የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ አንዲት ክርስቲያን ሴት ጌጣጌጥ ብታደርግ ወይም እንደ ኩልና ቅባት በመሳሰሉ ነገሮች ብትጠቀም፣ የጸጉር ቀለም ብትቀባ ወይም ተመሳሳይ ልማዶችን ብትከተል ትክክል ነውን?
በድሮ ጊዜ የነበሩ ወይም ባሁኑ ዘመን ያሉ መጽሐፍ ቅዱስን እንከታተላለን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ስለ ጌጥ በጣም ሃይለኛ የሆኑና በጣም የተለያዩ አስተያየቶች ገልጸዋል።a
ዛሬ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሴቶች ከሜክአፕና ከጌጣ ጌጥ ይርቃሉ። ለምሳሌ ያህል የአሚሽ ሕዝብ የተባለው መጽሐፍ እነዚህ ሕዝቦች “አካላዊ መልካቸውን ይጨቁኑታል፤ ምክንያቱም ስለ ዓለማዊ መልክ የሚጨነቅ አባላቸው አደጋ ላይ ወድቋል ብለው ያምናሉ። የሰውየው ትኩረት ማረፍ ያለበት በሥጋዊ ሳይሆን በመንፈሣዊ አሳቦች ላይ መሆን አለበት። አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሳሉ።”
በዚያን ጊዜ የተጠቀሰው ጥቅስ 1 ሳሙኤል 16:7 ሲሆን እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ (አዓት)] ግን ሳሙኤልን ፊቱን፣ የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ [ይሖዋ (አዓት)] አያይምና . . . ሰው ፊትን ያያል፤ [ይሖዋ (አዓት)] ግን ልብን ያያል አለው።” ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ዳዊት ወንድም ስለ ኤልያብ ቁመት ነው። በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ብንመረምር አምላክ እየተናገረ የነበረው ስለ ሰውነት አያያዝ፣ ለምሳሌ ዳዊት ወይም ወንድሞቹ ጸጉራቸውን ስለማበጠራቸው ወይም ሌላ ዓይነት ማጌጫ በልብሳቸው ላይ ስለማድረጋቸው እንዳልሆነ ግልጽ ይሆንልናል።—ዘፍጥረት 38:18፤ 2 ሳሙኤል 14:25, 26፤ ሉቃስ 15:22
ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ማጌጫ ማድረግ የለባቸውም የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ጥቅሶችን አለቦታቸው ተጠቅመው ድጋፍ ለማግኘት እንደሚሞክሩ ይህ ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸጉር አያያዝ በዝርዝር አይገልጽም። አንዱን ዓይነት ቅባት ከልክሎ ሌላውን ዐይነት የሚፈቅድ ትእዛዝ አልያዘም። መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊ የሆነ መመሪያ ይሰጣል። እነዚህን መመሪያዎች አሁን እንመልከታቸውና ዛሬ እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚቻል እንመልከት።
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷል፦ “እንዲሁ ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ . . . በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ጴጥሮስም ተመሳሳይ ሐሳብ ጽፏል፦ “ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:3, 4
“በሚገባ” እና “ይሸለሙ” ተብለው የተተረጐሙት ግሪክኛ ቃላት ኮስሞስ ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ያላቸው ናቸው። ኮስሜቲክ የሚለው ቃል የመጣው ከዚህ ቃል ሲሆን “ለውበት የሚረዳ፣ በተለይ የቆዳን ቀለም የሚያሳምር” ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ጥቅሶች ስለ ልዩ ልዩ ቅባቶች ወይም ሜክአፕ፣ ስለ ጌጣጌጥና ሴቶች ስለሚጠቀሙባቸው መልክን የሚያሳምሩ ሌሎች ነገሮች ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ይሰጡናል።
ጳውሎስና ጴጥሮስ ሴቶች ጸጉራቸውን ሽሩባ መሠራት፣ የዕንቁ ወይም የወርቅ ጌጥ ማንጠልጠል፣ ወይም መልክን ለማስዋብ በሚደረጉ ቅባቶች መጠቀም የለባቸውም ማለታቸው ነበርን? አልነበረም። የአነጋገራቸው ትርጉም ይህ ነው ካልን እንግዲያው ክርስቲያን ሴቶች ‘መጐናጸፊያ ወይም ነጠላ’ ጭምር ከመልበስ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ከሞት ያስነሳት ዶርቃ ‘ቀሚስና ልብስ’ ለሌሎች እህቶች ትሠራ ስለነበረ የተወደደች ነበረች። (ሥራ 9:39) ስለዚህ 1 ጢሞቴዎስ 2:9 እና 1 ጴጥሮስ 3:3, 4 የሚሰጡት ምክር እህቶች ሽሩባ መሠራት፣ የዕንቊ ጌጥ ማድረግ፣ ተጨማሪ ልብስ መደረብ አይችሉም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ አጥብቆ የገለጸው ሴቶች ራሳቸውን ሲይዙ ልከኝነትንና አስተዋይነትን ማሳየት እንዳለባቸው ነው። ጴጥሮስም ሴቶች የማያምኑ ባሎቻቸውን ወደራሳቸው ለመሳብ ከውጭው መልካቸውና ጌጣቸው ይልቅ ለውስጣዊ መንፈሳቸው ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳይቷል።
ባጭሩ መጽሐፍ ቅዱስ መልክን ለማሻሻል ወይም ለማሳመር የሚደረጉትን ሙከራዎች አይከለክልም። አንዳንዶቹ የአምላክ አገልጋዮች (ወንዶችም ሴቶችም) ጌጥ አድርገዋል። (ዘፍጥረት 41:42፤ ዘጸአት 32:2, 3፤ ዳንኤል 5:29) ታማኟ አስቴር በቅባትና በሽቶ እየታሸች ብዙ ጊዜ የሚፈጅ መልክን የማስዋብ ዝግጅት እንዲደረግላት ተስማምታለች። (አስቴር 2:7, 12, 15፤ ከዳንኤል 1:3-8 ጋር አወዳድር) አምላክ በምሳሌያዊ አባባል እሥራኤልን አምባር፣ የአንገት፣ የአፍንጫና የጆሮ ጌጥ አድርጎ እንዳስዋባት ተናግሯል። እነዚህ ነገሮች “እጅግ በጣም ውብ” እንድትሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል።—ሕዝቅኤል 16:11-13
ይሁን እንጂ ሕዝቅኤል ላይ ያለው መግለጫ ለውጫዊ መልክ ትኩረት መስጠት እንደሌለብን የሚገልጽ ትምህርት ይዟል። አምላክ እንዲህ አለ፦ “በውበትሽ ታምነሻል፤ ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል፤ ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ።” (ሕዝቅኤል 16:15፤ ኢሳይያስ 3:16, 19) ስለዚህ ሕዝቅኤል 16:11-15 ከዘመናት በኋላ ጳውሎስና ጴጥሮስ ለውጫዊው ውበት ትኩረት ስላለመስጠት ያቀረቡት ምክር ጥበብ ያለበት መሆኑን ያሳያል። አንዲት ሴት ራሷን በጌጣ ጌጥ ለማስዋብ ከመረጠች መጠኑና ዐይነቱ ከልከኝነት ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ከመጠን ያለፈ፣ ልታይ ባይነትን የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭ የበዛበት መሆን የለበትም።—ያዕቆብ 2:2
ነገር ግን አንዲት ክርስቲያን ሴት ሊፕስቲክ ወይም የጉንጭ ቀለም ወይም ሽፋሽፍቷ ላይ ኩል ብትቀባስ? በመሬት ቁፋሮ ታሪክን የሚያጠኑ ሰዎች በእሥራኤልና በአቅራቢያው የሜክአፕ መያዣ ዕቃዎች፣ መቀቢያዎችና መስተዋት አግኝተዋል። አዎን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በድሮ ጊዜ ሴቶች ዛሬ ካሉት ከብዙዎቹ መኳኳያዎች ጋር የሚመሳሰሉ ነገሮችን ይቀቡ ነበር። ከኢዮብ ሴት ልጆች አንዷ የነበረችው አማልቶያስ ቂራስ የስሟ ትርጉም “የኩል ማስቀመጫ” ማለት ነው።—ኢዮብ 42:13-15
