ኢየሱስ በመንግሥቱ ክብር ሲመጣ
“የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።”— ማቴዎስ 16:28
1, 2. በ32 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ምን ነገር ተከሰተ? የክስተቱ ዓላማ ምን ነበር?
በ32 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል ሦስቱ ምንጊዜም የማይረሳ አንድ ራእይ ተመለከቱ። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ታሪክ “ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ” በማለት ይገልጻል።— ማቴዎስ 17:1, 2
2 ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠበት ራእይ የታየው ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነበር። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ውስጥ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል ለተከታዮቹ መናገር ጀምሮ ነበር፤ ሆኖም የሚነግራቸውን ነገር ማስተዋል ተስኗቸው ነበር። (ማቴዎስ 16:21-23) ይህ ራእይ ሦስቱን የኢየሱስ ሐዋርያት ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው የእሱ ሞት እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ ለሚጠብቀው ብዙ ዓመት የሚወስድ ከባድ ሥራና ፈተና እንዲዘጋጁ በማድረግ እምነታቸውን አጠንክሮላቸዋል። እኛ ዛሬ ከዚህ ራእይ የምንማረው ነገር ይኖራልን? አዎን፣ ምክንያቱም ራእዩ የሚያመለክተው ነገር በቀጥታ የሚፈጸመው በዘመናችን ነው።
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ከመለወጡ ከስድስት ቀን በፊት ምን ብሎ ነበር? (ለ) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ወቅት ምን እንደተከሰተ ግለጽ።
3 ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ከመለወጡ ከስድስት ቀን በፊት ለተከታዮቹ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል” ሲል ነግሯቸው ነበር። እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት “በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ላይ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 16:27, 28፤ 24:3 NW፤ 25:31-34, 41፤ ዳንኤል 12:4) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠው በእነዚህ ቃላት ፍጻሜ መሠረት ነው።
4 ሦስቱ ሐዋርያት የተመለከቱት ነገር ምን ነበር? ሉቃስ ሁኔታውን በተመለከተ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል:- “[ኢየሱስ] ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ። እነሆም፣ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጸም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።” ከዚያም “ደመና መጣና [ሐዋርያቱን] ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም:- የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።”— ሉቃስ 9:29-31, 34, 35
እምነታችን ይጠነክራል
5. ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ በሐዋርያው ጴጥሮስ ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?
5 ሐዋርያው ጴጥሮስ ቀደም ብሎ ኢየሱስን “ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” ሲል ጠርቶታል። (ማቴዎስ 16:16) ይሖዋ ከሰማይ የተናገራቸው ቃላት የዚህን አባባል ትክክለኛነት ያረጋገጡ ሲሆን ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ የታየበት ራእይ ደግሞ ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣንና ክብር እንደሚመጣና በመጨረሻም በሰው ልጆች ላይ እንደሚፈርድ የሚያመለክት ነበር። ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ከተለወጠ 30 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። ከገናናው ክብር:- በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።”— 2 ጴጥሮስ 1:16-18፤ 1 ጴጥሮስ 4:17
6. ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ከተለወጠ በኋላ አንዳንድ ሁኔታዎች ደረጃ በደረጃ የተከሰቱት እንዴት ነበር?
6 ሦስቱ ሐዋርያት ያዩት ነገር ዛሬ የእኛንም እምነት የሚያጠነክር ነው። ከ32 እዘአ ጀምሮ የተለያዩ ሁኔታዎች ደረጃ በደረጃ ተከስተዋል። በቀጣዩ ዓመት ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ሰማይ ሄዶ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ። (ሥራ 2:29-36) በዚያው ዓመት በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት አዲሱ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተወለደ፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ከጊዜ በኋላ እስከ ምድር ዳርቻ እየሰፋ የሄደ የስብከት ዘመቻ ተጀመረ። (ገላትያ 6:16፤ ሥራ 1:8) ወዲያው ማለት ይቻላል የኢየሱስ ተከታዮች እምነት ፈተና ደረሰበት። ሐዋርያት መስበክ አናቆምም በማለታቸው ታሰሩ፣ ክፉኛም ተደበደቡ። ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ ተገደለ። ከዚያም ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሲለወጥ ተመልክቶ የነበረው ያዕቆብ ተገደለ። (ሥራ 5:17-40፤ 6:8 እስከ 7:60፤ 12:1, 2) ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን በሕይወት ቆይተው ለብዙ ተጨማሪ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። እንዲያውም ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃ አካባቢ ስለ ኢየሱስ ሰማያዊ ክብር የሚገልጽ ተጨማሪ ራእይ መዝግቧል።— ራእይ 1:12-20፤ 14:14፤ 19:11-16
7. (ሀ) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠበት ራእይ ፍጻሜ ማግኘት የጀመረው መቼ ነበር? (ለ) ኢየሱስ ለአንዳንዶች እንደ ሥራቸው ያስረከበው መቼ ነበር?
7 ዮሐንስ ያያቸው ብዙዎቹ ራእዮች የ“ጌታ ቀን” ከጀመረበት ከ1914 ጀምሮ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (ራእይ 1:10) ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በተለወጠበት ጊዜ በታየው መሠረት ‘በአባቱ ክብር እንደሚመጣ’ የሚያሳየው ራእይ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? ይህ ራእይ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ከተቋቋመበት ከ1914 ጀምሮ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ኢየሱስ የተሾመ ንጉሥ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በአጽናፈ ዓለም መድረክ እንደ ንጋት ኮከብ ብቅ ሲል በምሳሌያዊ አነጋገር አንድ አዲስ ቀን ጠብቷል። (2 ጴጥሮስ 1:19፤ ራእይ 11:15፤ 22:16) በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለአንዳንዶች እንደ ሥራቸው አስረክቧቸዋልን? አዎን። የቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ትንሣኤ የጀመረው ከዚያ ብዙም ሳይቆይ መሆኑን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ አለ።— 2 ጢሞቴዎስ 4:8፤ ራእይ 14:13
8. ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠበት ራእይ ፍጻሜ ወደ ታላቅ መደምደሚያው መድረሱን የሚያሳዩት ሁኔታዎች የትኞቹ ይሆናሉ?
8 ሆኖም በቅርቡ ኢየሱስ በመላው የሰው ዘር ላይ ለመፍረድ ‘በክብሩ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር’ ይመጣል። (ማቴዎስ 25:31) በዚያን ጊዜ በታላቅ ክብሩ ሙሉ በሙሉ በመገለጥ “ለሁሉ” እንደ ሥራው ወይም እንደ ሥራዋ ያስረክባል። በግ መሰል ሰዎች በተዘጋጀላቸው መንግሥት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ሲወርሱ ፍየል መሰል የሆኑ ሰዎች ደግሞ ወደ “ዘላለም ቅጣት” ይሄዳሉ። ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠበት ራእይ ለሚኖረው ፍጻሜ ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ መደምደሚያ ይሆናል!— ማቴዎስ 25:34, 41, 46፤ ማርቆስ 8:38፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-10
ከኢየሱስ ጋር ክብር የተጎናጸፉት ሰዎች
9. ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠበት ራእይ ፍጻሜውን በሚያገኝበት ጊዜ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ይሆናሉ ብለን መጠበቅ ይኖርብናልን? አብራራ።
9 ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ወቅት ብቻውን አልነበረም። ሙሴና ኤልያስ አብረውት ታይተዋል። (ማቴዎስ 17:2, 3) ቃል በቃል አብረውት ነበሩ ማለት ነውን? አይደለም፣ ሁለቱም ሰዎች ከረጅም ጊዜ በፊት የሞቱ ሲሆን መቃብር ውስጥ ሆነው ትንሣኤ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። (መክብብ 9:5, 10፤ ዕብራውያን 11:35) ኢየሱስ በሰማያዊ ክብር በሚመጣበት ጊዜ አብረውት ይሆናሉን? አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሙሴና ኤልያስ የሞቱት የሰው ልጆች ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ከመከፈቱ በፊት ነው። ሙሴና ኤልያስ በምድር ላይ ለመኖር ‘ከሞት ከሚነሱት ጻድቃን’ መካከል ይሆናሉ። (ሥራ 24:15) ስለዚህ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ጊዜ መታየታቸው ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ነው። ይህ ምሳሌያዊ ትርጉም ምንድን ነው?
10, 11. ኤልያስና ሙሴ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እነማንን ለማመልከት አገልግለዋል?
10 ሙሴና ኤልያስ በሌሎች ቦታዎች ላይ በትንቢታዊ ጥላነት አገልግለዋል። የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ የነበረው ሙሴ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ለሆነው ለኢየሱስ ጥላ ነበር። (ዘዳግም 18:18፤ ገላትያ 3:19፤ ዕብራውያን 8:6) ኤልያስ ደግሞ የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ለነበረው ለመጥምቁ ዮሐንስ ጥላ ነበር። (ማቴዎስ 17:11-13) በተጨማሪም ሙሴና ኤልያስ በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ በፍጻሜው ዘመን የሚኖሩትን ቅቡዓን ቀሪዎችን እንደሚያመለክቱ ሆነው ተገልጸዋል። ይህን እንዴት እናውቃለን?
11 ራእይ 11:1-6ን አውጡ። ቁጥር 3 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።” ይህ ትንቢት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቀሪዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል።a ሁለት ምስክሮች የተባሉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቅቡዓን ቀሪዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር የሚመሳሰሉ ሥራዎችን ስለሚያከናውኑ ነው። በቁጥር 5 እና 6 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን:- “[ሁለቱን ምስክሮች] ማንም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፣ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው።” ይህም ኤልያስና ሙሴ የፈጸሟቸውን ተአምራት እንድናስታውስ ያደርገናል።— ዘኁልቁ 16:31-34፤ 1 ነገሥት 17:1፤ 2 ነገሥት 1:9-12
12. ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ራእይ ላይ በሙሴና በኤልያስ የተመሰሉት እነማን ናቸው?
12 ታዲያ ሙሴና ኤልያስ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ጊዜ የታዩት እነማንን ለማመልከት ነው? ሉቃስ ከኢየሱስ ጋር “በክብር” እንደታዩ ገልጿል። (ሉቃስ 9:31) ከኢየሱስ ጋር ‘አብረው ወራሾች’ እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡትንና ከእርሱ ጋር ‘ክብር የመጎናጸፍ’ አስደናቂ ተስፋ ያገኙትን ክርስቲያኖች እንደሚያመለክቱ ግልጽ ነው። (ሮሜ 8:17) ኢየሱስ “ለሁሉ እንደ ሥራው ለማስረከብ” በአባቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ ከሞት የተነሱት ቅቡዓን አብረውት ይሆናሉ።— ማቴዎስ 16:27
እንደ ሙሴና ኤልያስ ያሉ ምስክሮች
13. ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ክብር በመጎናጸፍ አብረው ወራሾች የሚሆኑትን ቅቡዓን በትክክል ያመለክታሉ የሚያሰኙት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?
13 ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ወራሽ የሆኑትን ቅቡዓን በሚገባ የሚያመለክቱ ትንቢታዊ ጥላዎች መሆናቸውን የሚያሳዩ ጉልህ ገጽታዎች አሉ። ሙሴና ኤልያስ ለብዙ ዓመታት የይሖዋ ቃል አቀባዮች ሆነው አገልግለዋል። ሁለቱም ከገዥዎች ቁጣ ደርሶባቸዋል። ችግር ላይ በወደቁበት ወቅት እያንዳንዳቸው ባዕድ ከሆነ ቤተሰብ ድጋፍ አግኝተዋል። ሁለቱም በድፍረት ለነገሥታት ትንቢት ከመናገራቸውም በላይ ሐሰተኛ ነቢያትን በጽናት ተቋቁመዋል። ሙሴም ሆነ ኤልያስ የይሖዋን ኃይል መግለጫዎች በሲና ተራራ ላይ (ኮሬብ ተብሎም ይጠራል) አይተዋል። ሁለቱም ተተኪዎቻቸውን የሾሙት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ነው። በኢየሱስ ዘመን የተፈጸሙትን ሳይጨምር በጣም ብዙ ተአምራት የተፈጸሙት ሙሴ (ከኢያሱ) ኤልያስ (ከኤልሳዕ) ጋር በነበሩበት ዘመን ነው።b
14. ቅቡዓኖች እንደ ሙሴና ኤልያስ የይሖዋ ቃል አቀባዮች ሆነው ያገለገሉት እንዴት ነው?
14 ይህ ሁሉ የአምላክ እስራኤልን አያስታውሰንምን? በሚገባ ያስታውሰናል። ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑት ተከታዮቹ እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ትእዛዝ በማክበር በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የይሖዋ ቃል አቀባዮች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። እንደ ሙሴና ኤልያስ ከገዢዎች ቁጣ ደርሶባቸዋል፤ እንዲሁም ለገዢዎች መስክረዋል። ኢየሱስ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት “ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ” ሲል ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:18) ኢየሱስ የተናገረው ነገር በክርስቲያን ጉባኤ ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተፈጽሟል።— ሥራ 25:6, 11, 12, 24-27፤ 26:3
15, 16. (ሀ) ያለፍርሃት ለእውነት መቆማቸውን (ለ) እስራኤላውያን ካልሆኑ ሰዎች ድጋፍ ማግኘታቸውን በተመለከተ ሙሴና ኤልያስን ከቅቡዓን ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው?
