አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
የዛሬ ስድስት ሺህ ዓመት ገደማ የመጀመሪያው ሕፃን ተወለደ። ልጁ ከተወለደ በኋላ እናቱ ሔዋን “በእግዚአብሔር ዕርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። (ዘፍጥረት 4:1 የ1980 ትርጉም) የሔዋን አነጋገር እርሷና ባሏ አዳም በአምላክ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ሞት ቢፈረድባቸውም የይሖዋን አምላክነት ይቀበሉ እንደነበር ያሳያል። በኋላም ሁለተኛ ልጅ ወለዱ። የልጆቹ ስም ቃየንና አቤል ነበር።
ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ፍጥረታቱን በመመርመር ብቻ ይሖዋ ስላለው ፍቅር ብዙ ነገር እንዳወቁ አያጠራጥርም። ተፈጥሮ የተላበሰቻቸውን ውብ ኅብረ ቀለማት እንዲሁም የተለያዩ እንስሳትንና ተክሎችን በማየት ይደሰቱ ነበር። አምላክ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥ ደስታ የሚያገኙበትን ችሎታ ጭምር ሰጥቷቸው ነበር።
ወላጆቻቸው ፍጹም ተደርገው እንደተፈጠሩና የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ መሆኑን ያውቁ ነበር። አዳምና ሔዋን ውብ ስለሆነው ኤደን ገነት ተርከውላቸውና እንዲህ ካለው ገነታዊ መኖሪያ የተባረሩበትን ምክንያት በሆነ መንገድ ነግረዋቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ቃየንና አቤል በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተመዘገበውን መለኮታዊ ትንቢት ያውቁት ይሆናል። ይሖዋ በዚህ ትንቢት አማካይነት እርሱን የሚወዱትንና ለእርሱ ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩትን ሰዎች ለመጥቀም ሲል በተገቢው ጊዜ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ያለውን ዓላማ ገልጿል።
ቃየንና አቤል ስለ ይሖዋና ስላሉት ባሕርያት ማወቃቸው የአምላክን ሞገስ የማግኘት ፍላጎት አሳድሮባቸው መሆን አለበት። በዚህ የተነሳ መሥዋዕት ይዘው ወደ ይሖዋ ቀረቡ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ታሪክ “ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ” ይላል።—ዘፍጥረት 4:3, 4
የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የነበራቸው ፍላጎት ከእርሱ ጋር ለመዛመድ መሠረት ጥሎላቸዋል። ቃየን በመጨረሻ በአምላክ ላይ ያመፀ ሲሆን በሌላ በኩል ግን አቤል ለአምላክ ልባዊ ፍቅር ማሳየቱን ቀጥሏል። አቤል በመጀመሪያ ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ዓላማዎች እውቀት ባያገኝ ኖሮ ከአምላክ ጋር እንደዚህ ያለ ዝምድና አይኖረውም ነበር።
አንተም ብትሆን ይሖዋን ልታውቀው ትችላለህ። ለምሳሌ አምላክ ነገሮችን በአጋጣሚ የሚፈጥር ሕይወት አልባ ኃይል ሳይሆን እውን አካል እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር ትችላለህ። (ከዮሐንስ 7:28 አዓት፤ ዕብራውያን 9:24፤ ራእይ 4:11 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።—ዘጸአት 34:6
‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’
ከቃየንና ከአቤል ታሪክ እንደታየው አምላክን ማወቅና ከእርሱ ጋር የቅርብ ዝምድና ለመመሥረት መፈለግ ብቻ አይበቃም። ሁለቱ ወንድማማቾች መሥዋዕት በመያዝ ወደ አምላክ ቀርበው ነበር። ሆኖም “እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።”—ዘፍጥረት 4:3-5
