የጥናት ርዕስ 18
ፍቅርና ፍትሕ—በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ (ከአራት ተከታታይ ክፍሎች ሁለተኛው)
“አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ፤ በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።”—ገላ. 6:2
መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ
የትምህርቱ ዓላማa
1. ስለ የትኞቹ ሁለት ነገሮች እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹን ይወዳል። ጥንትም ሆነ ዛሬ ለአገልጋዮቹ ያለው ስሜት አልተለወጠም፤ ወደፊትም ቢሆን አይለወጥም። በተጨማሪም ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል። (መዝ. 33:5) በመሆኑም ስለ ሁለት ነገሮች እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ (1) ይሖዋ በአገልጋዮቹ ላይ የሚፈጸመውን በደል ሲያይ ያመዋል። (2) አገልጋዮቹ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ በመጀመሪያው ላይb እንደተመለከትነው አምላክ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። በተጨማሪም ይህ ሕግ ሁሉም ሰዎች በተለይም ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዙ ያደርግ ነበር። (ዘዳ. 10:18) ሕጉ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ያህል እንደሚያስብ ያሳያል።
2. የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን?
2 በ33 ዓ.ም. የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም የአምላክ ሕዝቦች በሙሴ ሕግ ሥር መሆናቸው አበቃ። ታዲያ ክርስቲያኖች በፍቅር ላይ የተመሠረተና ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሕግ ከለላ አይኖራቸውም ማለት ነው? በፍጹም! ክርስቲያኖች አዲስ ሕግ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ በቅድሚያ ይህ ሕግ ምን እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ ይህ ሕግ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይህ ሕግ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል የምንለው ለምንድን ነው? በዚህ ሕግ ሥር፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሌሎችን እንዴት ሊይዙ ይገባል?
‘የክርስቶስ ሕግ’ ምንድን ነው?
3. በገላትያ 6:2 ላይ የተገለጸው ‘የክርስቶስ ሕግ’ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
3 ገላትያ 6:2ን አንብብ። ክርስቲያኖች ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው። ክርስቶስ ለተከታዮቹ በጽሑፍ የሰፈረ ዝርዝር ሕግ አልሰጣቸውም፤ ሆኖም ሕይወታቸውን ሊመሩባቸው የሚገቡ ትእዛዞች፣ መመሪያዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቷቸዋል። ‘የክርስቶስ ሕግ’ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች በሙሉ ያጠቃልላል። በቀጣዮቹ አንቀጾች ላይ ስለዚህ ሕግ በጥልቀት እንመረምራለን።
4-5. ኢየሱስ ያስተማረው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ያስተማረውስ መቼ ነው?
4 ኢየሱስ ያስተማረው በየትኞቹ መንገዶች ነው? አንደኛ፣ በንግግሩ ሰዎችን አስተምሯል። ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች ስለ አምላክ እውነቱን ስለሚያስተምሩ፣ ትክክለኛውን የሕይወት ትርጉም ስለሚያስገነዝቡና በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም መከራ መፍትሔው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ስለሚጠቁሙ ከፍተኛ ኃይል ነበራቸው። (ሉቃስ 24:19) በተጨማሪም ኢየሱስ ምሳሌ በመሆን አስተምሯል። የኢየሱስ አኗኗር ተከታዮቹ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳይ ነበር።—ዮሐ. 13:15
5 ኢየሱስ ያስተማረው መቼ ነው? ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ያስተምር ነበር። (ማቴ. 4:23) በተጨማሪም ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹን አስተምሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ተከታዮቹ “ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ መስጠቱን ቀጥሏል። ለምሳሌ በ96 ዓ.ም. አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስን ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ማበረታቻና ምክር እንዲሰጥ መርቶታል።—ቆላ. 1:18፤ ራእይ 1:1
6-7. (ሀ) ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ተመዝግበው የሚገኙት ምን ላይ ነው? (ለ) የክርስቶስን ሕግ እንደምንታዘዝ የምናሳየው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ተመዝግበው የሚገኙት ምን ላይ ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተናገራቸውና ያደረጋቸው በርካታ ነገሮች በአራቱ ወንጌሎች ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ያላቸው ሰዎች በመንፈስ ተመርተው የጻፏቸው ሌሎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ደግሞ ኢየሱስ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አስተሳሰብ እንድናውቅ ይረዱናል።—1 ቆሮ. 2:16
7 የምናገኘው ትምህርት፦ የኢየሱስ ትምህርቶች ሁሉንም የሕይወታችንን ዘርፎች ይዳስሳሉ። በመሆኑም የክርስቶስ ሕግ በቤታችን፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የምናደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ይነካል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ይህን ሕግ መማር እንችላለን። በመንፈስ መሪነት በተጻፉት በእነዚህ ዘገባዎች ላይ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ መመሪያዎችና ትእዛዞች መሠረት ሕይወታችንን በመምራት ይህን ሕግ እንደምንታዘዝ እናሳያለን። የክርስቶስን ሕግ ስንታዘዝ ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ሁሉ ምንጭ የሆነውን አፍቃሪ አምላካችንን ይሖዋን እንታዘዛለን።—ዮሐ. 8:28
በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሕግ
8. የክርስቶስ ሕግ የተገነባው በምን ላይ ነው?
