መንፈሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል
“የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።”—ሮም 8:16
1-3. የጴንጤቆስጤ በዓል ልዩ እንዲሆን ያደረጉት የትኞቹ ክንውኖች ናቸው? እነዚህ ክንውኖች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም ያደረጉት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
እሁድ ማለዳ ላይ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ነው። ይህ ቀን በኢየሩሳሌም ለነበሩ ሰዎች ልዩ ትርጉም አለው። ዕለቱ በዓል በመሆኑ ሰንበት ነው። ዘወትር ጠዋት ላይ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች በቤተ መቅደሱ ቀርበው መሆን አለበት። ሊቀ ካህናቱ ከአዲስ እህል የተዘጋጁና እርሾ ገብቶባቸው የተጋገሩ ሁለት ቂጣዎችን የሚወዘወዝ መባ አድርጎ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ሲሆን ሕዝቡም በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። (ዘሌ. 23:15-20) ይህ መባ የስንዴ መከር መጀመሩን ያበስራል። ጊዜው በ33 ዓ.ም. የዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው።
2 እነዚህ ነገሮች በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየተከናወኑ ሳለ ከዚህ የበለጠ ትርጉም ያለው ክንውን ሊፈጸም ነው፤ ይህ ክንውን የሚፈጸመው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ደርብ ላይ ባለ አንድ ክፍል ነው። መቶ ሃያ የሚያህሉ ክርስቲያኖች አንድ ላይ ሆነው “ተግተው ይጸልዩ ነበር።” (ሥራ 1:13-15) ሊቀ ካህናቱ በየዓመቱ በጴንጤቆስጤ ዕለት የሚያከናውነው ነገር፣ አሁን በእነዚህ ክርስቲያኖች ላይ ከሚፈጸመው ነገር ጋር ተያያዥነት አለው፤ በዚህ ዕለት የሚከናወነው ነገር ነቢዩ ኢዩኤል ከ800 ዓመታት በፊት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸምም አድርጓል። (ኢዩ. 2:28-32፤ ሥራ 2:16-21) ይሁንና ይህን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምን ነገር ሊከናወን ይችላል?
3 የሐዋርያት ሥራ 2:2-4ን አንብብ። ደርብ ላይ በተሰበሰቡት ክርስቲያኖች ላይ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወረደ። (ሥራ 1:8) እነሱም ትንቢት መናገር ይኸውም ስላዩአቸውና ስለሰሟቸው ድንቅ ነገሮች መመሥከር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚያ የተፈጸመው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ለተሰበሰቡት ሰዎች አብራራላቸው። አክሎም አድማጮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ።” በዚያ ቀን በአጠቃላይ 3,000 የሚያህሉ ሰዎች የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው ተጠመቁ፤ እንዲሁም በትንቢት በተነገረው መሠረት መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።—ሥራ 2:37, 38, 41
4. (ሀ) የጴንጤቆስጤ በዓል ለእኛ ትልቅ ትርጉም ያለው ለምንድን ነው? (ለ) ከበርካታ ዓመታት በፊት በዚያው ዕለት፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምን ነገር ተከናውኖ ሊሆን ይችላል? (ተጨማሪ ሐሳቡን ተመልከት።)
4 በ33 ዓ.ም. የዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ በተከናወነው ነገር ምክንያት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በቤተ መቅደሱ የሚከናወነው ትንቢታዊ ጥላነት ያለው ነገር ፍጻሜውን እንዲያገኝ ስላደረገ ነው።[1] በዚያ ዕለት ሊቀ ካህናቱ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ሁለት ቂጣዎችን ለይሖዋ አቅርቧል። በቤተ መቅደሱ የቀረቡት እርሾ ገብቶባቸው የተጋገሩ ቂጣዎች፣ የተቀቡትን ደቀ መዛሙርት ያመለክታሉ፤ አምላክ እነዚህን ደቀ መዛሙርት ከኃጢአተኛው የሰው ዘር መካከል እንደ ልጆቹ አድርጎ ወስዷቸዋል። በመሆኑም ከሰው ዘር መካከል አንዳንዶች “በኩራት” ሆነው ከጊዜ በኋላ ወደ ሰማይ በመሄድ የአምላክ መንግሥት አባላት መሆን የሚችሉበት መንገድ ተከፈተ፤ ይህ መንግሥት ታዛዥ ለሆኑት የቀሩት የሰው ልጆች ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶችን ያመጣል። (ያዕ. 1:18፤ 1 ጴጥ. 2:9) እንግዲያው ተስፋችን በሰማይ ከኢየሱስ ጋር መኖርም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር፣ በጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወኑት ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ትርጉም አላቸው።
አንድ ሰው የሚቀባው እንዴት ነው?
