የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የያዕቆብና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ካለፈ ወደ 30 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ለመንፈሳዊ እስራኤል ‘አሥራ ሁለት ነገዶች’ ደብዳቤ ጻፈ። (ያዕ. 1:1) ደብዳቤውን የጻፈበት ዓላማ በእምነት ጠንካሮች እንዲሆኑና ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው ጽናት እንዲያሳዩ ለማሳሰብ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በጉባኤዎቹ ውስጥ ተከስተው የነበሩትን አሳሳቢ ሁኔታዎች ለማስተካከል የሚረዳ ምክር ሰጥቷል።
የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ በ64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በክርስቲያኖች ላይ ካካሄደው የስደት ዘመቻ ትንሽ ቀደም ብሎ ሐዋርያው ጴጥሮስ በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ ለማበረታታት የመጀመሪያ ደብዳቤውን ለክርስቲያኖች ጻፈ። የመጀመሪያ ደብዳቤውን ከጻፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ የእምነት ባልንጀሮቹ ለአምላክ ቃል ትኩረት እንዲሰጡ ያበረታታቸው ከመሆኑም ሌላ ስለ መጪው የይሖዋ ቀን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። በእርግጥም ያዕቆብና ጴጥሮስ የጻፏቸው ደብዳቤዎች ለያዟቸው መልእክቶች ትኩረት በመስጠት ጥቅም ማግኘት እንችላለን።—ዕብ. 4:12
አምላክ ‘በእምነት ለሚለምኑት’ ጥበብ ይሰጣል
ያዕቆብ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም . . . የሕይወትን አክሊል ያገኛል” ሲል ጽፏል። ይሖዋ ‘በእምነት ለሚለምኑት’ ሰዎች በፈተና ለመጽናት የሚያስችላቸውን ጥበብ ይሰጣቸዋል።—ያዕ. 1:5-8, 12
በጉባኤ ውስጥ ‘አስተማሪዎች የሚሆኑም’ እምነትና ጥበብ ሊኖራቸው ይገባል። ያዕቆብ፣ ምላስ ‘ሰውነትን ሁሉ ልታረክስ’ የምትችል “ትንሽ የሰውነት ክፍል” እንደሆነች ከገለጸ በኋላ ዓለማዊ ዝንባሌዎችም አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሹበት እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። በተጨማሪም በመንፈሳዊ የታመመ ማንኛውም ሰው ፈውስ ማግኘት እንዲችል ሊወስዳቸው የሚገቡትን እርምጃዎች ዘርዝሯል።—ያዕ. 3:1, 5, 6፤ 5:14, 15
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:13—‘ምሕረት በፍርድ ላይ የሚያይለው’ በምን መንገድ ነው? እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ በምንሰጥበት ጊዜ አምላክ ለሌሎች ያሳየነውን ምሕረት ግምት ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም ሌላ የልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ይቅር ይለናል። (ሮሜ 14:12) ምሕረት በሕይወታችን ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ባሕርይ እንዲሆን ለማድረግ እንድንጥር የሚያነሳሳን አንዱ ምክንያት ይህ አይደለም?
4:5—ያዕቆብ እዚህ ላይ የጠቀሰው የትኛውን ጥቅስ ነው? ያዕቆብ በቀጥታ የጠቀሰው ጥቅስ የለም። ይሁን እንጂ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው እነዚህ ቃላት እንደ ዘፍጥረት 6:5፤ 8:21፤ ምሳሌ 21:10 እና ገላትያ 5:17 ያሉት ጥቅሶች በያዙት አጠቃላይ ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ።
5:20—“ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው” ከሞት የሚያድነው የማንን ነፍስ ነው? መጥፎ ድርጊት የሚፈጽምን ሰው ከኃጢአት ጎዳና የሚመልስ ክርስቲያን ንስሐ የገባውን ግለሰብ ነፍስ ከመንፈሳዊ ሞት ምናልባትም ከዘላለማዊ ጥፋት ያድናል። በተጨማሪም ኃጢአተኛውን በዚህ መንገድ የሚረዳ ግለሰብ የሰውየውን ‘ብዙ ኀጢአት ይሸፍናል።’
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:14, 15፦ የኃጢአት መነሻ መጥፎ ምኞት ነው። በመሆኑም መጥፎ ምኞቶችን በማውጠንጠን በውስጣችን እንዲያድጉ መፍቀድ የለብንም። ከዚህ ይልቅ የሚያንጹ ነገሮችን ዘወትር በማሰብ አእምሯችንና ልባችን በእነዚህ ነገሮች እንዲሞላ ማድረግ ይኖርብናል።—ፊልጵ. 4:8
2:8, 9 [የ1954 ትርጉም]፦ ‘አድልዎ ማድረግ’ ከንጉሣዊው የፍቅር ሕግ ጋር ይቃረናል። በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች አድልዎ አያደርጉም።
2:14-26፦ ‘የምንድነው በእምነት’ ነው እንጂ የሙሴን ሕግ በመፈጸም ወይም ክርስቲያን በመሆናችን በምናከናውነው ‘ሥራ አይደለም።’ እምነታችን በቃል ብቻ የሚገለጽ መሆን የለበትም። (ኤፌ. 2:8, 9፤ ዮሐ. 3:16) ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ተግባር እንድንፈጽም ሊያነሳሳን ይገባል።
3:13-17፦ ‘ከሰማይ የሆነው ጥበብ’ “ከምድር ከሥጋና ከአጋንንት” ከሆነው ጥበብ የላቀ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም! አምላካዊ ጥበብን ‘እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀን ልንሻው’ ይገባል።—ምሳሌ 2:1-5
3:18፦ የመንግሥቱ ምሥራች ዘር ‘ሰላምን በሚያደርጉ ሰዎች በሰላም መዘራት’ አለበት። እብሪተኞች፣ ጠበኞች ወይም ዓመፀኞች ከመሆን ይልቅ ሰላም ፈጣሪዎች መሆናችን በጣም አስፈላጊ ነው።
“በእምነት ጸንታችሁ” ቁሙ
ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን በሰማይ ርስት ተደርጎ ስለሚሰጣቸው “ሕያው ተስፋ” አስታውሷቸዋል። “እናንተ . . . የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ . . . ናችሁ” ብሏቸዋል። ተገዥነትን በተመለከተ ቀጥተኛ ምክር ከሰጠ በኋላ “በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ” ሲል ሁሉንም አጥብቆ መክሯቸዋል።—1 ጴጥ. 1:3, 4፤ 2:9፤ 3:8
የአይሁድ ሥርዓት ‘መጨረሻ ተቃርቦ’ ስለነበር ጴጥሮስ ወንድሞችን “ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” ሲል መክሯቸዋል። በተጨማሪም “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ . . . [ሰይጣንን] በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” ብሏቸዋል።—1 ጴጥ. 4:7 NW፤ 5:8, 9
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
3:20-22—ጥምቀት የሚያድነን እንዴት ነው? ጥምቀት መዳን የሚፈልጉ ሰዎች ሊያሟሉት የሚገባ ብቃት ነው። ይሁን እንጂ ጥምቀት በራሱ አያድነንም። እንደ እውነቱ ከሆነ መዳን የሚገኘው “በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው።” የጥምቀት እጩው መዳን የሚገኝበት ብቸኛ መንገድ ሊከፈት የቻለው ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞቱ፣ ትንሣኤ በማግኘቱና በሕያዋንም ሆነ በሙታን ላይ ሥልጣን ኖሮት ‘በአምላክ ቀኝ’ በመቀመጡ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በእንዲህ ዓይነቱ እምነት ላይ የተመሠረተ ጥምቀት ‘ስምንት ሰዎች በውኃ ከዳኑበት’ ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል።
4:6—‘ወንጌል የተሰበከላቸው ሙታን’ እነማን ናቸው? እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን ከመስማታቸው በፊት ‘በበደላቸውና በኃጢአታቸው ሙታን’ የነበሩ ወይም በመንፈሳዊ ሙት የነበሩ ናቸው። (ኤፌ. 2:1) በምሥራቹ ላይ እምነት ካሳደሩ በኋላ ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘መኖር’ ጀምረዋል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:7፦ እምነታችን የላቀ ዋጋ እንዲኖረው ጥራቱ የተረጋገጠ ወይም የተፈተነ መሆን ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ እምነት በእርግጥም ‘ለመዳን’ ያበቃል። (ዕብ. 10:39) እምነታችን እንዲፈተን ከሚያደርጉ ነገሮች ማፈግፈግ የለብንም።
1:10-12፦ መላእክት የጥንቶቹ የአምላክ ነቢያት ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የጻፏቸውን ጥልቀት ያላቸው መንፈሳዊ እውነቶች በቅርበት ለማየትና ለመረዳት ይመኙ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ግልጽ የሆኑት ይሖዋ ከጉባኤው ጋር ግንኙነት ከመሠረተ በኋላ ነው። (ኤፌ. 3:10) እኛስ የመላእክትን ምሳሌ በመከተል “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” ለመመርመር ጥረት ማድረግ አይኖርብንም?—1 ቆሮ. 2:10
2:21፦ ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመኮረጅ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ስንል እስከ ሞት ድረስ እንኳ ቢሆን መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል።
5:6, 7፦ ጭንቀታችንን በይሖዋ ላይ የምንጥል ከሆነ ነገ ምን ይመጣ ይሆን ብለን ሳያስፈልግ ከመጨነቅ ይልቅ በሕይወታችን ውስጥ ለእውነተኛው አምልኮ ቅድሚያ እንድሰጥ ይረዳናል።—ማቴ. 6:33, 34
‘የይሖዋ ቀን ይመጣል’
ጴጥሮስ “ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም” ሲል ጽፏል። ለትንቢታዊው ቃል ትኩረት መስጠታችን ‘ከሐሰተኞች መምህራን’ እና መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሌሎች ግለሰቦች ሊጠብቀን ይችላል።—2 ጴጥ. 1:21፤ 2:1-3
ጴጥሮስ “በመጨረሻው ዘመን . . . ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ” ሲል አስጠንቅቋል። “የጌታ [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል።” ጴጥሮስ ደብዳቤውን የደመደመው ‘የአምላክን ቀን ለሚጠባበቁና መምጫውን ለሚያፋጥኑ’ ሰዎች ገንቢ ምክር በመስጠት ነው።—2 ጴጥ. 3:3, 10-12
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:19—“የንጋት ኮከብ” ማን ነው? ይህ ኮከብ የወጣው መቼ ነው? ይህ ሁኔታ መከሰቱንስ የምናውቀው እንዴት ነው? “የንጋት ኮከብ” የተባለው ንጉሣዊ ሥልጣኑን የያዘው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ራእይ 22:16) ኢየሱስ በ1914 በፍጥረት ሁሉ ፊት መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በመውጣት አዲስ ቀን መጥባቱን አስታውቋል። ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ ወደፊት የሚያገኘውን ክብርና መንግሥታዊ ሥልጣን በራእይ መልክ ለማየት ያስቻለ ሲሆን የአምላክ ትንቢታዊ ቃል አስተማማኝ መሆኑንም አረጋግጧል። ለዚህ ቃል ትኩረት መስጠታችን በልባችን ውስጥ ብርሃን እንዲፈነጥቅ የሚያደርግ ሲሆን በዚህ መንገድም የንጋት ኮከብ መውጣቱን እንገነዘባለን።
2:4 NW—“እንጦሮጦስ” ምንድን ነው? ዓመፀኞቹ መላእክት ወደዚያ የተጣሉትስ መቼ ነበር? እንጦሮጦስ ሰብዓዊ ፍጥረታት ሳይሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚቆዩበትን እንደ እሥር ቤት ያለ ሁኔታ ያመለክታል። የአምላክን ብሩህ ዓላማ በተመለከተ አእምሯቸው በጨለማ መዋጡን ያሳያል። በእንጦሮጦስ ያሉ ሁሉ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ የላቸውም። አምላክ ታዛዥ ያልሆኑትን መላእክት ወደ እንጦሮጦስ የጣላቸው በኖኅ ዘመን ሲሆን እስከሚጠፉበት ጊዜ ድረስም በዚህ ሁኔታ እንደተዋረዱ ይቆያሉ።
3:17—ጴጥሮስ ‘አስቀድሞ ማወቅ’ ሲል ምን ማለቱ ነው? ጴጥሮስ ይህን ሲል ለእሱም ሆነ ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች በመንፈስ የተገለጠላቸውን ነገር ማመልከቱ ነበር። ይህ እውቀት ገደብ ያለው ስለነበረ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች እያንዳንዱን ዝርዝር እንዲያውቁ አላስቻላቸውም። ከዚህ ይልቅ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በደፈናው እንዲያውቁ ብቻ አስችሏቸዋል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2, 5-7፦ እንደ እምነት፣ ጽናትና ለአምላክ ማደር ያሉ ባሕርያትን ለማፍራት ልባዊ ጥረት ማድረጋችን ‘ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ያለን እውቀት’ እንዲጨምር የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ይህን እውቀት ካገኘን በኋላ “ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች” እንዳንሆን ያስችለናል።—2 ጴጥ. 1:8
1:12-15፦ ‘በእውነት ጸንተን’ ለመቀጠል በጉባኤ ስብሰባዎቻችን፣ በግል ጥናትና በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ እንደምናገኛቸው ያሉ ማሳሰቢያዎች ሁልጊዜ ያስፈልጉናል።
2:2፦ አኗኗራችን በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ነቀፋ እንዳያስከትል ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል።—ሮሜ 2:24
2:4-9፦ ከዚህ በፊት ካደረገው ነገር በመነሳት፣ ይሖዋ “በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል” የሚል እምነት ሊኖረን ይችላል።
2:10-13 [NW]፦ ‘የተከበሩ’ የተባሉት ማለትም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጉድለት ያለባቸው ቢሆኑና አንዳንድ ጊዜም ሊሳሳቱ ቢችሉም እነሱን መሳደብ የለብንም።—ዕብ. 13:7, 17
3:2-4, 12፦ “ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም . . . በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ” በትኩረት መከታተላችን የይሖዋ ቀን ቅርብ መሆኑን ምንጊዜም እንዳንዘነጋ ይረዳናል።
3:11-14፦ ‘የይሖዋን ቀን የምንጠባበቅና መምጫውን የምናፋጥን’ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን (1) አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን በመጠበቅ ‘በቅድስና መኖር’ ይገባናል፤ (2) የመንግሥቱን ምሥራች መስበክንና ደቀ መዛሙርት ማድረግን የመሳሰሉ “እውነተኛ መንፈሳዊነት” የሚንጸባረቅባቸው ሥራዎች የበዙልን ልንሆን ይገባል፤ (3) አኗኗራችንና ባሕርያችን “ያለ ነውር” ሆኖ እንዲገኝ ይኸውም በዓለም እንዳይበከል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ (4) ማንኛውንም ነገር በንጹሕ ልብ በማከናወን “ያለ ነቀፋ” መኖር አለብን፤ እንዲሁም (5) “በሰላም” መኖር ይኸውም ከአምላክ፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል።