ውድ የሆነውን እምነታችንን አጽንተን እንያዝ!
“[እኛ] ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ።”—2 ጴጥሮስ 1:1
1. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ሲያስጠነቅቅ ምን ብሏቸው ነበር? ሆኖም ጴጥሮስ ምን ብሎ በጉራ ተናገረ?
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ሐዋርያቱ በሙሉ ትተውት እንደሚሸሹ ተናገረ። ከእነርሱ መካከል ግን አንዱ ማለትም ጴጥሮስ “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል በጉራ ተናገረ። (ማቴዎስ 26:33፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሁኔታው የተገላቢጦሽ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። በዚያው ዕለት ምሽት “እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና [“አበርታ፣” NW]” ሲል የነገረው ለዚህ ነበር።—ሉቃስ 22:32
2. ጴጥሮስ ከልክ በላይ በራሱ ቢተማመንም እምነቱ ደካማ እንደነበር ያጋለጡት የትኞቹ ድርጊቶቹ ናቸው?
2 በእምነቱ ከልክ በላይ ተመክቶ የነበረው ጴጥሮስ የዚያኑ ዕለት ምሽት ኢየሱስን ካደው። ጭራሽ ክርስቶስ የሚባል ሰው አላውቅም ሲል ሦስት ጊዜ ሽምጥጥ አድርጎ ካደ! (ማቴዎስ 26:69-75) ‘በተመለሰ ጊዜ’ ‘ወንድሞችህን አበርታ’ የሚሉት የጌታው ቃላት ጆሮው ላይ አቃጭለውበት መሆን አለበት። ይህ ማሳሰቢያ የጴጥሮስን ቀሪ የሕይወት ዘመን በጥልቅ እንደነካው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ሁለት ደብዳቤዎቹ በግልጽ መረዳት ይቻላል።
ጴጥሮስ ደብዳቤዎቹን የጻፈበት ምክንያት
3. ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልእክቱን የጻፈው ለምን ነበር?
3 ኢየሱስ ከሞተ ከ30 ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ በዛሬዋ ቱርክ ሰሜናዊና ምዕራባዊ ክፍል ባሉት በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያ እና በቢታንያ ለሚገኙት ወንድሞቹ የመጀመሪያውን ደብዳቤውን ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 1:1) ጴጥሮስ ከጻፈላቸው ሰዎች መካከል በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ክርስቲያን የሆኑ አንዳንድ አይሁዶች እንደነበሩበት ምንም ጥርጥር የለውም። (ሥራ 2:1, 7-9) ብዙዎቹ ከተቃዋሚዎች ከባድ ፈተና የሚደርስባቸው አሕዛብ ነበሩ። (1 ጴጥሮስ 1:6, 7፤ 2:12, 19, 20፤ 3:13-17፤ 4:12-14) በመሆኑም ጴጥሮስ ለእነዚህ ወንድሞች የጻፈው ሊያበረታታቸው አስቦ ነው። ዓላማው “የእምነታ[ቸውን] ፍጻሜ እርሱም የነፍሳ[ቸውን] መዳን” እንዲያገኙ መርዳት ነበር። በመሆኑም በመደምደሚያው ላይ “[ዲያብሎስን] በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” ሲል አጥብቆ አሳስቧል።—1 ጴጥሮስ 1:9፤ 5:8-10
4. ጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክቱን የጻፈው ለምን ነበር?
4 ከጊዜ በኋላም ጴጥሮስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ሁለተኛ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:1) ለምን? ምክንያቱም ከመጀመሪያው የከፋ አደገኛ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር። ሥነ ምግባር የጎደላቸው ግለሰቦች በአማኞች ዘንድ ርካሽ አድራጎታቸውን ለማስፋፋት እየሞከሩና አንዳንዶችን እያሳቱ ነበር! (2 ጴጥሮስ 2:1-3) ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ ዘባቾች እንደሚመጡ አስጠንቅቋል። በመጀመሪያው ደብዳቤው ‘የነገር ሁሉ መጨረሻ መቅረቡን’ ገልጾ ስለነበር ከዚያ በኋላ አንዳንዶች በዚህ ሐሳብ ሳያፌዙ አልቀሩም። (1 ጴጥሮስ 4:7፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4) እስቲ የጴጥሮስን ሁለተኛውን መልእክት እየመረመርን ወንድሞች በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በዚህ የመጀመሪያው ጥናት ርዕስ 2 ጴጥሮስ ምዕራፍ አንድን እንመረምራለን።
የምዕራፍ 1 ዓላማ
5. ጴጥሮስ ችግሮችን ከመጥቀሱ በፊት የአንባቢዎቹን አእምሮ ያዘጋጀው እንዴት ነው?
