በትዕግሥት ተጠባበቅ
ተኩላ ሳይመጣ “ተኩላ፣ ተኩላ!” እያለ ይጮኽ የነበረው እረኛ የኋላ ኋላ ያሰማው የድረሱልኝ ጩኸት ምላሽ ተነፍጎታል። በተመሳሳይም ዛሬ ብዙ ሰዎች እንደተጠበቁት ሳይፈጸሙ የቀሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ማስጠንቀቂያዎች በመስማታቸው የይሖዋ ቀን መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን አምነው ለመቀበል ያዳግታቸዋል። ብዙ ሰዎች ትክክለኛውና ሊከተሉት የሚገባቸው ማስጠንቀቂያ የትኛው እንደሆነ የማያስተውሉት በአምላክ ቀንደኛ ጠላትና ‘የብርሃን መልአክ’ መስሎ ለመቅረብ በሚሞክረው በሰይጣን ምክንያት ነው።—2 ቆሮንቶስ 11:14
ይሖዋን ለተወሰኑ ጊዜያት ሲያገለግሉ ለቆዩትም እንኳ ቢሆን ብዙ መጨነቅ አያስፈልግም የሚል መንፈስ ማዳበር አደገኛ ሊሆን ይችላል። ለምን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል።
በትክክል አስቡ
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ሁለተኛው የጴጥሮስ ደብዳቤ ጥንት ለነበሩ ክርስቲያኖች የተሰጠ ማሳሰቢያ ሲሆን ለእኛም ይሠራል። “ወዳጆች ሆይ፣ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት። በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን [“በትክክል የማሰብ ችሎታችሁን፣” NW] አነቃቃለሁ” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:1) ጴጥሮስ እንዲህ ሊል የቻለው ምን የተመለከተው ነገር ቢኖር ነው? ጴጥሮስ የአምላክ አገልጋዮች የሚኖሩበትን ጊዜ በተመለከተ ሊኖራቸው የሚገባውን የጥድፊያ ስሜት የሚያቀዘቅዙ ቃላትን የሚናገሩ ዘባቾች እንዳሉ ጎላ አድርጎ ገልጿል። በፌዘኞች ከመታለል መጠንቀቅ የሚገባው አሁን ነው። በመሆኑም ጴጥሮስ ‘በቅዱሳን ነቢያት ቀድሞ የተባለውን ቃል እንዲያስቡ’ አንባቢዎቹን በጥብቅ ይመክራል። (2 ጴጥሮስ 3:2፤ ሥራ 3:22, 23) ነቢያት ምን ተናግረዋል?
የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች በተለያዩ ጊዜያት መለኮታዊ ፍርድ ክፋትን እንዴት እንዳስወገደ ሰዎች እንዲያስተውሉ አድርገዋል። አምላክ ጣልቃ በመግባት በኖኅ ዘመን በክፋት የተሞላችውን ምድር ለማጽዳት የጥፋት ውኃ እንዳመጣ ጴጥሮስ ለአንባቢዎቹ ገልጿል። ይህ ኃይለኛ ጎርፍ በዚያን ዘመን የነበረውን ዓለም ሙሉ በሙሉ አጥፍቷል። ይሁን እንጂ አምላክ ኖኅንና ቤተሰቡን እንዲሁም “ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ” ለዘር የቀሩትን ፍጥረታት በአንድ መርከብ አድኗል። በዓለም ዙሪያ የሚነገሩ አፈ ታሪኮች የመጽሐፍ ቅዱሱን ዘገባ እውነታ ያረጋግጣሉ።a—ዘፍጥረት 6:19፤ 2 ጴጥሮስ 3:5, 6
ጴጥሮስ ይህን መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በአንዳንድ ሰዎች ‘ትኩረት የተነፈገው እውነታ’ በማለት ጠርቶታል። ሌሎች ደግሞ በዘመኑ በነበሩት ዘባቾች ተታለው የግዴለሽነት ሕይወት መምራት ጀምረዋል። እኛ ግን ይሖዋ ቀደም ሲል ያደረጋቸውን ነገሮች መርሳት የለብንም። ጴጥሮስ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከ ሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል” ይለናል። (2 ጴጥሮስ 3:7) አዎን፣ አምላክ በድጋሚ በሰዎች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ይገባል።
አምላክ አይዘገይም
በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። አምላክ ለሰው ልጆች ችግር እልባት ሳያደርግ ይህን ያህል ረጅም ዘመን የቆየው ለምንድን ነው? አሁንም ጴጥሮስ ትኩረቱን በሌላ እውነታ ላይ ያደርጋል። “እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ፣ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 3:8) ይሖዋ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከእኛ ይለያል። ለዘላለማዊው አምላክ አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያለው ጊዜ ሳምንት እንኳን አይሞላም። ይሁን እንጂ ስለ ጊዜ ያለን አመለካከት ምንም ይሁን ምን እያንዳንዱ ሺህ ዓመትና እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት ጊዜ ይበልጥ እንደሚያቀርበን መዘንጋት የለብንም።
