ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ማንበቡን አስደሳች ሆኖ አግኝተኸዋልን? ከሆነ ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች ማስታወሱን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ:-
◻ ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚመሩ ግለሰቦችን በተመለከተ በሚያደርገው ምርጫ ረገድ ትምክህት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ በተወሰነ ወቅት ላይ ሕዝቦቹን እሱ በሚፈልገው መንገድ በመምራት ረገድ በጊዜው ተፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ያላቸውን ግለሰቦች እንደሚመርጥ የታወቀ ነው።—8/15፣ ገጽ 14
◻ ከዮናስ ተሞክሮ ምን ልንማር እንችላለን?
ዮናስ ስለ ሌሎች ሳይሆን ስለ ራሱ ከሚገባው በላይ ያስብ ነበር። ራሳችንንና የግል ስሜቶቻችንን በሁለተኛ ደረጃ በማስቀመጥ ከዮናስ መማር እንችላለን።—8/15፣ ገጽ 19
◻ “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 18:10)
የአምላክን ስም መሸሸጊያ ማድረጋችን በራሱ በይሖዋ መታመን እንዳለብን ያመለክታል። (መዝሙር 20:1፤ 122:4) ሉዓላዊነቱን መደገፍ፣ ሕጎቹንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ማክበርና በተስፋዎቹ ላይ እምነት ማሳደር ማለት ነው። በተጨማሪም ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ መስጠትን ያካትታል። (ኢሳይያስ 50:10፤ ዕብራውያን 11:6)—9/1፣ ገጽ 10
◻ ጳውሎስ በሹማምንት ፊት ለመመሥከር የተጠቀመበት ዘዴ ለእኛ ግሩም የሆነ ምሳሌ የያዘው እንዴት ነው?
ጳውሎስ ከንጉሥ አግሪጳ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ እርሱንና አግሪጳን ሊያስማሙ በሚችሉ ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል። በተመሳሳይ እኛም ለሁላችንም የተዘረጋውን ተስፋ ጠበቅ አድርገን በመግለጽ በምሥራቹ አዎንታዊ ገጽታ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 9:22)—9/1፣ ገጽ 31
◻ ከይሖዋ ትዕግሥት ተጠቃሚዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው?
ይሖዋ በመታገሡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እየቀረበ ካለው “የይሖዋ ቀን” ለመዳን እንዲችሉ አጋጣሚውን በማግኘት ላይ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:9–15) በተጨማሪም ትዕግሥቱ እያንዳንዳችን ‘በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችንን መዳን እንድንፈጽም’ በማስቻል ላይ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:12)—9/15፣ ገጽ 20
◻ የሴፕቱጀንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ምን ያህል ጠቃሚ ነበር?
ይህ ትርጉም ስለ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ስለሆነለት የይሖዋ መንግሥት እውቀት በማዳረሱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሴፕቱጀንት አማካኝነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዶችና አሕዛብ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲቀበሉ የሚያስችል አንድ አስፈላጊ መሠረት ተጥሏል።—9/15፣ ገጽ 30
◻ ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸው ምሳሌ ስለ አምላክ ምን ያስተምረናል?
በመጀመሪያ ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን ያስተምረናል። (ዘጸአት 34:6) በተጨማሪም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችለውን የልብ መለወጥ ሲመለከት “ይቅር ለማለት ዝግጁ” መሆኑን ያስተምረናል። (መዝሙር 86:5 NW)—10/1፣ ገጽ 12, 13
◻ በኢሳይያስ 65:21–25 ላይ ቃል የተገባላቸው ሰላማዊ ሁኔታዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼ ነው?
በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይሖዋን በአንድነት በማምለክ ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው መጠን ቅቡዓኑና “ሌሎች በጎች” በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ሰላም አግኝተዋል። (ዮሐንስ 10:16) እንዲሁም ‘በሰማይ የሆነው የአምላክ ፈቃድ በምድርም በሚሆንበት’ ጊዜ እንዲህ የመሰለው ሰላም በምድራዊ ገነት ውስጥ ይሰፍናል። በዚህ ጊዜ የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። (ማቴዎስ 6:10)—10/15፣ ገጽ 24
◻ ክርስቲያኖች የጋብቻ ቀናቸውን እንጂ የልደት ቀናቸውን የማያከብሩት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን አሉታዊ በሆነ መንገድ አይገልጸውም። አንድ ባልና ሚስት በየዓመቱ የተጋቡበትን ቀን ቢያስቡና የተለየ ጊዜ መድበው የሠርጋቸውን ቀን ደስታ መለስ ብለው ቢያስታውሱ ወይም ትዳራቸውን የተሳካ ለማድረግ የጋራ ጥረታቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ቢያድሱ ምንም ስህተት አይኖረውም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የምናገኛቸው የልደት ቀን ክብረ በዓሎች አረማውያን ያከበሩዋቸው ከመሆኑም በላይ ከጭካኔ ድርጊቶች ጋር ያያይዛቸዋል።—10/15፣ ገጽ 30, 31
◻ በ1 ቆሮንቶስ 3:12, 13 ላይ ተመዝግቦ በምናገኘው የጳውሎስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው “እሳት” ምን ያመለክታል? ሁሉም ክርስቲያኖች ንቁ መሆን ያለባቸውስ ለምን ነገር ነው?
ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመን እሳት አለ። ይህም በእምነታችን ላይ የሚደርሱ ፈተናዎች ናቸው። (ዮሐንስ 15:20፤ ያዕቆብ 1:2, 3) እውነትን የምናስተምረው እያንዳንዱ ሰው ይፈተናል። ጳውሎስ እንዳስጠነቀቀው በጥሩ ሁኔታ የማናስተምር ከሆነ ውጤቱ አሳዛኝ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 3:15)—11/1፣ ገጽ 11
◻ ኖኅ ‘አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ያደረገው’ በምን መንገድ ነው? (ዘፍጥረት 6:9)
ኖኅ አምላክ አድርግ ያለውን በመታዘዝ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል። ኖኅ ሙሉ በሙሉ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ያደረ ሰው ስለነበረ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ሞቅ ያለና የተቀራረበ ዝምድና ሊመሠርት ችሏል።—11/15፣ ገጽ 10
◻ አምላክ በክፉ ሰዎች ላይ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበትን ትክክለኛውን ጊዜ አለማወቃችን ምን ለማረጋገጥ አጋጣሚ ይሰጠናል?
ይህ ሁኔታ አካሄዳችንን ለዘላለም ከአምላክ ጋር ለማድረግ እንደምንፈልግና ይሖዋን ከልብ እንደምንወደው ለማረጋገጥ ያስችለናል። በተጨማሪም ለአምላክ ታማኞች እንደሆንንና እሱ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት እንዳለን ያሳያል። ከዚህም በላይ ትጉና በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመቀጠል ይረዳናል። (ማቴዎስ 24:42–44)—11/15፣ ገጽ 18
◻ “በእግዚአብሔር ልጅ ስም” ማመን ሲባል ምን ማለት ነው? (1 ዮሐንስ 5:13)
‘እርስ በርሳችን እንድንዋደድ’ የሰጠንን ትእዛዝ ጨምሮ የክርስቶስን ትእዛዛት ባጠቃላይ ማክበር ማለት ነው። (ዮሐንስ 15:14, 17) ፍቅር ለሌሎች ጥሩ ነገር ማድረግ ይፈልጋል። ፍቅር ማንኛውንም የዘር፣ የሃይማኖትና የኑሮ ደረጃ መድሎዎችን ያስወግዳል።—12/1፣ ገጽ 7
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የሚጠሉት’ ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 10:22)
የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ስደት እንዲደርስባቸው ያደረገው ምክንያትና ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሉበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው። በመጀመሪያ የይሖዋ ምሥክሮች በሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው መሠረት የሚያደርጓቸው ነገሮች በአንዳንዶች ዘንድ እንዲጠሉ ያደርጓቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነሱ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነገር በሚናገሩና እምነቶቻቸውን አጣምመው በሚያቀርቡ ሰዎች የሐሰት ክስ ይሰነዘርባቸዋል።—12/1፣ ገጽ 14