ይሖዋ የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለው ለምንድን ነው? በመሥዋዕቱ ላይ አንድ እንከን ነበረበትን? ይሖዋ በመሥዋዕቱ ያልተደሰተው ቃየን የእንስሳ መሥዋዕት ማቅረብ ሲገባው “ከምድር ፍሬ” ስላቀረበ ነውን? ለዚህ ላይሆን ይችላል። አምላክ ከጊዜ በኋላ እርሱን የሚያመልኩ ብዙ ሰዎች ያቀረቡለትን የእህልና የሌሎች የምድር ፍሬዎች መሥዋዕት በደስታ ተቀብሏል። (ዘሌዋውያን 2:1-16) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በቃየን ልብ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ነገር ነበረ። ይሖዋ የቃየንን ልብ ማንበብ ከመቻሉም በተጨማሪ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆት ነበር፦ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው።”—ዘፍጥረት 4:6, 7
ለአምላክ ልባዊ ፍቅር ማሳየት መሥዋዕት ከማቅረብ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። ቃየን ‘መልካም እንዲያደርግ’ ይሖዋ ያበረታታው ለዚህ ነው። አምላክ ታዛዥነት ፈልጎ ነበር። ቃየን ለአምላክ እንዲህ ያለ ታዛዥነት ቢያሳይ ኖሮ ከፈጣሪ ጋር ፍቅር የተሞላበት ዝምድና ለመገንባት የሚያስችል ጥሩ መሠረት ለመጣል ይረዳው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ታዛዥነት ያለውን ዋጋ በሚከተሉት ቃላት ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል፦ “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።”—1 ሳሙኤል 15:22
ከጊዜ በኋላም የታዛዥነት አስፈላጊነት በ1 ዮሐንስ 5:3 ላይ በሚገኙት በሚከተሉት ቃላት ጥሩ ተደርጎ ተገልጿል፦ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።” ራሳችንን ለይሖዋ ከማስገዛት የተሻለ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ሌላ መንገድ የለም። ራሳችንን ለይሖዋ ማስገዛት ማለት ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያ መታዘዝ ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይህም ጥሩ የሆነውን መውደድና መጥፎ የሆነውን መጥላት ማለት ነው።—መዝሙር 97:10፤ 101:3፤ ምሳሌ 8:13
ለአምላክ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ዋነኛው መንገድ ሰዎችን መውደድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፦ “ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?”—1 ዮሐንስ 4:20
የአምላክ የቅርብ ወዳጅ መሆን ይቻላል
አንዳንዶች እንዲህ ይሉ ይሆናል፦ ‘ይሖዋን አመልካለሁ። ሕጎቹን እጠብቃለሁ። ሰዎችን አላበላልጥም። እነዚህን ሁሉ ባደርግም ከአምላክ ጋር የተቀራረብኩ ሆኖ አይሰማኝም። በጣም የምወደው መስሎ አይሰማኝም፤ ይህም የጥፋተኝነት ስሜት አሳድሮብኛል።’ አንዳንዶች ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት ለመመሥረት ብቁ እንዳልሆኑ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።
አንድ ክርስቲያን 37 ለሚያክሉ ዓመታት ይሖዋን ካገለገለ በኋላ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ብዙ ጊዜ ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎት በቅንዓት እንዳላከናወንኩ ይሰማኛል፤ ይሖዋን ከልቤ ያገለገልኩት አይመስለኝም። ሆኖም ይሖዋን ማገልገል አስፈላጊ ሥራ መሆኑን ስለማውቅ ማገልገሌን አላቆምኩም ነበር። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ‘ልባቸው በይሖዋ ፍቅር መሞላቱን’ እንደተናገሩ የሚገልጽ ጽሑፍ ባነበብኩ ቁጥር ‘እኔ እንደዚህ የማይሰማኝ ለምንድን ነው?’ በማለት ራሴን እጠይቃለሁ።” ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት ነው?
