የጥናት ርዕስ 27
ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችሁ በማሰብ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ
“እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው . . . እመክራለሁ።”—ሮም 12:3
መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ
ማስተዋወቂያa
1. ፊልጵስዩስ 2:3 እንደሚናገረው ትሕትና ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?
ይሖዋ ለእኛ ከሁሉ የተሻለው ምን እንደሆነ እንደሚያውቅ ስለምንገነዘብ በትሕትና ለእሱ መሥፈርቶች እንገዛለን። (ኤፌ. 4:22-24) ትሕትና ከራሳችን ይልቅ የይሖዋን ፈቃድ እንድናስቀድምና ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ እንድናስብ ያነሳሳናል። ይህ ደግሞ ከይሖዋም ሆነ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ይረዳናል።—ፊልጵስዩስ 2:3ን አንብብ።
2. ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ጠቁሟል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 ይሁን እንጂ ካልተጠነቀቅን በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ኩራተኛና ራስ ወዳድ ሰዎች ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ።b በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞ የነበረ ይመስላል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር የሰጣቸው ለዚህ ሊሆን ይችላል፤ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው . . . እመክራለሁ” በማለት ጽፏል። (ሮም 12:3) ጳውሎስ በተወሰነ መጠን ለራሳችን አክብሮት ሊኖረን እንደሚገባ ጠቁሟል። ሆኖም ትሕትና ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ይህ ርዕስ በሦስት አቅጣጫዎች ረገድ ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን በማሰብ ራሳችንን ከፍ አድርገን ከመመልከት እንድንቆጠብ ትሕትና የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያብራራል። እነሱም (1) ትዳራችን፣ (2) የአገልግሎት መብታችን እና (3) የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ናቸው።
በትዳራችሁ ውስጥ ትሕትና አሳዩ
3. በትዳር ውስጥ ግጭት መፈጠሩ የማይቀረው ለምንድን ነው? አንዳንዶች ግጭት ሲያጋጥማቸው ምን ያደርጋሉ?
3 ይሖዋ የጋብቻን ዝግጅት ያደረገው ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ነው። ይሁንና ፍጹም የሆነ ሰው ስለሌለ በትዳር ውስጥ ግጭቶች መፈጠራቸው አይቀርም። እንዲያውም ጳውሎስ የሚያገቡ ሰዎች በተወሰነ መጠን መከራ እንደሚደርስባቸው ተናግሯል። (1 ቆሮ. 7:28) አንዳንዶች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ነጋ ጠባ ስለሚጣሉ ‘የምንጣጣም ሰዎች አይደለንም’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። በዚህ ዓለም ተጽዕኖ ከተሸነፉ ደግሞ መፍትሔው ፍቺ እንደሆነ ለመደምደም ይቸኩላሉ። በተጨማሪም ከሁሉም በላይ የራሳቸውን ስሜት ማስቀደም እንዳለባቸው ያስባሉ።
4. ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል?
4 በትዳራችን ተስፋ ከመቁረጥ መቆጠብ ይኖርብናል። ፍቺ ለመፈጸም የሚያበቃው ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የፆታ ብልግና እንደሆነ አንዘነጋም። (ማቴ. 5:32) ስለዚህ ጳውሎስ የጠቀሰው ዓይነት መከራ ሲያጋጥመን በኩራት ተነሳስተን ‘የትዳር ጓደኛዬ አያስብልኝም፤ የሚገባኝን ትኩረት አይሰጠኝም፤ ሌላ ሰው ባገባ ይበልጥ ደስተኛ የምሆን ይመስለኛል’ እያልን ማሰብ አይኖርብንም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ነው። የዚህ ዓለም ጥበብ ልባችንን እንድናምነውና እኛን የሚያስደስተንን ነገር እንድናደርግ ያበረታታናል፤ እንዲያውም ራሳችንን ለማስደሰት ስንል ትዳራችንን ከማፍረስ እንኳ እንዳንመለስ ይገፋፋናል። አምላካዊ ጥበብ ግን “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” በማለት ይመክረናል። (ፊልጵ. 2:4) ይሖዋ ትዳራችሁን እንድትታደጉት እንጂ እንድታፈርሱት አይፈልግም። (ማቴ. 19:6) ከራሳችሁ ስሜት ይልቅ ለእሱ አመለካከት ቅድሚያ እንድትሰጡ ይፈልጋል።
5. በኤፌሶን 5:33 መሠረት ባልና ሚስት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
5 ባልና ሚስት እርስ በርስ መዋደድና መከባበር አለባቸው። (ኤፌሶን 5:33ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (ሥራ 20:35) ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት እንዲያሳዩ የሚረዳቸው የትኛው ባሕርይ ነው? ትሕትና ነው። ትሑት የሆኑ ባሎችና ሚስቶች የራሳቸውን ሳይሆን “የሌላውን ሰው ጥቅም” ይፈልጋሉ።—1 ቆሮ. 10:24
6. ስቲቨን እና ስቴፋኒ ከተናገሩት ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
6 ትሕትና በርካታ ክርስቲያኖች በትዳራቸው ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ስቲቨን የተባለ አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “በተለይ ችግር ሲያጋጥማችሁ እንደ አንድ ቡድን ተባብራችሁ መሥራት ይኖርባችኋል። እንዲህ ካደረጋችሁ ‘ለእኔ የሚበጀኝ ምንድን ነው?’ ብላችሁ ከማሰብ ይልቅ ‘ለእኛ የሚበጀን ምንድን ነው?’ ብላችሁ ታስባላችሁ።” ባለቤቱ ስቴፋኒም ተመሳሳይ ስሜት አላት። እንዲህ ብላለች፦ “ሁሌ እየተጨቃጨቀ መኖር የሚፈልግ ሰው እንደሌለ የታወቀ ነው። ግጭት ሲያጋጥመን የችግሩን መንስኤ ለማወቅ እንሞክራለን። ከዚያም እንጸልያለን፣ ምርምር እናደርጋለን እንዲሁም ስለ መፍትሔው እንነጋገራለን። ከመጣላት ይልቅ ችግሩን በመፍታት ላይ እናተኩራለን።” ባለትዳሮች ከሚገባው በላይ ስለ ራሳቸው በማሰብ ራሳቸውን ከፍ አድርገው የማይመለከቱ ከሆነ በትዳራቸው ደስተኛ ይሆናሉ።
“በፍጹም ትሕትና” ይሖዋን አገልግሉ
7. አንድ ወንድም ኃላፊነት ሲሰጠው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል?
7 ይሖዋን በየትኛውም የአገልግሎት መስክ ማገልገል ከፍ ተደርጎ የሚታይ መብት ነው። (መዝ. 27:4፤ 84:10) አንድ ወንድም ለልዩ የአገልግሎት መብት ራሱን ቢያቀርብ ይህ የሚያስመሰግን ነገር ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል” በማለት ይናገራል። (1 ጢሞ. 3:1) ይሁንና አንድ ወንድም ኃላፊነት ሲሰጠው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ መመልከት አይኖርበትም። (ሉቃስ 17:7-10) ከዚህ ይልቅ ግቡ በትሕትና ሌሎችን ማገልገል ሊሆን ይገባል።—2 ቆሮ. 12:15
8. ዲዮጥራጢስ፣ ዖዝያና አቢሴሎም ካደረጉት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ስለተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ይናገራል። ልኩን የማያውቀው ዲዮጥራጢስ በጉባኤ ውስጥ “የመሪነት ቦታ” ለመያዝ ፈልጎ ነበር። (3 ዮሐ. 9) ኩራተኛው ዖዝያ ይሖዋ ያልፈቀደለትን ሥራ ለማከናወን ሞክሯል። (2 ዜና 26:16-21) መሠሪው አቢሴሎም ንጉሥ መሆን ስለፈለገ ሕዝቡን በማታለል ድጋፋቸውን ለማግኘት ጥረት አድርጓል። (2 ሳሙ. 15:2-6) እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በግልጽ እንደሚያሳዩት ይሖዋ የራሳቸውን ክብር በሚሹ ሰዎች አይደሰትም። (ምሳሌ 25:27) ይዋል ይደር እንጂ ኩራትም ሆነ የሥልጣን ጥመኝነት ለውድቀት መዳረጉ አይቀርም።—ምሳሌ 16:18
9. ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?
