣ በሺዎች፣ በሚሊዮኖች አልፎ ተርፎም በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት ስንኖር ስለ ይሖዋ አምላክ የምናገኘው ትምህርት አሁን ካለን እውቀት ብዙ ጊዜ እጥፍ እየጨመረ እንደሚሄድ የታወቀ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሌሎች ድንቅ ነገሮች ገና መማር እንደሚቀረን እንገነዘባለን። “እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል” ሲል እንደዘመረው መዝሙራዊ ስለሚሰማን ብዙ ለመማር እንጓጓለን። (መዝሙር 73:28) የዘላለም ሕይወት ልንገምተው ከምንችለው በላይ አርኪና አስደሳች ነው፤ ከሁሉ ይበልጥ የሚያስደስተው ደግሞ ይህ ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብን ለመሄድ የሚያስችል አጋጣሚ የሚሰጠን መሆኑ ነው።
23. ምን እንድታደርግ የሚያነሳሳ ማበረታቻ ተሰጥቶሃል?
23 እንግዲያው ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህ፣ አእምሮህና ኃይልህ በመውደድ እሱ ላሳየህ ፍቅር ምላሽ ለመስጠት የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። (ማርቆስ 12:29, 30) ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ምንጊዜም የማይናወጥ ይሁን። ትንሽም ይሁን ትልቅ በየዕለቱ የምታደርገው ማንኛውም ውሳኔ ከሰማያዊ አባትህ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር ቆርጠህ እንደተነሳህ በግልጽ የሚያንጸባርቅ ይሁን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለዘላለም ዓለም አንተም ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረብክ እንድትሄድ እሱም ወደ አንተ ይበልጥ እንዲቀርብ እንመኛለን!