የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሚካኤል (አንዳንድ ሃይማኖቶች “ቅዱስ ሚካኤል” ይሉታል) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትና ተመልሶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ የሚጠራበት ስም እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።a ሚካኤል ሙሴ ከሞተ በኋላ ከሰይጣን ጋር ተከራክሯል እንዲሁም የአምላክን መልእክት ወደ ነቢዩ ዳንኤል እንዲያደርስ አንድን መልአክ ረድቷል። (ዳንኤል 10:13, 21፤ ይሁዳ 9) ሚካኤል ለአምላክ አገዛዝ በመቆምና ከአምላክ ጠላቶች ጋር በመዋጋት “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም ካለው ስሙ ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል።—ዳንኤል 12:1፤ ራእይ 12:7
እስቲ ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው እንድንል የሚያደርጉ ነጥቦችን እንመልከት።
ሚካኤል “የመላእክት አለቃ” ነው። (ይሁዳ 9) “የመላእክት አለቃ” የሚለው ማዕረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሁለት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው። ሁለቱም ቦታዎች ላይ የተጠቀሰው በነጠላ ቁጥር ሲሆን ይህም በዚህ ማዕረግ የሚጠራው አንድ መልአክ ብቻ እንደሆነ ይጠቁማል። ከእነዚህ ጥቅሶች አንዱ፣ ጌታ ኢየሱስ “በትእዛዝ ድምፅ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በአምላክ መለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳል” በማለት ይናገራል። (1 ተሰሎንቄ 4:16) ኢየሱስ ‘የመላእክት አለቃ ድምፅ’ ያለው እሱ ራሱ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስለሆነ ነው።
ሚካኤል የመላእክት ሠራዊት አዛዥ ነው። “ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው [ከሰይጣን] ጋር ተዋጉ።” (ራእይ 12:7) ሚካኤል “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ” እንዲሁም “ታላቁ አለቃ” በመባል መጠራቱ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ትልቅ ሥልጣን እንዳለው ያሳያል። (ዳንኤል 10:13, 21፤ 12:1) የአዲስ ኪዳን ምሁር የሆኑት ዴቪድ ኦን እንደተናገሩት እነዚህ ማዕረጎች ሚካኤል “የመላእክት ሠራዊት ዋና አዛዥ” እንደሆነ ያሳያሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሚካኤል ከሚለው ስም ሌላ በመላእክት ሠራዊት ላይ ሥልጣን እንዳለው አድርጎ የሚጠቅሰው ሌላ አንድ ስም አለ። ‘ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር በሰማይ በሚንበለበል እሳት እንደሚገለጥና የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ’ ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 1:7, 8፤ ማቴዎስ 16:27) “ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን . . . መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።” (1 ጴጥሮስ 3:21, 22) አምላክ ኢየሱስንና ሚካኤልን በቅዱሳን መላእክቱ ላይ ተቀናቃኝ አዛዦች አድርጎ ይሾማቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስና ሚካኤል የሚሉት ሁለቱም ስሞች የሚያመለክቱት ተመሳሳይ አካልን ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው።
ሚካኤል ከዚያ ቀደም ሆኖ በማያውቅ ‘የጭንቀት ዘመን ወቅት ይነሳል።’ (ዳንኤል 12:1) በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ‘መነሳት’ የሚለው አገላለጽ አንድ ንጉሥ አንድ ለየት ያለ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚነሳ ለማሳየት በተደጋጋሚ ተሠርቶበታል። (ዳንኤል 11:2-4, 21) “የአምላክ ቃል” ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ “የነገሥታት ንጉሥ” በመሆን የአምላክን ጠላቶች በሙሉ ለማጥቃትና የአምላክን ሕዝቦች ለመጠበቅ እርምጃ ይወስዳል። (ራእይ 19:11-16) ይህን የሚያደርገው “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ” ታላቅ መከራ በሚከሰትበት ወቅት ነው።—ማቴዎስ 24:21, 42
a መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ በሆነ ስም የሚጠራቸው ሌሎች ሰዎችም ይገኛሉ፤ ከእነዚህም መካከል ያዕቆብ (እስራኤል ተብሎም ተጠርቷል)፣ ጴጥሮስ (ስምዖን ተብሎም ተጠርቷል) እንዲሁም ታዴዎስ (ይሁዳ ተብሎም ተጠርቷል) ይገኙበታል።—ዘፍጥረት 49:1, 2፤ ማቴዎስ 10:2, 3፤ ማርቆስ 3:18፤ የሐዋርያት ሥራ 1:13