የክርስቶስ መመለስ
ፍቺ:- ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርን ትቶ ከመሄዱ በፊት እንደሚመለስ ቃል ገብቶ ነበር። በአምላክ መንግሥት ውስጥ ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁት አስደናቂ ክንውኖች ከዚህ ተስፋ ጋር የተያያዙ ናቸው። በመምጣት እና በመገኘት መካከል ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ይገባል። ስለዚህ የአንድ ሰው መምጣት (ከመድረስ ወይም ከመመለስ ጋር የተዛመደ ስለሆነ) በአንድ የተወሰነ ጊዜ ላይ የሚፈጸም ነገር ሲሆን በቦታው መገኘቱ ወይም መኖሩ ግን ከመጣ በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቀጥል ነገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤርኮማይ (“መምጣት” ማለት ነው) የሚለው የግሪክኛ ቃል በተጨማሪ ኢየሱስ በመገኘቱ ጊዜ በአንድ የተወሰነ ወቅት አስፈላጊ በሆነ ተግባር ማለትም የይሖዋ ቅጣት አስፈጻሚ በመሆን ሁሉን በሚችለው ታላቅ የጦርነት ቀን እርምጃ በመውሰድ ላይ ማተኮሩን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
በክርስቶስ መገኘት ጊዜ የሚከሰቱት ነገሮች በአንድ አፍታ ተፈጽመው የሚያበቁ ናቸው ወይስ በዓመታት የሚቆጠር ጊዜ የሚፈጁ?
ማቴ. 24:37–39:- “የኖኅ ዘመን እንደነበረ የሰው ልጅ መምጣት [“መምጣት” ሪስ፣ ቱኢቨ፤ “መገኘት” ያን፣ ሮዘ፣ ኤዳ፣ አዓት፤ በግሪክኛ ፓሩሲያ ] እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” (እዚህ ላይ የተጠቀሱት “በኖኅ ዘመን” የተፈጸሙ ነገሮች ረዘም ያሉ ዓመታት የፈጁ ናቸው። ኢየሱስ መገኘቱን በኖኅ ዘመን ከተፈጸሙ ሁኔታዎች ጋር አመሳስሎታል።)
በማቴዎስ 24:37 ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል ፓሩሲያ ነው። ይህም ቃል በቃል “በ . . . አጠገብ መሆን” ማለት ነው። በሊዴልና ስኮትስ የተዘጋጀው ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (ግሪክኛ–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት) (ኦክስፎርድ፣ 1968) የፓሩሲያ የመጀመሪያ ትርጉም “የአንድ ሰው መገኘት ወይም መኖር” እንደሆነ ይገልጻል። ቃሉ የሚያስተላልፈው ስሜት ሐዋርያው ጳውሎስ የራሱን በአንድ ቦታ መኖር (ፓሩሲያ ) ካለመኖሩ (አፑሲያ ) ጋር አነጻጽሮ በተናገረበት በፊልጵስዩስ 2:12 ላይ በግልጽ ተመልክቷል። በሌላ በኩል ደግሞ በማቴዎስ 24:30 ላይ ‘የሰው ልጅ የይሖዋ ቅጣት አስፈጻሚ ሆኖ በአርማጌዶን በኃይልና በታላቅ ክብር በደመናት እንደሚመጣ’ ሲናገር የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ኤርኮሜኖን ነው። አንዳንድ ተርጓሚዎች ሁለቱንም ቃላት ‘መምጣት’ እያሉ ተርጉመዋል። ይሁን እንጂ ይበልጥ ጠንቃቃ የሆኑ ተርጓሚዎች በሁለቱ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት አመልክተዋል።
ክርስቶስ የሚመለሰው በሰብዓዊ ዓይኖች በሚታይ ሁኔታ ነውን?
