ምዕራፍ 8
ድል አድራጊ ለመሆን መጣጣር
ሰምርኔስ
1. (ሀ) ክብር ከተቀዳጀው ኢየሱስ መልእክት የተቀበለው ሁለተኛ ጉባኤ የትኛው ነበር? (ለ) ኢየሱስ ራሱን “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” ብሎ በመጥራቱ በዚያ ጉባኤ የነበሩትን ክርስቲያኖች ስለምን ነገር አሳስቦአቸው ነበር?
በዛሬው ጊዜ የጥንትዋ የኤፌሶን ከተማ ፈራርሳለች። ኢየሱስ ሁለተኛ መልእክቱን የላከባት ከተማ ግን አሁንም የደራች ከተማ ነች። የኤፌሶን ፍርስራሽ ከሚገኝበት ሥፍራ በስተሰሜን በኩል 56 ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ ኢዝሚር የምትባለው የቱርክ ከተማ ትገኛለች። በዚህች ከተማ ዛሬም እንኳን ቢሆን ቀናተኛ የሆኑ አራት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ። ሰምርኔስ በአንደኛው መቶ ዘመን ትገኝ የነበረው በዚህ ሥፍራ ነበር። አሁን ኢየሱስ ቀጥሎ የሚናገረውን እናስተውል:- “በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል።” (ራእይ 2:8) ኢየሱስ በሰምርኔስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ይህን ቃል ሲነግራቸው ይሖዋ ራሱ በቀጥታ ከሙታን አስነስቶ የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት የሰጠው የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው ሰው እርሱ መሆኑን ማስገንዘቡ ነበር። የቀሩትን ቅቡዓን በሙሉ ከሙታን የሚያስነሳው ኢየሱስ ነው። ስለዚህ ከእርሱ ጋር በማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት የመካፈል ተስፋ ላላቸው ወንድሞቹ ምክር ለመስጠት የሚያስችል ብቃት አለው ማለት ነው።
2. ሁሉም ክርስቲያኖች “ሞቶ የነበረውና ሕያው የሆነው” በተናገረው ቃል የሚጽናኑት ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ስለ ጽድቅ ተሰድዶ የመጽናትን መንገድ አሳይቶናል። ለዚህም አድራጎቱ የሚገባውን ሽልማት አግኝቶበታል። የክርስቲያኖች ሁሉ ተስፋ የተመሠረተው ኢየሱስ በታማኝነት በመሞቱና በኋላም ከሙታን በመነሳቱ ላይ ነው። (ሥራ 17:31) ኢየሱስ “ሞቶ የነበረና ሕያውም የሆነ” መሆኑ ለእውነት ሲባል የምንቀበለው ማንኛውም ዓይነት መከራ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር ያረጋግጣል። የኢየሱስ ትንሣኤ ለክርስቲያኖች ሁሉ በተለይም ለእምነታቸው ሲሉ መከራ ለመቀበል በሚገደዱበት ጊዜ ብርቱ ማጽናኛ ይሆናቸዋል። አንተስ እንደዚህ ባለው ሁኔታ ሥር የምትገኝ ነህን? ከሆንክ ኢየሱስ ለሰምርኔስ ጉባኤ የተናገረው የሚከተለው ቃል በጣም ያበረታታል።
3. (ሀ) ኢየሱስ ለሰምርኔስ ክርስቲያኖች ምን ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር? (ለ) በሰምርኔስ የነበሩት ክርስቲያኖች ድሆች ቢሆኑም “ባለ ጠጎች” እንደሆኑ ኢየሱስ የተናገረው ለምን ነበር?
3 “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፣ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማህበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ:- አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።” (ራእይ 2:9) ኢየሱስ በሰምርኔስ የነበሩትን ወንድሞቹን ሞቅ ባለ ሰሜት ከማመስገን በስተቀር የሚወቅስበት ምክንያት አልነበረውም። በእምነታቸው ምክንያት ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። በታማኝነታቸው ምክንያት ይመስላል፣ ቁሳዊ ሀብት አልነበራቸውም። (ዕብራውያን 10:34) ይሁን እንጂ ዋናው ጭንቀታቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ነበር። ኢየሱስ እንደመከረው በሰማይ መዝገብ አከማችተዋል። (ማቴዎስ 6:19, 20) በዚህም ምክንያት ዋነኛው እረኛ “ባለ ጠጋ” እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ከያዕቆብ 2:5 ጋር አወዳድር።
4. በሰምርኔስ የነበሩት ክርስቲያኖች ከፍተኛ ተቃውሞ የደረሰባቸው ከእነማን ነበር? ኢየሱስ እነዚህን ተቃዋሚዎች እንዴት ይመለከታቸው ነበር?
