በጉ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲመራቸው የበቁ ሆነው ተቆጥረዋል
‘በጉ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል።’ —ራእይ 7:17
1. የአምላክ ቃል ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ምን በማለት ይጠራቸዋል? ኢየሱስ ምን ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል?
የአምላክ ቃል፣ በምድር ላይ ያሉትን የክርስቶስ ንብረቶች እንዲቆጣጠሩ የተሾሙትን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በማለት ይጠራዋል። ክርስቶስ በ1918 ‘ባሪያውን’ በመረመረበት ወቅት በምድር ላይ የነበሩት ቅቡዓን ‘በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡን’ ሥራ በታማኝነት ሲያከናውኑ አግኝቷቸዋል። በመሆኑም፣ ጌታው ማለትም ኢየሱስ ‘ባለው [ንብረት] ሁሉ ላይ’ ሾሟቸዋል። (ማቴዎስ 24:45-47ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) በዚህ መንገድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ውርሻቸውን ከማግኘታቸው በፊት በምድር ላይ ያሉትን የይሖዋን አምላኪዎች ያገለግላሉ።
2. የኢየሱስ ንብረቶች ምን እንደሆኑ ግለጽ።
2 አንድ ጌታ ንብረቱን ወይም የእሱ የሆነውን ሁሉ እንደፈቀደ ሊጠቀምበት ሥልጣን አለው። በይሖዋ የተሾመው ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረት፣ በምድር ላይ ያሉትን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ነገሮች በሙሉ ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የተመለከታቸውን ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ይጨምራል። ዮሐንስ ስለዚህ እጅግ ብዙ ሕዝብ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር።”—ራእይ 7:9
3, 4. እጅግ ብዙ ሕዝቦች ታላቅ መብት ያገኙት እንዴት ነው?
3 የዚህ እጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ሲል ከጠራቸው መካከል ናቸው። (ዮሐ. 10:16) ተስፋቸው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው። ኢየሱስ ‘ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ እንደሚመራቸውና አምላክ እንባን ሁሉ ከዐይናቸው እንደሚያብስ’ እርግጠኞች ናቸው። ይህንን ተስፋ ስለሚያደርጉ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል።’ (ራእይ 7:14, 17) በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው በአምላክ ዓይን ‘ነጭ ልብስ’ እንደለበሱ ተደርገው ተቆጥረዋል። ልክ እንደ አብርሃም፣ የአምላክ ወዳጆች በመሆን ጻድቅ ተደርገው ተቆጥረዋል።
4 ከዚህም በላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝቦች በአምላክ ዓይን ጻድቅ ተደርገው ስለተቆጠሩ፣ ይህ ሥርዓት በታላቁ መከራ በሚጠፋበት ወቅት በሕይወት እንደሚተርፉ ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ያዕ. 2:23-26) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚችሉ ሲሆን በቡድን ደረጃ ከአርማጌዶን የመትረፍ አስደሳች ተስፋም አላቸው። (ያዕ. 4:8፤ ራእይ 7:15) እንዲሁም በራሳቸው ከመመራት ይልቅ በሰማይ ባለው ንጉሥና በምድር ላይ ባሉት ቅቡዓን ወንድሞቹ አመራር ሥር ሆነው ለማገልገል ፈቃደኞች ናቸው።
5. የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የክርስቶስን ቅቡዓን ወንድሞች እየደገፏቸው ያሉት እንዴት ነው?
5 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሰይጣን ዓለም ከባድ ተቃውሞ ሲደርስባቸው የቆየ ሲሆን ይህ ሁኔታ ወደፊትም ይቀጥላል። ይሁንና የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሆኑት ወንድሞቻቸው ድጋፍ እንደሚሰጧቸው እርግጠኞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ቁጥር ግን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች እየጨመረ ይገኛል። ቅቡዓኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን ወደ 100,000 የሚጠጉ ጉባኤዎች በአካል ተገኝተው መምራት አይችሉም። ሌሎች በጎች ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የሚረዱበት አንዱ መንገድ፣ ከእጅግ ብዙ ሕዝቦች መካከል ብቃት ያላቸው ወንዶች የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ነው። እነዚህ የጉባኤ ሽማግሌዎች በዛሬው ጊዜ ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ በአደራ የተሰጡትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በመንከባከብ ቅቡዓኑን ይረዷቸዋል።
6. ሌሎች በጎች ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለሚያደርጉት ድጋፍ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነው?
6 ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ሌሎች በጎች ለቅቡዓን ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት ስለሚያደርጉት እርዳታ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ነቢዩ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ይሖዋ] እንዲህ ይላል፤ ‘የግብፅ ሀብትና [“በነጻ የሚሠሩ የግብፅ የጉልበት ሠራተኞችና፣” NW] የኢትዮጵያ ንግድ፣ ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ የአንተ ይሆናሉ፤ ከኋላ ይከተሉሃል።’” (ኢሳ. 45:14) በዛሬው ጊዜ፣ በምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች በመንፈስ የተቀባው የባሪያው ክፍልና የበላይ አካሉ የሚሰጡትን መመሪያ በመታዘዝ በምሳሌያዊ ሁኔታ ከኋላ ይከተሏቸዋል። እነዚህ ሰዎች ልክ ‘በነጻ እንደሚሠሩ የጉልበት ሠራተኞች፣’ ክርስቶስ በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ተከታዮቹ እንዲያከናውኑ ያዘዘውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ለመደገፍ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን በፈቃደኝነት ይሰጣሉ።—ሥራ 1:8፤ ራእይ 12:17
7. የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ወደፊት ለሚያገኙት ለየትኛው መብት እየሠለጠኑ ነው?
7 የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን በሚረዱበት ጊዜ ከአርማጌዶን በኋላ ለሚኖረው አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ መሠረት ለመሆን የሚያስችላቸውን ሥልጠና ያገኛሉ። ይህ መሠረት ጠንካራና የማይናወጥ መሆን አለበት፤ አባላቱም የጌታቸውን መመሪያ ለመፈጸም ፈቃደኞች ሊሆኑና ብቃት ሊኖራቸው ይገባል። እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ንጉሡ ክርስቶስ ኢየሱስ ሊጠቀምበት እንደሚችል የሚያስመሰክርበት አጋጣሚ እየተሰጠው ነው። በመሆኑም አሁን እምነትና ታማኝነት በማሳየት፣ ንጉሡ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ለሚሰጠው መመሪያ በፈቃደኝነት እንደሚገዛ ያሳያል።
የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እምነታቸውን አስመስክረዋል
8, 9. የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እምነታቸውን እያስመሰከሩ ያሉት እንዴት ነው?
8 ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ጎን የተሰለፉት ሌሎች በጎች እምነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ያስመሰክራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ቅቡዓኑን ይረዷቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በሁለተኛ ደረጃ፣ የበላይ አካሉ ለሚሰጠው አመራር በፈቃደኝነት ይገዛሉ።—ዕብ. 13:17፤ ዘካርያስ 8:23ን አንብብ።
9 በሦስተኛ ደረጃ፣ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው በመኖር ለቅቡዓኑ ድጋፍ መስጠታቸውን ያሳያሉ። እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ባሕርያት ለማፍራት ጥረት ያደርጋሉ። (ገላ. 5:22, 23) በዛሬው ጊዜ ‘የሥጋ ሥራን’ አስወግዶ እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ እምብዛም ተቀባይነት ላያስገኝ ይችላል። እንደዚያም ሆኖ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት “ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቊጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፤ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን [የመሰሉ]” ድርጊቶችን ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።—ገላ. 5:19-21
10. የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል?
10 ፍጹማን ስላልሆን የመንፈስ ፍሬን ማፍራት፣ ከሥጋ ሥራ መራቅ እንዲሁም የሰይጣን ዓለም የሚያደርስብንን ጫና መቋቋም ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ የግል ድክመታችን፣ ኢየሱስን ለመኮረጅ ስንጥር የሚያጋጥመን ጊዜያዊ እንቅፋት ወይም ያለብን የአቅም ውስንነት ተስፋ አስቆርጦን እምነታችን እንዲዳከም አሊያም ለይሖዋ ያለን ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ይሖዋ እጅግ ብዙ ሕዝቦችን ከታላቁ መከራ እንደሚያድናቸው የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ እናውቃለን።
11. ሰይጣን የክርስቲያኖችን እምነት ለማዳከም ምን ዓይነት ዘዴዎችን ይጠቀማል?
