‘ሰላምን ፈልገው፤ ተከተለውም’
“የባሪያውን ሰላም የሚወድድ [ይሖዋ (አዓት)] ታላቅ ይሁን።”—መዝሙር 35:27
1. በአሁኑ ጊዜ ምን ሰላም አግኝተናል?
በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በሰላም መኖር እንዴት የሚያስደስት ነው! “የሰላም አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ማምለክ እና “በሰላም ቃል ኪዳኑ“ በረከቶች ተካፋይ መሆን እንዴት ደስ ይላል! በሕይወት ጭንቀቶች መሃከል “አእምሮን ሁሉ የሚያልፈውን የአምላክን ሰላም” ማወቅና ምንም ዓይነት ዜግነት፣ ቋንቋ፣ ዘር ወይም ማኅበራዊ አቋም (ደረጃ) ቢኖራቸውም የአምላክን ሕዝቦች የሚያስተባብራቸውን “የሰላም ማሠሪያ” መቅመስ እንዴት የሚያጽናና ነው!—1 ተሰሎንቄ 5:23፤ ሕዝቅኤል 37:26፤ ፊልጵስዩስ 4:7፤ ኤፌሶን 4:3
2, 3. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች በጥቅሱ የሚጸኑ ሲሆን ግለሰብ ክርስቲያኖች ግን ምን ሊሆኑ ይችላሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንድናደርግ ይመክረናል?
2 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይህን ሰላም ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ይሁን እንጂ እንዲሁ ያለ ምንም ጥረት እንደሚገኝ አድርገን መገመት አንችልም። ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ስለተባበርን ወይም የክርስቲያን ቤተሰብ አባል ስለሆንን ብቻ ሰላም እንዲሁ አይገኝም። ቅቡዓን ቀሪዎችና የ“ሌሎች በጐች” ክፍል የሆኑ ባልንጀሮቻቸው እንደ አንድ መንጋ እስከ ፍጻሜው ይጸናሉ፤ ግለሰቦች ግን ሰላማቸውን ሊያጡና ሊወድቁ ይችላሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 24:13፤ ሮሜ 11:22፤ 1 ቆሮንቶስ 10:12
3 ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ወንድሞች ሆይ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ዕብራውያን 3:12) ይህ ማስጠንቀቂያ እጅግ ብዙ ሰዎች ለተባሉትም ጭምር ይሠራል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት ይመክራቸዋል፦ “ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ [የይሖዋ (አዓት)] ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል።[የይሖዋ (አዓት)] ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:10-12፤ መዝሙር 34:14, 15
“ስለ ሥጋ ማሰብ”
4. ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ምን ሊያናጋው ይችላል?
4 ሰላምን መከተላችንን ምን ሊያደናቅፍብን ይችላል? ጳውሎስ እንደሚከተለው ባለ ጊዜ አንዱን ነገር ይጠቅሳል፦ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና።” (ሮሜ 8:6, 7) ጳውሎስ “ሥጋ” ሲል ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት ከተወረሱ የኃጢአት ዝንባሌዎቻችን ጋር ውድቅ የሆነ ሁኔታችንን ማመልከቱ ነው። ለውዳቂው ሥጋችን ዝንባሌዎች እጅ መስጠት ሰላማችንን ያጠፋል። አንድ ክርስቲያን ንስሐ ባለመግባት ብልግና የሚፈጽም፣ የሚዋሽ፣ የሚሰርቅ፣ ዕፅ የሚወስድ ወይም በሌላ መንገድ መለኮታዊውን ሕግ የሚጥስ ከሆነ በአንድ ወቅት ከይሖዋ ጋር አግኝቶት የነበረውን ሰላም ያደፈርሳል። (ምሳሌ 15:8, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8) ከዚህም ሌላ ሥጋዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ቦታ የሚሰጣቸው ከሆነ ከአምላክ ጋር ያለው ሰላም በአስጊ ሁኔታ ላይ ይወድቃል።—ማቴዎስ 6:24፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
5. ሰላምን መከተል ምን ማድረግ ማለት ነው?
5 በሌላው በኩል ጳውሎስ “ስለ መንፈስ ማሰብ ሕይወትና ሰላም ነው” ብሏል። ሰላም ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው። ስለዚህ ልባችን መንፈሳዊ ነገሮችን እንዲያደንቅ ካሰለጠነውና በዚህ ረገድ የአምላክ መንፈስ እንዲረዳን ከጸለይን “ስለ ሥጋ ማሰብን” እናስወግዳለን። (ገላትያ 5:22-24) በ1 ጴጥሮስ 3:10-12 ላይ ሰላም ከጽድቅ ጋር ተያይዟል። (ሮሜ 5:1) ጴጥሮስ ሰላምን መከተል ‘ከክፉ መራቅንና መልካም ማድረግን’ እንደሚያጠቃልል ይናገራል። የአምላክ መንፈስ “ጽድቅን በመከተል” ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም እንድንጠብቅ ሊረዳን ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:11, 12
6. የጉባኤውን ሰላም በሚመለከት ከሽማግሌዎች ኃላፊነቶች አንዱ ምንድን ነው?
6 ሰላምን የመከተሉ ጉዳይ በጉባኤ ውስጥ ላሉት ሽማግሌዎች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሌሎችን የሚበክሉ አድራጎቶችን ለማስገባት በሚሞክርበት ጊዜ ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ለመገሰጽ በመሞከር ጉባኤውን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። ኃጢአተኛውም ተግሳጹን ከተቀበለ ሰላሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላል። (ዕብራውያን 12:11) ካልተቀበለ ግን ጉባኤው ከይሖዋ ጋር ያለውን ሰላማዊ ዝምድና እንዲጠብቅ መወገድ ያስፈልገው ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 5:1-5
ከወንድሞቻችን ጋር የሚኖረን ሰላም
7. ጳውሎስ ‘ስለ ሥጋ የማሰብ’ መግለጫ ስለሆነ ስለ ምን ነገር ነው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ያስጠነቀቀው?
7 ‘ስለ ሥጋ ማሰብ’ ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያለንን መልካም ዝምድናም ያጠፋብናል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:3) ቅንዓትና ጠብ የሰላም ተቃራኒ ናቸው።
8. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ቅንዓትና ጥል የሚያነሣሣ ሰው ምን ይሆናል? (ለ) ከአምላክ ጋር ያለን ሰላም በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
8 ቅንዓትና ጠብ በማነሣሣት የጉባኤውን ሰላም መረበሽ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። የመንፈስ ፍሬ ከሆነው ሰላም ጋር ስለሚዛመድ ነገር ሲናገር ዮሐንስ “ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው። ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወድድ እንዴት ይችላል?” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ዮሐንስ 4:20) በተመሳሳይ መንገድ አንድ ግለሰብ በወንድሞች መካከል ቅንኣትና ጥል የሚያነሣሣ ከሆነ ከአምላክ ጋር ሰላም ሊኖረው ይችላልን? በእርግጥ ሊኖረው አይችልም። “ፍጹማን [የተስተካከላችሁ (አዓት)] ሁኑ፤ ምክሬን ስሙ፤ በአንድ ልብ ሁኑ፤ በሰላም ኑሩ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” በማለት ተመክረናል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) አዎ፣ እርስ በርሳችን በሰላም በመኖር ከቀጠልን የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል።
9. ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ አለመግባባትና አለመስማማት እንደሚኖራቸው እንዴት እናውቃለን?
9 ይህ ማለት ግን በክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ፈጽሞ ሊኖር አይችልም ማለት አይደለም። ከበዓለ ሐምሳ ቀጥሎ በነበሩት ሳምንታት ገና ለጋ በነበረችው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በየዕለቱ ይደረግ ስለነበረው የምግብ እደላ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። (ሥራ 6:1) በአንድ ወቅት በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተነሣው አለመግባባት ወደ “መከፋፈል” አምርቷል። (ሥራ 15:39) ጳውሎስም ያለጥርጥር መልካምና ቀናተኛ እህቶች የነበሩትን ሴንጢኬንና ኤዎዲያንን መምከር አስፈልጎታል። (ፊልጵስዩስ 4:2) እንግድያውስ ኢየሱስ በክርስቲያኖች መካከል የሚነሳውን የሰላም መረበሽ ስለ መፍታት ዝርዝር ምክር መስጠቱና እንዲህ ዓይነቶች ችግሮች ወዲያውኑ መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚገባቸው ማጉላቱ አያስደንቅም። (ማቴዎስ 5:23-25፤ 18:15-17) በተከታዮቹ መካከል ችግሮች እንደሚነሱ ባይጠብቅ ኖሮ ይህን ምክር አይሰጥም ነበር።
10. አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ እንዴት ያሉ ሁኔታዎች ይነሳሉ? ይህስ ነገሩ በሚመለከታቸው ሁሉ ላይ ምን ኃላፊነት ያስከትላል?
10 እንግዲያውስ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው በክርስቲያን ጓደኛው በሚሰነዘር የሚያስቀይም ቃል ወይም ችላ የተባለ ከመሰለው ሊጐዳ ይችላል። የአንዱ ሰው ልዩ ባሕርይ ሌላውን በጣም የሚያናድድ ሊሆን ይችላል። ባሕርያት ሊጋጩ ይችላሉ። አንድ ሰው ሽማግሌዎች የሚያደርጉትን ውሳኔ በጣም ይቃወም ይሆናል። በሽማግሌዎች አካል መካከል ራሱ አንዱ ሽማግሌ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ባይ ይሆንና ሌሎቹን ሽማግሌዎች ችላ የሚል ሊሆን ይችላል። ይህን የመሰሉ ነገሮች ሊፈጸሙ ቢችሉም ሰላምን መሻትና መከተል አለብን። ትግል የሚጠይቀው ጉዳይ “የሰላምን አንድ አድራጊ ማሰሪያ” ለመጠበቅ ሲባል እነዚህን ችግሮች ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ መያዙ ነው።—ኤፌሶን 4:3
11. እርስ በርሳችን ሰላምን እንድንከተል ለመርዳት ይሖዋ ምን ዝግጅቶች ሰጥቶናል?
11 መጽሐፍ ቅዱስ “የባሪያውን ሰላም የሚወድድ [ይሖዋ (አዓት)] ታላቅ ይሁን” ይላል። (መዝሙር 35:27) አዎ፣ ይሖዋ ሰላም እንዲኖረን ይፈልጋል። በመሆኑም በመካከላችንና ከእርሱ ጋር ሰላምን ለመጠበቅ እንዲረዱን ሁለት የላቁ ዝግጅቶችን አድርጓል። አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው። እንደ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ በጐነትና ራስን መግዛት የመሳሰሉ ተዛማጅ እርቅ አውራጅ ባሕርያት የዚህ መንፈስ ፍሬ ናቸው። (ገላትያ 5:22, 23) ሌላው መለኰታዊ ጥበብ ነው። ስለ እርሱ እንዲህ እናነባለን፦ “ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና በጐ ፍሬ የሞላባት ናት።”—ያዕቆብ 3:17, 18
12. ከወንድሞቻችን ጋር የነበረን ሰላም ከተናጋብን ምን ማድረግ አለብን?
12 ስለዚህ ከሌሎች ጋር ያለን ሰላም ሲረበሽ ምን ማድረግ እንዳለብን ያመለክተን ዘንድ ይሖዋ የላይኛውን ጥበብ እንዲሰጠን መጸለይ አለብን። እንዲሁም ትክክል የሆነውን ለማድረግ እንዲያበረታን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን መለመን አለብን። (ሉቃስ 11:13፤ ያዕቆብ 1:5፤ 1 ዮሐንስ 3:22) ከጸሎታችን ጋር በመስማማት ለመመሪያነት የመለኮታዊ ጥበብ ምንጭ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርና ቅዱስ ጽሑፎቹን እንዴት በሥራ እንደምናውላቸው ምክር ለማግኘት የምናገኛቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን መመልከት እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በተጨማሪም ከጉባኤ ሽማግሌዎች ምክር ልንሻ እንችላለን። የመጨረሻው እርምጃ የተገኘውን መመሪያ መከተሉ ይሆናል። ኢሳይያስ 54:13 “ልጆችሽም ሁሉ [ከይሖዋ (አዓት)] የተማሩ ይሆናሉ። የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ይላል። ይህ የሚያመለክተው ሰላማችን ይሖዋ የሚያስተምረንን በተግባር ላይ በማዋላችን የተመካ መሆኑን ነው።
“ሰላማውያን ደስተኞች ናቸው”
13, 14. (ሀ) “ሰላማዊ” የሚለው የኢየሱስ አነጋገር ምን ያመለክታል? (ለ) ሰላምን የምንፈጥር ለመሆን የምንችለው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ሰላማውያን ብፁአን [ደስተኞች ]ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” ብሎአል። (ማቴዎስ 5:9) እዚህ ላይ “ሰላማውያን” የሚለው ቃል እንዲሁ በተፈጥሮ ረጋ ያለ ሰውን ብቻ አያመለክትም። የመጀመሪያው የግሪክኛ ቃል “ሰላምን የሚፈጥር” ማለት ነው። ሰላም በሚበጠበጥበት ጊዜ ለመመለስ ችሎታ ያለው ነው። ከሁሉ በላይ ግን ሰላምን የሚፈጥር ሰው በመጀመሪያ ደረጃ ሰላምን ከመበጥበጥ ለመራቅ ይጥራል። ‘ሰላም በልቡ ይገዛል።’ (ቆላስይስ 3:15) የአምላክ አገልጋዮች ሰላምን የሚፈጥሩ ለመሆን ከጣሩ በመካከላቸው የሚነሱት ችግሮች በጣም ይቀንሳሉ።
14 ሰላማዊ መሆን ድካማችንን መገንዘብንም ያጠቃልላል። ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን ግልፍተኛ ወይም በቀላሉ የሚቀየም ሊሆን ይችላል። ጭንቀት ሲያድርበት ስሜቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያስረሳው ይሆናል። ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ይህ የማይጠበቅ አይደለም። (ሮሜ 7:21-23) ይሁን እንጂ ጠላትነት፣ ጥልና ቁጣ የሥጋ ሥራ ተብለው ተገልጸዋል። (ገላትያ 5:19-21) እንዲህ ዓይነት ዝንባሌዎችን በራሳችን ላይ ከተመለከትን ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች እነዚህ ዝንባሌዎች እንዳሉብን ከጠቀሱልን ራስን መግዛትንና የዋህነትን በውስጣችን እንድናሳድግ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን ከልብና ያለማቋረጥ መጸለይ አለብን። እነዚህ የአዲሱ ሰውነት (ባሕርይ) ክፍሎች ስለሆኑ ማንኛውም ሰው እነዚህን ጠባዮች ለመኰትኰት መጣር አለበት።—ኤፌሶን 4:23, 24፤ ቆላስይስ 3:10, 15
15. የላይኛይቱ ጥበብ ያለምክንያት በአንድ ሐሳብ ድርቅ ማለትን የሚቃረነው እንዴት ነው?
15 አንዳንድ ጊዜ ጉባኤው ወይም የሽማግሌዎች አካል በአንድ ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ይሁን በሚል ግትር ሰው ይበጠበጣል። እርግጥ፤ ነገሩ መለኮታዊ ሕግን የሚመለከት ከሆነ በሐሳባችን መጽናት፣ እንዲያውም ከአቋማችን ፈጽሞ ፈቀቅ የማንል መሆን አለብን። ሌሎችን የሚጠቅም ጥሩ ሐሳብ ያለን ሆኖ ከተሰማን ምክንያታችንን መግለጽ እስከቻልን ድረስ ሐሳባችንን ለሌሎች ማሳወቁ ምንም ስህተት የለበትም። ይሁን እንጂ “እርቅን የማይሰሙ” እንደተባለላቸው ዓለማውያን መሆን የለብንም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) ላይኛይቱ ጥበብ ታራቂና ገር ናት። ስለዚህ በአድራጐታቸው ሁሉ መንቻካ ድርቅናን ልማድ ያደረጉ ሰዎች ጳውሎስ “በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ” በማለት የሰጠውን ምክር ልብ ማለት አለባቸው።—ፊልጵስዩስ 2:3
16. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መጽሐፍ ላይ የሰጠው ምክር ከንቱ ውዳሴን ለማሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 በዚያው ደብዳቤ ላይ ‘ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ በትሕትና እንድንቆጥር ጳውሎስ መክሮናል። ይህም የከንቱ ውዳሴ ተቃራኒ ነው። አንድ የጐለመሰ ክርስቲያን በቅድሚያ የራሱን ሐሳብ እንዲቀበሉት ሌሎችን አይጫንም። ራሱን ከእፍረት ስለማዳን ወይም ቦታና ሥልጣኑን ስለማስጠበቅ አያስብም። እንዲህ ማድረግ ጳውሎስ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ሲል ያሳሰበውን መቃረን ይሆናል።—ፊልጵስዩስ 2:4፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3, 6
ሰላማዊ ቃሎች
17. የጉባኤውን ሰላም እንዴት ያለ የተሳሳተ የምላስ አጠቃቀም ሊያናጋው ይችላል?
17 ሰላምን የሚከተል ሰው በተለይ ስለ ምላሱ አጠቃቀም ይጠነቀቃል። ያዕቆብ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል፦ “አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል፤ እነሆ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል!” (ያዕቆብ 3:5) የተንኰል ሐሜት፤ ሰውን ከኋላው መንቀፍ፣ ክፉና ሻካራ ቃላት፣ ማጉረምረምና ማማረር እንዲሁም ለግል ጥቅም ሲባል ሰዎችን በውሸት ማሞገስ እነዚህ ሁሉ የአምላክን ሕዝቦች ሰላም የሚበጠብጡ የሥጋ ሥራዎች ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 10:10፤ 2 ቆሮንቶስ 12:20፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:13፤ ይሁዳ 16
18. (ሀ) አንድ ሰው በደንብ ሳያስብበት አንድ ነገር ቢናገር ነገሩ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊከተሉት የሚገባው ትክክለኛው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ቁጣ አንድን ሰው ጐጂ ቃላት እንዲናገር ቢገፋፋው የበሰሉ ክርስቲያኖች ምን ያደርጋሉ?
18 እውነት ነው ያዕቆብ “ነገር ግን አንደበትን ሊገታ ማንም ሰው አይችልም” ብሏል። (ያዕቆብ 3:8) የጐለመሱ ክርስቲያኖችም እንኳ ሳይቀሩ አንዳንድ ጊዜ በኋላ ከልብ የሚጸጸቱበትን ነገር ይናገራሉ። ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ስህተቶችን ይቅር እንደምንላቸው ሌሎችም ይቅር እንዲሉን ተስፋ እናደርጋለን። (ማቴዎስ 6:12) አንዳንዴ የቁጣ ግንፋሎት ጐጂ ቃላትን ሊያመጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ሰላምን የሚፈጥር ሰው “የለዘበች መልስ ቁጣን እንደምትመልስና ሻካራ ቃል ግን ቁጣን እንደምታነሣሣ” ያስታውሳል። (ምሳሌ 15:1) አብዛኛውን ጊዜ ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ የቁጣ ቃላትን በበለጡ የቁጣ ቃላት ከመመለስ ይቆጠባል። በኋላ ንዴቱ ሲበርድ ልበ ሰፊ የሆነ ሰላማዊ ሰው በቁጣ ግለት ወቅት የተነገሩትን ነገሮች እንዴት ችላ እንደሚል ያውቃል። እንዲሁም አንድ ትሁት ክርስቲያን እንዴት ይቅርታ እንደሚጠይቅና ያስከተለውን ቁስል እንዴት እንደሚፈውስ ያውቃል። ከልብ “ይቅርታ” ለማለት መቻል የመንፈስ ጥንካሬ ምልክት ነው።
19. ስለ ምክር አሰጣጥ ከጳውሎስና ከኢየሱስ ምን እንማራለን?
19 ምላስ ሌሎችን ለመምከር ሊያገለግል ይችላል። ጴጥሮስ በአንጾኪያ ስህተት በፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ በሰው ሁሉ ፊት ገስጾታል። ኢየሱስም ለሰባቱ ጉባኤዎች በመልእክቶቹ ጠንካራ ምክር ሰጥቷል። (ገላትያ 2:11-14፤ ራእይ ምዕራፍ 2, 3) እነዚህን ምሳሌዎች ካጠናን ምክር ዋናው ነጥቡ እስኪጠፋ ድረስ በጣም ለስላሳ መሆን እንደሌለበት እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጳውሎስ ሻካራዎች ወይም ጨካኞች አልነበሩም። ምክራቸው ለብስጭታቸው መወጫ የተደረገ አልነበረም። ወንድሞቻቸውን ከልብ ለመርዳት እየሞከሩ ነበር። ምክር ሰጪው በዚያ ሰዓት ምላሱን ለመቆጣጠር የማይችል መስሎ ከተሰማው አንዳች ነገር ከመናገሩ በፊት በረድ እስኪል ድረስ መቆየቱን ሊመርጥ ይችላል። አለዚያ ግን ሻካራ ቃል ይናገርና ሊያስተካክለው ከፈለገው የባሰ ችግር ሊያስከትል ይችላል።—ምሳሌ 12:18
20. ስለ ወንድሞቻችንና ስለ እህቶቻችን የምንናገረው ነገር ሁሉ ምን የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት?
20 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሰላምና ፍቅር ሁለቱም የመንፈስ ፍሬዎች ስለሆኑ የቅርብ ዝምድና አላቸው። ለወንድሞቻችን የምንናገረው ወይም ስለነሱ የምናወራው ሁልጊዜ ለእነሱ ያለንን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ከሆነ ይህ ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽዖ ያበረክታል። (ዮሐንስ 15:12, 13) ንግግራችን “ሁልጊዜ በጨው እንደተቀመመ በፀጋ” መሆን አለበት። (ቆላስይስ 4:6) የምንናገረው ቃል የሚጣፍጥ፣ ልብን ደስ የሚያሰኝ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ “በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፣ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ” ሲል መክሯል።—ማርቆስ 9:50
‘የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ’
21. የአምላክ ሕዝቦች በሣምንታዊ ስብሰባዎቻቸውና በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ በግልጽ የሚታይባቸው ምንድን ነው?
21 መዝሙራዊው “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 133:1) እውነትም ከወንድሞቻችን ጋር አብረን መሆን በተለይም በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን፣ በትላልቅና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ወቅት አብረን መሆን ደስ ይለናል። በእነዚህ ወቅቶች ሰላማችን ለውጭ ተመልካቾች እንኳን ግልጽ ነው።
22. (ሀ) በቅርቡ ብሔራት ምን የውሸት ሰላም እንደጨበጡ ይመስላቸዋል? ይህስ ወደምን ይመራል? (ለ)የአምላክ የሰላም ቃል ኪዳን እንዴት ያለ እውነተኛ ሰላም ያመጣል?
22 በቅርቡ መንግሥታት ያለ ይሖዋ ዕርዳታ ሰላም ያገኙ የሚመስላቸው ጊዜ ይመጣል። ይሁን እንጂ “ሰላምና ደህንነት” ነው ሲሉ ከአምላካቸው ጋር ሰላም በሌላቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ድንገተኛ ጥፋት ይመጣል። (1 ተሰሎንቄ 5:3) ከዚያ በኋላ ታላቁ የሰላም መስፍን ከአምላክ ጋር ሰላም የታጣበት የመጀመሪያው ሁኔታ ካስከተላቸው አሰቃቂ ውጤቶች የሰው ልጆችን መፈወስ ይቀጥላል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ራእይ 22:1, 2) ከዚያም የአምላክ የሰላም ቃል ኪዳን ዓለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ ያመጣል። የዱር አውሬዎችም ሳይቀሩ እርስ በርሳቸው ከመጐዳዳት ተቆጥበው ሰላም ያገኛሉ።—መዝሙር 37:10, 11፤ 72:3-7፤ ኢሳይያስ 11:1-9፤ ራእይ 21:3, 4
23. ሰላማዊ አዲስ ዓለም ይመጣል የሚለውን ተስፋ እንደ ውድ ነገር የምንቆጥረው ከሆነ ምን ማድረግ አለብን?
23 ያ ጊዜ እንዴት ያለ ታላቅ ጊዜ ይሆናል! እዚያ ጊዜ ለመድረስ በጉጉት እየተጠባበቅህ ነውን? ከሆነ “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተል።” በአሁኑ ጊዜ ከወንድሞችህ ጋር በተለይም ከይሖዋ ጋር ሰላምን እሻ። አዎን፣ “ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ [በሚቻላችሁ (አዓት)] ሁሉ ትጉ።”—ዕብራውያን 12:14፤ 2 ጴጥሮስ 3:14
ታስታውሳለህን?
◻ ከይሖዋ ጋር ያለንን ሰላም ምን ሊያናጋው ይችላል?
◻ በጉባኤ ውስጥ መፈታት የሚያስፈልጋቸው ምን ዓይነት አለመግባባቶች ሊኖሩ ይችላሉ?
◻ ሰላምን ለመሻትና ለመከተል ይረዳን ዘንድ ይሖዋ ምን ዝግጅት አድርጐልናል?
◻ ምን ሥጋዊ ዝንባሌዎች ናቸው የጉባኤውን ሰላም ሊረብሹ የሚችሉት? እንዴትስ ልንከላከላቸው እንችላለን?
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ያስተማራቸው ሰዎች በመሃከላቸው ሰላም ተትረፍርፏል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድነት የሚያገለግሉት ወንድሞች ያላቸው ሰላም እንዴት ደስ የሚል ነው!