4 ኢየሱስ የሰምርኔስ ክርስቲያኖች በተለይ ከሥጋውያን አይሁዶች ብዙ ተቃውሞ እንደ ደረሰባቸው ተናግሮአል። በቀደሙት ዘመናት ብዙዎቹ የዚህ ሃይማኖት አባሎች የክርስትናን መስፋፋት ተቃውመው ነበር። (ሥራ 13:44, 45፤ 14:19) አሁን ደግሞ ኢየሩሳሌም ከወደመች ከጥቂት ዓመታት በኋላ በሰምርኔስ የነበሩት አይሁዶች ይህንኑ ሰይጣናዊ መንፈስ አሳይተዋል። ኢየሱስ “የሰይጣን ማህበር ናቸው” ማለቱ አያስደንቅም።a
5. በሰምርኔስ የነበሩት ክርስቲያኖች ከፊታቸው እንዴት ያለ ፈተና ይጠብቃቸው ነበር?
5 በሰምርኔስ የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥላቻ ይደርስባቸው ስለነበረ የሚከተለው የኢየሱስ ቃል አጽናንቶአቸው ነበር:- “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፣ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወህኒ ሊያገባችሁ አለው፣ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ደረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” (ራእይ 2:10) እዚህ ላይ ኢየሱስ በግሪክኛ ቋንቋ “እናንተ” የሚለውን ተውላጠ ስም ሦስት ጊዜ ተጠቅሞአል። ይህም የተናገረው ቃል መላውን ጉባኤ የሚመለከት መሆኑን ያሳያል። ኢየሱስ በሰምርኔስ በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረው ፈተና ቶሎ እንደሚያቆም ቃል ሊገባላቸው አልቻለም። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ይሰደዳሉ፣ ወደ ወህኒም ይገባሉ። “ለአሥር ቀን” መከራ ይቀበላሉ። አሥር ምድራዊ ሙላትን ወይም አጠቃላይነትን የሚያመለክት ቃል ነው። እነዚህ በመንፈሳዊ ባለጠጎች የነበሩት ፍጹም አቋም ጠባቂዎች እንኳን በሥጋ በነበሩበት ጊዜ በጣም ከባድ ፈተና እንደሚደርስባቸው ተገለጸ።
6. (ሀ) የሰምርኔስ ክርስቲያኖች መፍራት የማይገባቸው ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ በሰምርኔስ ለነበረው ጉባኤ የላከውን መልእክት የደመደመው እንዴት ነበር?
6 ይሁን እንጂ በሰምርኔስ የነበሩት ክርስቲያኖች መፍራት ወይም አቋማቸውን ማላላት አልነበረባቸውም። እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከጸኑ “የሕይወት አክሊል” ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል። ለእነርሱም የሚሰጠው ሽልማት የማይጠፋ የዘላለም ሰማያዊ ሕይወት ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:25፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:6-8) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሽልማት ለማግኘት ሌላውን ነገር ሁሉ፣ ምድራዊ ሕይወቱን ጭምር መስዋዕት ማድረግ እንደሚገባው ቆጥሮ ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:8) በሰምርኔስ የነበሩትም ክርስቲያኖች እንደዚህ ይሰማቸው እንደነበረ ግልጽ ነው። ኢየሱስ “መንፈስ ለአብያተ ክርስያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጎዳም” በማለት መልእክቱን ይደመድማል። (ራእይ 2:11) ድል አድራጊዎቹ ሞት የማይነካው ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚሰጣቸው ተረጋግጦላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:53, 54
“አሥር ቀንም መከራ”
7, 8. ዘመናዊው የክርስቲያን ጉባኤ በሰምርኔስ እንደነበረው ጉባኤ በ1918 የተፈተነው እንዴት ነበር?
7 የዘመናችን የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ባልንጀሮቻቸውም እንደ ሰምርኔስ ክርስቲያኖች ሲፈተኑ ቆይተዋል፣ ወደፊትም ይፈተናሉ። በደረሰባቸው ፈተና ሁሉ በታማኝነት መጽናታቸው የአምላክ ሕዝቦች መሆናቸውን አረጋግጦላቸዋል። (ማርቆስ 13:9, 10) የጌታ ቀን ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በሰምርኔስ ለነበሩት ክርስቲያኖች የተናገረው ቃል በጣም ጥቂት የነበሩትን የይሖዋ ሕዝቦች ዓለም አቀፍ ቡድን በጣም አጽናንቶት ነበር። (ራእይ 1:10) እነዚህ የአምላክ ሕዝቦች ከ1879 ጀምሮ ከአምላክ ቃል መንፈሳዊ ሀብቶችን ሲቆፍሩ ቆይተዋል። ይህንንም ሀብት ለሌሎች ሰዎች በነፃ ሲያካፍሉ ቆይተዋል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ግን በጣም የጠነከረ ጥላቻና ተቃውሞ ደረሰባቸው። ይህም የሆነባቸው በከፊል በጦርነት ስሜት ስላልተቃጠሉ ሲሆን በከፊል ደግሞ የሕዝበ ክርስትናን ስህተቶች በድፍረት ያጋልጡ ስለነበረ ነው። በአንዳንዶቹ የሕዝበ ክርስትና መሪዎች አነሳሽነት ይደርስባቸው የነበረው ስደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በ1918 ነበር። ይህም የሆነው የሰምርኔስ ክርስቲያኖች በዚያ ይኖር ከነበረው የአይሁዳውያን ማህበረሰብ የደረሰባቸውን የመሰለ ሁኔታ በደረሰባቸው ጊዜ ነው።
8 በዩናይትድ ስቴትስ ተቀጣጥሎ የነበረው ስደት አዲሱ የመጠበቂያ ግንብ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ እና ሰባት ተባባሪዎቹ ሰኔ 22 ቀን 1918 አብዛኞቹ የ20 ዓመት እሥራት ተፈርዶባቸው ወደ ወህኒ በወረዱ ጊዜ በዩናይትድ ስቴት የተጀመረው ስደት የመጨረሻውን ከፍተኛ ደረጃ ያዘ። ከዘጠኝ ወር በኋላም በዋስ ተለቀቁ። ግንቦት 14 ቀን 1919 ደግሞ ይግባኛቸውን ያዳመጠው ፍርድ ቤት የቀድሞው ፍርድ ቤት በችሎቱ ላይ 130 ስህተቶች እንደ ፈጸመ ተረድቶ ፍርዱን ሻረው። በ1918 ለእነዚህ ክርስቲያኖች የዋስ መብት የነፈጉት የሮማ ካቶሊክ አማኝና የታላቁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ኒሻን ተሸላሚ የሆኑት ዳኛ ማንተን በ1939 በስድስት ጉቦ የመቀበልና የማጭበርበር ወንጀል ተከስሰው የሁለት ዓመት እሥራትና የ10, 000 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ተፈርዶባቸዋል።
9. በጀርመን አገር በናዚ ግዛት ሥር የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሂትለር ምን ዓይነት ግፍ ተፈጽሞባቸው ነበር? ቀሳውስቱስ ምን አድርገው ነበር?
9 በጀርመን አገር በናዚዎች የግዛት ዘመን ሂትለር የይሖዋ ምሥክሮችን የስብከት ሥራ ሙሉ በሙሉ አግዶ ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በማጎሪያ ካምፖችና በወህኒ ቤቶች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በግፍ እንዲቆዩ ሲደረግ ብዙዎቹ እዚያው እንዳሉ ሞተዋል። ሁለት መቶ የሚያህሉ ወጣቶች በሂትለር ጦር ሠራዊት ውስጥ ገብተው ለመዋጋት እምቢተኞች በመሆናቸው ተገድለዋል። ይህን ሁሉ ድርጊት ቀሳውስት የደገፉት መሆኑን ዘ ጀርመን ዌይ በተባለው ጋዜጣ በግንቦት 29, 1938 እትም ላይ አንድ የካቶሊክ ቄስ ከጻፉት መረዳት ይቻላል። በከፊል እንዲህ ብለው ነበር:- “በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚባሉት [የይሖዋ ምሥክሮች] የተከለከሉበት አገር አንድ ብቻ ነው። ይህም አገር ጀርመን ነው። . . . አዶልፍ ሂትለር ሥልጣን በያዘበትና የጀርመን ካቶሊክ ኤጲስ ቆጶሳት ድጋሚ ጥያቄ ባቀረቡለት ጊዜ ሂትለር እንዲህ ብሎ ነበር:- ‘እነዚህ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነን ባዮች [የይሖዋ ምሥክሮች] ችግር ፈጣሪዎች ናቸው። . . . እንደ አስመሳዮች እቆጥራቸዋለሁ። የጀርመን ካቶሊኮች በዚህ ራዘርፎርድ በሚባል አሜሪካዊ ዳኛ እንዲህ ባለ ሁኔታ እንዲበከሉ አልፈቅድም። በጀርመን አገር ውስጥ [የይሖዋ ምሥክሮችን] አጠፋለሁ።’” ቄሱ በዚህ የሂትለር አነጋገር ላይ “ብራቮ!” (ጐበዝ!) የሚል ቃል ጨምረዋል።
10. (ሀ) የጌታ ቀን ወደ ፊት በገፋ መጠን የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ስደት ደርሶባቸዋል? (ለ) ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ነፃነት ለማግኘት በተሟገቱባቸው ፍርድ ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ እንዴት ያለ ውጤት አግኝተዋል?
10 የጌታ ቀን ወደ ፊት እየገፋ በሄደ መጠን እባቡና የእባቡ ዘር ቅቡዓን ክርስቲያኖችንና ባልንጀሮቻቸውን መዋጋታቸውን አላቆሙም። ከእነኚህም መካከል ብዙዎቹ ታስረዋል፣ ከባድም ስደት ደርሶባቸዋል። (ራእይ 12:17) እነዚህ ጠላቶች በሕግ ስም ተንኮል መሥራታቸውን አልተውም። የይሖዋ ሕዝቦች ግን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል። (መዝሙር 94:20፤ ሥራ 5:29) በ1954 መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ሪፖርት አቅርቦ ነበር። “ባለፉት አርባ ዓመታት ከሰባ የሚበልጡ አገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የእገዳ አዋጅ አውጀውባቸው ወይም አሳደዋቸው ነበር።” እነዚህ ክርስቲያኖች የሚቻል ሆኖ ባገኙባቸው አገሮች ሁሉ የሃይማኖት ነፃነታቸውን ለማስከበር በፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። በተለያዩ አገሮችም አስደናቂ ድል አግኝተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች 50 ክሶችን ረትተዋል።
11. በጌታ ቀን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፈጸመው ኢየሱስ ስለመገኘቱ የተናገረው የትኛው ትንቢት ነው?
11 የቄሣርን ለቄሣር ስለመስጠት ኢየሱስ የሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸም ረገድ የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል ትጋት ያሳየ የሃይማኖት ክፍል አይገኝም። (ሉቃስ 20:25፤ ሮሜ 13:1, 7) ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል በተለያዩ ዓይነት የመንግሥት አስተዳደሮችና በብዙ የተለያዩ አገሮች አባሎቹ የታሰሩበት የሃይማኖት ክፍል የለም። እስከ አሁን ድረስ እንኳን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በእስያ አገሮች ይታሰራሉ። ኢየሱስ መገኘቱን ስለሚያመለክተው ምልክት በተናገረው ታላቅ ትንቢት ውስጥ የሚከተሉትን ቃላት አክሎ ነበር። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።” (ማቴዎስ 24:3, 9) ይህ ትንቢት በእርግጥም በጌታ ቀን በሚኖሩት ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተፈጽሞአል።
12. የዮሐንስ ክፍል የአምላክ ሕዝቦች ስደት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲኖራቸው ያደረገው እንዴት ነው?
12 የዮሐንስ ክፍል የአምላክ ሕዝቦች የሚደርስባቸውን መከራ ጠንክረው እንዲቋቋሙ ለማበርታት ኢየሱስ ለሰምርኔስ ጉባኤ የተናገረውን ቃል ፍሬ ሐሳብ አለማቋረጥ ሲያስገነዝብ ኖሮአል። ለምሳሌ ያህል የናዚዎች ስደት በጀመረበት ጊዜ በ1933 እና በ1934 የወጣው መጠበቂያ ግንብ ማቴዎስ 10:26-33ን የሚያብራራውን “አትፍሩአቸው”፣ በዳንኤል 3:17, 18 ላይ የተመሠረተውን “የማቅለጫው ሸክላ” እና ዳንኤል 6:22ን ቁልፍ ጥቅስ ያደረገውን “የአንበሶቹ አፍ” የሚሉትንና ሌሎች ተመሳሳይ ርዕሰ ትምህርቶችን አውጥቶ ነበር። ይህ መጽሐፍ መጀመሪያ በተዘጋጀባቸው በ1980ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ከ40 በሚበልጡ አገሮች ከባድ ስደት ሲደርስባቸው መጠበቂያ ግንብ “ስደት ቢደርስም ደስተኛ መሆን” እና “ክርስቲያኖች ስደትን በጽናት ይቋቋማሉ” እንደሚሉት ባሉ ርዕሰ ትምህርቶች የአምላክን ሕዝቦች አጠናክሮአቸው ነበር።b
13. የሰምርኔስ ክርስቲያኖች ስደትን እንዳልፈሩት ሁሉ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮችም ያልፈሩት ለምንድን ነው?
13 በእውነትም ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች በምሳሌያዊ አሥር ቀናት አካላዊ ስደትና ሌላ ዓይነት ፈተና ሲደርስባቸው ቆይቶአል። በሰምርኔስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች በፍርሐት አልተዋጡም። ማናችንም ብንሆን በምድር ላይ የሚታየው ችግር እየተባባሰ ሲሄድ መፍራት አይገባንም። በመከራ ሁሉ ለመጽናትና ‘የንብረታችንን ዝርፊያ’ በደስታ ለመቀበል ፈቃደኞች ነን። (ዕብራውያን 10:32-34) የአምላክን ቃል በማጥናትና ከራሳችን ጋር እንዲዋሃድ በማድረግ በእምነት ጸንተን ለመቆም እንችላለን። ፍጹም አቋማችሁን ጠብቃችሁ ለመገኘት በምታደርጉት ጥረት ይሖዋ ሊጠብቃችሁ እንደሚችልና ሊጠብቃችሁም ፈቃደኛ እንደሆነ እርግጠኞች ሁኑ። “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:6-11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዮሐንስ ከሞተ ከ60 ዓመታት ያህል ጊዜ በኋላ የ86 ዓመት ሽማግሌ የነበረው ፖሊካርፕ በኢየሱስ ላይ የነበረውን እምነት ለመካድ አሻፈረኝ በማለቱ በሰምርኔስ ከተማ በእሳት ተቃጥሎ ተገድሎአል። ይህ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ የተጻፈ ነው የሚባለው የፖሊካርፕ ሰማዕትነት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ፖሊካርፕ የተቃጠለበት እንጨት በሚሰበሰብበት ጊዜ “አይሁዳውያን እንደልማዳቸው በታላቅ ቅንዓት እንጨት በመሰብሰብ ሥራ ተካፍለው ነበር።” ፖሊካርፕ የተገደለው “በትልቁ የሰንበት ቀን” መሆኑ እንኳን በዚህ ሥራ እንዳይካፈሉ አላገዳቸውም።
b ህዳር 1, 1933፤ ጥቅምት 1 እና 15፣ ታህሣሥ 1 እና 15, 1934 እንዲሁም ግንቦት 1, 1983 መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።
[በገጽ 39 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለበርካታ ዓመታት ታሪክ ጸሐፊዎች በጀርመን አገር ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ስለነበራቸው ፍጹም አቋም የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ክላውዲያ ኩንዝ የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ በ1986 በታተመው እናቶች በአባት አገር ውስጥ በተባለው መጽሐፋቸው የሚከተለውን ብለዋል። “ከናዚዎች ጋር ህብረት ያልነበራቸው በጣም ብዙ ጀርመኖች ከሚጠሉት መንግሥት ጋር ተመሳስለው ለመኖር ችለው ነበር። . . . በሌላው አንጻር የተሰለፉትን የርዕዮተ ዓለም ክፍሎች ስንመለከት ደግሞ 20, 000 የሚያክሉትን የይሖዋ ምሥክሮች እናገኛለን። ለናዚ መንግሥት በማናቸውም መንገድ ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆነ አንድ ሰው እንኳን ከመካከላቸው አልተገኘም። . . . በጣም ጠንካራና የጸና ተቃውሞ ያጋጠመው ከሃይማኖታውያን ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ከመጀመሪያው ጀምሮ ከማንኛውም የናዚ መንግሥት ክፍል ጋር አልተባበሩም። ጌስታፖዎች በ1933 ብሔራዊ ጽሕፈት ቤታቸውን ካጠፉባቸውና በ1935 ሥራቸውን ካገዱባቸው በኋላ እንኳን ‘ሄይል ሂትለር’ ለማለት እንኳን እምቢተኞች እስከመሆን ድረስ አልተባበሩአቸውም ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት (አብዛኞቹ ወንዶች ነበሩ) ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተልከው ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ ተገድለዋል። ከ1933 እስከ 1945 ደግሞ ሌሎች አንድ ሺህ የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች ተገድለዋል። . . . ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ግን ቄሶቻቸው ከሂትለር ጋር እንዲተባበሩ የሚሰጡአቸውን ምክር ያዳምጡ ነበር። የተቃወሙ እንኳን ቢኖሩ የተቃወሙት የቤተ ክርስቲያናቸውንም ሆነ የመንግሥቱን ትዕዛዝ ተጋፍተው ነበር።”