በእሥራኤል አገር ሴቶች ልዩ ልዩ መኳኳያ ይጠቀሙ ነበር፤ ሆኖም ከመጠን ካለፈ አደገኛ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ኤልዛቤል የእሥራኤል ንግሥት ከሆነች ከአያሌ ዓመታት በኋላ “ዓይኗን ተኳለች፤ ራስዋንም አስጌጠች።” (2 ነገሥት 9:30) በኋላም እሥራኤል ሌሎች አገሮችን ለስነ ምግባራዊ ርኩሰት ለመሳብ ምን ታደርግ እንደነበረች አምላክ ሲገልጽ ‘በወርቅ አምባር እንዳጌጠች፣ ዓይኗን ኩል እንደተኳለችና እንዳጌጠች’ ተናግሯል። (ኤርምያስ 4:30፤ ሕዝቅኤል 23:40) መልክን ለማሳመር በአርቲፊሻል ነገሮች መጠቀሙ ስሕተት ነው በማለት ይህ ጥቅስም ሆነ ሌላ ጥቅስ አይናገርም። ሆኖም የኤልዛቤል ታሪክ እንደሚያመለክተው በዓይኖቿ ዙሪያ የተኳለችው ኩል በጣም ብዙ ስለነበረ የሁ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ ቆሞ ሊያየው ችሏል። ይህ ምን ትምህርት ይዟል? ከመጠን በላይ ኩል ወይም ሌላ ቅባት ማድረግ ጥሩ አለመሆኑን ነው።b
እርግጥ ጌጥ ወይም ሜክአፕ የምታደርግ የትኛዋም ሴት እርሷ የምትጠቀምበት ነገር ወይም መጠኑ ትክክል አይደለም ብላ አታስብም። ይሁን እንጂ ስለ ራሷ ስጋት ስለሚሰማት ወይም በበዝባዡ የንግድ ማስታወቂያ ተታልላ ከመጠን በላይ ሜክአፕ የመጠቀም ልማድ ሊኖራት እንደሚችል አያከራክርም። አዲሱ መልኳን በጣም ትለምደውና አብዛኞቹ ክርስቲያን ሴቶች ከሚያሳዩት ‘ልከኝነትና ባለ አእምሮነት’ ጋር እንደሚጋጭ ልትዘነጋው ትችላለች።—ያዕቆብ 1:23-24
የሰው ስሜት እንደሚለያይ የታወቀ ነው። አንዳንድ ሴቶች ሜክአፕ ወይም ጌጥ የሚያደርጉት በትንሹ ነው፤ ወይም ጨርሶ በዚህ አይጠቀሙም። ሌሎች ደግሞ በዛ አድርገው ይጠቀማሉ። ስለዚህ የተለየ ዓይነት ወይም መጠን ሜክአፕና ጌጥ በሚጠቀሙት ላይ መፍረድ ጥበብ አይደለም። ሌላው መታየት ያለበት የአካባቢ ባሕል ነው። አንዳንድ ስታይሎች በሌላ አገር ተቀባይነት ያላቸው መሆኑ (ወይም በጥንት ዘመን አብዛኛው ሰው ስለተጠቀመባቸው) ዛሬ ባለንበት አካባቢ ጥሩ ናቸው ማለት አይደለም።
ጥበበኛ የሆነች ክርስቲያን ሴት አለፍ አለፍ እያለች ሁኔታዋን ትገመግማለች። ራሷን ለማታለል ሳትሞክር እንዲህ ብላ ልትጠይቅ ትችላለች፦ ‘በአካባቢዬ ካሉት ከአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይልቅ እኔ ሜክአፕና ጌጣ ጌጥ አበዛለሁን? ራሴን የምይዘው መሽቀርቀር ብቻ የሚታያቸውን ሴቶች ወይም ከንቱ የሆኑት የፊልም ኮከቦችን በመከተል ነው ወይስ ዋናው መመሪያዬ በ1 ጢሞቴዎስ 2:9 እና በ1 ጴጥሮስ 3:3, 4 ላይ ያለው ምክር ነው? የራሴ አያያዝ ልከኛ ሆኖ የሌሎችን አስተያየትና ስሜት እንደማከብር የሚያሳይ ነውን?’—ምሳሌ 31:30
ክርስቲያን ባል ያላቸው ሴቶች ሐሳብና ምክር እንዲሰጧቸው ሊጠይቋቸው ይችላሉ። በተጨማሪም ቅን ፍላጎት ካለ ከሌሎች እህቶችም ጠቃሚ ምክር ማግኘት ይቻላል። ሆኖም ተመሳሳይ ስሜት ያላቸውን ሴቶች ከመጠየቅ ይልቅ በሚዛናዊነታቸውና በጥበባቸው የሚከበሩትን በዕድሜ የገፉትን መጠየቁ የተሻለ ነው። (ከ1 ነገሥት 12:6-8 ጋር አወዳድር) በዕድሜ የገፉ የተከበሩ ሴቶች ‘የአምላክ ቃል እንዳይሰደብ ቆነጃጅትን ራሳቸውን የሚገዙ፣ ንጹሖች እንዲሆኑ መምከር እንዳለባቸው’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ቲቶ 2:2-5) ከቅጥ በላይ በሆነው የሰውነቷ ሁኔታና ጌጧ ምክንያት የአምላክ ቃል ወይም ሕዝብ እንዲሰደብ የምትፈልግ ጐልማሳ ክርስቲያን አትኖርም።
ስለ ትዕማር የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አንዲት ሴት የራሷ አያያዝ ከሆኑ ዓይነት ሴቶች ጋር ሊያስመድባት፣ ኃይለኛ መልእክት ሊያስተላልፍባት እንደሚችል ያሳያል። (ዘፍጥረት 38:14, 15) የአንዲት ክርስቲያን የጸጉር አያያዝ ወይም የጸጉር ቀለም ወይም የጌጣ ጌጥና የሜክአፕ አጠቃቀሟ ምን መልዕክት ያስተላልፋል? ይህች የምታዩዋት ሴት ንጹሕ፣ ልከኛና ሚዛናዊት የሆነች የአምላክ አገልጋይ ናት የሚል ነውን?
