ምዕራፍ 12
“ያለህን አጽንተህ ያዝ”
ፊልድልፍያ
1. የኢየሱስ ስድስተኛ መልእክት የተላከው በየትኛው ከተማ ይኖር ለነበረ ጉባኤ ነው? የዚህስ ከተማ ስም ትርጉሙ ምንድን ነው?
የወንድማማች መዋደድ፣ በጣም ተፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። ኢየሱስ በፊልድልፍያ ለነበረው ጉባኤ የላከውን ስድስተኛ መልእክቱን በተናገረ ጊዜ ይህን ቁምነገር በአእምሮው ይዞ ነበር። ፊልድልፍያ ማለት “የወንድማማች መዋደድ” ማለት ነው። አረጋዊው ዮሐንስ ከ60 ዓመታት በፊት ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚወደው ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ባረጋገጠበት ጊዜ የሆነውን አልዘነጋም። (ዮሐንስ 21:15-17) በፊልድልፍያ የነበሩትስ ክርስቲያኖች የወንድማማች ፍቅር ነበራቸውን? እንደነበራቸው ግልጽ ነው።
2. ፊልድልፍያ እንዴት ያለች ከተማ ነበረች? በዚያችስ ከተማ እንዴት ያለ ጉባኤ ይገኝ ነበር? ኢየሱስ ለዚህ ጉባኤ መልአክ ምን ተናገረ?
2 ከሰርዴስ ደቡባዊ ምሥራቅ 48 ኪሎ ሜትር ርቃ (አላሴሂር የምትባለው ዘመናዊ የቱርክ ከተማ ባለችበት ቦታ) ትገኝ የነበረችው ፊልድልፍያ በዮሐንስ ዘመን መጠነኛ ብልጽግና የነበራት ከተማ ነበረች። ከዚህ ይበልጥ ሊተኮርበት የሚገባው ግን በዚያ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ብልጽግና ነው። በሰርዴስ በኩል አድርጎ ሊጠይቃቸው የመጣውን አገልጋይ እንዴት ባለ ደስታ ተቀብለውት ይሆን! ይዞላቸው የመጣው መልእክት በጣም የሚቀሰቅሳቸው ምክር ነበር። በመጀመሪያ ግን የመልእክቱ ላኪ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን ይገልጻል። እንዲህ ይላል:- “በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- የዳዊት መክፈቻ ያለው የሚከፍት፣ የሚዘጋም የሌለ የሚዘጋ፣ የሚከፍትም የሌለ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል።”—ራእይ 3:7
3. ኢየሱስ “ቅዱስ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? “እውነተኛ” ሊባል የሚችለውስ ለምንድን ነው?
3 ጴጥሮስ ሰው ለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፣ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምነናል” ሲል ዮሐንስ ሰምቶ ነበር። (ዮሐንስ 6:68, 69) ይሖዋ ሁለመናው “ቅዱስ” ስለሆነ አንድያ ልጁም ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። (ራእይ 4:8) በተጨማሪም ኢየሱስ “እውነተኛ” ነው። እዚህ ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል (አሌቲኖስ) ሐቀኝነትን ወይም እውነተኛነትን ያመለክታል። በዚህ መሠረት ኢየሱስ እውነተኛ ብርሃን፣ ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ ነው። (ዮሐንስ 1:9፤ 6:32) እውነተኛውም የወይን ግንድ እርሱ ነው። (ዮሐንስ 15:1) በተጨማሪም ኢየሱስ ታማኝ ስለሆነ እውነተኛ ነው። ሁልጊዜ የሚናገረው እውነት ነው። (ዮሐንስ 8:14, 17, 26 ተመልከት።) በእርግጥም ይህ የአምላክ ልጅ ንጉሥና ፈራጅ ሆኖ ለማገልገል ሙሉ ብቃት አለው።—ራእይ 19:11, 16
“የዳዊት መክፈቻ”
4, 5. “የዳዊት መክፈቻ” ከየትኛው ቃል ኪዳን ጋር የተዛመደ ነው?
4 ኢየሱስ “የዳዊት መክፈቻ” አለው። በዚህም መክፈቻ በመጠቀም ‘ይከፍታል፣ የሚዘጋም አይኖርም፤ ይዘጋልም፣ የሚከፍት አይኖርም።’ ታዲያ ይህ “የዳዊት መክፈቻ” ምንድን ነው?
5 ይሖዋ ለዘላለም መንግሥት ቃል ኪዳን የገባው ከእሥራኤሉ ንጉሥ ዳዊት ጋር ነበር። (መዝሙር 89:1-4, 34-37) የዳዊት ተወላጆች ከ1070 እስከ 607 ከዘአበ ድረስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ዙፋን ላይ በመቀመጥ ገዝተው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ይህ መንግሥት በክፋት ስለተዋጠ የአምላክ የጥፋት ፍርድ ተፈረደበት። በዚህም ምክንያት ይሖዋ በሕዝቅኤል 21:27 ላይ የተናገረውን ትንቢት መፈጸም ጀመረ። “ባድማ፣ ባድማ፣ ባድማ አደርጋታለሁ [ምድራዊት ኢየሩሳሌምን]። ፍርድ ያለው [“ሕጋዊ መብት ያለው፣” NW] እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ [ከዳዊት መስመር የሆኑት የሚጨብጡት በትረ መንግሥት] አትሆንም። ለእርሱም እሰጣታለሁ።”
6, 7. “ፍርድ ያለው” ወይም “ሕጋዊ መብት” ያለው የሚገለጠው እንዴትና መቼ ነው?
6 ይህ ‘ሕጋዊ መብት ያለው’ የሚገለጠው እንዴትና መቼ ነው? የዳዊት በትረ መንግሥት ለእርሱ የሚሰጠውስ እንዴት ነው?
7 ይህ ከሆነ ከ600 ዓመታት ያህል በኋላ የንጉሥ ዳዊት ተወላጅ የሆነች ማርያም የተባለች አይሁዳዊት ድንግል በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንድትጸንስ ተደረገች። አምላክ መልአኩ ገብርኤልን ኢየሱስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ እንደምትወልድ ለማርያም እንዲነግራት ላከው። ገብርኤልም የሚከተለውን ቃል ጨምሮ ነገራት። “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል። ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”—ሉቃስ 1:31-33
8. ኢየሱስ የዳዊትን መንግሥት ለመውረስ ብቃት ያለው መሆኑን ያስመሰከረው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ በ29 እዘአ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀና በመንፈስ ቅዱስ በተቀባ ጊዜ በዳዊት ሥርወ መንግሥት የሚገዛ እጩ ንጉሥ ሆነ። የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክም ረገድ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ቅንዓት አሳየ። ደቀ መዛሙርቱም ልክ እንደ እርሱ እንዲሰብኩ አዘዛቸው። (ማቴዎስ 4:23፤ 10:7, 11) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ራሱን አዋርዶአል። ይህን በማድረጉም የዳዊትን ንግሥና ለመውረስ ብቃት ያለው መሆኑን አስመስክሮአል። ይሖዋ ኢየሱስን ከሙታን አስነስቶ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ከሰጠው በኋላ በሰማያት በቀኙ እንዲቀመጥ በማድረግ ከፍ ከፍ አድርጎታል። የዳዊት መንግሥት የሚያስገኘውንም መብት በሙሉ ወርሶአል። በተወሰነለት ጊዜም “በጠላቶችህ መካከል ግዛ” በመባል የሚሰጠውን መብት ይቀበላል።—መዝሙር 110:1, 2፤ ፊልጵስዩስ 2:8, 9፤ ዕብራውያን 10:13, 14
9. ኢየሱስ የዳዊትን መክፈቻ ለመክፈትና ለመዝጋት የሚጠቀምበት እንዴት ነው?
9 ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ኢየሱስ ከአምላክ መንግሥት ጋር ተዛማጅነት ያለው መብትና አጋጣሚ በመክፈት በዳዊት መክፈቻ ይጠቀማል። አሁን ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት በምድር የሚኖሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከጨለማ ሥልጣን” አውጥቶ “ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት” ሊያፈልሳቸው ይችላል። (ቆላስይስ 1:13, 14) በተጨማሪም መክፈቻው ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች ይህን መብት እንዳያገኙ ለማገድ ያገለግላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:12, 13) ይህ የዳዊት ንግሥና ዘላለማዊ ወራሽ የይሖዋ ድጋፍ ስላለው እነዚህን የሥራ ግዴታዎች እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ማንም ፍጡር የለም።—ከማቴዎስ 28:18-20 ጋር አወዳድር።
10. ኢየሱስ በፊልድልፍያ ለነበረው ጉባኤ ምን ማበረታቻ ሰጥቶአል?
10 ኢየሱስ በፊልድልፍያ ለነበሩት ክርስቲያኖች የተናገረው ቃል እንዲህ ካለ ታላቅ ባለ ሥልጣን የመጣ ስለሆነ በጣም ሳያጽናናቸው አልቀረም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል አመሰገናቸው:- “ሥራህን አውቃለሁ እነሆ፣ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ። ማንም ሊዘጋው አይችልም ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፣ ስሜንም አልካድህምና።” (ራእይ 3:8) ጉባኤው ለሥራ ሲንቀሳቀስ የቆየ ስለሆነ ማንም ሊዘጋው የማይችል በር ተከፍቶለታል። ይህም የአገልግሎት አጋጣሚ በር መሆኑ አያጠራጥርም። (ከ1 ቆሮንቶስ 16:9ና ከ2 ቆሮንቶስ 2:12 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ጉባኤው ባገኘው የስብከት አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀም ኢየሱስ አበረታቶታል። ጸንተው ስለተገኙ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ሥራ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል እንዳላቸው አረጋግጠዋል። (2 ቆሮንቶስ 12:10፤ ዘካርያስ 4:6) የኢየሱስን ትዕዛዝ ፈጽመዋል፣ በአንደበታቸውም ሆነ በድርጊታቸው ክርስቶስን አልካዱም።
“በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ . . . አደርጋቸዋለሁ”
11. ኢየሱስ ለክርስቲያኖች ምን በረከት ሊሰጣቸው ቃል ገብቶአል? ይህስ የተፈጸመው እንዴት ነው?
11 ስለዚህም ኢየሱስ የታማኝነታቸውን ፍሬ እንደሚያገኙ ቃል ገባላቸው:- “እነሆ፣ አይሁድ ሳይሆኑ:- አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፣ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።” (ራእይ 3:9) ምናልባት የፊልድልፍያም ጉባኤ እንደ ሰምርኔስ ጉባኤ በአካባቢው ከነበሩት ከአይሁዳውያን ችግር ሳይደርስበት አልቀረም። እነዚህን ሰዎች ኢየሱስ “የሰይጣን ማኅበር” ብሎአቸዋል። ሆኖም ግን ከእነዚህ አይሁዳውያን አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ሲሰብኩ የቆዩት ሁሉ እውነት መሆኑን ሊገነዘቡ ነው። ‘ይሰግዱ ዘንድ ይገባቸዋል’ የተባለውም ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 14:24, 25 ላይ በገለጸው መንገድ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ታላቅ ፍቅር እንዳሳየ ተገንዝበው ንስሐ በመግባት ክርስቲያን ይሆናሉ ማለት ነው።—ዮሐንስ 15:12, 13
12. በፊልድልፍያ የነበረው የአይሁድ ምኩራብ አባሎች ከመካከላቸው አንዳንዶቹ በከተማቸው ለነበረው የክርስቲያኖች ማህበረሰብ እንደ ሰገዱ ሲያውቁ የደነገጡት ለምንድን ነው?
12 በፊልድልፍያ የነበረው የአይሁድ ምኩራብ አባሎች በመካከላቸው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በከተማው ውስጥ ለነበረው የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ ‘ሲሰግዱ’ ማየታቸው ሳያስደነግጣቸው አልቀረም። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አይሁዳውያን ያልሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚኖሩ የተረጋገጠ ስለሆነ አይሁዳውያን ለክርስቲያኖች ሳይሆን ክርስቲያኖች ለአይሁዳውያን ተጎንብሰው ይሰግዳሉ ብለው ሳይጠብቁ አልቀረም። ለምን ቢባል ኢሳይያስ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሮ ነበር። “[አይሁዳውያን ያልሆኑ] ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ [ለአይሁድ ሕዝብ] ይሆናሉ፣ እተጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል።” (ኢሳይያስ 49:23፤ 45:14፤ 60:14) ዘካርያስም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ትንቢት ተናግሮ ነበር:- “በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው:- እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።” (ዘካርያስ 8:23) አዎ፣ አይሁድ ያልሆኑ ሰዎች ለአይሁዳውያን ይሰግዳሉ እንጂ አይሁዳውያን አይሁድ ላልሆኑ ሰዎች አይሰግዱም ማለት ነው።
13. ለጥንትዋ እስራኤል የተነገሩት ትንቢቶች የሚፈጸምላቸው አይሁድ እነማን ነበሩ?
13 እነዚህ ትንቢቶች የተነገሩት ለአምላክ ምርጥ ሕዝብ ነበር። ትንቢቶቹ በተነገሩበት ጊዜ እሥራኤላውያን ይህን የመሰለ የክብር ቦታ ይዘው ነበር። የአይሁድ ሕዝብ መሲሑን አልቀበልም ባለ ጊዜ ግን ይሖዋ ይህን ሕዝብ ተወው። (ማቴዎስ 15:3-9፤ 21:42, 43፤ ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 1:10, 11) ይሖዋ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በአይሁድ ሕዝብ ምትክ እውነተኛውን የአምላክ እሥራኤል ማለትም የክርስቲያን ጉባኤን መረጠ። የጉባኤው አባሎች ልባቸውን የተገረዙ መንፈሳዊ አይሁዶች ነበሩ። (ሥራ 2:1-4, 41, 42፤ ሮሜ 2:28, 29፤ ገላትያ 6:16) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግለሰብ ሥጋዊ አይሁዶች ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖራቸው የሚችለው የኢየሱስን መሲሕነት በመቀበልና በማመን ብቻ ነው። (ማቴዎስ 23:37-39) አንዳንድ በፊልድልፍያ ይኖሩ የነበሩ ግለሰቦች ይህንን እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ተገልጿል።a
14. ኢሳይያስ 49:23 እና ዘካርያስ 8:23 በዘመናችን በጉልህ የተፈጸሙት እንዴት ነው?
