ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ አስተምሯቸው
“በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው።”—መዝሙር 127:4
1, 2. ልጆች “በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች” የሆኑት እንዴት ነው?
አንድ ቀስተኛ ዒላማውን ለመምታት ፍላጻውን እያዘጋጀ ነው እንበል። ፍላጻውን፣ ማስፈንጠሪያው ጅማት ላይ በጥንቃቄ በማድረግ ደጋኑን ይወጥረዋል። ይህን ማድረግ ጥረት ቢጠይቅበትም በጥንቃቄና በትዕግሥት ፍላጻውን ዒላማው ላይ ያነጣጥራል። እንዲህ ካደረገ በኋላ ፍላጻውን ያስፈነጥረዋል! ፍላጻው የታለመለትን ዒላማ ይመታ ይሆን? ይህ በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ ነው፤ ከእነዚህም መካከል የቀስተኛው ብቃት እንዲሁም የነፋሱና የፍላጻው ሁኔታ ይገኙበታል።
2 ንጉሥ ሰሎሞን ልጆችን ‘በጦረኛ እጅ ካሉ ፍላጾች’ ጋር አመሳስሏቸዋል። (መዝሙር 127:4) ይህ ምሳሌ ከወላጆች ጋር በተያያዘ እንዴት እንደሚሠራ እንመልከት። አንድ ቀስተኛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ፍላጻውን አነጣጥሮ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ነው። ዒላማውን ለመምታት፣ ፍላጻውን በፍጥነት ሊያስፈነጥረው ይገባል። በተመሳሳይም ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን ከልባቸው እንዲወዱት ለመርዳት ያላቸው ጊዜ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ይወጣሉ። (ማቴዎስ 19:5) ታዲያ ልጆቹ የታለመላቸውን ዒላማ ይመቱ ይሆን? በሌላ አባባል ከቤት ከወጡ በኋላም አምላክን መውደዳቸውንና ማገልገላቸውን ይቀጥሉ ይሆን? ይህ በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ ነው። ከእነዚህም መካከል የወላጆች ብቃት፣ ልጆቹ ያደጉበት ሁኔታና ‘ፍላጻዎቹ’ ወይም ልጆቹ ለሚያገኙት ሥልጠና የሚሠጡት ምላሽ ይገኙበታል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከታቸው። በመጀመሪያ ብቃት ያለው ወላጅ የሚያደርጋቸውን አንዳንድ ነገሮች እንመለከታለን።
ብቃት ያላቸው ወላጆች ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ
3. ወላጆች የሚናገሩትን ነገር በተግባር ማዋል ያለባቸው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ፣ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖር ስለነበር ለወላጆች ምሳሌ ይሆናቸዋል። (ዮሐንስ 13:15) በሌላ በኩል ግን ፈሪሳውያን “እንደሚናገሩት” ‘ስለማያደርጉ’ አውግዟቸዋል። (ማቴዎስ 23:3) ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ለማድረግ ከፈለጉ የሚናገሩትን ነገር በተግባር ማዋል አለባቸው። በተግባር ያልተደገፉ ቃላት ማስፈንጠሪያ እንደሌለው ፍላጻ ዋጋ ቢስ ናቸው።—1 ዮሐንስ 3:18
4. ወላጆች ራሳቸውን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይገባቸዋል? ለምንስ?
4 የወላጆች ምሳሌነት ያን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አዋቂዎች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን መውደድ መማር እንደሚችሉ ሁሉ ልጆችም ከወላጆቻቸው ጥሩ ምሳሌነት ይህን መማር ስለሚችሉ ነው። ልጆች የሚመርጧቸው ጓደኞች ሊያበረታቷቸው አሊያም ‘መልካም ጠባያቸውን ሊያበላሹባቸው’ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) አንድ ልጅ፣ በአብዛኛው የሕይወቱ ክፍል በጣም የሚቀርቡትና ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩበት ጓደኞቹ ወላጆቹ ናቸው፤ በተለይም በልጁ ባሕርይና አመለካከት ላይ ጠቃሚ እንዲሁም ዘላቂ የሆነ ተጽዕኖ ማሳደር በሚቻልባቸው እድገት በሚያደርግባቸው ዓመታት ይህ እውነት ነው። በመሆኑም ወላጆች እንደሚከተለው በማለት ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው:- ‘ለልጄ ምን ዓይነት ጓደኛ ነኝ? የእኔ ምሳሌነት ልጄ ጠቃሚ ልማዶችን እንዲያዳብር የሚያበረታታው ነው? እንደ ጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባሉት በጣም አስፈላጊ ነገሮች ረገድ ምን ዓይነት ምሳሌ ነኝ?’
ብቃት ያላቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ይጸልያሉ
5. ልጆች፣ ወላጆቻቸው ከሚያቀርቡት ጸሎት ምን ሊማሩ ይችላሉ?
5 ልጆቻችሁ የእናንተን ጸሎት በማዳመጥ ስለ ይሖዋ ብዙ ሊማሩ ይችላሉ። በምግብ ሰዓት አምላክን ስታመሰግኑና መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠኑበት ወቅት ስትጸልዩ ሲሰሙ ምን መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ? ይሖዋ፣ ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን እንደሚያሟላልንና ለዚህም ልናመሰግነው እንደሚገባ እንዲሁም መንፈሳዊ እውነቶችን እንደሚያስተምረን ሊገነዘቡ ይችላሉ። እነዚህ ደግሞ በጣም ጠቃሚ ትምህርቶች ናቸው።—ያዕቆብ 1:17
6. ልጆች፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው እንዲሰማቸው ወላጆች ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
6 ከምግብ ሰዓትና ከቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተጨማሪ በሌሎች ጊዜያት ከቤተሰባችሁ ጋር የምትጸልዩ እንዲሁም በጸሎታችሁ ውስጥ እናንተንና ልጆቻችሁን የሚነኩ ጉዳዮችን የምትጠቅሱ ከሆነ ደግሞ ለልጆቻችሁ የበለጠ ትምህርት ትሰጧቸዋላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁ፣ ይሖዋ የቤተሰባችሁ ክፍል እንደሆነና ለእያንዳንዳችሁ በጥልቅ እንደሚያስብ እንዲሰማቸው ታደርጋላችሁ። (ኤፌሶን 6:18፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) አንድ አባት እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ልጃችን ከተወለደችበት ጊዜ አንስቶ አብረናት እንጸልይ ነበር። እያደገች ስትሄድ ከሰዎች ጋር ስለሚኖራት ግንኙነትና እሷን ስለሚያሳስቧት ሌሎች ጉዳዮች አንስተን እንጸልይ ነበር። አግብታ ከቤት እስከወጣችበት ጊዜ ድረስ አብረን ሳንጸልይ አንድም ቀን አልፎ አያውቅም።” እናንተስ ከልጆቻችሁ ጋር በየቀኑ መጸለይ ትችላላችሁ? ይሖዋን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን ስሜታቸውንም የሚረዳላቸው ወዳጅ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት ልትረዷቸው ትችሉ ይሆን?—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
7. ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ሁኔታ ለይተው በመጥቀስ ለመጸለይ ምን ማወቅ አለባቸው?
7 እርግጥ ነው፣ ስለ ልጃችሁ ሁኔታ ለይታችሁ በመጥቀስ መጸለይ እንድትችሉ ልጃችሁ ስለሚያጋጥሙት ነገሮች ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ሁለት ሴቶች ልጆችን ያሳደገ አንድ አባት የሰጠውን ሐሳብ እንመልከት:- “በሳምንቱ መጨረሻ ራሴን ሁለት ጥያቄዎች እጠይቃለሁ፤ ‘በዚህ ሳምንት ልጆቼን ያሳሰቧቸው ጉዳዮች ምን ነበሩ? ምን ጥሩ ነገርስ አጋጥሟቸዋል?’” ወላጆች፣ እናንተስ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ በመጠየቅ ከምታገኙት መልስ አንዳንዱን ከልጆቻችሁ ጋር በምትጸልዩበት ጊዜ መጥቀስ ትችላላችሁ? እንዲህ ካደረጋችሁ ጸሎት ሰሚ ወደሆነው ወደ ይሖዋ እንዲጸልዩ ብቻ ሳይሆን እሱን እንዲወዱትም እያስተማራችኋቸው ነው።—መዝሙር 65:2
ብቃት ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ያበረታታሉ
8. ወላጆች፣ ልጆቻቸው የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ሊረዷቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
8 አንድ ወላጅ መጽሐፍ ቅዱስን ስለማጥናት ያለው አመለካከት ልጁ ከአምላክ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት እንዲጠናከርና ቀጣይነት እንዲኖረው ከተፈለገ ጓደኛሞቹ እርስ በርስ መነጋገር ብቻ ሳይሆን መደማመጥም አለባቸው። ይሖዋን ከምናዳምጥባቸው መንገዶች አንዱ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያቀርባቸው ጽሑፎች ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ ምሳሌ 4:1, 2) በመሆኑም ወላጆች፣ ልጆቻቸው ከይሖዋ ጋር ዘላቂና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ዝምድና እንዲኖራቸው ለመርዳት ልጆቹ የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ማበረታታት አለባቸው።
9. ልጆች ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
9 ታዲያ ልጆች ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? በዚህም ረገድ ቢሆን ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ራሳቸው ምሳሌ በመሆን ነው። ልጆቻችሁ አዘውትራችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችሁ ስታነቡ ወይም ስታጠኑ ይመለከቷችኋል? እርግጥ ነው፣ ልጆቻችሁን በመንከባከብ ስለምትጠመዱ ‘ለንባብና ለጥናት የሚሆን ጊዜ እንዴት ማግኘት እችላለሁ?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ሆኖም ‘ልጆቼ አዘውትሬ ቴሌቪዥን ስመለከት ያዩኛል?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። እንዲህ ከሆነ የተወሰነውን ጊዜ የግል ጥናት ለማድረግ በማዋል ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ መሆን ትችላላችሁ?
10, 11. ወላጆች ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖር ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?
10 ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያዳምጡ ማስተማር የሚችሉበት ሌላው መንገድ ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንዲኖር ማድረግ ነው። (ኢሳይያስ 30:21) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ወላጆች ልጆቻቸውን አዘውትረው ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች የሚወስዷቸው ከሆነ የቤተሰብ ጥናት ለምን ያስፈልጋቸዋል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። በርካታ ምክንያቶች አሉ። ይሖዋ፣ ልጆችን የማስተማርን ኃላፊነት በዋነኝነት የሰጠው ለወላጆች ነው። (ምሳሌ 1:8፤ ኤፌሶን 6:4) የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ልጆች የይሖዋ አምልኮ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚከናወን የአምልኮ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡ ሕይወት ክፍል መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።—ዘዳግም 6:6-9
11 ከዚህም በላይ በጥሩ ሁኔታ የሚደረግ የቤተሰብ ጥናት ወላጆች፣ ልጆቻቸው ስለ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ልጆቻቸው ትንሽ እያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እና ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) እንደሚሉት በመሳሰሉት መጻሕፍት ሊጠቀሙ ይችላሉ።a በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠኛ ጽሑፎች በአብዛኞቹ አንቀጾች ላይ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ስለ ትምህርቱ ያላቸውን ሐሳብ እንዲገልጹ ሊጠይቋቸው ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙት ጥቅሶች በመጠቀም ልጆቻቸው ‘መልካሙን ከክፉው የመለየት’ ችሎታ እንዲያዳብሩ ሊረዷቸው ይችላሉ።—ዕብራውያን 5:14
12. ወላጆች የቤተሰብ ጥናቱ ልጆቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያካተተ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድስ ውጤታማ ሆኖ ያገኛችሁት ዘዴ አለ?
12 ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ ጥናቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያካተተ እንዲሆን አድርጉ። አንድ ባልና ሚስት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆቻቸው ትምህርት ቤታቸው ባዘጋጀው የዳንስ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ሲጠይቋቸው በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበት የረዷቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። አባትየው እንዲህ ብሏል:- “በሚቀጥለው የቤተሰብ ጥናት ወቅት፣ እኔና ባለቤቴ እንደ ልጆች ልጆቻችን ደግሞ እንደ ወላጆች የሚሆኑበት የተወሰነ ጊዜ እንደምንመድብ ለልጆቻችን ነገርናቸው። አንደኛዋ አባት ሌላኛዋ ደግሞ እናት መሆን የሚችሉ ቢሆንም በትምህርት ቤት ስለሚደረጉ የዳንስ ዝግጅቶች ምርምር ለማድረግና ለእኛ መመሪያ ለመስጠት አንድ ላይ መሥራት እንደሚኖርባቸው ገለጽንላቸው።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? አባትየው እንዲህ ብሏል:- “ሴት ልጆቻችን እንደ ወላጅ ሆነው ለእኛ ለልጆች ወደ ዳንስ ፕሮግራሙ መሄድ ጥበብ የጎደለው አካሄድ የሆነበትን ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው ሲያብራሩልን መልካሙን ከክፉ የመለየት ችሎታቸው አስደነቀን።” አክሎም እንዲህ ብሏል:- “በጣም ያስገረመን ሌላው ነገር ደግሞ ተቀባይነት ባላቸው ሌሎች ዝግጅቶች መካፈል እንደምንችል ሐሳብ ማቅረባቸው ነው። ይህ ደግሞ ምን እንደሚያስቡና እንደሚፈልጉ ለማስተዋል አስችሎናል።” በእርግጥም፣ የቤተሰብ ጥናቱ ቋሚና ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ያካተተ እንዲሆን አስቀድሞ ማሰብና ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ከሚገኘው ጥቅም አንጻር ጥረቱ አያስቆጭም።—ምሳሌ 23:15
ቤታችሁ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን አድርጉ
13, 14. (ሀ) ወላጆች ቤታቸው ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ስህተቶቻቸውን የሚያምኑ ከሆነ ምን ጠቃሚ ውጤት ሊገኝ ይችላል?
13 ቀስተኛው ፍላጻውን አነጣጥሮ በሚያስፈነጥርበት ጊዜ አየሩ ጥሩ ከሆነ ፍላጻው የታለመለትን ዒላማ የመምታት አጋጣሚው ሰፊ ነው። በተመሳሳይም ወላጆች ቤታቸው ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ካደረጉ ልጆች ይሖዋን ለመውደድ የተሻለ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ያዕቆብ “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 3:18) ወላጆች በቤታቸው ውስጥ ሰላማዊ ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ባልና ሚስት ግንኙነታቸው ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ጥረት ማድረግ አለባቸው። እርስ በርሳቸው የሚዋደዱና የሚከባበሩ ባልና ሚስት ልጆቻቸው ይሖዋንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን እንዲወዱና እንዲያከብሩ ለማስተማር የተሻለ አጋጣሚ አላቸው። (ገላትያ 6:7፤ ኤፌሶን 5:33) ፍቅርና መከባበር ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እርስ በርሳቸው ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው ባልና ሚስት በቤተሰብ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመፍታት ይችላሉ።
14 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ፍጹም ጋብቻ እንደሌለ ሁሉ ፍጹም የቤተሰብ ሕይወትም የለም። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ፍሬ ሳያሳዩ ሊቀሩ ይችላሉ። (ገላትያ 5:22, 23) ይህ በሚሆንበት ወቅት ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ወላጆች ስህተት መሥራታቸውን የሚያምኑ ከሆነ ልጃቸው ለእነሱ ያለው አክብሮት ይቀንስ ይሆን? የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያው ለብዙዎች መንፈሳዊ አባት ነበር። (1 ቆሮንቶስ 4:15) ያም ሆኖ ግን ስህተት መሥራቱን በግልጽ ተናግሯል። (ሮሜ 7:21-25) ጳውሎስ ትሑትና ሐቀኛ መሆኑ ለእሱ ያለን አክብሮት እንዲጨምር እንጂ እንዲቀንስ አላደረገም። ጳውሎስ ድክመቶች ቢኖሩትም ለቆሮንቶስ ጉባኤ “እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ” በማለት በድፍረት መናገር ችሏል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) እናንተም ስህተቶቻችሁን የምታምኑ ከሆነ ልጆቻችሁ በድክመቶቻችሁ ላይ ትኩረት ላያደርጉ ይችላሉ።
15, 16. ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እንዲወዱ ሊያሠለጥኗቸው የሚገባው ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት ከላይ ካየናቸው ነጥቦች በተጨማሪ ምን ማድረግ ይችላሉ? ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ማንም፣ ‘እግዚአብሔርን እወደዋለሁ’ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና።” (1 ዮሐንስ 4:20, 21) በመሆኑም ልጆቻችሁ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እንዲወዱ ስታሠለጥኗቸው አምላክን እንዲወዱ እያስተማራችኋቸው ነው። ወላጆች ‘ስለ ጉባኤ አንስቼ ሳወራ በአብዛኛው የምሰነዝረው ሐሳብ የሚያንጽ ነው? ወይስ መንቀፍ ይቀናኛል?’ በማለት ራሳቸውን ቢጠይቁ ጥሩ ነው። ይህን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? ልጆቻችሁ ስለ ስብሰባዎችም ሆነ ስለ ጉባኤው አባላት ምን ብለው እንደሚናገሩ አዳምጡ። የሚናገሩት ነገር የእናንተን አስተሳሰብ እንደሚያስተጋባ ትመለከቱ ይሆናል።
16 ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ? በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት ፒተር የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል:- “ልጆቻችን ትንሽ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞችንና እህቶችን ቤታችን መጥተው አብረውን እንዲመገቡና ጊዜ እንዲያሳልፉ አዘውትረን እንጋብዛቸዋለን። ይህም በጣም ያስደስተናል። ልጆቻችን ያደጉት ይሖዋን በሚወዱ ሰዎች ተከበው በመሆኑ አምላክን ማገልገል አስደሳች መሆኑን መመልከት ችለዋል።” የአምስት ሴት ልጆች አባት የሆነው ዴኒስ እንዲህ ብሏል:- “ልጆቻችን በጉባኤ ውስጥ ካሉ በዕድሜ ከእነሱ ከሚበልጡ አቅኚዎች ጋር ጓደኝነት እንዲመሠርቱ እናበረታታቸዋለን፤ እንዲሁም በተቻለ መጠን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ባለቤቶቻቸውን እንጋብዛለን።” እናንተስ፣ ልጆቻችሁ የጉባኤውን አባላት እንደ ቤተሰባቸው አድርገው እንዲመለከቷቸው ለመርዳት ጥረት ታደርጋላችሁ?—ማርቆስ 10:29, 30
የልጆች ኃላፊነት
17. ልጆች ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል?
17 እስቲ ወደ ቀስተኛው ምሳሌ እንመለስ። ግለሰቡ ብቃት ያለው ቀስተኛ ቢሆንም ፍላጻው የተጣመመ ከሆነ የታለመለትን ዒላማ ላይመታ ይችላል። ወላጆች በምሳሌያዊ አነጋገር ፍላጻውን ለማቃናት ይኸውም የልጁን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ አይካድም። ዞሮ ዞሮ ግን፣ ይህ ዓለም በራሱ መንገድ እንዲቀርጻቸው አሊያም ይሖዋ ‘ጎዳናቸውን ቀና’ እንዲያደርግላቸው መወሰን ያለባቸው ልጆች ራሳቸው ናቸው።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ሮሜ 12:2
18. ልጆች የሚያደርጉት ምርጫ ሌሎችን የሚነካው እንዴት ነው?
18 ወላጆች፣ ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” የማሳደግ ከባድ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ልጁ ሲያድግ ምን ዓይነት ሰው እንደሚሆን የሚወስነው ራሱ ነው። (ኤፌሶን 6:4) በመሆኑም ልጆች ‘ወላጆቼ በፍቅር የሚሰጡኝን ሥልጠና ተግባራዊ አደርጋለሁ?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። ወላጆቻችሁ የሚሰጧችሁን ሥልጠና ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና መርጣችኋል። ይህን ካደረጋችሁ ወላጆቻችሁን በጣም የምታስደስቱ ሲሆን ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛላችሁ።—ምሳሌ 27:11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።
ታስታውሳለህ?
• ወላጆች በጸሎትና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
• ወላጆች ቤታቸው ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
• ልጆች ምን ምርጫ አላቸው? ይህስ ሌሎችን የሚነካው እንዴት ነው?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በግል ጥናት ረገድ ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰላም የሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋል