የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርባችሁ ተመልከቱ
‘በመጨረሻው ዘመን ዘባቾች ይመጣሉ።’—2 ጴጥሮስ 3:3
1. በዚህ ዘመን ያለ አንድ ክርስቲያን ስለ ጊዜው አጣዳፊነት ምን አመለካከት እንዳለው ገልጿል?
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ66 ዓመታት በላይ የቆየ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጊዜውን አጣዳፊነት ላፍታ እንኳ ዘንግቼው አላውቅም። ሁልጊዜ አርማጌዶን ነገ እንደሆነ አድርጌ አስባለሁ። (ራእይ 16:14, 16) እንደ አያቴና እንደ አባቴ ሁሉ እኔም ‘የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርባችሁ ተመልከቱ’ የሚለውን የሐዋርያው [ጴጥሮስ] ጥብቅ ምክር ስከተል ኖሬያለሁ። ‘በዓይን የማይታየውን’ የአዲሱን ዓለም ተስፋ ዘወትር እውን እንደሆነ አድርጌ እመለከታለሁ።”—2 ጴጥሮስ 3:11, 12 NW፤ ዕብራውያን 11:1፤ ኢሳይያስ 11:6-9፤ ራእይ 21:3, 4
2. የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርቦ መመልከት ማለት ምን ማለት ነው?
2 ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን ‘ሁልጊዜ አቅርባችሁ ተመልከቱት’ ሲል ምን ጊዜም ከአእምሮአችን ልናወጣው እንደማይገባ መናገሩ ነው። ይሖዋ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም ከማምጣቱ በፊት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚወስደው እርምጃ በጣም ቅርብ እንደሆነ ልንዘነጋው አይገባም። ከፊት ለፊታችን እንዳለ ነገር ወለል ብሎ ሊታየን ይገባል። ለጥንቶቹ የአምላክ ነቢያት ይህን ያህል እውን ሆኖ ታይቷቸው የነበረ ሲሆን ይህ ቀን መቅረቡን ደጋግመው ገልጸዋል።—ኢሳይያስ 13:6፤ ኢዩኤል 1:15፤ 2:1፤ አብድዩ 15፤ ሶፎንያስ 1:7, 14
3. ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን አስመልክቶ ምክር እንዲሰጥ ያነሳሳው ምንድን ነው ለማለት ይቻላል?
3 ጴጥሮስ የይሖዋ ቀን ልክ “ነገ እንደሆነ” አድርገን እንድናስብ ያበረታታን ለምንድን ነው? ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ክፉ አድራጊዎች የሚቀጡበትን የክርስቶስን መገኘት በተመለከተ በተሰጠው ተስፋ አንዳንዶች ማፌዝ ጀምረው ስለነበር ነው። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) በመሆኑም ጴጥሮስ ከዚህ ቀጥሎ በምንመረምረው በሁለተኛው መልእክቱ በምዕራፍ 3 ውስጥ እነዚህ ፌዘኞች ለሚሰነዝሩት ሐሳብ መልስ ሰጥቷል።
የቀድሞውን እንዲያስታውሱ የተነገረ ፍቅራዊ ማሳሰቢያ
4. ጴጥሮስ እንድናስታውሰው የፈለገው ነገር ምንድን ነው?
4 ጴጥሮስ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ወንድሞቹን “ወዳጆች ሆይ” እያለ መጥራቱ ለእነርሱ ያለውን የጠበቀ ፍቅር የሚያሳይ ነው። ጴጥሮስ ከአሁን ቀደም የተማሯቸውን ነገሮች እንዳይዘነጉ በፍቅር ሲያሳስባቸው እንዲህ በማለት ጀምሯል:- “ወዳጆች ሆይ፣ . . . በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ።”—2 ጴጥሮስ 3:1, 2, 8, 14, 17፤ ይሁዳ 17
5. አንዳንድ ነቢያት ስለ ይሖዋ ቀን ምን ተናግረዋል?
5 ጴጥሮስ አንባቢዎቹ እንዲያስታውሷቸው ያበረታታው ‘አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገሩትን’ የትኞቹን ቃላት ነው? ክርስቶስ በመንግሥት ሥልጣኑ እንደሚገኝና አምላካዊ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ላይ የፍርድ እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጹትን ቃላት ነበር። ጴጥሮስ ቀደም ሲል እነዚህን ቃላት ጠቅሷል። (2 ጴጥሮስ 1:16-19፤ 2:3-10) ይሁዳ፣ አምላክ በክፉ አድራጊዎች ላይ የሚወስደውን የጥፋት ፍርድ እንዳስታወቀ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበውን ነቢይ፣ ሄኖክን ጠቅሶታል። (ይሁዳ 14, 15) ከሄኖክ በኋላም ሌሎች ነቢያት የተነሡ ሲሆን ጴጥሮስ እነርሱ የጻፉትንም እንዳንረሳ አሳስቦናል።—ኢሳይያስ 66:15, 16፤ ሶፎንያስ 1:15-18፤ ዘካርያስ 14:6-9
6. የይሖዋን ቀን በሚመለከት የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅልን የትኛው የክርስቶስና የሐዋርያቱ አነጋገር ነው?
6 ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ አንባቢዎቹ “የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ” እንዲያስቡ ነግሯቸዋል። የኢየሱስ ትእዛዝ የሚከተለውንም ማሳሰቢያ ይጨምራል:- “ልባችሁ . . . እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ።” (ሉቃስ 21:34-36፤ ማርቆስ 13:33) ጴጥሮስ የሐዋርያትንም ቃል ልብ እንድንል አሳስቦናል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጌታ ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ።”—1 ተሰሎንቄ 5:2, 6
የዘባቾች ምኞት
7, 8. (ሀ) በአምላክ የማስጠንቀቂያ መልእክት የሚዘብቱት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? (ለ) ዘባቾች ምን ይላሉ?
7 ቀደም ሲል እንዳየነው ጴጥሮስ ማሳሰቢያ እንዲሰጥ ያነሳሳው ልክ ከዚያ ቀደም የኖሩት እስራኤላውያን በይሖዋ ነቢያት ላይ እንዳላገጡት አንዳንዶች እነዚህን በመሳሰሉት ማስጠንቀቂያዎች ማሾፍ መጀመራቸው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 36:16) ጴጥሮስ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ” ሲል ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:3፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ይሁዳ የእነዚህ ዘባቾች ምኞት ‘የኃጢአተኝነት ’ ምኞት እንደሆነ ተናግሯል። “ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም [“መንፈሳዊነት፣” NW] የሌላቸው” ሲል ጠርቷቸዋል።—ይሁዳ 17-19፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
8 ጴጥሮስ ‘በርኩስ ምኞት የሥጋን ፍትወት ይከተላሉ’ ያላቸው ሐሰተኛ አስተማሪዎች ከእነዚህ መንፈሳዊነት የሌላቸው ዘባቾች መካከል እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። (2 ጴጥሮስ 2:1, 10, 14) የታመኑ ክርስቲያኖችን “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና” በማለት ይዘብቱባቸዋል።—2 ጴጥሮስ 3:4
9. (ሀ) ዘባቾች በአምላክ ቃል ውስጥ በጉልህ ተንጸባርቆ የሚገኘውን የጥድፊያ ስሜት ለማዳፈን የሚሞክሩት ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርበን መመልከት ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?
9 እንዲህ የሚያፌዙት ለምንድን ነው? የክርስቶስ መገኘት ፈጽሞ አይመጣም፣ አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ እጁን ጣልቃ አስገብቶ አያውቅም ወደፊትም ፈጽሞ ጣልቃ አያስገባም የሚሉት ለምንድን ነው? እነዚህ ሥጋውያን የሆኑ ዘባቾች በአምላክ ቃል ውስጥ በጉልህ ተንጸባርቆ የሚገኘውን የጥድፊያ ስሜት በማዳፈን ሌሎች በመንፈሳዊ ግዴለሽነት ተውጠው በቀላሉ በእነርሱ የራስ ወዳድነት ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡላቸው ያደርጋሉ። ይህ ዛሬ ላለነው ሰዎች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር እንዴት ያለ ጠንካራ ማበረታቻ ነው! የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርበን እንመልከት፤ የይሖዋም ዓይኖች በእኛ ላይ መሆናቸውን ፈጽሞ አንዘንጋ! እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን በቅንዓት ለማገልገል እንዲሁም የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ይገፋፋናል።—መዝሙር 11:4፤ ኢሳይያስ 29:15፤ ሕዝቅኤል 8:12፤ 12:27፤ ሶፎንያስ 1:12
የአዋቂ አጥፊዎችና የተናቁ
10. ጴጥሮስ ዘባቾች የተሳሳቱ መሆናቸውን ያረጋገጠው እንዴት ነው?
10 እንዲህ ያሉት ዘባቾች አንድ በጣም ወሳኝ የሆነ ሐቅ ቸል ይላሉ። እነርሱ ሆነ ብለው ቸል ማለታቸው ሳይበቃ ሌሎች ሰዎች እንዲዘነጉት ለማድረግ ይጥራሉ። ለምን? ሰዎቹን በቀላሉ ለማታለል እንዲመቻቸው ሲሉ ነው። ጴጥሮስ “ወደው አያስተውሉምና” ሲል ጽፏል። ያላስተዋሉት የትኛውን ሐቅ ነው? “ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ” አላስተዋሉም። (2 ጴጥሮስ 3:5, 6፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ይሖዋ በኖኅ ዘመን ባመጣው የጥፋት ውኃ ምድርን ከክፋት ያጸዳት ሲሆን ይህንን እውነታ ኢየሱስም ጠበቅ አድርጎ ገልጾታል። (ማቴዎስ 24:37-39፤ ሉቃስ 17:26, 27፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) በመሆኑም ዘባቾቹ እንደሚሉት አይደለም፤ ሁሉ ነገር “ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ” እንዳለ አልቀጠለም።
11. አንዳንዶች በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ላይ ሊዘብቱ የቻሉት ክርስቲያኖቹ ምን ነገር ያለ ጊዜው ተስፋ በማድረጋቸው ነው?
11 የታመኑት ክርስቲያኖች የሚጠብቋቸው ነገሮች በወቅቱ ገና ፍጻሜያቸውን ባለማግኘታቸው ዘባቾቹ አላግጠውባቸው ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱ ‘የአምላክ መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው መስሏቸው ነበር።’ ትንሣኤ ካገኘም በኋላ መንግሥቱ ወዲያው ይቋቋም እንደሆነና እንዳልሆነ ጥያቄ አቅርበዋል። ከዚህም ሌላ ጴጥሮስ ሁለተኛውን ደብዳቤ ከመጻፉ አሥር ዓመታት ቀደም ብሎ አንዳንዶች ምናልባትም ከሐዋርያው ጳውሎስ ወይም ከእርሱ አጋሮች በደረሳቸው ‘የቃል መልእክት’ ወይም ደብዳቤ ሳይሆን አይቀርም “የጌታ ቀን ደርሷል” ብለው በማሰብ ‘ፈንድቀው’ ነበር። (ሉቃስ 19:11፤ 2 ተሰሎንቄ 2:2፤ ሥራ 1:6) ይሁን እንጂ ስህተቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያለጊዜው ተስፋ ማድረጋቸው እንጂ ተስፋው ውሸት ነበር ማለት አይደለም። የይሖዋ ቀን መምጣቱ አይቀርም ነበር!
የአምላክ ቃል ትምክህት የሚጣልበት ነው
12. የአምላክ ቃል ‘የይሖዋን ቀን’ በሚመለከት በሚናገራቸው ትንቢቶች ረገድ ትምክህት የሚጣልበት መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?
12 አስቀድሞ እንደተገለጸው በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩት ነቢያት የይሖዋ የበቀል ቀን ቅርብ መሆኑን ሲያስጠነቅቁ ኖረዋል። ይሖዋ ዓመፀኛ በነበሩት ሕዝቦቹ ላይ በ607 ከዘአበ የበቀል እርምጃ በወሰደ ጊዜ “የይሖዋ ቀን” ምን እንደሚመስል በጥቂቱ ታይቷል። (ሶፎንያስ 1:14-18) ከጊዜ በኋላ ባቢሎንንና ግብጽን ጨምሮ ሌሎች ብሔራትም እንዲህ ያለውን “የይሖዋ ቀን” ቀምሰዋል። (ኢሳይያስ 13:6-9፤ ኤርምያስ 46:1-10፤ አብድዩ 15) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የአይሁዳውያኑ የነገሮች ሥርዓት ላይ የመጣውም ጥፋት አስቀድሞ በትንቢት ተነግሯል። ይህ ጥፋት የደረሰው የሮማውያን ሠራዊት በ70 እዘአ ይሁዳን በደመሰሰ ጊዜ ነው። (ሉቃስ 19:41-44፤ 1 ጴጥሮስ 4:7) ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የተናገረው ገና ወደፊት ስለሚመጣው “የይሖዋ ቀን” ሲሆን ምድር አቀፉ የጥፋት ውኃ እንኳን ከዚህ ቀን ጋር ሲወዳደር ኢምንት ይሆናል!
13. የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መምጣቱ እንደማይቀር የሚያሳዩት ታሪካዊ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
13 ጴጥሮስ ስለ መጪው ጥፋት ሲገልጽ “በዚያ ቃል” በማለት ተናግሯል። ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ደግሞ ከጥፋት ውኃው በፊት የነበረችው ምድር “በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል” እንደነበረች ተናግሮ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱሱ የፍጥረት ዘገባ ውስጥ በተገለጸው በዚህ ሁኔታ አማካኝነት በአምላክ ትእዛዝ ወይም ቃል ውኆች ከሰማይ የወረዱበት የጥፋት ውኃ ሊመጣ ችሏል። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከ ሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።” (2 ጴጥሮስ 3:5-7፤ ዘፍጥረት 1:6-8) ለዚህ ደግም አስተማማኝ የሆነው የአምላክ ቃል ማስረጃ ይሆነናል! በታላቁና በሚያስፈራው የቁጣ ቀኑ ‘ሰማያትንና ምድርን’ ማለትም ይህን የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል! (ሶፎንያስ 3:8) ይሁን እንጂ መቼ?
መጨረሻው እንዲመጣ መጓጓት
14. ዛሬ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
14 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መጨረሻው የሚመጣበትን ጊዜ ለማወቅ ጓጉተው ስለ ነበር “ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው እነርሱ የጠየቁት የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሚሆን ነበር፤ ይሁን እንጂ የኢየሱስ መልስ በመጀመሪያ ደረጃ ያተኮረው በዛሬዎቹ ‘ሰማያትና ምድር’ ላይ በሚመጣው ጥፋት ላይ ነበር። ኢየሱስ ታላላቅ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረት፣ የምድር መናወጦች፣ በሽታ እና ወንጀል የመሳሰሉት ነገሮች እንደሚኖሩ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3-14 NW፤ ሉቃስ 21:5-36) ኢየሱስ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” እንደሚሆኑ የተናገረላቸውና ጳውሎስ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክት ይሆናሉ ያላቸው ነገሮች ከ1914 ወዲህ ሲፈጸሙ ተመልክተናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በእርግጥም በዚህ የነገሮች ሥርዓት የፍጻሜ ዘመን ላይ እንደምንኖር የሚያሳዩት ማስረጃዎች እጅግ በርካታ ናቸው!
15. ኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ክርስቲያኖች ምን ለማድረግ ቃጥቷቸዋል?
15 የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋ ቀን የሚመጣበትን ጊዜ ለማወቅ ሲጓጉ ቆይተዋል። አንዳንድ ጊዜም ከመጓጓታቸው የተነሣ ቀኑ መቼ እንደሚመጣ ለመገመት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ይህን በማድረጋቸው እንደ ኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁም” ሲል ጌታቸው የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሳያስተውሉ ቀርተዋል። (ማርቆስ 13:32, 33) እነዚህ የታመኑ ክርስቲያኖች ያለ ጊዜው ተስፋ አድርገው በመጠባበቃቸው የዘባቾች ማላገጫ ሆነዋል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) የሆነ ሆኖ ጴጥሮስ የይሖዋ ቀን ራሱ ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ እንደሚመጣ አረጋግጧል።
የይሖዋን ዓይነት አመለካከት የመያዙ አስፈላጊነት
16. የትኛውን ማሳሰቢያ መከተላችን ጥበብ ይሆናል?
16 ጴጥሮስ በመቀጠል እንደሚያሳስበን ጊዜን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል:- “እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ፣ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።” ከዚህ አንጻር ሲታይ 70 ወይም 80 ዓመት የሆነው ዕድሜያችን ምንኛ አጭር ነው! (2 ጴጥሮስ 3:8፤ መዝሙር 90:4, 10) ስለዚህ የአምላክ ተስፋ ፍጻሜውን ሳያገኝ የዘገየ መስሎ ከተሰማን የአምላክ ነቢይ የሰጠውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ መቀበል ይኖርብናል:- “[የተወሰነው ጊዜ] ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱም አይዘገይም።”—ዕንባቆም 2:3፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
17. የመጨረሻዎቹ ቀናት ብዙዎች ከጠበቁት በላይ የረዘሙ ቢሆንም ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
17 የዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ብዙዎች ካሰቡት በላይ የረዘመው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ ይህ የሆነበትን ግሩም ምክንያት ጠቅሷል:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) ይሖዋ ለመላው የሰው ዘር የሚበጁትን ነገሮች ያውቃል። “ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም” ሲል እንደገለጸው የሰዎች ሕይወት ጉዳይ ያሳስበዋል። (ሕዝቅኤል 33:11) እንግዲያውስ እጅግ ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነውን ፈጣሪ ዓላማ ለማሳካት መጨረሻው በትክክለኛው ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን!
የሚያልፈው ምንድን ነው?
18, 19. (ሀ) ይሖዋ ይህን የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት የቆረጠው ለምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የገለጸው እንዴት ነው? የሚጠፋውስ ምንድን ነው?
18 ይሖዋ የሚያገለግሉትን ሰዎች በጣም ስለሚወዳቸው እነርሱን የሚያስጨንቋቸውን ሰዎች ጠራርጎ ያጠፋል። (መዝሙር 37:9-11, 29) ጳውሎስ አስቀድሞ እንዳሳሰበው ሁሉ ጴጥሮስም ጥፋቱ ድንገት እንደሚመጣ በመገንዘብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የይሖዋ ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ንጥረ ነገሮች በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣሉ፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይገለጣል።” (2 ጴጥሮስ 3:10 NW፤ 1 ተሰሎንቄ 5:2) በጥፋት ውኃው ወቅት ሰማያትና ምድር ቃል በቃል እንዳልጠፉ ሁሉ በይሖዋም ቀን ቢሆን አይጠፉም። እንግዲያውስ በዚያን ጊዜ ‘የሚያልፈው’ ወይም የሚጠፋው ነገር ምንድን ነው?
19 የሰውን ዘር እንደ “ሰማያት” ሆነው የጨቆኑት ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲሁም “ምድር” ማለትም አምላካዊ አክብሮት የሌለው የሰው ልጅ ኅብረተሰብ ያከትማሉ። “በታላቅ ድምፅ” የሚለው መግለጫ የሰማያቱን በፍጥነት ማለፍ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ዛሬ ያለው ብልሹ የሰው ልጅ ማኅበረሰብ የተገነባበት ‘ንጥረ ነገርም’ “ይቀልጣል” ወይም ይደመሰሳል። እንዲሁም “ምድር” እና “በእርስዋም የተደረገው ሁሉ” “ይገለጣል።” ይሖዋ ለመላው ዓለም ሥርዓት የሚገባውን ፍርድ በማከናነብ የሰዎችን ክፉ ሥራ ሁሉ ይገልጣል።
ምን ጊዜም ተስፋችሁ ላይ አትኩሩ
20. ከፊታችን ስለሚጠብቀን ነገር ያገኘነው እውቀት ሕይወታችንን ሊነካው የሚገባው እንዴት ነው?