ዮሐ. 14:19:- “ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን [የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያት] ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።” (ኢየሱስ እንደሚመለስና ሐዋርያቱ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ወደ ሰማይ እንደሚወስዳቸው ቃል ገብቷል። እነርሱም መንፈሳዊ ፍጡራን ስለሚሆኑ ሊያዩት ይችላሉ። ዓለም ግን ዳግመኛ አያየውም። ከ1 ጢሞቴዎስ 6:16 ጋር አወዳድር።)
ሥራ 13:34:- “እንደገናም [ኢየሱስ] ወደ መበስበስ እንዳይመለስ [አምላክ ከሙታን አስነሣው።]” (ሰብዓዊ አካል በተፈጥሮው ሊበሰብስና ሊጠፋ የሚችል ነው። 1 ቆሮንቶስ 15:42, 44 “መበስበስ” የሚለውን ቃል ከ“አካላዊ ሥጋ” ጋር አዛምዶ የሚገልጸው በዚህ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ዳግመኛ እንዲህ ያለ አካል አይኖረውም።)
ዮሐ. 6:51:- “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” (ኢየሱስ ይህን ሥጋውን አንድ ጊዜ ስለሰጠ መልሶ አይወስደውም። እንዲህም በማድረግ የሰው ልጅ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱ ያስገኘውን ጥቅም እንዲያጣ አያደርግም።)
በተጨማሪም በገጽ 312, 313 ላይ “በአካል መነጠቅ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንዳረገ “እንዲሁ ይመጣል” ሲባል ምን ማለት ነው?
ሥራ 1:9–11:- “ይህንንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ [የኢየሱስ ሐዋርያት] እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፣ እነሆ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም:- የገሊላ ሰዎች ሆይ፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፣ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” (ይህ ጥቅስ የሚለው “እንዲሁ” ወይም “በዚያው ዓይነት ሁኔታ” ይመጣል ነው እንጂ በዚሁ አካሉ ይመጣል እንደማይል ልብ በል። ያረገው በምን ዓይነት ሁኔታ ነበር? ቁጥር 9 እንደሚያመለክተው ሲያርግ ከዓይናቸው ጠፋ። የተመለከቱትም ደቀ መዛሙርቱ ብቻ ነበሩ። ዓለም በአጠቃላይ ምን በመፈጸም ላይ እንደነበረ አልተገነዘበም ነበር። ክርስቶስ ሲመለስም እንዲሁ ይሆናል።)
‘በደመና ይመጣል፤’ ‘ዓይኖች ሁሉ ያዩታል’ ሲባል ምን ማለት ነው?
ራእይ 1:7:- “እነሆ፣ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፣ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ።” (በተጨማሪም ማቴዎስ 24:30፤ ማርቆስ 13:26፤ ሉቃስ 21:27ን ተመልከት።)
“ደመና ” ምን ያመለክታል? አለመታየትን ነው። አንድ አውሮፕላን ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ ሲገባ ወይም ከደመና በላይ ሲሆን መሬት ላይ ያሉ ሰዎች የአውሮፕላኑን ሞተር ድምፅ ሊሰሙ ቢችሉም በዓይናቸው ግን ሊያዩት አይችሉም። ይሖዋ ለሙሴ “እነሆ በከባድ ደመና እመጣልሃለሁ” ብሎት ነበር። ሙሴ አምላክን አላየም፤ ደመናው ግን አምላክ ለዓይን በማይታይ ሁኔታ በቦታው መኖሩን ወይም መገኘቱን ያመለክት ነበር። (ዘጸ. 19:9፤ በተጨማሪም ዘሌዋውያን 16:2፤ ዘኁልቁ 11:25ን ተመልከት።) ክርስቶስ በሰማያት እየታየ ቢመጣም እንኳ ‘ዓይን ሁሉ ሊያው’ እንደማይችል ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል በአውስትራሊያ ቢታይ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ ወይም በአሜሪካ የሚኖሩ ሰዎች ሊያዩት አይችሉም፤ ይችላሉ እንዴ?
