ፍቅር—ውድ የሆነ ባሕርይ
ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወታችን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ልናዳብራቸው ስለምንችላቸው ዘጠኝ ባሕርያት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ገላ. 5:22, 23) የእነዚህን ግሩም ባሕርያት ድምር ውጤት “የመንፈስ ፍሬ” በማለት ገልጾታል።a ይህ ፍሬ ‘የአዲሱ ስብዕና’ መገለጫ ነው። (ቆላ. 3:10) አንድ ዛፍ ተገቢውን እንክብካቤ ካገኘ ፍሬ እንደሚያፈራ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም በአንድ ግለሰብ ሕይወት ውስጥ በነፃነት የሚሠራ ከሆነ ግለሰቡ የመንፈስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል።—መዝ. 1:1-3
ጳውሎስ ያሰፈረው የመጀመሪያው የመንፈስ ፍሬ ገጽታ እጅግ ውድ ባሕርይ የሆነው ፍቅር ነው። ይህ ባሕርይ ምን ያህል ውድ ነው? ጳውሎስ “ፍቅር . . . ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 13:2) ይሁንና ፍቅር ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማዳበርና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማንጸባረቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?
ፍቅር የሚገለጸው እንዴት ነው?
የፍቅርን ምንነት በቃላት መግለጽ አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ስለሚገለጽባቸው መንገዶች ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ፍቅር “ታጋሽና ደግ ነው” ይላል። በተጨማሪም ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል” እንዲሁም “ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል” ይላል። ከዚህም ሌላ ፍቅር ለሌሎች ያለንን ጥልቅ የሆነ የመውደድ ስሜትና ከልብ የመነጨ አሳቢነት እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያለንን የጠበቀ ቁርኝት ያካትታል። በአንጻሩ ግን አንድ ሰው ፍቅር ከሌለው እንደ ቅናት፣ ኩራት፣ ራስ ወዳድነትና ቂመኝነት ያሉ ባሕርያትን ያንጸባርቃል፤ በተጨማሪም እንዲህ ያለው ግለሰብ ጨዋነት የጎደለው ምግባር የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አይሆንም። ደግነት ከጎደላቸውና ከንቱ ከሆኑት ከእነዚህ ባሕርያት በተለየ መልኩ ፍቅር “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮ. 13:4-8
ይሖዋና ኢየሱስ የተዉት የፍቅር ምሳሌ
“አምላክ ፍቅር ነው።” በእርግጥም ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ የሠራቸውም ሆነ ያደረጋቸው ነገሮች የእሱን ፍቅር ይመሠክራሉ። ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ኢየሱስ ወደ ምድር እንዲመጣና ለእኛ ሲል ተሠቃይቶ እንዲሞት ማድረጉ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።” (1 ዮሐ. 4:9, 10) አምላክ ባሳየን ፍቅር የተነሳ የኃጢአት ይቅርታ፣ ተስፋና ሕይወት ማግኘት ችለናል።
ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን በማቅረብ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ኢየሱስም] ‘እነሆ፣ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ’ አለ። . . . በዚህ ‘ፈቃድ’ መሠረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት ተቀድሰናል።” (ዕብ. 10:9, 10) ማንም ሰው ከዚህ የላቀ ፍቅር ሊያሳየን አይችልም። ኢየሱስም “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 15:13) ይሁንና ፍጽምና የጎደለን የሰው ልጆች ይሖዋና ኢየሱስ ፍቅር በማሳየት ረገድ የተዉልንን ምሳሌ መከተል እንችላለን? እንዴታ! እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
“በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”
ጳውሎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶናል፦ “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤ ክርስቶስ እንደወደደንና . . . ራሱን ስለ እኛ . . . እንደሰጠ ሁሉ እናንተም በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:1, 2) “በፍቅር መመላለሳችንን [መቀጠል]” የምንችለው በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ይህን ባሕርይ ለማንጸባረቅ ጥረት በማድረግ ነው። እንዲህ ያለው ፍቅር በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባርም መገለጽ ይኖርበታል። ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 3:18) ለምሳሌ ያህል፣ ከአምላክና ከባልንጀራችን ጋር በተያያዘ በፍቅር የምንመላለስ ከሆነ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ለሰዎች ለመናገር እንነሳሳለን። (ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 10:27) በተጨማሪም ታጋሽ፣ ደግና ይቅር ባይ በመሆን በፍቅር እንደምንመላለስ ማሳየት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ” የሚል ምክር የሚሰጠን ለዚህ ነው።—ቆላ. 3:13
ይሁንና እንዲህ ያለው እውነተኛ ፍቅር ከስሜታዊነት የተለየ ነው። ለምሳሌ ስሜታዊ የሆነ አንድ ወላጅ፣ የሚያለቅስ ልጁን ለማባበል ሲል ልጁ የጠየቀውን ሁሉ ሊያደርግለት ይችላል። ለልጁ እውነተኛ ፍቅር ያለው ወላጅ ግን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቆራጥ እርምጃ ይወስዳል። በተመሳሳይም አምላክ ፍቅር ቢሆንም ‘የሚወዳቸውን ከመገሠጽ’ ወደኋላ አይልም። (ዕብ. 12:6) እኛም በፍቅር የምንመላለስ ከሆነ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ተግሣጽ ከመስጠት ወደኋላ አንልም። (ምሳሌ 3:11, 12) እርግጥ ነው፣ ተግሣጽ በምንሰጥበት ጊዜ እኛም ኃጢአተኞች እንደሆንንና ፍቅር የጎደለው እርምጃ ልንወስድ እንደምንችል መዘንጋት አይኖርብንም። በመሆኑም ፍቅር በማሳየት ረገድ ሁላችንም ማሻሻያ የምናደርግበት አቅጣጫ መኖሩ አይቀርም። ይሁንና ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እንመልከት።
ፍቅርን ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?
አንደኛ፣ አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህ ጸልይ፤ ይህ መንፈስ ፍቅርን እንድታዳብር ይረዳሃል። ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” እንደሚሰጥ ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:13) በመሆኑም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት የምንጸልይ እንዲሁም ‘በመንፈስ መመላለሳችንን ለመቀጠል’ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይበልጥ አፍቃሪዎች እየሆንን እንሄዳለን። (ገላ. 5:16) ለምሳሌ ያህል፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሽምግልና እያገለገልክ ያለህ ወንድም ከሆንክ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መስጠት እንድትችል የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ልትጠይቅ ትችላለህ። ወላጅ ከሆንክ ደግሞ ልጆችህን በቁጣ ሳይሆን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መገሠጽ እንድትችል መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳህ መጠየቅ ትችላለህ።
ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሚያበሳጭ ነገር ባጋጠመው ጊዜም እንኳ ፍቅር ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማስታወስ ሞክር። (1 ጴጥ. 2:21, 23) በተለይም ደግሞ አንድ ሰው ቅር ሲያሰኘን አሊያም ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ሲፈጸምብን ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ‘ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ይረዳናል። ሊ የተባለች እህት እንዲህ ብላ ራሷን መጠየቋ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ቆም ብላ እንድታስብ እንደረዳት ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት፣ አብራኝ የምትሠራ አንዲት ሴት ስለ እኔና ስለምሠራው ሥራ መጥፎ ነገር ጽፋ ለሥራ ባልደረቦቼ በኢሜይል ላከችላቸው። ያደረገችው ነገር ስሜቴን በጥልቅ ጎድቶት ነበር። ሆኖም ‘ከዚህች ሴት ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምችለው እንዴት ነው?’ በማለት ራሴን ጠየቅኩ። ኢየሱስ ቢሆን ምን እርምጃ እንደሚወስድ ማሰቤ ጉዳዩን ችላ ብዬ እንዳልፍ ረድቶኛል። ከጊዜ በኋላ፣ ይህች ሴት ከባድ የጤና እክል እንዳጋጠማትና በጣም ተጨንቃ እንደነበር ሰማሁ። በመሆኑም ያንን ነገር የጻፈችው በክፋት ተነሳስታ ላይሆን እንደሚችል አሰብኩ። ኢየሱስ የሚያበሳጭ ነገር ባጋጠመው ጊዜም እንኳ ፍቅር ያሳየው እንዴት እንደሆነ ማሰቤ እኔም ለሥራ ባልደረባዬ ተመሳሳይ ፍቅር እንዳሳይ ረድቶኛል።” አዎ፣ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ምንጊዜም ለሌሎች ፍቅር እናሳያለን።
