ታስታውሳለህን?
በቅርቡ በወጡት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ ያሉትን ሐሳቦች በጥንቃቄ አስበህባቸዋልን? እንግዲያውስ የሚከተሉትን ሐሳቦች ማስታወስህ ትኩረት የሚስብ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ:-
◻ የወደፊቱ ዕጣ አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው መሠረተ ትምህርት ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው?
አምላክ አዳም ወደ ኃጢአት እንደሚወድቅ አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ ሰውን በፈጠረበት ጊዜ የኃጢአት ጠንሳሽ ከመሆኑም በላይ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው ክፋትና መከራ ሁሉ ተጠያቂ ይሆን ነበር። ይህ ይሖዋ ክፋትን የሚጠላ የፍቅር አምላክ ነው ከሚለው ሐቅ ጋር ሊጣጣም አይችልም። (መዝሙር 33:5፤ ምሳሌ 15:9፤ 1 ዮሐንስ 4:8)—4/15, ገጽ 7, 8
◻ በኢሳይያስ 2:2–4 ፍጻሜ መሠረት ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ምን በማድረግ ላይ ናቸው?
ወደ ይሖዋ የአምልኮ ቤት እየጎረፉ ሲመጡ የሰላም ጠላቶችን ለመደምሰስ በተጠንቀቅ የቆመው የአምላክ ሰማያዊ ሠራዊት ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ስለሚተማመኑ ‘ጦርነትን ከመማር’ ይታቀባሉ።—4/15፣ ገጽ 30
◻ በኢዩኤል 3:10, 11 ላይ የአምላክ ኃያላን የተባሉት እነማን ናቸው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛው አምላክ 280 ጊዜ ያህል ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ’ ተብሎ ተጠርቷል። (2 ነገሥት 3:14) ይህ ሠራዊት የይሖዋን ትእዛዝ ለመፈጸም በተጠንቀቅ የሚጠባበቀው የሰማይ መላእክት ጭፍራ ነው።—5/1፣ ገጽ 23
◻ ኢዮብ እሱን በመቃወም ኃጢአት ለሠሩት አጽናኞች እንዲጸልይላቸው ይሖዋ መጠየቁ ለእኛ ምን ትምህርት ይዟል? (ኢዮብ 42:8)
ኢዮብ እሱን በመቃወም ኃጢአት ለሠሩት አጽናኞች እንዲጸልይላቸው ይሖዋ የጠየቀው ገና ጤንነቱ ሳይመለስለት በፊት ነው። ይህ ሁኔታ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲልልን እኛ በቅድሚያ የበደሉንን ይቅር እንድንል እንደሚጠብቅብን ያሳያል። (ማቴዎስ 6:12፤ ኤፌሶን 4:32)—5/1፣ ገጽ 31
◻ ያዕቆብ “ትዕግሥትም [“ጽናትም፣” NW] . . . ሥራውን ይፈጽም” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (ያዕቆብ 1:4)
ጽናት አንድ የሚያከናውነው ተግባር ማለትም “ሥራ” አለው። ሥራው በሁሉም አቅጣጫ እኛን ምሉዓን ማድረግ ነው። ስለዚህ የሚደርሱብንን ፈተናዎች እስከ መጨረሻው እንዲቀጥሉ ከፈቀድንና ቶሎ ለመገላገል ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ዘዴዎችን ተጠቅመን በአጭሩ ካልቀጨናቸው እምነታችን የተፈተነና የተጣራ ይሆናል።—5/15፣ ገጽ 16
◻ አምላክ ለሰው ልጆች ችግር እልባት ሳያደርግ ይህን ያህል ረጅም ዘመን የቆየው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከእኛ ይለያል። ለዘላለማዊ አምላክ አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያለው ጊዜ ሳምንት እንኳን አይሞላም። (2 ጴጥሮስ 3:8) ይሁን እንጂ ስለ ጊዜ ያለን አመለካከት ምንም ይሁን ምን እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት ቀን ይበልጥ ያቀርበናል።—6/1፣ ገጽ 5, 6
◻ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲሰብኩ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?
የይሖዋ ትምህርት እርስ በርስ መፋቀርን እንዲሁም ጎረቤታቸውን እንደ ራሳቸው መውደድን የተማሩ ልዩ ሕዝቦች አፍርቷል። (ኢሳይያስ 54:13) ሰዎች ለመልእክታቸው ግዴለሽ ቢሆኑም ወይም ስደት ቢደርስባቸውም የይሖዋ ምሥክሮች መስበካቸውን እንዲቀጥሉ የሚገፋፋቸው ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:36–40፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1–8)—6/15፣ ገጽ 20
◻ ኢየሱስ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ” ሲል የተናገራቸው ቃላት ምን ያመለክታሉ? (ሉቃስ 13:24)
የኢየሱስ ቃላት የሚያመለክቱት መታገልንና አቅም የፈቀደውን ሁሉ ማድረግን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የእርሱ ቃላት አንዳንዶች በሚመቻቸው ጊዜ ወይም እነርሱ በሚመርጡት በተዝናናና ቀላል በሆነ አካሄድ ‘በበሩ ለመግባት’ እንደሚፈልጉ ያመለክታሉ። ስለዚህ እያንዳንዳችን ‘በትጋትና በታታሪነት እየጣርኩ ነውን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።—6/15፣ ገጽ 31
◻ ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ‘በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድ የሚቀበሉት’ እንዴት ነው? (ራእይ 20:12)
እነዚህ መጻሕፍት ቀደም ሲል የሠሯቸውን ሥራዎች ዘግበው የያዙ መዝገቦች አይደሉም፤ በሞቱበት ጊዜ በሕይወት ዘመናቸው ከፈጸሟቸው ኃጢአቶች ነፃ ወጥተዋል። (ሮሜ 6:7, 23) ይሁን እንጂ ከሞት ከተነሱ በኋላም በአዳማዊ ኃጢአት ሥር ይሆናሉ። እንግዲያው እነዚህ መጻሕፍት ከኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን እንዲችሉ ሊከተሏቸው የሚገቡትን መለኮታዊ መመሪያዎች የያዙ መሆን አለባቸው።—7/1፣ ገጽ 22
◻ ኢየሱስ መልካም ባልንጀራ ስለሆነው ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ ለእኛ የሚሆኑ ምን ትምህርቶች ይዟል? (ሉቃስ 10:30–37)
ትክክል የሆነውን ነገር ከልቡ የሚሠራ ሰው የአምላክን ሕግ መታዘዝ ብቻ ሳይሆን ባሕርያቱንም መኮረጅ እንዳለበት የኢየሱስ ምሳሌ ያሳያል። (ኤፌሶን 5:1) ከዚህም በተጨማሪ ለሰዎች የምናሳየው ወዳጃዊ ስሜት ብሔራዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ድንበሮችን አልፎ መሄድ እንዳለበትም ያሳያል። (ገላትያ 6:10)—7/1፣ ገጽ 31
◻ ልጆቻችሁን ማወቅና ወላጃዊ መመሪያ መስጠት የምትችሉባቸው ሦስት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?
(1) ልጆቻችሁ ተገቢ የሆነ የሥራ ዓይነት እንዲመርጡ እርዷቸው፤ (2) በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ የሚገጥሟቸውን የስሜት ውጥረቶች እንዲቋቋሙ አዘጋጁአቸው፤ (3) የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች እንዴት ሊያሟሉ እንደሚችሉ አሳዩዋቸው።—7/15፣ ገጽ 4
◻ አምላክ “በሰባተኛው ቀን” ያረፈው ለምን ዓላማ ነበር? (ዘፍጥረት 2:1–3)
አምላክ ያረፈው ስለደከመው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ምድራዊ የፍጥረት ሥራውን ያቆመው የእጁ ሥራዎች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱና ወደ ሙሉ ክብር እንዲመጡ ሲል ነው። ይህ ደግሞ ለእሱ ውዳሴና ክብር ያመጣለታል።—7/15፣ ገጽ 18
◻ ፍትሕ ልናሳይ የምንችልባቸው ሦስት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ ከአምላክ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ጋር መስማማት አለብን። (ኢሳይያስ 1:17) በሁለተኛ ደረጃ ይሖዋ እኛን እንዲይዘን በምንፈልግበት መንገድ ሌሎችን የምንይዝ ከሆነ ፍትሕን እናሳያለን። (መዝሙር 130:3, 4) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ስንካፈል አምላካዊ ፍትሕ እናሳያለን። (ምሳሌ 3:27)—8/1፣ ገጽ 14, 15