9 ከእነዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች በተለየ መልኩ ኢየሱስ “በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም የሥልጣን ቦታን ለመቀማት ማለትም ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን አላሰበም።” (ፊልጵ. 2:6) ኢየሱስ ከይሖዋ ቀጥሎ ያለውን ሥልጣን የያዘ ቢሆንም ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አልተመለከተም። እንዲያውም ለደቀ መዛሙርቱ “ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 9:48) እንደ ኢየሱስ ትሑት ከሆኑ አቅኚዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮች፣ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር መሥራት እንዴት ያለ በረከት ነው! ትሑት የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነው ፍቅር እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—ዮሐ. 13:35
10. በጉባኤህ ውስጥ ተገቢው መፍትሔ ያልተሰጠው ችግር እንዳለ ቢሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
10 በጉባኤህ ውስጥ ተገቢው መፍትሔ ያልተሰጠው ችግር እንዳለ ቢሰማህስ? ከማጉረምረም ይልቅ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች በመደገፍ ትሕትና ማሳየት ትችላለህ። (ዕብ. 13:17) ለዚህ እንዲረዳህ እንደሚከተለው በማለት ራስህን ጠይቅ፦ ‘በእርግጥ ጉዳዩ መፍትሔ የሚያሻው አሳሳቢ ችግር ነው? ችግሩን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው? ችግሩን ማስተካከል የእኔ ኃላፊነት ነው? በእርግጥ ያሳሰበኝ በጉባኤው ውስጥ አንድነት የመስፈኑ ጉዳይ ነው ወይስ ራሴን ከፍ ከፍ ለማድረግ እየሞከርኩ ነው?’
11. ኤፌሶን 4:2, 3 እንደሚናገረው ይሖዋን በትሕትና ማገልገል ምን ውጤት ያስገኛል?
11 ይሖዋ ከችሎታ ይልቅ ለትሕትና፣ ከቅልጥፍና ይልቅ ደግሞ ለአንድነት ቦታ ይሰጣል። በመሆኑም ይሖዋን በትሕትና ለማገልገል የተቻለህን ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግክ በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ታበረክታለህ። (ኤፌሶን 4:2, 3ን አንብብ።) አዘውትረህ በአገልግሎት ተካፈል። ደግነት በማሳየት ሌሎችን ማገልገል የምትችልበትን መንገድ ፈልግ። የኃላፊነት ቦታ የሌላቸውን አስፋፊዎች ጨምሮ ለሁሉም ሰው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይ። (ማቴ. 6:1-4፤ ሉቃስ 14:12-14) በትሕትና ከጉባኤው ጋር ተባብረህ ስትሠራ ሰዎች ችሎታህን ብቻ ሳይሆን ትሕትናህንም ማስተዋላቸው አይቀርም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ስትጠቀሙ ትሕትና አሳዩ
12. መጽሐፍ ቅዱስ ጓደኞች እንድናፈራ ያበረታታናል? አብራራ።
12 ይሖዋ ከጓደኞቻችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ እንድንደሰት ይፈልጋል። (መዝ. 133:1) ኢየሱስም ጥሩ ጓደኞች ነበሩት። (ዮሐ. 15:15) መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት ያለውን ጥቅም ይገልጻል። (ምሳሌ 17:17፤ 18:24) በተጨማሪም ራስን ማግለል ጎጂ እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 18:1) ብዙዎች ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ብዙ ጓደኞች ለማግኘትና የብቸኝነት ስሜትን ለማስወገድ እንደሚረዳ ይሰማቸዋል። ይሁንና ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ጋር በተያያዘ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል።
13. ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ አንዳንድ ሰዎች ለብቸኝነትና ለመንፈስ ጭንቀት ሊዳረጉ የሚችሉት ለምንድን ነው?
13 በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችን በማየት ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ለብቸኝነትና ለመንፈስ ጭንቀት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያወጡት፣ ለየት ያሉ የሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ስለሆነ ነው፤ የራሳቸውንና የጓደኞቻቸውን ቆንጆ ፎቶግራፍ ወይም የጎበኟቸውን አስገራሚ ቦታዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ብቻ መርጠው ያወጣሉ። እነዚህን ፎቶግራፎች የሚያይ ሰው የእሱ ሕይወት ከእነዚህ ሰዎች ሕይወት ጋር ሲነጻጸር አስደሳች እንዳልሆነ እንዲያውም አሰልቺ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። አንዲት የ19 ዓመት እህታችን “ቅዳሜና እሁድ ስልችት ብሎኝ ቤቴ ቁጭ ብዬ ሌሎች ግን አስደሳች ጊዜ እያሳለፉ እንደሆነ ሳይ መቅናት ጀመርኩ” ብላለች።
14. በ1 ጴጥሮስ 3:8 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?
14 እርግጥ ነው፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ለጥሩ ዓላማ መጠቀም ይቻላል፤ ለምሳሌ ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር ለመገናኘት ልንጠቀምበት እንችላለን። ይሁንና ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንዳንድ ነገሮችን የሚያወጡት የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍ ብቻ እንደሆነ አስተውለሃል? “እዩኝ! እዩኝ!” የሚል መልእክት ማስተላለፍ የፈለጉ ይመስላል። ሌሎች ደግሞ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች ባወጧቸው ፎቶግራፎች ላይ አክብሮት የጎደለው ወይም የብልግና ሐሳብ ይጽፋሉ። ሆኖም ክርስቲያኖች ትሕትናና የሌሎችን ስሜት የመረዳት ባሕርይ እንዲያዳብሩ የተበረታቱ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።
15. መጽሐፍ ቅዱስ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ እንዳይጠናወተን የሚረዳን እንዴት ነው?
15 ማኅበራዊ ሚዲያ የምትጠቀም ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምጽፋቸው ሐሳቦች ወይም የማወጣቸው ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች ጉራ እየነዛሁ እንዳለ የሚያስመስሉ ናቸው? ሌሎች ሰዎች እንዲቀኑ እያደረግኩ ይሆን?’ መጽሐፍ ቅዱስ “በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐ. 2:16) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት” የሚለውን ሐረግ “ተፈላጊ ሰው መስሎ ለመታየት መሞከር” በማለት ተርጉሞታል። ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ያውላሉ። (ገላ. 5:26) ትሕትና ማዳበራችን በዓለም ላይ የሚታየው የኩራትና ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መንፈስ እንዳይጋባብን ይረዳናል።
“ጤናማ አስተሳሰብ” ይኑራችሁ
16. ከኩራት መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?
16 ትሕትና ማዳበር የሚያስፈልገን ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች “ጤናማ አስተሳሰብ” ስለሌላቸው ነው። (ሮም 12:3) ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች ጠበኛና ትምክህተኛ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ይጎዳል። አስተሳሰባቸውን ካላስተካከሉ ሰይጣን አእምሯቸውን ያሳውረዋል እንዲሁም ያበላሸዋል። (2 ቆሮ. 4:4፤ 11:3) በሌላ በኩል ግን ትሑት ሰው ጤናማ አስተሳሰብ አለው። ሌሎች በብዙ መንገዶች ከእሱ እንደሚበልጡ ስለሚገነዘብ ለራሱ ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት አለው። (ፊልጵ. 2:3) በተጨማሪም ‘አምላክ ትዕቢተኞችን እንደሚቃወምና ለትሑታን ጸጋን እንደሚሰጥ’ ያውቃል። (1 ጴጥ. 5:5) ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው የይሖዋ ጠላት መሆን አይፈልግም።
17. ምንጊዜም ትሑት ለመሆን ምን ማድረግ አለብን?
17 ምንጊዜም ትሑት ለመሆን ከፈለግን “አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ፤ እንዲሁም . . . አዲሱን ስብዕና ልበሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ማዋል አለብን። እርግጥ እንዲህ ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መመርመርና አቅማችን በፈቀደ መጠን ምሳሌውን ለመከተል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ቆላ. 3:9, 10፤ 1 ጴጥ. 2:21) ይሁንና የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ አይደለም። ትሕትናን ባዳበርን መጠን የቤተሰብ ሕይወታችን ይሻሻላል፤ በጉባኤ ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን እናደርጋለን፤ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያን ጎጂ በሆነ መንገድ ከመጠቀም እንቆጠባለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን በረከትና ሞገስ እናገኛለን።
መዝሙር 117 ጥሩነት
a የምንኖረው ኩራተኛና ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም የእነዚህ ሰዎች ባሕርይ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህ ርዕስ በሦስት አቅጣጫዎች ረገድ ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን በማሰብ ራሳችንን ከፍ አድርገን ከመመልከት መቆጠብ እንዳለብን ይናገራል።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ኩራተኛ ሰው ከሌሎች ይልቅ ራሱን ከፍ አድርጎ ይመለከታል። በመሆኑም ኩራተኛ ሰው ራስ ወዳድ ነው። በሌላ በኩል ግን ትሕትና ራስ ወዳድ እንዳንሆን ይረዳናል። ትሕትና ከኩራት ወይም ከእብሪት ነፃ መሆንን እንዲሁም ለራስ የተጋነነ አመለካከት አለመያዝን ያመለክታል።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ በክልል ስብሰባ ላይ ንግግር የማቅረብና ለሌሎች አመራር የመስጠት ኃላፊነት ያለው የጉባኤ ሽማግሌ በአገልግሎት ግንባር ቀደም ሆኖ የመካፈልና የስብሰባ አዳራሹን የማጽዳት መብቱንም ከፍ አድርጎ ይመለከታል።