ምዕራፍ 17
ምንጊዜም ከይሖዋ ድርጅት ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ
ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ሲል ጽፏል። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ ካለው ታላቅ ግርማ የተነሳ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች የሚያቀርቡትን ጸሎት እንደማይሰማ እንዲሁም ፈጽሞ ወደ እኛ ሊቀርብ እንደማይችል አድርገን ልናስብ አይገባም። (ሥራ 17:27) ወደ አምላክ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችለው ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና በመመሥረት ሲሆን ይህም ልባዊ ጸሎት ማቅረብን ይጨምራል። (መዝ. 39:12) በተጨማሪም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በማጥናት ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። በዚህ መንገድ ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ዓላማዎቹና ለእኛ ስላለው ፈቃድ ማወቅ እንችላለን። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ይህም ይበልጥ እንድንወደውና እሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል።—መዝ. 25:14
2 ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችለው በልጁ በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው። (ዮሐ. 17:3፤ ሮም 5:10) ከኢየሱስ የተሻለ የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት እንድናውቅ ሊረዳን የሚችል ማንም የለም። አባቱን በቅርብ ስለሚያውቀው “ከአብ በስተቀር ወልድ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም” ብሎ ሊናገር ችሏል። (ሉቃስ 10:22) ስለዚህ ስለ ኢየሱስ አስተሳሰብና ስሜት የሚገልጹትን የወንጌል ዘገባዎች ስናጠና በተዘዋዋሪ መንገድ የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት እያጠናን ነው ማለት ይቻላል። እንዲህ ያለው እውቀት ወደ አምላካችን ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።
3 ከአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ጋር ተቀራርበን በመኖር በአምላክ ልጅ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆነን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት እንችላለን። በማቴዎስ 24:45-47 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለእምነት ቤተሰቦች “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን” የሚሰጥ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። በዛሬው ጊዜ ታማኙ ባሪያ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። ይሖዋ በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ቃሉን በየዕለቱ እንድናነብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንድንገኝና ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመስበኩ ሥራ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንድናደርግ ይመክረናል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20፤ ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 1:1-3) ታማኙን ባሪያ በተመለከተ ሰብዓዊ አመለካከት እንዲያድርብን ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም። ከይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ጋር ተቀራርበን ለመኖርና በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና ጥንካሬ ይሰጠናል።
ፈተናዎች እየጨመሩ የመጡት ለምንድን ነው?
4 ለብዙ ዓመታት በእውነት ቤት ውስጥ የቆየህ ክርስቲያን ልትሆን ትችላለህ። ከሆነ ንጹሕ አቋምህን አደጋ ላይ የሚጥሉ ፈተናዎችን መቋቋም አስፈልጎህ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋን ያወቅከውና ከአምላክ ሕዝቦች ጋር የተቀላቀልከው በቅርቡ ቢሆንም እንኳ ሰይጣን ዲያብሎስ ለይሖዋ ሉዓላዊነት የሚገዛን ማንኛውንም ሰው እንደሚቃወም ሳትመለከት አትቀርም። (2 ጢሞ. 3:12) ፈተናዎችን ተቋቁመህ መጽናት ያስፈለገህ ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረጅም ጊዜ፣ የምትፈራበት ወይም ተስፋ የምትቆርጥበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ እንደሚደግፍህ፣ እንደሚያድንህና የዘላለም ሕይወት በመስጠት ወሮታ እንደሚከፍልህ ቃል ገብቷል።—ዕብ. 13:5, 6፤ ራእይ 2:10
