ሰዎች መጥፎ ነገር የሚሠሩት ለምንድን ነው?
ብዙ ሰዎች አሌ የማይሉት አንድ ሐቅ አለ፦ ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን እንሳሳታለን፤ እንዲሁም በኋላ ላይ የምንጸጸትባቸውን ነገሮች እንፈጽማለን። ያም ሆኖ በየቀኑ ማለት ይቻላል፣ እኛ ራሳችን ለምናያቸው ወይም በመገናኛ ብዙኃን ለምንሰማቸው ከባድም ሆኑ ቀላል የሚባሉ መጥፎ ድርጊቶች ሁሉ መንስኤው ሰዎች ፍጹማን አለመሆናቸው ነው?
ሰዎች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ሊጣሱ የማይገባቸው የሥነ ምግባር ደንቦች እንዳሉና የሰው ልጆች ክፉ ተግባር ከመፈጸም መራቅ እንደሚችሉ ብዙዎች የማይክዱት ሐቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ባለማወቅ የተሳሳተ ነገር በመናገርና ሆን ብሎ የሌሎችን ስም በማጥፋት እንዲሁም በድንገት በሰው ላይ ጉዳት በማድረስና ታስቦበት በሚፈጸም ነፍስ ግድያ መካከል ልዩነት እንዳለ አብዛኞቹ ሰዎች ይስማማሉ። ይሁንና ብዙውን ጊዜ አስደንጋጭ የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈጽሙት በማኅበረሰቡ ውስጥ ፈጽሞ ያልተጠበቁ ሰዎች ናቸው። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሰዎች መጥፎ ነገር የሚሠሩት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ጉዳይ ግልጽ ያደርግልናል። ሰዎች መጥፎ እንደሆኑ የሚያውቋቸውን ድርጊቶች ለመፈጸም የሚያነሳሷቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች በትክክል ለይቶ ይገልጻል። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።
▪ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል።”—መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም
ሰዎች በሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ የማያደርጉትን ነገር በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተነሳ ለማድረግ የሚነሳሱበት ጊዜ እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። እንዲያውም አንዳንዶች ለመከራና ለፍትሕ መዛባት መፍትሔ እንደሚያመጡ በማሰብ የወንጀል ድርጊቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ። ኧርባን ቴረሪዝም የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኛውን ጊዜ . . . አንድን ሰው አሸባሪ እንዲሆን የሚያነሳሳው ዋነኛው ምክንያት የማይለወጡ መስለው በሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃይሎች ላይ የሚያድርበት ብስጭት ነው።”
▪ “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:10 አ.መ.ት
ጥሩ ሰዎችም እንኳ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ከቀረበላቸው የሥነ ምግባር ደንቦችን ለመጣስ ፈቃደኞች እንደሚሆኑ አንዳንዶች ይናገራሉ። ለወትሮው ተወዳጅ እና ደግ የሚመስሉ ሰዎች ለገንዘብ ሲሉ ባሕርያቸው ተለውጦ ጨካኝና መጥፎ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ በስግብግብነት የተነሳ የሚፈጸሙትን በርካታ ወንጀሎች ይኸውም ማጭበርበርን፣ አፈናንና ጠለፋን እንዲሁም ሚስጥርን ለማጋለጥ በማስፈራራት ገንዘብ መቀበልን አልፎ ተርፎም ነፍስ ማጥፋትን መጥቀስ ይቻላል።
▪ “በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ።”—መክብብ 8:11 የ1954 ትርጉም
ሰዎች፣ ሕግ ተፈጻሚነት ከሌለው አንድ ሰው ማንኛውንም ወንጀል ፈጽሞ ሳይቀጣ ማምለጥ ይችላል ብለው ሊያስቡ እንደሚችሉ ይህ ጥቅስ ይጠቁማል። በአውራ ጎዳናዎች ላይ ከሚፈቀደው ፍጥነት በላይ መኪና የሚያሽከረክሩ፣ ፈተና የሚኮርጁ፣ የሕዝብን ገንዘብ የሚያጭበረብሩና ከዚህም የከፋ ነገር የሚፈጽሙ ሰዎች ከላይ የተገለጸው ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ሕግ እምብዛም ተፈጻሚነት ከሌለው ወይም እጋለጣለሁ የሚለው ፍርሃት ከጠፋ ለወትሯቸው ሕግ አክባሪ የነበሩ ሰዎችም እንኳ ሌላ ጊዜ የማያደርጉትን ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም ሊደፋፈሩ ይችላሉ። አርጊውመንትስ ኤንድ ፋክትስ የተሰኘው መጽሔት “ወንጀለኞች በቀላሉ ቅጣትን ማምለጥ መቻላቸው . . . ሌሎች ሰዎች እጅግ አሰቃቂ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ የሚገፋፋቸው ይመስላል” ብሏል።
▪ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15
ሰዎች ስንባል መጥፎ ነገር ማሰብ ይቀናናል። በየቀኑ መጥፎ ነገር እንድንሠራ የሚገፋፉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ፈተናዎች ያጋጥሙናል። በጥንት ጊዜ ክርስቲያኖች “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም” ተብለው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:13) እንደዚያም ሆኖ ፈተናው የሚያስከትለው ውጤት የተመካው በግለሰቡ ምርጫ ላይ ነው፤ ግለሰቡ መጥፎውን ሐሳብ ቶሎ ከአእምሮው ማውጣት ወይም እንዲህ ባለው ሐሳብ ላይ በማውጠንጠን ምኞቱ እያደገ እንዲሄድ መፍቀድ ይችላል። ያዕቆብ በመንፈስ መሪነት ከጻፈው ደብዳቤ ላይ የተወሰደው ከላይ ያለው ጥቅስ፣ አንድ ሰው መጥፎ ምኞት በውስጡ ‘እንዲፀነስ’ ከፈቀደ መጥፎ ድርጊት መፈጸሙ እንደማይቀር ያስጠነቅቃል።
▪ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
ጓደኞቻችን በበጎም ይሁን በመጥፎ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብን መዘንጋት አይኖርብንም። ብዙ ጊዜ ሰዎች በእኩዮቻቸው ተጽዕኖ ምክንያት ወይም ብዙዎች እንደሚሉት ከመጥፎ ጓደኞች ጋር በመግጠማቸው የተነሳ ፈጽሞ ያላሰቡትን ነገር አድርገው ከባድ ችግር ውስጥ ይገባሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ “ተላሎች” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የመረዳት ችሎታቸው ዝቅተኛ የሆነ ሰዎችን ሳይሆን ከአምላክ ቃል የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ችላ የሚሉትን ሰዎች ነው። ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች ጓደኞቻችንንና አብረናቸው የምንውላቸውን ሰዎች በጥበብ ማለትም ጠቃሚ በሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ካልመረጥን ‘ጉዳት እንደሚያገኘን’ የታወቀ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህና ሌሎችም ጥቅሶች ለወትሮው ደህና የነበሩ ሰዎች መጥፎ እንዲያውም በጣም አስደንጋጭ ድርጊት የሚፈጽሙት ለምን እንደሆነ ቁልጭ አድርገው ይገልጻሉ። ሰዎች አሰቃቂ የሆኑ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸውን ምክንያቶች መረዳት ጠቃሚ መሆኑ የማይካድ ቢሆንም እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ሊሻሻሉ እንደሚችሉ ተስፋ ማድረግ ይቻል ይሆን? አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙበትን ምክንያት ከመግለጽም አልፎ እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች የሚወገዱበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። እነዚህ ተስፋዎች ምንድን ናቸው? በዓለም ላይ የሚፈጸሙት መጥፎ ነገሮች በሙሉ የሚወገዱበት ጊዜ በእርግጥ ይመጣል? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይሰጠናል።