አብርሃም እና ሣራ—እምነታቸውን መኮረጅ ትችላለህ!
አብርሃም “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” ተብሎ ተጠርቷል። (ሮሜ 4:11 የ1954 ትርጉም) ሚስቱ ሣራም ብትሆን እምነት ነበራት። (ዕብራውያን 11:11 የ1954 ትርጉም) ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው እነዚህ ባልና ሚስት ግሩም የእምነት ምሳሌ ነበሩ የምንለው ለምንድን ነው? ምን ዓይነት መከራዎችን በጽናት ተቋቁመዋል? የእነርሱን ታሪክ መመርመራችንስ ለእኛ ምን ጥቅም አለው?
አምላክ ቤቱን ለቅቆ እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ አብርሃም እምነት አሳይቷል። ይሖዋ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 12:1) ታማኙ አብርሃም የታዘዘውን ፈጽሟል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ እሺ ብሎ ሄደ” ይላል። (ዕብራውያን 11:8) ይህ ጉዞ ምን ይጠይቅበት እንደነበር እስቲ እንመልከት።
አብርሃም ይኖር የነበረው አሁን በኢራቅ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው በዑር ነበር። ዑር በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ምናልባትም በኢንደስ ሸለቆ ከሚገኙ አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ የምታደርግ የበለጸገች የመስጴጦምያ ማዕከል ነበረች። በዑር የተካሄደውን የመሬት ቁፋሮ የመሩት ሰር ሊዮናርድ ዉሊ፣ በአብርሃም ዘመን አብዛኞቹ ቤቶች ከጡብ የተገነቡና የተለሰኑ እንዲሁም በኖራ የተቀቡ እንደሆኑ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል የአንድ ሃብታም የዑር ነዋሪ መኖሪያ ባለ አንድ ፎቅ ሕንጻ ሲሆን ግቢው በድንጋይ የተነጠፈ ነበር። ከታች ባሉት ክፍሎች ውስጥ የቤት ሠራተኞችና እንግዶች ይኖሩበት ነበር። በፎቁ ላይ ወደሚገኙት የቤተሰቡ መኖሪያ ክፍሎች የሚያስገባ የእንጨት በረንዳ በቤቱ ዙሪያ አለ። ከ10 እስከ 20 የሚደርሱ ክፍሎች ያላቸው እነዚህ ቤቶች “ሰፋ ያሉ ሲሆኑ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ተስማሚና ምቹ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ የኑሮ ሁኔታ አንጻር ደግሞ ከቅንጦት የሚመደቡ” እንደሆኑ ዉሊ ይናገራሉ። ቤቶቹ “በአብዛኛው የሰለጠኑ ሰዎች መኖሪያ የነበሩ ሲሆን አንድ የከተማ ሰው የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ አሟልተው የያዙ ነበሩ።” አብርሃምና ሣራ በድንኳን ለመኖር ትተው የሄዱት እንዲህ ዓይነቱን ቤት ከሆነ በእርግጥም ይሖዋን ለመታዘዝ ሲሉ ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል ለማለት ይቻላል።
አብርሃም ቤተሰቡን ይዞ መጀመሪያ የተጓዘው አሁን በሰሜናዊ ሶርያ ወደምትገኘው ወደ ካራን ሲሆን ከዚያም ወደ ከነዓን አቀና። ከ1,600 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው ይህ ጉዞ በዕድሜ ለገፉት ባልና ሚስት በጣም ከባድ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ከካራን ሲነሱ አብርሃም 75 ዓመቱ ሚስቱ ደግሞ 65 ዓመቷ ነበር።—ዘፍጥረት 12:4
አብርሃም ዑርን ለቅቀው ሊሄዱ እንደሆነ ሲነግራት ሣራ ምን ተሰምቷት ይሆን? ምቹ የሆነውን ቤቷን ትታ ከዚህ በፊት ወደማታውቀውና ለተለያዩ አደጋዎች ሊያጋልጥ ወደሚችል አካባቢ መዛወሩ እንዲሁም ከበፊቱ ዝቅ ባለ የአኗኗር ደረጃ መኖሩ አሳስቧት ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ ሣራ አብርሃምን እንደ ‘ጌታዋ’ አድርጋ ትመለከተው ስለነበር ሐሳቡን ተቀብላዋለች። (1 ጴጥሮስ 3:5, 6) አንዳንድ ምሑራን ሣራ እንዲህ ብላ መጥራቷ “[ለአብርሃም] የነበራትን የተለመደ የአክብሮት መንፈስ ወይም ባሕርይ” እንዲሁም “በአስተሳሰብም ሆነ በስሜት የሚንጸባረቅን እውነተኛ ልማድ” የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ከሁሉም በላይ ግን ሣራ በይሖዋ ላይ እምነት ነበራት። ታዛዥነቷና እምነቷ ለክርስቲያን ሚስቶች ግሩም ምሳሌ ነው።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በሌሎች አገሮች ምሥራቹን ለመስበክ የትውልድ አገራቸውን ጥለው የሚሄዱ ቢሆንም እኛ ግን ለአምላክ የምንታዘዝ መሆናችንን ለማሳየት ቤታችንን ለቅቀን እንድንሄድ አልተጠየቅንም። አምላክን የምናገለግለው የትም ይሁን የት በሕይወታችን ውስጥ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመጀመሪያው ሥፍራ እስካደረግን ድረስ በሚያስፈልገን ሁሉ ይንከባከበናል።—ማቴዎስ 6:25-33
አብርሃምም ሆነ ሣራ ባደረጉት ውሳኔ አልተጸጸቱም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ትተውት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው” በማለት ተናግሯል። ቢሆንም አልተመለሱም። ይሖዋ ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ እንደሚሰጥ’ እርግጠኞች ስለነበሩ በገባላቸው ቃል ላይ እምነት አሳድረዋል። እኛም ይሖዋን በሙሉ ልባችን እያገለገልን ለመቀጠል ከፈለግን በገባልን ቃል ላይ እምነት ማሳደር ይኖርብናል።—ዕብራውያን 11:6, 15, 16
መንፈሳዊና ቁሳዊ ብልጽግና
አብርሃም ከነዓን ከደረሰ በኋላ አምላክ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣታለሁ” አለው። አብርሃም ምሥጋናውን ለመግለጽ መሠዊያ የሠራ ሲሆን “የይሖዋን ስም ጠራ።” (ዘፍጥረት 12:7, 8 NW) ይሖዋ አብርሃምን ያበለጸገው ከመሆኑም በላይ ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎችም በጣም እየበዙ ሄዱ። በአንድ ወቅት 318 የሚያህሉ የሰለጠኑ ወንዶችን በቤቱ ከተወለዱት ባሪያዎች መካከል ማሰባሰብ ችሎ ስለነበር “አብረውት የነበሩት ሰዎች በአጠቃላይ ከአንድ ሺህ ሳይበልጡ እንደማይቀር” ተገምቷል። በዚህም ሆነ በዚያ ሰዎች “ከእግዚአብሔር [እንደተላከ] አለቃ” አድርገው ይቆጥሩት ነበር።—ዘፍጥረት 13:2፤ 14:14፤ 23:6 የ1954 ትርጉም
አብርሃም በአምልኮ ግንባር ቀደም የነበረ ሲሆን ቤተሰቡን “ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ” ያስተምራቸው ነበር። (ዘፍጥረት 18:19) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶችም የአብርሃምን ምሳሌ በመመልከት ሊበረታቱ ይችላሉ። አብርሃም የቤተሰቡ አባላት በይሖዋ እንዲታመኑና በትክክለኛው ጎዳና እንዲሄዱ በማስተማር ረገድ ስኬታማ ነበር። ከዚህ አኳያ የሣራ አገልጋይ የነበረችው ግብጻዊቷ አጋር፣ የአብርሃም ልጅ ይስሐቅና በዕድሜ ትልቅ የነበረው የአብርሃም አገልጋይ በይሖዋ መታመናቸው ብዙም የሚያስገርም አይደለም።—ዘፍጥረት 16:5, 13፤ 24:10-14፤ 25:21
አብርሃም ሰላም ፈጣሪ ነበር
በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የተከሰቱት ገጠመኞች አንድ አምላካዊ ባሕርይ እንደነበረው ይጠቁማሉ። አብርሃም በእርሱ እረኞችና በወንድሙ ልጅ በሎጥ እረኞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ ወደተለያየ አቅጣጫ እንዲሄዱ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን በዕድሜ ከእርሱ ያንስ የነበረው ሎጥ የፈለገውን መሬት እንዲመርጥ ፈቅዶለታል። አዎን፣ አብርሃም ሰላም ፈጣሪ ነበር።—ዘፍጥረት 13:5-13
መብቴ ነው ብለን አንድን ነገር የሙጥኝ ከማለትና ሰላምን ለማውረድ መሥዋዕትነት ከመክፈል አንዱን ለመምረጥ በምንገደድበት ጊዜ አብርሃም ለሎጥ ቅድሚያ በመስጠቱ እንዲጎዳ ይሖዋ እንዳልፈቀደ ልናስታውስ እንችላለን። እንዲያውም አብርሃም በዙሪያው ዓይኑ እስከፈቀደለት ድረስ ሊያየው የቻለውን ምድር በሙሉ ለእርሱና ለዘሩ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል። (ዘፍጥረት 13:14-17) ኢየሱስ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:9
የአብርሃም ወራሽ የሚሆነው ማን ነው?
አብርሃምና ሣራ ዘር እንደሚያገኙ ቃል ቢገባላቸውም ሣራ መካን ነበረች። አብርሃም ጉዳዩን በጸሎት ለአምላክ ነገረው። ንብረቱን በሙሉ የሚወርሰው አገልጋዩ ኤሊዔዘር እንደሆነ ጠየቀ። ይሖዋም “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል” በማለት ወራሹ እርሱ እንዳልሆነ ነገረው።—ዘፍጥረት 15:1-4
ቢሆንም አብርሃምና ሣራ ልጅ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ 75 ዓመት የሆናት ሣራ ልጅ ለመጸነስ የነበራት ተስፋ ተሟጥጦ ነበር። በመሆኑም አብርሃምን “እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ አድርጎኛል። ምናልባት በእርሷ በኩል ልጆች አገኝ እንደሆን ሄደህ ከአገልጋዬ ጋር ተኛ” አለችው። አብርሃም አጋርን ሁለተኛ ሚስቱ አድርጎ ወሰዳትና ከእርሷ ጋር ተኛ፤ እርሷም ጸነሰች። አጋር መጸነሷን እንዳወቀች እመቤቷን መናቅ ጀመረች። በዚህ የተማረረችው ሣራ አቤቱታዋን ለአብርሃም ያሰማች ሲሆን አጋርንም ታሰቃያት ጀመር። በመጨረሻም አጋር ተነስታ ኮበለለች።—ዘፍጥረት 16:1-6
ሣራ አጋርን ለአብርሃም የሰጠችውም ሆነ አብርሃም አጋርን በሚስትነት የወሰደው በወቅቱ ይደረግ በነበረው ልማድ መሠረት ሲሆን በቅንነት ያደረጉት ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለአብርሃም ዘር ለመስጠት ያሰበው በዚህ መንገድ አልነበረም። በባሕላችን በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ሥር አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ምንም ስህተት የለውም ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል ይሖዋ ይስማማበታል ማለት አይደለም። ስለ ሁኔታው ያለው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ልንወስደው የሚገባንን እርምጃ እንዲጠቁመን ወደ አምላክ በመጸለይ የእርሱን አመራር መሻት ይኖርብናል።—መዝሙር 25:4, 5፤ 143:8, 10
“ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር” የለም
ከጊዜ በኋላ አጋር እስማኤል የተባለ ልጅ ለአብርሃም ወለደችለት። ቢሆንም እስማኤል ተስፋ የተሰጠበት ዘር አልነበረም። ሣራ ዕድሜዋ የገፋ ቢሆንም ይህ ወራሽ ከእርሷ የተወለደ መሆን ነበረበት።—ዘፍጥረት 17:15, 16
አምላክ ሣራ ወንድ ልጅ እንደምትወልድለት ለአብርሃም ሲነግረው “አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ ‘እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?’ አለ።” (ዘፍጥረት 17:17) በሌላ ጊዜም አንድ መልአክ ለአብርሃም ይህንን መልእክት ሲነግረው ሣራ በሰማች ጊዜ ‘በልቧ ሳቀች።’ ቢሆንም ለይሖዋ “የሚሳነው ነገር” የለም። እኛም የፈለገውን ሊያደርግ እንደሚችል እምነት ልንጥልበት እንችላለን።—ዘፍጥረት 18:12-14
ሣራ ‘ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፣ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን ያገኘችው በእምነት’ ነበር። (ዕብራውያን 11:11 የ1954 ትርጉም) ከጊዜ በኋላ ሣራ ይስሐቅን የወለደች ሲሆን የስሙ ትርጓሜ “ሳቅ” ማለት ነው።
አምላክ በገባው ተስፋ ላይ ሙሉ እምነት ማሳደር
ይሖዋ ለረዥም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ወራሽ ይስሐቅ መሆኑን ገልጾ ነበር። (ዘፍጥረት 21:12) በመሆኑም አብርሃም፣ አምላክ ልጁን እንዲሠዋለት ሲጠይቀው በጣም ተገርሞ መሆን አለበት። ቢሆንም በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲተማመን የሚያደርግ ምክንያት ነበረው። ይሖዋ ይስሐቅን ከሞት ለማስነሳት አይችልም ነበር? (ዕብራውያን 11:17-19) መጀመሪያውኑም ቢሆን አምላክ ይስሐቅ እንዲወለድ ለማድረግ የአብርሃምንና የሣራን የመራባት ችሎታ በተአምራዊ መንገድ በማደስ ይህን ችሎታውን አሳይቶ የለም? አምላክ ቃሉን የመፈጸም ችሎታ እንዳለው ስለሚያውቅ አብርሃም የታዘዘውን ለመፈጸም ዝግጁ ነበር። እርግጥ በኋላ ላይ ልጁን እንዳይሠዋው መልአክ ከልክሎታል። (ዘፍጥረት 22:1-14) የሆነ ሆኖ አብርሃም በዚህ ታሪክ ውስጥ የተጫወተው ሚና ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን መስጠት’ ለይሖዋ አምላክ ምን ያህል ከባድ እንደነበር እንድንገነዘብ ይረዳናል።—ዮሐንስ 3:16፤ ማቴዎስ 20:28
አብርሃም በአምላክ ላይ እምነት ስለነበረው ይሖዋ የገባውን ተስፋ የሚወርሰው ልጁ ከከነዓን ምድር የሐሰት አምልኮን የምትከተል ሴት ማግባት እንደማይችል ያውቅ ነበር። ፈሪሃ አምላክ ያለው ወላጅ ይሖዋን ለማያገለግል ሰው እንዴት ልጁን ሊድር ይችላል? በመሆኑም አብርሃም 800 ኪሎ ሜትር ርቀው በመስጴጦምያ ከሚኖሩት ዘመዶቹ ለይስሐቅ የምትሆን ተስማሚ ሚስት ለመፈለግ ዝግጅት አደረገ። አምላክም የይስሐቅ ሚስትና የመሲሑ ቅድመ አያት እንድትሆን የመረጣት ሴት ርብቃ እንደሆነች በመጠቆም ይህን ጥረቱን ባርኮለታል። አዎን፣ ይሖዋ ‘አብርሃምን በሁሉ ነገር ባርኮታል።’—ዘፍጥረት 24:1-67፤ ማቴዎስ 1:1, 2
ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን በረከት
አብርሃምና ሣራ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋምና አምላክ በገባላቸው ቃል ላይ እምነት በማሳደር ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። ይሖዋ ለአብርሃም “ቃሌን ስለሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” ብሎት ስለነበር የገባላቸው ቃል ከሰው ዘር ዘላለማዊ ተስፋ ጋር ግንኙነት አለው።—ዘፍጥረት 22:18
እርግጥ ነው፣ አብርሃምና ሣራ እንደ እኛው ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ አንድን ጉዳይ በሚመለከት የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ሲገነዘቡ የቱንም ያህል መሥዋዕትነት ቢጠይቅባቸው ያለማመንታት ይታዘዙ ነበር። በዚህም ምክንያት አብርሃም “የእግዚአብሔር ወዳጅ” የሚል ስም ያተረፈ ሲሆን ሣራም ‘ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ የጣለች ቅዱስ ሴት’ ተብላለች። (ያዕቆብ 2:23፤ 1 ጴጥሮስ 3:5) እኛም የአብርሃምንና የሣራን እምነት ለመኮረጅ በመጣር ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንችላለን። ይሖዋ ለአብርሃም ከገባለት ውድ ተስፋም ጥቅም ማግኘት እንችላለን።—ዘፍጥረት 17:7
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃምና ሣራ እምነት ስለነበራቸው ይሖዋ በስተርጅናቸው ልጅ በመስጠት ባርኳቸዋል
[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአብርሃም ምሳሌ ይሖዋ አንድያ ልጁ እንዲሞት መፍቀዱ ምን ያህል ከባድ እንደነበር እንድንገነዘብ ይረዳናል