“ጀበና ከጠበቁት ቶሎ አይፈላም” የሚል አንድ አባባል አለ። ይህ አባባል አንድን ነገር ዝም ብሎ መጠባበቅ የሚፈጸምበትን ጊዜ የሚያርቀው ይመስላል የሚል መልእክት አለው። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቅንና እያስቸኰልን መኖር’ እንደሚገባን ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 3:12) መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበን በንቃት ለመመላለስ የሚያስችለንን አስተሳሰብ ልናዳብር የምንችለው እንዴት ነው?
ከቃላት ይልቅ የተግባር ድምፅ የጎላ ነው
ጴጥሮስ ለሥራና ለተግባር ትኩረት ሰጥቷል። ስለ ‘ቅዱስ ኑሮ’ ተግባራትና ‘ለአምላክ ማደርን ስለሚያሳዩ’ ሥራዎች ጠቅሷል። (2 ጴጥሮስ 3:11) እነዚህ ምንን ይጨምራሉ?
እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ይመላለሳል። የእንዲህ ያለው እውነተኛ አምላኪ እምነት በአኗኗሩ ይንጸባረቃል። ይህ ደግሞ በአምላክና በተስፋዎቹ እናምናለን ብለው ለአፋቸው ያህል ብቻ ከሚናገሩ ሰዎች ለይቶ ያሳውቀዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለሕዝብ የሚሰጡት ምሥክርነት ከሌሎች ልዩ እንደሚያደርጋቸው ሳትገነዘብ አትቀርም። ቤትህ በመምጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ተገለጹት የአምላክ ተስፋዎች ይነግሩሃል። በተጨማሪም ሰዎችን በሚያገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለ ተስፋቸውና ስለ እምነታቸው ይመሠክራሉ።
ስለ እምነቱ ለሌሎች በመናገር ራሱን የሚያስጠምድ ምሥክር በሚያምንባቸው ነገሮች ላይ ጠንካራና የጎለበተ እምነት ይኖረዋል። ቃላትን አውጥቶ መናገር የምንናገረው ነገር በጥልቅ እንዲቀረጽብን ያደርጋል። ይህ ደግሞ በተራው ውስጣዊ ደስታና እርካታ ይሰጣል። ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በምናሳውቅበት ጊዜ ይሖዋም ይደሰታል። የጴጥሮስ ጓደኛ የሆነው ጳውሎስ እንደተናገረው ‘ያደረግነውን ሥራና ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ እንዳይደለ’ እናውቃለን።—ዕብራውያን 6:10፤ ሮሜ 10:9, 10
በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ የመንግሥቱን ምሥራች በማዳረሱ ሥራ መጠመዱ የሚያስገኘው ውጤት ምንድን ነው? በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዴት ሊመሠርቱ እንደሚችሉ፣ ይገባናል ከማንለው ደግነቱ ተጠቃሚዎች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት እንደሆነና ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ተስፋ እንዴት ሊደሰቱ እንደሚችሉ በመማር ላይ ናቸው።
አስቀድሞ የተገለጠ እውቀት
ይሖዋ አምላክ እሱ ራሱ ባቀደው ጊዜ ጣልቃ እንደሚገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተረዳን ቢሆንም ጴጥሮስ የሰጠውን አንድ ሌላ ማስጠንቀቂያ ግን ልብ ልንል ይገባል። “ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፣ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ።”—2 ጴጥሮስ 3:17
ይሖዋ ጠንካራ እምነት የሌላቸው ሰዎች የዘገየ በሚመስለው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ተስፋ ሊቆርጡ እንደሚችሉ በሚገባ ያውቅ ነበር። በተጨማሪም አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች ተጽእኖ የእውነተኛ አገልጋዮቹን አመለካከት ሊያዛባ ወይም ደግሞ የአምላክ ስም የሚቀደስበት ጊዜ ቅርብ ነው የሚለውን እምነታቸውን ሊያዳክም እንደሚችል ያውቃል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት አቋምን ማላላት ምንኛ አደገኛ ይሆናል!
ያለንበት ጊዜ ይሖዋ ወደፊት ስለሚያደርጋቸው ነገሮች የጥርጣሬ ሐሳቦችን የምናስተናግድበት አይደለም። (ዕብራውያን 12:1) ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ትዕግሥት ላስገኘው ጥቅም ያለንን አድናቆት ከፍ የምናደርግበት ጊዜ ነው። ትዕግሥቱ በዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል የሆኑና መጪውን ታላቅ መከራ በሕይወት በማለፍ ለመዳን ተስፋ የሚያደርጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስገኝቷል። (ራእይ 7:9, 14) ጴጥሮስ “ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን” ሲል አሳስቧል።—2 ጴጥሮስ 3:18
“በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ”
በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መጠመድ እንዲሁም ለአምልኮና የአምላክን ቃል ለማጥናት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ጥበቃ ይሆንልናል። ስለዚህ የዚህ ክፉ ሥርዓት ሁኔታዎች እየተበላሹ ስለ መሄዳቸው ከመጠን በላይ በማሰብ ጊዜያችንን አናጠፋም። በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ፍርሃትና ጭንቀት ቦታ የላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ይሖዋን በማገልገሉ ሥራ ራሳችንን ካስጠመድን ጊዜው ሳይታሰብ ያልፋል።
ከጴጥሮስ ጋር በአንድ ዘመን ይኖር የነበረው የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ይሁዳ እንዲህ ሲል ያሳስበናል:- “ወዳጆች ሆይ፣ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” (ይሁዳ 20, 21) በጸሎት በመጽናት አዎንታዊ አመለካከት የመያዝን አስፈላጊነት ልብ በል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሁዳ አክሎም “አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፣ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፣ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።” (ይሁዳ 22, 23) በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት አንዳችን ሌላውን ማጠንከራችን ምንኛ ተገቢ ነው! እንዲሁም በሥነ ምግባር በተበላሸው በዚህ ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ እንደሚገኘው ይህን “የመዳን ቀን” “ለሴሰኝነት” በመጠቀም መጥፎ ነገር በመሥራት እንዳንሸነፍ መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው።—ይሁዳ 4፤ 2 ቆሮንቶስ 6:1, 2
የጴጥሮስን፣ የጳውሎስንና የይሁዳን በፍቅር የተሰጠ ምክር በመከተል እንዲሁም በአምላክ አገልግሎት በመጠመድና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ይሖዋ ጣልቃ እስከሚገባበት ጊዜ ድረስ በትዕግሥት መጠባበቅ ትችላለህ። ይሁን እንጂ እንዲህ ታደርግ ይሆን?
ፈጣሪ በሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ ያለህን እምነት እንድታጎለብት ሊረዱህ የሚችሉትን በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለማነጋገር ዛሬ ነገ አትበል። ወደፊት በፍጹም በማይደገመውና እየቀረበ ባለው ታላቅ መከራ በሚደመደመው በዓለም አቀፋዊው የምሥክርነት ሥራ ተካፋይ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ተማር። (ማርቆስ 13:10) ስለዚህ ይሖዋ በሰጠው ተስፋ መሠረት ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ልትጠብቅ ትችላለህ። (2 ጴጥሮስ 3:13) ማሳሰቢያዎቹን ተግባራዊ አድርግ! በትዕግሥት ተጠባበቅ! በሥራ የተጠመድህ ሁን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተሰኘውን መጽሐፍ ገጽ 116ን እባክህ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ስለ ሰጠው የገነት ተስፋ አሁኑኑ ተማር
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ተኩላ:- Animals/Jim Harter/Dover Publications, Inc.; ወጣት እረኛ:- Children: A Pictorial Archive from Nineteenth-Century Sources/Grafton/Dover Publications, Inc.