እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነት የሚያሰለጥነው ጊልያድ
“ተማሪዎቻችን እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነት በሚገባ ሰልጥነዋል።” እነዚህ እሁድ መስከረም 12, 1993 የተካሄደው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጊልያድ ትምህርት ቤት የ95ኛው ኮርስ ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ስርዓት የመክፈቻ ቃላት ነበሩ። በዚያን ዕለት ጠዋት 4,614 የሚያክሉ ተጋባዦችና የቤቴል ቤተሰብ አባሎች በተሰበሰቡበት በጀርሲ ሲቲ የክልል ስብሰባ አዳራሽ የተከናወነው ዝግጅት ጆርጅ ጋንገስ ባደረገው ጸሎት ተከፈተ። የ97 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድም ጋንገስ በቤቴል ቤተሰብ ውስጥ 65 ዓመታት የኖረና ከአስተዳደር አካል አባላት በዕድሜ አንጋፋው ወንድም ነው።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነውና የስብሰባው ሊቀመንበር የነበረው አልበርት ሽሮደር “የጊልያድ ስልጠና ለአምስት ወራት ያህል የቆየ ሲሆን ያተኮረው እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነት ላይ ነው” ብሏል። ነገር ግን ይህ ‘እጅግ ቅዱስ የሆነ እምነት’ ምንድን ነው? በይሁዳ 20 ላይ የተጠቀሰው ይህ ‘ከሁሉ በላይ የተቀደሰ እምነት’ የመላው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው በማለት አስረድቷል። ስለዚህ የጊልያድ ስልጠና ያተኮረው የትምህርት ቤቱ ዋነኛ የማስተማሪያ መጽሐፍ በሆነው በይሖዋ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው።
ተማሪዎች ተጨማሪ መመሪያ ተቀበሉ
“ጠቢባን ሰዎች ከሚያሳድሩት ተፅዕኖ መጠቀም” የሚል መልእክት ያለው ንግግር ያቀረበው የመጀመሪያው ተናጋሪ የመጠበቂያ ግንብ እርሻ ኮሚቴ አባል የሆነው ጆን ስቱፍሎትን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከጠቢባን ጋር የሚሄዱ ጠቢብ ይሆናሉ’ ይላል። (ምሳሌ 13:20) ተማሪዎቹ በጊልያድ ስልጠና ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት 900 ሰዓታት አሳልፈዋል። ወንድም ስቱፍሎትን ተማሪዎቹን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ይሖዋ ያሳደረባችሁ በጎ ተፅዕኖ የሚነካችሁ እንዴት ነው? በጠቅላላው 170 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ወደሚኖሩባቸው 18 አገሮች ልትሄዱ ነው። ታዲያ በእነዚህ ሰዎች ላይ እንዴት ያለ ተፅዕኖ ታሳድራላችሁ?” አዲሶቹ ሚስዮናውያን የይሖዋን ጥበብ በማንጸባረቅ ሌሎች ዳርቻ የሌለው ጥበብ ምንጭ የሆነው የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ከዚህ ቀጥሎ “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ መሆን” የሚል መልእክት ያለው ንግግር ያቀረበው