ምዕራፍ ሃያ አንድ
የይሖዋ ዓላማ በሚያስደንቅ ሁኔታ ግቡን ይመታል
1, 2. (ሀ) ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታቱን በተመለከተ ያለው ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) አምላክን አንድ ሆኖ የሚያመልከው ቤተሰብ እነማንን ያቀፈ ነው?
የይሖዋ ፍቅራዊ ዓላማ፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ እውነተኛውን አንድ አምላክ በማምለክ በአንድ አምልኮ ጥላ ሥር ተሰባስበውና የአምላክን ልጆች ታላቅ ነፃነት አግኝተው በደስታ እንዲኖሩ ነው። ጽድቅን የሚወዱ ሁሉ አጥብቀው የሚመኙት ነገርም ይኸው ነው።
2 ይሖዋ ይህን ታላቅ ዓላማ መፈጸም የጀመረው ገና የፍጥረት ሥራውን እንደጀመረ ነው። ይሖዋ በመጀመሪያ የፈጠረው፣ ከሞት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ “የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ” የሆነውን ልጁን ነው። (ዕብራውያን 1:1-3) ይህ ልጅ አምላክ ብቻውን የፈጠረው ስለሆነ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ነው። ሌሎች ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ የሰማይ መላእክት በኋላም በምድር የሚኖሩ ሰዎች የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው። (ኢዮብ 38:7፤ ሉቃስ 3:38) እነዚህ ሁሉ በአንድነት አንድ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ሆነዋል። ለሁሉም ይሖዋ አምላካቸው፣ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥያቸውና አፍቃሪ አባታቸው ነበር።
3. (ሀ) ሁላችንም ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምን ወርሰናል? (ለ) ይሖዋ ለአዳም ዘሮች ምን ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጓል?
3 የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን አውቀው ኃጢአት በመሥራታቸው አምላክ ሞት የፈረደባቸውና ከኤደን ያባረራቸው ሲሆን ልጆቹ የመሆን መብትም አጥተዋል። ከአጽናፈ ዓለማዊው የይሖዋ ቤተሰብ ተገለሉ። (ዘፍጥረት 3:22-24፤ ዘዳግም 32:4, 5) ሁላችንም የእነሱ ዘሮች እንደመሆናችን መጠን የኃጢአት ዝንባሌዎችን ወርሰናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከአዳምና ሔዋን ዘሮች መካከል አንዳንዶቹ ጽድቅን የሚወዱ እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር። በመሆኑም “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት” መድረስ እንዲችሉ ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎላቸዋል።—ሮሜ 8:20, 21
እስራኤላውያን በአምላክ ፊት የነበራቸውን ሞገስ አጡ
4. ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን ምን መብት ሰጥቷቸው ነበር?
4 አዳም ከተፈጠረ ከ2,500 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ የተወሰኑ ሰዎች ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰጥቶ ነበር። የጥንቶቹን እስራኤላውያን ሕዝቡ እንዲሆኑ የመረጣቸው ከመሆኑም ሌላ ሕጉንም ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 12:1, 2) አንድ ብሔር አድርጎ ያደራጃቸው ሲሆን ከዓላማው ጋር በተያያዘም ተጠቅሞባቸዋል። (ዘዳግም 14:1, 2፤ ኢሳይያስ 43:1) ይሁን እንጂ ገና ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ስላልተላቀቁ አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ዓይነት ድንቅ የሆነ ነፃነት አልነበራቸውም።
5. እስራኤላውያን በአምላክ ፊት የነበራቸውን ልዩ ሞገስ ያጡት እንዴት ነው?
5 ያም ሆኖ እስራኤላውያን በአምላክ ፊት ልዩ ሞገስ አግኝተው ነበር። በተጨማሪም ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው የማክበርና ከዓላማው ጋር ተስማምተው የመሥራት ኃላፊነት ነበረባቸው። ኢየሱስ ይህን ግዴታቸውን መወጣታቸው በጣም አስፈላጊ እንደነበረ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 5:43-48) ሆኖም የእስራኤል ሕዝብ ይህን ሳያደርግ ቀረ። አይሁዳውያን ‘አባታችን አንዱ እግዚአብሔር ነው’ ብለው ቢናገሩም ኢየሱስ ድርጊታቸውና መንፈሳቸው ከዚህ አባባላቸው ጋር እንደሚጋጭ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:41, 44, 47) በ33 አምላክ ሕጉን የሻረው ሲሆን እስራኤላውያን ከእሱ ጋር የነበራቸው ልዩ ዝምድናም አበቃ። ይሁንና እንዲህ ሲባል ከዚህ በኋላ ሰዎች ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት አይችሉም ማለት ነው?
‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች’ መሰብሰብ
6. ጳውሎስ በኤፌሶን 1:9, 10 ላይ የገለጸው ዝግጅት ዓላማ ምንድን ነው?
6 ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰው ዘሮች መካከል የተወሰኑ ሰዎች ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት እንደሚችሉ አመልክቷል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ እምነት የሚያሳዩ ሰዎች የአምላክ ቤተሰብ አባላት መሆን ስለሚችሉበት የይሖዋ ዝግጅት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[አምላክ] በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌሶን 1:9, 10) ይህ ዝግጅት ያተኮረው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው። የሰው ልጆች በእሱ አማካኝነት በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ያገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ አላቸው። ሌሎች ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።
7. ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ የተባሉት እነማን ናቸው?
7 በመጀመሪያ በ33 ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት አንስቶ ‘በሰማይ ላሉት ነገሮች’ ማለትም ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ለሚገዙት ትኩረት ተሰጠ። በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት በአምላክ ፊት ጻድቃን ሆነዋል። (ሮሜ 5:1, 2) ከጊዜ በኋላ ይህ ቡድን ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎችን ያቀፈ ሲሆን ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ የተባሉት በአጠቃላይ ቁጥራቸው 144,000 ነው። (ገላትያ 3:26-29፤ ራእይ 14:1) ከእነዚህ መካከል በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት የተወሰኑ ቀሪዎች ብቻ ናቸው።
‘በምድር ያሉትን ነገሮች’ መሰብሰብ
8. ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት እነማን ናቸው? ከይሖዋስ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና አላቸው?
8 ‘በምድር ያሉትም ነገሮች’ የሚሰበሰቡት በዚሁ ዝግጅት አማካኝነት ነው። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በመሰብሰብ ላይ ናቸው። የመንግሥቱ ወራሾች ከሆኑት ቀሪዎች ጋር አንድ በመሆን የይሖዋን ስምና አምልኮ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። (ኢሳይያስ 2:2, 3፤ ሶፎንያስ 3:9) በተጨማሪም የሕይወት ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ስለሚያውቁ “አባት” ብለው ይጠሩታል። እንዲሁም በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ ባላቸው እምነት መሠረት በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ያገኛሉ። (ራእይ 7:9, 14) ይሁንና አሁንም ቢሆን ገና ፍጹማን ስላልሆኑ የአምላክ ልጆች በመሆን ሙሉ ተቀባይነት የሚያገኙት ወደፊት ነው።
9. ሮሜ 8:21 ለሰው ዘር ምን ተስፋ ይዟል?
9 እነዚህ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች፣ ሰብዓዊው ፍጥረት ‘ከመበስበስ ባርነት ነጻ የሚወጣበትን’ ጊዜ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። (ሮሜ 8:21) ይህ የነፃነት ጊዜ የሚጀምረው ክርስቶስና ሰማያዊ ሠራዊቱ ታላቁ መከራ በአርማጌዶን እንዲደመደም ካደረጉ በኋላ ነው። ይህም መላው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ተጠራርጎ ከጠፋ በኋላ ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ ሆኖ በሚገዛበት የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን በረከት እንደሚፈስ ያሳያል።—ራእይ 19:17-21፤ 20:6
10. የይሖዋ አገልጋዮች ምን የውዳሴ መዝሙር ይዘምራሉ?
10 በምድር ላይ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች “ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው። የዘመናት ንጉሥ ሆይ፤ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው። ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና። የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ” በማለት በደስታ የሚያውጁትን በሰማይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ስሜት በአንድነት የሚያስተጋቡበት ጊዜ ምንኛ አስደሳች ይሆናል! (ራእይ 15:3, 4) አዎን፣ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በእውነተኛው አንድ አምላክ አምልኮ አንድ ይሆናሉ። ሌላው ቀርቶ የሞቱ ሰዎች እንኳ ትንሣኤ አግኝተው ከሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ጋር በመሆን ይሖዋን የማወደስ አጋጣሚ ያገኛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 24:15
ወደፊት የሚገኝ አስደናቂ ነፃነት
11. ከታላቁ መከራ የሚተርፉ ሁሉ ምን አስደናቂ ነፃነት ያገኛሉ?
11 በአርማጌዶን የሚደመደመው ታላቁ መከራ ምድርን ከክፋት ካጸዳ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” መሆኑ ያከትማል። ከዚያ በኋላ የይሖዋ አምላኪዎች ሰይጣን ከሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ ጋር የሚያደርጉት ትግል ያበቃል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 20:1, 2) በዚያን ጊዜ የይሖዋን ስም የሚያሰድብም ሆነ ሰዎችን የሚከፋፍል የሐሰት ሃይማኖት አይኖርም። የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች በሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት የሚደርስባቸው ግፍና በደል ያከትማል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ነፃነት ነው!
12. ሰዎች ከኃጢአትና ከኃጢአት ውጤቶች የሚላቀቁት እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ “የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ስለሆነ በመሥዋዕቱ ዋጋ አማካኝነት የሰውን ዘር ኃጢአት ይደመስሳል። (ዮሐንስ 1:29) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአንድን ሰው ኃጢአት ይቅር ሲል በእርግጥ ይቅር እንዳለ ለማሳየት ሰውየውን ይፈውሰው ነበር። (ማቴዎስ 9:1-7፤ 15:30, 31) በተመሳሳይ ሁኔታ ክርስቶስ ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ማየት፣ መናገርና መስማት የተሳናቸውን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የአእምሮ ሕመም ያለባቸውንና በሌሎች በሽታዎች የሚሠቃዩትን ሁሉ በተአምራዊ መንገድ ይፈውሳል። (ራእይ 21:3, 4) ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ‘ከኀጢአት ሕግ’ ነፃ ስለሚሆኑ ሐሳባቸውና ድርጊታቸው እነሱንም ሆነ አምላክን የሚያስደስት ይሆናል። (ሮሜ 7:21-23) በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ስለሚደርሱ የእውነተኛውን አንድ አምላክ ‘መልክና አምሳል’ በትክክል ያንጸባርቃሉ።—ዘፍጥረት 1:26
13. ክርስቶስ በሺው ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል? ከምንስ ውጤት ጋር?
13 ክርስቶስ የሰውን ዘር ወደ ፍጽምና ደረጃ ካደረሰ በኋላ ይህን ሥራ ለማከናወን የተሰጠውን ሥልጣን ለአባቱ መልሶ ያስረክባል:- “ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።” (1 ቆሮንቶስ 15:24, 25) የመንግሥቱ የሺህ ዓመት አገዛዝ የታለመለትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ዳር ያደርሳል፤ ስለሆነም በይሖዋና በሰዎች መካከል ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ይህ መንግሥት ከዚያ በኋላ አያስፈልግም። በተጨማሪም ኃጢአትና ሞት ሙሉ በሙሉ ስለሚወገዱና የሰው ዘር ስለሚዋጅ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለመቤዠት ሲያከናውነው የቆየው አገልግሎት ያበቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል” ሲል ይገልጻል።—1 ቆሮንቶስ 15:28
14. ፍጹም የሆኑ ሰዎች ሁሉ ምን እንዲደርስባቸው ይደረጋል? ለምንስ?
14 ከዚህ በኋላ ፍጹም የሆኑት የሰው ልጆች ምርጫቸው እውነተኛውን አንድ አምላክ ለዘላለም ማገልገል እንደሆነ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። በመሆኑም ይሖዋ ፍጹም የሆኑትን የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ ልጆቹ አድርጎ ከመቀበሉ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈተኑ ያደርጋል። ሰይጣንና አጋንንቱ ከጥልቁ ይለቀቃሉ። ይህ ይሖዋን ከልብ በሚወዱ ላይ ዘላቂ ጉዳት አያስከትልም። ሆኖም በይሖዋ ላይ የሚያምጹ ሁሉ ከመጀመሪያው ዓመጸኛ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:7-10
15. የይሖዋ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፍጥረታት ሁሉ ዳግመኛ ምን የሚያደርጉበት ጊዜ ይመጣል?
15 ይሖዋ በመጨረሻው ፈተና ወቅት የእሱን ሉዓላዊነት የሚደግፉትን ፍጹማን ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባላት በመሆን የአምላክ ልጆች የሚያገኙትን አስደናቂ የሆነ ነፃነት በተሟላ ሁኔታ ይጎናጸፋሉ። በሰማይና በምድር ያሉት መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፍጥረታት ሁሉ ዳግመኛ እውነተኛውን አንድ አምላክ አንድ ሆነው ያመልካሉ። የይሖዋ ዓላማ በሚያስደንቅ ሁኔታ ግቡን ይመታል! የዚህ ደስተኛ፣ ዘላለማዊና ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባል መሆን ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ዮሐንስ 2:17 ላይ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንድታደርግ እናበረታታሃለን።
የክለሳ ውይይት
• የይሖዋ አምላኪዎች ሁሉ በኤደን ዓመጽ ከመፈጸሙ በፊት ከእሱ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና ነበራቸው?
• የአምላክ አገልጋዮች ምን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል?
• ወደፊት የአምላክ ልጆች የሚሆኑት እነማን ናቸው? ይህስ ይሖዋ የአምልኮ አንድነት እንዲኖር ለማድረግ ካለው ዓላማ ጋር ምን ግንኙነት አለው?
[በገጽ 190 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ምድር አቀፍ በሆነች ገነት ውስጥ ይኖራሉ