ለአንድ ሰው እውነተኛ ፍቅር ካደረብህ ብዙ ጊዜ ስለዚያ ሰው ታስባለህ። ስለምታስብለት ፈጽሞ ከእርሱ መራቅ አትፈልግም። ይበልጥ ባየኸው፣ ባነጋገርከውና ስለ እርሱ ባሰብክ መጠን ለእርሱ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለአምላክ ያለህን ፍቅር ለማዳበርም ይጠቅምሃል።
በመዝሙር 77:12 (የ1980 ትርጉም) ላይ አንድ ጸሐፊ በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ “ስላደረግኸው ነገር ሁሉ አስባለሁ፤ ስለ ታላላቅ ሥራዎችህም በማሰላሰል አስታውሳለሁ” ብሏል። ለአምላክ ያለንን ፍቅር በመኮትኮት በኩል ማሰላሰል ከፍተኛ ጥቅም አለው። ይሖዋ የማይታይ ስለሆነ በተለይ በዚህ ረገድ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። ሆኖም ስለ እርሱ ይበልጥ ባሰብክ መጠን ይበልጥ እውን ይሆንልሃል። ከእርሱ ጋር ልባዊና ፍቅር የተሞላበት ዝምድና መመሥረት የምትችለው ስለ እርሱ ካሰላሰልክ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ካደረግህ እውን ይሆንልሃል።
ስለ ይሖዋ መንገዶችና ሥራዎች ዘወትር ለማሰላሰል ያለህ ዝንባሌ እርሱን በምታዳምጥበት መጠን ላይ የተመካ ነው። አምላክን የምታዳምጠው ቃሉ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ዘወትር በማንበብና በማጥናት ነው። መዝሙራዊው ‘የይሖዋን ሕግ የሚወድ፣ በቀንና በሌሊት የሚያነበው’ ሰው ደስተኛ እንደሆነ ተናግሯል።—መዝሙር 1:1, 2 አዓት
ሌላው ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚረዳ አስፈላጊ ነገር ጸሎት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዘወትር ጸልዩ፣’ ‘ለጸሎት ትጉ፣’ “በጸሎት ጽኑ” እና “ሳታቋርጡ ጸልዩ” በማለት በተደጋጋሚ አጥብቆ የሚመክረን ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 6:18፤ 1 ቆሮንቶስ 7:5፤ ሮሜ 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) ለይሖዋ የምናቀርበው የማያቋርጥ ጸሎት በእርሱ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል፤ በተጨማሪም እንደሚሰማን ያለን ትምክህት ወደ እርሱ እንድንቀርብ ያስችለናል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ” በማለት ይህ እውነት መሆኑን አረጋግጧል።—መዝሙር 116:1, 2
የፍቅርን አምላክ መምሰል
ይሖዋ ለእኛ ጥሩ አምላክ ነው። የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ስለሆነ በእእምሮው የሚይዛቸውና የሚያሳስቡት ብዙ ነገሮች አሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከፍተኛ ግርማ ሞገስ ያለው ታላቅ አምላክ ቢሆንም ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ያስባል። በጣም ይወደናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ይህንን ያረጋግጥልናል፦ “አቤቱ ጌታችን፣ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፣ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና። የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ [“ሟች የሆነ፣” አዓት] ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?”—መዝሙር 8:1, 3, 4
ይሖዋ ሟች የሆነውን ሰው የሚያስበው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”—1 ዮሐንስ 4:9, 10
ይህ የኃጢአት ማስተስርያ የአምላክ ፍቅር የላቀ ማስረጃ የሆነው እንዴት ነው? በኤደን የአትክልት ስፍራ የተፈጸመውን ነገር እንመልከት። አዳምና ሔዋን በፊታቸው ምርጫ ቀርቦ ነበር። ይኸውም ለይሖዋ ሕግ በመገዛት ፍጹም ሆኖ ለዘላለም መኖር ወይም በይሖዋ ላይ ዓምፆ መሞት። አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ማመፁን መረጡ። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይህን በማድረጋቸውም በሁሉም የሰው ዘር ላይ ሞት ፈረዱ። (ሮሜ 5:12) ለራሳችን ራሳችን የመወሰን መብታችንን በማንአለብኝነት ቀሙን። ማናችንም ብንሆን በጉዳዩ ላይ የራሳችንን ውሳኔ ለማድረግ አጋጣሚው አልነበረንም።
ሆኖም ይሖዋ ሟች የሆኑት ሰዎች ያለባቸውን አሳዛኝ ሁኔታ በመገንዘብ ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ ለሰዎች ማሰቡን አላቆመም። ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት አማካይነት እያንዳንዱ ሰው ሕይወትን ወይም ሞትን፣ ታዛዥነትን ወይም ዓመፅን ራሱ እንዲመርጥ የሚያስችል ዝግጅት አደረገ። (ዮሐንስ 3:16) ይሖዋ እኛ ራሳችን ባደረግነው ምርጫ መሠረት ፍርድ እንድናገኝ ያደረገ ያህል ነው፤ በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደ ኤደን ተመልሰን የራሳችንን ምርጫ የማድረግ አጋጣሚ ሰጥቶናል። ይህም እስከ ዛሬ ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ የላቀ ነው።
ይሖዋ የበኩር ልጁ ሲሰደብ፣ ሲሠቃይና እንደ ወንጀለኛ ሲሰቀል በሚመለከትበት ጊዜ ያሳለፈውን ሥቃይ አስብ። አምላክ ይህን ሁሉ ዝም ብሎ የተመለከተው ለእኛ ሲል ነው። ይሖዋ በራሱ አነሳሽነት አስቀድሞ እንደወደደን ማወቃችን እርሱን እንድንወደውና እንድንፈልገው ሊያንቀሳቅሰን ይገባል። (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ዮሐንስ 4:19) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። . . . የሠራትን ድንቅ አስቡ፣ ተኣምራቱን የአፉንም ፍርድ” በማለት ይጋብዘናል።—መዝሙር 105:4, 5
ከአምላክ ጋር የግል ቅርርብና ፍቅራዊ ዝምድና መመሥረት ወይም በሌላ አባባል የእርሱ ጓደኛ መሆን የማይቻል ነገር አይደለም። ይህንን ማድረግ ይቻላል። ለአምላክ ያለንን ፍቅር ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ከምናሳየው ፍቅር ጋር አንድ በአንድ ልናወዳድረው እንደማንችል የታወቀ ነው። ለትዳር ጓደኛችን፣ ለሥጋዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ለልጆቻችን ወይም ለጓደኞቻችን የምናሳየው ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር የተለየ ነው። (ማቴዎስ 10:37፤ 19:29) ይሖዋን ማፍቀር ለእርሱ ያደርን እንድንሆን፣ እንድናመልከውና ራሳችንን ያለ ገደብ እንድንወስንለት ይጠይቅብናል። (ዘዳግም 4:24) እነዚህን ነገሮች የሚጠይቅ ሌላ ዓይነት ዝምድና የለም። ለአምላክ ግን እንደምናከብረውና እንደምናደንቀው በሚያሳይ መንገድ ጠንካራና ጥልቅ ፍቅር ማሳየት እንችላለን።—መዝሙር 89:7
ምንም እንኳ እንደ ቃየንና አቤል ፍጽምና የጎደለህ ብትሆንም ፈጣሪህን መውደድ ትችላለህ። ቃየን የራሱን ምርጫ በማድረግ ከሰይጣን ጋር ተባበረና የመጀመሪያው ሰብዓዊ ነፍሰ ገዳይ ሆነ። (1 ዮሐንስ 3:12) በሌላ በኩል ይሖዋ አቤልን የእምነት ሰውና ጻድቅ አድርጎ ያስበዋል፤ በተጨማሪም ከሞት አስነስቶ ወደፊት በሚመጣው ገነት ውስጥ በሕይወት እንዲኖር ያደርገዋል።—ዕብራውያን 11:4
በአንተም ፊት ምርጫ ቀርቧል። አምላክ በመንፈሱና በቃሉ በሚያቀርብልህ እርዳታ አማካኝነት አምላክን “በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ” መውደድ ትችላለህ። (ዘዳግም 6:5) እንዲህ ካደረግህ ይሖዋ ‘ለሚፈልጉት ዋጋ የሚሰጥ’ ስለሆነ አንተን መውደዱን ይቀጥላል።—ዕብራውያን 11:6
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የአቤልን መሥዋዕት ተቀብሏል