ደግሞ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሎይድ ባሪ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ወንድም ባሪ ራሱ ከ45 ዓመታት በፊት የ11ኛው የጊልያድ ኮርስ ተማሪ ነበር። የ95ኛው ኮርስ ተማሪዎች በውጭ አገሮች የብዙ ዓመታት ልምድ ካለው ከዚህ የቀድሞ ሚስዮናዊ ተግባራዊ ምክር በመቀበላቸው ተደስተዋል። ተማሪዎቹ የአካባቢውን ባሕል በማወቅና ቋንቋውን በመማር በሚሄዱበት አዲስ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር በፍጥነት እንዲመሳሰሉ አበረታታቸው። የአካባቢውን ባሕልና ቋንቋ በፍጥነት ለመማር የሚቻለው ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመቀላቀልና አብሮ በመሥራት እንዲሁም ባህላቸውን በማወቅ ተገቢ ሆኖ ሲገኝም እነርሱን በመምሰል እንደሆነ ተናግሯል።
ቀጥሎ የፋብሪካ ኮሚቴ አባል የሆነው ዲን ሶንገር “ከሌሎች ግዴታዎች ነፃ ሁኑ” የሚል ንግግር አቀረበ። ወንድም ሶንገር ከ35 ዓመታት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈ በመሆኑ ወደ አንዱ አቅጣጫ ብቻ ያተኮረ፣ ቀላል፣ ለቁሳዊ ነገር ከመጨነቅ የራቀ፣ በሚሠራው ሥራ ላይ ያተኮረ ሕይወት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃል። ለተማሪዎቹ የሰጠው ምክር ፍሬ ሐሳብም ይኸው ነበር። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ያገለግሉ የነበሩት መዘምራን ለተሰጣቸው ልዩ ኃላፊነት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ማቅረብ እንዲችሉ ሌሎቹ ሌዋውያን ይሰጧቸው ከነበሩት አገልግሎቶች ሁሉ ነፃ ተደርገው ነበር። (1 ዜና መዋዕል 9:33) በተመሳሳይም የጊልያድ ሚስዮናውያን በተሰጣቸው ልዩ ሥራ ላይ ማተኮር እንዲችሉ እንደ ዓለማዊ ሥራ ካሉት ተራ ጉዳዮች ነፃ ሆነዋል። ወንድም ሶንገር ንግግሩን በሚከተሉት ማሳሰቢያዎች ደመደመ:- “አመለካከታችሁ የተስተካከለና አኗኗራችሁ ቀላል ይሁን። ኃላፊነታችሁ ይሖዋን ቀንና ሌሊት ለማገልገል ከሌሎች ግዴታዎች ነፃ እንደነበሩት ሌዋውያን ይሖዋን ማወደስ ነው።”
በመቀጠል የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ “ሌሎች ከሕይወታቸው የበለጠ መጠቀም እንዲችሉ ማስተማር” የሚል መልእክት ያለው ንግግር አቀረበ። ተማሪዎቹን “መሠረተ ትምህርቶችን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ሰዎች ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለማሳየት የሚያስችል ድፍረት” እንዲኖራቸው አበረታታቸው። ጥሩ አስተማሪዎች የተማሪዎቻቸውን መንፈስ ማነሣሳትና መቀስቀስ አለባቸው። “ሕግና ሥርዓት ማስተማር ብቻ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ለሆኑ ነገሮች ከፍተኛ ግምት እንዲኖራቸው ለማድረግ ንቁዎች ሁኑ።” በመደምደሚያውም ላይ “ውድ ወንድሞች ከሁሉም በላይ የፍጻሜ ማሰሪያ ነውና ሌሎች ሰዎችን እንዴት መውደድ እንደሚቻል ራሳችሁንና ሌሎችን አስተምሩ” አለ። — 1 ቆሮንቶስ 13:1–3፤ ቆላስይስ 3:14