11 ቀንደኛው ጠላታችን፣ ዲያብሎስ መሆኑንና እሱም በቀላሉ ተስፋ እንደማይቆርጥ ስለምናውቅ ምንጊዜም ነቅተን እንኖራለን። (1 ጴጥሮስ 5:8ን አንብብ።) ዲያብሎስ የምንከተላቸው ትምህርቶች የተሳሳቱ ናቸው ብለን እንድናምን ለማድረግ ከሃዲዎችንና ሌሎችን ይጠቀማል። ይሁንና ይህ ዘዴው በአብዛኛው አይሳካለትም። በተመሳሳይም አንዳንድ ጊዜ ስደት የስብከቱን ሥራ በተወሰነ መጠን ቢያስተጓጉለውም፣ በአብዛኛው ግን ስደት እየደረሰባቸው ያሉትን ክርስቲያኖች እምነት አጠናክሯል። በመሆኑም ሰይጣን በብዛት የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች እምነታችንን በማዳከም ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆኑ አድርጎ የሚያስባቸውን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የተስፋ መቁረጥን ስሜት ይጠቀምበታል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች “ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን ዐስቡ” የሚል ምክር በተሰጣቸው ጊዜ እንዲህ ስላለው አደጋ ማስጠንቀቂያ እየተነገራቸው ነበር። ይህን ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈለገው ‘ዝለው ተስፋ እንዳይቈርጡ’ ለማሳሰብ ነበር።—ዕብ. 12:3
12. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ምክር ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች ብርታት የሚሰጣቸው እንዴት ነው?
12 የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቶህ ይሖዋን ማገልገልህን ለማቆም ያሰብክበት ጊዜ አለ? አልፎ አልፎ፣ ምንም እንደማትጠቅም ሆኖ ይሰማሃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ሰይጣን ይህን ስሜትህን ተጠቅሞ ይሖዋን ማገልገልህን እንድታቆም እንዲያደርግህ አትፍቀድ። ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ፣ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ እንዲሁም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ዘወትር መሰብሰብና መቀራረብ ያጠነክርሃል ብሎም ‘ዝለህ ተስፋ እንዳትቆርጥ’ ይረዳሃል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። የገባውን ቃል እንደሚፈጽምም እምነት አለን። (ኢሳይያስ 40:30, 31ን አንብብ።) በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመድ። ጊዜህን የሚያባክኑ ነገሮችን ትተህ ሌሎችን በመርዳት ላይ አተኩር። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚሰማህ ቢሆንም እንኳ ለመጽናት የሚያስችልህ ጥንካሬ ታገኛለህ።—ገላ. 6:1, 2
ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ዓለም መግባት
13. ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ምን ሥራ ይጠብቃቸዋል?
13 ከአርማጌዶን በኋላ ከሞት የሚነሱ በጣም ብዙ ኃጢአተኛ ሰዎች የይሖዋን መንገዶች መማር ያስፈልጋቸዋል። (ሥራ 24:15) እነዚህ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መማር ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ የኢየሱስ መሥዋዕት ከሚያስገኘው ጥቅም ለመካፈል በቤዛው ማመን እንዳለባቸው ሊማሩ ይገባል። በፊት ያምኑበት የነበረውን የሐሰት ሃይማኖት ትምህርትና የቀድሞ አኗኗራቸውን መተው ይኖርባቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ የሚያሳውቀውን አዲሱን ሰው መልበስ አለባቸው። (ኤፌ. 4:22-24፤ ቈላ. 3:9, 10) ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ሌሎች በጎች ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። አሁን ያለው ክፉ ዓለም የሚያሳድረው ጫና እንዲሁም ሐሳብን የሚሰርቁ ነገሮች ሳይኖሩ ለይሖዋ እንዲህ ያለውን አገልግሎት ማቅረብ ምንኛ አስደሳች ይሆናል!
14, 15. ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ሰዎችና ከሞት የሚነሱት ጻድቃን ተሞክሯቸውን የሚለዋወጡት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
14 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት የሞቱ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችም በዚያን ጊዜ ብዙ የሚማሩት ነገር ይኖራቸዋል። በጉጉት ሲጠባበቁት ስለነበረው ሆኖም ለማየት አጋጣሚ ስላላገኙት ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ማንነት ይማራሉ። እነዚህ ሰዎች በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ከይሖዋ ለመማር ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል የጻፋቸውን ሆኖም ትርጉማቸውን ያልተረዳቸውን ትንቢቶች ፍጻሜ ለራሱ ለነቢዩ ማብራራት እንዴት ያለ አስደሳች መብት እንደሆነ አስብ!—ዳን. 12:8, 9
15 ትንሣኤ የሚያገኙት ከእኛ የሚማሩት ብዙ ነገር እንደሚኖር እሙን ቢሆንም እኛም እነሱን የምንጠይቃቸው በርካታ ጥያቄዎች ይኖሩናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአጭሩ የተገለጹ ታሪኮችን በዝርዝር ሊነግሩን ይችላሉ። የኢየሱስ የአክስት ልጅ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሕይወት ዝርዝር ታሪኮችን ሲነግረን መስማት እንዴት አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ገምት! ከእነዚህ ታማኝ ምሥክሮች የምንሰማቸው ነገሮች የአምላክን ቃል ከአሁኑ ይበልጥ ለመረዳት እንደሚያስችለን ጥርጥር የለውም። በመጨረሻው ቀን የሞቱትን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ጨምሮ ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች “የተሻለውን ትንሣኤ” ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ማገልገል የጀመሩት ሰይጣን በሚገዛው ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም ይበልጥ ምቹ ሁኔታ በሚኖርበት በአዲሱ ዓለም አገልግሎታቸውን መቀጠል መቻላቸው በእርግጥም ታላቅ ደስታ ያመጣላቸዋል!—ዕብ. 11:35፤ 1 ዮሐ. 5:19
16. በትንቢት በተነገረው መሠረት የፍርድ ቀን ሂደት ምን ይመስላል?
16 በፍርድ ቀን ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ መጻሕፍት ይከፈታሉ። እነዚህ መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚያን ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመፍረድ መሠረት ይሆናሉ። (ራእይ 20:12, 13ን አንብብ።) በፍርድ ቀን መጨረሻ እያንዳንዱ ሰው በአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ ለተነሳው ክርክር ከየትኛው ወገን እንደቆመ ለማሳየት የሚያስችሉት በርካታ አጋጣሚዎች አግኝቷል። ታዲያ ለመንግሥቱ ዝግጅት ለመታዘዝና በጉ ‘ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ’ እንዲመራው ፈቃደኛ ይሆናል? ወይስ ለአምላክ መንግሥት ለመገዛት አሻፈረኝ ይላል? (ራእይ 7:17፤ ኢሳ. 65:20) በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ያሉ ሁሉ የኃጢአት ዝንባሌ ወይም ክፉ የሆነ ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ሳያሳድርባቸው የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ አጋጣሚ አግኝተዋል። በመሆኑም ይሖዋ በሚወስደው የመጨረሻ ፍርድ ትክክለኛነት ላይ ማንም ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም። ክፉዎች ብቻ ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:14, 15
17, 18. ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌሎች በጎች የፍርድ ቀንን በጉጉት የሚጠባበቁት እንዴት ነው?
17 በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንግሥትን ለመቀበል የበቁ ተደርገው ስለተቆጠሩ በፍርድ ቀን ለመግዛት በጉጉት ይጠባበቃሉ። እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ይጠብቃቸዋል! ይህ ተስፋ ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ወንድሞቻቸው የሰጠውን የሚከተለውን ምክር እንዲከተሉ ይገፋፋቸዋል:- “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ምክንያቱም እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም፤ በዚህም ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል።”—2 ጴጥ. 1:10, 11
18 ሌሎች በጎች ቅቡዓን ወንድሞቻቸው እንዲህ ያለ ተስፋ ስላላቸው ደስተኞች ናቸው። እነሱን ለመርዳትም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። የአምላክ ወዳጆች እንደመሆናቸው መጠን በይሖዋ አገልግሎት የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ተነሳስተዋል። በፍርድ ቀን ኢየሱስ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ሲመራቸው የአምላክን ዝግጅቶች በሙሉ ልባቸው ለመደገፍ ዝግጁ ናቸው። በመጨረሻም፣ ይሖዋን በምድር ላይ ለዘላለም ከሚያገለግሉት መካከል ለመሆን የበቁ ሆነው ይቆጠራሉ።—ሮሜ 8:20, 21፤ ራእይ 21:1-7
ታስታውሳለህ?
• የኢየሱስ ንብረቶች ምንን ያጠቃልላሉ?
• እጅግ ብዙ ሕዝቦች ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን የሚደግፉት እንዴት ነው?
• የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ምን ዓይነት መብት እንዲሁም ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
• የፍርድ ቀንን የምትመለከተው እንዴት ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትንሣኤ ከሚያገኙት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ምን ለመማር ትጓጓለህ?