ይሖዋ መዳን እንድናገኝ ይጠብቀናል
“አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው።”—1 ጴጥ. 1:5
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ይሖዋ ወደ እውነተኛው አምልኮ የሚስበን እንዴት ነው?
ሕይወታችንን ከይሖዋ በምናገኘው ምክር አማካኝነት ለመምራት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ይሖዋ ማበረታቻ የሚሰጠን እንዴት ነው?
1, 2. (ሀ) አምላክ ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል ብለን እንድንተማመን የሚያደርገን የትኛው ማረጋገጫ ነው? (ለ) ይሖዋ ስለ እያንዳንዳችን ምን ያህል ያውቃል?
“እስከ መጨረሻው የጸና ግን እሱ ይድናል።” (ማቴ. 24:13) ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው አምላክ በሰይጣን ዓለም ላይ የፍርድ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት በሕይወት ለመትረፍ እስከ መጨረሻው ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንዳለብን ግልጽ ለማድረግ ነው። እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ በራሳችን ጥበብ ወይም ኃይል እንድንጸና ይተወናል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል፦ “አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” (1 ቆሮ. 10:13) ታዲያ ይህ ጥቅስ ምን ያስገነዝበናል?
2 ይሖዋ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዳይደርስብን ለማድረግ ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ማለትም የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ አፈጣጠራችንን እንዲሁም አቅማችን እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ማወቅ አለበት። ታዲያ አምላክ ይህን ያህል ስለ እኛ ያውቃል? ይህ ምንም ጥያቄ የለውም። ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ እያንዳንዳችንን ጠንቅቆ እንደሚያውቀን ይናገራሉ። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንንና ልማዶቻችንን በሚገባ ያውቃል። ሌላው ቀርቶ የምናስበውን ነገርና የልባችንን ዝንባሌ ማስተዋል ይችላል።—መዝሙር 139:1-6ን አንብብ።
3, 4. (ሀ) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች ትኩረት እንደሚሰጥ የዳዊት ተሞክሮ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እያከናወነ ያለው አስደናቂ ሥራ ምንድን ነው?
3 አምላክ እዚህ ግቡ ለማይባሉ ሰብዓዊ ፍጥረታት ትኩረት ይሰጣል ብሎ ማመን የሚከብድ ነገር ነው? መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይህ ጥያቄ ወደ አእምሮው መጥቶ ነበር፤ ለይሖዋ እንዲህ ብሎ መናገሩ ይህን ያሳያል፦ “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?” (መዝ. 8:3, 4) ዳዊት ይህን ጥያቄ እንዲያነሳ የገፋፋው በራሱ ሕይወት የተመለከተው ነገር ሊሆን ይችላል። የእሴይ የመጨረሻ ልጅ የሆነው ዳዊት ለይሖዋ ‘እንደ ልቡ የሆነለት ሰው’ ስለነበር ይሖዋ ‘ከበግ ጥበቃ ወስዶ’ በእስራኤል ላይ ገዥ እንዲሆን አድርጎታል። (1 ሳሙ. 13:14፤ 2 ሳሙ. 7:8) ዳዊት፣ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ የአንድን ተራ እረኛ የውስጥ ሐሳብ መረዳቱን ሲገነዘብ ምን ሊሰማው እንደሚችል መገመት አያዳግትም!
4 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ስለ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብ ማወቃችን በአግራሞት ስሜት እንድንዋጥ ያደርገናል። ይሖዋ ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡ ዕቃዎችን’ ወደ እውነተኛው አምልኮ እየሰበሰበ ከመሆኑም በላይ አገልጋዮቹ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ እየረዳቸው ነው። (ሐጌ 2:7 የ1954 ትርጉም) ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በደንብ ለመገንዘብ በቅድሚያ ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ የሚስባቸው እንዴት እንደሆነ መመልከት ይኖርብናል።
አምላክ ስቦናል
5. ይሖዋ ሰዎችን ወደ ልጁ የሚስባቸው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
5 ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 6:44) ይህ ሐሳብ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ይጠቁማል። ይሖዋ በግ መሰል ሰዎችን ወደ ልጁ የሚስባቸው እንዴት ነው? ይህን የሚያደርገው ምሥራቹ እንዲሰበክ በማድረግና መንፈስ ቅዱሱን በመጠቀም ነው። ለምሳሌ ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ በፊልጵስዩስ ሳሉ ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት አግኝተው ምሥራቹን ሰበኩላት። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ “ይሖዋም ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል እንድትሰማ ልቧን በደንብ ከፈተላት” ይላል። በእርግጥም አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት መልእክቱ እንዲገባት ረድቷታል፤ በዚህም የተነሳ እሷና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎች ተጠመቁ።—ሥራ 16:13-15
6. አምላክ ሁላችንንም ወደ እውነተኛ አምልኮ የሳበን እንዴት ነው?