ተማሪዎቹ ባሳለፏቸው የሥልጠና ወራት ለሁለት የጊልያድ አስተማሪዎቻቸው የተለየ ፍቅር አድሮባቸዋል። በመጀመሪያ ንግግር ያደረገው ሚስዮናዊ የነበረው ጃክ ሬድፎርድ ሲሆን የንግግሩ ርዕስ “ትክክለኛውን ምርጫ አድርጋችኋል” የሚል ነበር። ጳውሎስ ክርስቲያን ሐዋርያ ከመሆኑ በፊት በጥንቱ የአይሁድ ዓለም ውስጥ ሥልጣን፣ ክብር፣ ተሰሚነትና የተደላደለ ቁሳዊ ንብረት ነበረው። ነገር ግን ጳውሎስ እንደ ፊሊፕስ ትርጉም በፊሊጵስዩስ 3:8 ላይ ይህ ሁሉ ነገር እንደ “ቆሻሻ ክምር” ወይም “ጥራጊ” እንደሆነ ተናግሯል። ልቡ ያተኮረው በአገልግሎቱ ላይ ነበር። ያደረገው ምርጫ ትክክል ነበር። የዘመናችን ሰዎች ግን በአብዛኛው ቁሳዊ ሀብታቸውን ከዘላለም ሕይወት እንደሚያስበልጡ በምርጫቸው አሳይተዋል። የጊልያድ ሚስዮናውያን ትክክለኛውን ነገር መርጠዋል። ጃክ ሬድፎርድ “የሰይጣን ዓለም ከሚሲዮናዊነት አገልግሎት ጋር የሚወዳደር ምንም ነገር ሊሰጣችሁ አይችልም። ያገኛችሁትን በዋጋ ሊተመን የማይችል መብት ተንከባከቡ፤ ዓለም የራሱን ጥራጊ እንዲንከባከብ ተውት!” በማለት ንግግሩን ደመደመ።
ዩሊሰስ ግላስ ላለፉት 32 ዓመታት የጊልያድ አስተማሪ ሆኖ አገልግሏል። ለተማሪዎቹ በመዝሙር 1:3 ላይ የተመሠረተ “ዛፍ ማሳደግ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው” የሚል ርዕስ ያለው ምክር ሰጣቸው። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በአምላክ የተነደፈውን የዛፍ አፈጣጠር ሊተካከል የሚችል ነገር ለማስገኘት አልቻለም። ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ መንገድ ይሖዋ እንደተከላቸውና እንደሚያጠጣቸው ዛፎች ናቸው። ወንድም ግላስ ተማሪዎቹ በመንፈሳዊ ደን ወይም ገነት ውስጥ እንደሚገኝ ዛፍ ለአምስት ወራት ያለማቋረጥ “በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው ሕይወት ሰጪ የውኃ ምንጭ” ሲጠጡ እንደቆዩ ጠቀሰ። ይሁንና ሚስዮናውያን እንደመሆናቸው መጠን “ያላቸውን መንፈሳዊ ሥር ከማንኛውም ጉዳት መከላከል ይኖርባቸዋል።” ‘ዛፍ ማሳደግ የሚችለው አምላክ ብቻ ስለሆነ ከይሖዋ የሚገኘውን የሕይወት ውኃ መጠጣታቸውን እንዲቀጥሉ’ በጥብቅ አበረታታቸው።
የመጨረሻው ንግግር ያደረገው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ካሬይ ባርበር ነበር። ከ70 ዓመታት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በኋላ ይህ ወንድም “ለአምላክ ብቻ የተወሰናችሁ ሁኑ” የሚል መልእክት ያለውን ንግግር በልበ ሙሉነት ሊያቀርብ ችሎ ነበር። አብዛኛው የሰው ዘር ለይሖዋ የተወሰነ አይደለም። (ዘዳግም 5:9) ይሁን እንጂ ወንድም ባርበር እንደተናገረው ፍጽምና የሌለን ብንሆንም እንኳ “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደርን ሰዎች ለመሆን እንችላለን።” ጨምሮም “ማንም ሰው ‘ይህንን እንድፈጽም ያደረገኝ ሰይጣን ነው’ ማለት አይችልም” ብሏል። ነገር ግን ሰይጣንን ካልተቃወምነው ሊያሸንፈን ይችላል። (ያዕቆብ 4:7) ሰይጣንንና ዓለሙን በመቃወም ለይሖዋ ብቻ የተወሰንን መሆን የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በይሖዋ ሥራ መጠመድ ነው።