ሦስተኛ፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለማዳበር ጥረት አድርግ። (ዮሐ. 13:34, 35) በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረውን አስተሳሰብ’ እንድናዳብር ያበረታታናል። ኢየሱስ ለእኛ ሲል፣ በሰማይ የነበረውን ቦታ ትቶ በመምጣት ‘ራሱን ባዶ ያደረገ’ ከመሆኑም ሌላ “እስከ ሞት ድረስ” መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሆኗል። (ፊልጵ. 2:5-8) ኢየሱስ ያሳየውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለማንጸባረቅ ጥረት ስናደርግ በአስተሳሰብም ሆነ በስሜት ይበልጥ እሱን እየመሰልን እንሄዳለን፤ ይህም የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት ከራሳችን እንድናስቀድም ያነሳሳናል። ፍቅርን ማዳበራችን ምን ሌሎች ጥቅሞች ያስገኝልናል?
ፍቅር ማሳየት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
ፍቅር ማሳየት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ሁለቱን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦
ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር፦ እርስ በርሳችን ፍቅር ስላለን በየትኛውም አገር ወዳለ ጉባኤ ብንሄድ ወንድሞችና እህቶች በደስታ እንደሚቀበሉን እናውቃለን። ‘በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ባሉት ወንድሞቻችን’ መወደድ በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው! (1 ጴጥ. 5:9) እንዲህ ያለውን ፍቅር ልናገኝ የምንችለው በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ብቻ ነው።
ሰላም፦ ‘አንድ ላይ የሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ’ ሊኖረን የቻለው ‘እርስ በርሳችን በፍቅር ተቻችለን በመኖራችን’ ነው። (ኤፌ. 4:2, 3) በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይህን ሰላም በገዛ ዓይናችን የመመልከት አጋጣሚ እናገኛለን። ዛሬ ባለው እርስ በርሱ የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለውን ሰላም ማየት በእርግጥም አስደናቂ አይደለም? (መዝ. 119:165፤ ኢሳ. 54:13) ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት በማድረግ ለሰዎች ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ እናሳያለን፤ ይህም በሰማይ ያለውን አባታችንን ያስደስተዋል።—መዝ. 133:1-3፤ ማቴ. 5:9
‘ፍቅር ያንጻል’
ጳውሎስ “ፍቅር . . . ያንጻል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 8:1) ፍቅር የሚያንጸው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ 13ተኛ ምዕራፍ ላይ ሐዋርያው ፍቅር የሚያንጸው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። አንደኛ ነገር፣ ፍቅር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልጋል። (1 ቆሮ. 10:24፤ 13:5) በተጨማሪም ፍቅር አሳቢ፣ የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ የሚያስገባ፣ ታጋሽና ደግ ስለሆነ ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ እርስ በርስ የሚዋደድ ቤተሰብና አንድነት ያለው ጉባኤ ለመገንባት ይረዳል።—ቆላ. 3:14
ከሁሉ የበለጠ ዋጋ ያለውና የሚያንጸው ፍቅር፣ ሁላችንም ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር ከተለያየ አስተዳደግ፣ ዘርና ቋንቋ የተውጣጡ ሰዎች “እጅ ለእጅ ተያይዘው” ይሖዋን በአንድነት እንዲያገለግሉት ያስችላል። (ሶፎ. 3:9) እንግዲያው ሁላችንም የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ይህን ውድ ባሕርይ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለማንጸባረቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
a ይህ ርዕስ በመንፈስ ፍሬ ውስጥ ስለተካተቱት ባሕርያት ወይም ስለ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ከሚያብራሩ ዘጠኝ ተከታታይ ርዕሶች መካከል የመጀመሪያው ነው።