8 ጠንካራ በሆነ መሠረት ላይ የተገነባ ቤት፣ በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። በተመሳሳይም ጠንካራ በሆነ መሠረት ላይ የተገነባ ሕግ፣ የሚመሩበት ሰዎች የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። የክርስቶስ ሕግ፣ ከሁሉ በተሻለ መሠረት ላይ ይኸውም በፍቅር ላይ የተገነባ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
9-10. ኢየሱስ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ እንደነበር የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው? እኛስ የእሱን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
9 አንደኛ፣ ኢየሱስ ማንኛውንም ነገር ያደርግ የነበረው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። ፍቅር የሚገለጸው ደግሞ ለሌሎች ባለን የርኅራኄ ወይም የአዘኔታ ስሜት ነው። ኢየሱስ በርኅራኄ ተነሳስቶ ሕዝቡን አስተምሯል፣ የታመሙትን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል እንዲሁም የሞቱትን አስነስቷል። (ማቴ. 14:14፤ 15:32-38፤ ማር. 6:34፤ ሉቃስ 7:11-15) እነዚህን ነገሮች ማከናወን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅበት ቢሆንም ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ለማስቀደም ፈቃደኛ ሆኗል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ታላቅ ፍቅር አሳይቷል።—ዮሐ. 15:13
10 የምናገኘው ትምህርት፦ ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። በተጨማሪም በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት በማድረግ የኢየሱስን አርዓያ እንከተላለን። በርኅራኄ ተነሳስተን ምሥራቹን በመስበክና ሰዎችን በማስተማር የክርስቶስን ሕግ እንደምንታዘዝ እናሳያለን።
11-12. (ሀ) ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
11 ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የአባቱን ፍቅር አንጸባርቋል። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ያከናወናቸው ነገሮች ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ያህል እንደሚያስብ ያሳያሉ። ኢየሱስ ያስተማራቸውን የሚከተሉትን ትምህርቶች እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፦ በሰማይ ያለው አባታችን እያንዳንዳችንን ከፍ አድርጎ ይመለከተናል። (ማቴ. 10:31) አንድ የጠፋ በግ ንስሐ ለመግባትና ወደ ጉባኤው ለመመለስ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ ይሖዋ በደስታ ይቀበለዋል። (ሉቃስ 15:7, 10) ይሖዋ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር አሳይቷል።—ዮሐ. 3:16
12 የምናገኘው ትምህርት፦ ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ኤፌ. 5:1, 2) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን፤ እንዲሁም አንድ ‘የጠፋ በግ’ ወደ ይሖዋ ሲመለስ በደስታ እንቀበለዋለን። (መዝ. 119:176) ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሳንሰስት ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን በመስጠት እንደምንወዳቸው እናሳያለን፤ በተለይም በችግራቸው ወቅት ከጎናቸው በመሆን እንረዳቸዋለን። (1 ዮሐ. 3:17) ሌሎችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ በመያዝ የክርስቶስን ሕግ እንታዘዛለን።
13-14. (ሀ) ዮሐንስ 13:34, 35 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ተከታዮቹን ምን በማለት አዟቸዋል? ይህስ አዲስ ትእዛዝ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አዲሱን ትእዛዝ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?
13 ሦስተኛ፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲያሳዩ አዟል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ።) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ትእዛዝ አዲስ ነው፤ ምክንያቱም በሙሴ ሕግ ሥር፣ እስራኤላውያን እንዲህ ያለ ፍቅር እንዲያሳዩ አይጠበቅባቸውም ነበር። የኢየሱስ ተከታዮች ግን ኢየሱስ እንደወደዳቸው እነሱም ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ ታዘዋል። ይህን ትእዛዝ መፈጸም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርc ማሳየትን ይጠይቃል። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከራሳችንም እንኳ አስበልጠን መውደድ ይኖርብናል። ለወንድሞቻችን ያለን ጥልቅ ፍቅር ልክ እንደ ኢየሱስ ሕይወታችንን ጭምር አሳልፈን እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይገባል።
14 የምናገኘው ትምህርት፦ አዲሱን ትእዛዝ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው? በአጭር አነጋገር፣ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ስንል መሥዋዕትነት በመክፈል ነው። ለእምነት ባልንጀሮቻችን ከሁሉ የላቀውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ማለትም ሕይወታችንን አሳልፈን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ትናንሽ ነገሮችንም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ነን። ለምሳሌ በዕድሜ የገፉ የጉባኤያችንን አባላት ወደ ስብሰባ ይዘን ለመሄድ፣ ወንድሞቻችንን ቅር ላለማሰኘት ስንል የግል ምርጫችንን ለመተው ወይም ከሥራችን እረፍት ወስደን በአደጋ የተጎዱትን ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። በዚህ መልኩ የክርስቶስን ሕግ እንፈጽማለን። በተጨማሪም በጉባኤው ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ግለሰብ የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማው የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሕግ
15-17. (ሀ) ኢየሱስ ያደረጋቸው ነገሮች ለፍትሕ ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
15 “ፍትሕ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ያለምንም አድልዎ ማድረግን ለማመልከት ነው። የክርስቶስ ሕግ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል የምንለው ለምንድን ነው?
16 በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ያደረጋቸው ነገሮች እሱ ለፍትሕ ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቁት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችን ይጠሉ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርት ያልተማሩ አይሁዳውያንን ያንቋሽሹ እንዲሁም ሴቶችን ይንቁ ነበር። ኢየሱስ ግን ሁሉንም ፍትሐዊ በሆነና አድልዎ በሌለበት መንገድ ይይዝ ነበር። አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች በእምነት ወደ እሱ ሲቀርቡ በደስታ ተቀብሏቸዋል። (ማቴ. 8:5-10, 13) ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም ያለአድልዎ ሰብኳል። (ማቴ. 11:5፤ ሉቃስ 19:2, 9) ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ ወይም የሚያንቋሽሽ ነገር በጭራሽ አድርጎ አያውቅም። ከዚህ በተቃራኒ፣ በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሴቶችን ጨምሮ ሁሉንም ሴቶች በአክብሮትና በደግነት ይይዝ ነበር።—ሉቃስ 7:37-39, 44-50
17 የምናገኘው ትምህርት፦ ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ በመያዝ እንዲሁም የኑሮ ደረጃቸው ወይም ሃይማኖታቸው ምንም ሆነ ምን፣ ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ በመስበክ ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። ክርስቲያን ወንዶች ለሴቶች አክብሮት በማሳየት ኢየሱስን መምሰል ይችላሉ። በዚህ መንገድ፣ የክርስቶስን ሕግ እንደምንፈጽም እናሳያለን።
18-19. ኢየሱስ ስለ ፍትሕ ምን አስተምሯል? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ስለ ፍትሕ ያስተማራቸውን ነገሮች እንመልከት። ኢየሱስ ተከታዮቹ ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲይዙ የሚያበረታቱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተምሯል። ወርቃማውን ሕግ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። (ማቴ. 7:12) ሁላችንም፣ ሌሎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲይዙን እንፈልጋለን። ስለዚህ እኛም ሌሎችን በዚሁ መንገድ መያዝ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን እነሱም እኛን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ ሊነሳሱ ይችላሉ። ይሁንና ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ተፈጽሞብን ከሆነስ? ኢየሱስ፣ ይሖዋ “ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ” እንደሚያደርግ በማስተማር ተከታዮቹ በአምላክ ላይ እምነት እንዲጥሉ አበረታቷል። (ሉቃስ 18:6, 7) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ የሚከተለውን ዋስትና ይሰጠናል፦ ፍትሐዊ የሆነው አምላካችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ በትክክለኛው ጊዜ ላይ ፍትሕ እንድናገኝ ያደርጋል።—2 ተሰ. 1:6
19 የምናገኘው ትምህርት፦ ኢየሱስ ያስተማራቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላችን ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ ይረዳናል። በተጨማሪም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብን ከሆነ ይሖዋ ፍትሕ እንድናገኝ እንደሚያደርግ ማወቃችን ያጽናናናል።
ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሌሎችን እንዴት ሊይዙ ይገባል?
20-21. (ሀ) ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሌሎችን እንዴት እንዲይዙ ይጠበቅባቸዋል? (ለ) ባሎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? አባቶችስ ልጆቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?
20 በክርስቶስ ሕግ ሥር፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሌሎችን እንዴት ሊይዙ ይገባል? ይህ ሕግ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች በሥራቸው ያሉትን ሁሉ በፍቅርና በአክብሮት መያዝ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ክርስቶስ ማንኛውንም ነገር በፍቅር እንድናደርግ እንደሚጠብቅብን ማስታወስ አለባቸው።
21 በቤተሰብ ውስጥ። “ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ” ሁሉ ባሎችም ሚስቶቻቸውን መውደድ ይኖርባቸዋል። (ኤፌ. 5:25, 28, 29) አንድ ባል ከራሱ ይልቅ የሚስቱን ፍላጎት በማስቀደም ልክ እንደ ኢየሱስ፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት አለበት። አንዳንድ ወንዶች እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማሳየት ይከብዳቸው ይሆናል፤ ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ ባደጉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሌሎችን በፍቅርና በአክብሮት መያዝ ስላልተለመደ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለውን መጥፎ ባሕርይ ማስወገድ ከባድ ሊሆንባቸው ቢችልም የክርስቶስን ሕግ መታዘዝ ከፈለጉ ይህን ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለባቸው። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የሚያሳይ ባል የሚስቱን አክብሮት ያተርፋል። ልጆቹን ከልቡ የሚወድ አባት፣ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ በልጆቹ ላይ በደል አይፈጽምም። (ኤፌ. 4:31) ከዚህ ይልቅ ፍቅሩንና አድናቆቱን በመግለጽ ልጆቹ የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። እንዲህ ያለው አባት የልጆቹን ፍቅርና አመኔታ ያተርፋል።
22. በ1 ጴጥሮስ 5:1-3 ላይ በተገለጸው መሠረት ‘በጎቹ’ የማን ንብረት ናቸው? እነዚህ በጎች እንዴት ሊያዙ ይገባል?
22 በጉባኤ ውስጥ። ሽማግሌዎች ‘በጎቹ’ የእነሱ እንዳልሆኑ ማስታወስ አለባቸው። (ዮሐ. 10:16፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3ን አንብብ።) ‘የአምላክ መንጋ፣’ “በአምላክ ፊት” እና “የአምላክ ንብረት” የሚሉት አገላለጾች ሽማግሌዎች በጎቹ የይሖዋ እንደሆኑ እንዲያስታውሱ ያደርጋሉ። ይሖዋ የእሱ ንብረት የሆኑት በጎች በፍቅርና በገርነት እንዲያዙ ይፈልጋል። (1 ተሰ. 2:7, 8) የእረኝነት ኃላፊነታቸውን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ የሚወጡ ሽማግሌዎች የይሖዋን ሞገስ ያገኛሉ። በተጨማሪም የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ፍቅርና አክብሮት ያተርፋሉ።
23-24. (ሀ) ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ ሽማግሌዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ሲመለከቱ የትኞቹን ነገሮች ያመዛዝናሉ?