6 እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማት ሊዲያ ብቻ ናት? በፍጹም። አንተም ራስህን የወሰንክ ክርስቲያን ከሆንክ ወደ እውነተኛው አምልኮ የሳበህ አምላክ ነው። በሰማይ የሚኖረው አባታችን በሊዲያ ልብ ውስጥ አንድ ጥሩ ነገር እንዳገኘ ሁሉ በአንተም ልብ ውስጥ አንድ የተመለከተው ነገር አለ። ይሖዋ ለምሥራቹ ጆሮህን መስጠትህን ሲያይ መልእክቱን ማስተዋል እንድትችል በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ረድቶሃል። (1 ቆሮ. 2:11, 12) የተማርከውን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ስታደርግ ፈቃዱን ለመፈጸም የምታደርገውን መፍጨርጨር ባርኮልሃል። ራስህን ለእሱ ስትወስን ልቡ በጣም ተደስቷል። በሕይወት መንገድ ላይ ጉዞ ከጀመርክበት ጊዜ አንስቶ በእያንዳንዱ እርምጃህ ይሖዋ ከጎንህ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
7. ታማኝ ሆነን መቀጠል እንድንችል አምላክ ይረዳናል የምንለው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ከእሱ ጋር አብረን መጓዝ እንድንጀምር ከረዳን እስከ መጨረሻው ታማኝ ሆነን እንድንጸናም ይረዳናል ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። በራሳችን ወደ እውነት መምጣት እንዳልቻልን ሁሉ በራሳችን ጥረት ብቻም በእውነት ውስጥ መጽናት እንደማንችል ያውቃል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚከተለውን ጽፎላቸዋል፦ “አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው።” (1 ጴጥ. 1:5) ይህ ሐሳብ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሠራ በመሆኑ የእኛንም ትኩረት ሊስብ ይገባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሁላችንም ለአምላክ ታማኝ ሆነን ለመቀጠል የእሱ እርዳታ ያስፈልገናል።
የተሳሳተ እርምጃ እንዳንወስድ ይጠብቀናል
8. የተሳሳተ እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?
8 ኑሮ የሚያሳድርብን ጫና ፍጹማን ካለመሆናችን ጋር ተዳምሮ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳናተኩር አልፎ ተርፎም ሳይታወቀን የተሳሳተ እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን ይችላል። (ገላትያ 6:1ን አንብብ።) በዳዊት ሕይወት ውስጥ የተከሰተው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል።
9, 10. ዳዊት የተሳሳተ እርምጃ እንዳይወስድ ይሖዋ የጠበቀው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ እኛን የሚረዳንስ እንዴት ነው?