‘ዓይን ሁሉ የሚያየው ’ በምን መንገድ ነው? በማይታይ ሁኔታ የተገኘ መሆኑን በምድር ላይ ከሚታዩት ሁኔታዎች ይገነዘባሉ። በተጨማሪም ዮሐንስ 9:41 አካላዊ ስላልሆነ ማየት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስም [ፈሪሳውያንን] አላቸው:- ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን:- እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።” (ከሮሜ 1:20 ጋር አወዳድር።) ክርስቶስ ከተመለሰ በኋላ አንዳንድ ሰዎች እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። የመገኘቱን ምልክት ይገነዘባሉ። ሌሎች ደግሞ ማስረጃውን ለመቀበል አሻፈረን ይላሉ። ይሁን እንጂ ክርስቶስ የአምላክን የቅጣት ፍርድ በክፉዎች ላይ በሚያስፈጽምበት ጊዜ የኃይሉን መግለጫ ተመልክተው መዓቱ ከሰማይ እንጂ ከሰዎች የመጣ እንዳልሆነ ይገባቸዋል። ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው በመፈጸም ላይ የሚገኘው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃሉ። በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደወደቁ ስለሚገነዘቡ “ዋይ ዋይ ይላሉ።”
“የወጉት” እነማን ናቸው? ኢየሱስ በተገደለበት ጊዜ ሮማውያን ወታደሮች ቃል በቃል ወግተውት ነበር። ግን እነዚህ ሰዎች ከሞቱ ብዙ ጊዜ አልፏል። ስለዚህ ይህ የሚያመለክተው በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ የክርስቶስን እውነተኛ ተከታዮች ‘የሚወጉትን’ ወይም በተከታዮቹ ላይ ተመሳሳይ የሆነ በደል የሚያደርሱትን ሰዎች መሆን ይኖርበታል።—ማቴ. 25:40, 45
አንድ ሰው በዓይን ሳይታይ ‘መጣ’ ወይም ‘አለ’ ሊባል ይችላልን?
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ሲጽፍ “በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፣ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ ” ብሏል።—1 ቆሮ. 5:3
ይሖዋ የባቤልን ግንብ ይሠሩ የነበሩትን ሰዎች ቋንቋ ለመዘበራረቅ ‘እንደወረደ’ (ዘፍ. 11:7) በተጨማሪም እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ለማውጣት ‘እንደሚወርድ’ ተናግሯል። ሙሴ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማስገባት ሲመራቸው አምላክ “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ” ብሎ ለሙሴ ማረጋገጫ ሰጥቶት ነበር። (ዘጸ. 3:8፤ 33:14) አምላክን ግን አንድም ያየው ሰው የለም።—ዘጸ. 33:20፤ ዮሐ. 1:18
መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ መገኘት ጋር የሚያዛምዳቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ዳን. 7:13, 14:- “የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም [ይሖዋ አምላክ] ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።”
1 ተሰ. 4:15, 16 የ1980 ትርጉም:- “ከጌታ [“ከይሖዋ” አዓት ] በተቀበልነው ቃል መሠረት የምንነግራችሁ ይህ ነው፤ ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሕያዋን ሆነን የምንገኝ የሞቱትን አንቀድምም። የትእዛዝ ድምፅ፣ የመላእክት አለቃ ድምፅ፣ የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፤ ጌታ ራሱም ከሰማይ ይወርዳል፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ።” (ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር የሚነግሡት ከእርሱ ጋር በሰማይ ለመሆን ይነሣሉ። በመጀመሪያ የሚነሡት ቀደም ባሉት ዓመታት የሞቱት ሲሆኑ ከጌታ መመለስ በኋላ የሚሞቱት ደግሞ ይከተላሉ።)
ማቴ. 25:31–33:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።”
2 ተሰ. 1:7–9:- “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ [“ከኃያላኑ” አዓት ] መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፣ መከራን ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።”
ሉቃስ 23:42, 43 አዓት:- “እርሱም [ከኢየሱስ ጐን ተሰቅሎ የነበረውና ሐዘኔታ ያሳየው ክፉ አድራጊ] እንዲህ አለው:- ‘ኢየሱስ ሆይ፣ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ።’ እርሱም:- ‘እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ አለው።” (በኢየሱስ ግዛት ዘመን መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ የሚኖሩ ሙታን ከሞት ተነሥተው በምድር ላይ ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።)
በተጨማሪም በገጽ 234–238 ላይ “የመጨረሻ ቀኖች” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።