የጥናት ርዕስ 41
ከጴጥሮስ ሁለት ደብዳቤዎች የምናገኛቸው ትምህርቶች
“ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም።”—2 ጴጥ. 1:12
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
ማስተዋወቂያa
1. ሐዋርያው ጴጥሮስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በመንፈስ መሪነት ምን አደረገ?
ሐዋርያው ጴጥሮስ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። ከኢየሱስ ጋር አብሮ ተጉዟል፤ አዳዲስ የስብከት መስኮችን ከፍቷል፤ እንዲሁም የበላይ አካል አባል ሆኖ አገልግሏል። አሁን ወደ ሕይወቱ መገባደጃ እየተቃረበ ነው። በዚህ ወቅት ይሖዋ ተጨማሪ ሥራ ሰጠው። ከ62-64 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በመንፈስ ተመርቶ ሁለት ደብዳቤዎችን ጻፈ። ደብዳቤዎቹ 1 ጴጥሮስ እና 2 ጴጥሮስ ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ደብዳቤዎች እሱ ከሞተ በኋላ ክርስቲያኖችን እንደሚረዷቸው ተስፋ አድርጎ ነበር።—2 ጴጥ. 1:12-15
2. የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ወቅታዊ ነበሩ የምንለው ለምንድን ነው?
2 ጴጥሮስ በመንፈስ ተመርቶ ደብዳቤዎቹን በጻፈበት ወቅት የእምነት አጋሮቹ ‘በልዩ ልዩ ፈተናዎች ተጨንቀው’ ነበር። (1 ጴጥ. 1:6) ክፉ ሰዎች የሐሰት ትምህርትንና ርኩስ ምግባርን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለማስገባት እየሞከሩ ነበር። (2 ጴጥ. 2:1, 2, 14) በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች “የሁሉም ነገር መጨረሻ” ቀርቦባቸዋል፤ ኢየሩሳሌምና የአይሁድ ሥርዓት በሮም ሠራዊት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል። (1 ጴጥ. 4:7) የጴጥሮስ ደብዳቤዎች፣ ክርስቲያኖች በወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በጽናት እንዲቋቋሙና ወደፊት ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እንዲዘጋጁ እንደረዷቸው ምንም ጥያቄ የለውም።b
3. ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸውን ደብዳቤዎች መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?
3 ጴጥሮስ ደብዳቤዎቹን የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች ቢሆንም ይሖዋ እነዚህ ደብዳቤዎች የቃሉ ክፍል እንዲሆኑ አድርጓል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜም ከእነዚህ ደብዳቤዎች ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ሮም 15:4) እኛም የምንኖረው ርኩስ ምግባር በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ስለሆነ ይሖዋን ማገልገል ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። በቅርቡ ደግሞ የአይሁድ ሥርዓት በጠፋበት ጊዜ ከነበረው የበለጠ መከራ እንደሚመጣ እንጠብቃለን። ጴጥሮስ በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ውስጥ አንዳንድ ወሳኝ ማሳሰቢያዎችን እናገኛለን። እነዚህ ማሳሰቢያዎች የይሖዋን ቀን በጉጉት እንድንጠብቅ፣ የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ እንዲሁም አንዳችን ለሌላው የጠለቀ ፍቅር እንድናዳብር ይረዱናል። በተጨማሪም እነዚህ ማሳሰቢያዎች፣ ሽማግሌዎች መንጋውን በሚገባ እንዲንከባከቡ ይረዷቸዋል።
በጉጉት ጠብቁ
4. በ2 ጴጥሮስ 3:3, 4 መሠረት እምነታችንን የሚያናጋ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ምንም ዓይነት እምነት በሌላቸው ሰዎች ተከበናል። ለበርካታ ዓመታት መጨረሻውን በጉጉት ስንጠባበቅ በመቆየታችን የተነሳ ተቃዋሚዎች ያሾፉብን ይሆናል። አንዳንድ ተቺዎች ደግሞ መጨረሻው ጨርሶ እንደማይመጣ ይናገራሉ። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4ን አንብብ።) አገልግሎት ላይ ያገኘነው ሰው፣ የሥራ ባልደረባችን ወይም የቤተሰባችን አባል እንዲህ ያለ ነገር ሲናገር ከሰማን እምነታችን ሊናጋ ይችላል። ጴጥሮስ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን እንደሚችል ተናግሯል።
5. የዚህን ሥርዓት መጨረሻ በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን ምንድን ነው? (2 ጴጥሮስ 3:8, 9)
5 አንዳንዶች ይሖዋ ይህን ሥርዓት ለማጥፋት እንደዘገየ ይሰማቸው ይሆናል። ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዱናል። ምክንያቱም ጴጥሮስ፣ ይሖዋ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከሰዎች አመለካከት በእጅጉ የተለየ እንደሆነ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:8, 9ን አንብብ።) በይሖዋ ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው። ይሖዋ ታጋሽ ነው፤ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። እሱ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ግን ይህ ሥርዓት ይጠፋል። የቀረውን ጊዜ ተጠቅመን ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች ምሥክርነት መስጠት መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
6. የይሖዋን ቀን ‘በአእምሯችን አቅርበን መመልከት’ የምንችለው እንዴት ነው? (2 ጴጥሮስ 3:11, 12)
6 ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን ‘በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ አበረታቶናል። (2 ጴጥሮስ 3:11, 12ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአዲሱ ዓለም ውስጥ በምናገኛቸው በረከቶች ላይ ከተቻለ በየቀኑ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። ንጹሕ አየር ስትተነፍሱ፣ ጤናማ ምግብ ስትመገቡ፣ ከሞት የተነሱ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ስትቀበሉ እንዲሁም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ለኖሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ ስታስተምሩ ይታያችሁ። በዚህ መልኩ ማሰላሰላችሁ የይሖዋን ቀን በጉጉት እንድትጠባበቁ እንዲሁም መጨረሻው መቅረቡን እንዳትዘነጉ ይረዳችኋል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ‘አስቀድመን ስላወቅን’ በሐሰተኛ አስተማሪዎች ‘ተታልለን አንወሰድም።’—2 ጴጥ. 3:17
የሰው ፍርሃትን አሸንፉ
7. የሰው ፍርሃት ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?
7 የይሖዋን ቀን በአእምሯችን አቅርበን የምንመለከት ከሆነ ምሥራቹን ለሌሎች ለመናገር እንነሳሳለን። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹን መናገር ሊከብደን ይችላል። ለምን? ለጊዜውም ቢሆን ለሰው ፍርሃት እጅ እንሰጥ ይሆናል። ጴጥሮስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ላይ ጴጥሮስ በፍርሃት ተሸንፎ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑን ሳይናገር ቀርቷል፤ ይባስ ብሎም ኢየሱስን “አላውቀውም” ብሎ በተደጋጋሚ ክዶታል። (ማቴ. 26:69-75) ያም ቢሆን ጴጥሮስ ራሱ “እነሱ የሚፈሩትን እናንተ አትፍሩ፤ ደግሞም አትሸበሩ” በማለት በልበ ሙሉነት ሊናገር ችሏል። (1 ጴጥ. 3:14) ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት የሰው ፍርሃትን ማሸነፍ እንደምንችል ዋስትና ይሰጡናል።
8. የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል? (1 ጴጥሮስ 3:15)
8 የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ ምን ይረዳናል? ጴጥሮስ “ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት” በማለት መልሱን ነግሮናል። (1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።) ይህም ጌታችንና ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ሥልጣንና ኃይል ላይ ማሰላሰልን ይጨምራል። ምሥራቹን ለሌሎች ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ ስታገኙ የምትፈሩ ወይም የምትጨነቁ ከሆነ ንጉሣችንን አስታውሱ። ክርስቶስ በሰማይ ላይ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መላእክት ተከቦ ሲገዛ በዓይነ ሕሊናችሁ ይታያችሁ። ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” እንደተሰጠው እንዲሁም “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር” እንደሚሆን አስታውሱ። (ማቴ. 28:18-20) ጴጥሮስ ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም ዘወትር ዝግጁ እንድንሆን አበረታቶናል። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ቦታ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠት ትፈልጋላችሁ? ምሥክርነት መስጠት ስለምትችሉበት አጋጣሚ አስቀድማችሁ አስቡ፤ እንዲሁም ምን ብላችሁ እንደምትናገሩ ተዘጋጁ። ይሖዋ የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ እንደሚረዳችሁ በመተማመን ድፍረት ለማግኘት ጸልዩ።—ሥራ 4:29
“የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ”
9. ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ፍቅር ሳያሳይ የቀረው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
9 ጴጥሮስ ፍቅር ማሳየት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተምሯል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ትእዛዝ በሰጠበት ወቅት ጴጥሮስ በቦታው ነበር። (ዮሐ. 13:34) ያም ቢሆን ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ በተጽዕኖ ተሸንፎ ከአሕዛብ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር መብላቱን አቁሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ ያደረገውን ነገር “የግብዝነት ድርጊት” በማለት ጠርቶታል። (ገላ. 2:11-14) ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ የሰጠውን እርማት ተቀብሎ በሥራ ላይ አውሎታል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ ብቻ ሳይሆን ፍቅር ልናሳይ እንደሚገባም ጭምር በሁለቱም ደብዳቤዎቹ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጿል።
10. “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” የሚመነጨው ከምንድን ነው? አብራራ። (1 ጴጥሮስ 1:22)
10 ጴጥሮስ ለእምነት አጋሮቻችን “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” ሊኖረን እንደሚገባ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 1:22ን አንብብ።) እንዲህ ያለው መዋደድ የሚመነጨው ‘ለእውነት ከመታዘዝ’ ነው። ይህ እውነት “አምላክ እንደማያዳላ” የሚገልጸውን ትምህርት ያካትታል። (ሥራ 10:34, 35) በጉባኤው ውስጥ ላሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ፍቅር እያሳየን ለሌሎቹ ግን የማናሳይ ከሆነ ኢየሱስ ስለ ፍቅር የሰጠውን ትእዛዝ ተከትለናል ሊባል አይችልም። እርግጥ ነው፣ እኛም እንደ ኢየሱስ ከአንዳንዶቹ ወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንቀራረብ ይሆናል። (ዮሐ. 13:23፤ 20:2) ሆኖም ጴጥሮስ ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “የወንድማማች መዋደድ” ማለትም በቤተሰብ ውስጥ ያለው ዓይነት ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ አሳስቦናል።—1 ጴጥ. 2:17
11. ሌሎችን ‘አጥብቆ ከልብ መውደድ’ ምን ይጨምራል?
11 ጴጥሮስ “እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቶናል። ‘አጥብቆ መዋደድ’ የሚለው አገላለጽ ፍቅር ማሳየት በሚከብደን ጊዜም ጭምር መዋደድን ያካትታል። ለምሳሌ አንድ ወንድም ቅር ቢያሰኘን ወይም በሆነ መንገድ ቢጎዳንስ? የሚቀናን ፍቅር ማሳየት ሳይሆን አጸፋውን መመለስ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጴጥሮስ አጸፋ መመለስ አምላክን እንደማያስደስተው ከኢየሱስ ተምሯል። (ዮሐ. 18:10, 11) ጴጥሮስ “ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 3:9) ሌሎችን አጥብቀን የምንወድ ከሆነ ጉዳት ላደረሱብን ሰዎችም ጭምር ደግነትና አሳቢነት ለማሳየት እንነሳሳለን።
12. (ሀ) የጠለቀ ፍቅር ሌላስ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል? (ለ) ውድ የሆነውን አንድነታችሁን ጠብቁ የሚለውን ቪዲዮ ስትመለከቱ ምን ለማድረግ ተነሳሳችሁ?
12 ጴጥሮስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ “የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ” በማለት ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል። እንዲህ ያለው ፍቅር ትናንሽ ስህተቶችን ብቻ ሳይሆን “የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥ. 4:8) ምናልባትም ጴጥሮስ ከበርካታ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ስለ ይቅር ባይነት የሰጠውን ትምህርት አስታውሶ ሊሆን ይችላል። በዚያ ወቅት ጴጥሮስ “[ወንድሜን] እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” ሲል በጣም ይቅር ባይ እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ “እስከ 77 ጊዜ” ማለትም ያለገደብ ይቅር ማለት እንዳለበት አስተምሮታል። (ማቴ. 18:21, 22) ይህ ትምህርት እኛንም ይመለከታል። ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ከብዷችሁ ከሆነ አይዟችሁ! ፍጹማን ያልሆኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ይቅር ማለት የከበዳቸው ጊዜ አለ። ዋናው ነገር ከዚህ በኋላ ወንድማችሁን ይቅር ለማለት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዳችሁና ከእሱ ጋር ሰላም መፍጠራችሁ ነው።c
ሽማግሌዎች፣ መንጋውን ተንከባከቡ
13. ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መንከባከብ ከባድ እንዲሆንባቸው የሚያደርገው ምንድን ነው?
13 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያለውን ነገር ፈጽሞ እንዳልረሳው ምንም ጥያቄ የለውም፤ “ግልገሎቼን ጠብቅ” ብሎት ነበር። (ዮሐ. 21:16) አንተም ሽማግሌ ከሆንክ፣ ይህ መመሪያ አንተንም እንደሚመለከት ታውቃለህ። ይሁንና አንድ ሽማግሌ ይህን አስፈላጊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ጊዜ ማግኘት ሊከብደው ይችላል። ሽማግሌዎች ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው የቤተሰባቸውን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ነው። ከዚህም ሌላ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል እንዲሁም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ክፍል ተዘጋጅተው ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ወይም በአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል ውስጥ ሥራ ሊሰጣቸው ይችላል። በእርግጥም ሽማግሌዎች በጣም ብዙ ሥራ አላቸው!
14. ሽማግሌዎች መንጋውን እንዲንከባከቡ ምን ሊያበረታታቸው ይችላል? (1 ጴጥሮስ 5:1-4)
14 ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች “የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:1-4ን አንብብ።) ሽማግሌ ከሆንክ፣ ወንድሞችህንና እህቶችህን እንደምትወዳቸው እንዲሁም እነሱን መንከባከብ እንደምትፈልግ እርግጠኞች ነን። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ በሥራ ከመወጠርህ ወይም ከመድከምህ የተነሳ ይህን ኃላፊነትህን መወጣት እንደማትችል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? ስሜትህን አውጥተህ ለይሖዋ ንገረው። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሚያገለግል ማንም ቢኖር አምላክ በሚሰጠው ኃይል ተማምኖ ያገልግል።” (1 ጴጥ. 4:11) ወንድሞችህንና እህቶችህን የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ችግሮች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሊፈቱ አይችሉ ይሆናል። ይሁንና “የእረኞች አለቃ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንተ ይበልጥ ሊረዳቸው እንደሚችል አትዘንጋ፤ በአሁኑ ጊዜም ሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሊረዳቸው ይችላል። አምላክ ከሽማግሌዎች የሚጠብቅባቸው ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ፣ እንደ እረኛ እንዲንከባከቧቸው እንዲሁም ‘ለመንጋው ምሳሌ እንዲሆኑ’ ብቻ ነው።
15. አንድ ወንድም ለመንጋው እረኝነት የሚያደርገው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 ለበርካታ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለው ዊልያም የእረኝነትን አስፈላጊነት ተገንዝቧል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጀመረበት ወቅት እሱና አብረውት የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች በቡድናቸው ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን አስፋፊ በየሳምንቱ ለማነጋገር ጥረት አደረጉ። ዊልያም ምክንያቱን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ወንድሞች ብቻቸውን ቤት ውስጥ ከመቀመጥ ውጭ ሌላ የሚያደርጉት ነገር አልነበራቸውም። በመሆኑም አፍራሽ አስተሳሰብ በቀላሉ ሊጠናወታቸው ይችላል።” አንድ አስፋፊ ችግር ሲያጋጥመው ዊልያም ግለሰቡ ያሳሰበውንና የሚያስፈልገውን ነገር ለማወቅ በጥሞና ያዳምጠዋል። ከዚያም ግለሰቡን የሚያበረታታ ሐሳብ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ የሚጠቀመው ድረ ገጻችን ላይ ያሉትን ቪዲዮዎች ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት እረኝነት ማድረግ ያስፈልጋል። ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። የይሖዋ በጎች በእውነት ውስጥ እንዲቀጥሉ ለመርዳትም እረኝነት በማድረግ ተመሳሳይ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።”
ይሖዋ ሥልጠናችሁን እንዲያጠናቅቀው ፍቀዱ
16. ከጴጥሮስ ደብዳቤዎች የምናገኛቸውን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
16 እስካሁን የተመለከትነው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች የምናገኛቸውን ጥቂት ትምህርቶች ብቻ ነው። ምናልባትም በሆነ አቅጣጫ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ አስተውላችሁ ይሆናል። ለምሳሌ በአዲሱ ዓለም በምናገኛቸው በረከቶች ላይ ይበልጥ ማሰላሰል ትፈልጋላችሁ? በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ቦታ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ግብ አውጥታችኋል? ለወንድሞቻችሁና ለእህቶቻችሁ ይበልጥ የጠለቀ ፍቅር ማሳየት የምትችሉባቸውን መንገዶች አግኝታችኋል? ሽማግሌዎች፣ የይሖዋን በጎች በፈቃደኝነትና በጉጉት ለመንከባከብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጋችኋል? ራሳችሁን በሐቀኝነት ስትመረምሩ በአንዳንድ አቅጣጫዎች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ትገነዘቡ ይሆናል። ያም ቢሆን ተስፋ አትቁረጡ። “ጌታ ደግ” ነው፤ ማሻሻያ እንድታደርጉ ይረዳችኋል። (1 ጴጥ. 2:3) ጴጥሮስ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “አምላክ . . . ራሱ ሥልጠናችሁ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።”—1 ጴጥ. 5:10
17. ከጸናንና ይሖዋ እንዲያሠለጥነን ከፈቀድን ምን ውጤት እናገኛለን?
17 ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ከአምላክ ልጅ አጠገብ መቆም እንኳ እንደማይገባው ተሰምቶት ነበር። (ሉቃስ 5:8) ሆኖም ይሖዋና ኢየሱስ ባደረጉለት ፍቅራዊ ድጋፍ ጴጥሮስ የክርስቶስ ተከታይ ሆኖ መጽናት ችሏል። በመሆኑም ጴጥሮስ “ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት” ለመግባት ብቁ ሆኗል። (2 ጴጥ. 1:11) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ሽልማት ነው! እናንተም እንደ ጴጥሮስ ከጸናችሁና ይሖዋ እንዲያሠለጥናችሁ ከፈቀዳችሁ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ታገኛላችሁ። “የእምነታችሁ ግብ ላይ” መድረስ ይኸውም ‘ራሳችሁን ማዳን’ ትችላላችሁ።—1 ጴጥ. 1:9
መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ
a ጴጥሮስ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች የምናገኛቸው ትምህርቶች ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚረዱን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ሽማግሌዎች መንጋውን የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ።
b በፓለስቲና የሚኖሩት ክርስቲያኖች በ66 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ላይ የመጀመሪያው ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ሁለቱም የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ደርሰዋቸው የነበረ ይመስላል።
c በjw.org ላይ የሚገኘውን ውድ የሆነውን አንድነታችሁን ጠብቁ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።