5 ጴጥሮስ ከባዶቹን ችግሮች በቀጥታ መዘርዘር አልጀመረም። ከዚህ ይልቅ አንባቢዎቹ ወደ ክርስትና በተለወጡ ጊዜ ላገኟቸው ነገሮች ያላቸውን አድናቆት በመገንባት ወደተነሡት ችግሮች ለመሸጋገር መንገዱን አመቻችቷል። ስለ አምላክ ድንቅ ተስፋዎችና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተአማኒነት እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ይህንንም ያደረገው ክርስቶስ በመንግሥት ክብሩ ሲገለጥ ያየውን ራእይ በመተረክ ነበር።—ማቴዎስ 17:1-8፤ 2 ጴጥሮስ 1:3, 4, 11, 16-21
6, 7. (ሀ) ጴጥሮስ ለመልእክቱ ከተጠቀመበት መግቢያ ምን ልንማር እንችላለን? (ለ) ምክር ስንሰጥ አንዳንድ ጊዜ ምን ነገር ማመናችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል?
6 ከጴጥሮስ መግቢያ አንድ የምንማረው ነገር ይኖራልን? ምክር ከመስጠታችን በፊት ከአድማጮቻችን ጋር በጋራ ስላለን ታላቅ የመንግሥቱ ተስፋ መግለጻችን ምክሩ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ አያደርግምን? የግል ተሞክሮአችንን መናገርስ? ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ በመንግሥቱ ክብር ተገልጦ ስላየበት ራእይ ከኢየሱስ ሞት በኋላ ብዙ ጊዜ ሳይናገር አይቀርም።—ማቴዎስ 17:9
7 ሌላው ልትዘነጋው የማይገባ ነገር ጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክቱን ከመጻፉ ቀደም ብሎ የማቴዎስ ወንጌልና ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የላከው ደብዳቤ በስፋት ተሠራጭተው ነበር። በመሆኑም የጴጥሮስ ሰብዓዊ ድክመቶችና ያሳየው እምነት በዚያ ዘመን ሰዎች ዘንድ በሰፊው የሚታወቁ ነገሮች ኖረው ይሆናል። (ማቴዎስ 16:21-23፤ ገላትያ 2:11-14) ይሁን እንጂ ይህ በነፃነት ከመናገር አላገደውም። እንዲያውም ደብዳቤው የራሳቸው ድካም በሚታወቃቸው ሰዎች ዘንድ ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን አድርጎት ሊሆን ይችላል። እንግዲያውስ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በምንረዳበት ጊዜ እኛም ራሳችን ስህተት እንደምንሠራ ማመናችን ጥሩ ውጤት አይኖረውምን?—ሮሜ 3:23፤ ገላትያ 6:1
የሚያበረታ ሰላምታ
8. ጴጥሮስ “እምነት” የሚለውን ቃል ምን ትርጉም በሚያስተላልፍ መንገድ ተጠቅሞበት ሊሆን ይችላል?
8 አሁን ደግሞ ጴጥሮስ ያቀረበውን ሰላምታ ተመልከት። አንባቢዎቹን “[እኛ ] ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ” ብሎ በመጥራት ገና በመግቢያው ላይ ስለ እምነት ጠቅሷል። (2 ጴጥሮስ 1:1) እዚህ ላይ የገባው “እምነት” የሚለው ቃል “ጠንካራ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ስለሚችል አንድ ክርስቲያን የሚያምንባቸውን ነገሮች ወይም ትምህርቶቹን ያመለክታል፤ አንዳንድ ጊዜ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “እውነት” ተብሎም ተጠርቷል። (ገላትያ 5:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:2፤ 2 ዮሐንስ 1) “እምነት” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት በዚህ መንገድ እንጂ በአንድ ሰው ወይም ነገር ላይ መታመን ወይም ትምክህት መጣል በሚለው አጠቃላይ ትርጉሙ አይደለም።—ሥራ 6:7 (NW)፤ 2 ቆሮንቶስ 13:5 (የ1980 ትርጉም)፤ ገላትያ 6:10 (NW)፤ ኤፌሶን 4:5 (የ1980 ትርጉም )፤ ይሁዳ 3 (የ1980 ትርጉም)
9. የጴጥሮስ ሰላምታ በተለይ ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን አስደስቷቸው መሆን ይኖርበታል የምንለው ለምንድን ነው?
9 የጴጥሮስ ሰላምታ በተለይ ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን አንባቢዎቹን ይበልጥ አስደስቷቸው መሆን አለበት። አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር ምንም ግንኙነት ያልነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ለእነርሱ የንቀት አመለካከት ነበራቸው፤ እንዲሁም ስሜታዊ ጥላቻ በወቅቱ ክርስቲያን በነበሩት አይሁዶች ዘንድ ሲንጸባረቅ ቆይቷል። (ሉቃስ 10:29-37፤ ዮሐንስ 4:9፤ ሥራ 10:28) ይሁንና በትውልድ አይሁዳዊ የሆነውና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የነበረው ጴጥሮስ ከአይሁዳውያንና ከአሕዛብ የተውጣጡት አንባቢዎቹን አንድ ዓይነት እምነት እንዳላቸውና ከእርሱ ጋር የሚተካከል መብት እንዳገኙ ገልጿል።
10. ከጴጥሮስ ሰላምታ ምን ልንማር እንችላለን?
10 ዛሬ ከጴጥሮስ ሰላምታ ምን መልካም ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ አስብ። አምላክ አያዳላም፤ አንዱን ዘር ወይም ብሔር ከሌላው አያበላልጥም። (ሥራ 10:34, 35፤ 11:1, 17፤ 15:3-9) ኢየሱስ ራሱ እንዳስተማረው ሁሉም ክርስቲያኖች ወንድማማች ናቸው፤ አንዳችን ከሌላው እንደምንበልጥ ሊሰማን አይገባም። ከዚህም በላይ የጴጥሮስ ሰላምታ እርሱም ሆነ ሌሎች ሐዋርያት ከነበራቸው ጋር ‘የተካከለ ክብር’ ያለው እምነት ያገኘን ዓለም አቀፍ ወንድማማቾች መሆናችንን ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ማቴዎስ 23:8፤ 1 ጴጥሮስ 5:9
እውቀትና አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች
11. ጴጥሮስ ከሰላምታው በማስከተል ጎላ አድርጎ የገለጻቸው በጣም አስፈላጊ ነገሮች ምንድን ናቸው?
11 ጴጥሮስ ከሰላምታው በማስከተል “ጸጋና [“ይገባናል የማንለው ደግነትና፣” NW] ሰላም ይብዛላችሁ” ሲል ጽፏል። ይገባናል የማንለው ደግነትና ሰላም ሊበዛልን የሚችለው እንዴት ነው? ጴጥሮስ “በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ [“ትክክለኛ፣” NW] እውቀት” ነው በማለት መልሱን ይሰጣል። በመቀጠልም “የመለኮቱ ኃይል . . . ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ” ሰጠን በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ እነዚህን በጣም አስፈላጊ ነገሮች የምናገኘው እንዴት ነው? “በገዛ ክብሩና በጎነቱ የጠራንን በማወቅ [“በትክክል በማወቅ፣” NW]” ነው። በዚህ መንገድ ጴጥሮስ ስለ አምላክና ስለ ልጁ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ሁለት ጊዜ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።—2 ጴጥሮስ 1:2, 3፤ ዮሐንስ 17:3
12. (ሀ) ጴጥሮስ የትክክለኛ እውቀትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለማግኘት በመጀመሪያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
12 ጴጥሮስ በምዕራፍ 2 ላይ ስለ “ሐሰተኞች አስተማሪዎች” ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖችን ለማታለል ‘የሽንገላ ቃላት’ ይናገራሉ። በዚህ መንገድ ትተውት ወደ ነበረው የጾታ ብልግና እንዲመለሱ ሊያስቷቸው ይሞክራሉ። “በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት” አማካኝነት ከዳኑ በኋላ እንዲህ ላለው ማታለያ እጃቸውን የሚሰጡ ሁሉ መጨረሻቸው አያምርም። (2 ጴጥሮስ 2:1-3, 20 NW) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ጴጥሮስ ገና በመልእክቱ መጀመሪያ ላይ በአምላክ ፊት ንጹህ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ትክክለኛ እውቀት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ የጠቀሰው ይህን ችግር በኋላ በሰፊው እንደሚዳስሰው በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት። ጴጥሮስ “ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፣ [አምላክ] በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን” ሲል ተናግሯል። ይሁንና ጴጥሮስ ከእምነታችን ተነጥለው የማይታዩትን እነዚህን ተስፋዎች ለማግኘት በመጀመሪያ ‘ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት [“ምግባረ ብልሹነት፣” NW] ማምለጥ’ እንደሚኖርብን ተናግሯል።—2 ጴጥሮስ 1:4
13. ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ምንን አጽንተው ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል?
13 አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች እንዴት ትመለከታቸዋለህ? ቀሪዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያላቸው ዓይነት አመለካከት አለህን? ለ75 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የቆየውና የወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት ወንድም ፍሬደሪክ ፍራንዝ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ስሜት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ በ1991 እንደሚከተለው ብሏል:- “‘የተወደደውንና እጅግ ታላቅ’ የሆነውን ተስፋችንን እስከዚህች ሰዓት ድረስ አጽንተን ይዘናል፤ ወደፊትም አምላክ ይህንን ቃሉን እስኪፈጽም ድረስ አጽንተን እንደያዝን እንቀጥላለን።” ወንድም ፍራንዝ አምላክ ሰማያዊ ትንሣኤን በሚመለከት ስለሰጠው ተስፋ ሁልጊዜ እርግጠኛ ነበረ፤ በ99 ዓመት ዕድሜው እስከሞተበት ጊዜ ድረስም እምነቱን አጽንቶ ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 15:42-44፤ ፊልጵስዩስ 3:13, 14፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:10-12) በተመሳሳይም ሰዎች ለዘላለም ተደስተው ገነት በምትሆን ምድር ላይ ይኖራሉ በሚለው የአምላክ ተስፋ ላይ ትኩረት በማድረግ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እምነታቸውን አጽንተው ይዘዋል። አንተስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ነህን?—ሉቃስ 23:43፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4
ለአምላክ የተስፋ ቃል የምንሰጠው ምላሽ
14. ጴጥሮስ በጎነትን በእምነት ላይ ሊጨመር የሚገባው የመጀመሪያ ባሕርይ አድርጎ የጠቀሰው ለምንድን ነው?
14 አምላክ ለገባው የተስፋ ቃል አመስጋኝ ነንን? ከሆንን አመስጋኝ መሆናችንን ልናሳይ እንደሚገባን ጴጥሮስ ገልጿል። “ስለዚህም ምክንያት” (አምላክ በጣም ውድ የሆኑ ተስፋዎችን ስለ ሰጠን) እርምጃ ለመውሰድ ልባዊ ጥረት ማድረግ ይገባናል። በእምነት ውስጥ በመሆናችን ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋር በመተዋወቃችን ብቻ ልንረካ አይገባም። ይህ ብቻውን በቂ አይደለም! በጴጥሮስ ዘመን በጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች ስለ እምነት ብዙ እየተናገሩ በጾታ ብልግና ተዘፍቀው የነበረ ይመስላል። ባሕርያቸው በጎ መሆን ያስፈልገው ስለነበር ጴጥሮስ “በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል።—2 ጴጥሮስ 1:5፤ ያዕቆብ 2:14-17
15. (ሀ) እውቀት ከበጎነት ቀጥሎ በእምነታችን ላይ ሊጨመር የሚገባው ባሕርይ ሆኖ የተጠቀሰው ለምንድን ነው? (ለ) እምነታችንን አጽንተን እንድንይዝ የሚያግዙን ሌሎች ባሕርያት ምንድን ናቸው?
15 ጴጥሮስ በጎነትን ከጠቀሰ በኋላ በእምነታችን ላይ ሊጨመሩ ወይም ሊታከሉ የሚገባቸውን ስድስት ባሕርያት ጠቅሷል። ‘በእምነት ጸንተን ለመቆም’ ከፈለግን እነዚህ እያንዳንዳቸው እንዲኖሩን ያስፈልጋል። (1 ቆሮንቶስ 16:13) ከሃዲዎች ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን ያጣምሙና’ ‘የማታለያ ትምህርት’ ይለፍፉ ስለነበር ጴጥሮስ ቀጥሎ “በበጎነትም እውቀትን [ጨምሩ]” በማለት እውቀት በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑን ጠቅሷል። ከዚያም በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በእውቀትም ራስን መግዛት፣ ራስንም በመግዛት መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:5-7፤ 2:12, 13፤ 3:16
16. ጴጥሮስ የዘረዘራቸው ባሕርያት በእምነት ላይ ከተጨመሩ ውጤቱ ምን ይሆናል? ካልተጨመሩስ?
16 እነዚህን ሰባት ነገሮች በእምነታችን ላይ ከጨመርን ውጤቱ ምን ይሆናል? ጴጥሮስ “እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት [“ትክክለኛ እውቀት፣” NW] ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና” በማለት መልሱን ይሰጣል። (2 ጴጥሮስ 1:8) በአንጻሩ ደግሞ ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፣ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፣ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።” (2 ጴጥሮስ 1:9) ጴጥሮስ ‘እናንተ፣’ ‘እኛ’ እያለ መጠቀሙን ትቶ ‘እርሱ’ ‘የእርሱ’ እያለ መናገር እንደጀመረ ልብ በል። አንዳንዶች ዕውሮች፣ የቀደመውን የሚረሱ እና ርኩሶች መሆናቸው የሚያሳዝን ቢሆንም ጴጥሮስ የመልእክቱን አንባቢ ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለመመደብ አልፈለገም።—2 ጴጥሮስ 2:2
ወንድሞቹን ማበርታት
17. ጴጥሮስ “እነዚህን ነገሮች” ተግባራዊ እንዲያደርጉ ልባዊ ማበረታቻ ለመስጠት ያነሳሳው ምን ሊሆን ይችላል?
17 ጴጥሮስ በተለይ አዲሶች በቀላሉ ሊታለሉ እንደሚችሉ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም “ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” በማለት ልባዊ ማበረታቻ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 1:10፤ 2:18) ጴጥሮስ “እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና” ብሎ እንደተናገረው በእምነታቸው ላይ እነዚህን ሰባት ነገሮች የሚጨምሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታላቅ ወሮታ ያገኛሉ። (2 ጴጥሮስ 1:11) ‘ሌሎች በጎች’ በአምላክ መንግሥት ምድራዊ ግዛት ውስጥ ዘላለማዊ ውርሻ ያገኛሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:33, 34
18. ጴጥሮስ ወንድሞቹን ‘ዘወትር ሊያሳስባቸው’ የፈለገው ለምን ነበር?
18 ጴጥሮስ ወንድሞቹ እንዲህ ያለውን ታላቅ ወሮታ እንዲያገኙ ከልቡ ይመኝ ነበር። “ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ምንም ብትጸኑ፣ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 1:12) ጴጥሮስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ‘ጸኑ’ ተብሎ የተተረጎመውን ስቴሪዞ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ሲሆን ይህ ቃል ቀደም ሲል ኢየሱስ ለጴጥሮስ በሰጠው “ወንድሞችህን አበርታ” በሚለው ማሳሰቢያ ውስጥ ‘ማበርታት’ ተብሎ ተተርጉሟል። (ሉቃስ 22:32 NW) ጴጥሮስ ይህንን ቃል መጠቀሙ ጌታው የሰጠውን ጠንካራ ማሳሰቢያ እንዳልዘነጋ ሊጠቁመን ይችላል። ቀጥሎ ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ [በሰብዓዊ አካል] ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና።”—2 ጴጥሮስ 1:13, 14
19. ዛሬ እኛ ምን እርዳታ ያስፈልገናል?
19 ጴጥሮስ አንባቢዎቹ ‘በእውነት እንደ ጸኑ’ በደግነት ቢናገርም እምነታቸው እንደመርከብ ሊሠበር እንደሚችል ዘንግቷል ማለት አልነበረም። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚሞት ያውቅ ስለነበር ትዝ ሲሏቸው መንፈሳዊ ጥንካሬ ሊሰጧቸው የሚችሉትን ነገሮች በመናገር ወንድሞቹን አበርትቶአቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:15፤ 3:12, 13) ዛሬ እኛም በእምነት ጸንተን ለመኖር የማያቋርጥ ማሳሰቢያ ያስፈልገናል። ማንም እንሁን ማን፣ የቱንም ያህል ዘመን በእውነት ውስጥ እንቆይ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን፣ የግል ጥናትንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ችላ ልንል አይገባም። አንዳንዶች ዛሬ በጣም ደክሞኛል፣ ትምህርቶቹ ተደጋጋሚ ናቸው ወይም ክፍሎቹ እንደሚገባቸው ሆነው አይቀርቡም የሚል ሰበብ በመስጠት ከስብሰባዎች ይቀራሉ፤ ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ማናችንም ብንሆን በራሳችን ከልክ በላይ የምንተማመን ከሆነ ድንገት እምነታችንን ልናጣ እንደምንችል ተገንዝቧል።—ማርቆስ 14:66-72፤ 1 ቆሮንቶስ 10:12፤ ዕብራውያን 10:25
የእምነታችን ጽኑ መሠረት
20, 21. የኢየሱስ በተዓምራዊ ሁኔታ መለወጥ የጴጥሮስን እንዲሁም ዛሬ ያለነውን ሰዎች ጨምሮ መልእክቱን የሚያነቡትን ሁሉ እምነት የሚያጠናክር የሆነው እንዴት ነው?
20 እምነታችን የተመሠረተው በብልሃት በተፈጠሩ ተረቶች ላይ ነውን? ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ጠንከር ያለ መልስ ሰጥቷል:- “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።” ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር አብረው ሳሉ ክርስቶስ በመንግሥት ክብሩ ሲገለጥ ተመልክተዋል። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል አብራርቷል:- “ከገናናው ክብር:- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።”—2 ጴጥሮስ 1:16-18
21 ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህንን ራእይ ሲመለከቱ የአምላክ መንግሥት እውን ሆኖላቸዋል! ከዚህ የተነሣ ጴጥሮስ “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን” ሲል ተናግሯል። አዎን፣ ዛሬ ያለነውን እኛን ጨምሮ የጴጥሮስን መልእክት ያነበቡ ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹትን ትንቢቶች በትኩረት የሚከታተሉበት በቂ ምክንያት አላቸው። ትንቢታዊውን ቃል በትኩረት መከታተል የምንችለው እንዴት ነው? ጴጥሮስ “ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፣ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ [“በትኩረት እንደሚከታተል፣” NW]” ነው በማለት መልሱን ይሰጠናል።—2 ጴጥሮስ 1:19፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ኢሳይያስ 9:6, 7
22. (ሀ) ልባችን ስለ ምን ነገር ንቁ ሊሆን ይገባል? (ለ) ትንቢታዊውን ቃል በትኩረት መከታተል የምንችለው እንዴት ነው?
22 ያለ ትንቢታዊው ቃል ብርሃን ልባችን ይጨልማል። ይሁን እንጂ የክርስቲያኖች ልብ ትንቢታዊውን ቃል በትኩረት በመከታተል “የንጋት ኮከብ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በመንግሥቱ ክብር ለሚመጣበት ጊዜ ንቁ ነበር። (ራእይ 22:16) ዛሬ ለትንቢታዊው ቃል ትኩረት የምንሰጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በዚያ ተገኝቶ ተሳትፎ በማድረግ እንዲሁም ‘እነዚህን ነገሮች በማሰብና በማዘውተር’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ትንቢታዊው ቃል “በጨለማ ስፍራ” (በልባችን) ውስጥ እንደሚበራ መብራት እንዲሆን ከፈለግን በጥልቅ እንዲነካን በሌላ አባባል በምኞታችን፣ በስሜታችን፣ በውስጣዊ ግፊታችን እንዲሁም በግባችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ልንፈቅድለት ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆን ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ጴጥሮስ ምዕራፍ 1ን እንደሚከተለው ሲል ደምድሟል:- “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጕም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:20, 21
23. የ2 ጴጥሮስ የመጀመሪያው ምዕራፍ አንባቢዎቹን ለምን ነገር አዘጋጅቷቸዋል?
23 ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ የመክፈቻ ምዕራፍ ውስጥ ውድ የሆነውን እምነታችንን አጽንተን እንድንይዝ ጠንካራ ውስጣዊ ግፊት ጨምሮልናል። አሁን ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንመረምራለን። በቀጣዩ ርዕስ ውስጥ ሐዋርያው ወደ ጉባኤዎቹ ውስጥ ሰርጎ ስለነበረው የብልግና ተጽዕኖ የዘረዘረበትን 2 ጴጥሮስ ምዕራፍ 2ን እንዳስሳለን።
ታስታውሳለህን?
◻ ጴጥሮስ የትክክለኛን እውቀት አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው?
◻ በጎነት በእምነት ላይ የሚጨመር የመጀመሪያው ባሕርይ ሆኖ የተጠቀሰው ለምን ሊሆን ይችላል?
◻ ጴጥሮስ ሁልጊዜ ወንድሞቹን ለማሳሰብ የፈለገው ለምን ነበር?
◻ ጴጥሮስ ለእምነታችን ጠንካራ መሠረት የሚሆን ምን ነገር ዘግቧል?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ የነበሩበት ድክመቶች እምነቱን እርግፍ አድርጎ እንዲተው አላደረጉትም