5 የሰይጣን ሥርዓት እስካለ ድረስ ከፈተና ነፃ የሚሆን አንድም ሰው የለም። በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሰይጣን፣ ይሖዋ ወደሚኖርበት ሰማይ እንዳይሄድ ታግዷል። ሰይጣን ወደ ምድር የተጣለ ሲሆን የእሱም ሆነ የክፉ መላእክቱ እንቅስቃሴ በምድር ላይ ብቻ የተገደበ እንዲሆን ተደርጓል። ራሳቸውን በወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን የተፋፋመ ስደት ጨምሮ በምድር ላይ እየጨመረ የመጣው ወዮታ የሰይጣን ቁጣ ውጤት ከመሆኑም በላይ የሰይጣን ክፉ አገዛዝ ሊያበቃ በተቃረበበት ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ራእይ 12:1-12
6 ሰይጣን በደረሰበት ውርደት በጣም የተናደደ ከመሆኑም ሌላ የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ያውቃል። ከአጋንንቱ ጋር በመተባበር የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለማስተጓጎል እንዲሁም የይሖዋን አገልጋዮች አንድነት ለማናጋት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል። በመሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ውጊያ ላይ ናቸው ማለት ይቻላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ውጊያ በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “የምንታገለው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዢዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።” ከይሖዋ ጎን በመቆም ውጊያውን በድል አድራጊነት ማጠናቀቅ ከፈለግን ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችንን አሟልተን እንገኛለን። እንዲህ በማድረግ “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም” ይኖርብናል። (ኤፌ. 6:10-17) ይህ ደግሞ ጽናት ይጠይቃል።
ጽናትን ማዳበር
7 ጽናት ማለት “መከራን ወይም ችግርን ተቋቁሞ ማለፍ” ማለት ነው። በመንፈሳዊ ሁኔታ ደግሞ ጽናት የሚለው ቃል መከራን፣ ተቃውሞን፣ ስደትን ወይም በአምላክ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም እንድናላላ ለማድረግ የሚቀርብን ማንኛውንም ፈተና ተቋቁሞ ማለፍን ያመለክታል። ክርስቲያናዊ ጽናት፣ ሊዳብር የሚገባው ባሕርይ ነው። ይህ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል። መንፈሳዊ እድገት እያደረግን ስንሄድ የመጽናት አቅማችንም የዚያኑ ያህል እየጎለበተ ይሄዳል። ክርስቲያናዊ ጉዟችንን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የሚደርሱብንን ትናንሽ የእምነት ፈተናዎች መቋቋማችን ኃይላችን እንዲጠናከር ስለሚያደርግ ወደፊት የሚመጡብንን ከባድ ፈተናዎች ተቋቁመን ማለፍ እንችላለን። (ሉቃስ 16:10) ከባድ ፈተናዎችን በእምነት ጸንተን ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ፈተናዎቹ ከደረሱብን በኋላ ሳይሆን ፈተናዎቹ ከመድረሳቸው በፊት ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ጽናትን ጨምሮ ሌሎች አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ማዳበር እንዳለብን ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ልባዊ ጥረት በማድረግ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነት ላይ እውቀትን፣ በእውቀት ላይ ራስን መግዛትን፣ ራስን በመግዛት ላይ ጽናትን፣ በጽናት ላይ ለአምላክ ማደርን፣ ለአምላክ በማደር ላይ ወንድማዊ መዋደድን፣ በወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።”—2 ጴጥ. 1:5-7፤ 1 ጢሞ. 6:11
የሚደርሱብንን ፈተናዎች ተቋቁመን ስናልፍ ከዕለት ወደ ዕለት ጽናትን እያዳበርን እንሄዳለን
8 ያዕቆብ በደብዳቤው ላይ እንደሚከተለው ብሎ በመጻፍ ጽናት የማዳበርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል፦ “ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፤ ይህን ስታደርጉ ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ። ይሁንና በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።” (ያዕ. 1:2-4) ያዕቆብ፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን ፈተናዎች ጽናትን ለማዳበር እንደሚረዱት በመገንዘብ ፈተናዎችን በደስታ መቀበል እንዳለበት ተናግሯል። አንተስ ለሚደርሱብህ ፈተናዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት አለህ? ያዕቆብ በመቀጠል ጽናት ክርስቲያናዊ ባሕርያችንን ፍጹም በማድረግና በአምላክ ፊት ሙሉ ተቀባይነት እንድናገኝ በማስቻል ረገድ የሚያከናውነው ሥራ እንዳለ አመልክቷል። አዎ፣ የሚደርሱብንን ፈተናዎች ተቋቁመን ስናልፍ ከዕለት ወደ ዕለት ጽናትን እያዳበርን እንሄዳለን። ጽናት ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል።