23 ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ ሽማግሌዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው? የጉባኤ ሽማግሌዎች ኃላፊነት፣ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን ሕግ ያስፈጽሙ ከነበሩት ዳኞችና ሽማግሌዎች ኃላፊነት የተለየ ነው። በሙሴ ሕግ ሥር፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶች መንፈሳዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን ጭምር ይመለከቱ ነበር። በክርስቶስ ሕግ ሥር ግን ሽማግሌዎች አንድ ኃጢአት ሲፈጸም ጉዳዩን የሚመለከቱት ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር ብቻ ነው። ሽማግሌዎች፣ አምላክ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን የመመልከት ኃላፊነት የሰጠው ለሰብዓዊ ባለሥልጣናት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ይህም ጥፋተኛው የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልበት፣ እንዲታሰር ወይም በሌላ መንገድ እንዲቀጣ የማድረግ ኃላፊነትን ይጨምራል።—ሮም 13:1-4
24 ሽማግሌዎች አንድ ከባድ ኃጢአት ሲፈጸም ጉዳዩን ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር የሚመለከቱት እንዴት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ ውሳኔ ያስተላልፋሉ። የክርስቶስ ሕግ የተመሠረተው በፍቅር ላይ እንደሆነ አይዘነጉም። በመሆኑም በፍቅር ተነሳስተው የሚከተለውን ጥያቄ ያጤናሉ፦ ‘በጉባኤው ውስጥ ካሉት መካከል በተፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የተጎዱ ካሉ እነሱን መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?’ በተጨማሪም ፍቅር፣ በደል ከፈጸመው ግለሰብ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነገሮች እንዲያመዛዝኑ ያደርጋቸዋል፦ ‘ግለሰቡ ንስሐ ገብቷል? ከመንፈሳዊ ሕመሙ እንዲያገግም ልንረዳው እንችላለን?’
25. ቀጣዩ ርዕስ የትኛውን ጉዳይ ያብራራል?
25 በክርስቶስ ሕግ ሥር በመሆናችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ሁላችንም ይህን ሕግ ለመፈጸም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ ከስጋት ነፃ ሆነው የሚኖሩ ከመሆኑም ሌላ እንደሚወደዱና ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጣቸው ይሰማቸዋል። ይሁንና የምንኖረው “ክፉ ሰዎች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” በሚሄዱበት ዓለም ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:13) በመሆኑም ምንጊዜም ንቁዎች መሆናችን አስፈላጊ ነው። ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዘ ኃጢአት ሲፈጸም የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክን ፍትሕ በሚያንጸባርቅ መንገድ ጉዳዩን መያዝ የሚችለው እንዴት ነው? ቀጣዩ ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል።
መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!
a ይህ ርዕስና ቀጣዮቹ ሁለት ርዕሶች ይሖዋ የፍቅርና የፍትሕ አምላክ መሆኑን እንድንተማመን የሚያደርጉንን ምክንያቶች ከሚያብራሩት ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ይሖዋ ሕዝቡ ፍትሕ እንዲያገኙ የሚፈልግ ከመሆኑም ሌላ በክፋት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ፍትሕ የተነፈጉ ሰዎችን ያጽናናል።
b በየካቲት 2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ፍቅርና ፍትሕ—በጥንቷ እስራኤል ውስጥ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ቅድሚያ እንድንሰጥ ያነሳሳናል። ሌሎችን ለመርዳት ወይም ለመጥቀም ስንል አንዳንድ ነገሮችን ለመተው ወይም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች እንሆናለን።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ አንድ ልጇን በሞት ያጣችውን መበለት አይቶ ስለራራላት ልጇን ከሞት አስነስቶላታል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ፣ ስምዖን በተባለ ፈሪሳዊ ቤት ውስጥ በማዕድ ተቀምጧል። አንዲት ሴት (ዝሙት አዳሪ ሳትሆን አትቀርም) መጥታ የኢየሱስን እግር በእንባዋ ካራሰች በኋላ በፀጉሯ አበሰችው፤ ከዚያም እግሩን ዘይት ቀባችው። ስምዖን ሴትየዋን ቢያወግዛትም ኢየሱስ ግን እሷን ደግፎ ተናግሯል።