15 በተጨማሪም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርትን በመቃወምና ለእውነት በመቆም ረገድ እንደ ሙሴና ኤልያስ ደፋሮች ሆነዋል። ጳውሎስ በርያሱስ የተባለውን ሐሰተኛ የአይሁድ ነቢይ እንዴት እንዳወገዘና የአቴናውያንን አማልክት ሐሰተኝነት ዘዴ በመጠቀም እንዴት በድፍረት እንዳጋለጠ አስታውሱ። (ሥራ 13:6-12፤ 17:16, 22-31) በዘመናችንም ቅቡዓን ቀሪዎች ሕዝበ ክርስትናን በድፍረት እንዳጋለጡና ይህ ምስክርነት እንዳሰቃያት አስታውሱ።— ራእይ 8:7-12c
16 ሙሴ ከፈርዖን ቁጣ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እስራኤላዊ ባልሆነውና ዮቶር ተብሎም በሚጠራ ራጉኤል በተባለ ሰው ቤት መጠጊያ አግኝቶ ነበር። ከጊዜ በኋላም ሙሴ አደረጃጀትን በተመለከተ ከራጉኤል ጠቃሚ የሆነ ምክር የተቀበለ ሲሆን የራጉኤል ልጅ ኦባብ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ መርቷል።d (ዘጸአት 2:15-22፤ 18:5-27፤ ዘኁልቁ 10:29) የአምላክ እስራኤል አባላት ቅቡዓን የአምላክ እስራኤል አባላት ካልሆኑ ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ድጋፍ አግኝተዋልን? አዎን፣ በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ወደ መድረኩ ብቅ ካሉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል ከሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ድጋፍ አግኝተዋል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16፤ ኢሳይያስ 61:5) እነዚህ “በጎች” ለቅቡዓን ወንድሞቹ የሚሰጡትን የጋለ ፍቅራዊ ድጋፍ አስመልክቶ ኢየሱስ እንዲህ ሲል በትንቢት ተናግሯል:- “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። . . . እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።”— ማቴዎስ 25:35-40
17. ቅቡዓኖች ኤልያስ በኮሬብ ተራራ ካጋጠመው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያጋጠማቸው እንዴት ነው?
17 በተጨማሪም የአምላክ እስራኤል የሆኑት ኤልያስ በኮሬብ ተራራ ካጋጠመው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሁኔታ አጋጥሟቸዋል።e ኤልያስ ከንግሥት ኤልዛቤል በሸሸበት ጊዜ እንደተሰማው ሁሉ በፍርሃት ተውጠው የነበሩት ቅቡዓን ቀሪዎችም በአንደኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ ሥራችን ይጠናቀቃል ብለው አስበው ነበር። ከዚያም በኤልያስ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ይሖዋ ‘የአምላክ ቤት’ ነን በሚሉት ላይ ሊፈርድ በመጣበት ጊዜ አገኛቸው። (1 ጴጥሮስ 4:17፤ ሚልክያስ 3:1-3) ሕዝበ ክርስትና እንደሚጠበቅባት ሆና ባለመገኘቷ ቅቡዓን ቀሪዎች እንደ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው እውቅና በማግኘት በመላው የኢየሱስ ምድራዊ ንብረት ላይ ተሾሙ። (ማቴዎስ 24:45-47) በኮሬብ ተራራ ላይ ይሖዋ ኤልያስን ‘ዝግ ባለ ድምፅ’ በማነጋገር ተጨማሪ ሥራ ሰጠው። ከጦርነቱ በኋላ በነበረው የተረጋጋ ወቅት ቅቡዓን ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የይሖዋን ድምፅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ሰሙ። እነሱም ገና የሚፈጽሙት ተልዕኮ እንዳለ ተገነዘቡ።— 1 ነገሥት 19:4, 9-18፤ ራእይ 11:7-13
18. በአምላክ እስራኤል አማካኝነት አስደናቂ የይሖዋ ኃይል መግለጫ የታየው እንዴት ነው?
18 በመጨረሻም በአምላክ እስራኤል አማካኝነት የይሖዋ ኃይል መግለጫ የሆኑ ድንቅ ነገሮች ተከናውነዋልን? ሐዋርያት ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ብዙ ተዓምራት ፈጽመዋል፤ ይሁን እንጂ ይህ ነገር ከጊዜ በኋላ ቆሟል። (1 ቆሮንቶስ 13:8-13) በአሁኑ ጊዜ ቃል በቃል የሚፈጸሙ ተአምራትን አናይም። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:12) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን በመላው የሮም ግዛት በመስበካቸው ይህ አነጋገር የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሮሜ 10:18) ቅቡዓን ቀሪዎች ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን በዓለም በሙሉ’ እየተካሄደ ባለው ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፋቸው በዛሬው ጊዜ ከዚያም የበለጠ ነገር በመከናወን ላይ ይገኛል። (ማቴዎስ 24:14) ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የተሰበሰቡት በ20ኛው መቶ ዘመን ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:9, 10) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ የይሖዋ ኃይል መግለጫ ነው!— ኢሳይያስ 60:22
የኢየሱስ ወንድሞች ክብር ተጎናጽፈው ይመጣሉ
19. የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ከእሱ ጋር ክብር ተጎናጽፈው የሚታዩት መቼ ነው?
19 ቀሪዎቹ ቅቡዓን የኢየሱስ ወንድሞች ምድራዊ ሕይወታቸውን ሲጨርሱ ከእሱ ጋር ክብር ይጎናጸፋሉ። (ሮሜ 2:6, 7፤ 1 ቆሮንቶስ 15:53፤ 1 ተሰሎንቄ 4:14, 17) በዚህ መንገድ በሰማያዊው መንግሥት ለዘላለም የማይሞቱ ነገሥታትና ካህናት ይሆናሉ። ከዚያም ከኢየሱስ ጋር በመሆን ‘ሰዎችን በብረት በትር ይገዟቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ያደቋቸዋል።’ (ራእይ 2:27፤ 20:4-6፤ መዝሙር 110:2, 5, 6) “በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ” ሲፈርዱ ከክርስቶስ ጋር በዙፋኖች ላይ ይቀመጣሉ። (ማቴዎስ 19:28) በመቃተት ላይ ያለው ፍጥረት ‘የአምላክ ልጆች መገለጥ’ ክፍል የሆኑትን እነዚህን ክንውኖች በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነው።— ሮሜ 8:19-21፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-8
20. (ሀ) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ የጴጥሮስን እምነት ያጠነከረው በምን ረገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚያጠነክረው እንዴት ነው?
20 “በታላቁ መከራ” ወቅት የኢየሱስን መገለጥ በተመለከተ ጳውሎስ “በቅዱሳኑ ሊከበር፣ በሚያምኑትም ሁሉ ዘንድ . . . ሊደነቅ” ይመጣል ሲል ጽፏል። (ማቴዎስ 24:21፤ 2 ተሰሎንቄ 1:10 የ1980 ትርጉም ) ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብ፣ ለዮሐንስና በመንፈስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች በጠቅላላ ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ የጴጥሮስን እምነት አጠንክሮለታል። እኛም ብንሆን ይህን ዘገባ ማንበባችን እምነታችንን እንደሚያጠነክርልንና በቅርቡ ኢየሱስ ‘ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው እንደሚያስረክብ’ ያለንን ትምክህት ከፍ እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ነው። አሁን በሕይወት ያሉ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ክብር እንደሚጎናጸፉ የጸና ትምክህት እንዲኖራቸው አድርጓል። ሌሎች በጎች ደግሞ ከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ድነው ክብራማ ወደሆነው አዲስ ዓለም እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸው ማወቃቸው እምነታቸውን አጠንክሮላቸዋል። (ራእይ 7:14) እስከ መጨረሻው እንድንጸና የሚያደርግ እንዴት ያለ ግሩም ማበረታቻ ነው! በሚቀጥለው ርዕስ እንደምንመለከተው ይህ ራእይ ሌላ ተጨማሪ ነገርም ሊያስተምረን ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙትን “ስምህ ይቀደስ” የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ገጽ 313-14 እና ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 164-5 ተመልከት።
b ዘጸአት 2:15-22፤ 3:1-6፤ 5:2፤ 7:8-13፤ 8:18፤ 19:16-19፤ ዘዳግም 31:23፤ 1 ነገሥት 17:8-16፤ 18:21-40፤ 19:1, 2, 8-18፤ 2 ነገሥት 2:1-14
d ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ከአርማጌዶን በሕይወት ተርፋችሁ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ትገቡ ይሆናል የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ገጽ 281-3 ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
◻ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ እነማን አብረውት ታይተዋል?
◻ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በመለወጡ የሐዋርያት እምነት የጠነከረው እንዴት ነበር?
◻ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ አብረውት “ክብር ተጎናጽፈው” የታዩት ሙሴና ኤልያስ እነማንን ያመለክታሉ?
◻ ሙሴና ኤልያስን ከአምላክ እስራኤል ጋር የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትንም ሆነ ዛሬ ያሉትን ክርስቲያኖች እምነት አጠንክሯል