9 ፈተናዎችን በጽናት መቋቋማችን ይሖዋን ደስ የሚያሰኘው ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንዲሰጠን ይገፋፋዋል። ያዕቆብ በመቀጠል “ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ፣ ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል” ሲል ገልጿል። (ያዕ. 1:12) አዎ፣ ፈተናዎችን በጽናት የምንቋቋመው ሕልውናችንን የሚነካ ጉዳይ ስለሆነ ነው። ካልጸናን በእውነት ውስጥ መቆየት አንችልም። ይህ ዓለም በሚያሳድርብን ተጽዕኖዎች ከተሸነፍን ወደ ዓለም መመለሳችን አይቀርም። ካልጸናን የይሖዋን መንፈስ ማግኘት ስለማንችል በሕይወታችን ውስጥ የመንፈሱን ፍሬ አናፈራም።
10 በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ መጽናት ከፈለግን ክርስቲያን በመሆናችን ለሚደርስብን መከራ ትክክለኛ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ያዕቆብ “እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት” ብሎ እንደጻፈ አስታውስ። እርግጥ ነው፣ ፈተናው አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ ሊያስከትልብን ስለሚችል እንዲህ ማድረጉ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ የወደፊት ሕይወትህን የሚነካ ጉዳይ እንደሆነ አስታውስ። በአንድ ወቅት በሐዋርያት ላይ የደረሰው ሁኔታ፣ ልዩ ልዩ መከራዎች ቢደርሱብንም መደሰት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ይህ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፏቸው፤ ከዚያም በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ አዘው ለቀቋቸው። እነሱም ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው ከሳንሄድሪን ሸንጎ ወጡ።” (ሥራ 5:40, 41) ሐዋርያቱ የደረሰባቸው መከራ የኢየሱስን ትእዛዝ እንደፈጸሙና የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ የሚያሳይ ማረጋገጫ መሆኑን ተረድተው ነበር። ጴጥሮስ ከዓመታት በኋላ በመንፈስ መሪነት በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ለጽድቅ ሲባል ይህን ዓይነቱን መከራ መቀበል የሚያስገኘውን ጥቅም ገልጿል።—1 ጴጥ. 4:12-16
11 በተጨማሪም ጳውሎስና ሲላስ ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። በፊልጵስዩስ ሚስዮናዊ ሥራቸውን እያከናወኑ በነበሩበት ወቅት ከተማዋን ረብሸዋል እንዲሁም ያልተፈቀዱ ልማዶችን አስተምረዋል በሚል ወንጀል ተይዘው ተከሰሱ። በዚህ የተነሳ በኃይል ከተደበደቡ በኋላ እስር ቤት ተጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጳውሎስና ሲላስ ገና እስር ቤት ውስጥ እያሉና ቁስላቸውን ሳይታከሙ ስለተከናወነው ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር።” (ሥራ 16:16-25) ጳውሎስና ሲላስ ለክርስቶስ ሲሉ ለተቀበሉት መከራ ትክክለኛው አመለካከት ነበራቸው፤ የደረሰባቸው መከራ፣ በአምላክና በሰዎች ፊት ጽኑ አቋም እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ብቻ ሳይሆን ምሥራቹን የመስማት ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ተጨማሪ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ተገንዝበው ነበር። ይህ የሌሎች ሰዎችንም ሕይወት የሚነካ ጉዳይ ነበር። በዚያው ምሽት፣ የእስር ቤቱ ጠባቂና ቤተሰቡ ምሥራቹን ሰምተው ደቀ መዛሙርት ለመሆን በቅተዋል። (ሥራ 16:26-34) ጳውሎስና ሲላስ በይሖዋ፣ እሱ ባለው ኃይልና በመከራዎቻቸው ሁሉ እነሱን ለመደገፍ ባለው ፈቃደኝነት ይተማመኑ ነበር። ይሖዋም አላሳፈራቸውም።
12 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ የሚደርስብንን ፈተና መቋቋም የምንችልበት ዝግጅት አድርጎልናል። ይህን ያደረገው እንድንጸና ስለሚፈልግ ነው። ስለ ዓላማው ትክክለኛ እውቀት እንዲኖረን ለመርዳት ሲል በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃሉን ሰጥቶናል። ይህም እምነታችንን ይገነባልናል። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር የምንሰበሰብበትና ቅዱስ አገልግሎት የምናቀርብበት አጋጣሚ አለን። ከዚህም በተጨማሪ በጸሎት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና የመመሥረት መብት አለን። ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን ምስጋና እንዲሁም በፊቱ ንጹሕ አቋም ይዘን እንድንኖር ይረዳን ዘንድ የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ልመና ይሰማል። (ፊልጵ. 4:13) ወደፊት ስለሚጠብቀን ተስፋ ማሰላሰላችንም ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ይሆነናል።—ማቴ. 24:13፤ ዕብ. 6:18፤ ራእይ 21:1-4
ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መጽናት
13 በዛሬው ጊዜ የሚደርሱብን ፈተናዎች የጥንቶቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከደረሱባቸው ፈተናዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። በዘመናችንም የይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ መረጃ በተሰጣቸው ተቃዋሚዎች ተሰድበዋል እንዲሁም ተደብድበዋል። በሐዋርያት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም አብዛኛውን ጊዜ ተቃውሞ የሚቆሰቁሱት የአምላክ ቃል የሐሰት ትምህርታቸውንና ተግባራቸውን ያጋለጠባቸው አክራሪ ሃይማኖተኞች ናቸው። (ሥራ 17:5-9, 13) አንዳንዴ የይሖዋ ሕዝቦች፣ ፖለቲካዊ መንግሥታት የሚሰጧቸውን ሕጋዊ መብቶች በማስከበር ከሚደርስባቸው ተቃውሞ እፎይታ ማግኘት ችለዋል። (ሥራ 22:25፤ 25:11) ይሁን እንጂ ገዥዎች ራሳቸው ሥራችንን በይፋ በማገድ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ለማስቆም ጥረት የሚያደርጉበት ጊዜ አለ። (መዝ. 2:1-3) እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት የተናገሩትን የታማኝ ሐዋርያትን ምሳሌ በድፍረት እንከተላለን።—ሥራ 5:29
14 በመላው ምድር ላይ ብሔራዊ ስሜት እየተጋጋለ በሄደ መጠን የምሥራቹ ሰባኪዎች አምላክ የሰጣቸውን አገልግሎት ማከናወናቸውን እንዲያቆሙ የሚደርስባቸው ተጽዕኖም እየጨመረ ይሄዳል። የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ በራእይ 14:9-12 ላይ “አውሬውንና ምስሉን” ማምለክን በተመለከተ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር በሚገባ ተገንዝበዋል። ዮሐንስ “የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን እምነት አጥብቀው የሚከተሉ ቅዱሳን፣ መጽናት የሚያስፈልጋቸው እዚህ ላይ ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ እንረዳለን።
15 በጦርነት፣ በአብዮታዊ ነውጥ፣ ቀጥተኛ በሆነ ስደትና በእገዳ ምክንያት የሚመጡ ፈተናዎች ክርስቲያናዊ አምልኮህን በይፋ ማከናወን እንዳትችል ሊያደርጉህ ይችላሉ። በጉባኤ ደረጃ አንድ ላይ መሰብሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠር ይሆናል። ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ግንኙነት ማድረግ አይቻል ይሆናል። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉብኝት ሊስተጓጎል ይችላል። ጽሑፎችን ማግኘትም ቢሆን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ?
16 ንጹሕ አምልኮን ለማራመድ የቻልከውንና ሁኔታዎቹ የሚፈቅዱልህን ሁሉ አድርግ። የግል ጥናት ማድረግ ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ የተወሰኑ ወንድሞችን ያቀፉ ቡድኖች በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተሰብስበው ሊያጠኑ ይችላሉ። ቀደም ሲል የተጠኑ ጽሑፎችንና መጽሐፍ ቅዱስን በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መጠቀም ይቻላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ልትደናገጥ ወይም ልትረበሽ አይገባም። በአብዛኛው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር ግንኙነት ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ይፈጥራል።
17 ከክርስቲያን ወንድሞችህ ጋር ያለህ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ቢቋረጥም እንኳ ከይሖዋም ሆነ ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለህ ግንኙነት እንደማይቋረጥ አስታውስ። ተስፋህ ብሩሕ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል። በዚህም ሁኔታ ሥር፣ ይሖዋ ጸሎትህን የሚሰማ ከመሆኑም ሌላ በመንፈሱ አማካኝነት ያበረታሃል። ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጥህ ጠይቀው። የይሖዋ አገልጋይና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ አስታውስ። በመሆኑም ለሌሎች ለመመሥከር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች በሚገባ ተጠቀምባቸው። ይሖዋ፣ ሌሎች በእውነተኛው አምልኮ ከጎንህ እንዲሰለፉ በማድረግ ጥረትህን ሊባርከው ይችላል።—ሥራ 4:13-31፤ 5:27-42፤ ፊልጵ. 1:27-30፤ 4:6, 7፤ 2 ጢሞ. 4:16-18
18 እንደ ሐዋርያትና እንደ ሌሎቹ የአምላክ አገልጋዮች አንተም የግድያ ዛቻ ሊደርስብህ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ “ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ” ላይ ጠንካራ እምነት ይኑርህ። (2 ቆሮ. 1:8-10) ይሖዋ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለህ እምነት በጣም ከባድ የሆነን ተቃውሞም ጭምር እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። (ሉቃስ 21:19) ክርስቶስ ኢየሱስ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የሚደርሱበትን ፈተናዎች በታማኝነት መወጣቱ ሌሎችን እንዲጸኑ ሊያበረታታ እንደሚችል ያውቅ ነበር። አንተም በተመሳሳይ ለወንድሞችህ የብርታት ምንጭ ልትሆን ትችላለህ።—ዮሐ. 16:33፤ ዕብ. 12:2, 3፤ 1 ጴጥ. 2:21
19 ከስደትና ከቀጥተኛ ተቃውሞ በተጨማሪ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ሊያስፈልግህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በክልላቸው ውስጥ ያሉ ሰዎች ግድየለሽነት ተስፋ አስቆርጧቸዋል። ሌሎች ደግሞ ያለባቸውን አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሕመም መቋቋም አሊያም ሰብዓዊ አለፍጽምናቸው ከሚያስከትልባቸው የአቅም ገደብ ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም አገልግሎቱን ማከናወን አስቸጋሪ እንዲሆንበት የሚያደርግን ችግር ተቋቁሞ ለመኖር ተገዷል። (2 ቆሮ. 12:7) በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፊልጵስዩስ ይኖር የነበረ አፍሮዲጡ የተባለ ክርስቲያን፣ ወዳጆቹ ‘እንደታመመ መስማታቸውን ስላወቀ ተጨንቆ’ ነበር። (ፊልጵ. 2:25-27) የራሳችንም ሆነ የሌሎች አለፍጽምና፣ ለመቋቋም የሚከብድ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥርብን ይችላል። ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ከሌሎች ክርስቲያኖች ሌላው ቀርቶ ከቤተሰባችን አባላትም ጋር እንድንጋጭ የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይሁን እንጂ በይሖዋ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር አጥብቀው የሚከተሉ ሁሉ እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋምና መወጣት ይችላሉ።—ሕዝ. 2:3-5፤ 1 ቆሮ. 9:27፤ 13:8፤ ቆላ. 3:12-14፤ 1 ጴጥ. 4:8
ምንጊዜም ታማኝ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ
20 ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ የጉባኤው ራስ አድርጎ ከሾመው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ ልናደርግ ይገባል። (ቆላ. 2:18, 19) ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲሁም የበላይ ተመልካች ሆነው ከተሾሙት ወንድሞች ጋር በቅርብ ተባብረን መሥራት ያስፈልገናል። (ዕብ. 13:7, 17) ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን ሙሉ በሙሉ የምንደግፍና ግንባር ቀደም ሆነው ከሚያገለግሉት ጋር ተባብረን የምንሠራ ከሆነ በተደራጀ መልኩ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም እንችላለን። በጸሎት መብታችን በሚገባ መጠቀም አለብን። የእስር ቤት ግንብም ሆነ ለብቻችን መታሠራችን በሰማይ ካለው አፍቃሪ አባታችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያቋርጠው ወይም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን አንድነት ሊያሳጣን እንደማይችል አስታውስ።
21 የተሰጠንን የስብከት ተልእኮ በጽናት ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚከተለው በማለት ለተከታዮቹ የሰጠውን ሥራ ዳር ለማድረስ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴ. 28:19, 20) ልክ እንደ ኢየሱስ እስከ መጨረሻው እንጽና። የመንግሥቱ ተስፋና የምናገኘው የዘላለም ሕይወት ሽልማት ቁልጭ ብሎ ይታየን። (ዕብ. 12:2) የተጠመቅን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ’ አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ላይ የበኩላችንን ድርሻ የማበርከት መብት አለን። ኢየሱስ “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 24:3, 14) በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ልባችን በዚህ ሥራ የምንካፈል ከሆነ ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን!