“በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ”
‘በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት ጠብቁ።’—1 ጴጥ. 5:2
1. ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን በጻፈበት ጊዜ ክርስቲያኖች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ?
ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን የጻፈው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ በሮም በሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ ስደት ከማስነሳቱ ቀደም ብሎ ነው። ጴጥሮስ የክርስቲያን ባልንጀሮቹን እምነት ለማጠናከር ፈልጎ ነበር። በወቅቱ ዲያብሎስ የሚውጣቸውን ክርስቲያኖች ለማግኘት ‘እየተንጎራደደ’ ነበር። ክርስቲያኖች ይህን ጠላታቸውን ለመቋቋም ‘የማስተዋል ስሜቶቻቸውን መጠበቅ’ ብሎም ‘ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳቸውን ዝቅ ማድረግ’ ነበረባቸው። (1 ጴጥ. 5:6, 8) በተጨማሪም አንድነታቸውን ጠብቀው መኖር ይገባቸዋል። ‘እርስ በርሳቸው መነካከሳቸውና መባላታቸው’ ፈጽሞ አያዋጣቸውም፤ ምክንያቱም ይህ የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ‘እርስ በርስ መጠፋፋት’ ብቻ ነው።—ገላ. 5:15
2, 3. ትግል የምንገጥመው ከማን ጋር ነው? የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?
2 በዛሬው ጊዜ እኛም ያለንበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ዲያብሎስ እኛን ለመዋጥ የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች በመፈላለግ ላይ ይገኛል። (ራእይ 12:12) ከፊታችን ደግሞ ‘ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ መከራ’ ይጠብቀናል። (ማቴ. 24:21) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በረባው ባልረባው ከመነታረክ መቆጠብ እንደነበረባቸው ሁሉ እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ የሽማግሌዎች እርዳታ የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል፤ ሽማግሌዎች ደግሞ ይህን ለማድረግ ብቃቱ አላቸው።
3 በመጀመሪያ፣ ሽማግሌዎች ‘በአደራ የተሰጣቸውን የአምላክ መንጋ’ እንደ እረኛ ሆነው ከመጠበቅ መብታቸው ጋር በተያያዘ ያላቸውን አድናቆትና ግንዛቤ ማሳደግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። (1 ጴጥ. 5:2) ከዚያም ሽማግሌዎች የእረኝነት ሥራቸውን በተገቢው መንገድ መወጣት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ የጉባኤው አባላት፣ “በትጋት እየሠሩና” ለመንጋው ‘አመራር እየሰጡ ያሉትን ማክበር’ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እናያለን። (1 ተሰ. 5:12) ትግል የምንገጥመው ከሰይጣን ጋር መሆኑን ስለምናውቅ እነዚህን ጉዳዮች መመርመራችን ይህን ቀንደኛ ጠላታችንን ለመቋቋም ይረዳናል።—ኤፌ. 6:12
የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ በመሆን ጠብቁ
4, 5. ሽማግሌዎች ለመንጋው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? በምሳሌ አስረዳ።
4 ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መካከል የሚገኙት ሽማግሌዎች በአደራ ለተሰጣቸው መንጋ የአምላክ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው አበረታቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:1, 2ን አንብብ።) ምንም እንኳ ጴጥሮስ በጉባኤው ውስጥ እንደ ዓምድ የሚታይ ቢሆንም ሽማግሌዎችን ያናገራቸው የእነሱ የበላይ እንደሆነ በሚያሳይ መንገድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምክር የሰጣቸው አብረውት እንደሚሠሩ ሽማግሌዎች አድርጎ በመቁጠር ነው። (ገላ. 2:9) ከጴጥሮስ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካልም የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ በመሆን የሚጠብቁት የጉባኤ ሽማግሌዎች ይህን ከባድ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት እንዲያደርጉ ያሳስባቸዋል።
5 ሐዋርያው “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ” በማለት ለሽማግሌዎች ጽፎላቸዋል። እነዚህ ሽማግሌዎች መንጋው የይሖዋና የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረት እንደሆነ መገንዘባቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ሽማግሌዎቹ የአምላክን በጎች የያዙበትን መንገድ በተመለከተ ለይሖዋ መልስ መስጠት ነበረባቸው። ለምሳሌ አንድ የቅርብ ጓደኛችሁ የሆነ ቦታ ሲሄድ ልጆቹን እንድትጠብቁለት አደራ ቢላችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ልጆቹን በደንብ ለመንከባከብና ለመመገብ ጥረት አታደርጉም? ከልጆቹ መካከል አንዱ ቢታመም አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኝ አታደርጉም? በተመሳሳይም የጉባኤ ሽማግሌዎች “አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን [መጠበቅ]” አለባቸው። (ሥራ 20:28) ሽማግሌዎች እያንዳንዱ በግ ውድ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተገዛ መሆኑን ይገነዘባሉ። በተጨማሪም በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ መሆናቸውን ስለሚረዱ መንጋውን ይመግባሉ፣ ይጠብቃሉ እንዲሁም ይንከባከባሉ።
6. በጥንት ዘመን የነበሩ እረኞች ምን ኃላፊነቶች ነበሩባቸው?
6 እስቲ በጥንት ዘመን የነበሩ እረኞች ምን ኃላፊነቶች እንደነበሩባቸው ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። እረኞቹ በጎቹን ለመጠበቅ የቀኑን ሐሩርና የሌሊቱን ቁር መቻል ነበረባቸው። (ዘፍ. 31:40) ሌላው ቀርቶ ለበጎቻቸው ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥሉ ነበር። እረኛ የነበረው ወጣቱ ዳዊት እንደ አንበሳና ድብ ካሉ አውሬዎች መንጋውን ታድጓል። ዳዊት ምን እንዳደረገ ሲናገር “ጕሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር” ብሏል። (1 ሳሙ. 17:34, 35) ይህ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ነው! በጎቹን ለማስጣል የአውሬው መንጋጋ ውስጥ የመግባት ያህል መቅረብ ነበረበት! ያም ቢሆን በጎቹን ከማዳን ወደኋላ አላለም።
7. ሽማግሌዎች በምሳሌያዊ ሁኔታ በጎቹን ከሰይጣን መንጋጋ የሚነጥቁት እንዴት ነው?
7 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች ዲያብሎስ ልክ እንደ አንበሳ የሚሰነዝረውን ጥቃት ለመከላከል ነቅተው መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ደግሞ በጎችን ከዲያብሎስ መንጋጋ የመንጠቅ ያህል ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። ሽማግሌዎች በምሳሌያዊ ሁኔታ የአውሬውን ጉሮሮ አንቀው በመያዝ በጎቹን ማስጣል ይችላሉ። በሰይጣን ወጥመድ እየተሳቡ እንደሆነ ያልተገነዘቡ ወንድሞችን አደጋውን እንዲያስተውሉ መርዳት ይችሉ ይሆናል። (ይሁዳ 22, 23ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ያለ ይሖዋ እርዳታ ይህን ማድረግ አይችሉም። አንድ ሰው መንፈሳዊ ጉዳት ሲያጋጥመው ሽማግሌዎች በምሳሌያዊ ሁኔታ በቁስሉ ላይ ዘይት በማፍሰስ በጨርቅ ይጠቀልሉታል፤ ይህንንም የሚያደርጉት በጥንቃቄ ብሎም ፈዋሽ ዘይት የሆነውን የአምላክ ቃል በመጠቀም ነው።
8. ሽማግሌዎች መንጋውን የሚመሩት ወዴት ነው? እንዴትስ?
8 በተጨማሪም በጥንት ዘመን የነበሩ እረኞች መንጎቻቸውን ጥሩ ወደሆነ መስክና ውኃ ወደሚገኝበት ቦታ ይወስዷቸው ነበር። በተመሳሳይም ሽማግሌዎች በጎቹ አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ በማበረታታት ወደ ጉባኤ ይመሯቸዋል፤ በጎቹ ጉባኤ መሄዳቸው “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን” እንዲያገኙና በጥሩ መንገድ እንዲመገቡ ያስችላቸዋል። (ማቴ. 24:45) ሽማግሌዎች፣ በመንፈሳዊ የታመሙ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው በዘዴ ለማሳመን ረዘም ያለ ጊዜ ማጥፋት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ምናልባትም አንድ የባዘነ በግ ወደ መንጋው ለመመለስ ጥረት እያደረገ ሊሆን ይችላል። ሽማግሌዎች ይህ ወንድማቸው እንዲበረግግና እንዲሸማቀቅ ከማድረግ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዘዴ ሊያስረዱት አልፎ ተርፎም እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የሚያደርግበትን መንገድ ሊጠቁሙት ይችላሉ።
9, 10. ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የታመሙትን መንከባከብ ያለባቸው እንዴት ነው?
9 በምትታመሙበት ጊዜ ምን ዓይነት ዶክተር ቢያክማችሁ ደስ ይላችኋል? ቀጣዩን ሕመምተኛ ለማስገባት ከመቸኮሉ የተነሳ ጊዜ ሰጥቶ ሳያዳምጣችሁ መድኃኒት የሚያዝላችሁ? ወይስ በደንብ የሚያዳምጣችሁ እንዲሁም ችግራችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያስረዳችሁና መፍትሔ ሊሆን የሚችለውን ሕክምና የሚገልጽላችሁ ዶክተር? አንዳንድ ጊዜ፣ ዶክተሩ ከሚሰጣችሁ መፍትሔ የበለጠ እናንተን ያናገረበትና የያዘበት መንገድ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
10 ሽማግሌዎችም በመንፈሳዊ የታመመውን ሰው በማዳመጥና በምሳሌያዊ መንገድ ‘በይሖዋ ስም ዘይት በመቀባት’ ቁስሉ እንዲድን መርዳት ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:14, 15ን አንብብ።) ከገለዓድ እንደሚገኝ ዘይት የአምላክ ቃል በበሽታ ለደከመው ሰው ፈውስ ያስገኝለታል። (ኤር. 8:22፤ ሕዝ. 34:16) ሽማግሌዎች የአምላክን ቃል የሚጠቀሙ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመንፈሳዊ እየተንገዳገደ ያለውን ግለሰብ እንደገና ሚዛኑን እንዲጠብቅ ሊረዱት ይችላሉ። በእርግጥም ሽማግሌዎች የታመመው በግ የሚያሳስበውን ነገር ሲናገር ካዳመጡና አብረውት ከጸለዩ ጥረታቸው ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት ጠብቁ
11. ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ በፈቃደኝነት እንዲጠብቁ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?
11 ጴጥሮስ በመቀጠል ሽማግሌዎች የእረኝነቱን ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ ማድረግ ስላለባቸውና ማድረግ ስለሌለባቸው ነገር አሳስቧቸዋል። ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ መጠበቅ ያለባቸው “በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት” ነው። ታዲያ ወንድሞቻቸውን በፈቃደኝነት እንዲያገለግሉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ጴጥሮስ የኢየሱስን በጎች እንዲጠብቅና እንዲመግብ ያነሳሳው ምን እንደሆነ ማወቃችን መልሱን ለማግኘት ያስችለናል። ጴጥሮስን ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ለጌታው የነበረው ጥልቅ ፍቅር ነው። (ዮሐ. 21:15-17) ሽማግሌዎችም “ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ” ፍቅር ግድ ይላቸዋል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) ይህ ፍቅር ለአምላክና ለወንድሞቻቸው ካላቸው ፍቅር ጋር ተዳምሮ ጉልበታቸውን፣ ሀብታቸውንና ጊዜያቸውን ተጠቅመው መንጋውን ለማገልገል እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል። (ማቴ. 22:37-39) በቅሬታ ሳይሆን በፈቃደኝነት ራሳቸውን ይሰጣሉ።
12. ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን የሰጠው እስከ ምን ድረስ ነው?
12 ሽማግሌዎች ራሳቸውን መስጠት ያለባቸው እስከ ምን ድረስ ነው? ጳውሎስ የኢየሱስን አርዓያ እንደተከተለ ሁሉ እነሱም በጎቹን ሲንከባከቡ የጳውሎስን አርዓያ ይከተላሉ። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስና የሥራ ባልደረቦቹ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ወንድሞቻቸው ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው ለእነሱ “የአምላክን ምሥራች ብቻ ሳይሆን የገዛ [ነፍሳቸውን] ጭምር” ሊያካፍሏቸው ዝግጁ ነበሩ። “የምታጠባ እናት ልጆቿን እንደምትንከባከብ” ሁሉ እነሱም ይህን ያደረጉት በገርነት ነው። (1 ተሰ. 2:7, 8) ጳውሎስ አንዲት የምታጠባ እናት ለልጆቿ ምን ዓይነት ስሜት እንዳላት ተገንዝቦ ነበር። ይህች እናት ልጆቿን ለመመገብ ስትል በሌሊት መነሳትን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ናት።
13. ሽማግሌዎች በምን ረገድ ሚዛናቸውን መጠበቅ አለባቸው?
13 ሽማግሌዎች የእረኝነት ኃላፊነታቸውንና ለቤተሰባቸው ያለባቸውን ግዴታ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መወጣት ያስፈልጋቸዋል። (1 ጢሞ. 5:8) ሽማግሌዎች ለጉባኤው የሚሰጡት ለቤተሰባቸው ሊያውሉት የሚችሉትን ውድ ጊዜ ነው። ሁለቱን ኃላፊነቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመወጣት የሚችሉበት አንዱ መንገድ የጉባኤውን አባላት አልፎ አልፎ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ መጋበዝ ነው። ማሳናኦ የተባለ በጃፓን የሚኖር አንድ ሽማግሌ፣ በመንፈሳዊ የሚንከባከብ አባት የሌላቸውን ቤተሰቦችና ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖችን ላለፉት ዓመታት በቤተሰብ ጥናቱ ላይ ሲጋብዝ ቆይቷል። ማሳናኦ በዚህ መልኩ የረዳቸው አንዳንድ ወንድሞች ከጊዜ በኋላ ሽማግሌ የሆኑ ሲሆን እሱ የተወላቸውን ግሩም ምሳሌ ተከትለዋል።
አግባብ ካልሆነ ጥቅም ራቁ —ለማገልገል በመጓጓት መንጋውን ጠብቁ
14, 15. ሽማግሌዎች ‘አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የመመኘት’ ዝንባሌ በውስጣቸው እንዳያቆጠቁጥ መጠንቀቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉትስ እንዴት ነው?
14 በተጨማሪም ጴጥሮስ “አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት” መንጋውን እንዲጠብቁ ሽማግሌዎችን አበረታቷቸዋል። ሽማግሌዎች ይህ ሥራቸው ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም ለሚያደርጉት ነገር ገንዘብ እንዲከፈላቸው አይጠብቁም። ጴጥሮስ “አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት” መንጋውን መጠበቅ ያለውን አደጋ አብረውት ለሚሠሩት ሽማግሌዎች ማስጠንቀቁ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ይዞ ማገልገል ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ውስጥ የሚታየው ነገር ምሥክር ነው፤ ሃይማኖታዊ መሪዎቿ የቅንጦት ሕይወት እየመሩ አብዛኛው ሕዝብ ግን በድህነት ይማቅቃል። (ራእይ 18:2, 3) ከዚህ አንጻር በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ በውስጣቸው እንዳያቆጠቁጥ መጠንቀቃቸው ተገቢ ነው።
15 ጳውሎስ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን ‘ብዙ ወጪ ማስወጣት’ ቢችልም ‘የማንንም ምግብ በነፃ አልበላም።’ ከዚህ ይልቅ ‘ሌት ተቀን ይደክምና ይለፋ’ ነበር። (2 ተሰ. 3:8) ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ጨምሮ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። የእምነት አጋሮቻቸው የሚያደርጉላቸውን መስተንግዶ ቢቀበሉም “ብዙ ወጪ በማስወጣት” በማንም ላይ ሸክም መሆን አይፈልጉም።—1 ተሰ. 2:9
16. መንጋውን “ለማገልገል በመጓጓት” መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
16 ሽማግሌዎች መንጋውን የሚጠብቁት “ለማገልገል በመጓጓት” ነው። መንጋውን በሚረዱበት ጊዜ የራሳቸውን ጥቅም በመሠዋት እንዲህ ዓይነት ጉጉት እንዳላቸው ያሳያሉ። ይህ ሲባል ግን መንጋው ይሖዋን እንዲያገለግል ያስገድዱታል ማለት አይደለም፤ በተጨማሪም አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች የጉባኤው አባላት በፉክክር መንፈስ አምላክን እንዲያገለግሉ አያበረታቱም። (ገላ. 5:26) ሽማግሌዎች አንዱ በግ ከሌላው የተለየ እንደሆነ ይገነዘባሉ። የጉባኤ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸው ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉ የመርዳት ጉጉት አላቸው።
ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ምሳሌ በመሆን መንጋውን ጠብቁ
17, 18. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ ሐዋርያቱ ኢየሱስ ትሕትናን አስመልክቶ የሰጠውን ትምህርት መረዳት ይከብዳቸው የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ወንድሞች ከሐዋርያቱ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
17 ከላይ እንዳየነው ሽማግሌዎች በእረኝነት የሚጠብቁት መንጋ የአምላክ እንጂ የራሳቸው እንዳልሆነ መዘንጋት የለባቸውም። ‘የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናቸውን ላለማሳየት’ መጠንቀቅ አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 5:3ን አንብብ።) የኢየሱስ ሐዋርያት የተሳሳተ ዝንባሌ ስለነበራቸው እንደ አሕዛብ ገዥዎች ትልቅ ቦታ ለማግኘት የፈለጉባቸው ጊዜያት ነበሩ።—ማርቆስ 10:42-45ን አንብብ።
18 በዛሬው ጊዜ ‘የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣሩ’ ወንድሞች እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የተነሳሱበትን ዓላማ ለማወቅ ራሳቸውን መመርመራቸው የተገባ ነው። (1 ጢሞ. 3:1) በአሁኑ ወቅት ሽማግሌ ሆነው እያገለገሉ ያሉ ወንድሞችም አንዳንድ ሐዋርያት ቀደም ሲል የነበራቸው ዓይነት ምኞት ይኸውም ሥልጣን ወይም ትልቅ ቦታ የማግኘት ፍላጎት ይኖራቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ራሳቸውን በሐቀኝነት መመርመር ይፈልጉ ይሆናል። በዚህ ረገድ ሐዋርያቱ ትግል ማድረግ ካስፈለጋቸው ዛሬ ያሉት ሽማግሌዎች ሥልጣናቸውን በሌሎች ላይ የማሳየት ዓለማዊ ዝንባሌ እንዳይጠናወታቸው ብርቱ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ አያቅታቸውም።
19. ሽማግሌዎች መንጋውን ለመጠበቅ እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርባቸዋል?
19 እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች መንጋውን ‘ከጨካኝ ተኩላዎች’ ለመጠበቅ ሲሉ አሊያም በሌላ ምክንያት ጠንከር ያለ ምክር መስጠት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይኖራል። (ሥራ 20:28-30) ጳውሎስ “በተሰጠህ ሙሉ የማዘዝ ሥልጣን መሠረት . . . አጥብቀህ መምከርህንና መገሠጽህን ቀጥል” በማለት ለቲቶ ነግሮታል። (ቲቶ 2:15) ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜም ቢሆን ተግሣጽ የሚሰጧቸውን ሰዎች በአክብሮት መያዝ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉትን ግለሰቦች ልብ ለመንካትና ትክክለኛውን መንገድ እንዲከተሉ ለመርዳት አብዛኛውን ጊዜ የተሻለው መንገድ ኃይለ ቃል ተጠቅሞ እርማት ለመስጠት መሞከር ሳይሆን ጥሩ ምሳሌ ሆኖ መገኘት መሆኑን ይገነዘባሉ።
20. ሽማግሌዎች ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ረገድ የኢየሱስን አርዓያ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
20 ክርስቶስ የተወው መልካም ምሳሌ ሽማግሌዎች መንጋውን እንዲወዱና እሱን እንዲመስሉ ያነሳሳቸዋል። (ዮሐ. 13:12-15) ኢየሱስ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በተመለከተ ደቀ መዛሙርቱን ስላስተማረበት መንገድ ስናነብ ልባችን በደስታ ይሞላል። ትሕትና በማሳየት ረገድ የተወው ምሳሌ የደቀ መዛሙርቱን ልብ በመንካቱ እነሱም በበኩላቸው ‘ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው በትሕትና እንዲያስቡ’ አነሳስቷቸዋል። (ፊልጵ. 2:3) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ሲሆን እነሱም በተራቸው “ለመንጋው ምሳሌ” ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።
21. ሽማግሌዎች ወደፊት ምን ሽልማት እንደሚያገኙ መጠበቅ ይችላሉ?
21 ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች የሰጠውን ማሳሰቢያ ያጠቃለለው ከፊታቸው የተዘረጋላቸውን ተስፋ በመጥቀስ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:4ን አንብብ።) ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር “የማይጠፋ የክብር አክሊል” ይቀበላሉ። ‘የሌሎች በጎች’ አባል የሆኑት የበታች እረኞች ደግሞ በምድር ላይ የሚኖሩትን የአምላክ በጎች ‘በእረኞች አለቃ’ አገዛዝ ሥር ሆነው የመጠበቅ መብት ይኖራቸዋል። (ዮሐ. 10:16) የሚቀጥለው ርዕስ ደግሞ የጉባኤው አባላት፣ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር እንዲሰጡ የተሾሙ ወንድሞችን መደገፍ የሚችሉባቸውን መንገዶች ያብራራል።
ለክለሳ ያህል
• ጴጥሮስ አብረውት የሚሠሩትን ሽማግሌዎች በአደራ የተሰጣቸውን የአምላክ መንጋ እንዲጠብቁ ማሳሰቡን ተገቢ ሆኖ ያገኘው ለምንድን ነው?
• እረኛ የሆኑት ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የታመሙትን ሊጠብቋቸው የሚገባው እንዴት ነው?
• ሽማግሌዎች በአደራ የተሰጣቸውን የአምላክ መንጋ እንደ እረኛ በመሆን እንዲጠብቁ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንት ዘመን እንደነበሩ እረኞች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም በአደራ የተሰጧቸውን “በጎች” መጠበቅ ይኖርባቸዋል