20 እነዚህ አስደናቂ ክስተቶች የሚታዩበት ጊዜ ስለ ቀረበ ጴጥሮስ “የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እያስቸኮላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” መጠመድ ይኖርባችኋል ሲል ተናግሯል። ይህ አንዳችም የሚያጠራጥር አይደለም! “ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት [“ንጥረ ነገሮች፣” NW] በትልቅ ትኩሳት ይፈታል!” (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) እነዚህ አስገራሚ ክስተቶች ነገ መታየት ሊጀምሩ መቻላቸው በምናደርገውና ልናደርግ በምናቅደው ነገር ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይገባል።
21. ዛሬ ያሉት ሰማያትና ምድር በምን ይተካሉ?
21 ጴጥሮስ በመቀጠል ይህ አሮጌ ዓለም በምን እንደሚተካ እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል:- “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17) አቤት፣ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! ክርስቶስና 144,000 ተባባሪ ገዥዎቹ “አዲስ” አስተዳደራዊ “ሰማያት” ሲሆኑ የዚህን ዓለም ፍጻሜ በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች ደግሞ ‘የአዲሱ ምድር’ አባላት ይሆናሉ።—1 ዮሐንስ 2:17፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3
የጥድፊያ ስሜታችሁንና የሥነ ምግባር ንጽሕናችሁን ጠብቁ
22. (ሀ) ከማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ እድፍ ወይም ነቀፋ እንድንጠበቅ የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ ስለ የትኛው አደገኛ ሁኔታ አስጠንቅቋል?
22 ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ስለዚህ፣ ወዳጆች ሆይ፣ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፣ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ።” የይሖዋን ቀን በጉጉት መጠባበቃችንና የዘገየ መስሎ ቢታየን እንኳ የመለኮታዊ ትዕግሥት መግለጫ እንደሆነ አድርገን መመልከታችን ከማንኛውም መንፈሳዊ እንከን ወይም ነቀፋ እንድንጠበቅ ይረዳናል። ይሁንና ሌላ አደጋ አለ! ጴጥሮስ “የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ” በጻፈው መልእክቱ ውስጥ “ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፣ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ” ሲል አስጠንቅቋል።—2 ጴጥሮስ 3:14-16
23. ጴጥሮስ በመደምደሚያው ላይ የሰጠው ማሳሰቢያ ምንድን ነው?
23 ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የሐሰት አስተማሪዎች ጳውሎስ ይገባናል የማንለውን የአምላክ ደግነት አስመልክቶ የጻፈውን መልእክት ነውረኛ ድርጊቶች ለመፈጸም ማሳበቢያ አድርገው ለመጠቀም አጣምመውት ነበር። ጴጥሮስ በመደምደሚያው ላይ በሰጠው ማሳሰቢያ እንደሚከተለው ብሎ ሲጽፍ ይህን ነገር በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም:- “እንግዲህ እናንተ፣ ወዳጆች ሆይ፣ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፣ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ።” ከዚያም ጴጥሮስ “ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ” ሲል አጥብቆ በማሳሰብ ደብዳቤውን ደምድሟል።—2 ጴጥሮስ 3:17, 18
24. ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
24 በእርግጥም ጴጥሮስ ወንድሞቹን ሊያበረታቸው ቆርጦ ተነስቶ ነበር። ሁሉም ክርስቲያኖች በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው የ82 ዓመት ዕድሜ ያለው የታመነ ምሥክር የገለጸውን ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ተመኝቷል:- “‘የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርባችሁ ተመልከቱት’ የሚለውን የሐዋርያው [ጴጥሮስ] ጥብቅ ምክር ስከተል ኖሬያለሁ። ‘በዓይን የማይታየውን’ የአዲሱ ዓለም ተስፋ ዘወትር እውን እንደሆነ አድርጌ እመለከታለሁ።” ሁላችንንም በዚህ መንገድ የምንመላለስ ያድርገን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የይሖዋን ቀን ‘ሁልጊዜ አቅርቦ መመልከት’ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ዘባቾች ሆነ ብለው ችላ የሚሉት ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
◻ ዘባቾች በታመኑት ክርስቲያኖች ላይ ያላገጡባቸው ለምንድን ነው?
◻ የትኛውን ዓይነት አመለካከት እንደጠበቅን መኖር ይገባናል?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ አቅርባችሁ ተመልከቱ . . .
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
. . . አዲሱ ዓለም ይከተላል