ንቁዎችና ትጉዎች ሁኑ!
“ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”—ማቴዎስ 25:13
1. ሐዋርያው ዮሐንስ ምንን በጉጉት ይጠባበቅ ነበር?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በመጨረሻው የቃል ምልልስ ላይ ኢየሱስ “በቶሎ እመጣለሁ” ሲል ቃል ገብቷል። ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ “አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና” ሲል መልሷል። ሐዋርያው ስለ ኢየሱስ መምጣት ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ አልነበረውም። “ይህ መቼ ይሆናል? የመገኘትህና [በግሪክኛ ፓሩሲያ] የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱስ ምንድን ነው?” በማለት ኢየሱስን ከጠየቁት ሐዋርያት አንዱ ዮሐንስ ነበር። አዎን፣ ዮሐንስ የኢየሱስን መገኘት በእርግጠኝነት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር።—ራእይ 22:20፤ ማቴዎስ 24:3 NW
2. የኢየሱስን መገኘት በተመለከተ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
2 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች እንዲህ ዓይነት መንፈስ የላቸውም። በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ኢየሱስ “መምጣት” የሚናገር ይፋዊ መሠረተ ትምህርት ቢኖራቸውም በእርግጥ ይመጣል ብለው የሚጠባበቁት አባሎቻቸው ግን ከስንት አንድ ናቸው። አኗኗራቸውም ኢየሱስ ይመጣል ብለው እንደማይጠብቁ የሚያሳይ ነው። ዘ ፓሩሲያ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “የፓሩሲያ ተስፋ በቤተ ክርስቲያን አባላት ሕይወት፣ አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ያሳደረው ምንም አዎንታዊ ተጽእኖ የለም ለማለት ይቻላል። . . . ቤተ ክርስቲያን በጥድፊያ ስሜት ልታከናውነው የሚገባት የንስሐ ተግባርና ወንጌልን የመስበክ ሚስዮናዊ ተልእኮ ሙሉ በሙሉ ባይቆምም እጅግ ተዳክሟል።” ሆኖም ይህ አባባል ሁሉንም የሚያጠቃልል አይደለም!
3. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ፓሩሲያ ምን ይሰማቸዋል? (ለ) በተለይ አሁን መመርመር የሚያስፈልገን የትኛውን ነጥብ ነው?
3 የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የዚህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይህን በታማኝነት ማድረጋችንን በመቀጠል የኢየሱስ መገኘት ለሚያካትታቸው ነገሮች ትክክለኛውን አመለካከት ማዳበርና ከዚህም ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ይገባናል። ይህም ‘እስከ መጨረሻው ለመጽናትና ለመዳን’ ያስችለናል። (ማቴዎስ 24:13) በማቴዎስ ምዕራፍ 24ና 25 ላይ የሚገኘውን ትንቢት በተናገረበት ጊዜ ኢየሱስ ለዘላቂ ጥቅማችን ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለው ጥበብ ያለበት ምክር ሰጥቷል። ምዕራፍ 25 የአሥሩን ቆነጃጅትና (ልባሞቹና ሰነፎቹ ቆነጃጅት) የመክሊቶቹን ምሳሌ ጨምሮ በአብዛኛው የምታውቋቸውን ምሳሌዎች የያዘ ነው። (ማቴዎስ 25:1-30) ከእነዚህ ምሳሌዎች ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
እንደ አምስቱ ቆነጃጅት ንቁዎች ሁኑ!
4. ስለ ቆነጃጅቱ የሚናገረው ምሳሌ ፍሬ ነገር ምንድን ነው?
4 በማቴዎስ 25:1-13 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የቆነጃጅቱን ምሳሌ በድጋሚ ማንበብ ትፈልጉ ይሆናል። ታሪኩ ስለ አንድ ታላቅ የአይሁዳውያን ሰርግ የሚናገር ሲሆን ሙሽራው ሙሽሪትን ወደ ሙሽራው ቤት (ወይም ወደ አባቱ ቤት) ለማምጣት ወደ አባቷ ቤት እንደሄደ ይናገራል። እንዲህ ያለው አጀብ ሙዚቀኞችንና ዘፋኞችን ሊጨምር የሚችል ሲሆን ሰርገኞቹ የሚደርሱበት ጊዜ በትክክል አይታወቅም። ምሳሌው ሙሽራውን በመጠባበቅ እስከ ሌሊት ድረስ ስለቆዩ አሥር ቆነጃጅት ይናገራል። አምስቱ ሰነፎች ስለነበሩ በቂ ዘይት ይዘው አልመጡም፤ በመሆኑም ተጨማሪ ዘይት ለመግዛት መሄድ ነበረባቸው። የተቀሩት አምስቱ ግን ጥበበኞች በመሆን ትርፍ ዘይት በማሰሮአቸው ይዘው መጥተው ነበር፤ ስለዚህ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ መብራቶቻቸውን ሊሞሉ ይችሉ ነበር። ሙሽራው በመጣ ጊዜ በቦታው የተገኙት እነዚህ አምስቱ ብቻ ነበሩ። በመሆኑም ወደ ግብዣው እንዲገቡ የተፈቀደላቸው እነሱ ብቻ ናቸው። አምስቱ ሰነፍ ቆነጃጅት ሲመለሱ ሊገቡ የሚችሉበት ጊዜ አልፎ ነበር።
5. ስለ ቆነጃጅቱ የሚናገረው ታሪክ የያዘውን ምሳሌያዊ ትርጉም ግልጽ የሚያደርጉት የትኞቹ ቅዱሳን ጽሑፎች ናቸው?
5 የዚህ ታሪክ በርካታ ገጽታዎች ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው መሆኑን ልንመለከት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ሙሽራ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። (ዮሐንስ 3:28-30) ኢየሱስ የሰርግ ግብዣ ከተዘጋጀለት የንጉሥ ልጅ ጋር ራሱን አመሳስሏል። (ማቴዎስ 22:1-14) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስን ከባል ጋር ያነጻጽረዋል። (ኤፌሶን 5:23) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሌሎች ቦታዎች ላይ እንደ ክርስቶስ “ሙሽራ” ተደርገው ቢገለጹም ምሳሌው ስለ ሙሽራይቱ የሚናገረው ነገር አለመኖሩ ትኩረትን የሚስብ ነው። (ዮሐንስ 3:29፤ ራእይ 19:7፤ 21:2, 9) ይሁንና ምሳሌው ስለ አሥር ቆነጃጅት የሚናገር ሲሆን ቅቡዓኑ ደግሞ በሌሎች ቦታዎች ላይ ለክርስቶስ በታጨች ድንግል ተመስለው ተገልጸዋል።—2 ቆሮንቶስ 11:2a
6. ኢየሱስ የቆነጃጅቱን ምሳሌ ሲደመድም ምን ምክር ሰጠ?
6 እነዚህን ከመሳሰሉ ዝርዝር ሐሳቦችና ተግባራዊ የሆኑ ትንቢቶች በተጨማሪ ከዚህ ምሳሌ የምንማራቸው ግሩም የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደሚኖሩ እሙን ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ምሳሌውን ለመደምደም የተጠቀመባቸውን ቃላት ልብ በሉ:- “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።” ስለዚህ ምሳሌው እየቀረበ ላለው ለዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው። መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀን መናገር ባንችልም መጨረሻው እንደሚመጣ ምንም አያጠያይቅም። በዚህ ረገድ ሁለቱ የቆነጃጅት ቡድኖች የነበራቸውን አመለካከት ተመልከት።
7. በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት አምስቱ ቆነጃጅት ሰነፎች መሆናቸውን ያሳዩት በምን መንገድ ነበር?
7 ኢየሱስ ‘አምስቱ ሰነፎች እንደ ነበሩ’ ተናግሯል። ሰነፎች የሆኑት ሙሽራው ይመጣል የሚል እምነት ስላልነበራቸው ነው? የግል ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ይሯሯጡ ስለነበር ነው? ወይም ደግሞ ተታለው ነው? አይደለም። ኢየሱስ እነዚህ አምስቱ ቆነጃጅት ‘ሙሽራውን ሊቀበሉ እንደወጡ’ ተናግሯል። እንደሚመጣ ያውቁ የነበረ ሲሆን በቦታውም ለመገኘትና ሌላው ቀርቶ ‘የሰርጉ ድግስ’ ታዳሚዎች ለመሆን ፈልገው ነበር። ይሁንና በቂ ዝግጅት አድርገው ነበር? እስከ ‘እኩለ ሌሊት’ ድረስ ጠብቀውታል፤ ይሁን እንጂ እነሱ ካሰቡት ጊዜ ፈጥኖም ይምጣ ዘግይቶ በማንኛውም ጊዜ እሱን ለመቀበል ዝግጁዎች አልነበሩም።
8. በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት አምስቱ ቆነጃጅት ልባሞች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር?
8 ኢየሱስ ልባሞች ብሎ የጠራቸው የተቀሩት አምስቱ ቆነጃጅት ግን ሙሽራውን ለመቀበል መብራታቸውን አብርተው ሄደዋል። እነሱም ቢሆኑ መጠበቅ ነበረባቸው፤ ሆኖም “ልባሞች” ነበሩ። “ልባም” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ጠንቃቃ፣ አስተዋይና ተግባራዊ ጥበብ ያለው” መሆን የሚል ሐሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። እነዚህ አምስቱ ቆነጃጅት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መብራቶቻቸውን ለመሙላት የሚያስችላቸውን ትርፍ ዘይት በማሰሮዎች ይዘው በመምጣት ልባሞች መሆናቸውን አስመስክረዋል። እንዲያውም ሙሽራውን ለመቀበል ዝግጁ በመሆን ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ዘይታቸውን ለመስጠት ፈቃደኞች አልሆኑም። ሙሽራው በሚመጣበት ጊዜ በቦታው ላይ ከመገኘታቸውና ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ከመሆናቸው አንጻር ስንመለከተው እንዲህ ያለው ንቃት ከልክ ያለፈ አልነበረም። እነዚህ “ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፣ ደጁም ተዘጋ።”
9, 10. ስለ ቆነጃጅቱ የሚናገረው ምሳሌ የያዘው ዋና መልእክት ምንድን ነው? ራሳችንንስ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን?
9 ኢየሱስ በሰርግ ላይ ሊኖር የሚገባውን ተገቢ ሁኔታ ወይም ለሌሎች ማካፈልን የሚመለከት ምክር መስጠቱ አልነበረም። ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” የሚል ነበር። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- የኢየሱስን መገኘት በሚመለከት በእርግጥ ንቁ ነኝን? በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ በመግዛት ላይ እንዳለ እናምናለን፤ ይሁን እንጂ ‘የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና እንደሚመጣ ስላወቅነው’ እውነት ምን ያህል ትኩረት ሰጥተናል? (ማቴዎስ 24:30) ቆነጃጅቱ ሙሽራውን ለመቀበል ከወጡበት ከመጀመሪያው ሰዓት ይልቅ ‘እኩለ ሌሊት’ ላይ የሙሽራው መምጫ ይበልጥ ቀርቦ እንደነበር የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይም የሰው ልጅ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት የሚመጣበት ጊዜ ስለ መምጫው ማሰብ ከጀመርንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ይበልጥ ቀርቧል። (ሮሜ 13:11-14) አሁንም ንቁ ሆነን በመጠባበቅ ላይ ነንን? ጊዜው እየቀረበ ሲመጣስ ይበልጥ ይህን ማድረጋችንን እንቀጥላለንን?
10 “ንቁ” የሚለውን ትእዛዝ ማክበር ሁልጊዜ በንቃት መጠባበቅን ይጠይቃል። አምስቱ ቆነጃጅት ዘይታቸውን በመጨረሳቸው ተጨማሪ ዘይት ለመግዛት ሄዱ። ዛሬም አንድ ክርስቲያን ሐሳቡ ተከፋፍሎ አይቀሬ ለሆነው የኢየሱስ መምጣት ሙሉ በሙሉ ሳይዘጋጅ ሊቀር ይችላል። ይህ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተከስቷል። ዛሬም በአንዳንዶች ላይ ሊከሰት ይችላል። ስለዚህ ‘ይህ ሁኔታ በእኔ ላይ እየደረሰ ነውን?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።—1 ተሰሎንቄ 5:6-8፤ ዕብራውያን 2:1፤ 3:12፤ 12:3፤ ራእይ 16:15
መጨረሻው እየቀረበ በመሆኑ ትጉዎች ሁኑ
11. ኢየሱስ ቀጥሎ የትኛውን ምሳሌ ተናገረ? ከምንስ ጋር የሚመሳሰል ነበር?
11 ኢየሱስ ቀጥሎ በተናገረው ምሳሌ ላይ ተከታዮቹን ያሳሰበው ንቁዎች እንዲሆኑ ብቻ አልነበረም። ስለ ልባሞቹና ሰነፎቹ ቆነጃጅት ታሪክ ከተናገረ በኋላ የመክሊቶቹን ምሳሌ ተናግሯል። (ማቴዎስ 25:14-30ን አንብብ።) ይህ ምሳሌ ኢየሱስ ቀደም ሲል ‘የአምላክ መንግሥት ፈጥኖ ይገለጣል የሚል ግምት ለነበራቸው’ ሰዎች ከተናገረው የምናኖቹ ምሳሌ ጋር በብዙ መልኩ ይመሳሰላል።—ሉቃስ 19:11-27
12. የመክሊቶቹ ምሳሌ ፍሬ ነገር ምንድን ነው?
12 ኢየሱስ በመክሊቶቹ ምሳሌ ላይ ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ሦስት ባሪያዎቹን ስለ ጠራ ሰው ይናገራል። “ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ፣” ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለሌላው ሁለትና ለመጨረሻው ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው። ይህ ምናልባት የብር መክሊት ማለት ሊሆን ስለሚችል በወቅቱ አንድ የቀን ሞያተኛ በ14 ዓመት ውስጥ የሚያገኘው መደበኛ ክፍያ ነበር። ትንሽ ገንዘብ አልነበረም! ሰውየው ሲመለስ ተለይቷቸው በቆየበት ‘ረዥም ዘመን’ ውስጥ ባሪያዎቹ የሠሩትን እንዲያስረክቡት አደረገ። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች በአደራ የተሰጣቸውን ገንዘብ እጥፍ አድርገው ቆዩት። ጌታውም “መልካም” አድርጋችኋል ካላቸው በኋላ ተጨማሪ ሹመት ሊሰጣቸው ቃል በመግባት ‘ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ’ በማለት ደመደመ። አንድ መክሊት የተቀበለው ባሪያ ጌታው በጣም ስግብግብ ነው በሚል ሰበብ በተቀበለው መክሊት አልተጠቀመም ነበር። ገንዘቡን ቆፍሮ ቀበረው እንጂ ወለድ እንዲያስገኝ እንኳ ባንክ አላስገባውም። የጌታውን ፍላጎት ባለማሟላቱ ጌታው “ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ” አለው። በዚህ ምክንያት መክሊቱ ተወስዶበት “ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት” ወዳለበት ወደ ውጪ እንዲወጣ ተደረገ።
13. ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ከተጠቀሰው ጌታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነበር?
13 እዚህም ላይ ቢሆን የታሪኩን ዝርዝር ሐሳብ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ወደ ሌላ አገር በሚሄደው ሰው የተመሰለው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ትቶ ወደ ሰማይ በመሄድ ንጉሣዊ ሥልጣን እስኪቀበል ድረስ ለረዥም ጊዜ ይቆያል።b (መዝሙር 110:1-4፤ ሥራ 2:34-36፤ ሮሜ 8:34፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ይሁንና አሁንም ቢሆን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ የምናደርገው ሰፊ የሆነ ትምህርት ወይም መሠረታዊ ሥርዓት ልናገኝ እንችላለን። ይህ ምንድን ነው?
14. የመክሊቶቹ ምሳሌ የሚያጎላው የምንን አስፈላጊነት ነው?
14 የኢየሱስ ምሳሌ ግልጽ እንዳደረገው ተስፋችን የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት ማግኘትም ይሁን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን ማስጠመድ አለብን። እንዲያውም የዚህ ምሳሌ መልእክት ትጋት በሚለው አንድ ቃል ተጠቃልሎ ሊገለጽ ይችላል። ሐዋርያት በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ጀምሮ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር አከናውነዋል። እንዲህ እናነባለን:- “[ጴጥሮስ] በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና:- ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው።” (ሥራ 2:40-42) ጥረቱ እንዴት ያለ ግሩም ውጤት አስገኝቶለታል! ከሐዋርያቱ ጋር በመተባበር በክርስቲያናዊው የስብከት ሥራ መካፈል የጀመሩ ሰዎችም ትጉዎች ስለነበሩ ምሥራቹ ‘በመላው ዓለም ሊያድግ’ ችሏል።—ቆላስይስ 1:3-6, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 3:5-9
15. የመክሊቶቹ ምሳሌ የያዘውን ፍሬ ነገር ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባን በምን ልዩ መንገድ ነው?
15 ስለ ኢየሱስ መገኘት የሚናገረውን የዚህን ምሳሌ ቁም ነገር ልብ በል። የኢየሱስ ፓሩሲያ በሂደት ላይ መሆኑንና በቅርቡም ወደ ታላቁ መደምደሚያው እንደሚደርስ የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉን። ኢየሱስ ‘መጨረሻውንና’ ክርስቲያኖች ሊሠሩት የሚገባቸውን ሥራ አያይዞ እንደተናገረ አስታውሱ:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህን በአእምሯችን በመያዝ የትኛውን ባሪያ ነው የምንመስለው? እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ:- ‘ምናልባት የግል ጉዳዩን ለማሟላት ሲሯሯጥ በአደራ የተሰጠውን ነገር ቆፍሮ ከቀበረው ባሪያ ጋር እመስላለሁ ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ ምክንያት ይኖር ይሆን? ወይስ ጥሩና የታመኑ የነበሩትን ባሪያዎች የምመስል መሆኔ በግልጽ ይታያል? በማንኛውም አጋጣሚ የጌታን ሥራ ለማሳደግ ቆርጬ ተነስቻለሁን?’
በመገኘቱ ጊዜ ንቁዎችና ትጉዎች መሆን
16. ቀደም ሲል የተወያየንባቸው ሁለቱ ምሳሌዎች ለአንተ ምን መልእክት ያስተላልፋሉ?
16 አዎን፣ ከምሳሌያዊና ከትንቢታዊ ትርጉማቸው በተጨማሪ እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ከራሱ ከኢየሱስ አፍ የፈለቀ ግልጽ ማበረታቻን የያዙ ናቸው። ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት በተለይ የክርስቶስ ፓሩሲያ ምልክት በሚታይበት ጊዜ ንቁዎችና ትጉዎች ሁኑ የሚል ነው። ምልክቱ እየታየ ያለው ደግሞ አሁን ነው። ታዲያ በእርግጥ ንቁዎችና ትጉዎች ነንን?
17, 18. የኢየሱስን መገኘት በተመለከተ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ምን ምክር ለግሷል?
17 የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ የኢየሱስን ትንቢት ለመስማት በደብረ ዘይት ተራራ ከተገኙት ሰዎች መካከል አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ስለ ትንቢቱ የተማረ ሲሆን ፍሬ ነገሩንም በሚገባ ተረድቶት ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ [“እስከ ጌታ መገኘት፣” NW] ድረስ ታገሡ። እነሆ፣ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፣ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት [“መገኘት፣” NW] ቀርቦአልና።”—ያዕቆብ 5:7, 8 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
18 ያዕቆብ ሀብታቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ አምላክ እንደሚፈርድባቸው ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ሲጠባበቁ ትዕግሥታቸውን እንዳያጡ ክርስቲያኖችን አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ትዕግሥቱን ያጣ ክርስቲያን ሰዎች የሠሯቸውን ስህተቶች ማረም እንዳለበት ተሰምቶት የበቀል እርምጃ ይወስድ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ሊሆን አይገባም፤ ምክንያቱም የፍርድ ጊዜ በእርግጥ ይመጣል። ያዕቆብ የተናገረው የገበሬው ምሳሌ ይህንን ያሳያል።
19. አንድ እስራኤላዊ ገበሬ ምን ዓይነት ትዕግሥት ሊያሳይ ይችል ነበር?
19 አንድ እስራኤላዊ ገበሬ ዘርን ከዘራ በኋላ ዘሩ እስኪበቅል፣ ከዚያም አዝመራው ደርሶ እስኪሰበሰብ መጠበቅ ነበረበት። (ሉቃስ 8:5-8፤ ዮሐንስ 4:35) በእነዚህ ወራት ውስጥ ስለ አንዳንድ ነገሮች በማሰብ የሚጨነቅባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። የፊተኛው ዝናብ ይመጣ ይሆን? በበቂስ መጠን ይዘንብ ይሆን? የኋለኛው ዝናብስ? ተባይ ወይም ዓውሎ ነፋስ ሰብሌን ያጠፋብኝ ይሆን? (ከኢዩኤል 1:4፤ 2:23-25 ጋር አወዳድር።) ያም ሆኖ ግን በአጠቃላይ ሲታይ አንድ እስራኤላዊ ገበሬ በይሖዋና እሱ ባዘጋጃቸው ተፈጥሯዊ ዑደቶች ላይ እምነት ሊያሳድር ይችል ነበር። (ዘዳግም 11:14፤ ኤርምያስ 5:24) የገበሬው ትዕግሥት በእርግጠኝነት የሚጠባበቅ መሆኑን ሊያሳይ ይችላል። የሚጠብቀው ነገር እንደሚመጣ ስለሚያውቅ በእምነት ይጠባበቃል። ደግሞም ይመጣል!
20. ከያዕቆብ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ትዕግሥታችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
20 ገበሬው የአዝመራው መሰብሰቢያ ጊዜ መቼ እንደሚሆን የተወሰነ እውቀት ሊኖረው ቢችልም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ግን የኢየሱስ መገኘት መቼ እንደሚሆን ማስላት አይችሉም ነበር። ሆኖም ያ ጊዜ መድረሱ የማይቀር ነገር ነበር። ያዕቆብ ‘የጌታ መገኘት [በግሪክኛ ፓሩሲያ] ቀርቦአልና’ ሲል ጽፏል። ያዕቆብ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ጊዜ የክርስቶስን መገኘት የሚያሳየው ምልክት በሰፊው ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ገና ግልጽ አልሆነም ነበር። አሁን ግን ግልጽ ሆኗል! ታዲያ በዚህ ጊዜ እንዴት ሊሰማን ይገባል? ምልክቱ በግልጽ እየታየ ነው። እኛም እያየነው ነው። በመሆኑም ‘ምልክቱ ሲፈጸም እያየሁ ነው’ በማለት በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። አፋችንን ሞልተን ‘ያለነው በጌታ መገኘት ወቅት ላይ ነው፤ መደምደሚያውም ሩቅ አይደለም’ ለማለት እንችላለን።
21. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል?
21 ስለዚህ በተለይ እኛ ቀደም ሲል የተወያየንባቸውን የኢየሱስ ሁለት ምሳሌዎች ልብ የምንልበትና የሚያስተላልፉትን ትምህርት ተግባራዊ የምናደርግበት ጠንካራ ምክንያት አለን። ኢየሱስ “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ብሏል። (ማቴዎስ 25:13) ይህ ወቅት በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ቀናተኛ የምንሆንበት ጊዜ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ፍሬ ነገር እንደገባን በሚያሳይ መንገድ ዘወትር እንመላለስ። ንቁዎች እንሁን! ትጉዎች እንሁን!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የታሪኩን ምሳሌያዊ ዝርዝር ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ሺህ ዓመት የሚገዛው የአምላክ መንግሥት ቀርቧል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 169-182, 183-211 ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
◻ ስለ ልባሞቹና ስለ ሰነፎቹ ቆነጃጅት ከሚናገረው ምሳሌ ምን ቁልፍ የሆነ መልእክት አግኝተሃል?
◻ ስለ መክሊቶቹ በሚናገረው ምሳሌ አማካኝነት ኢየሱስ ሊሰጥህ የፈለገው መሠረታዊ ምክር ምንድን ነው?
◻ ፓሩሲያውን በትዕግሥት መጠባበቅህ አንድ እስራኤላዊ ገበሬ ከሚያሳየው ትዕግሥት ጋር የሚመሳሰለው በምን መልኩ ነው?
◻ በዚህ ዘመን መኖርን ከሌሎች ጊዜያት በተለየ አስደሳችም ፈታኝም የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ስለ ቆነጃጅቱና ስለ መክሊቶቹ ከሚናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?