9 ዳዊት፣ ንጉሥ ሳኦል እያሳደደው ቢሆንም እንኳ ቅናት ላሳበደው ለዚህ ንጉሥ አጸፋ ባለመመለስ አስደናቂ የሆነ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። (1 ሳሙ. 24:2-7) ይሁን እንጂ ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ዳዊት አለፍጽምናው አሸንፎት ነበር። በአንድ ወቅት ዳዊት አብረውት ለነበሩት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲሰጠው ወገኑ የሆነውን ናባልን በአክብሮት ጠየቀው። ናባል መልእክተኞቹን ሰድቦ ሲያባርራቸው ዳዊት በሁኔታው በጣም ተበሳጨ። በመሆኑም በናባል ቤት የሚገኙትን ወንዶች በሙሉ በማጥፋት ራሱ ለመበቀል ቆርጦ ተነሳ፤ በዚህ ወቅት ንጹሕ ሰዎችን መግደሉ በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ እንደሚያደርገው ዘንግቶ ነበር። ዳዊት አስከፊ የሆነ ስህተት ከመሥራት የተቆጠበው የናባል ሚስት የሆነችው አቢግያ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ጣልቃ ስለገባች ነው። ዳዊት በነገሩ ላይ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ስለተረዳ አቢግያን እንዲህ አላት፦ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።”—1 ሳሙ. 25:9-13, 21, 22, 32, 33
10 ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ይሖዋ በአቢግያ ተጠቅሞ ዳዊት የተሳሳተ እርምጃ እንዳይወስድ ጠብቆታል። ዛሬም ይሖዋ ለእኛ ተመሳሳይ ነገር ያደርግልናል። እርግጥ ነው፣ ስህተት ለመሥራት በምንነሳበት ጊዜ ሁሉ ጣልቃ በመግባት የሚያስቆመን አንድ ሰው ይልክልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። በተጨማሪም ከአንድ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ወይም ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ምን ዓይነት ሁኔታዎችን እንደሚፈቅድ ሙሉ በሙሉ ላንረዳ እንችላለን። (መክ. 11:5) ያም ሆኖ ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ ምንጊዜም እንደሚረዳና ለእሱ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” (መዝ. 32:8) ታዲያ ይሖዋ ምክር የሚሰጠን እንዴት ነው? ከይሖዋ ምክር ተጠቃሚ መሆን የምንችለውስ እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን እየመራ እንደሆነ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? እስቲ የራእይ መጽሐፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።
ምክር በመስጠት ይጠብቀናል
11. ይሖዋ በጉባኤዎች ውስጥ ስለሚከናወኑት ነገሮች የሚያውቀው እስከ ምን ድረስ ነው?
11 በራእይ ምዕራፍ 2 እና 3 ላይ የሚገኘው ዘገባ ክብር የተላበሰው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሿ እስያ የሚገኙ ሰባት ጉባኤዎችን እንደመረመረ ይናገራል። ይህ ራእይ ክርስቶስ የጉባኤዎቹን ሁኔታ በጥቅሉ ብቻ ሳይሆን በዝርዝርም እንደተመለከተ ይገልጻል። እንዲያውም ኢየሱስ የጉባኤውን አባላት በግለሰብ ደረጃ የጠቀሰበት ጊዜ ነበር፤ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ጉባኤ ተገቢውን ምስጋናና ምክር ሰጥቷል። ታዲያ ይህ ምን ይጠቁማል? በራእዩ ፍጻሜ መሠረት ሰባቱ ጉባኤዎች የሚያመለክቱት ከ1914 ወዲህ ያሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ሲሆን ለሰባቱ ጉባኤዎች የተሰጠው ምክር ደግሞ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ይሠራል። በመሆኑም ይሖዋ ዛሬም ቢሆን በልጁ አማካኝነት ሕዝቦቹን እየመራ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ታዲያ ከዚህ አመራር ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
12. ይሖዋ አካሄዳችንን እንዲመራልን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ከይሖዋ ፍቅራዊ አመራር ጥቅም ማግኘት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ የግል ጥናት ነው። ይሖዋ ታማኝና ልባም ባሪያ በሚያዘጋጃቸው ጹሑፎች አማካኝነት በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ይሰጠናል። (ማቴ. 24:45) ከዚህ ዝግጅት ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን ግን ጹሑፎቹን ጊዜ ወስደን ማጥናት እንዲሁም የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋ ‘ከመደናቀፍ እንድንጠበቅ’ ከሚያደርግበት መንገድ አንዱ የግል ጥናት ነው። (ይሁዳ 24) የግል ጥናት በምታደርግበት ወቅት ልክ ለአንተ እንደተጻፈ ሆኖ የተሰማህ ጽሑፍ አጋጥሞህ ያውቃል? ከሆነ፣ ምክሩን ከይሖዋ እንደተሰጠህ አድርገህ ተቀበል። አንድ ጓደኛህ የሆነ ነገር ሊያሳይህ ሲፈልግ ትከሻህን ነካ ነካ እንደሚያደርግህ ሁሉ ይሖዋም አንተ ብቻ ሳትሆን ሌሎች የእምነት ባልንጀሮችህም በባሕርያችሁ ረገድ ልታሻሽሉት የሚገባ ነገር እንዳለ ለመጠቆም በመንፈሱ ሊጠቀም ይችላል። በመሆኑም መንፈሱ ለሚሰጠን አመራር ንቁዎች ከሆንን ይሖዋ አካሄዳችንን እንዲመራልን እናደርጋለን። (መዝሙር 139:23, 24ን አንብብ።) እንግዲያው የጥናት ልማዳችንን መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው።
13. የጥናት ልማዳችንን መመርመራችን ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?