14 በዘመናችንም እንደ ኢሳይያስ 49:23 እና ዘካርያስ 8:23 የመሰሉት ትንቢቶች በጉልህ ሁኔታ ተፈጽመዋል። የዮሐንስ ክፍል አባሎች ባከናወኑት የስብከት ሥራ ምክንያት በጣም ብዙ ሰዎች በተከፈተው በር በኩል ወደ መንግሥቱ አገልግሎት ገብተዋል።b ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ የመጡት በሐሰት መንፈሣዊ እሥራኤል ነኝ ከምትለው ከሕዝበ ክርስትና ነው። (ከሮሜ 9:6 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ሰዎች የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል እንደመሆናቸው መጠን በኢየሱስ ቤዛዊ ደም በማመን ልብሳቸውን አጥበው አንጽተዋል። (ራእይ 7:9, 10, 14) የክርስቶስን ንጉሣዊ አገዛዝ ስለሚታዘዙ የዚህችን መንግሥት በረከት በዚህችው ምድር ላይ ለመውረስ ተስፋ ያደርጋሉ። አምላክ ከኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ጋር እንዳለ ስለ ሰሙ በመንፈሳዊ አባባል ወደ እነርሱ ሄደው ይሰግዱላቸዋል። እነዚህን በምድር አቀፍ የወንድማማችነት ማህበር የተባበሩአቸውን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያገለግሉአቸዋል።—ማቴዎስ 25:34-40፤ 1 ጴጥሮስ 5:9
“የፈተና ሰዓት”
15. (ሀ) ኢየሱስ በፊልድልፍያ ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር? ምንስ እንዲያደርጉ ተበረታተዋል? (ለ) ክርስቲያኖች የትኛውን “አክሊል” ለመቀበል በጉጉት ይጠባበቁ ነበር?
15 ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “የትዕግሥቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ፣ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ።” (ራእይ 3:10, 11) በዮሐንስ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች (በ1914 የጀመረው) የጌታ ቀን እስኪመጣ ድረስ በሕይወት የማይቆዩ ቢሆንም ኢየሱስ እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆናቸው በስብከቱ ሥራ እንዲተጉ የሚያስችላቸውን ኃይል ሰጥቶአቸዋል። (ራእይ 1:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2) የዘላለም ሕይወት ሽልማት ወይም “አክሊል” በሰማይ ይጠብቃቸው ነበር። (ያዕቆብ 1:12፤ ራእይ 11:18) እስከሞታቸው ድረስ ታማኝ ሆነው ከቆዩ ይህን ሽልማት ሊያሳጣቸው የሚችል ማንም አይኖርም።—ራእይ 2:10
16, 17. (ሀ) በመላው ምድር ላይ ሊመጣ ያለው “የፈተና ሰዓት” ምንድን ነው? (ለ) “በፈተናው ሰዓት” መጀመያ ላይ ቅቡዓን እንዴት ባለ ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር?
16 ይሁን እንጂ “የፈተናው ሰዓት” ምንድን ነው? እነዚህ የእስያ ክርስቲያኖች ከሮማ አፄያዊ መንግሥት የሚደርስባቸውን ሌላ ከባድ ስደት መቋቋም እንደነበረባቸው አያጠራጥርም።c ትንቢቱ ዋናውን ፍጻሜ የሚያገኘው ግን ከ1918 ጀምሮ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረውና በጌታ ቀን በተፈጸመው የማበጠርና የፍርድ ጊዜ ነው። ፈተናው አንድ ሰው የተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ደጋፊ ወይም የሰይጣን ዓለም ደጋፊ መሆኑን የሚያሳውቅ ነው። ፈተናው የሚቆየው አጠር ላለ ጊዜ ወይም ለአንድ “ሰዓት” ነው። ቢሆንም ፈተናው ገና አላበቃም። እስኪያበቃ ድረስ ግን ‘በፈተናው ሰዓት’ እንደምንኖር ፈጽሞ መዘንጋት አይገባንም።—ሉቃስ 21:34-36
17 በ1918 የዮሐንስ ክፍል አባሎች የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በፊልድልፍያ እንደ ነበረው ጠንካራ ጉባኤ ከዘመናዊው “የሰይጣን ምኩራብ” የሚደርስባቸውን ተቃውሞ መቋቋም ነበረባቸው። መንፈሳዊ አይሁዳውያን ነን ይሉ የነበሩት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ገዥዎችን በማሳሳትና በመጠምዘዝ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለማፈን መሣሪያ አድርገው ተጠቀሙባቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ክርስቲያኖች የኢየሱስን የጽናት ቃል ጠብቀው ለመኖር ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ስለዚህ በተሰጣቸው መንፈሳዊ እርዳታ ያላቸውን ‘ትንሽ ኃይል’ ጠብቀው ስለተገኙ ተከፍቶ ይጠብቃቸው በነበረው በር ለመግባት ተነሳሱ። ግን ወደዚህ በር የገቡት እንዴት ነው?
“የተከፈተ በር”
18. ኢየሱስ በ1919 ምን ዓይነት ሹመት ሰጠ? ተሿሚውስ ታማኝ እንደነበረው የሕዝቅያስ መጋቢ የሆነው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ በ1919 እነዚህን እውነተኛ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ‘ታማኝና ልባም ባሪያው’ አድርጎ በመሾም የገባላቸውን ቃል ፈጸመላቸው። (ማቴዎስ 24:45-47) እነዚህ ክርስቲያኖች በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን ታማኝ መጋቢ የነበረው ኤልያቄም የተሰጠውን መብት የመሰለ መብት አገኙ።d ይሖዋ ስለ ኤልያቄም ሲናገር እንዲህ አለ:- “የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ። እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም፤ እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም።” ኤልያቄም የዳዊት ንጉሣዊ ልጅ ለሆነው ለሕዝቅያስ ከባድ ኃላፊነት ተሸክሞ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ የዮሐንስ ክፍል በሆኑት ቅቡዓን ጫንቃ ላይ “የዳዊት ቤት መከፈቻ” ተጭኖአል። የመሲሐዊውን መንግሥት ፍላጎቶች የማስከበር ኃላፊነት ተጭኖባቸዋል። ይሖዋ አገልጋዮቹን ለዚህ መብታቸው ብቁ ሆነው እንዲገኙ አበርትቶአቸዋል። ያላቸውን ትንሽ ኃይል በጣም ስለጨመረላቸው ከፍተኛ ለሆነው ምድር አቀፍ የምሥክርነት ሥራ አብቅቶአቸዋል።—ኢሳይያስ 22:20, 22፤ 40:29
19. የዮሐንስ ክፍል ኢየሱስ በ1919 የሰጠውን ኃላፊነት የተወጣው እንዴት ነው? ምንስ ውጤት አስገኘ?
19 ቅቡዓን ቀሪዎች ከ1919 ጀምሮ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የመንግሥቱን ምሥራች የማወጅ ዘመቻ ጀምረዋል። (ማቴዎስ 4:17፤ ሮሜ 10:18) በዚህም ዘመቻቸው ምክንያት ዘመናዊ የሰይጣን ምኩራብ ከሆነችው ከሕዝበ ክርስትና ውስጥ የወጡ አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ገብተው በመስገድ ለባሪያው የተሰጠውን ሥልጣን ተቀብለዋል። እነዚህም ሰዎች ቀደም ካሉት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ጋር በመተባበር ይሖዋን ማገልገል ጀምረዋል። ይህ ሥራ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ቁጥር እስከ ሞላበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎአል። ከዚያም በኋላ ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ለቅቡዓን ባሮች መስገድ ጀምረዋል። (ራእይ 7:3, 4, 9) ባሪያውና እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን አንድ መንጋ ሆነው ያገለግላሉ።
20. የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ በአሁኑ ጊዜ በእምነት ጠንካሮችና በአምላክ አገልግሎት ትጉሆች መሆን የሚገባቸው ለምንድን ነው?
20 የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ በፊልድልፍያ እንደነበሩት ክርስቲያኖች ልባዊ በሆነ የወንድማማች ፍቅር ስለተሳሰሩ የስብከት ሥራቸው በታላቅ ጥድፊያ መፈጸም እንደሚኖርበት ያውቃሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ታላቁ መከራ በሰይጣን ክፉ ዓለም ላይ የመጨረሻ ጥፋት ያመጣል። በዚያ ጊዜ ስማችን ከይሖዋ የሕይወት መጽሐፍ እንዳይፋቅ ሁላችንም ጠንካራ እምነት ያለንና በአምላክ አገልግሎት የምንተጋ ሆነን እንገኝ። (ራእይ 7:14) የአገልግሎት መብታችን እንዳይወሰድብንና የዘላለምን ሕይወት ሽልማት ለማግኘት እንድንችል ኢየሱስ ለፊልድልፍያ ጉባኤ የሰጠውን ምክር በጥሞና እንከተል።
ድል አድራጊዎች የሚያገኙት በረከት
21. በዘመናችን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ስለ ኢየሱስ ጽናት የሚገልጸውን ቃል’ የጠበቁት እንዴት ነው? ምንስ ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
21 በዘመናችን የሚኖሩት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ‘የኢየሱስን የትዕግሥት ቃል’ ጠብቀዋል። ይህም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ጸንተዋል ማለት ነው። (ዕብራውያን 12:2, 3፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ለፊልድልፍያ ጉባኤ በተናገረው በሚቀጥለው ቃል በጣም ተጽናንተዋል። “ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፣ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም።”—ራእይ 3:12ሀ
22. (ሀ) የኢየሱስ አምላክ ቤተ መቅደስ ምንድን ነው? (ለ) ድል የሚነሱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ አምድ የሚሆኑት እንዴት ነው?
22 በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዓምድ ለመሆን መቻል በጣም ታላቅ መብት ነው። በጥንቷ ኢየሩሳሌም የነበረው ግዑዝ ቤተ መቅደስ የይሖዋ አምልኮ እምብርት ወይም ማዕከል ነበር። በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ቀን ‘በቅድስተ ቅዱሳኑ’ ውስጥ የይሖዋን መገኘት በሚያመለክተው ተአምራዊ ብርሃን ፊት ለመሥዋዕት የቀረቡ እንስሳትን ደም ያቀርብ ነበር። (ዕብራውያን 9:1-7) ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ግን ሌላ ቤተ መቅደስ ተገኘ። ይህም ቤተ መቅደስ ይሖዋ የሚመለክበት ታላቅ መቅደስ መሰል መንፈሳዊ ዝግጅት ነው። የዚህ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገኘው ኢየሱስ ‘በአምላክ ፊት’ በቀረበበት በሰማይ ነው። (ዕብራውያን 9:24) ሊቀ ካህኑ ኢየሱስ ነው። ለሰው ሁሉ ኃጢአት ሥርየት የቀረበው መሥዋዕት ፍጹም ሰው የነበረው የኢየሱስ ደም ብቻ ነው። (ዕብራውያን 7:26, 27፤ 9:25-28፤ 10:1-5, 12-14) በምድር ላይ የሚኖሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝነታቸውን ጠብቀው እስከኖሩ ድረስ በዚህ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ የበታች ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (1 ጴጥሮስ 2:9) ድል ካደረጉ በኋላ ግን ወደ ሰማያዊው ቅድስተ ቅዱሳን ገብተው በቤተ መቅደስ የተመሰለው የአምልኮ ዝግጅት የማይነቃነቁ ደጋፊዎች ወይም አምዶች ይሆናሉ። (ዕብራውያን 10:19፤ ራእይ 20:6) ከዚህ ቦታቸው ሊያነቃንቃቸው የሚችል ነገር አይኖርም። ‘ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጡም።’
23. (ሀ) ኢየሱስ ቀጥሎ ድል ለሚነሱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ተስፋ ሰጠ? (ለ) የይሖዋ ስምና የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ስም በድል አድራጊ ክርስቲያኖች ላይ መጻፉ ምን ውጤት ያስገኛል?
23 ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፣ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፣ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።” (ራእይ 3:12ለ) አዎ፣ በእነዚህ ድል አድራጊዎች ላይ የእነርሱም ሆነ የኢየሱስ አምላክ የሆነው የይሖዋ ስም ይጻፍባቸዋል። ይህም ይሖዋና ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ አካላት እንጂ አንድነት በሦስትነት ያለው ሥላሴያዊ አምላክ ሁለት ክፍሎች አለመሆናቸውን በግልጽ ያመለክታል። (ዮሐንስ 14:28፤ 20:17) ፍጥረት ሁሉ እነዚህ ቅቡዓን የይሖዋ ንብረት መሆናቸውን ማወቅ ይኖርበታል። እነርሱ የእሱ ምሥክሮች ናቸው። በተጨማሪም ከሰማይ የምትወርደው ሰማያዊት ከተማ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ስም ተጽፎባቸዋል። የዚህች ከተማ የቸርነት አገዛዝ በታማኝ የሰው ልጆች ሁሉ ላይ ስለሚሰፍን ከሰማይ ወደ ምድር እንደወረደች ይቆጠራል። (ራእይ 21:9-14) ስለዚህ ምድራውያን ክርስቲያን በጎች በሙሉ እነዚህ ድል አድራጊ ቅቡዓን የመንግሥቱ፣ ማለትም የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ዜጎች መሆናቸውን ያውቃሉ።—መዝሙር 87:5, 6፤ ማቴዎስ 25:33, 34፤ ፊልጵስዩስ 3:20፤ ዕብራውያን 12:22
24. የኢየሱስ አዲስ ስም ምን ያመለክታል? በታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ የተጻፈው እንዴት ነው?
24 በመጨረሻም በድል አድራጊዎቹ ቅቡዓን ላይ የኢየሱስ አዲስ ስም ይጻፍባቸዋል። ይህም ስም የኢየሱስን አዲስ ሹመትና ይሖዋ የሰጠውን ልዩ መብት ያመለክታል። (ፊልጵስዩስ 2:9-11፤ ራእይ 19:12) ይህን ተሞክሮ ያገኘ ወይም ይህ ልዩ መብት የተሰጠው ሌላ ማንም ስለሌለ ያንን ስም ሊያውቀው የቻለ የለም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስሙን በታማኝ ወንድሞቹ ላይ ሲጽፍ በሰማያዊው ዓለም ውስጥ ልዩ የሆነ የተቀራረበ ዝምድና ከማግኘታቸውም በላይ ከመብቶቹም አብረውት ሊካፈሉ ይችላሉ። (ሉቃስ 22:29, 30) ኢየሱስ ለእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የላከውን መልእክት የሚከተለውን ምክር በመስጠት መደምደሙ አያስደንቅም። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።”—ራእይ 3:13
25. እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቲያን ኢየሱስ ለፊልድልፍያ ጉባኤ የሰጠው ምክር የተመሠረተበትን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ የሚያውለው እንዴት ነው
25 ይህ ቃል በፊልድልፍያ የነበሩትን ታማኝ ክርስቲያኖች በጣም ሳያበረታታቸው አልቀረም። በዚህ የጌታ ዘመን ለሚኖሩት የዮሐንስ ክፍል አባሎችም ጠንካራ ትምህርት ይዟል። መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ግን ለማንኛውም ግለሰብ ክርስቲያን፣ የተቀባም ሆነ የሌሎች በጎች ክፍል ለሁሉም አስፈላጊ ናቸው። (ዮሐንስ 10:16) ሁላችንም ብንሆን በፊልድልፍያ እንደነበሩት ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ፍሬዎች እያፈራን ብንኖር በጣም ጥሩ ነው። ሁላችንም እጅግ ቢያንስ ጥቂት ኃይል አለን። ሁላችንም በይሖዋ አገልግሎት የምንሠራው ሥራ ሊኖረን ይችላል። በዚህ ኃይላችን እንጠቀም። የመንግሥት መብታችንን በማስፋት ረገድ በሚከፈትልን በር ሁሉ ለመግባት ንቁዎች እንሁን። እንዲያውም ይሖዋ እንዲህ ያለውን በር እንዲከፍትልን ልንጸልይ እንችላለን። (ቆላስይስ 4:2, 3) የኢየሱስን የጽናት ምሳሌ ስንከተልና ለስሙ እውነተኞች ሆነን ስንገኝ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለጉባኤዎች የሚለውን እንደምንሰማ እናሳያለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጳውሎስ ዘመን በቆሮንቶስ የነበረው የአይሁድ ምኩራብ አለቃ የነበረው ሶስቴኔስ ክርስቲያን ወንድም ሆኖአል።—ሥራ 18:17፤ 1 ቆሮንቶስ 1:1
b በዮሐንስ ክፍል የሚታተመው መጠበቂያ ግንብ መጽሔት በዚህ አጋጣሚ መጠቀምና በተቻለ መጠን በስብከቱ ሥራ መካፈል በጣም አጣዳፊ መሆኑን ሲያስገነዝብ ቆይቶአል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥር 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ “ሰው ሁሉ የይሖዋን ክብር ያውጅ” እና “‘ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ወጣ’” በሚሉ ርዕሶች የቀረቡትን ትምህርቶች ተመልከት። በሰኔ 1, 2004 እትም ላይ “ለአምላክ ክብር የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው” በሚል ርዕስ በቀረበው ትምህርት ላይ ‘በተከፈተው በር’ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት በጣም አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል። በ2005 በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 1,093,552 የደረሰ ከፍተኛ የአቅኚዎች ቁጥር ሪፖርት ተደርጓል።
c የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒድያ (ጥራዝ 10፣ ገጽ 519) እንዲህ ይላል:- “ክርስትና የንጉሠ ነገሥቶችን ትኩረት የሳበው የዚህን እምነት በአስደንጋጭ ሁኔታ መስፋፋት በመመልከታቸው የተደናገጡት አረማዊ ቀሳውስት በሕዝቡ መካከል ከባድ ረብሻ በማስነሳታቸው ነው። በዚህም ምክንያት ትራጃን [98-117 እዘአ] ሰዎች አማልክትን እንዲጠሉ የሚያደርገውን ይህን ትምህርት እንዳይስፋፋ የሚያፍን አዋጅ አወጣ። የቢታንያ [በሰሜን በኩል ከእስያ የሮማ ግዛት ጋር የሚዋሰነው ክፍል] ገዥ በነበረው በወጣቱ ፕሊኒ አስተዳደር ክርስትና በጣም ይስፋፋ ስለነበረና በዚህም ምክንያት በክፍለ ሀገሩ ውስጥ የሚኖሩ አረማውያን በጣም ስለተቆጡ ከባድ ችግር ደርሶ ነበር።”
d ሕዝቅያስ የሚለው ስም ትርጉም “ይሖዋ ያበረታል” ማለት ነው። ሁለተኛ ነገሥት 16:20 የግርጌ ማስታወሻ፣ ባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ተመልከት።
[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብዙ ሰዎችን እንዲሰግዱ መርዳት
ሰማያዊውን መንግሥት ከሚወርሱት 144,000 ቅቡዓን መካከል ገና ምድራዊ ሕይወታቸውን ያልፈጸሙ ከ9, 000 የሚያንሱ የዮሐንስ ክፍል አባሎች ወይም ቀሪዎች ብቻ የቀሩ ይመስላል። በዚሁ ጊዜ ግን የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሮ ከ6,600,000 በላይ ሆኖአል። (ራእይ 7:4, 9) ይህ ታላቅ ጭማሪ እንዲገኝ የረዳው ምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱአቸው የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ዓለማዊ ፍልስፍናዎችን እያስተማሩ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያቃልሉት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች በጣም የተለዩ በመሆን በአምላክ ቃል ላይ የጠለቀ እምነት ያሳድራሉ። የአምላክ ቃል ንጹሕ በሆነ ሥነ ምግባር ስለመኖርና የሙሉ ልብ አገልግሎት ለአምላክ ስለማቅረብ የሚሰጠውን ተግባራዊ ጠቀሜታ ያመለክታሉ። ከ1943 ጀምሮ በዓለም በሙሉ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በየመንግሥት አዳራሾቻቸው የቲኦክራቲካዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ያካሂዳሉ። በየሳምንቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ ትምህርት ቤቶች እየተገኙ አንድ ወጥ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ይከታተላሉ።
ከ1959 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት የሚሰለጥኑበትን የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። በ1977 በተጀመረው የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ደግሞ የፊልድልፍያ ክርስቲያኖችን በመሰለ መንፈስ ተነሳስተው በስብከቱ ሥራ ይሖዋን በሙሉ ጊዜያቸው በማገልገል ላይ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ሰልጥነዋል። በ1987 መከሩ በሚሠራበት ዓለም ውስጥ ልዩ የሥራ መደብ የሚሰጣቸው ወንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰለጥኑበት የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተቋቁሞአል።
የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያካሂዱአቸው ትምህርት ቤቶች በሙሉ ግንባር ቀደም የሆነው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ነው። ይህ በኒውዮርክ ክፍለ ሐገር የሚገኘው የሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ከ1943 ጀምሮ በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ቆይቶአል። በጠቅላላው ከ7,000 የሚበልጡ የይሖዋ አገልጋዮችን ለውጭ አገር ሚሲዮናዊ አገልግሎት አሰልጥኖአል። የዚህ ትምህርት ቤት ምሩቃን ከመቶ በሚበልጡ አገሮች አገልግለዋል። አብዛኛውን ጊዜም የመንግሥቱን ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ በመክፈት መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል። ከመጀመሪያዎቹ ሚሲዮናውያን አንዳንዶቹ በሥራቸው ላይ 60 የሚያህሉ ዓመታት የቆዩ ቢሆኑም የይሖዋን ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስፋፋቱ ሥራ ከአዳዲሶቹ ሚሲዮናውያን ጋር በመካፈል ላይ ናቸው። በጣም አስደናቂ የሆነ እድገት አስገኝተዋል።
[በገጽ 64 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
ንግሥና የተቀበለው ኢየሱስ በ1919 ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የአጋጣሚ በር ከፈተ። በዚህም አጋጣሚ ቁጥራቸው እየበዛ የመጣ ብዙ ውስን ክርስቲያኖች ተጠቅመዋል።
1918 14 3,868 591
1928 32 23,988 1,883
1938 52 47,143 4,112
1948 96 230,532 8,994
1958 175 717,088 23,772
1968 200 1,155,826 63,871
1978 205 2,086,698 115,389
1988 212 3,430,926 455,561
1998 233 5,544,059 698,781
2005 235 6,390,022 843,234
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
e ከላይ የተጠቀሱት ቁጥሮች የየወሩን አማካይ ቁጥር የሚያመለክቱ ናቸው።
f ከላይ የተጠቀሱት ቁጥሮች የየወሩን አማካይ ቁጥር የሚያመለክቱ ናቸው።
[በገጽ 65 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በሙሉ ልብ የሚከናወን እንቅስቃሴ ነው። ለምሳሌ ያህል በስብከትና በማስተማር ሥራ የሚያሳልፉትን ሰዓት መጠንና በሰዎች ቤት ውስጥ በነፃ የመሩአቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛት ተመልከት።
በስብከቱ ሥራ የዋለው ሰዓት
የተመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
ዓመት (የዓመቱ ጠቅላላ ድምር) (የወሩ አማካይ ቁጥር)
1918 19,116 አልተመዘገበም
1928 2,866,164 አልተመዘገበም
1938 10,572,086 አልተመዘገበም
1948 49,832,205 130,281
1958 110,390,944 508,320
1968 208,666,762 977,503
1978 307,272,262 1,257,084
1988 785,521,697 3,237,160
1998 1,186,666,708 4,302,852
2005 1,278,235,504 6,061,534
[በገጽ 59 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮማውያን ቁልፍ