ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ስጦታ የሆኑ ወንዶች ናቸው
“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን[“ስጦታ የሆኑ ወንዶችን፣” አዓት] ሰጠ።”—ኤፌሶን 4:8
1. በ1894 በዚህ መጽሔት ላይ ምን አዲስ ነገር ተገልጾ ነበር?
ከአንድ መቶ ዓመት በፊት መጠበቂያ ግንብ አንድ አዲስ ነገር አስታውቆ ነበር። ይህ አዲስ ነገር “የስብከቱን ሥራ አንድ ሌላ ዘርፍ” የሚመለከት እንደሆነ ተገልጾ ነበር። ይህ አዲስ ሥራ ምን ነበር? የዘመናችን የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሥራ መጀመር ነበር። የዚህ መጽሔት የመስከረም 1, 1894 እትም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድኖችን ‘በእውነት ውስጥ ጸንተው እንዲቆሙ ለማበረታታት’ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ጉብኝት እንደሚያደርጉ አብራርቶ ነበር።
2. የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ያሏቸው ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የክርስቲያን ጉባኤዎች እንደ ጳውሎስና በርናባስ ባሉት የበላይ ተመልካቾች ይጎበኙ ነበር። እነዚህ እምነት የሚጣልባቸው ወንዶች ዓላማቸው ጉባኤዎችን ‘ማነጽ’ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 10:8) በዛሬው ጊዜ ሥርዓት ባለው መንገድ ይህን የሚያከናውኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች በማግኘታችን ተባርከናል። የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል እነዚህን ሰዎች የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ሾሟቸዋል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች 20 የሚያህሉ ጉባኤዎችን የሚያገለግል ሲሆን እያንዳንዳቸውን በዓመት ሁለት ጊዜ ያህል ለአንድ ሳምንት ይጎበኛቸዋል፤ በዚህ ወቅት የጉባኤ መዛግብቶችን ይመረምራል፣ ንግግሮችን ይሰጣል እንዲሁም ከጉባኤው የመንግሥት አስፋፊዎች ጋር በመስክ አገልግሎት ይሳተፋል። የአውራጃው የበላይ ተመልካች የተለያዩ ወረዳዎች በሚያደርጓቸው የወረዳ ስብሰባዎች ላይ ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለግላል፣ ከአስተናጋጆቹ ጉባኤዎች ጋር በመስክ አገልግሎት ይሳተፋል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ንግግሮች አማካኝነት ማበረታቻዎች ይሰጣል።
የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋሉ
3. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ሊኖራቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
3 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በየጊዜው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይጓዛሉ። ይህ ራሱ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ መጓዝ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህ ወንዶችና ሚስቶቻቸው ይህን የሚያደርጉት በደስተኛ መንፈስ ነው። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ በጣም ተባባሪና የማታማርር ናት . . . ላላት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ልትመሰገን ይገባታል።” አንዳንድ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ ሲሄዱ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛሉ። ብዙዎቹ መኪና ያላቸው ቢሆንም ሌሎች በሕዝብ ትራንስፖርት፣ በፈረስ ወይም በእግር ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። እንዲያውም አንድ አፍሪካዊ የወረዳ የበላይ ተመልካች ወደ አንድ ጉባኤ ለመድረስ ባለቤቱን አዝሎ ወንዝ ለማሻገር ተገዶ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞዎቹ ወቅት ብርድና ሙቀት፣ ረሃብና ጥማት፣ ሌሊቱን ሳይተኙ ማደር፣ ልዩ ልዩ አደጋዎችንና ከባድ ስደቶችን ተቋቁሟል። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ያሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚያጋጥሟቸው ዓይነት ‘የጉባኤዎች ሁሉ አሳብ’ ነበረበት።—2 ቆሮንቶስ 11:23-29
4. የጤና መታወክ በተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና በሚስቶቻቸው ሕይወት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
4 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው የጳውሎስ ጓደኛ እንደ ነበረው እንደ ጢሞቴዎስ አንዳንድ ጊዜ የጤና መታወክ ያጋጥማቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) ይህም በእነሱ ላይ ተጨማሪ ጭንቀት ይፈጥርባቸዋል። የአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሚስት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “ጤንነቴ ትንሽ ከታወከ ከወንድሞች ጋር መሆን ሁልጊዜ ያስጨንቀኛል። በተለይ የወር አበባዬ ዑደት ሊቋረጥ ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ይህን አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በየሳምንቱ ጓዛችንን በሙሉ መጠቅለልና እንደገና ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ፈታኝ ነው። ብዙውን ጊዜ ትንሽ ቆም እልና በዚሁ ለመቀጠል የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ።”
5. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩባቸውም እንኳ ምን መንፈስ አሳይተዋል?
5 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው የጤና መታወክና ሌሎች ፈተናዎች ቢኖሩባቸውም በአገልግሎታቸውና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርገውን ፍቅር በማሳየታቸው ይደሰታሉ። አንዳንዶቹ በስደት ወይም በጦርነት ወቅት ለሌሎች መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። ጉባኤዎችን በሚጎበኙበት ወቅት ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት እንደተናገረው ዓይነት መንፈስ ያሳያሉ፦ “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።”—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8
6, 7. ተግተው የሚሠሩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምን አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ?
6 በጉባኤ ውስጥ እንዳሉት ሌሎች ሽማግሌዎች ሁሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ‘በመስበክና በማስተማር ይደክማሉ።’ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሽማግሌዎች በሙሉ “እጥፍ ክብር ይገባቸዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 5:17) ‘የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልክተን በእምነታቸው ከመሰልናቸው’ ምሳሌነታቸው ሊጠቅመን ይችላል።—ዕብራውያን 13:7
7 አንዳንድ ተጓዥ ሽማግሌዎች በሌሎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል? አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወንድም ፒ በሕይወቴ ላይ ያሳደረው በጎ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ከ1960 ጀምሮ በሜክሲኮ ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግሏል። ልጅ በነበርኩበት ወቅት ጉብኝቶቹን በጉጉትና በደስታ እጠባበቅ ነበር። የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ ‘አንተም የወረዳ የበላይ ተመልካች ነው የምትሆነው’ ብሎኝ ነበር። ዘወትር ጥበብ የተሞላበት ምክር ያካፍለኝ ስለ ነበር አስቸጋሪ በሆነው አፍላ የጉርምስና ዕድሜዬ ወቅት ብዙውን ጊዜ እሱን እፈልገው ነበር። ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መንጋውን መጠበቅ ነበር! አሁን እኔ ራሴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ነኝ። እሱ ለእኔ ያደርግ እንደ ነበረው ሁሉ ዘወትር ጊዜዬን ለወጣቶች እየሠዋሁ ቲኦክራሲያዊ ግቦችን እንዲከታተሉ ለማበረታታት እሞክራለሁ። ወንድም ፒ ሊሞት አቅራቢያ የልብ ድካም ይዞት በነበረበት ጊዜም እንኳ ሁልጊዜ አንድ የሚያበረታታ ቃል ለመናገር ይፈልግ ነበር። በየካቲት 1995 ከመሞቱ አንድ ቀን በፊት አብረን ወደ ልዩ ስብሰባ ሄደን ነበር፤ በዚያን ቀን አንድን መሐንዲስ ወንድም ጠቃሚ ግቦች እንዲያወጣ አበረታታው። ወንድም ወዲያውኑ በቤቴል ለማገልገል ማመልከቻ አስገባ።”
የሚደነቁ ናቸው
8. በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ላይ የተገለጹት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ እነማን ናቸው? ጉባኤውን ሊጠቅሙ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
8 ይገባናል በማይባለው የአምላክ ደግነት ልዩ የአገልግሎት መብቶች የተሰጣቸው ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሌሎች ሽማግሌዎች “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” ተብለው ተጠርተዋል። ኢየሱስ የይሖዋ ወኪልና የጉባኤው ራስ እንደ መሆኑ መጠን እኛ በግለሰብ ደረጃ እንድንታነጽና ወደ ጉልምስና እንድንደርስ እነዚህን መንፈሳዊ ወንዶች ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:8-15) ማናቸውም ስጦታ አድናቆት ሊቸረው ይገባል። በተለይ ደግሞ አንድ ስጦታ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚያበረታን ከሆነ ይህን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሥራ አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህን ሰዎች ‘እንደምናከብራቸው’ በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?—ፊልጵስዩስ 2:29
9. ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው በምን በምን መንገዶች ነው?
9 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት በማስታወቂያ ሲነገር እሱ በሚጎበኝበት ሳምንት ጉባኤው በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ እቅድ ማውጣት ልንጀምር እንችላለን። ምናልባት በጉብኝቱ ወቅት በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ተጨማሪ ጊዜ መመደብ እንችል ይሆናል። በዚያ ወር ረዳት አቅኚ ሆነን ለማገልገል እንችል ይሆናል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ አገልግሎታችንን እንድናሻሽል የሚሰጣቸውን ሐሳቦች በሥራ ላይ ለማዋል እንደምንፈልግ አያጠራጥርም። እንዲህ ዓይነቱ የተቀባይነት መንፈስ እኛን ከመጥቀሙም በላይ ጉብኝቱ ውጤታማ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። እርግጥ፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤውን የሚጎበኙት እኛን ለማነጽ ነው፤ ሆኖም እነሱም ጭምር በመንፈሳዊ መታነጽ ይፈልጋሉ። ጳውሎስ ማበረታቻ የፈለገባቸው ጊዜያት ነበሩ። ብዙውን ጊዜም ሌሎች ክርስቲያኖች እንዲጸልዩለት ይጠይቅ ነበር። (ሥራ 28:15፤ ሮሜ 15:30-32፤ 2 ቆሮንቶስ 1:11፤ ቆላስይስ 4:2, 3፤ 1 ተሰሎንቄ 5:25) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የእኛ ጸሎትና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል።
10. የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሥራ አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
10 ለወረዳ የበላይ ተመልካቹና ለባለቤቱ ጉብኝታቸውን ምን ያህል እንደምናደንቅ ነግረናቸው እናውቃለን? ለሰጠን ጠቃሚ ምክር እናመሰግነዋለን? የመስክ አገልግሎትን በተመለከተ ያቀረባቸው ሐሳቦች በአገልግሎት የምናገኘውን ደስታ ከፍ እንዳደረጉልን እንገልጽለታለን? ይህን ማድረጋችን ሥራው አስደሳች እንዲሆንለት ያደርጋል። (ዕብራውያን 13:17) በስፔይን የሚገኝ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉባኤዎችን ከጎበኙ በኋላ የሚቀበሏቸውን የምስጋና ካርዶች እሱና ባለቤቱ ምን ያህል ከፍ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ገልጿል። እንዲህ አለ፦ “እነዚህን ካርዶች እናስቀምጣቸውና ተስፋ በምንቆርጥበት ወቅት እናነባቸዋለን። የእውነተኛ ማበረታቻ ምንጭ ሆነውልናል።”
11. የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾችን ሚስቶች እንደምንወዳቸውና እንደምናደንቃቸው እንዲያውቁ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
11 የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ሚስቶች ማመስገን ጥሩ መሆኑ አያጠራጥርም። የተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ሚስት በዚህ የአገልግሎት መስክ ባሏን ለመርዳት ብዙ መሥዋዕትነቶችን ከፍላለች። እነዚህ ታማኝ እህቶች በራሳቸው ቤት የመኖርና ብዙውን ጊዜም ልጅ የመውለድ የተፈጥሮ ፍላጎታቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ። የዮፍታሔ ልጅ አባቷ ለአምላክ የተሳለውን ስዕለት ለመፈጸም ስትል ባል ለማግባትና ቤተሰብ ለመመሥረት ያላትን አጋጣሚ በፈቃደኝነት የተወች የአምላክ አገልጋይ ነበረች። (መሳፍንት 11:30-39) የከፈለችው መሥዋዕትነት እንዴት ታይቶ ነበር? መሳፍንት 11:40 “የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ [“እንዲያመሰግኑ፣” የ1879 እትም] በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ” ሲል ይገልጻል። የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾችን ሚስቶች እንደምናፈቅራቸውና እንደምናደንቃቸው ለመናገር ጥረት ብናደርግ መልካም ነው።
“እንግዶችን መቀበል አትርሱ”
12, 13. (ሀ) ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንድናሳይ የሚያደርገን ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለ? (ለ) እንዲህ ዓይነቱ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የጋራ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
12 እንግዳ ተቀባይነት በክርስቲያናዊው የተጓዥነት ሥራ ላይ ላሉት ፍቅራችንንና አድናቆታችንን የምንገልጽበት ሌላው መንገድ ነው። (ዕብራውያን 13:2) በተጓዥ ሚስዮናዊነት ጉባኤውን ለሚጎበኙት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየቱ ሐዋርያው ዮሐንስ ጋይዮስን አመስግኖታል። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ወዳጅ ሆይ፣ ምንም እንግዶች ቢሆኑ፣ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፣ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ፤ ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና። እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል።” (3 ዮሐንስ 5-8) በዛሬው ጊዜ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው ተመሳሳይ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ልናስፋፋ እንችላለን። እርግጥ የጉባኤው ሽማግሌዎች ጥሩ መስተንግዶ መደረጉን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ ሆኖም አንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “ከወንድሞች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ለእኛ አንድ ነገር ሊያደርጉልን በመቻላቸው ላይ የተመካ መሆን የለበትም። እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ማሳደር አንፈልግም። ሀብታምም ሆነ ድሀ ማንኛውም ወንድማችን የሚያደርግልንን መስተንግዶ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን።”
13 እንግዳ ተቀባይነት የጋራ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል። ቀደም ሲል የወረዳ የበላይ ተመልካች የነበረውና በአሁኑ ጊዜ በቤቴል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኘው ዦርዤ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “እነዚህ ጉብኝቶች ካሰብኩት በላይ የረዱኝ ይመስለኛል። በጉርምስና ዕድሜዬ መንፈሳዊ ችግሮች ነበሩብኝ። እናቴ ይህ ሁኔታ ቢያስጨንቃትም እንዴት ልትረዳኝ እንደምትችል ግራ ገባት፤ ስለዚህ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እኔን እንዲያነጋግረኝ ጠየቀችው። በመጀመሪያ ላይ ገና ለገና ይገስጸኛል ብዬ በመፍራት እርቀው ነበር። ሆኖም የወዳጅነት አቀራረቡ በመጨረሻ ከእሱ ጋር እንድነጋገር አስገደደኝ። አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ምግብ ጋበዘኝ፤ ችግሬን እንደሚረዳልኝ እርግጠኛ ስለ ነበርኩ የልቤን አጫወትኩት። በጥሞና አዳመጠኝ። የሰጠኝ በጣም ጠቃሚ የሆነ ምክር ረድቶኛል። ከዚያ ወዲህ በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጀመርኩ።”
14. ተጓዥ ሽማግሌዎችን ከመተቸት ይልቅ ማድነቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
14 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወጣቶችንም ሆነ አረጋውያንን ሳይለይ መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ጥረት ያደርጋል። ስለሆነም ለሚያደርጋቸው ጥረቶች አድናቆት ማሳየት እንዳለብን እሙን ነው። ሆኖም በደካማ ጎኖቹ ምክንያት ብንተቸው ወይም ጉባኤውን ከጎበኙ ሌሎች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ብናወዳድረው ምን ሊሰማው ይችላል? ይህ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ስላከናወናቸው ሥራዎች ነቀፋ መስማቱ ጳውሎስን አላበረታታውም። አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ቁመናውና የንግግር ችሎታው መጥፎ አስተያየት የሰነዘሩ ይመስላል። እነዚህ ተቺዎች “መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፣ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” እንዳሉ እሱ ራሱ ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 10:10) ሆኖም ብዙውን ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ከፍቅር የመነጩ የአድናቆት ቃላት የሚሰሙ መሆናቸው ያስደስታል።
15, 16. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው የእምነት ጓደኞቻቸው በሚያሳዩት ፍቅርና ቅንዓት የሚነኩት እንዴት ነው?
15 በላቲን አሜሪካ የሚገኝ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የሽምቅ ተዋጊዎች በሚቆጣጠሩት ክልል ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞቹንና እህቶቹን ለመጎብኘት አንድ ቀን ሙሉ በጭቃማ መንገድ ላይ ተጓዘ። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወንድሞች ለጉብኝቱ ያሳዩትን አድናቆት ማየት ልብ የሚነካ ነው። እዚህ ቦታ ለመድረስ ብዙ አደጋዎችንና ችግሮችን መጋፈጥ የነበረብኝ ቢሆንም ወንድሞች ባሳዩት ፍቅርና ቅንዓት ተክሻለሁ።”
16 አንድ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኝ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወንድሞች ለእኛ ባሳዩን ፍቅር ምክንያት የታንዛኒያ ክልላችንን በጣም እንወደዋለን! ወንድሞች ከእኛ ለመማር ዝግጁዎች ናቸው። እኛን በቤታቸው ለማስተናገድም ፈቃደኞች ናቸው።” በሐዋርያው ጳውሎስ እንዲሁም አቂላና ጵርስቅላ በተባሉት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ባልና ሚስት መካከል ፍቅራዊና አስደሳች ግንኙነት ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ስለ እነሱ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፣ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም።” (ሮሜ 16:3, 4) ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየትና ጊዜያቸውን ከእነሱ ጋር ለማሳለፍ ልዩ ጥረት የሚያደርጉ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ያሉ ወዳጆች በማግኘታቸው አመስጋኝ ናቸው።
ጉባኤዎችን ማበረታታት
17. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንዲኖሩ ከተደረገው ዝግጅት በስተጀርባ ጥበብ አለ ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ትምህርት የሚያገኙት ከየት ነው?
17 ኢየሱስ “ጥበብ በሥራዎቿ ጸደቀች” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19 አዓት) የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መኖር የአምላክ ሕዝብ ጉባኤዎችን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑ ከዚህ ዝግጅት በስተጀርባ ላለው ጥበብ ሕያው ማስረጃ ነው። በጳውሎስ ሁለተኛ የሚስዮናዊ ጉዞ ወቅት እሱና ሲላስ ‘ጉባኤዎችን እያበረታቱ በሶርያና በኪልቅያ በኩል አልፈው ነበር።’ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “በየከተማው ሲያልፉ በኢየሩሳሌም ባሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የተወሰነውን ደንብ ለአማኞች ያስታውቁ ነበር፤ በሥራ ላይ እንዲያውሉትም ያሳስቡአቸው ነበር። ስለዚህ አብያተ ክርስቲያናት [“ጉባኤዎች፣” አዓት] በእምነት ጠነከሩ፤ ቁጥራቸውም በየቀኑ እየጨመረ ይሄድ ነበር።” (ሥራ 15:40, 41 የ1980 ትርጉም፤ 16:4, 5 የ1980 ትርጉም) እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም በቅዱሳን ጽሑፎችና “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች አማካኝነት መንፈሳዊ መመሪያ ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 24:45
18. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን የሚያበረታቱት እንዴት ነው?
18 አዎን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ከይሖዋ መንፈሳዊ ማዕድ መመገባቸውን መቀጠል ያስፈልጋቸዋል። ከአምላክ ድርጅት አሠራሮችና መመሪያዎች ጋር በሚገባ መተዋወቅ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ካደረጉ እነዚህ ወንዶች ለሌሎች በረከት ሊሆኑ ይችላሉ። ለመስክ አገልግሎት ባላቸው ቅንዓት ረገድ ግሩም ምሳሌ በመሆን የእምነት ጓደኞቻቸው በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንዲሻሻሉ ሊረዷቸው ይችላሉ። እነዚህ ጎብኚ ሽማግሌዎች የሚሰጧቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮች አድማጮችን በመንፈሳዊ ይገነባሉ። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር ሌሎች በሥራ ላይ እንዲያውሉ በመርዳት፣ በመላው ዓለም ከሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ጋር ተስማምተው በማገልገልና አምላክ ‘በታማኙ ባሪያ’ በኩል ያደረጋቸውን መንፈሳዊ ዝግጅቶች በመጠቀም የሚጎበኟቸውን ጉባኤዎች ያበረታታሉ።
19. ገና መብራራት የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
19 ይህ መጽሔት የይሖዋ ድርጅት ከመቶ ዓመት በፊት ተጓዥ ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን እንዲጎበኙ ዝግጅት ባደረገበት ወቅት “ይህ ዝግጅት የሚያስገኘውን ውጤትና የይሖዋን ተጨማሪ አመራር ወደፊት እንመለከታለን” ሲል ገልጾ ነበር። የይሖዋ አመራር በግልጽ ታይቷል። በእሱ በረከትና በአስተዳደር አካሉ የበላይ ቁጥጥር አማካኝነት ይህ ሥራ ከጊዜ በኋላ እየሰፋና ይበልጥ ጥራት እያገኘ ሄዷል። በዚህም ምክንያት በመላው ምድር የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በእምነት ሊጠነክሩና ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨረ ሊሄድ ችሏል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ እነዚህ ስጦታ የሆኑ ወንዶች ያሳዩትን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ባርኳል። ይሁን እንጂ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሥራቸውን በተሳካ መንገድ ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው? ዓላማቸው ምንድን ነው? ጉባኤዎችን በይበልጥ ለመጥቀም የሚችሉት እንዴት ነው?
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ያሏቸው አንዳንድ ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
◻ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
◻ ለተጓዥ ሽማግሌዎችና ለሚስቶቻቸው ሥራ አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎች በእምነት እንዲጠነክሩ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በየጊዜው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓዝ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይተህ ታውቃለህን?