13 በመዝናኛ ከልክ በላይ የሆነ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ ለግል ጥናት ማዋል የሚገባንን ጊዜ ሊሻማብን ይችላል። አንድ ወንድም እንዲህ ሲል የታዘበውን ተናግሯል፦ “አንድ ሰው በቀላሉ የግል ጥናት የማድረግ ልማዱን ሊያቆም ይችላል። ሰዎች የሚዝናኑባቸው ነገሮች ከበፊቱ ይበልጥ ዛሬ በገፍ ይገኛሉ፤ ዋጋቸውም ቢሆን እየረከሰ መጥቷል። እንዲህ ያሉ መዝናኛዎች በቴሌቪዥን፣ በኮምፒውተርና በስልክ አማካኝነት በቀላሉ ይገኛሉ። እነዚህ ነገሮች አጥለቅልቀውናል ማለት ይቻላል።” በዚህ ረገድ ጠንቃቆች ካልሆንን ጥልቀት ያለው የግል ጥናት ለማድረግ የምናውለው ጊዜ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሊሄድ አልፎ ተርፎም ይህን ልማዳችንን ከናካቴው ልናቆም እንችላለን። (ኤፌ. 5:15-17) በመሆኑም ሁላችንም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘የአምላክን ቃል አዘውትሮ በጥልቀት የመመርመር ልማዱ አለኝ? ወይስ እንዲህ ያለ ዝግጅት የማደርገው ጉባኤ ላይ ንግግር ወይም ክፍል ሲኖረኝ ብቻ ነው?’ ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ይሖዋ መዳን እንድናገኝ እኛን ለመጠበቅ የሚጠቀምበትን መንፈሳዊ ጥበብ ማካበት እንድንችል ለቤተሰብ አምልኮ ወይም ለግል ጥናት የመደብነውን ጊዜ በተሻለ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል።—ምሳሌ 2:1-5
ማበረታቻ በመስጠት እንድንጸና ይረዳናል
14. ይሖዋ ለስሜታችን የሚያስብ አምላክ መሆኑን ቅዱሳን መጻሕፍት የሚገልጹት እንዴት ነው?
14 ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ አስጨናቂ ነገሮች ደርሰውበታል። (1 ሳሙ. 30:3-6) በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ሐሳቦች ይሖዋ ስሜቱን እንደተረዳለት ይገልጻሉ። (መዝሙር 34:18ን እና 56:8ን አንብብ።) አምላክ የእኛንም ስሜት ቢሆን ይረዳልናል። ‘ልባችን’ ወይም ‘መንፈሳችን’ ሲሰበር እሱ ወደ እኛ ይቀርባል። ይህን ማወቁ በራሱ ልክ እንደ ዳዊት እኛንም ሊያጽናናን ይችላል፤ ዳዊት “በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 31:7) ይሁን እንጂ ይሖዋ ጭንቀታችንን ከመረዳት ያለፈ ነገር ያደርግልናል። ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት እንድንጸና ያደርገናል። ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ነው።
15. አሳፍ ካጋጠመው ተሞክሮ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
15 በስብሰባዎች ላይ መገኘት ምን ያህል ጥቅም እንዳለው መዝሙራዊው አሳፍ ካጋጠመው ተሞክሮ መመልከት ይቻላል። አሳፍ በሚያያቸው ፍትሕ የጎደላቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰሉ አምላክን ማገልገል ምንም ፋይዳ እንደሌለው እንዲሰማው አድርጎት ነበር። ይህ ሁኔታ ተስፋ አስቆርጦት ነበር። አሳፍ ‘ነፍሴ ተማረረች፣ ልቤም ተቀሠፈ’ በማለት የተሰማውን ስሜት ገልጿል። በዚህም ምክንያት ይሖዋን ማገልገሉን ሊያቆም ተቃርቦ ነበር። ታዲያ አሳፍ ሚዛኑን እንዲጠብቅ የረዳው ምንድን ነው? ‘ወደ አምላክ መቅደስ መግባቱ’ እንደሆነ ተናግሯል። በአምላክ መቅደስ ማለትም ይሖዋን በሚያመልኩ ሰዎች መካከል መገኘቱ አመለካከቱን እንዲያስተካክል ረድቶታል። ክፉዎች ያገኙት ስኬት ጊዜያዊ እንደሆነ ብሎም ይሖዋ ነገሮችን ማስተካከሉ እንደማይቀር ተገንዝቧል። (መዝ. 73:2, 13-22) በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥመን ይችላል። በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚታዩት ፍትሕ የጎደላቸው ነገሮች ውጥረት ሊፈጥሩብንና እንድንዝል ሊያደርጉን ይችላሉ። ከወንድሞቻችን ጋር መሰብሰባችን ግን መንፈሳችንን የሚያድስልን ከመሆኑም በላይ ይሖዋን በማገልገል የምናገኘውን ደስታ ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።
16. ከሐና ምሳሌ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
16 በጉባኤ ውስጥ ያጋጠመህ አንድ ሁኔታ በስብሰባ ላይ መገኘትን አዳጋች ቢያደርግብህስ? ምናልባትም በጉባኤ ውስጥ ያለህን መብት በማጣትህ ኀፍረት ተሰምቶህ ወይም ከአንድ ወንድም ወይም ከእህት ጋር ሳትግባባ ቀርተህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሐና የተወችው ምሳሌ ሊረዳህ ይችላል። (1 ሳሙኤል 1:4-8ን አንብብ።) ሐና፣ ጣውንቷ ፍናና በምታደርስባት በደል የተነሳ በጣም ትበሳጭ እንደነበር አስታውስ። በተለይ በየዓመቱ ቤተሰቡ በሴሎ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ በሚሄድበት ጊዜ ይህ ሁኔታ የከፋ ይሆን ነበር። ሐና “እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ” በነገሩ በጣም ታዝን ነበር። ሆኖም ይህ ሁኔታ ለአምልኮ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ከመሄድ አላገዳትም። ይሖዋም ታማኝነቷን በመመልከት ባርኳታል።—1 ሳሙ. 1:11, 20
17, 18. (ሀ) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ማበረታቻ ማግኘት የምንችለው በምን መንገዶች ነው? (ለ) ይሖዋ መዳን እንድናገኝ ሲል ፍቅራዊ እንክብካቤ የሚያደርግልን መሆኑ ምን እንዲሰማህ ያደርግሃል?
17 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በታማኝነት በመገኘት ረገድ የሐናን ምሳሌ የሚከተሉበት ጥሩ ምክንያት አላቸው። ከራሳችን ተሞክሮ እንዳየነው ስብሰባዎች የብርታት ምንጭ ናቸው። (ዕብ. 10:24, 25) የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያሳዩን ፍቅር ያጽናናል። ንግግር በሚቀርብበት ወይም የጉባኤው አባላት ሐሳብ በሚሰጡበት ወቅት ልባችንን የሚነካ አንድ ነገር ልናገኝ እንችላለን። ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ጆሮ ሰጥቶ ሊያዳምጠን አሊያም የሚያጽናና ሐሳብ ሊያካፍለን ይችላል። (ምሳሌ 15:23፤ 17:17) ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለይሖዋ ስንዘምር መንፈሳችን ይታደሳል። በተለይ ‘በጭንቀት’ ስንዋጥ ከስብሰባ የምናገኘው ማጽናኛ በጣም ያስፈልገናል። ይሖዋ ጸንተን እንድንቆም የሚረዳንን ‘ማጽናኛ’ የሚሰጠን እንዲሁም ታማኝ ሆነን ለመመላለስ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ይዘን እንድንቀጥል የሚደግፈን በዚህ ቦታ ስንገኝ ነው።—መዝ. 94:18, 19
18 በአምላካችን ፍቅራዊ እንክብካቤ ሥር በመሆናችን “ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። በምክርህ መራኸኝ” በማለት እንደዘመረው እንደ መዝሙራዊው አሳፍ ይሰማናል። (መዝ. 73:23, 24) ይሖዋ መዳን እንድናገኝ ጥበቃ የሚያደርግልን በመሆኑ በጣም አመስጋኝ ነን!
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ አንተንም ቢሆን ስቦሃል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ጥበቃ ሆኖልናል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምናገኛቸው ማበረታቻዎች ጸንተን እንድንቆም ያደርጉናል