5. በመንፈስ የተቀቡ ሁሉም ክርስቲያኖች የተቀቡበት መንገድ ተመሳሳይ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?
5 የእሳት ምላሶች የሚመስሉ ነገሮች ካረፉባቸው ደቀ መዛሙርት አንዱ ብትሆን በዚያ ዕለት የተከናወነውን ነገር መቼም አትረሳውም። በመንፈስ ቅዱስ መቀባትህን ፈጽሞ አትጠራጠርም፤ በተለይ ደግሞ በማታውቀው ቋንቋ የመናገር ተአምራዊ ስጦታም ተሰጥቶህ ከሆነ መቀባትህን እርግጠኛ ትሆናለህ። (ሥራ 2:6-12) ይሁንና በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ሁሉ፣ የተቀቡት ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ 120 ደቀ መዛሙርት አስደናቂ በሆነ መንገድ ነው? አይደለም። በኢየሩሳሌም በዚያን ዕለት የነበሩት ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ የተቀቡት ሲጠመቁ ነው። (ሥራ 2:38) የእሳት ምላሶች የሚመስሉ ነገሮች ጭንቅላታቸው ላይ አላረፉም። በሌላ በኩል ደግሞ በተጠመቁበት ወቅት በመንፈስ የተቀቡት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም። ሳምራውያን በመንፈስ የተቀቡት ከተጠመቁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። (ሥራ 8:14-17) ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የተቀቡበት መንገድም ለየት ያለ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት ገና ከመጠመቃቸው በፊት ነው።—ሥራ 10:44-48
6. ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ያገኛሉ? ይህስ ምን እንዲሰማቸው ያደርጋል?
6 ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው ሁሉም ቅቡዓን በመንፈስ የሚቀቡት በተመሳሳይ መንገድ አይደለም። አንዳንዶች እንደተጠሩ የተገነዘቡት በቅጽበት ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ይህን ያወቁት በጊዜ ሂደት ነው። የተቀቡበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ ሁሉም ሐዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ የገለጸውን ነገር አግኝተዋል፦ “ካመናችሁ በኋላ በእሱ አማካኝነት፣ ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤ ይህም . . . ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።” (ኤፌ. 1:13, 14) በዚህ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸው፣ እንደ ቀብድ አሊያም ወደፊት ለሚመጣው ነገር እንደ ዋስትና (ወይም መያዣ) ነው። አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ይህን ማረጋገጫ ስላገኘ መቀባቱን ይተማመናል።—2 ቆሮንቶስ 1:21, 22ን እና 5:5ን አንብብ።
7. እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ሰማያዊ ሽልማቱን ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?
7 እንዲህ ዓይነት ማረጋገጫ የተሰጠው ክርስቲያን በሰማይ ሕይወት ማግኘቱ ተረጋግጧል ማለት ነው? አይደለም። ግለሰቡ ጥሪውን እንደተቀበለ እርግጠኛ ነው። ሆኖም በሰማይ ሽልማቱን ማግኘት አለማግኘቱ የተመካው ለጥሪው ታማኝ ሆኖ በመገኘቱ ላይ ነው። ጴጥሮስ ነጥቡን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “በመሆኑም ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁምና። እንዲያውም በእጅጉ ትባረካላችሁ፤ ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥትም ትገባላችሁ።” (2 ጴጥ. 1:10, 11) እንግዲያው እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ታማኝነቱን ለመጠበቅ መታገል አለበት። ታማኝ ካልሆነ ግን ሰማያዊ ጥሪ ወይም ግብዣ ማግኘቱ ምንም አይጠቅመውም።—ዕብ. 3:1፤ ራእይ 2:10
አንድ ሰው መቀባቱን የሚያውቀው እንዴት ነው?
8, 9. (ሀ) አብዛኞቹ ሰዎች አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ የሚቀባው እንዴት እንደሆነ መረዳት የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው ወደ ሰማይ ለመሄድ ግብዣ እንደቀረበለት እንዴት ያውቃል?
8 በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች፣ አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ የሚቀባው እንዴት እንደሆነ መረዳት ይከብዳቸው ይሆናል፤ ይህም የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም ይህ እነሱ የሚያጋጥማቸው ነገር አይደለም። አምላክ መጀመሪያ ላይ ለሰው ዘሮች የነበረው ዓላማ በዚህ ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (ዘፍ. 1:28፤ መዝ. 37:29) አንዳንዶች ወደ ሰማይ ሄደው ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ መመረጣቸው ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር ነው። ይህ ለየት ያለ ዝግጅት ነው። አንድ ሰው እንዲህ ላለው ሕይወት መጠራቱ በአስተሳሰቡ፣ በአመለካከቱና በተስፋው ላይ ትልቅ ለውጥ ያስከትላል።—ኤፌሶን 1:18ን አንብብ።
9 ይሁንና አንድ ሰው ለሰማያዊ ሕይወት እንደተጠራ ይኸውም ይህን ልዩ ማረጋገጫ እንደተቀበለ እንዴት ያውቃል? ጳውሎስ ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩት’ በሮም ላሉት ቅቡዓን ወንድሞች የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግልጽ መልስ ይሆናል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።” (ሮም 1:7፤ 8:15, 16) በአጭር አነጋገር፣ ግለሰቡ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ወራሽ እንዲሆን መጠራቱን ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ግልጽ ያደርግለታል።—1 ተሰ. 2:12
10. በ1 ዮሐንስ 2:27 ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ማንም ሊያስተምራቸው እንደማያስፈልግ የሚገልጸው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው?
10 ከአምላክ እንዲህ ያለ ልዩ ጥሪ ያገኙ ግለሰቦች ይህን የሚያረጋግጥላቸው ሌላ ምሥክር አይፈልጉም። ለመቀባታቸው ማስተማመኛ የሚሰጣቸው ሌላ አካል አያስፈልጋቸውም። ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ በልባቸው ውስጥ አንዳች ጥርጣሬ እንዳያድር ያደርጋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን “እናንተ ግን ቅዱስ ከሆነው ከእሱ የመንፈስ ቅብዓት አግኝታችኋል፤ ደግሞም ሁላችሁም እውቀት አላችሁ” ብሏቸዋል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ግን ከእሱ የተቀበላችሁት የመንፈስ ቅብዓት በውስጣችሁ ይኖራል፤ በመሆኑም ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ያገኛችሁት ይህ ቅብዓት ስለ ሁሉም ነገር እያስተማራችሁ ነው፤ ደግሞም እውነት እንጂ ውሸት አይደለም። ይህ ቅብዓት ባስተማራችሁ መሠረት ከእሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ።” (1 ዮሐ. 2:20, 27) እነዚህ ቅቡዓን እንደ ማንኛውም ሰው መንፈሳዊ ትምህርት ማግኘት አለባቸው። ይሁንና መቀባታቸውን ሌላ አካል እንዲያጸድቅላቸው አያስፈልግም። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለው ከሁሉ የላቀ ኃይል ይህን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል!
‘እንደ አዲስ መወለድ’
11, 12. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኞቹ ጥያቄዎች ይፈጠሩባቸው ይሆናል? ስለ የትኛው ጉዳይ ግን ፈጽሞ ጥያቄ አይፈጠርባቸውም?
11 አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን መቀባቱን መንፈስ ቅዱስ ሲያረጋግጥለት ትልቅ ለውጥ ያጋጥመዋል። ኢየሱስ ይህን ለውጥ ‘ዳግመኛ መወለድ’ ወይም ‘ከላይ መወለድ’ በማለት ገልጾታል።[2] (ዮሐ. 3:3, 5 ግርጌ) አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልኩህ አትገረም። ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።” (ዮሐ. 3:7, 8) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ቅቡዓን በግለሰብ ደረጃ የሚደረግላቸውን ይህን ጥሪ፣ በመንፈስ ላልተቀቡ ሰዎች በዝርዝር ማስረዳት አስቸጋሪ ነው።
12 በዚህ መንገድ ጥሪ የተደረገላቸው ክርስቲያኖች ‘እኔ የተመረጥኩት ለምንድን ነው? ሌሎች ሳይመረጡ እንዴት እኔ ተመረጥኩ?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርባቸው ይሆናል። እንዲያውም ይህን ጥሪ ማግኘት ይገባቸው እንደሆነ ይጠራጠሩ ይሆናል። ይሁንና መጠራታቸውን ፈጽሞ አይጠራጠሩም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለ ስጦታ በማግኘታቸው ልባቸው በደስታና በአድናቆት ይሞላል። ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ሐሳብ ሲያሰፍር የነበረው ዓይነት ስሜት አላቸው፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናልና፤ እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል።” (1 ጴጥ. 1:3, 4) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ ሲያነቡ በሰማይ ያለው አባታቸው በግለሰብ ደረጃ እያናገራቸው እንደሆነ ቅንጣት ታክል አይጠራጠሩም።
13. በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ አንድ ግለሰብ በአመለካከቱ ላይ ምን ለውጥ ይከሰታል? ይህ ለውጥ እንዲከሰት ያደረገውስ ምንድን ነው?
13 እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈስ በግለሰብ ደረጃ ሳይመሠክርላቸው በፊት፣ በምድር ላይ የመኖር ተስፋን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይሖዋ ይህችን ምድር የሚያጸዳበትን ጊዜ ለማየት ይጓጉ እንዲሁም በዚያ ከሚገኘው በረከት መካፈል ይፈልጉ ነበር። ምናልባትም በሞት የተለዩአቸው የሚወዷቸው ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙና እነሱን ሲቀበሉ በዓይነ ሕሊናቸው ያዩ ነበር። ራሳቸው በሠሩት ቤት ውስጥ ለመኖርና የተከሏቸውን ዛፎች ፍሬ ለመብላት ይጓጉ ነበር። (ኢሳ. 65:21-23) ታዲያ አመለካከታቸው የተለወጠው ለምንድን ነው? በዚህ ተስፋ ስላልረኩ አይደለም። አስተሳሰባቸው የተለወጠው ጭንቀት ወይም መከራ ስለበዛባቸው አይደለም። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር አሰልቺ እንደሆነና ደስታ እንደማያስገኝ ተሰምቷቸው በድንገት ሐሳባቸውን ስለቀየሩም አይደለም፤ አሊያም በሰማይ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል ለማወቅ ስለፈለጉ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አመለካከታቸው የተቀየረው የአምላክ መንፈስ ስለጠራቸው አልፎ ተርፎም አስተሳሰባቸውንና ተስፋቸውን ስለለወጠው ነው።
14. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ስላላቸው ሕይወት ምን ይሰማቸዋል?
14 ታዲያ እነዚህ ቅቡዓን መሞት ይፈልጋሉ ብለን ማሰብ ይኖርብናል? ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን መልስ ሰጥቷል፦ “እንዲያውም በዚህ ድንኳን ውስጥ ያለነው እኛ ከባድ ሸክም ተጭኖን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ዘላለማዊው ሕይወት ሟች የሆነውን አካል እንዲተካ ይህን ድንኳን ማውለቅ ሳይሆን ሰማያዊውን መኖሪያ መልበስ እንፈልጋለን።” (2 ቆሮ. 5:4) ቅቡዓን ይሄኛው ሕይወት ስለሰለቻቸው ቶሎ እንዲያከትም ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። እንዲያውም እያንዳንዱን ቀን ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በይሖዋ አገልግሎት ለማሳለፍ ይፈልጋሉ። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት እየሠሩ ያሉት ምንም ይሁን ምን፣ ወደፊት የሚጠብቃቸውን አስደናቂ ተስፋ ማሰባቸው አይቀርም።—1 ቆሮ. 15:53፤ 2 ጴጥ. 1:4፤ 1 ዮሐ. 3:2, 3፤ ራእይ 20:6
አንተስ ተጠርተሃል?
15. አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን የትኞቹ ነገሮች አያረጋግጡም?
15 ምናልባት አንተም ‘ይህን አስደናቂ ጥሪ አግኝቼ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብህ ይሆናል። ይህን ጥሪ አግኝተህ ሊሆን እንደሚችል ከተሰማህ ልታስብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጥያቄዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦ በአገልግሎት የተለየ ቅንዓት እንዳለህ ይሰማሃል? “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” መቆፈር የሚያስደስትህ ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪ ነህ? (1 ቆሮ. 2:10) በአገልግሎትህ የይሖዋን ልዩ በረከት እንዳገኘህ ይሰማሃል? የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አለህ? ሌሎችን በመንፈሳዊ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለብህ ከልብ ይሰማሃል? በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ እንዳየህ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ተመልክተሃል? ለእነዚህ ጥያቄዎች በልበ ሙሉነት “አዎ” የሚል መልስ የምትሰጥ ከሆነ ሰማያዊ ጥሪ አለህ ማለት ነው? አይደለም። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማቸው ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። የይሖዋ መንፈስ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ባላቸው ሰዎች ላይም በእኩል ደረጃ ይሠራል። እንዲያውም ሰማያዊ ጥሪ እንዳለህ ጥያቄ የሚፈጠርብህ ከሆነ ይህ በራሱ እንዲህ ዓይነት ጥሪ እንዳላገኘህ ያሳያል። ይሖዋ የጠራቸው ሰዎች ጥሪውን ስለማግኘታቸው ጥርጣሬ አይገባቸውም! ጥሪውን ማግኘታቸውን በእርግጠኝነት ያውቃሉ!
16. የአምላክን መንፈስ ያገኙ ሁሉ ወደ ሰማይ ለመሄድ እንዳልተጋበዙ እንዴት እናውቃለን?
16 ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንመረምር መንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው በርካታ የእምነት ሰዎችን እናገኛለን፤ ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች በሰማይ የመኖር ተስፋ አልነበራቸውም። እንዲህ ካሉት ሰዎች መካከል መጥምቁ ዮሐንስ አንዱ ነው። ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስን በእጅጉ ያደነቀው ቢሆንም ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ ተናግሯል። (ማቴ. 11:10, 11) ዳዊትም የይሖዋን መንፈስ አግኝቶ ነበር። (1 ሳሙ. 16:13) ዳዊት ጥልቅ መንፈሳዊ እውቀት ያለው ሰው ከመሆኑም ባሻገር አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ማር. 12:36) ያም ሆኖ ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም” ብሏል። (ሥራ 2:34) መንፈስ ቅዱስ በእነዚህ ሰዎች በመጠቀም ታላቅ ሥራ አከናውኗል፤ ሆኖም በሰማይ ሕይወት ለማግኘት መመረጣቸውን የሚያሳየውን ልዩ ምሥክርነት አልሰጣቸውም። ይህ መሆኑ ግን ብቃት ጎድሏቸዋል ወይም እንከን አለባቸው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ከሞት አስነስቶ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል ማለት ነው።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
17, 18. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ተስፋቸው ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
17 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ሰማያዊ ጥሪ አልተቀበሉም። እነዚህ ሰዎች ዳዊት፣ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲሁም በጥንት ዘመን የኖሩ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የነበራቸው ዓይነት ተስፋ አላቸው። እንደ አብርሃም ሁሉ እነሱም የመንግሥቱ ተገዢዎች ሆነው ለመኖር ይጠባበቃሉ። (ዕብ. 11:10) ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ከተመረጡት መካከል በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በምድር ላይ የቀሩት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። (ራእይ 12:17) ከተመረጡት 144,000ዎች መካከል አብዛኞቹ ታማኝነታቸውን ጠብቀው ሞተዋል።
18 ታዲያ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች፣ ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ለሚናገሩ ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? በጉባኤህ ያለ አንድ ሰው በጌታ ራት ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ መውሰድ ቢጀምር ምን ይሰማሃል? ሰማያዊ ጥሪ አለን የሚሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ሊያሳስብህ ይገባል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
^ [1] (አንቀጽ 4) የጴንጤቆስጤ በዓል የሚከበርበት ጊዜ የሚውለው ሕጉ በሲና ለሕዝቡ በተሰጠበት ጊዜ ላይ ሳይሆን አይቀርም። (ዘፀ. 19:1) ይህ ከሆነ ደግሞ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የሕጉ ቃል ኪዳን የተሰጠው በዚያ ዕለት እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም ከአዲሱ ብሔር ወይም ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የገባው በተመሳሳይ ዕለት ነው።
^ [2] (አንቀጽ 11) ዳግመኛ መወለድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሚያዝያ 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 3-11 ተመልከት።