ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ተጠንቀቁ!
“በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ።”—2 ጴጥሮስ 2:1
1. ይሁዳ ስለ ምን ነገር ሊጽፍ አስቦ ነበር? ርዕሰ ጉዳዩንስ የቀየረው ለምንድን ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሐሰተኛ አስተማሪዎች መነሳታቸው በጣም አስደንጋጭ ነገር ነበር! (ማቴዎስ 7:15፤ ሥራ 20:29, 30) የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ይሁዳ ይህንን ሁኔታ ተገንዝቦ ነበር። ለመሰል አማኞች ‘አብረው ስለሚካፈሉት መዳን’ ሊጽፍላቸው አስቦ እንደነበር ከገለጸ በኋላ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት [“እምነት፣” NW] እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” ሲል ተናግሯል። ይሁዳ ርዕሰ ጉዳዩን የቀየረው ለምንድን ነው? “አንዳንዶች ሰዎች [ወደ ጉባኤዎች] ሾልከው ገብተዋልና፤ . . . የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል።—ይሁዳ 3, 4
2. ሁለተኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 2 እና ይሁዳ በጣም ተመሳሳይ የሆኑት ለምንድን ነው?
2 ይሁዳ መልእክቱን የጻፈው ጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክቱን ከጻፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ይሁዳ ከጴጥሮስ ደብዳቤ ጋር ትውውቅ እንደነበረው ምንም አያጠራጥርም። ይሁዳ ጥብቅ ማሳሰቢያ በሰጠበት ደብዳቤው ውስጥ ከጴጥሮስ መልእክት ጋር የሚመሳሰሉ ብዙ ሐሳቦች ገልጿል። ስለዚህ 2 ጴጥሮስ ምዕራፍ ሁለትን እየመረመርን ስንሄድ ከይሁዳ ደብዳቤ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል እንመለከታለን።
የሐሰት ትምህርቶች የሚያስከትሉት ውጤት
3. ጴጥሮስ እንደገና እንደሚፈጸም የተናገረለት ጥንት የተፈጸመ ምን ነገር አለ?
3 ጴጥሮስ ወንድሞቹ ትንቢታዊውን ቃል በትኩረት እንዲከታተሉ ካሳሰበ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል [በጥንቱ እስራኤል መካከል] ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ።” (2 ጴጥሮስ 1:14–2:1) ጥንት የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች እውነተኛ ትንቢቶችን ተቀብለው የነበረ ቢሆንም የሐሰተኛ ነቢያትን የሚበክሉ ትምህርቶች መቋቋም አስፈልጓቸው ነበር። (ኤርምያስ 6:13, 14፤ 28:1-3, 15) ኤርምያስ “በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ” ሲል ጽፏል።—ኤርምያስ 23:14
4. ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጥፋት የሚገባቸው ለምንድን ነው?
4 ጴጥሮስ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን እንደሚያደርጉ ሲገልጽ “እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ [ኢየሱስ ክርስቶስን] እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 2:1፤ ይሁዳ 4) እንደምናውቀው እንዲህ ዓይነቱ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ኑፋቄ የዛሬዋን ሕዝበ ክርስትና አፍርቷል። ጴጥሮስ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በእርግጥም ጥፋት የሚገባቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል” ብሏል።—2 ጴጥሮስ 2:2
5. የሐሰት አስተማሪዎች ለምን ነገር ተጠያቂ ናቸው?
5 እስቲ አስበው! ሐሰተኛ አስተማሪዎች በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት ከጉባኤ አባላት ብዙዎች ነውረኛ ድርጊት ይፈጽማሉ። “ነውር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ስድነት፣ ጋጠ ወጥነት፣ መማገጥ እንዲሁም ኃፍረት የለሽ አድራጎት የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ጴጥሮስ ቀደም ሲል ክርስቲያኖች “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት [“ምግባረ ብልሹነት፣” NW]” እንዳመለጡ ተናግሮ ነበር። (2 ጴጥሮስ 1:4) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ወደዚያ ምግባረ ብልሹነት ይመለሱ ነበር፤ ለዚህ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች በጉባኤዎቹ ውስጥ የነበሩት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ናቸው! ከዚህ የተነሣ የእውነት መንገድ ይሰደባል። እንዴት የሚያሳዝን ነው! ይህ ጉዳይ ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አኗኗራችን ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን ሊያስመሰግን ወይም ደግሞ ሊያስነቅፍ እንደሚችል ፈጽሞ መዘንጋት አይገባንም።—ምሳሌ 27:11፤ ሮሜ 2:24
የሐሰት ትምህርቶችን ማስገባት
6. ሐሰተኛ አስተማሪዎችን የሚያነሳሳቸው ነገር ምንድን ነው? የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘትስ የሚጣጣሩት እንዴት ነው?
6 የሐሰት አስተማሪዎች ብልሹ የሆነ ሐሳባቸውን ወደ ጉባኤው እንዴት እንደሚያስገቡ ማስተዋላችን ጥበብ ይሆናል። ጴጥሮስ በመጀመሪያ ትምህርታቸውን በረቀቀ መንገድ በስውር አሹልከው እንደሚያስገቡ ተናግሯል። አክሎም “የሚሸነግሉ ቃላት በመናገር ለራሳቸው ምኞት መጠቀሚያ ያደርጓችኋል” (NW) ብሏል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል “በመሠሪ ንግግር እናንተን ለማግባባት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ” በማለት የሐሰት አስተማሪዎችን የሚያነሳሳቸው የራስ ወዳድነት ምኞች እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። በተመሳሳይም የጄምስ ሞፋት ትርጉም ይህንኑ ጥቅስ “የሚያባብሉ ቃላት በመናገር ከመጠን በላይ ለሚጓጉለት ነገር መጠቀሚያ ያደርጓችኋል” ሲል ተርጉሞታል። (2 ጴጥሮስ 2:1, 3) የሐሰት አስተማሪዎች የሚናገሩት ነገር በመንፈሳዊ ንቁ ላልሆነ ሰው እውነት ሊመስል ይችላል፤ ይሁን እንጂ ንግግራቸው ሰዎች የስስት ፍላጎታቸውን እንዲያራምዱላቸው ‘ለማግባባት’ ሲባል በዘዴ የታቀደ ነው።
7. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ገንኖ የነበረው ፍልስፍና ምንድን ነው?
7 የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሐሰት አስተማሪዎች በወቅቱ የነበረው ዓለማዊ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሰዎች እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። የጴጥሮስ መልእክት በተጻፈበት ጊዜ ግኖስቲሲዝም የሚባል ፍልስፍና እየገነነ መጥቶ ነበር። ግኖስቲኮች ቁስ አካል ሁሉ ክፉ ሲሆን መልካም የሆነው ከመንፈስ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ብቻ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ከዚህ የተነሣ አንዳንዶቹ፣ አንድ ሰው በሰብዓዊ አካሉ የሚፈጽመው ነገር ምንም ለውጥ አያመጣም ይሉ ነበር። ከጊዜ በኋላም ሰው ይህንን አካሉን ይዞ አይቀጥልም ማለት ጀመሩ። ስለዚህ የጾታ ኃጢአቶችን ጨምሮ በሥጋ የሚሠሩ ኃጢአቶች ያን ያህል ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች አይደሉም ብለው ደምድመዋል። እንደዚህ ያሉት አስተሳሰቦች ክርስቲያን ነን በሚሉት አንዳንዶች ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድሩ አይቀሩም።
8, 9. (ሀ) አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች በየትኛው የተዛባ አስተሳሰብ ተነክተው ነበር? (ለ) እንደ ይሁዳ አገላለጽ አንዳንዶች በጉባኤዎች ውስጥ ምን ያደርጉ ነበር?
8 “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ጸጋ” ወይም “ይገባናል የማንለው ደግነት” “የሚሰጠውን ትምህርት የሚያጣምሙ ሰዎች” እንደነበሩ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ተናግረዋል። (ኤፌሶን 1:5-7 NW) እንደ እኚህ ምሁር አባባል ከሆነ አንዳንዶቹ እንዲህ የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው:- “የአምላክ [ይገባናል የማንለው ደግነት] ኃጢአትን ሁሉ ለመሸፈን ይችላል ብላችሁ ታምናላችሁን? . . . እንግዲያስ የአምላክ [ይገባናል የማንለው ደግነት] ኃጢአትን ሁሉ ሊደመስስ ስለሚችል ኃጢአት መሥራታችንን እንቀጥል። እንዲያውም የአምላክ [ይገባናል የማንለው ደግነት] ጥቅም ላይ ለመዋል ይበልጥ አጋጣሚ የሚያገኘው ይበልጥ ኃጢአት ስንሠራ ነው።” ከዚህ የከፋ ምን ጠማማ አስተሳሰብ ይኖራል?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ምሕረት በሚመለከት የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ሰዎች ገጥመውት ስለነበር እንደሚከተለው ሲል ጠይቋል:- “ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን?” ጨምሮም “ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን?” ሲል ጠይቋል። ጳውሎስ ሁለቱንም ጥያቄዎች በሚመለከት “ከቶ አይሆንም” [የ1980 ትርጉም] ሲል ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። (ሮሜ 6:1, 2, 15) ይሁዳ እንዳስተዋለው ‘ይገባናል የማንለውን የአምላክን ደግነት በሴሰኝነት የሚለውጡ’ ሰዎች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንደገለጸው የእነዚህ ሰዎች ‘ጥፋት አያንቀላፋም።’—ይሁዳ 4፤ 2 ጴጥሮስ 2:3
የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች
10, 11. ጴጥሮስ የጠቀሳቸው ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
10 ጴጥሮስ ሆነ ብለው ኃጢአት በሚሠሩ ሰዎች ላይ አምላክ እርምጃ እንደሚወስድ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ከቅዱሳን ጽሑፎች ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ጠቅሷል። በመጀመሪያ “እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት” አልራራላቸውም ሲል ጽፏል። ይሁዳ እንደገለጸው እነዚህ የሰማይ ‘መኖሪያቸውን የተዉና አለቅነታቸውን ያልጠበቁ’ መላእክት ናቸው። ከጥፋት ውኃው በፊት ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ሥጋዊ አካል ለብሰው ወደ ምድር መጡ። ተገቢ ያልሆነና ከተፈጥሮአቸው ውጭ የሆነ ነገር በመፈጸማቸው ወደ “እንጦሮጦስ” ተጥለዋል ወይም የይሁዳ መጽሐፍ እንደሚለው “በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።”—2 ጴጥሮስ 2:4 የ1980 ትርጉም፤ ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:1-3
11 ቀጥሎም ጴጥሮስ በኖኅ ዘመን ስለነበሩት ሰዎች ጠቅሷል። (ዘፍጥረት 7:17-24) በኖኅ ዘመን አምላክ “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ . . . በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ” እንዳወረደ ገለጸ። በመጨረሻም ጴጥሮስ “ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ” እንዲሆኑ “ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ” እንደፈረደባቸው ጽፏል። ይሁዳም እነዚህ ሰዎች ‘ዝሙትን እንዳደረጉና ሌላን ሥጋ እንደተከተሉ’ በመግለጽ ተጨማሪ መረጃ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 2:5, 6፤ ይሁዳ 7) ወንዶቹ ከሴቶች ጋር ልቅ የጾታ ግንኙነት ከመፈጸምም አልፈው ወንዶችንና ምናልባትም እንስሳትን ሳይቀር በጾታ ተገናኝተዋል።—ዘፍጥረት 19:4, 5፤ ዘሌዋውያን 18:22-25
12. ጴጥሮስ እንደገለጸው የጽድቅ አኗኗር የሚክሰው እንዴት ነው?
12 ሆኖም ይሖዋ የታመኑ ሆነው የሚያገለግሉትን ሰዎች የሚክስ አምላክ መሆኑን ጴጥሮስ ሳይጠቅስ አላለፈም። ለምሳሌ ያህል የጥፋት ውኃ ባመጣበት ጊዜ “ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን” እንዳዳነው ገልጿል። በሰዶም ጊዜም ‘ጻድቁን ሎጥ’ ይሖዋ እንዴት እንዳዳነው ከገለጸ በኋላ እንዲህ በማለት ደምድሟል:- “እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።”—2 ጴጥሮስ 2:5, 7-9
ቅጣት የሚያስከትሉ ድርጊቶች
13. ለፍርድ የተጠበቁት በተለይ እነማን ናቸው? የሚያልሙትስ ስለምን ነገር ሊሆን ይችላል?
13 ጴጥሮስ “በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን” የአምላክ ፍርድ ይጠብቃቸዋል ሲል ለይቶ ተናግሯል። ጴጥሮስ “ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም” ባለ ጊዜ እንዴት ተናድዶ እንደነበር መገመት አይከብደንም። ይሁዳም “እነዚህ ሰዎች . . . እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ . . . ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 2:10፤ ይሁዳ 8) ሕልማቸው የጾታ ብልግና የመፈጸም ምኞታቸውን ወደ ግቡ እንዲያደርሱ የሚያበረታታ ርኩስ የጾታ ቅዠት ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘ጌትነትን የሚንቁትና’ ‘ሥልጣን ያላቸውን የሚሳደቡት’ እንዴት ነው?
14. የሐሰት አስተማሪዎች ‘ጌትነትን የሚንቁትና’ ‘ሥልጣንን የማያከብሩት’ በምን መንገድ ነው?
14 ይህንን የሚያደርጉት ከመለኮታዊ ምንጭ የተገኘውን ሥልጣን በማቃለል ነው። ክርስቲያን ሽማግሌዎች ታላቁን ባለ ሥልጣን ይሖዋ አምላክንና ልጁን የሚወክሉ በመሆናቸው እነርሱም የተወሰነ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ጴጥሮስ ራሱ ስህተት ሠርቶ እንደነበር ሁሉ ስህተት እንደሚሠሩ አይካድም፤ ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች የጉባኤው አባላት ለእነዚህ ሰዎች እንዲታዘዙ አጥብቀው ያሳስባሉ። (ዕብራውያን 13:17) የሚፈጽሙት ስህተት እነርሱን ለመሳደብ ምክንያት አይሆንም። ጴጥሮስ “መላእክት . . . በጌታ ፊት በእነርሱ [በሐሰት አስተማሪዎች] ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም” ብሏል፤ ይሁን እንጂ ለእነዚህ ሰዎች ይህም ሲያንሳቸው ነበር። ጴጥሮስ በመቀጠል “እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ሆነው፣ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ” ብሏል።—2 ጴጥሮስ 2:10-13
“ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ”
15. የሐሰት አስተማሪዎች የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው? የማባበያ ወጥመዳቸውን የሚዘረጉት የት ነው?
15 እነዚህ ብልሹ ሰዎች ‘በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ቢቆጥሩትም’ “ነውረኞችና ርኵሳን” እንዲሁም በተንኮል የተሞሉ ናቸው። ጴጥሮስ ‘በቃላት ሽንገላ’ ‘ውስጥ ውስጡን’ እንደሚንቀሳቀሱ ቀደም ብሎ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 2:1, 3, 13) ሽማግሌዎቹ የአምላክን የሥነ ምግባር ደረጃዎች ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት ፊት ለፊት አይቃወሙ ወይም ደግሞ የጾታ ምኞታቸውን ለማርካት በግልጽ አይሯሯጡ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ግን ጴጥሮስ እንዳለው “ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ [“በአታላይ ትምህርቶቻቸው ከልክ በላይ ይደሰታሉ፣” NW]።” ይሁዳም እንዲሁ “እነዚህ ሰዎች በፍቅር ግብዣችሁ ከውኃ በታች እንደተሠወሩ ዓለቶች ናቸው” ሲል ጽፏል። (ይሁዳ 12 NW) አዎን፣ ከውኃ በታች እንደተሰወሩና የአንድን ጀልባ የታችኛውን ክፍል በመቅደድ ያልጠረጠሩ ባሕረተኞችን ለመስጠም እንደሚዳርጉ የሾሉ ዓለቶች የሐሰት አስተማሪዎችም ‘በፍቅር ግብዣዎች’ ወቅት ወዳጅ መስለው ቀርበው የግብዝነት ፍቅር በማሳየት ያልጠረጠሩትን ሰዎች ያበላሻሉ።
16. (ሀ) “የፍቅር ግብዣዎች” የተባሉት ምንድን ናቸው? ዛሬስ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰዎች የትኞቹን ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ይጠቀማሉ? (ለ) የሐሰት አስተማሪዎች ዓይናቸውን የሚጥሉት እነማን ላይ ነው? እንግዲያውስ እነዚህ ሰዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
16 እነዚህ “የፍቅር ግብዣዎች” የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አንድ ላይ ተሰባስበው እየተመገቡ የሚጫወቱባቸው አጋጣሚዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ ጊዜ ለሠርግ፣ ሽርሽር ለመሄድ ወይም ምሽት ላይ ሰብሰብ ብለው ለመጫወት ይገናኛሉ። ብልሹ የሆኑ ሰዎች እንደነዚህ ያሉትን አጋጣሚዎች ሰለባዎቻቸውን ለማጥመድ የሚጠቀሙባቸው እንዴት ነው? ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ምንዝር የሞላባቸው . . . ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ።” ‘መመኘትን የለመደ ልባቸውን’ በመንፈሳዊ ባልጸኑት ሰዎች ላይ በሌላ አባባል እውነትን ሙሉ በሙሉ የራሳቸው ማድረግ በተሳናቸው ሰዎች ላይ ይተክላሉ። እንግዲያውስ በጴጥሮስ ዘመን ከደረሰው ነገር ትምህርት በመውሰድ ተጠንቀቁ! ንጹህ ያልሆኑ ማባበያዎችን ተቋቋሙ፤ በጾታ የሚያባብላችሁ ሰው መልክ ወይም ቁመና አያታልላችሁ!—2 ጴጥሮስ 2:14
‘የበለዓም መንገድ’
17. “የበለዓም መንገድ” ምንድን ነበር? 24,000 የሚያክሉትን እስራኤላውያንንስ የነካቸው እንዴት ነው?
17 እነዚህ “የተረገሙ” ሰዎች እውነት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የቆዩ ናቸው። አሁንም በጉባኤ ውስጥ ንቁ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ። ግን ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ።” (2 ጴጥሮስ 2:14, 15) ነቢዩ በለዓም የተከተለው መንገድ ለግል ጥቅሙ ሲል ሌሎች በብልግና ወጥመድ እንዲያዙ ምክር መስጠት ነበር። ከዚህም የተነሣ ብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች በሞዓባውያን ሴቶች ተታልለው በፈጸሙት የብልግና ድርጊት ምክንያት 24,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።—ዘኁልቁ 25:1-9፤ 31:15, 16፤ ራእይ 2:14
18. በለዓም ከጀመረው ጎዳና ላለመመለስ ምን ያህል ግትር ነበር? በለዓም የደረሰበትስ ነገር ለሐሰት አስተማሪዎች ምን መልእክት ያስተላልፋል?
18 ጴጥሮስ አህያው ተናግሮ በለዓምን እንዳገደው ገልጿል፤ ይሁንና በለዓም ‘የዓመፃን ገንዘብ እጅግ ከመውደዱ’ የተነሣ ይህንን እያየም ‘ከዕብደት ጎዳናው’ አልተመለሰም። (2 ጴጥሮስ 2:15, 16) እንዴት ያለ ክፋት ነው! እንደ በለዓም የአምላክን ሕዝቦች የጾታ ብልግና እንዲፈጽሙ በመፈተን ለመበከል ለሚጥሩ ሰዎች ወዮላቸው! በለዓም በፈጸመው ክፋት ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል፤ ይህም የእርሱን መንገድ የሚከተሉ ሁሉ ምን እንደሚደርስባቸው የሚያሳይ መቀጣጫ ነው።—ዘኁልቁ 31:8
ዲያብሎሳዊ ማባበያዎቻቸው
19, 20. (ሀ) እንደ በለዓም ያሉት ሰዎች ከምን ነገር ጋር ተመሳስለዋል? (ለ) የሚያስቱት ማንን ነው? ለምንስ? (ሐ) ማባበያዎቻቸው ዲያብሎሳዊ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? ከእነዚህስ ማባቢያዎች ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ጴጥሮስ እንደ በለዓም ስላሉት ሰዎች ሲገልጽ “እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው” ብሏል። ውኃ ለተጠማ አንድ የበረሃ ተጓዥ ባዶ የውኃ ጉድጓድ ማግኘት ሞቱን የሚያረዳው ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ ነገሮች ጋር እንደሚመሳሰሉ ሆነው የተገለጹት ሰዎች ‘ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም ቢጠበቅላቸው’ ምንም አያስገርምም! ጴጥሮስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፣ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ።” ጴጥሮስ እንዳለው “ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው:- አርነት ትወጣላችሁ እያሉ” ተሞክሮ የሌላቸውን ያታልላሉ።—2 ጴጥሮስ 2:17-19፤ ገላትያ 5:13
20 እነዚህ ብልሹ አስተማሪዎች የሚጠቀሙባቸው ማባበያዎች ዲያብሎሳዊ ናቸው። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ይሉ ይሆናል:- ‘አምላክ ደካማ እንደሆንና ስሜታችን እንደሚያሸንፈን ያውቃል። ስለዚህ ለምኞታችን ተገዥ ሆነን የጾታ ፍላጎታችንን ብናረካ አምላክ ይምረናል። ኃጢአታችንን ከተናዘዝን መጀመሪያ ወደ እውነት ስንመጣ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ይቅር ይለናል።’ ሔዋን ኃጢአት ብትሠራም ቅጣት እንደማያገኛት ዲያብሎስ ተስፋ ሲሰጣት ተመሳሳይ አቀራረብ መጠቀሙ እንደነበር አስታውስ። በአምላክ ላይ ኃጢአት ብትሠራ ዓይኗ እንደሚከፈትና ነፃነት እንደምታገኝ ነግሯታል። (ዘፍጥረት 3:4, 5) በጉባኤ ውስጥ የሚመላለስ እንዲህ ዓይነት ብልሹ ሰው ካጋጠመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ላላቸው ወንዶች ስለዚህ ሰው በማሳወቅ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከችግር የመጠበቅ ግዴታ አለብን።—ዘሌዋውያን 5:1
በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ጥበቃ ማግኘት
21-23. (ሀ) ትክክለኛውን እውቀት በሥራ ላይ ሳያውሉ መቅረት የሚያስከትላቸው ውጤቶች ምንድን ናቸው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የሚብራራው ጴጥሮስ የጠቀሰው ሌላ ችግር ምንድን ነው?
21 ጴጥሮስ ቀደም ሲል ‘ለሕይወትና ለአምላክ ያደሩ ለመሆን’ በጣም አስፈላጊ ነው ያለውን ትክክለኛ እውቀት አለማግኘት የሚያስከትለውን ውጤት በመግለጽ ይኼኛውን የደብዳቤውን ክፍል ደምድሟል። (2 ጴጥሮስ 1:2, 3, 8) እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ [“ትክክለኛ፣” NW] እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፣ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል።” (2 ጴጥሮስ 2:20፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) እንዴት ያሳዝናል! በጴጥሮስ ዘመን የነበሩት እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከጾታ ለሚያገኙት ቅጽበታዊ ደስታ ሲሉ የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት የማግኘት ውድ ተስፋቸውን አሽቀንጥረው ጥለዋል።
22 በመሆኑም ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ኪመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፣ ደግሞ:- የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።”—2 ጴጥሮስ 2:21, 22፤ ምሳሌ 26:11
23 ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ያጋጠማቸው ሌላው ችግር ዛሬ አንዳንዶቹን ከሚገጥማቸው ጋር የሚመሳሰል ነው። በዚያን ጊዜ አንዳንዶች ተስፋ የተደረገበት የክርስቶስ መገኘት የሚመጣ መስሎ ባለመታየቱ ያጉረመርሙ እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ ይህን ጉዳይ በሚመለከት የተናገረውን ነገር እስቲ እንመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ ጴጥሮስ ምን ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ጠቅሷል?
◻ የሐሰት አስተማሪዎች ‘ጌትነትን የሚንቁት’ እንዴት ነው?
◻ የበለዓም መንገድ ምንድን ነው? የእርሱን ጎዳና ለመከተል የሚጥሩ ሰዎች ሌሎችን እንዴት ለማሳሳት ይሞክሩ ይሆናል?
◻ ትክክለኛውን እውቀት በሥራ ላይ ሳያውሉ መቅረት የሚያስከትላቸው ውጤቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በለዓም የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ነው