የሚስዮናዊነት ሹመት ተቀበሉ
46ቱም ተማሪዎች ሚስዮናዊያን በመሆን በይፋ ከተሾሙ በኋላ የጠዋቱ ፕሮግራም ተጠናቀቀ። እነዚሁ 23 ባልና ሚስት ሚስዮናውያን ተመራቂዎች በከፊል የሚከተለው መግለጫ የሰፈረበት ዲፕሎማ ተቀበሉ:- “በጎ ፈቃድ የሚያስፋፋ፣ በሕዝቦች መካከል ዘላቂነት ያለው ሰላም፣ ፍጹም የሆነ የሥርዓትና የጽድቅ ሕግ እንዲሰፍን የሚያስችል ትምህርት ለማስተማር ልዩ ብቃት አለው።” የ95ኛው የጊልያድ ኮርስ ተመራቂዎች ተመድበው በሚሄዱባቸው 18 አገሮች ይህንን በጣም ከፍተኛ የሆነ ተልዕኮ ለመፈጸም እንደሚጥሩ የተረጋገጠ ነው። የተመደቡባቸው አገሮች በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን የሚገኙ ናቸው።
ከሰዓት በኋላ በአገልግሎት ክፍል ኮሚቴ አባል በቻርልስ ዉዲ አጭር የመጠበቂያ ግንብ ንግግር ከቀረበ በኋላ አዲሶቹ የጊልያድ ምሩቃን “ጊልያድ ሚሲዮናውያን በመሆን እንድናስተምር አሰልጥኖናል” በሚል ርዕስ የተማሪ ፕሮግራማቸውን አቀረቡ። ጠቅላላ ፕሮግራሙ “ከፊታችን የሚጠብቁን ምርጫዎች” የሚል ርዕስ ባለው ድራማ ተጠናቀቀ።
ከዚህ የሚያነቃቃ ፕሮግራም በኋላ አዲሶቹ ሚስዮናዊያን ‘እጅግ ቅዱስ የሆነውን እምነት’ ለሌሎች ለማካፈል ወደ አራቱ የምድር ማዕዘናት ለመላክ ዝግጁ ሆኑ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አሐዛዊ መረጃዎች
ሚስዮናውያኑ የመጡባቸው አገሮች:- 7
የተመደቡባቸው አገሮች:- 18
የተማሪዎች ጠቅላላ ቁጥር:- 46
ባልና ሚስት የሆኑ:- 23
አማካይ ዕድሜ:- 30.06
በዕውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12.92
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 9.4
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች የ95ኛው ክፍል
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር የረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን የእያንዳንዱ ረድፍ የስም ዝርዝር የተጻፈው ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) በዌሎ ዲ፤ ዶንዛ ቪ፤ ኢንስ ኤስ፤ ፍለክ ኤን፤ ቢሊኒስቤ ኤም፤ ሆድኖት ኤል፤ ኒየግራን ቢ፤ ኤሪክሶን ኤል፤ (2) ቦክር ጄ፤ ቶማስ ኤም፤ ስቴድማን ኤስ፤ ቢሊንግስባይ ዲ፤ ዎ አይ፤ ፐረቪስ ኤም፤ ለትረል ኤም፤ (3) ያኮብሰን ቲ፤ ቦክር ጄ፤ ማርቲኔዝ ኤል፤ ኔልሰን ኢ፤ ፐርቨስ ፒ፤ ሆልት ኤል፤ ላርስን ኤም፤ ጆንስ ኤል፤ (4) ኑሜነን ፒ፤ ኑሜነን ኤች፤ በዌሎ ኤም፤ ኦልሰን ደብሊዩ፤ ሆልት ኤስ፤ ዶንዝ ጂ፤ ዳዝሃርዳን ሲ፤ ዳዝሃርዳን ዲ፤ (5) ላርሰን ኬ፤ ማርቲኔዝ ዲ፤ ኒየግረን ፒ፤ ዎ ፒ፤ ጆንስ ዲ፤ ሆድኖት ጄ፤ ቶማስ ጂ፤ (6) ኢንስ ቢ፤ ፍለክ አር፤ ኤሪክሶን ኤ፤ ኒልሰን ኤስ፤ ስቴድማን ጄ፤ ኦልሰን ኬ፤ ያኮበሰን ኤፍ፤ ለትረል ጄ