ክርስቲያኖች በመስክ አገልግሎት ላይ ተሠማርተው የሚመለከት ወይም ወደ ስብሰባችን የሚመጣ ሰው በሚያያቸው ነገሮች ጥሩ ግምት እንዲያድርበት ማድረግ አለብን። አብዛኛውን ጊዜ እኛን የሚመለከቱ ሰዎች ጥሩ አስተያየት ይቀረጽባቸዋል። አብዛኞቹ ክርስቲያን ሴቶች አንድ የውጭ ሰው በአንድ በኩል ለማየት ደስ የማይል የድሮ ፋሽን ለብሰው የሚመጡ ናቸው ወይም በሜክአፕ መልካቸውን የለወጡ ወይም ከመጠን በላይ ራሳቸውን የሚያስጌጡ ናቸው ብሎ እንዲደመድም አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ የሰውነታቸው አያያዝ ‘ለአምላክ የጠለቀ አክብሮት አለን ለሚሉ ሴቶች የሚስማማ’ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ተርቱልያን “ቆዳቸውን በመድኃኒት የሚያሹ፣ ጉንጫቸውን ቀይ ቀለም የሚቀቡ፣ ዐይናቸውን ኩል የሚቀቡ ሴቶች በአምላክ ላይ ኃጢአት ይሠራሉ” ብሎ ይናገር ነበር። ጸጉራቸውን ቀለም የሚቀቡትንም ይነቅፋቸው ነበር። ተርቱልያን በማቴዎስ 5:36 ላይ ያሉትን የኢየሱስ ቃላት አለ ቦታቸው በመጠቀም “የጌታን ቃል ይሽራሉ፤ እስቲ ተመልከቱት፤ ጸጉራችን ጥቁር ወይም ነጭ መሆን ሲገባው ቢጫ ቀለም ቢቀባ ትክክል ነውን?” ሐሳቡን በመጨመር “እንዲያውም ባይገርማችሁ በዕድሜ የገፉ በመሆናቸው የሚያፍሩ ሰዎች ታገኛላችሁ፤ ስለዚህ ሽበታቸውን ጥቁር ቀለም በመቀባት ይሸፍኑታል” ብሏል። ይህ የተርቱልያን የግል አስተያየት ነበር። ይሁን እንጂ ነገሮችን አጣሞ ይመለከት ነበር። ለዚህ ሁሉ ክርክሩ መሠረት ያደረገው ሰውን ለኩነኔ ያበቃችው ሴት ስለሆነች አሁን ሴቶች “ልክ እንደ ሔዋን ሆነው መሄድ፣ ስለ መጀመሪያው ኃጢአት ማዘንና መጸጸት አለባቸው” የሚለው አመለካከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ ብሎ አይናገርም። ለሰው ዘር ኃጢአተኝነት አምላክ ተጠያቂ ያደረገው አዳምን ነው።—ሮሜ 5:12-14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14
b በጣም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ የዜና ማሰራጫ አንድ የቴሌቪዥን ሰባኪ የፈጸመውን መጥፎ ድርጊት አጋልጧል። በፊልም ተዋናይነት ሙያዋ ምስጉን የሆነችው ሚስቱም የእርሱን ያህል ትኩረት ስባ ነበር። በዜናው ዘገባ መሠረት “ሜክአፕና ፊልም” ኃጢአት ናቸው ተብላ ከልጅነቷ ተምራ ነበር። ሆኖም በኋላ አሳቧን ለወጠችና ኩልና ሊፕስቲክ በወፍራሙ ትቀባ ስለነበር ሐውልት ትመስል ነበር።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከመካከለኛ ምሥራቅ በመሬት ቁፋሮ የተገኙ፦ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ የመኳኳያ ማስቀመጫ፣ መስተዋት፣ የወርቅ ሐብል
[ምንጭ]
All three: Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.